ለመጨረሻው ጊዜ መዘጋጀት
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 2ኛ ሩብ ዓመት 2018
 
ከመጋቢት 29 - ሚያዝያ 5

ሁለተኛ ትምህርት

April 7 – 13
 
ዳንኤል እና የመጨረሻው ጊዜ

ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡--ሉቃ. 16:10፣ ዳን. 1፣ 2፣ 3:1–6፣ ራእ. 13:11–15፣ ዳን. 3:13–18፣ ዮሐ. 3:7፣ ዳን. 4፣ 6፡፡

የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “ንጉሡም ዳንኤልን፣ ‘ይህን ምስጢር ልትገልጥ ችለሃልና፣ በእውነት አምላካችሁ የአማልክት አምላክና የነገሥታት ጌታ፣ ምስጢርንም ገላጭ ነው’ አለው፡፡” (ዳን. 2፡47)፡፡

ለጥንቷ እስራኤል ታላላቅ እቅዶች ነበሩት፡፡ “እናንተ ለእኔ የመንግሥት ካህናት የተቀደሰ ሕዝብ ትሆናላችሁ” (ዘፀ. 19፡6)፡፡ ይህ ቅዱስ ሕዝብ እና የካህናት ግዛት ያህዌ ብቸኛ አምላክ መሆኑን ለዓለም እንዲመሰክር ተጠርቶ ነበር (ኢሳ. 43፡10-12)፡፡ የሚያሳዝነው ሕዝቡ እግዚአብሔር ከሰጠው ቅዱስ ጥሪ ጋር ተጣጥሞ መራመድ ሳይችል በመቅረቱ ውሎ አድሮ በባቢሎን ምርኮ ግዞት ስር ለመውደቅ በቃ፡፡ እስራኤላውያን በአስከፊ ምርኮ ስር ቢወድቁም እግዚአብሔር ግን አሁንም አንዳንድ አይሁዳውያንን ምስክሮቹ አድርጎ መጠቀሙ ደስ የሚያሰኝ ክስተት ነበር፡፡ በሌላ አነጋገር ቀደም ብሎ በእስራኤልና በይሁዳ አማካይነት መሠራት ያልቻለው ነገር አሁን በዳንኤልና ሦስቱ አብረውት በምርኮ የወደቁ ጓደኞቹ ታማኝነት በተወሰነ ደረጃ መሠራት የሚችል ሆነ፡፡ በአንድ በኩል እነዚህ ሰዎች እስራኤል እንደ አገር ልትሆንና ልታደርግ ይገባት ለነበረው ነገር ምሳሌዎች ነበሩ፡፡ አዎን የእነዚህ ወገኖች ታሪክ ከመጨረሻዎቹ ቀናት እጅግ ርቀው ይገኙ በነበሩ ጊዜያቶችና ቦታዎች ተገለጡ፡፡ ዳንኤልና ጓደኞቹ በባቢሎን ቅጥር ይኖሩ ለነበሩ እግዚአብሔርን ለማያውቁ ጣኦት አምላኪዎች ምስክር እንደሆኑ ሁሉ፤ እኛ ዛሬ በመጨረሻዎቹ ጊዜያቶች የምንኖር ሕዝቦችም ምሳሌ መሆን የሚችል ጸባይና ባህሪ ከእነርሱ ማግኘት እንችላለን፡፡
 
መጋቢት 30
Apr 08
 
በትንሽ ነገር ታማኝ መሆን

“‘በትንሽ ነገር ታማኝ የሆነ በትልቁም ይታመናል፤ በትንሽ ነገር ያልታመነ በትልቁም አይታመንም ’ ” (ሉቃ. 16:10)፡፡ የሱስ የተናገራቸውን ቃላቶች ልብ ይበሉ፡፡ በጥቅሱ እንደምንመለከተው ለትንሹ ነገር መታመን ያን ያህል ከባድ ሳይሆን ቀላል ነው፡፡ ችግሩ ያለው በራሱ “በትንሽ ነገር” ላይ መታመን ያን ያህል አሳሳቢ መሆኑ ላይ አይደለም፡፡ አብዛኞቻችን በግል ተሞክሮአችንም ሆነ ከሌሎች ባገኘነው ምሳሌ (ወይም በሁለቱም) እንደምንገነዘበው ለመጀመሪያው ነገር የምናደርገው የድርድር አካሄድ ወደ ሌላኛው ይመራናል፡፡ ሌላኛው ደግሞ ወደ ሌላው እያለ በመጨረሻ “ ‘በትልቁም አይታመንም’ ” እስከ ሚለው መድረስ ይመጣል፡፡ ይህን ሃሳብ በአእምሮአችን እንደያዝን በባቢሎን ምርኮ ስር የነበሩትን የአራቱን አይሁዳውያን ተሞክሮ በዳን. ምዕ. 1 ላይ እንመልከት፡፡ ከትንቢተ ዳንኤል መጽሐፍ ምዕ. 1 ያንብቡ፡፡ የጥንቷ እስራኤል አቋም እንደ ዳንኤል፣ አናንያ፣ ሚሳኤልና አዛርያ ሆኖ ሊንጸባረቅ የተገባ የነበረው እንዴት ነው? ዘዳ. 4፡6-8፣ ዘካ. 8፡23፡፡

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ምንም እንኳ ጥቅሱ (ዳን. 1፡20) ዳንኤልና ጓደኞቹ ከሌሎቹ “ዐሥር እጅ በልጠው” ለተገኙበት “ጥበብና ማስተዋል ጉዳይ” ይመገቡ የነበረውን ምግብ በቀጥታ ባያስተሳስረውም፤ ሆኖም ተያያዥነት እንደነበረው ግን በግልጽ መመልከት ይቻላል፡፡ ምዕራፉ በተጨማሪ እግዚአብሔር ይህንን እውቀት እና ጥበብ እንደ ሰጣቸው ይናገራል፡፡ ዳንኤልና ጓደኞቹ የባቢሎንን ንጹህ ያልሆኑ ምግቦች ለመመገብ በመቃወማቸውና በታማኝነታቸው በመጽናታቸው ጌታ ከእነርሱ ጋር መሥራት ችሎ ነበር፡፡ ወጣቶቹ ታዛዦች ሆኑ፤ እግዚአብሔርም ይህን መታዘዛቸውን ባረከ፡፡ እነዚያ ጥንታዊ እስራኤላውያን አራቱ ወጣቶች እንዳደረጉት ታማኝና ለአምላካዊው አስተምህሮ ጥብቅ ቢሆኑ ኖሮ እግዚአብሔር ለእነርሱ ያደረገውን ለሕዝቡም አያደርገውም ነበር? በእርግጥ ያደርገው ነበር! እኛም በመጨረሻው ዘመን የምንኖር፤ ታማኝ እስከሆንን ድረስ ለእነዚያ አራት ወጣቶች ያደረገውን ለእኛስ ቢሆን አያደርገውም? በጣም ብዙ ብርሃንና እውነት የተቀበልን ሕዝቦች እንደመሆናችን እንደ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል፡ ለተሰጠን ነገር ታማኝና ታዛዥ ኖረናል? እያንዳንዳችን በግል ለእግዚአብሔር ብርቱ ምስክር ለመሆን የሚያስችለንን አቋም መያዝ የምንችለው እንዴት ነው?
 
ሚያዝያ 1
Apr 09
 
የዳንኤል ትህትና

በዳን. ምዕ 2 የሚገኘው መልእክት በመላው ዓለም እንዲህ ተብሎ የማይገለጹ ሕዝቦች በመጽሐፍ ቅዱሳዊው አምላክ እንዲያምኑ እረድቶአል፡፡ ምዕራፉ ስለ እግዚአብሔር ሕልዎት ብቻ ሳይሆን እርሱ የወደፊቱን አስቀድሞ የሚያውቅ አምላክ መሆኑን ጭምር እጅግ ምክንያታዊ በሆነ ማስረጃ ያቀርብልናል፡፡ ዳን. ምዕ. 2 ያንብቡ፡፡ ምዕራፉ እግዚአብሔር በተጨባጭ የነበረ፣ ያለና የሚኖር አምላክ መሆኑን በአሳማኝ ማስረጃ የሚያቀርበው እንዴት ነው? በዳን. 2፡40-43 በቀረበው መሰረት የዛሬውን አውሮፓ ይመልከቱ፡፡ ከሁለት ሺ ስድስት መቶ ዓመታት በፊት ይኖር የነበረ ይህ ሰው ከመለኮታዊ መገለጥ በስተቀር የነበረውን ሁናቴ እንዴት በትከክል መግለጽ ቻለ?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ዳንኤል ለተገለጠለት ነገር ተገቢውን ክብርና ዝና በግልጽና ያለ አንዳች ሐፍረት ለእግዚአብሔር ሰጠ፡፡ የንጉሡን ሕልም በማወቁ ብቻ ሳይሆን ፍቺውንም በመስጠቱ ይህን ጥበብ የግል ችሎታው በማስመሰል ራሱን በቀላሉ መኮፈስ ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን ዳንኤል ከዚያ በተሻለ የሚያስተውል ሰው ነበር፡፡ እርሱና ሌሎች የጸለዩት ጸሎት (ዳን. 2፡17-23) በእግዚአብሔር ላይ የነበራቸውን መተማመን የሚያሳይ ነበር፡፡ ያለበለዚያማ ከተቀሩት ኮከብ ቆጣሪዎች ጋር በተገደሉ ነበር፡፡ ንጉሡ የጠየቀውን ምስጢር ከጠንቋዮቹ፣ ከአስማተኞቹም ሆኑ ከኮከብ ቆጣሪዎቹ መሃል አንዳቸውም ሊነግሩት እንደማይችሉ ዳንኤል ለንጉሡ ነግሮት ነበር፡፡ በተቃራኒው ብቸኛውና እውነተኛው ሰማያዊ አምላክ እግዚአብሔር ምስጢርን መግለጥ እንደሚችል ገለጸለት፡፡ ዳንኤል ከነበረው ትህትናና በእግዚአብሔር ላይ መታመን የተነሳ ብርቱ ምስክር ለመሆን ቻለ፡፡ በዚያ ዘመን የነበረው ዳንኤል ያን ትህትና ካሳየ እኛ በዚህ ዘመን የምንገኝ ወገኖች ምን ያህል የበለጠ ማሳየት ይኖርብን ይሆን? ደግሞስ እኛ ለዳንኤል ያልተገለጠው የደኅንነት እቅድ ተገልጦልን የለ? እንደው ምንም ነገር ትሑት ሊያደርገን ባይችል እንኳ የሱስ በመስቀል ላይ ያደረገውን ማወቃችን ብቻውን በቂ ምክንያት ሊሆነን ይገባል፡፡ መስቀሉ ስለ ትህትና ምን ሊያስተምረን ይገባል? ኃጢአተኞች ስለመሆናችን ብቻ ሳይሆን ለደኅንነታችን በእግዚአብሔር ላይ መተማመን እንደሚገባን አስመልክቶ ምን ይነግረናል? እርስዎ ያለ መስቀሉ የት ሊገኙ ይችሉ እንደ ነበር አሰብ ያድርጉ፡፡ ስለዚህ ከመስቀሉ ውጪ ሌላ በምን ሊመኩ ይችላሉ? ገላ. 6፡14፡፡
 
ሚያዝያ 2
Apr 10
 
የወርቁ ምስል

የመጽሐፍ ቅዱስ አጥኚዎች በዳን. ምዕ. 3 የምናገኘውን ሦስቱ ዕብራውያን በዱራ ሜዳ የተጋፈጡትን ነገር በምድር ታሪክ መዝጊያ ወቅት የእግዚአብሔር ሕዝቦች ከሚገጥማቸውና በራእ. ምዕ. 13 ከቀረበው የግድያ ትዕይንት ጋር ያዛምዱታል፡፡ እነዚህን ሁለት ጥቅሶች ያስተያዩ፡--ዳን. 3፡1-6፣ ራእ. 13፡11-15፡፡ በሁለቱ ጥቅሶች (በዳንኤልና በራእይ) መሃል የምናገኛቸው ተዛምዶዎች ምንድን ናቸው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

አምልኮ የሁለቱም ርዕሰ ጉዳዮች ማዕከላዊ ክፍል ሲሆን የግዳጅ አምልኮ በሁለቱም መልእክቶች ቀርቦአል፡፡ ይህ ደግሞ ማናለብኝ የፖለቲካዊ ኃይሎች ለጌታ ብቻ የተመደበውን አምልኮ ለራሳቸው መጠየቃቸው ነው፡፡ ይህን ጥቅስ ያንብቡ፡ ዳን. 3፡13-18፡፡ ታሪኩ በመጨረሻው ጊዜ ስለ ምንጋፈጠው ነገር ብቻ ሳይሆን ሊመጣ ያለውን ነገር እንዴት ማስተዋል እንደሚኖርብን ሊረዳን የሚችለው በምን መልኩ ነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

የወቅቱ ብቸኛ ልዕለ ኃያል አገር ንጉሥ የነበረው ናቡከደነፆር “ታዲያ ከእጄ ሊያድናችሁ የሚችል አምላክ ማን ነው?” ሲል በእነርሱና በሚያመልኩት እግዚአብሔር ላይ ተሳለቀ፡፡ ሆኖም ያ አምላክ ማን እንደሆነ ለራሱ ማወቅ የነበረበት ናቡከደነፆር ብዙም ሳይቆይ እንዲህ ሲል ምስክርነቱን ሰጠ፡ “መልአኩን ልኮ አገልጋዮቹን ያዳነ፣ የሲድራቅ፣ የሚሳቅና የአብደናጎ አምላክ ይባረክ፤ በእርሱ በመታመን የንጉሡን ትእዛዝ ጥሰው፣ ከአምላካቸው በቀር ሌላ አምላክ ለማገልገልም ሆነ ለእርሱ ለመስገድ ፈቃደኛ ባለመሆን ሕይወታቸውን አሳልፈው ሰጥተዋልና፡፡” (ዳን. 3፡28)፡፡ ንጉሡ እንደዚያ ዓይነቱን ታምራት ከተመለከተ በኋላ እነዚህ ሰዎች በሚያመልኩት አምላክ ዙሪያ አንድ የተለየ ነገር መኖሩን ለማመን አለመቸገሩ ብዙም አያጠያይቅም፡፡ ምናልባት እነዚህ ወጣቶች ከሚነደው እሳት ባይድኑም እንኳ በእግዚአብሔር ላይ የነበራቸው እምነት ጽኑ ነበር (ዳን. 3፡18)፡፡ እሳቱ ውስጥ በቁማቸው ገብተው ቢቃጠሉ እንኳ የንጉሡን ትእዛዝ ሳይሆን ትክክለኛውን ነገር ብቻ ማድረግ የነበረባቸው ለምንድን ነው? ይህ ታሪክ ምንም ይምጣ ምን ወጣቶቹ ባመኑበት ጸንተው ለመቆም ስለነበራቸው ቁርጠኝነት ብርቱ ምስክርነት ይሰጠናል፡፡ በመጨረሻዎቹ ዘመናት ከአምልኮ ጋር ተያያዥነት ያለው ጉዳይ ሲከሰት እንደ እነርሱ በታማኝነት መቆም ለመቻላችን ምን ያህል እርግጠኞች መሆን እንችላለን? ዛሬ “በትንሹ ነገር” ታማኝ ሳንሆን እንደ መጨረሻዎቹ ዘመናት ያሉ ታላላቅ ቀውሶች ሲከሰቱ ታማኝ ሆነን እንገኛለን ብለን እንዴት ልናስብ እንችላለን?
 
ሚያዝያ 3
Apr 11
 
ከአሕዛብነት መለወጥ

ዳን. ምዕ. 3 የሚያበቃው ናቡከደነፆር የእውነተኛውን አምላክ ህልዎት እና ኃይል መቀበል ከነገረን በኋላ ነው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔርንና የእርሱን ኃይል ማወቅ ዳግም ከመወለድ ተሞክሮ ጋር ተመሳሳይ አለመሆኑን አስመልክቶ የሱስ የተናገረው በጣም ወሳኝ ነጥብ ነው (ዮሐ. 3፡7)፡፡ በእርግጥ በዳን. 4፡30 የቀረበው ሰው ምንም ይሁን ምን እውነተኛውን አምላክ የተቀበለ ነፍስ ነው፡፡ ጥቅሱን ያንብቡ፡ ዳን. 4፡30፡፡ የዚህ ሰው ችግር ምን ነበር? በተጨማሪ የሚከተሉትን ጥቅሶች ይመልከቱ፡ ዮሐ. 15:5፣ ሐዋ. 17:28፣ ዳን. 5:23፡፡

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

አራተኛው ምዕራፍ በተገባደደበት ወቅት ማንኛውም እውነተኛ ኃይል የእግዚአብሔር መሆኑንና ያለዚህ አምላክ እርሱ ምንም መሆኑን በአስቸጋሪ መንገድም ቢሆን ናቡከደነፆር ትምህርት አግኝቶ ነበር፡፡ “በአንድ ወቅት በኩራት ታብዮ የነበረው ንጉሥ ትሑት የእግዚአብሔር ልጅ ሆነ፡፡ አምባገነኑና የሌሎችን ሀሳብ ይንቅ የነበረው ገዢ ጥበበኛና ርኅሩኅ ንጉሥ ወጣው፡፡ የሰማይ አምላክን አርክሶና ተሳድቦ የነበረው ይህ ሰው አሁን ግን የልዑል አምላክን ኃያልነት ተቀበለ፡፡ የእግዚአብሔር ሞገስና የተከታዮቹ ደስታ ይበልጥ እንዲንሰራፋ የማድረግ ጽኑ ምኞትም አደረበት፡፡ ናቡከደነፃር ከነገሥታት ንጉሥና ከጌቶች ጌታ ባገኘው ግሳጼ በመጨረሻ ገዢዎች ሁሉ ሊማሩት የሚገባውን ትምህርት ያገኘ ሲሆን ይኸውም--እውነተኛ ታላቅነት የእውነተኛ መልካምነት አካል መሆኑን ነበር፡፡ የሕያው እግዚአብሔርን ሕልውና በመቀበል እንዲህ አለ፡ ‘እኔ ናቡከደነፆር እርሱን አወድሰዋለሁ፤ ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ፤ አከብረዋለሁም፤ እርሱም በትዕቢት የሚመላለሱትን ማዋረድ ይችላል፡፡’ ”— Ellen G. White, Prophets and Kings, p. 521. ጥቅሱን ያንብቡ፡ ዳን. 4፡35፡፡ ናቡከደነፆር እግዚአብሔርን አስመልክቶ ምን ዓይነት እውነቶችን ገለጠ

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

አሕዛብ የነበረው ሰው ለዕብራውያኑ አምላክ ሥልጣን፣ ግዛት እና ኃይል እውቅና ከሰጠ በኋላ ዳንኤል ምዕ. 4 ይጠናቀቃል፡፡ ይህ ሁኔታ ኋላ ላይ በአይሁዳውያን ምስክርነትና በእግዚአብሔር ኃይል ቤተ ክርስቲያን ስትዋቀር አሕዛብ ስለ ጌታ እውነትን ተምረው ያን የተማሩትን እውነት መልሰው ለዓለም መስበክ ለጀመሩበት ትዕይንት ፈር ቀዳጅ ነበር፡፡ ጥቅሱን ያንብቡ፡ ዮሐ. 3፡7፡፡ ምንም እንኳ የመጨረሻውን ጊዜ ክስተቶች--ከሞት ዐዋጅ፣ ከአምልኮ እና ከስደት አኳያ ብናስበውም፤ ነገር ግን ከሁሉም በላይና ባሻገር ሕዝቡን ለመጨረሻው ጊዜ ስለሚያዘጋጀው ነገር የሱስ ምን ይላል?
 
ሚያዝያ 4
Apr 12
 
የዳንኤል ታማኝነት

ዳን. ምዕ. 6 ካነበቡ በኋላ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ይመልሱ፡ 1. ዳን. 6፡4-5 ስለ ዳንኤል ጸባይ ምን ይገልጽልናል? እንዴት ልንታይ እንደሚገባ አስመልክቶ ከእነዚህ ጥቅሶች ምን ዓይነት ትምህርቶች መውሰድ እንችላለን

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

2. በዚህ ምዕራፍ በራእይ መጽሐፍ ከቀረበው የመጨረሻው ዘመን ክስተቶች ጋር ተወራራሽነት ያላቸው ምን ዓይነት ክስተቶችን እናገኛለን? ራእ. 13:4፣ 8፣ 11–17፡፡

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

3. እስቲ ራስዎን ዳንኤል ይገኝበት በነበረው ሁናቴ ውስጥ ያኑሩ፡፡ ላለመጸለይ ምን ዓይነት ምክንያት ወይም የመከራከሪያ ሃሳብ ማቅረብ ይችል ነበር? ማለትም ያደረገውን ነገር ላለማድረግ እንዴት አድርጎ የማስመሰያ ነጥብ አንስቶ ራሱን ከአናብስት ጉድጓድ መታደግ ይችል ነበር?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

4. ዳንኤል ያን ያህል መጸለይ ባያስፈልገውም እርሱ ግን እንደ ሁል ጊዜው መጸለዩን የቀጠለው ለምን ይመስሎታል?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

5. ዳንኤል ወደ አንበሶች ጉድጓድ ከመጣሉ አስቀድሞም ቢሆን ስለ እርሱ አምላክ አንዳች የሚያውቀው ነገር እንደ ነበር በሚገልጥ መልኩ ንጉሥ ዳርዮስ ምን አለ (ዳን. 6፡16)፡፡ ዳንኤል ያመልከውና ያገለግለው ስለነበረው አምላክ አስመልክቶ የራሱን ምስክርነት ፍንትው አድርገው የሚያሳዩ ምን ዓይነት ቃላቶች ተጠቀመ?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ሚያዝያ 5
Apr 13
 
ተጨማሪ ሃሳብ፡

“ወደ ዓለም ታሪክ መቋጫ እየተቃረብን ስንመጣ በትንቢተ ዳንኤል የቀረቡት ትንቢቶች እየኖርን ካለንበት ዘመን ጋር ካላቸው መስተጋብር አኳያ የተለየ ትኩረት ይጠይቃሉ፡፡ ከአዲስ ኪዳን መጻሕፍት መሃል የመጨረሻው መጽሐፍ ከእነዚህ ትንቢቶች ጋር ትስስር ሊፈጥር የተገባ ነው፡፡ ሰይጣን የዳንኤል እና የዮሐንስ ራእይ ትንቢታዊ መጻሕፍት ሊስተዋሉ የማይችሉ ናቸው በማለት ብዙዎችን አስቶአል፡፡ ነገር ግን እነዚህን መጻሕፍት የሚያጠኑ ልዩ በረከት እንደሚያገኙ ግልጽ የሆነ አምላካዊ ቃል ተሰጥቶአል፡፡ “ጠቢባን ግን ያስተውላሉ” (ዳን. 12፡10) በሚል በትንቢተ ዳንኤል የተነገሩት ቃላት ታትሞ የነበረው የመጽሐፉ ቃል በዚህ የመጨረሻ ዘመን መከፈቱን ያመለክታሉ፡፡ በዘመናት ለእግዚአብሔር ሕዝቦች ምሪት ይሆን ዘንድ ክርስቶስ እንዲህ ሲል ለአገልጋዩ ዮሐንስ ገልጦለታል ‘ዘመኑ ቀርቦአል፤ እንግዲህ ይህን የትንቢት ቃል የሚያነብ ብፁዕ ነው፤ የሚሰሙትና የተጻፈውንም የሚጠብቁ ብፁአን ናቸው’ ራእ. 1:3”—Ellen G. White, Prophets and Kings, p. 547, 548. ምንም እንኳ የዳንኤልን መጽሐፍ ከመንግሥታት መነሳትና መውደቅ፣ ከፍርድ (ዳን. 7፡22፣ 26፣ 8፡14) እና በታላቁ የመከራ ጊዜ ገቢራዊ ከሚሆነው የእግዚአብሔር ሕዝቦች መዳን አኳያ አብልጠን ብንመለከተውም (ዳን. 12፡1)፤ በዚህ ሣምንት ጥናታችን--ሊመጣ ላለው ፈተና እና ስደት በግል መዘጋጀት ምን ማለት እንደሆነ መጽሐፉ ሊሰጠን የሚችለውን ምሳሌ ተመልክተናል፡፡ ታሪኮቹ በዚህ መልኩ ለመጨረሻው ዘመን ገጣሚነት ያላቸውን አንገብጋቢ መልእክቶች ይሰጡናል፡፡ “የአውሬው ምልክት”፣ አስጨናቂው “የመከራ ጊዜ” እና ስደትን አስመልክቶ አንዳንድ ነጥቦችን መመልከቱና ማወቁ ጠቃሚ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ሊኖረን የሚገባውንና በእጅጉ አስፈላጊያችን የሆነውን የግንኙነት ተሞክሮ ከወዲሁ መመስረት ካልቻልን ይህ ሁሉ ዕውቀት እኛን ከመኮነን ውጪ ሌላ የሚፈይደው ነገር አይኖርም፡፡ ከማንኛውም ነገር በላይ ናቡከደነፆርን ጨምሮ ዳንኤልና ሌሎቹ የነበራቸው ዓይነት የ“ዳግመኛ መወለድ” ተሞክሮ ሊኖረን ይገባል፡፡ የመወያያ ጥያቄዎች: 1.በዳን. 9፡3-19 የቀረበውን የዳንኤል ጸሎት ያንብቡ፡፡ እግዚአብሔር ከርኅራኄው የተነሳ የሚወደንና የሚዋጀን አምላክ እንደመሆኑ ከማንኛውም በመልካም ሥራም ሆነ በበጎነት ጽድቅ አገኛለሁ ከሚል እሳቤ በተቃራኒ ዳንኤል አምላካዊውን ጸጋ ማስተዋሉን ይህ ጸሎቱ እንዴት ያሳየናል? ይህ እውነት ለማስተዋል ሳይሆን ለመለማመድ በእጅጉ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? 2.በሰንበት ትምህርት ጥናትና ውይይታችሁ የፖለቲካ ባለሥልጣናት ሦስቱ ዕብራውያን (ዳን. 3) እና ዳንኤል (ዳን. 6) ለኃይማኖታዊ እሴቶቻቸው በጽናት እንዳይቆሙ በፈጠሩባቸው ተግዳሮቶች ዙሪያ ተወያዩ፡፡ ከላይ በቀረቡት በሁለቱ ሃሳቦች መሃል ምን ዓይነት መመሳሰል ያገኛሉ? ልዩነትስ? ታማኝነታችን እንዴት ብርቱ ምስክሮች ሊያደርገን እንደሚችል አስመልክቶ ከእነዚህ ሁለት ነጥቦች ምን መማር እንችላለን?