በክርስቶስ አንድ መሆን
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 4ኛ ሩብ ዓመት 2018

ከጥቅምት 10- 16

አራተኛ ትምህርት

Oct 20 - Oct 26




የኅብረት ቁልፉ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ኤፌ. 1:3–14፣ ገላ. 4:7፣ ኤፌ. 2:11–22፣ 4:1–6፣ 11፣ ማቴ. 20:25–28፣ ኤፌ. 5:15–6:9፡፡


መታሰቢያ ጥቅስ :--“በክርስቶስ ያቀደውንም የፈቃዱን ምስጢር እንደ በጎ ሐሳቡ እንድናውቅ አደረገ፡፡ በዘመን ፍጻሜ ይሆን ዘንድ ያለው ሐሳቡ በሰማይም በምድርም ያሉትን ነገሮች ሁሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ ሥር ለመጠቅለል ነው፡፡” (ኤፌ. 1፡9-10)፡፡

የ እስያ አካል በሆነችው የዛሬዋ የቱርክ ግዛት ማለትም በሜዲቴራንያን፣ በኤጅየን እና በጥቁር ባሕር መካከል ትገኝ የነበረችው ኤፌሶን በሐዋርያት ዘመን ዋንኛ የንግድ ማዕከል ከመሆኗ በተጨማሪ ብርቱ ተጽእኖም ነበራት፡፡ በዚያ ማለትም በኤፌሶን የነበረችው ቤተ ክርስቲያን ከአይሁዳውያን፣ ከአሕዛብ እና ከልዩ ልዩ ታሪካዊ ዳራ ከመጡ ማኅበረሰቦች የተውጣጡ አማኞች ነበሯት፡፡ በዚህ የተነሳ አባላት በክርስቶስ ባይሆኑና እንደ ክርስቶስ አካልነታቸው ኅብረት ባይፈጥሩ ከዘመኑ ዓለም አስተሳሰብ አኳያ ወደ ውዝግብ ሊያመሩ ይችሉ ነበር፡፡ በመሆኑም የክርስቶስ ተከታዮች አንድነት ጉዳይ ጳውሎስን በእጅጉ ያሳስበው እንደ ነበር ለኤፌሶን ሰዎች ከላከው ደብዳቤ መረዳት እንችላለን፡፡ ጳውሎስ ስለ ኅበረት የነበረው ጽንሰ ሃሳብ ሁለት ገጽታዎች ሲኖሩት አንደኛው፡--የቤተ ክርስቲያን ኅብረት ይኸውም አይሁዶችና አሕዛብ በክርስቶስ አንድ አካል ወደ መሆን የመጡበት፡፡ ሁለተኛው፡--የአጽናፈ ሰማይ (ዩኒቨርስ) ኅብረት ይኸውም በሰማይና በምድር ሁሉም ነገሮች በስተ መጨረሻ በክርስቶስ የሚያገኙት አንድነት ናቸው፡፡ የዚህ ኅብረት ምንጩ ክርስቶስ ነው፡፡ “በክርስቶስ” ወይም “ከክርስቶስ ጋር” የሚለው አገላለጽ በዚህ መልእክት እጅግ ተደጋግሞ ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን--እግዚአብሔር በየሱስ ክርስቶስ ሕይወት፣ ሞት እና ትንሣኤ ለእኛ ብሎም ለመላው አጽናፈ ሰማይ የፈጸመውን ለማሳየት ነው፡፡ በደኅንነት እቅድ የመጨረሻው የእግዚአብሔር ዓላማ ሁሉም ነገር በክርስቶስ አማካይነት ዳግመኛ ኅብረት እንዲፈጥር ማድረግ ነው፡፡ ይህ ኅብረት በሙላት ደምቆ የሚታየው በምድር ታሪክ መጨረሻ ነው፡፡

ጥቅምት 11
Oct21

በክርስቶስ የሚገኙ በረከቶች


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡--ኤፌ. 1፡3-14፡፡ እንደ ጳውሎስ አባባል እዚህ ላይ በክርስቶስ የተሰጠን ነገር ምንድን ነው?





የየሱስ ተከታዮች ለእግዚአብሔር ምስጋና የምናቀርብበት አያሌ ምክንያቶች አሉን፡፡ በክርስቶስ አማካይነት ወንዶችና ሴቶች ልጆቹ አድርጎ ተቀብሎን ሲያበቃ የዚህ ዓለም ወኪሎቹ አደርጎ መረጠን፡፡ ጳውሎስ በክርስቶስ አማካይነት ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ለመግለጽ አያሌ ሥዕላዊ ማሳያዎችን ጥቅም ላይ ሲያውል ይስተዋላል፡ ፡ ከእነዚህ ምስሎች መካከል እኛን እንደ ልጆቹ መቀበሉን የሚያሳየውና በኅብረት ላይ ትኩረት የሚያደርገው የዚህ ትምህርት ርዕሰ ጉዳይ ነው፡፡ እኛ በክርስቶስ አማካይነት የልጅነት ማዕረግ አግኝተን የእግዚአብሔር ቤተሰብ አካል ለመሆን በቅተናል፡፡ ደግሞም እግዚአብሔር ከእስራኤል ልጆች ጋር ገብቶ የነበረው ኪዳን ለዚህ ቤተሰባዊ ገጽታ በማመሳከሪያነት መቅረብ ይችላል፡፡ የሱስን እንደ መሲህ የተቀበሉ አሕዛብም እንዲሁ ለእስራኤል የተገባው ኪዳን ወራሽ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸውን ከጳውሎስ መልእክት ዐውድ መመልከት እንችላለን (ሮሜ 8፡17፣ ገላ. 4፡7)፡፡ ከክርስቶስ ጋር ኅብረት የመፍጠርና በክርስቶስ የመሆን ጥቅም ለሁሉም የክርስትና ኅብረት ወሳኝና መሰረታዊ ነው፡፡ መላው ሰብዓዊ ዘር ከክርስቶስ ጋር ኅብረት እንዲፈጥር ማድረግ የእግዚአብሔር ምኞት መሆኑን ከጥቅሱ መገንዘብ እንችላለን፡ ፡ በእግዚአብሔር ቤተሰብ ውስጥ እኛ ሁላችን በእኩል ዐይን በእርሱ የተወደድን፣ የከበረ ዋጋና እንክብካቤ የተቸረን ልጆቹ ነን፡፡

አስቀድሞ ወሰነን (ኤፌ. 1፡5፣ 11) በሚል የቀረበው ይህ የጳውሎስ መልእክት ክፍል በአንዳንዶች ላይ ግርታ ሲፈጥር ይስተዋላል፡፡ አባባሉ እግዚአብሔር እኛ እንድንድን በመምረጥ ኪዳን እንደ ገባ ሁሉ ሌሎችም እንዲጠፉ መርጦአል የሚል አንደምታ ያለው ይመስላል፡፡ ነገር ግን ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ አይደለም፡፡ ይልቁንም እግዚአብሔር መላው ሰብዓዊ ዘር የሚድንበትን የደኅንነትን ዕቅድ ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ አዘጋጀ፡፡ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድርስ ዓለምን ወዶአልና” (ዮሐ. 3፡16፣ 1ጢሞቴ. 2፡6፣ 2ጴጥ. 3፡9)፡፡ ምንም እንኳ እግዚአብሔር ያቀረበውን የደኅንነት እቅድ ማን እንደሚቀበልና እንደማይቀበል አስቀድሞ ሊያውቅ ቢችልም ነገር ግን ጉዳዩ በአንድ ሰው የግል ውሳኔ ላይ አስቀድሞ ከመወሰን ጋር ፍጹም ግንኙነት የለውም፡፡ ክርስቶስ ለእኛ ባደረገው ነገር ምክንያት እነሆ ደኅንነት ለመላው ሰብዓዊ ፍጡር ተሰጠ፡፡ ጥያቄው፡ ለዚህ ግብዣ ምላሽ የምንሰጠው እንዴት ነው? የሚል ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር ማንንም ለማዳን ከፍላጎት ውጪ አያስገድድም፡፡ “ምንም እንኳ ሰዎች አምላካዊውን ሕግ ቢተላለፉም ባለመታዘዛቸው ጠንቅ እንዳይጠፉ፤ ይልቁንም ለእነርሱ ቤዛ እና ዋስ በሚሆነው ክርስቶስ ላይ በሚኖራቸው እምነት የእግዚአብሔር የተመረጡ ሕዝቦች ይሆኑ ዘንድ በሰማያዊው ጉባዔ እቅድ ወጣ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ እርሱን ደስ እንደሚያሰኘው እንደ በጎ ፈቃዱ በራሱ በየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ልጆቹ አድርጎ በመቀበል አስቀድሞ ወሰነን፡፡ እነሆ ሰው ሁሉ ይድን ዘንድ አምላካዊው ፈቃድ ነው፡፡ ለአብነት ያህል የሰብዓዊውን ዕዳ ለመክፈል እግዚአብሔር አንድያ ልጁን የኃጢአት መሥዋዕት አድርጎ ሰጥቶአል፡፡ ሰዎች የሚጠፉት በክርስቶስ የሱስ በኩል የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው ለመጠራት በመቃወማቸው ነው፡፡”— Ellen G. White Comments, The SDA Bible Commentary, vol. 6, p. 1114.

ጥቅምት 12
Oct22

ግድግዳውን ማፍረስ


በሕዝቦች መካከል ከሚስተዋሉ ጥልቅ ልዩነቶች አንዳንዶቹ ዘርን፣ ብሔርንና ኃይማኖትን ያማከሉ ናቸው፡፡ ዛሬ ብዛት ባላቸው ሕዝቦች የነዋሪ መታወቂያ ወረቀት ላይ የግለሰቡ ብሔር ወይም ኃይማኖት ተጠቅሶ እንመለከታለን፡፡ ተደጋግሞ እንደሚስተዋለው እነዚህ ልዩነቶች ከሰዎች የዕለት ከዕለት ልዩ መብቶች ወይም ገደቦች ጋር ብርቱ ቁርኝት አላቸው፡፡ ታዲያ በአካባቢው ጦርነት ወይም ግጭቶች ሲቀሰቀሱ እነዚህ የልዩነትና የማንነት መገለጫ ጠቋሚዎች የጭቆና፣ የመድልዎ፣ የሁከትና ብጥብጥ አቀጣጣይ ይሆናሉ፡፡

ጳውሎስ በኤፌ. 2፡11-22 መልእክቱ ለክርስቲያኑ ማኅበረሰብ የተሻለ ጎዳና ያመላክታል፡፡ በክርስቶስ ያለን አንድነት በልዩነቶቻቻችን ላይ ተጽእኖ ማሳደር የሚችለው እንዴት ነው? በየሱስ የመስቀል ላይ ሞት የፈራረሰው ነገር ምን ነበር?





የኤፌሶን ሰዎች በክርስቶስ የእግዚአብሔርን ጸጋ ከመቀበላቸው አስቀድሞ ሕይወታቸው ምን ይመስል እንደ ነበር እንዲያስታውሱ ጳውሎስ ይጋብዛቸዋል፡ ፡ የብሔር፣ የባህልና የኃይማኖት ልዩነቶች በማኅበረሰቡ መሃል ጥላቻና ግጭት አስከትለው ነበር፡፡ ሆኖም ሁላችንም በክርስቶስ አንድ አዳኝና ጌታ ያለን ሕዝቦች መሆናችን በእርግጥም መልካም የምስራች ነው፡፡ እኛ ሁላችን የእግዚአብሔር ሕዝቦች ነን፡፡ “አሁን ግን እናንተ ቀድሞ ርቃችሁ የነበራችሁ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም አማካይነት ቀርባችኋል” (ኤፌ. 2፡13)፡፡

በየሩሳሌም የነበረችው የጥንቷ ቤተ መቅደስ ቅጥር ለአይሁዳውያን ብቻ አገልግሎት እንዲሰጥ ሆኖ በግድግዳ ተለይቶ ነበር፡፡ ይህ ቅጥር ከአይሁድ ዝርያ ውጪ የነበሩ ባዕዳን አልፈው በመሄድ የሥቃይና ቸነፈር ሰለባ እንዳይሆኑ የሚከለክል ጽሑፍ ነበረው፡፡ ጳውሎስ ከወንጌል ጉዞዎቹ መልስ ወደ ቤተ መቅደስ ሲገባ ይህን ሕገ ደንብ ጥሰሃል ተብሎ ተከስሶ ነበር፡፡ ጳውሎስ ተይዞ የታሰረው የኤፌሶኑን ሰው ጥሮፊሞስ (ሐዋ. 21፡29) የአይሁድ ቅጥር ወደ ሆነው ቤተ መቅደስ አስገብቶአል በሚል ነበር፡ ፡ ጳውሎስ በዚህ መልእክቱ፡ ክርስቶስ “ሁለቱን አንድ ያደረገ፣ የሚለያየውንም የጥል ግድግዳ ያፈረሰ ሰላማችን እርሱ ነውና” (ኤፌ. 2፡14) ሲል ይሞግታል፡፡ በክርስቶስ ያሉ አማኞች የአብርሃም ዝርያዎች እንደመሆናቸው የልብ መገረዝን ይቀበላሉ፡፡ እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠው አካላዊው ግርዘት አማኞች በክርስቶስ የሚቀበሉትን መንፈሳዊ መገረዝ ያመላክት ነበር (ዘዳ. 10፡16)፡፡ “በእርሱ ሆናችሁ በእጁ ባልተደረገ መገረዝ ተገረዛችሁ፤ በክርስቶስም መገረዝ የሥጋን ኃጢአታዊ ባሕርይ አስወገዳችሁ” (ቆለ. 2፡11)፡፡

ጥቅሶቹን በድጋሚ አንብቡ፡ (ኤፌ. 2፡11-22)፡፡ ይህን የጳውሎስ መልእክት በቤተ ክርስቲያናችን በተጨባጭ እያስተዋልን ያለንበት ሁናቴ ምን ይመስላል? አሁን ድረስ ያሉ ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው?

ጥቅምት 13
Oct23

ኅብረት በአንድ አካል ውስጥ


ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት ለኤፌሶን ሰዎች በጻፈው መልእክት ጭብጥ ላይ የተመረኮዘውን እውነታ አቅርቦላቸዋል፡፡ በአይሁዳውያን እና በአሕዛብ፣ የተለያየ ባህል በነበራቸው ሕዝቦች እና ዝርያ ታሪካዊ ዳራ መካከል የነበረው ኅብረት መሰረተ ቢስ አፈ ታሪክ ሳይሆን ለተቀበልነው ጥሪ የሚገባ ኑሮ እንድንኖር የቀረበልን ተማጽኖ ነው (ኤፌ. 4፡1)፡፡

በኤፌ. 4፡1-3 መሰረት ክርስቲያኖች በክርስቶስ ለቀረበላቸው ጥሪ ያለ ነቀፌታ መራመድ የሚችሉት እንዴት ነው?





በክርስቲያኖች ህይወት የሚተገበሩት የእነዚህ በጎ ምግባሮችና ጸጋዎች ተጨባጭ ውጤት “በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ” (ኤፌ. 4፡3) እንድንተጋ ይረዱናል፡፡ እነዚህ ሁሉ መለያ ባህሪያት የተመሰረቱት በፍቅር ላይ ነው (1ቆሮ. 13፡ 1-7)፡፡ ፍቅርን በንቃትና በተጨባጭ መለማመድ በክርስቲያን ብሎም በሌሎች ወንድም እህቶች መካከል የሚኖር ግንኙነት ተጠብቆ እንዲቆይ ይረዳል፤ ሰላምና ኅብረት እንዲነቃቃም ያደርጋል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚኖር ኅብረት ከወትሮ በተለየ የእግዚአብሔርን ፍቅር በመግለጽ ለሌሎች ምስክር ይሆናል፡፡ በተለይ ጠብ፣ ሁከት፣ መከፋፈልና ጦርነት በሚነሳበት ወቅት ቤተ ክርስቲያን ምስክር እንድትሆን ተጠርታለች፡፡ ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኤፌ. 4፡4-6፡፡ በእነዚህ ሦስት ቁጥሮች ወሳኝ የሆነው ጭብጥ ምንድን ነው?





ጳውሎስ በዚህ ምዕራፍ የመጀሪያ ቁጥሮች ላይ በቤተ ክርስቲያን ኅብረት ላይ ያለውን ጥልቅ ፍላጎት ሲገልጽ ይስተዋላል፡፡ በኅብረት ዙሪያ ልባዊ ምክር በመስጠት መልእክቱን የሚጀምረው ጳውሎስ (ኤፌ. 4፡1-3) አማኞችን የሚያስተሳስሩ ሰባት መሰረታዊ ነጥቦችን በማስከተል ጽሑፉን ይቀጥላል (ኤፌ. 4፡4-6)፡፡ ከሞላ ጎደል በአማኞች ውስጥ ያለው ይሄው ኅብረት (ኤፌ. 4፡4-6) ምዕመናን ያለማሰለስ የሚያሳድጉትና የሚንከባከቡት (ኤፌ. 4፡1-3) የተቻላቸውን ብርቱ ጥረት የሚያደርጉበትና የሚረባረቡበት የመጨረሻ ግብ ነው (ኤፌ. 4፡13)፡፡ “ሐዋርያው ለወንድሞቹ ያቀረበላቸውን የእውነት ኃይል በሕይወታቸው ገልጠው እንዲያሳዩ አደፋፍሯቸዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በታማኝነትና በእርጋታ፣ በትዕግሥትና በፍቅር የክርስቶስን ጸባይና የማዳኑን በረከቶች ማሳየት ነበረባቸው፡፡ አንድ አካል፣ አንድ መንፈስ፣ አንድ ጌታ፣ አንድ እምነት አለ፡፡ አማኞች እንደ ክርስቶስ አካልነታቸው በተመሳሳይ መንፈስና ተስፋ ብሩህ ኃይል የተሞሉ ናቸው፡፡ “በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚከሰቱ መከፋፈሎች የክርስቶስን ኃይማኖት በዓለም ፊት ውርደት ላይ በመጣል የእውነት ጠላቶች አካሄዳቸውን ተገቢ አስመስለው ለማቅረብ ዕድል ይፈጥርላቸዋል፡፡ የጳውሎስ ትእዛዞችና መመሪያዎች በእርሱ ዘመን ለነበረችው ቤተ ክርስቲያን ብቻ አልተጻፉም፡፡ ይልቁንም መልእክቶቹ ለእኛ ዘመን እንዲደርሱ የእግዚአብሔር እቅድ ነበር፡፡ በሰላም ማሰሪያ ውስጥ ኅብረታችንን ለመጠበቅ ምን እያደረግን ነው?”—Ellen G. White, Testimonies for the Church, vol. 5, p. 239. በተጠሩበት ለመራመድዎ እግጠኛ ለመሆን ዛሬ ምርጫዎ ምን ሊሆን ይገባል?

ጥቅምት 14
Oct24

የቤተ ክርስቲያን መሪዎችና ኅብረት


“ነገር ግን ክርስቶስ በወሰነው መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጥቶናል” (ኤፌ. 4፡7)፡፡ መዳን ለተቀበሉት ሁሉ የተሰጠ ስጦታ ቢሆንም አንዳንድ መንፈሳዊ ስጦታዎች ለተለየ ዓላማ ለተወሰኑ ሰዎች ይሰጣሉ፡፡ ጥቅሱን ያንብቡ፡ ኤፌ. 4፡11፡፡ እግዚአብሔር ምን ዓይነት የአመራር ስጦታ ለቤተ ክርስቲያን ይሰጣል?



በኤፌ. 4፡12 መሰረት እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን የተለየ የአመራር ስጦታ ሲሰጥ ዓላማው ምንድን ነው? እነዚህ ስጦታዎች እርስ በርሳቸው እንዴት ይዛመዳሉ?



ሁሉም ክርስቲያኖች የወንጌል ሠራተኞችና የእግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸው፡፡ በማቴ. 28፡19-20 ክርስቲያኖች ለአገልግሎት ወጥተው ሕዝቦችን ደቀ መዝሙሮቹ እንዲያደርጉ፣ እንዲያጠምቁ፣ እንዲያስተምሩ ክርስቶስ ተልዕኮ ሰጥቶአቸዋል፡፡ የወንጌል ሥራ የተሰጠው እንደ መጋቢዎችና ወንጌላውያን ላሉ ጥቂት ዕድለኞች ብቻ ሳይሆን የክርስቶስን ስም ለተሸከሙ ሁሉ ነው፡፡ ማንም አማኝ ወንጌልን ከማሰራጨት ራሱን ነፃ ሊያደርግ እንደማይችል ሁሉ--የትኛውም የቤተ ክርስቲያን መሪ ለእርሱ ብቻ የተነጠለ አገልግሎት እንዳለው መናገር አይችልም፡፡ የሥነ አመራር መንፈሳዊ ስጦታዎች ቤተ ክርስቲያንን የማነጽ የተለየ ሥራ ይሠራሉ፡፡ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በአማኞች መካከል ኅብረትን ለማጠናከርና ለማደርጀት አጥብቀው ይፈለጋሉ፡፡ የጳውሎስ ሥነ አመራር ስጦታ ዝርዝሮች የእግዚአብሔር ሕዝቦች ወደ ጠፉት እንዲደርሱ የሚያስችል ሚና እንዳላቸውም ይነግሩናል፡፡ የክርስቶስን አካል የማነጹ አገልግሎት የሰመረና ስኬታማ እንዲሆን እርዳታ መስጠት በተለይ በዚያው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተጠሩ ጥቂቶች ኃላፊነት ነው፡፡ “ይህም የሚሆነው ሁላችንም የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኘው አንድነት በመምጣትና ሙሉ ሰው በመሆን፣ በክርስቶስ ወዳለው ፍጹምነት ደረጃ እስከምንደርስ ነው፡፡” (ኤፌ. 4፡13)፡፡ አገልግሎታችን የክርስቶስን ምሳሌ በተከተለ ሥነ አመራር መራመድ ይኖርበታል፡፡ የሱስ ሌሎችን ሊያገለግል እንጂ ሊገለገል እንዳልመጣ ሁሉ (ማቴ. 20፡ 25-28) እኛም የእርሱን ፈለግ በመከተል ልንወጣ ይገባል፡፡

ሰዎች በገዛ ራሳቸው ሀሳብ የመምራትና ለማንም ተጠያቂ ያለመሆን ጠንካራ ዝንባሌ አላቸው፡፡ የምዕራቡ ማኅበረሰብ ደግሞ በተለይ የዚህ ወረርሽኝ ተጠቂ ነው፡፡ ሆኖም በዚህ ምድር አንድም ክርስቲያን ብቻውን አለመሆኑን የሚያስታውሰን ጳውሎስ፤ በጋራ ጉዞአችን እርስ በርስ እንድንበረታታ እገዛ የሚያደርጉልንን መንፈሳዊ መሪዎች በአማኝ ማኅበረሰብ ውስጥ እንደምንፈጥር ይነግረናል፡፡ እኛ ሁላችን፣ በአንድነት የክርስቶስ አካል ክፍል ነን፡፡

ምን ዓይነት መንፈሳዊ ስጦታዎች አሎት? ለአጥቢያ ቤተ ክርስቲያንዎ ኅብረት እንዴት እየተጠቀሙባቸው ይገኛሉ?

ጥቅምት 15
Oct25

ክርስቶስን ያማከለው ሰብዓዊ ግንኙነት


ክርስትና ግንኙነቶችን መሰረት ያደረገ ኃይማኖት ሲሆን፤ ይኸው ግንኙነት ደግሞ ከእግዚአብሔር እና እርስ በርስ ከሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት ያማከለ ነው፡፡ አንድ ሰው ከሌሎች ጋር የረባ ግንኙነት ሳይኖረው ከእግዚአብሔር ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳለው ቢያስብ ትርጉም የለውም፡፡ ክርስትና አንዳች በሌለበት ወና ውስጥ መኖር አይችልም፡፡ ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በጻፈው መልእክቱ የሚያነሳቸው የኅብረት መርኅዎች ከሌሎች ጋር ለሚኖሩን ግንኙነቶች ገጣሚ ናቸው፡፡ ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኤፌ. 5፡15-21፡፡ በቁ. 21 ጳውሎስ ምን እያለን ነው? በመታዘዝና በኅብረት መሃል ያለው ግንኙነት ምንድን ነው?





ጳውሎስ አንዱ ለሌላው የሚሸነፍና እሺ ባይ እንዲሆን የሰጠው ልባዊ ምክር “በመንፈስ ተሞሉ” (ኤፌ. 5፡18) ከሚለው ሀረግ ጋር ትስስር አለው፡፡ ሰዎች እርስ በርሳቸው የሚያሳዩት ትህትና በመንፈስ የመሞላት አንዱ መገለጫ ነው፡፡ ጉዳዩ ለሰዎች ከሚኖረን ቀናነትና በጎ አመለካከት ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ በእርግጥ ይህ የሰብዓዊው ተፈጥሮ ባህሪ ሳይሆን፤ በልባችን የሚኖረው መንፈስ ውጤት ነው፡፡ ይህ በክርስቶስ የምናገኘው የአንድነት ሰንሰለት ከዚያው ከአንድ ባሕር የሚቀዳው መንፈስ ስጦታ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር--ውስጣዊ ጥሩነት የሆነው ትህትናና መታዘዝ ለክርስቶስ ብሎም ለመሥዋዕትነቱ ያለንን አክብሮት ይገልጻል፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኤፌ. 5፡22-6፣ 9፡፡ ይህ በቤትም ሆነ በሥራ ቦታ በክርስቶስ አማኙ የሚስተዋለው ትህትና በሰብዓዊ ግንኙነታችን ላይ ምን ዓይነት ተጽእኖ ይኖረዋል?





የቤተ ክርስቲያን ኅብረት በመጠኑም ቢሆን በቤተሰብ ላይ ባለ አንድነት መተማመን ያደርጋል፡፡ በባልና ሚስት መሃል ሊኖር የሚገባ አንድነት፣ ፍቅር እና መከባበር ክርስቶስ ራሱን አሳልፎ እስከ መስጠት ቤተ ክርስቲያንን የመውደዱን ምሳሌ ሊከተል እንደሚገባ ሐዋርያው ጳውሎስ አጽንኦት ይሰጣል፡፡ ስለዚህ በክርስቶስ የተስተዋለው አክብሮት በቤት ውስጥ፣ በቤተ ክርስቲያን፣ በባሎች እንዲሁም በሚስቶች መሃል መታየቱ የግድ ይሆናል፡፡ ይህ የክርስቶስ ባህሪ የሆነው ጥሩነት በልጆች እና በወላጆች፣ በሠራተኞች እና በአለቆች መካከል በጉልህ ሊታይ ይገባል፡፡ በቤታችን ሊሰፍን የሚገባው ለዛ ያለው ስምምነትና ሰላም በቤተ ክርስቲያን ህይወትም ሊሰፍን የተገባ ነው፡፡ ለቤተሰብዎ አባል ወይም ለሥራ ባልደረባዎ እንዴት ዓይነት አቀራረብ ሊኖርዎ እንደሚገባ አስመልክቶ ለዛሬ ከቀረቡት ጥቅሶች ምን ዓይነት መርኅዎችን መውሰድ ይችላሉ?

ጥቅምት 16
Oct26


ተጨማሪ ሀሳብ


፡ Ellen G. White, “The Spirit of Unity,” pp. 179–188, in Testimonies for the Church, vol. 9. “ክርስቶስ በዜግነት፣ በማዕረግ ወይም በኃይማኖታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የማበላለጥ እውቅና አልሰጠም፡፡ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን መላውን የሰማይ ስጦታ ከተቀረው ዓለም የእግዚአብሔር ቤተሰብ በመነጠል ለብሔራዊ ጥቅማቸው ብቻ ለማዋል ተመኝተው ነበር፡፡ ክርስቶስ ግን እያንዳንዱን የመለያየት ግድግዳ ሊያፈራርስ መጣ፡፡ የአምላካዊው ምህረት ስጦታና ፍቅር ወደ ሳንባችን እንደምንስበው አየር፣ ማለዳ እንደምትፈነጥቀው የጸሐይ ጮራ ወይም ምድሪቱን እንደሚያረሰርሰው ካፊያ ነፃ መሆኑን ሊያሳየን መጣ፡፡ “የክርስቶስ ሕይወት አይሁድ እና አሕዛብ፣ ነፃ ሰዎችና ግዞተኞች በጋራ ወንድማማችነት የተቆራኙበትንና በእግዚአብሔር ፊት እኩል የሚሆኑበትን ከኅብረተሰባዊ ክፍፍል የጸዳ ኃይማኖት መሰረተ፡፡ የትኛውም ሕገ ደንብን ወይም መመሪያን የተከተለ ጥያቄ በእንቅስቃሴዎቹ ላይ ተጽእኖ አላሳደረም፡፡ በጎረቤቶቹና በሩቅ እንግዶች፣ በጓደኞቹና በጠላቶቹ መሃል አንዳችም ልዩነት አላደረገም፡፡ ወደ ልቡ የሚሳበው የሕይወትን ውሃ የተጠማው ነፍስ ነበር፡፡”—Ellen G. White, Testimonies for the Church, vol. 9, pp. 190, 191.


የመወያያ ጥያቄዎች



፡ 1. የሚከተለውን ሃሳብ ያሰላስሉ፡ “መላው የእግዚአብሔር ልጆች እውነትን አጥብቀው እንዲይዙ የሚያወሳው አምላካዊው እቅድ ግልጽና ቀላል በሆነ አቀራረብ በኤፌሶን አራተኛው ምዕራፍ ላይ ተገልጾአል፡፡ የቤተ ከርስቲያኑ ኅብረት ተጠብቆ የሚኖርበትና አባላት ጤናማውን ኃይማኖታዊ ተሞክሮ ለዓለም እንዲገልጹ የሚያስችለው ዘዴ ግልጽ በሆነ ቋንቋ በዚህ ስፍራ ቀርቦአል፡፡”—Ellen G. White Comments, The SDA Bible Commentary, vol. 6, p. 1117. በኤፌ. 4 የቤተ ክርስቲያን ኅብረትን የሚጠቁሙ ምን ዓይነት ነጥቦችን ይመለከታሉ? ኅብረቱ የሰመረ እንዲሆን በምን መልኩ የበኩልዎን እገዛ ማበርከት ይችላሉ? 2. ትህትና እና የአንተ ትብስ፣ አንቺ ትብሽ አስፈላጊነት የቤተ ክርስቲያን ኅብረት ጥያቄ አስኳል ነው፡፡ ለመሆኑ ያለ እነዚህ ባህሪያት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንድነት ሊኖር የሚችለው እንዴት ነው? የምንታበይ፣ በአመለካከታችንና በአቋማችን ከእኔ በላይ ላሳር የምንል ከሆንና ሌሎችን ለማድመጥ ፈቃደኞች ካልሆን ኅብረት የማምጣት ዕድላችን የመነመነ ነው፡፡ ለመሆኑ ይህን ትህትና እና ቅንነት መማር የምንችለው እንዴት ነው? 3. ሁሌም በሁሉም ነገር ባንስማማም እንኳ አንድነት ሊኖረን የሚችለው እንዴት ነው?

ማጠቃለያ፡ ጳውሎስ ለኤፌሶች ሰዎች በላከው በዚህ ደብዳቤው “በክርስቶስ መሆን” ምን ማለት እንደሆነ አስመልክቶ አያሌ ምክረ ሀሳቦችን ለሕዝበ ክርስቲያኑ ይለግሳል፡ ፡ በየሱስ የሚገኘው ደኅንነት ህይወትን በተጨባጭ ይለውጣል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ያሉ ወንድም እህቶችን ጨምሮ ሁሉም ዓይነት ሰብዓዊ ግንኙነቶቻችን በሕይወታችን መለወጥ የሚያገኙት በክርስቶስ ኃይል ነው፡፡ በመካከላችን ኅብረት ይኖር ዘንድ ይህ መለወጣችን እጅግ ወሳኝ ነው፡፡