በክርስቶስ አንድ መሆን
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 4ኛ ሩብ ዓመት 2018

ጥቅምት 3 - ጥቅምት 9

ሶስተኛ ትምህርት

Oct 13 - Oct 19


“ሁሉም አንድ እንዲሆኑ”



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዮሐ. 17:1– 26፣ 1ዮሐ. 5:19፣ ዮሐ. 13:18–30፣ ዮሐ. 5:20–23፣ ማር. 9:38–41፣ ራእ. 18:4፣ 1ዮሐ. 2:3–6፡፡


መታሰቢያ ጥቅስ :--“ ‘የእነርሱን ትምህርት ተቀብለው በእኔ ለሚያምኑ ጭምር እንጂ ለእነዚህ ብቻ አልጸልይም፤ ይህም፣ አባት ሆይ፤ አንተ በእኔ፣ እኔም በአንተ እንዳለሁ ሁሉም አንድ እንዲሆኑ፣ እንዲሁም አንተ እኔን እንደ ላክኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ፣ እነርሱም በእኛ እንዲሆኑ ነው፡፡” (ዮሐ. 17፡ 20-21)፡፡

በ የሱስ ላይ ሊደርስ የተቃረበው ክህደትና ሞት ከወዲሁ ያስከተለበትን ጭንቀትና በአድማሱ አጥልቶ የነበረውን አስፈሪ ድባብ የዮሐንስ ወንጌል ያስቃኘናል፡፡ አልፎ አልፎ “የሊቀ ካኅናት ጸሎት” (ዮሐ. 17) በሚል የሚታወቁትንና የየሱስ የመጨረሻ ቃላት የሆኑትን አስደማሚ መመሪያዎች በአምስቱ ወሳኝ ምዕራፎች (ዮሐ. 13-17) እናገኛቸዋለን፡፡

“በአንዴ ሁለቱንም--ማለትም ካኅን እና የመሥዋዕት በግ በመሆን በዚህ ጸሎት ራሱን ቀድሶና ቤዛ አድርጎ መስጠቱ ለጌታችን ገጣሚ ክብርና ማዕረግ ነው፡፡ በተመሳሳይ ይህ የቅድስና ጸሎት የተደረገው ቤዛ ስለ ሆናቸው በሰገነት ስለ ነበሩት ደቀ መዛሙርት እና የኋላ ኋላ በእነርሱ ምስክርነት ወደ እምነት ለሚመጡ ሁሉ ነበር፡፡”—F. F. Bruce, The Gospel of John (Grand Rapids: Eerdmans, 1983), p. 328. የዚህ ጸሎት ዋንኛ ክፍል--በደቀ መዛሙርቱ እና በወደፊቶቹ በአዳዲስ አማኞች መሃል ሊኖር የሚገባ ኅብረት ምን ያህል የሱስን እንደሚያሳስበው ያሳየ ነበር፡፡ “‘ስለ ሰጠኸኝና የአንተ ስለሆኑት እንጂ ለዓለም አልጸልይም፡፡ የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው፤ የአንተ የሆነውም ሁሉ የእኔ ነው፤ በእነርሱም ከብሬአለሁ’” (ዮሐ. 17፡9-10) ይህ የየሱስ ጸሎት ቁልፍ ጭብጥ ነበር፡፡

ለዚህ ጸሎት ጥንቃቄ የተሞላው ትኩረት ሳንሰጥ በክርስቶስ አንድ የመሆኑ የቤተ ክርስቲያን ኅብረት የተሟላና ፋይዳ ያለው ውይይት ሊኖረው አይችልም፡፡ የሱስ ስለ ምን ጸለየ? ስለ ማን ጸለየ? የእርሱ ጸሎት ዛሬ ለእኛ ምን ትርጉም አለው?

ጥቅምት 4
Oct 14


የሱስ ስለ ራሱ መጸለዩ


የሱስ እንደ ሊቀ ካኅንነቱ የጸለየው ጸሎት በሦስት ይከፈላል፡፡ በመጀመሪያ ለራሱ መጸለዩ (ዮሐ. 17፡1-5)፣ በሁለተኛ ደረጃ ለደቀ መዛሙርቱ ያደረገው ጸሎት (ዮሐ. 17፡6-19)፣ ሦስተኛው ደግሞ በእርሱ ለሚያምኑ የወደፊት አማኞች የጸለየው ጸሎት ናቸው (ዮሐ. 17፡20-26)፡፡ ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዮሐ. 17፡1-5፡፡ የጸሎቱ ይዘት ምንድን ነው? ለእኛ ያለው ትርጉምስ ምን ይመስላል?



የሱስ በመጀመሪያ ለራሱ ይማልዳል፡፡ በዚሁ በዮሐንስ ወንጌል ቀደምት መልእክቶች የሱስ ጊዜው ገና አለመድረሱን ሲናገር እንመለከታለን (ዮሐ. 2፡4፣ 7፡30፣ 8፡20)፡ ፡ አሁን ግን ለኃጢአት መሥዋዕት የሚሆንባት ያቺ ሰዓት መቃረቧን ያወቀው የየሱስ ምድራዊ ህይወት ትዕይንት ከፍጻሜ ደርሶ ነበር፡፡ ሰብዓዊነትን ወስዶ የመጣበትን ምድራዊ ተልዕኮ በድል ለማጠናቀቅ ብርቱ ጥንካሬ ያስፈልገዋል፡፡ እነሆ ጊዜው የጸሎት ነው፡፡

የሱስ በአስጨናቂው የመስቀል ጎዳና ማለፉ ግዴታ ቢሆንበት እንኳ የአባቱን ፈቃድ በማድረግ እርሱን ከማክበር ወደ ኋላ አይልም ነበር፡፡ የሱስ የመስቀል ላይ መሥዋዕትነቱን መቀበሉ በተለምዶ እንደሚባለው “ዕጣ ፈንታው” ወይም “የአርባ ቀን ዕድሉ” ሳይሆን--እውነታው አብ የሰጠውን ሥልጣን በተግባር የሚለማመድበት ነበር፡ ፡ የሱስ ሰብዓዊውን ሥጋ ለመልበስ ምክንያት የሆነውን ተልዕኮ በሙሉ ፈቃደኝነት በማሳካት ይኸውም ለዓለም ኃጢአት የመሥዋዕት ሞት በመሞት አባቱን አከበረ እንጂ የሰማዕት ሞት አልሞተም፡፡

በዮሐ. 17፡3 መሰረት የዘላለም ሕይወት ምን ማለት ነው? እግዚአብሔርን ማወቅ ስንል ፍቺው ምንድን ነው?



የዘላለም ሕይወት ጽንሰ ሃሳብ እግዚአብሔርን በግል በማወቃችን ላይ የተመሰረተ ነው ሲል የሱስ በቀዳሚና በዋነኝነት ይነግረናል፡፡ ደኅንነት የሚገኘው በሥራ ወይም በዕውቀት ሳይሆን የሱስ በመስቀል ላይ ካደረገልን ነገር አኳያ ጌታን የማወቅ ተሞክሮ ነው፡፡ ይህ ዕውቀት ከአብ ጋር ባለን የግል ግንኙነት ይማከላል፡፡ ዕውቀትን በጭብጥና ዝርዝር በሆኑ ጉዳዮች መገደብ ሰብዓዊ ዝንባሌአችን ቢሆንም፤ ነገር ግን የሱስ እዚህ ላይ ጥልቀት ያለውንና አብልጦ እርካታ ሊያመጣ የሚችለውን ይኸውም ከእግዚአብሔር ጋር ግላዊ ግንኙነት መፍጠርን ኢላማ ሲያደርግ ይታያል፡፡ ሌላኛው የመጀመሪያው የየሱስ ምጽአት ዓላማ ሰብዓዊው ፍጡር የእግዚአብሔርን ማንነት ለማወቅ ለሚያደርገው ፍተሻ ይበልጥ ትርጉም ወዳለውና የሚያድን ዕውቀት መምራት ነው፡፡ ይህ ዕውቀት ወደ እርስ በርስ ኅብረት መምራቱ ዕሙን ነው፡፡ ስለ እግዚአብሔር በማወቅና እርሱን በግል በማወቅ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ እንዲመጡ የረዱዎት ምን ዓይነት ተሞክሮዎች አሎት?

ጥቅምት 5
Oct 15


የሱስ ስለ ለደቀ መዛሙርቱ መጸለዩ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዮሐ. 17፡9-19፡፡ የሱስ በተለይ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በተያያዘ ምን ብሎ እየጸለየ ነው?



የሱስ በመቀጠል የጸለየው ለደቀ መዛሙርቱ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ያ የቀደመ የጌታ አብሮነት በማክተሙ፤ በእርሱ ላይ የነበራቸውን እምነት ሊያሳጡ የሚችሉ የከፉ አደጋዎች ከፊታቸው ባሉት ቀናት ተደቅነው ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ ለአብ ጥበቃና ጥንቃቄ አሳልፎ ሰጣቸው፡፡

ደቀ መዛሙርቱ ከዓለም ይጠበቁ ዘንድ የሱስ ስለ እነርሱ ጸለየ እንጂ ስለ ዓለም አልጸለየም፤ ምክንያቱም ዓለም የአብን ፈቃድ እንደሚቃወም ያውቃል (1ዮሐ. 5፡19)፡ ፡ ነገር ግን ይህ ዓለም ደቀ መዛሙርቱ አገልግሎት የሚሰጡበት አውድማ እንደመሆኑ በውስጡ ካለው ክፉ ሁሉ እንዲጠበቁ ጸለየ፡፡ የሱስ በዓለም ያሉ ፍጥረቶቹ ሁኔታ ግድ ስላለው የአዳኝነቱን ስፍራ ወሰደ፡፡ የወንጌል ስርጭት ወደ ዓለም ወጥተው መልካሙን የምስራች ከሚሰብኩ ወገኖች ጋር በጥብቅ የተሳሰረ በመሆኑ፤ ክፉው እንዳያሸንፋቸው ስለ እነርሱ መማለድ አስፈለገው (ማቴ. 6፡13)፡፡ የሆነው ሆኖ ከየሱስ ደቀ መዛሙርት መካከል አንዱ ሸንፈት አገኘው፡፡ ከዚያ ምሽት ቀደም ብሎ ከመካከላቸው አንዱ ሊክደው (አሳልፎ ሊሰጠው) መወሰኑን የሱስ ጠቅሶ ነበር (ዮሐ. 13፡18-30)፡፡ ምንም እንኳ የሱስ ብሉይ ኪዳን ስለ ይሁዳ ክህደት የተነገረውን ትንቢት ቢጠቅስም (መዝ. 41፡9) ይሁዳ የዕጣ ፈንታ ሰለባ አልነበረም፡፡ በዚያ የመጨረሻ የጌታ እራት አገልግሎት የሱስ የፍቅርና የወዳጅነት ስሜት አሳይቶት ነበር (ዮሐ. 13፡26-30)፡፡ “በፋሲካ የጌታ ራት የሱስ ክህደት ሊፈጽምበት የተሰናዳውን ደቀ መዝሙር ሃሳብ በመግለጥ መለኮታዊ ባህሪውን አሳየ፡፡ በደግነት የተሞላው የሱስ ይሁዳን በደቀ መዝሙርነት ተቀብሎ የአገልግሎቱ አካል አደረገው፡፡ ሆኖም የመጨረሻው የፍቅር ተማጽኖ ተገቢውን ከበሬታና ተቀባይነት ማግኘት ሳይችል ቀረ፡ ፡”—Ellen G. White, The Desire of Ages, p. 720. ቀደም ሲል እንደ ተከሰተው ክፉ ቅናትና ምቀኝነት ደቀ መዛሙርቱን ሊከፋፍል እንደሚችል ያውቅ የነበረው ጌታ በመካከላቸው ኅብረት እንዲኖር ጸለየ፡፡ “ቅዱስ አባት ሆይ፤ እኛ አንድ እንደ ሆንን፣ እነርሱም አንድ እንዲሆኑ በሰጠኸኝ በስምህ ጠብቃቸው” (ዮሐ. 17፡11)፡፡ እንዲህ ያለው ኅብረት ከሰብዓዊው ሥራ ውጤት በላይ በመሆኑ፤ የመለኮታዊው ጸጋ ስጦታ ውጤት ብቻ ይሆናል፡፡ አንድነታቸው በአብና በወልድ ኅብረት ላይ መመስረቱ ለወደፊቱ ውጤታማ አገልግሎት ወሳኝ ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡

በእውነት መቀደሳቸው ወይም መባረካቸው ሌላው ለአገልግሎት ወሳኙ ነጥብ ነው፡፡ በደቀ መዛሙርቱ ልብ ውስጥ የሚተገበረው የአምላካዊው ጸጋ ሥራ የተለወጡ ሰዎች ያደርጋቸዋል፡፡ የእግዚአብሔርን እውነት የመመስከር አገልግሎት እስከ ሰጡ ድረስ፤ እነርሱ ራሳቸው በዚያ እውነት መለወጣቸው የግድ ይሆናል፡፡ “ከዚህ ዓለም” አለመሆን ማለት ምን ማለት ነው? የዕለት ከዕለት ህይወታችንም ሆነ የአኗኗር ዘይቤአችን “ከዚህ ዓለም” አለመሆናችንን ማሳየት የሚችለው እንዴት ነው?

ጥቅምት 6
Oct 16


“በእኔ ለሚያምኑ”


የሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ከጸለየ በኋላ የልመናውን ይዘት በማስፋት እንዲህ ብሎአል፡ “የእነርሱን ትምህርት ተቀብለው በእኔ ለሚያምኑ ጭምር እንጂ ለእነዚህ ብቻ አልጸልይም” (ዮሐ. 17፡20)፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዮሐ. 17፡20-26፡፡ የሱስ ውሎ አድሮ በወንጌል መልእክት ለሚያምኑ ወገኖች የነበረው ምኞት ምን ነበር? የዚህ ጸሎት ፍጻሜ ማግኘት ወሳኝ የሆነው ለምንድን ነው?



አብ እና ወልድ አንድ እንደሆኑ ሁሉ የወደፊቶቹም አማኞች አንድ ይሆኑ ዘንድ የሱስ ጸለየ፡፡ የሱስ የአብን እና ወልድን አንድነት አስመልክቶ የጠቃቀሳቸውን ጥቂት ነጥቦች በዮሐንስ ወንጌል እናገኛለን፡፡ አብም ሆነ ወልድ ማንኛውንም ተግባር የሚያከናውኑት በተናጥል ሳይሆን ሁሌም በአንድነት ነው (ዮሐ. 5፡20-23)፡፡ አብ ልጁን ለዓለም አሳልፎ እስከ መስጠት ፈቃደኛ መሆኑ እና ወልድ ህይወቱን ለመስጠት እሺታውን መግለጹ ለወደቀው ሰብዓዊ ዘር ያላቸውን የማይነጣጠል ፍቅር ያሳያል (ዮሐ. 3፡16፣ 10፡15)፡፡ የሱስ በዚህ ጸሎቱ በአብ እና በወልድ መካከል ያለውን የፍቅርና የዓላማ እንድነት ይጠቅሳል፡ “‘እርስ በርሳችሁ ብትዋደዱ፣ ሰዎች ሁሉ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ’ ” (ዮሐ. 13፡35)፡፡ ከአብም ሆነ ከወልድ ጋር የሚኖርን አንድነት በፍቅር ገልጾ ማሳየት ለታዛቢው የማይታበል ማረጋገጫ ይሆናል፡፡ “እውነተኛ ልባዊ አንድነታቸውን የሚገልጸው ተግባራቸው፤ ለወንጌል እውነት አሳማኝ ምስክርነት መስጠቱ የግድ ይሆናል”—Andreas J. Köstenberger, John, Baker Exegetical Commentary on the New Testament (Grand Rapids: Baker Academic, 2004), p. 498. ይህ እንግዲህ የየሱስን አዳኝነት ዓለም የሚያውቅበት መንገድ ነው፡ ፡ በሌላ አነጋገር ይህ የሱስ የጸለየለት አንድነት በሰዎች የማይታይና የተሰወረ መሆን አይችልም፡፡ ዓለም በእግዚአብሔር ሕዝቦች መሃል ፍቅርና አንድነት ማየት ሳይችል የወንጌልን እውነትነት እንዴት አምኖ መቀበል ይሆንለታል?

“እግዚአብሔር በዘላለማዊው እውነት መድረክ በፍጹም አንድነት የሚቆሙ ሕዝቦችን እየመራ ነው… ሕዝቦቹ ሁሉ ወደ እምነት አንድነት ይመጡ ዘንድ አምላካዊው እቅድ ነው፡፡ ክርስቶስ ራሱን በመስቀል ላይ መሥዋዕት አድርጎ ከመስጠቱ ጥቂት ቀደም ብሎ እርሱ ከአብ ጋር አንድ እንደሆነ ደቀ መዛሙርቱም አንድ እንዲሆኑ ጸለየ፡፡ ክርስቶስ በአብ የተላከ አዳኝ መሆኑን ዓለም ማመን ነበረበት፡፡ ‘የእነርሱን ትምህርት ተቀብለው በእኔ ለሚያምኑ ጭምር እንጂ ለእነዚህ ብቻ አልጸልይም’--የተሰኘው ይህ በእጅጉ ልብ የሚነካና ወደር የማይገኝለት ጸሎት ዘመናትን ተሻግሮ እነሆ ከእኛም ጊዜ ደርሶአል፡፡ “የክርስቶስ ተከታዮች ለዚህ ጸሎት በሕይወታቸው ምላሽ የመስጠት ብርቱ ኃላፊነት ወድቆባቸዋል”—Ellen G. White, Testimonies for the Church, vol. 4, p. 17. በዚህ ስፍራ የቀረበው ዓይነት ኅብረት ላይ ለመድረስ በግል ሕይወታችንና በቤተ ክርስቲያን ምን እያደረግን እንገኛለን? ቤተ ክርስቲያናችን ወደሚፈለገው ኅብረት እንድታመራ ፍላጎታችን ከሆነ እያንዳንዳችን ለዓለም የሞትን መሆናችን ወሳኝ የሆነው ለምንድን ነው?

ጥቅምት 7
Oct 17


ኅብረት በክርስቲያኖች መሃል


የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ማር. 9፡38-41፣ ዮሐ. 10፡16፡፡ ማነው እውነተኛ የየሱስ ተከታይ በሚል ለሚነሳው ጥያቄ ከእኛ በላይ ላሳር ለተሰኘው ምላሽ እና ቅጽበታዊ ፍረጃ አግባብነት ዙሪያ የሱስ ለደቀ መዝሙሩ ዮሐንስ ከሰጠው ምላሽ ምን እንማራለን?



ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች የሱስ በዮሐ. 17 የጸለየውን ጸሎት በቀጥታ ከቤተ ክርስቲያናቸው ኅብረት ጋር ገጣሚ አድርገው የማስተዋል አካሄድ ይከተላሉ፡፡ የሦስቱን መላእክት መልእክት ለዓለም በማካፈል ተልዕኮአችንን ከዳር ለማድረስ እንደ ቤተ ክርስቲያን አንድ ልንሆን ይገባል፡፡ ሆኖም እዚህ ላይ መጠኑ ቢያንስም ሞጋች ሃሳብ አለ፡፡

ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ስለሚኖረን ኅብረትስ? የሱስ የጸለየውን ጸሎት ከእነርሱ ጋር ከሚኖረን ኅብረት ብርሃን አኳያ እንዴት እናዛምደዋለን ነው? ልክ እንደኛ ሁሉ እግዚአብሔር በሌሎች ቤተ ክርስቲያኖችም ታማኝ ሕዝቦች እንዳሉት እናምናለን፡፡ በተጨማሪ እግዚአብሔር በባቢሎን ሳይቀር ታማኞች እንዳሉት መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስቀምጥልናል፡፡ “‘ሕዝቤ ሆይ፤ በኃጢአቷ እንዳትተባበሩ፣ ከመቅሰፍቷም እንዳትካፈሉ፣ ከእርሷ ውጡ’ ” (ራእ. 18፡4)፡፡ በተመሳሳይ የክርስቶስ ተከታዮች ነን በሚሉ ታላቅ የክህደት ተግባር እንደሚፈጸም ከራእይ መጽሐፍ እንረዳለን፡፡ ይህን ተከትሎ አያሌ ሐሰተኛ ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው ብሎም ከመንግሥት ጋር በሚፈጥሩት ኅብረት በራእ. 13፡1-17 የተገለጸው ስደት ገቢራዊ ወደ መሆን ይመጣል፡፡ በዚህ የተነሳ አድቬንቲስቶች እንደ አለማቀፉ የአብያተ ክርስቲያናት ኅብረት የሚቀርቡላቸውን የኅብረታችን አካል ሁኑ ጥሪ የሚመለከቱት ሁሌም በጥንቃቄ ነው፡፡

ነገሩ እንዲህ ከሆነ ከሌሎች የክርስትና ድርጅቶች ጋር አግባብ መፍጠር የምንችለው እንዴት ነው? ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ከሌሎች አብያተ ክርስያናት ጋር አብራ በምትሠራቸው ሥራዎች ዙሪያ ኤለን ጂ. ኋይት የሚከተለውን ጽፋለች፡ ፡ “ሰብዓዊው ወኪል የገዛ ፈቃዱን ለእግዚአብሔር ሲያስገዛ መንፈስ ቅዱስ ግለሰቡ የሚያገለግላቸውን ወገኖች ልብ ይነካል፡፡ እንደ Women’s Christian Temperance Union የመሳሰሉትን ኅብረቶች መራቅም ሆነ መተው እንደሌለብን ተመልክቻለሁ፡ ፡ ከእነርሱ ጋር በምንፈጥረው ኅብረት ከሚያሰክር መጠጥም ሆነ በአካላችን ላይ ጉዳት ከሚያደርሱ ልል ልማዶች ሙሉ ለሙሉ ተጠብቀንና በሰንበት ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያለንን አቋም ጠብቀን፤ መሻትን በመግዛት ዙሪያ ያላቸውን አቋም ማድነቅ እንችላለን፡ ፡ መሻትን በመግዛት ዙሪያ ለሚነሱ ጥያቄዎች በራችንን ክፍተን ከእኛ ጋር ኅብረት ፈጥረው የሚሠሩበትን ግብዣ በማቅረብ ጽኑ እገዛቸውን ማግኘት እንችላለን፡፡ እነዚህ ወገኖች እንዲህ ያለውን ኅብረት ከእኛ ጋር ሲፈጥሩ አዳዲስ እውነቶችን ይሰማሉ፡፡ መንፈስ ቅዱስም እነዚህን ልቦች የማነቃቃት ሥራ ለመሥራት ይጠባበቃል፡፡”—Welfare Ministry, p. 163. ምንም እንኳ ጸሐፊዋ በአንድ ወቅት ስለ ነበረ ኅብረት እየተናገረች ቢሆንም ነገር ግን ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር በሚኖረን ዝምድና በተለይም በአብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ጥያቄዎች ዙሪያ ልንከተላቸው የሚገቡ መርኅዎችን ትሰጣለች፡፡ አብረን ልንሠራ የምንችልባቸው ነጥቦች፡--(1) የጋራ ፍላጎት ማሳደር በሚችሉ ማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ (2) የእምነታችን እሴቶችና ልምምዶች ሳይጣሱ እንዲጠበቁ አጽንኦት በመስጠት (3) የተባረክንባቸውን የከበሩ እውነቶች ለሌሎች በማካፈል ይህን “ኅብረት” ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል፡፡

ጥቅምት 8
Oct 18


በፍቅር የምንጋራው አንድ እምነት


ዘላለማዊ ሕይወት ማለት እግዚአብሔርን ማወቅ ነው--ሲል የሱስ በዮሐ. 17:3 ተናግሮአል፡፡ ለመሆኑ እግዚአብሔርን ማወቅ ምን ማለት ነው? እግዚአብሔርን ማወቃችንን በየቀኑ ሕይወታችን የምናሳየውስ እንዴት ነው?



ከመቼውም የዓለም ታሪክ በላቀ ሥልጡን እንደሆነ የሚናገረው የዘመናችን ማኅበረሰብ ራሱን ለሕግ ታዛዥ ዜጋ አድርጎ ሲያቀርብ ቢስተዋልም--ነገር ግን በእግዚአብሔር የተጣለበትን አምላካዊ ትእዛዛት የመጠበቅ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ግዴታውን ከመወጣት ይልቅ ጉዳዩን ዝቅ አድርጎ ሲመለከት ይስተዋላል፡፡ እንደውም አንዳንዶች ትእዛዛቱ በእግዚአብሔር ጸጋ ተወግደዋል ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ ሆኖም ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ አይደለም፡፡ “ትእዛዛቱን መጠበቅ እግዚአብሔርን የማወቃችን መሰረት ሳይሆን እግዚአብሔርን/ የሱስን የማወቃችንና እርሱን የመውደዳችን ምልክት ነው፡፡ ስለዚህ በእግዚአብሔር ላይ ያለን ዕውቀት በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ወደ ተግባር የሚመራን ጭምር ነው፡፡”—Ekkehardt Mueller, The Letters of John (Nampa, Idaho: Pacific Press, 2009), p. 39. የሱስ ራሱ ስለዚህ ጉዳይ አጽንኦት ሰጥቶ ሲናገር “ብትወዱኝ ትእዛዜን ትጠብቃላችሁ፡፡” “የሚወደኝ ትእዛዜን ተቀብሎ የሚጠብቅ ነው” ይላል (ዮሐ. 14፡15፣ 21)፡፡ “እግዚአብሔርን ስንወድና ትእዛዛቱን ስንፈጽም የእግዚአብሔርን ልጆች እንደምንወድ በዚህ እናውቃለን፤ እግዚአብሔርን መውደድ ትእዛዛቱን መፈጸም ነውና፡፡ ትእዛዛቱም ከባድ አይደሉም፡ ፡” (1ዮሐ. 5፡2-3)፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዮሐ. 13፡34-35፡፡ የሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸው አዲስ ትእዛዝ ምን ነበር? ይህ በየሱስ ተከታዮች መካከል ከሚኖር ኅብረት ጽንሰ ሀሳብ ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው?



ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ በሚል የቀረበው ትእዛዝ እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠው ትእዛዛት አካል እንደ መሆኑ በራሱ አዲስ አልነበረም (ዘሌዋ. 19፡18)፡፡ አዲስ የሆነው እርሱ እንደ ወደዳቸው ደቀ መዛሙርቱም እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱ የሰጣቸው ትእዛዝ ነበር፡፡ ራስን መሥዋዕት አድርጎ እስከ መስጠት የደረሰው የየሱስ ፍቅር ምሳሌ ለክርስቲያኑ ማኅበረሰብ በዓይነቱ አዲስ ሥነ ምግባራዊ አስተምህሮ ነበር፡፡

እንዴት ያለ እጹብ ድንቅ ሥርዓት ከፊታችን ተዘርግቶአል! የየሱስ ሕይወት--ፍቅር በተግባር የተገለጸበት ትዕይንት ነው፡፡ አጠቃላዩ የጸጋ ሥራ ራስን የመካድና መሥዋዕት አድርጎ የማቅረብ የማያቋርጥ የፍቅር አገልግሎት ጥረት ነው፡፡ የክርስቶስ ሕይወት ስለ ሌሎች መልካም ሲባል የማያቋርጥ ፍቅርና ራስን መሥዋዕት ማድረግ የተገለጸበት መሆኑን መረዳት እንችላለን፡፡ በክርስቶስ ላይ መነሳሳት የፈጠረው መርኅ በሕዝቦቹ የእርስ በርስ ግንኙነትም ላይ መነሳሳት ሊፈጥር የተገባ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር በመካከላችን አንድነት እንዲኖር መንስዔ ከመሆኑ ባሻገር ለዓለም ብርቱ ምስክር መሆኑ አንድና ሁለት የለውም፡፡ የሱስ የገለጠው ዓይነት ራስን መሥዋዕት አድርጎ የመስጠትን ፍቅር በተመሳሳይ ለሌሎች ገልጦ ማሳየትን መማር የምንችለው እንዴት ነው?

ጥቅምት 9
Oct 19


ተጨማሪ ሀሳብ


፡-- Ellen G. White, “God’s Law Immutable,” pp. 443–446, in The Great Controversy. Read the articles “Denominations, Relations to Other,” pp. 763, 764, and “Roman Catholic Church,” p. 1110, in The Ellen G. White Encyclopedia. “ምንም እንኳ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን የአያሌ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያኖች ባለቤት ዓለማቀፍ ተቋም ብትሆንም ነገር ግን አድቬንቲስቶች እንደ ብቸኛዋ ሁለንተናዊ ዩኒቨርስ አቀፍ የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን አይመለከቷትም፡፡ ለዚህ መንስዔው ዩኒቨርስ አቀፏ ሁለንተናዊ ቤተ ክርስቲያን ከማንኛውም የክርስትና ተቋም እጅግ የገዘፈ ባህሪ በመላበሷ ነው፡፡ ዩኒቨርስ አቀፏ በየሱስ የሚያምኑትንና እርሱን የሚከተሉትን ወገኖች በአንድ የምትይዝ እንደ መሆኗ ስፋትና መጠኗ የሚታይ፣ የማይታይም ነው፡፡ ይህ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ሥነ መለኮታዊ ጉዳይ በራእይ መጽሐፍ አሳዛኝ በሆነ ሁኔታ የተገለጸውንና በክርስቲያኖች መካከል ገቢራዊ የሆነውን ክህደት ከግምት ካስገባ ወደ ጡዘት ሊያመራ ይችላል፡፡ በበጉ፣ በሙሽራው፣ በቅድስት ከተማ ወይም በአዲሲቱ የሩሳሌም (ራእ. 21፣22) የተመሰለችውና በራእ. 12 የምናገኛት ጉድፍ ዐልባዋ ንጽሕት ቤተ ክርስቲያን ከራእ. 17 ታላቂቷ ‘አመንዝራ’ ከተማ ባቢሎን ጋር በንጽጽር ቀርባለች፡፡ ለምሳሌ ዩኒቨርስ አቀፏ ቤተ ክርስቲያን በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ በገሃድ የመታየት ሁኔታ ቢገጥማትም--ነገር ግን ይህችኑ ቤተ ክርስቲያን መካከለኛው ክፍለ ዘመን ላይ ማየት እጅግ ውስብስብና አስቸጋሪ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ “ስለዚህ አድቬንቲስቶች የእውነተኛዋን የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ጽንሰ ሃሳብ በራሳቸው ኃይማኖታዊ ተቋም ብቻ አይወስኑም ወይም ከሌሎች የክርስትና ኃይማኖታዊ ተቋሞች ጋር በቀጥታ አያያይዙም፡፡ እውነተኛዋ የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን እርሱን በእውነት የሚያምኑትን ወገኖች ታካትታለች፡፡ እግዚአብሔር እነዚህን ወገኖች ያውቃቸዋል፡፡ በሌላ በኩል አድቬንቲስቶች ራሳቸውን በራእ. 12፡17 እንዲሁም ከምዕራፍ 12-14 የተጠቀሱት የእግዚአብሔር የመጨረሻው ዘመን ትሩፋን አድርገው ያምናሉ፡፡ ትሩፋኑ አካባቢያዊም ሆነ ዩኒቨርስ አቀፍ ባህሪ የተላበሱ ናቸው፡ ፡”— Ekkehardt Mueller, “The Universality of the Church in the New Testament,” in Ángel Manuel Rodríguez, ed., and Message, Mission, and Unity of the Church (Silver Spring, Md.: Biblical Research Institute, General Conference of Seventh-day Adventists, 2013), p. 37.


የመወያያ ጥያቄዎች



፡ 1. የሱስ በዮሐ. 17 የጸለየው ጸሎት ፍጻሜ ማግኘት ለቤተ ክርስቲያናችን እጅግ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ለመጀመሪያው ክፍለ ዘመኗ ቤተ ክርስቲያን አንድነት የነበረው ፍላጎትስ ስለ ዛሬዋ ምን ያሳየናል?

2. አጥቢያ ቤተ ክርስቲያንዎ ከማኅበራዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር አብራ የምትሠራባቸው አጋጣሚዎች ተፈጥረዋል? የተገኘው ስኬት ምን ይመስላል? አመቺ ሁናቴዎች በተገኙ ቁጥር በተሰጡን እውነቶች ላይ ሳንደራደር አብረናቸው መሥራት የምንችለው እንዴት ነው?

3. በመቀጠል የቀረበው በታላቁ ተጋድሎ መጽሐፍ የምናገኘው መልእክት አንደምታ ምንድን ነው? ይህ በመካከላችን በተጨባጭ እንዲኖር ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? “የእግዚአብሔር ሕዝቦች ከቃሉ የሚንጸባረቀውን ብርሃን የሚቀበሉ ከሆነ ክርስቶስ ለእነርሱ የጸለየው የአንድነት ደረጃ ላይ ይደርሳሉ፡፡ ይኸውም ሐዋርያው እንዲህ ሲል የገለጸው ነው ‘በሰላም ማሰሪያ የመንፈስ አንድነት… አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤ አንድ ጌታ፣ አንድ እምነትና አንድ ጥምቀት አለ’ (ኤፌ. 4፡ 3-5)፡፡ ”—Ellen G. White, The Great Controversy, p. 379. ማጠቃለያ፡--በዮሐ. 17 የቀረበው የየሱስ የሊቀ ካኅናት ጸሎት ዛሬም የቤተ ክርስቲያን አንድነት ጌታን ግድ እንደሚለው አስታዋሽ ነው፡፡ ጸሎቱን ጸሎታችን በማድረግ በእግዚአብሔር ቃል ላይ ያለንን እምነት ለማጠናከር መጣር ይኖርብናል፡፡ እንዲሁም ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር የቱንም ዓይነት የሥነ መለኮታዊ አስተምህሮ ልዩነቶች ቢኖሩንም፤ ግንኙነታችን ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የሚለውን መርኅ መሰረት ያደረገ ሊሆን ይገባል፡፡