ለመጨረሻው ጊዜ መዘጋጀት
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 2ኛ ሩብ ዓመት 2018

ከሰኔ 16 - 22

አስራ ሶስተኛ ትምህርት

June 23 – 29


የጌታችን የየሱስ ዳግም ምጽአት



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ኢሳ. 13:6፣ 9፣ ማቴ. 24:30-31፣ ዳን. 2:34-35፣ 2ጢሞቴ. 4:6–8፣ 2ተሰ. 1:7–10፡፡


የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡- “መብረቅ ከምስራቅ ወጥቶ ምዕራብ ድረስ እንደሚያበራ፣ የሰው ልጅ አመጣጥም እንደዚሁ ይሆናል” (ማቴ. 24፡27)፡፡

ባለ ቅኔው ቲ.ኤስ. ኤሊዮት “መጀመሪያዬ መጨረሻዬ ነው” የሚል መስመር በአንድ ግጥማቸው ውስጥ፡ ይገኛል፡፡ ይህ ሀረግ እጥር ምጥን ቢልም ብርቱ እውነት ይዞአል፡፡ ጅማሮ ላይ ፍጻሜ አለ፡፡ ሁለት መሰረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮዎችን በያዘው ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት በሚለው መጠሪያ ስማችን ውስጥ ይህ ድምፅ ያስተጋባል፡፡ “ሰባተኛ ቀን” የሚሉት ቃላት የአስርቱ ትእዛዛት አካል የሆኑትን ስድስት ቀናት የፈጀውን የፍጥረት ሥራ ሲወክሉ፤ “አድቬንቲስት” ደግሞ የዘላለማዊው ህይወት ተስፋ ፍጻሜ ወደ ሆነው የየሱስ ዳግም ምጽአት ያመላክታል፡፡
ምድርና ሙላቷ የተፈጠሩበት ጊዜ (ጅማሮአችን) የቱንም ያህል ከየሱስ ዳግም ምጽአት የራቀ ሊሆን ቢችልም (የዚህ ኃጢአተኛ ህልውና መጨረሻ) ክስተቶቹ ግን የተሳሰሩ ናቸው፡፡ እኛን የፈጠረው ያው አምላክ (ዮሐ. 1፡1-3) ራሱ ዳግም ተመልሶ ሲመጣና “ድንገት በቅጽበተ ዐይን፤ መለከት ሲነፋ” (1ቆሮ. 15፡52) የመጨረሻው ደኅንነታችን እውን ይሆናል፡፡ በእርግጥም--በጅማሮአችን ውስጥ ፍጻሜአችን አለ፡፡ በዚህ ሣምንት ጥናታችን የሁሉም ክስተቶች መጨረሻ በሆነው የፍጻሜ ክስተት ይኸውም በጌታችን የሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት ዙሪያ እንነጋገራለን፡፡

ሰኔ 17
Jun 24

የጌታ ቀን


ብዙውን ጊዜ የየሱስን ዳግም ምጽአት የአዲስ ኪዳን አስተምህሮ ብቻ አድርጎ የማሰብ አዝማሚያ ቢታይብንም ነገር ግን ይህ ትክክል አይደለም፡፡ በእርግጥ ከየሱስ የመጀመሪያ ምጽአት፣ ከሞቱ፣ ከትንሣኤው እና ዕርገቱ በኋላ--በዳግም ምጽአቱ ዙሪያ ያለው እውነት በግልጽና በሙላት ተሰጥቶናል፡፡ ነገር ግን በአዲስ ኪዳን አብልጦ የተገለጸውን ያህል ብሉይ ኪዳንም ይህ ወሳኝ እውነት ገቢራዊ ከመሆኑ ረጅም ዓመታት አስቀድሞ ፍንጭ ይሰጠናል፤ ጥላውንም ያሳየናል፡፡ የየሱስን ዳግም ምጽአት አስመልክቶ የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች የገለጡት አዲስ እውነት አልነበረም፡፡ ይልቁንም አስቀድሞ በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጠውን እውነት አበለጸጉት፡፡ ሆኖም በተሰቀለውና ከሞት በተነሳው አዳኝ ብርሃን እነሆ ዛሬ የዳግም ምጽአቱ ተስፋ ይበልጥ መስተዋልና ከፍ ያለ አክብሮት ማግኘት ችሎአል፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኢሳ. 13:6-9፣ ዘካ. 14:9፣ ዳን. 12:1፡፡ ስለ የሱስ ዳግም ምጽአት ምን ያስተምሩናል?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

“የጌታ ቀን” ለጠፉት የውድመት፣ የሰቆቃና የሽብር ጊዜ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ሆኖም ስማቸው በመጽሐፉ ላይ ለተጻፈ (ፊልጵ. 4፡3፣ ራእ. 3፡5፣ 13፡8) የእግዚአብሔር ሕዝቦች ግን ታላቅ የመዳን ቀን ይሆንላቸዋል፡፡ ይህ በብሉይ ኪዳን “የጌታ ቀን” በሚል የቀረበ ርዕሰ ጉዳይ ለጠፉት የፍርድ ጊዜ-ለእግዚአብሔር ታማኞች ግን አምላካዊውን ከለላ የሚያገኙበትና የተዘጋጀላቸውን ሽልማት የሚቀበሉበት ዕለት ነው፡፡ ለአብነት ያህል ምንም እንኳ አንዳንዶች “የእግዚአብሔርን የቁጣ ቀን” መጋፈጣቸው አይቀሬ ቢሆንም “ጽድቅንና ትሕትናን” የሚፈልጉ ግን “ከእግዚአብሔር የቁጣ ቀን የሚሰወሩ ይሆናሉ” (ሶፎን. 2፡1-3)፡፡ ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማቴ. 24፡30-31፡፡ በየሱስ ዳግም ምጽአት ወቅት በጠፉትና በዳኑት መካከል የሚኖረውን ሁለት ተቃራኒ ሁኔታ የሚያወዳድሩበት መንገድ ምን ይመስላል? የመጨረሻዎቹ ክስተቶች እየተገለጡ በሄዱ ቁጥር የቆምንበት ጎራ ይበልጥ ግልጽ እየሆነ ይመጣል፡፡ በትክክለኛው በኩል ለመቆማችን እርግጠኞች መሆን እንችል ዘንድ አሁን ምርጫችን ምን መሆን ይኖርበታል?

ሰኔ 18
Jun 25

ዳንኤል እና የየሱስ ዳግም ምጽአት


ምንም እንኳ በመሲህነት ይጠበቅ የነበረው የሱስ በወቅቱ የነበረውን የሮማውያን ቅኝ ግዛት አፈራርሶ እስራኤልን እጅግ ኃያል አገር አድርጎ ይመሰርታል ብለው አይሁዳውያን ቢጠብቁም፤ ነገር ግን የእርሱ የመጀመሪያም ሆነ ሁለተኛው ምጽአት ያረጀውን ኃጢአተኛና የወደቀ ዓለም ለመጠገን አልነበረም፣ አይደለምም! እግዚአብሔር ለታማኝ ሕዝቦቹ ያዘጋጀው ከዚህ እጅግ የላቀና የከበረ ነገር አለው፡፡
ከብሉይ ኪዳን መልእክቶች ሁሉ አዲሷ ምድር ከአሮጌዋ ላይ አድጋ የምትወጣ ሳይሆን አዲስ እና አፈጣጠሯ ላይ መሰረታዊ ለውጥ ያላት የመሆኗን እውነታ የዳን. 2ን ያህል በግልጽ የሚያሳየን የለም፡፡ ዳን. 2 ወደ ዛሬዎቹ ዘመናዊ የአውሮፓ አገራት የሚሰነጣጠቁትን አራቱን የዓለም ታላላቅ መንግሥታት--ባቢሎን፣ ሜዶንና ፋርስ፣ ግሪክ እና ሮም አነሳስና አወዳደቅ ያሳየናል፡፡ ናቡከደነፆር በሕልሙ የተመለከተው ምስል (የአራቱ የዓለም ልዕለ ኃያላን አነሳስ ተምሳሌት) የመጨረሻ ክፍል ወደ አስደናቂ ልዩነት ያመራና በመጨረሻም በየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት ፍጻሜ ያገኛል፡፡ ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዳን. 2፡34-35፣ 44-45፡፡ ስለዚህ ዓለም ዕጣ ፈንታና ስለ አዲሱ ተፈጥሮ ምን ያስተምሩናል?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ጥቅሶቹ የየሱስ ዳግም ምጽአት ዕውን በሚሆንበት ወቅት ስለሚሆነው ነገር የሚያቀርቡት ሀሳብ በመጠኑም ቢሆን አሻሚነት አለው፡፡ የሱስ በሉቃ. 20፡ 1718 መልእክቱ ራሱን ሁሉንም በሚያደቅቀው የማእዘን ራስ ድንጋይ በመመሰል ሲናገር ይደመጣል፡፡ በዳን. 2፡35 እንደምናነበው የወርቁ ምስል፣ ብሩ፣ ሸክላው፣ ብረቱ እና ነሐሱ “ተሰባበሩ፤ በበጋ ወራት በዐውድማ ላይ እንደሚገኝ እብቅም ሆኑ፤ ነፋስም አንዳች ሳያስቀር ጠራረጋቸው” ከየሱስ ዳግም ምጽአት በኋላ በዚህ ምድር የሚቀር አንዳችም ነገር አይኖርም፡፡
በዚህ ምድር የነበረውን አሻራ አንድም ሳይቀር “የመታው ድንጋይ ግን ታላቅ ተራራ ሆነ፤ ምድርንም ሞላ፡፡” ይህ የዳግም ምጽአቱ ውጤት የሆነ መንግሥት “ፈጽሞ የማይፈርስና” “ለዘላለም ጸንቶ” የሚኖር ይሆናል (ዳን. 2፡44)፡፡ በዚህ ምድር የኖረ ማንኛውም ሰብዓዊ ፍጡር ከቀረቡለት ሁለት አማራጮች በአንዱ ላይ ብቻ ይወሰናል፡፡ ከየሱስ ጋር ለዘላለም መኖር ወይም ከአረጀውና ካፈጀው ምድር ጋር እንደ ዐውድማ እብቅ ተጠራርጎ መጥፋት፡፡ በዚህም ሆነ በዚያ--ዘላማዊነት እየጠበቀን ይገኛል፡፡

ሰኔ 19
Jun 26

ዘላቂውን ተስፋ ማድረግ


ጥቅሱን ያንብቡ፡ ቲቶ 2፡13፡፡ እንዴት ያለ ታላቅ ተስፋ አለን? ለምን?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

የአንድ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ስለ ዩኒቨርስ አፈጣጠር የሚያምኑበትን መላ ምት ሲገልጹ ከ13 ቢሊዮን ዓመታት በፊት “አንድ ከምንም ነገር በተከሰተ ጥቃቅንና ጥቅጥቅ ግዑዝ አካል ላይ ከፍተኛ ፍንዳታ ደረሰ፡፡” ካሉ በኋላ “ታዲያ ከዚያ ፍንዳታ ውስጥ ይህ የእኛ ዩኒቨርስ ብቅ አለ፡፡” በማለት ንግግራቸውን ደመደሙ፡፡ ለመሆኑ ይህ “ጥቃቅን ጥቅጥቅ ግዑዝ አካል” እንዴት ከምንም ነገር ላይ ተነስቶ መከሰት ቻለ--በሚል ሊነሳ ለሚችለው ጥያቄ ያሉት ነገር ግን አልነበረም፡፡ ብቻ በዚህ መንገድ መሆን ቻለ ብለው ንድፈ ሀሳቡን አምነው ተቀብለውታል፡፡
በዚህ ሣምንት ጥናታችን በመግቢያ ላይ እንደ ተመለከትነው፡ በጅማሮአችን ውስጥ ፍጻሜአችን አለ፡፡ ሆኖም እንደ ፕሮፌሰሩ መላ ምት ከሆነ መጨረሻችን ተስፋ ቢስ ነው፡፡ ከዚህ “ጥቃቅን ጥቅጥቅ ግዑዝ አካል” የተፈጠረ አጽናፈ ሰማይ በስተመጨረሻ ሰብዓዊውን ፍጡር ጨምሮ እርሱና በውስጡ ያለው ሁሉ እንዲጠፋ ተፈርዶበታል፡፡
ሆኖም ከዚህ በተቃራኒ የሚገኘውን የጅማሮአችንን ጽንሰ ሃሳብ የሚያስነብበው መጽሐፍ ቅዱስ--አመክኖአዊ ብቻ ሳይሆን ተስፋ ሰጪም ነው፡፡ የጅማሮ ሁሉ ባለቤት ለሆነው እግዚአብሔር አምላክ ምስጋና ይግባውና የወደፊቱ ተስፋችን መልካም ነው፡፡ ስለ ወደፊት ተስፋ እንድናደርግ የሚረዱን አያሌ ምክንያቶች ያሉን ሲሆን--ይህ ተስፋችን በየሱስ ዳግም ምጽአት ላይ ያርፋል፡፡ ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 2ጢሞቴ. 4፡6-8፡፡ ጳውሎስ ስለ ምን እየተናገረ ነው? ተስፋውን እያኖረ ያለውስ በማን ላይ ነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ምንም እንኳ ጳውሎስ የሚሰዋበት ጊዜ ቢቃረብም፤ ነገር ግን ህይወቱ መዳኑን ያረጋገጠና “በዚያ ቀን” ብሎ ለጠራው የክርስቶስ ዳግም ምጽአት ተስፋ የሰነቀ ነበር (2ጢሞቴ. 4፡8)፡፡ ተስፋው በየሱስ ዳግም ምጽአት ላይ ማረፉን የሚያውቀው ጳውሎስ፤ የሚጠብቀው “የጽድቅ አክሊል” የራሱ ጽድቅ ሳይሆን (1ጢሞቴ. 1፡15) የየሱስ ጽድቅ መሆኑን ይረዳል፡፡ በቅርቡ ሊደርስበት ያለው አስከፊ ሁናቴ ያላስጨነቀው ጳውሎስ (እስራት እና መሠዋት) የመጨረሻ ተስፋው ብሩህ መሆኑን ያውቅ ነበር፡፡ ለዚህ መንስዔው እንደ ጥላ የሚያልፈውን ሳይሆን ግዙፉን ትዕይነት መመልከት መቻሉ ነበር፡፡ እርስዎ አሁን ሊገኙ በሚችሉበት ሁናቴ ተስፋ ሳይቆርጡ፤ እንደ ጳውሎስ ተስፋ መሰነቅ የሚችሉት እንዴት ነው? ወደ ትልቁ ትዕይንት መመልከትና ትዕይንቱ የሚሰጠውን ተስፋ የግላችን ማድረግ መማር የምንችለው እንዴት ነው?

ሰኔ 20
Jun 27

በሰማይ ደመናዎች


ግም ምጽአቱ የቱንም ያህል የሁሉም ነገር ማዕከላዊና ወሳኝ ቢሆንም ሁሉም ክርስቲያኖች ግላዊውን የየሱስ ዳግም ምጽአት ቃል በቃል እንደ ተነገረው ክስተቱን እንደማይመለከቱ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ ለምሳሌ አንዳንዶች-የየሱስ ዳግም ምጽአት እውን የሚሆነው እርሱ ራሱ ወደ ምድር ሲመለስ ሳይሆን መንፈሱ በቤተ ክርስቲያኑ ሲገለጥ ነው በማለት ይሞግታሉ፡፡ በሌላ አነጋገር የክርስቶስ ዳግም ምጽአት ፍጻሜ የሚያገኘው የክርስትና ግብረገባዊ መርኅዎች በሕዝቡ ሲገለጡ ነው--እንደ ማለት፡፡ ይህ አስተምህሮ ሐሰተኛ ሆኖ መቅረቱ በጀ እንጂ--እውነት ቢሆን ኖሮ ምን ዓይነት ዘላቂ ተስፋ ሊኖረን ይችል ነበር? ከዚህ በታች የቀረቡትን ስለ ዳግም ምጽአቱ የሚናገሩ የአዲስ ኪዳን ጥቅሶች ያንብቡ፡፡ ስለ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት ተፈጥሮ ምን ይገልጣሉ?
ማቴ. 24:30______________________________________________
1ተሰ. 4:16______________________________________________
ማቴ. 26:64______________________________________________
ራእ. 1:7_________________________________________________
2ተሰ. 1:7–10____________________________________________
“ሰማይ እንደ መከፈትና መዘጋት ይል ነበር፡፡ ከእግዚአብሔር ዙፋን የሚወጣው ክብር የሚያንጸባርቅ ይመስል ነበር፡፡ ተራሮች በነፋስ እንደሚወዛወዙ ረጃምም ቄጤማዎች ሆኑ፡፡ ዐለቶች በሁሉም የምድር አቅጣጫዎች ተበተኑ፡፡ በብርቱ የሚያጓራ የዐውሎ ነፋስ ድምፅ ተሰማ፡፡ ባሕሩም በቁጣ ተሞላ፡፡ የጥፋት ተልዕኮ ይዘው እንደሚተሙ የአጋንንት ድምፀት ዓይነት የቁጣ ጩኸት ተስተጋባ፡፡
ምድር በውቂያኖስ ላይ እንደሚነሳ ብርቱ ሞገድ ዋለለች፡፡ የምድር ገጽ እየተሰባበረ መሰረቶቿ የሚሸሹ መሰሉ፡፡ የተራሮች ሰንሰለት ሰመጡ፡፡ ሰዎች ይኖሩባቸው የነበሩ ደሴቶቸም ጠፉ፡፡ እንደ ሶዶም የእርክስና መዲና የነበሩ የባሕር ወደቦች በቁጡ ውሖች ተሰለቀጡ፡፡ ታላቂቷ ባቢሎን በእግዚአብሔር ፊት ታወሰች ‘በብርቱ ቁጣው ወይን ጠጅ የተሞላውን ጽዋ ሰጣት’ ”—Ellen G. White, The Great Controversy, p. 637. የየሱስ ዳግም ምጽአት ይህችን የምናውቃትን ዓለም ወደ ፍጻሜ የሚያመጣ ግዙፍ ክስተት ነው፡፡ መሆን ሲጀምር ጉዳዩን ሁሉም ሰው ያውቃል፡፡ የሱስ በመጀመሪያ ምጽዓቱ ለእኛ ያደረገው ነገር ኋላ በዳግም ምጽአቱ ሙሉ ለሙሉ የሚታይ ይሆናል፡፡ በዳግም ምጽአቱ ተጨባጭ ሁናቴ ውስጥ መኖር በዛሬው አኗኗራችን ላይ ተጽእኖ ሊኖረው የሚችለው እንዴት ነው? ለህይወት በትክክል አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን እንድናስታውስ እንዴት ሊረዳን ይችላል?

ሰኔ 21
Jun 28

በሕይወት ያሉትና ያንቀላፉት


የሱስ ወዳጁ አልዓዛርን ከመቃብር ከማስነሳቱ አስቀድሞ እነዚህን ቃላቶች ተናግሮ ነበር “ ‘ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ በሕይወት ይኖራል’ ” (ዮሐ. 11፡5)፡፡ የሱስ ይህን የተናገረውን ለማመን የሚያዳግት አስገራሚ ነገር ባለቤትነት ሕዝቡ እንዲቀበል ብቻ አልፈለገም፤ ይልቁንም ከሞተ የሰነበተውንና መሽተት የጀመረውን የአልዓዛር በድን ለማስነሳት ተንቀሳቀሰ (ዮሐ. 11፡39)፡፡
በየሱስ የሚያምኑ እርሱ ራሱ እንደተናገረው በእርግጥ ቢያንቀላፉም ነገር ግን በትንሣኤ ዳግም ይነሳሉ፡፡ የሙታን ትንሣኤ ማለት ከዚህ ውጪ ሌላ ፍቺ የለውም፡፡ የየሱስን ዳግም ምጽአት የተስፋችን ማዕከላዊ ክፍል የሚያደርገው ይኸው ነው፡፡ በመቀጠል በቀረቡት ጥቅሶች መሰረት በክርስቶስ ያንቀላፉ የሱስ ዳግም ሲገለጥ ምን ይሆናሉ? ሮሜ. 6:5፣ 1ተሰ. 4:16፣ 1ቆሮ. 15:42–44፣ 53–55፡፡

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

የሱስ ራሱ ከሞት በመነሳት የተለማመደው የታላቁ ዳግም ምጽአት ተስፋ-በሁሉም የዕድሜ ክልል ሊገኙ የሚችሉ የእርሱ ታማኝ ተከታዮችም የሚለማመዱት እውነታ ነው፡፡ በእርሱ ትንሣኤ የየራሳቸው ተስፋና ማረጋገጫ አላቸው፡፡ የሱስ ዳግም ሲገለጥ በሕይወት የሚገኙት ላይ ምን ይከሰታል? ፊልጵ. 3፡21፣ 1ተሰ. 4፡17፡፡

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

የሱስ ዳግም ሲገለጥ በሕይወት የሚገኙት ታማኞች አዲስ አካል ይለብሳሉ፡፡ ከእንቅልፍ የተነሱት የለበሱት ዓይነት የማይበሰብስ አካል ይኖራቸዋል፡፡ “በሕይወት ያሉት ጻድቃን ‘በድንገት በቅጽበተ ዐይን’ ተለውጠዋል፡፡ በእግዚአብሔር ድምፅ ከብረዋል፡፡ አሁን ሕያው በመሆናቸው ከመቃብር ከተነሱ ቅዱሳን ጋር ጌታቸውን በአየር ለመገናኘት ይነጠቃሉ”—Ellen G. White, The Great controversy, p. 645.
በዚህ ምድር ከዘላለማዊው ሕይወት አስበልጠው የሚያዩአቸውና አስፈላጊውን ሁሉ መሥዋዕትነት የሚከፍሉላቸው የከበሩ ነገሮች ካሉ ዘርዝረው ያስቀምጡ ለመሆኑ እነዚህ ነገሮች ምንድን ናቸው?

ሰኔ 22
Jun 29

ተጨማሪ ሀሳብ፡


የየሱስ ዳግም ምጽአት አሳዛኙ የሰብዓዊው ፍጡር የኃጢአትና ሥቃይ ታሪክ በዚህ ዓለም ስለሚቀጥልበት ሁናቴ ተጨማሪ መግለጫ የሚዘከርበት ትዕይንት አይደለም፡፡ በዚህ ፋንታ የክርስቲያኖች እምነት ታላቅ ተስፋ በከፍተኛ ደረጃ የሚገለጥበት ነው፡፡ የዳግም ምጽአቱ ተስፋ ባይኖር ኖሮ የሰብዓዊው ዘር ታሪክ በሞት እስኪ ደመደም--በብዙ ሥቃይና አስቸጋሪ ሁናቴ ውስጥ ከማለፍ በዘለለ ፋይዳ ቢስ ሆኖ በቀረ ነበር፡፡ ህይወት የክርስቶስ ዳግም ምጽአት ከሚሰጠን ተስፋ የተነጠለ ሲሆን ዊልያም ሼክስፒር እንዳለው “በጩኸትና ንዴት የተሞላ ፋይዳ ቢስ የጅል ተረት ይሆናል፡፡” ሆኖም የእግዚአብሔር ቃል በተደጋጋሚ እንደሚያረጋግጥልን ይህ ተስፋ አለን፡፡ የሱስ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ በመስጠት (ማር. 10፡45) የዚህ ተስፋ ባለቤቶች እንዳደረገን ሁሉ--ለዚህ ዋጋ ለከፈለበት ብርቱ ጉዳይ ዳግም ይገለጣል፡፡ የሰማይ ከዋክብት ስለ ዳግም ምጽአቱ አይነግሩንም፡፡ ከአንዱ ዛፍ ወደ ሌላው እየበረሩ በማይሰለች ድምፃቸው የሚያዜሙ ዐዕዋፍም ይህን ታላቅ ዜና አያበስሩንም፡፡ ምንም እንኳ እነዚህ ነገሮች መልካም ወደሆነና ተስፋ ሊጣልበት ወደ ሚችል ተጨባጭ ነገር በራሳቸው ሊያመላክቱን ቢችሉም-አንድ ቀን የሱስ ሲገለጥ “መለከት ይነፋል፤ ሙታን የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ፤ እኛም እንለወጣለን” (1ቆሮ. 15፡5) ብለው አያስተምሩንም፡፡ “ ‘የሰው ልጅ በኀይሉ ቀኝ ሲቀመጥ፣ በሰማይ ደመናም ሲመጣ ታዩታላችሁ’ ” (ማር. 14:62) አይሉንም፡፡ ይልቁንም እነዚህን ነገሮች ማወቅ የቻልነው በእግዚአብሔር ቃል ስለተነገሩንና ቃሉ በሚሰጠን ተስፋ ላይ እምነት ስላለን ነው፡፡


የውይይት ጥያቄዎች፡




1. አንዳንዶች የየሱስ ዳግም ምጽአት የክርስትና መርኅዎች በክርስቶስ ተከታዮች ዘንድ በሙላት መገለጥ ነው ብለው ያስባሉ፡፡ ዳግም ምጽአቱ እንዲህ እንደ ተባለው ቢሆን ኖሮ ምን ዓይነት ትርጉም ሊኖረው ይችል ነበር? አባባሉ መልካም ሊሆን ቢችልም ነገር ግን በስተ መጨረሻ ያለ ምንም ተስፋ ሊተወን የሚችለው እንዴት ነው?
2. በዘመናችን ዝነኛ የሆነው--ዩኒቨርስ ወይም አጽናፈ ሰማያት ከምንም ነገር መጣ የሚለው መላ ምት የጅል አስተሳሰብ ነው የምንለው ለምንድን ነው? ሰዎች እንዲህ ያለውን አስተሳሰብ የሚያራምዱት ለምንድን ነው? ተከታዮች የሚያፈሩበት ምክንያቱስ ምንድን ነው? አጽናፈ ሰማያትን አስመልክቶ ሁሉንም ነገር የፈጠረውን ዘላለማዊ አምላክ ማመን ይበልጥ አመክኖአዊና ምክኒያታዊ የሆነው ለምንድን ነው?
3. በሐሙስ ትምህርት መጨረሻ ላይ በዚህ ምድር ከዘላለማዊው ሕይወት አስበልጠው የሚያዩአቸውና አስፈላጊውን ሁሉ መሥዋዕትነት የሚከፍሉላቸው የከበሩ ነገሮች ካሉ ዘርዝረው ያስቀምጡ በሚል ለቀረበው ጥያቄ የጻፏቸው ነገሮች ይኖራሉ? ካሉ ተወያዩባቸው፡፡ ከሌሉ፤ ከደኅንነት ሊያግደን የሚችል አንዳችንም ነገር በህይወታችን ላለመኖሩ እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን?