ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ሐዋ. 1:12– 14. ሐዋ. 2:5–13 ራእ. 14:12 ፣ሐዋ. 2:42–47. ሐዋ. 4:32–37. ሐዋ. 5:1–11፣ 2ቆሮ. 9:8–15፡፡
መታሰቢያ ጥቅስ :--“እነርሱም በሐዋርያት ትምህርት በኅብረት፣ እንጀራውንም በመቁረስና በጸሎት ይተጉ ነበር” (ሐዋ. 2፡42)፡፡
የ
ቤተ ክርስቲያን ኅብረት እውነት የሆነውን የሱስ የማካፈል መንፈሳዊ ውጤት
ነው፡፡ “መንገዱ እኔ ነኝ፣ እውነትና ሕይወትም እኔው ነኝ፣ በእኔ በኩል ካልሆነ
በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም፡፡” (ዮሐ. 14፡6)፡፡ ጠንካራ አንድነት ያላቸው
ኅብረቶች በጋራ መንፈሳዊ ጉዞ ተሞክሮ የተቀረጹ ናቸው፡፡ የሚለራይት እንቅስቃሴ
ዘመኖቹ ቀደምት አድቬንቲስቶች የእንዲህ ያለው ተሞክሮ ባለቤቶች ነበሩ፡፡ እነዚህ
ወገኖች በጎርጎሮሳውያኑ ቀመር 1844 ላይ ደርሶባቸው ለነበረው ተስፋ አስቆራጭ
ክስተት ትክክለኛውን ማብራሪያ እስኪያገኙ የጋራ ተሞክሮአቸው ልቦቻቸውን በአንድ
ማስተሳሰር ችለው ነበር፡፡ ይህ ተሞክሮ ለሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን
ውልደት እንዲሁም ከዳግም ምጽአቱ አስቀድሞ ስላለው ፍርድ እና ተዛማጅ እውነቶች
መንስዔ ለመሆን በቃ፡፡
የሱስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ በተስተዋለው የደቀ መዛሙርቱ ተሞክሮ የተለያየ
የኋላ ታሪክ በነበራቸው አማኞች መካከል ኅብረትና ስምምነት በመፍጠሩ ረገድ-የእግዚአብሔር ቃል፣ ጸሎት እና የአማኞች ኅብረት ብርቱ ኃይል እንዳለው ማሳያ
ምስክር ነበር፡፡ ይህ የቀደመ ተሞክሮ እነሆ ዛሬም መተግበር ይችላል፡፡
“የክርስትና ኅብረት ከፍ ላሉ ጉባዔዎች እጅግ አስፈላጊ ቅመም በመሆኑ የአምልኮአቸው
አካል እንዲሆን አጥብቄ ላበረታታ እወዳለሁ… አማኙ ከሌሎች አማኞችና ከጌታ የሱስ
ክርስቶስ ጋር መንፈሳዊ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችለው ከዚህ ውጪ ሌላ ምንም
ምትክ የለውም… የሱስ ክርስቶስ ሁሌም ቢሆን በመጀመሪያ አንድን ነፍስ ወደ ራሱ
ያመጣል፡፡ በመቀጠል አካሉ በሆነው ቤተ ክርስቲያን አማካይነት ከሌሎች አማኞች
ጋር ኅብረት እንዲፈጥር ያደርጋል፡፡”—Robert G. Rayburn, O Come, Let Us
Worship (Grand Rapids: Baker Book House, 1980), p. 91.
የሱስ በመስቀል ለኃጢአታችን ቤዛ ከመሆኑ አስቀድሞ በነበሩት የመጨረሻዎቹ ሰዓታት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በነበረው ቆይታ ብቻቸውን እንደማይተዋቸው ቃል ገባላቸው፡ ፡ የአገልግሎታቸው አካል የሆነው ሌላው አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ ይላክላቸዋል፡ ፡ መንፈስ የሱስ ነግሮአቸውና አድርጓቸው የነበሩ አያሌ ነገሮችን እንዲያስታውሱና (ዮሐ. 14፡26) ተጨማሪ አዳዲስ እውነቶችን እንዲረዱ ይመራቸዋል (ዮሐ. 16፡13)፡ ፡ የሱስ ወደ ሰማይ ሊያርግ በነረበት ዕለትም እንዲሁ አስቀድሞ የሰጣቸውን ተስፋ አድሶ ነበር፡፡ “‘እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ… መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኀይልን ትቀበላላችሁ” (ሐዋ. 1፡ 5፣8)፡፡ ደቀ መዛሙርት በየሩሳሌም፣ በይሁዳ፣ በሰማርያ ብሎም እስከ ምድር ጫፍ ምስክር ለመሆን የሚያስችላቸው የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ይሰጣቸዋል (ሐዋ. 1፡8)፡፡ ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሐዋ. 1፡12-14፡፡ በእነዚህ አሥር ቀናት ውስጥ ደቀ መዛሙርት ምን አደረጉ?
እነዚህ አሥር ቀናት እጅግ በተጋጋለ ስሜት ብርቱ መንፈሳዊ ዝግጅት የተደረገባቸው
ጊዜያቶች እንደነበሩ ለመገመት እንችላለን፡፡ ደቀ መዛሙርት በአንድነት ተሰባስበው
የቀደሙትን የየሱስ ተግባራት፣ አስተምህሮዎችና ታምራቶች እያሰላሰሉ “በአንድ ልብ
ሆነው ያለማቋረጥ ተግተው ይጸልዩ ነበር” (ሐዋ. 1፡14)፡፡
“ደቀ መዛሙርት በእውነተኛ ንስሐ ልቦቻቸውን ትሑት አድርገውና አለማመናቸውን
ተናዝዘው የሱስ የሰጣቸውን ተስፋ ፍጻሜ እየተጠባበቁ ነበር፡፡ ክርስቶስ ከመሞቱ
አስቀድሞ ለእነርሱ የተናገራቸውን ቃላት ማስታወስ ሲጀምሩ ፍቺያቸውን ይበልጥ
በሙላት አስተዋሉ፡፡ ተዘንግተዋቸው የነበሩ እውነቶች ዳግመኛ በአእምሮአቸው
አንቃጨሉ፡፡ አንዱ አስታውሶ ሲናገር ሌላውም ያንኑ ይደግም ነበር፡፡ በአዳኙ ላይ ስለ
ነበራቸው የተሳሳተ አስተሳሰብ ራሳቸውን ተቹ፡፡ የአስደናቂ ሕይወቱ ትዕይንት እንደ
ወታደራዊ ሰልፍ በፈርጅ በፈርጅ ሆኖ በፊታቸው አለፈ፡፡ ውብ የሆነውን የክርስቶስ
ጸባይ ብቻ በሕይወታቸው መመስከር ቢችሉ--ንጹህና ቅዱስ የሆነውን ሕይወቱን
እያሰላሰሉ አምልኮ ሲያደርጉ፣ የቱንም ዓይነት ልፋት ወይም መሥዋዕትነት የገዘፈ
ሊሆንባቸው እንደማይችል ተሰማቸው፡፡ ያለፉትን ሦስት ዓመታት ዳግም ሊያገኟቸው
ቢችሉ እንዴት በተለየ ይመላለሱባቸው እንደነበርና ለጌታቸው ያላቸው ፍቅር ምን
ያህል ጥልቅ እንደሆነ ሊያሳዩ በጣሩ ነበር፡፡ ከአንደበቶቻቸው በወጡ የስንፍና ቃላት
ወይም ባሳዩት ያለማመን ድርጊት ምን ያህል እንደ ጎዱት እያሰቡ ከልባቸው ተጸጸቱ፡፡
ሆኖም ይቅር መባላቸውን ሲያስቡ መጽናናት አገኙ፡፡ ከዚህ በኋላ በተቻላቸው እርሱን
በዓለም ፊት በጀግንነት እየመሰከሩ ሥርየት ያመጣላቸውን አዳኝ ለመካስ ቁርጥ ሃሳብ
አደረጉ… ልዩነቶቻቸውን በሙሉ በማስወገድና ምኞቶቻቸውን በላቀው ነገር ላይ
በማዋል በክርስትና ኅብረት ተቀራረቡ፡፡”—Ellen G. White, The Acts of the
Apostles, pp. 36, 37.
ከእምነትዎ ጋር በተያያዘ ምን ዓይነት ነገሮችን ማድረግ ይችላሉ? የወደፊቱን
በተሻለ ተስፋ የተሞላ ማድረግ ይቻል ዘንድ ባለፈው ከተጸጸቱባቸው ነገሮች ምን
መማር ይችላሉ?
የየሱስን ዕርገት ተከትሎ ገቢራዊ የሆኑት መንፈሳዊ ዝግጅት የተደረገባቸው ቀናት
በበዓለ ኀምሳው ትዕይንቶች ድምዳሜ አገኙ፡፡ የመጀመሪያው ጥቅስ እንደሚነግረን
መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ ከመውረዱ አስቀድሞ በዚያው ዕለት “ሁሉም
በአንድነት በአንድ ስፍራ ተሰብስበው ነበር” (ሐዋ. 2፡1)፡፡
በብሉይ ኪዳን እያንዳንዱ እስራኤላዊ ተባዕት እንዲካፈልባቸው ከሚጠየቁ ሦስት
አበይት በዓላት መካከል በዓለ ኀምሳ ሁለተኛውን ይይዛል፡፡ በግሪክኛ ጴንጤቆስጤ
በሚል ስያሜ የሚታወቀው ይህ በዓል የሚውለው ፋሲካ በተከበረ በኀምሳኛው ቀን
ላይ ነበር፡፡ በበዓሉ ላይ ዕብራውያን በበጋው ወቅት ከሚያፈሩት ፍራፍሬዎች በኩር
የሆኑትን በምስጋና ስጦታ ለእግዚአብሔር ያቀርባሉ፡፡
በተጨማሪ በየሱስ ዘመን በነበረው የበዓለ ኀምሳ አከባበር አሥርቱ ትእዛዛት በሲና
ተራራ ለሙሴ የተሰጡበትን በመታሰቢያነት ያካትት ነበር (ዘፀ. 19፡1)፡፡ በመሆኑም
የእግዚአብሔር ሕግ አስፈላጊነት የክርስትና መልእክት ጥቅል አካል ሆኖ መቀጠሉን
መመልከት እንችላለን፡፡ የሱስን አስመልክቶ የእግዚአብሔርን ሕግ ለጣሰ እያንዳንዱ
ተነሳሒ (ንስሐ የሚገባ) የእርሱ ሞት አምላካዊውን ይቅርታ ያሰጣል፡፡ ከዚህ አኳያ
ስለ መጨረሻዎቹ ቀናት ከሚነግሩን ወሳኝ ጥቅሶች አንዱ ስለ ሕጉ እና ስለ ወንጌል
የሚከተለውን ቢል እምብዛም ሊያስገርም አይችልም፡ “የእግዚአብሔርን ትእዛዛት
የሚጠብቁና ለኢየሱስም ታማኝ ሆነው በትዕግሥት የሚጸኑ ቅዱሳን የሚታወቁት
በዚህ ነው” (ራእ. 14፡22)፡፡
ሙሴ በሲና ተራራ አሥርቱን ትእዛዛት በተቀበለ ጊዜ (ዘፀ. 19፡16-25፣ ዕብ. 12፡
18) ከሆነው በተመሳሳይ በጴንጤቆጤ ወቅትም በእጅጉ ያልተለመዱ ድንቅ ክስተቶች
ገቢራዊ ሆነዋል፡፡ “ድንገትም እንደ ብርቱ ዐውሎ ነፋስ ያለ ድምፅ ከሰማይ መጥቶ
ተቀምጠው የነበሩበትን ቤት እንዳለ ሞላው፡፡ የእሳት ምላሶች የሚመስሉም
ታዩአቸው፤ ተከፋፍለውም በእያንዳንዳቸው ላይ ዐረፉ፡፡ ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ
ተሞሉ፤ መንፈስም እንዲናገሩ በሰጣቸው መጠን በሌሎች ቋንቋዎች ይናገሩ ጀመር፡፡
” ሐዋ. 2፡2-4)፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሐዋ. 2፡5-13፡፡ የዚህ አስደናቂ ክስተት አንደምታው ምንድን ነው?
በዓለ ኀምሳ ወይም ጴንጤቆስጤ ስለ ጌታ ችሮታና በጎነት ምስጋና የሚቀርብበት
የደስታ በዓል ነው፡፡ ምናልባት ያልፈላ የወይን ጠጅ ጠጥተዋል የሚል ክስ በሐዋርያቱ
ላይ የቀረበበት ምክንያት ይኸው ሊሆን ይችላል (ሐዋ. 2፡13-15)፡፡ ሐዋርያት በተለያዩ
ቋንቋዎች በመናገርና በመደመጥ ባሳዩት ታምራት የእግዚአብሔር ኃይል በተለየ
መታየት ቻለ፡፡ በዘመኑ ልዕለ ኃያል በነበረው ሮም ስር ይገዙ ከነበሩ ልዩ ልዩ አገራት
በዓሉን ለማክበር በየሩሳሌም የተሰባሰቡ አይሁዳውያን ስለ መሲሁ የሱስ የተሰጠውን
መልእክት በገዛ ቋንቋቸው ለመስማት ቻሉ፡፡
በባቤል ግንብ ከተጀመረው የቋንቋ መደበላለቅ አንስቶ ሰብዓዊው ዘር በተለያዩ
ብሔሮች ተከፋፍሎ መኖሩን ቢቀጥልም፤ ነገር ግን ለጌታ ችሮታና በጎነት ምስጋና
በሚቀርብበት በጴጥጤቆስጤ በዓል ከወትሮው እጅግ በተለየና ባልተለመደ መልኩ
የቀደመውን ሰብዓዊ መበታተን ዳግም ማስተሳሰር ተቻለ፡፡ የጸጋው ታምራት
ሰብዓዊውን ቤተሰብ ዳግም ማስተሳሰር ጀመረ፡፡ በዓለማቀፍ ደረጃ የተስተዋለው
የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ኅብረት በባቤል ጠፍቶ የነበረውን ዳግም በማደስ
የመንግሥቱን ተፈጥሮ የሚመሰክር ሆነ፡፡
ጴጥሮስ ለሕዝቡ ያቀረበውን ስብከትና በንስሐ እንዲመለሱ የመንገሩን ተማጽኖ ተከትሎ በምላሹ ሦስት ሺ ያህል ሰዎች የሱስን እንደ መሲህ ተቀበሉ፡፡ እግዚአብሔር ለእስራኤል የገባው የብሉይ ኪዳን ተስፋ ፍጻሜ መሆኑንም አመኑ፡፡ በእነዚያ ሁሉ ሰዎች ልብ ውስጥ ጌታ እየሠራ ነበር፡፡ በተለያዩ ሩቅ አገራት ይኖሩ የነበሩ ብዙዎች የየሱስን ዝና ሰምተው ስለ ነበር እርሱን ለማየት ተስፋ በማድረግ ወደ የሩሳሌም ተጉዘዋል፡፡ ምናልባት አንዳንዶች የሱስን ሊያዩና የእግዚአብሔርን አዳኝነት መልእክት ሊሰሙ ቢችሉም ነገር ግን ተከታዮቹ ለመሆን አልወሰኑም ነበር፡፡ በጴንጤቆስጤ በዓል ላይ እግዚአብሔር በደቀ መዛሙርቱ ሕይወት በታምር ጣልቃ ገብቶ ለየሱስ ትንሣኤ በምስክርነት ተጠቀመባቸው፡፡ አሁን ሰዎች በየሱስ ስም የኃጢአት ይቅርታ ማግኘት እንደሚችሉ ያውቃሉ (ሐዋ. 2፡38)፡፡ ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሐዋ. 2፡42-47፡፡ እነዚህ የመጀመሪያዎቹ የየሱስ ተከታይ አማኝ ማኅበረሰብ ክርስቲያኖች ምን ዓይነት እንቅስቃሴ ነበራቸው? ለመሆኑ ይህን አስደናቂ ኅብረት ምን ፈጠረው?
ይህ የሐዋርያው አስተምህሮ የተቀሰመበትና አዲሱ አማኝ ማኅበረሰብ ተካፋይ
የሆነበት የመጀመሪያ እንቅስቃሴ በዓይነቱ የተለየ ነበር፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳዊው መመሪያ
በአዳዲስ አማኞች መሃል የተዋጣለት መንፈሳዊ ዕድገት ለማምጣት የሚያስችል ቁልፍ
መሣሪያ ነው፡፡ የሱስ “ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው” (ማቴ. 28፡
20) ሲል ለደቀ መዛሙርቱ ተልዕኮ ሰጥቶአል፡፡ ይህ አዲስ ማኅበረሰብ በቂ ጊዜ ወስዶ
በደቀ መዛሙርቱ አማካይነት ስለ የሱስ ይማር ነበር፡፡ እነዚህ ወገኖች የቀደሙትን
የዕብራውያን መልእክቶች ፍጻሜ በሚያመላክቱት የሐዋርያት ጽሑፎች በቀረበው
መሰረት ስለ የሱስ ህይወት፣ አገልግሎት፣ አስተምህሮ፣ ታምራቶች፣ ተምሳሌታዊ
ንግግሮችና ስብከቶች ለመስማት እንደቻሉ ይታመናል፡፡
በተጨማሪ በየዕለቱ ተገናኝተው እየጸለዩና እንጀራ እየቆረሱ በደስታ ይመገቡ ነበር፡
፡ በእርግጥ “እንጀራ እየቆረሱ” የተሰኘው አባባል ቀጥተኛ ትስስር ከጌታ ራት ጋር
ይሁን ወይም በአንድ ላይ ማዕድ ከመቅረብ--ብዙም ግልጽ አይደለም (ሐዋ. 2፡46)፡
፡ በወቅቱ የአምልኮአቸው ማዕከል በመሆን አገልግሎት ትሰጥ በነበረችው በየሩሳሌሟ
ቤተ መቅደስ እና በቤታቸው ያደርጉ የነበረው መደበኛ አብሮነት የተጠቀሰውን
በዓይነቱ አዲስ አማኝ ማኅበረሰብ አንድነት በትክክል ይገልጻል፡፡ የጠለቀ ወዳጅነት
ተጋርተዋል፡፡ በአንድ ላይ ይጸልዩና ይመገቡ ነበር፡፡ ጸሎት የክርስትና ኅብረት በጣም
አስፈላጊ አላባ እንደመሆኑ፤ የመንፈሳዊ ሕይወት ዕድገት ወሳኝ መሰረታዊ ክፍል ነው፡
፡ ይህ አዲስ ማኅበረሰብ በቂ የአምልኮ ጊዜ ይወስድ ነበር፡፡ እያንዳንዱ እንቅስቃሴ
በጽናት ገቢራዊ ይሆን እንደ ነበር ከመልእክቱ እናነባለን፡፡
ይህ በጽናት የተሞላ ኅብረት በየሩሳሌም ከነበሩ ሌሎች ወንድሞች ጋር መልካም
ግንኙነት እንዲፈጠር መነቃቃት አመጣ፡፡ “በሕዝቡ ሁሉ ፊት ሞገስ ነበራቸው” (ሐዋ.
2፡47) በሚል የተገለጹት አዳዲሶቹ አማኞች በሕይወታቸው የታየው የመንፈስ ቅዱስ
ሥራ ዙሪያቸውን በነበሩ ወገኖች ላይ ብርቱ ተጽእኖ ማሳደሩና የሱስ በእርግጥ መሲህ
ለመሆኑ ምስክርነታቸው አያጠራጥርም፡፡
ከላይ በምሳሌ ከተገለጸው አንድነት፣ ኅብረትና ምስክርነት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያንዎ
ምን መማር ትችላለች?
የየሱስ ተከታዮች በጴንጤቆስጤ ማግስት ከተለማመዷቸው ተፈጥሮአዊ ፈጣን
ዕድገቶች አንዱ የእርስ በርስ መረዳዳት መሆኑን ሉቃስ ይነግረናል፡፡ “ያመኑ ሁሉ
በአንድነት ነበሩ፤ ያላቸውንም ሁሉ በጋራ አደረጉ፡፡ ሀብታቸውንና ንብረታቸውንም
እየሸጡ ለእያንዳንዱ ሰው የሚያስፈልገውን ያህል ይሰጡት ነበር” (ሐዋ. 2፡44-45)፡፡
ይህ እያንዳንዱ ያፈራውን በጋራ የመጠቀም አካሄድ ኅብረቱ የሚጠይቀው
መስፈርት ሳይሆን ያ የተለማመዱት ኅብረት ያመጣው በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ
የፍቅር ውጤት ነበር፡፡ በተጨማሪ የኅብረታቸው ጽኑ መገለጫ ነበር፡፡ ይህ የአማኞች
ማኅበራዊ አኗኗር ለተወሰኑ ጊዚያት የቀጠለ ሲሆን በዚህ ዙሪያ ተጨማሪ ዝርዝሮች
በሐዋ. ምዕ. 4እና 5 ቀርቧል፡፡ በተጨማሪ ቀጥሎ እንደምናየው በሌሎች የአዲስ ኪዳን
መልእክቶች የሚገኝም ጭብጥ ነው፡፡
በርናባስን ለመጀመሪያ ጊዜ የምንተዋወቀው በዚህ ዐውደ ጽሑፍ ነው፡፡ ግለሰቡ
የግል ርስት የነበረው ሀብታም እንደነበር መገመት ይቻላል፡፡ ንብረቱ ለክርስቲያን
ኅብረት ጥቅም እንዲውል በማሰብ ሸጠና ገንዘቡን ወደ ሐዋርያት አመጣ (ሐዋ. 4፡
36-37)፡፡ በርናባስ እንደ ምሳሌ ልንከተለው የሚገባ ሰው ሆኖ ቀርቦአል፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሐዋ. 4፡32-37፣ 5፡1-11፡፡ የበርናባስን ባህሪና አመለካከት ከሐናንያ
እና ባለቤቱ ሰጲራ ጋር ያስተያዩ፡፡ ባልና ሚስቱ ምን ነካቸው?
እነዚህ ሰዎች መንፈስ ቅዱስን በግልጽ ከመዋሸታቸው በተጨማሪ ስስትና ክፉ
ምኞት ተንጸባርቆባቸዋል፡፡ ምናልባት ራስ ወዳድነትንና ስስትን ያህል የአማኞችን
ኅብረትና ወንድማዊ ፍቅር በፍጥነት ሊያጠፋ የሚችል ኃጢአት የለም፡፡ የበርናባስ
ድርጊት ለጥንቷ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ኅብረት በአዎንታዊ ሲታይ፤ በተቃራኒው
ሐናንያ እና ሰጲራ ግን በአሉታዊ ምሳሌነት ይነሳሉ፡፡ ሉቃስ የሕብረቱ አካል የነበሩትን
ከመልካም ምግባር አፈንጋጭ ሰዎች ታሪክ በመናገር ረገድ ሐቀኛ ነው፡፡
ከአስርቱ ትእዛዛት አንዱ የሆነውና ስለ ክፉ ምኞት የሚናገረው የመጨረሻው ትእዛዝ
(ዘጸ. 20፡1-17) ከሌሎቹ የተለየ ነው፡፡ ሌሎቹ ትእዛዞች እግዚአብሔር ለሰብዓዊው
ፍጡር ያለውን ፈቃድ ፊት ለፊት ስለ መተላለፍ ሲናገሩ፤ የመጨረሻው ትእዛዝ ግን
በልብ ውስጥ ስለ ተደበቀው ነገር ያወሳል፡፡ የክፉ ምኞት ኃጢአት ድርጊታዊ ሳይሆን
ይልቁንም የአስተሳሰብ ሂደት ነው፡፡ ክፉ ምኞት እና ባልደረባው ራስ ወዳድነት
በዐይን የሚታይ ኃጢአት ሳይሆን ኃጢአተኛው ሰብዓዊ ፍጡር የሚገኝበት ሁናቴ
ነው፡፡ ይህ ኃጢአት ገሃድ መውጣት የሚችለው እንደ ሐናንያ እና ሰጲራ ዓይነቱ ራስ
ወዳድ ድርጊት ብቻ ነው፡፡ በዚህም የመጨረሻው ትእዛዝ በሁሉም ትእዛዞች የተኮነኑ
ድርጊቶች የሚገለጹበት የክፉው ሁሉ ተግባር ሥር መሆኑን መመልከት ይቻላል፡
፡ ይህ ክፉ ምኞት በቀላሉ በሰይጣን ተጽእኖ ስር የሚወድቁበትን በር በመክፈት
እግዚአብሔርን ወደ መዋሸት መራቸው፡፡ ሁኔታው ይሁዳን ከነዳው ክፉ ምኞት
የተለየ አልነበረም፡፡
ክፉውን ምኞት ወይም ስስትን ከሕይወታችን መንቀል የምንችልባቸው መንገዶች
ምንድን ናቸው? ላለን ነገር ምስጋና እና ውዳሴ ማቅረብ የዚህ ክፉ ነገር ማርከሻ
ኃይል የሆነው ለምንድን ነው?
አንዱ የነበረውን ለሌሎች የሚያካፍልበት ማኅበራዊ አኗኗር የቀደመችው
ቤተ ክርስቲያን ኅብረት ተጨባጭ መገለጫ ነበር፡፡ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ
የመጀመሪያዎቹ ምዕራፎች የተገለጸው የልግስና ተግባር ኋላ ላይ ጳውሎስ በመቄዶንያ
እና አንጾኪያ ያቋቋማቸው ቤተ ክርስቲያኖች በየሩሳሌም ለነበሩ ድኾች የድርሻቸውን
እንዲያበረክቱ ግብዣ ሲያቀርብላቸው እንደ ቀጠለ እንመለከታለን (ሐዋ. 11:27–30፣
ገላ. 2:10፣ ሮሜ 15:26፣ 1ቆሮ. 16:1–4)፡፡ ስጦታው በአብዛኛው አሕዛብ አማኞችን
ያቀፉ እነዚያ አብያተ ክርስቲያናት በየሩሳሌም ለነበሩ አይሁድ ወንድም እህቶች
የነበራቸውን ጥንቃቄና ፍቅር በተጨባጭ ገልጦ ማሳየት የቻለ ሆነ፡፡ አማኞች የባህልና
የብሔር ልዩነቶች ቢኖሯቸውም በክርስቶስ አንድ አካል ፈጥረው የከበረውን አንድ
ወንጌል ይጋሩ ነበር፡፡ ይህ በችግር ከነበሩ ወገኖች ጋር ተካፍሎ የማደር ተግባር
ቀድሞውኑ በቤተ ክርስቲያን የነበረውን ኀብረት መግለጥ ብቻ ሳይሆን ኅብረቱን ጽኑ
መሰረት ላይ የሚያቆምም ነበር፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 2ቆሮ. 9፡8-15፡፡ ጳውሎስ በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን የተገለጠው
ለጋስነት ውጤቱ ምን ይሆናል አለ?
በቀደመችው ቤተ ክርስቲያን የተስተዋለው ኅብረት ዛሬም ምን መሠራት
እንደሚኖርበት ያሳየ ነው፡፡ በአማኞች መሃል ዓለማቀፋዊ ቁርጠኝነት ባይኖር ኅብረት
መምጣት ባልቻለ ነበር፡፡ የጥንቱ የአማኞች ኅብረት መሪዎች--ከክርስቶስ ጋር
ያላቸውን ግንኙነት ማሳደግ የአገልግሎታቸው አካል አድርገው ተመልክተውት ነበር፡፡
በባልና ሚስት እንዲሁም በልጆች መሃል ያለ ፍቅር በቁርጠኝነት በየቀኑ እንዲጎለብት
እንደሚደረግ ሁሉ በአማኞች መካከል ያለውም ኅብረት ተመሳሳይ ነው፡፡ በክርስቶስ
ያለን ኅብረት በብዙ መንገዶች የሚደፋፈር ብሎም በጉልህ የሚታይ ጭምር ነው፡፡
በቀደመችው ቤተ ክርስቲያን ይህን አንድነት ያዳበሩ የታወቁ አላባዎች፡ ጸሎት፣
አምልኮ፣ ኅብረት፣ የጋራ ራዕይ እና የእግዚአብሔርን ቃል ማጥናት ናቸው፡፡ እነዚህ
ወገኖች ያስተዋሉት ወንጌልን ለዓለም የመስበክ ተልዕኮአቸውን ብቻ አልነበረም፡
፡ ይልቁንም አንዱ ለሌላው የፍቅርና እንክብካቤ ኃላፊነት እንዳለበትም ተረድተው
ነበር፡፡ ኅብረታቸው በገዛ አጥቢያቸው ያደርግ በነበረው የለጋስነት ተግባር ድጋፍ
ሰጭነቱን ገልጦ ማሳየት የቻለ ብቻ ሳይሆን፤ ከራሳቸው አልፎ በብዙ ርቀት የሚገኙ
የቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰቦችንም ያካተተ ነበር፡፡
“ቸርነታቸው የእግዚአብሔርን ጸጋ በከንቱ ላለመቀበላቸው ምስክር መሆን ችሎ
ነበር፡፡ እንዲህ ያለው ለጋስነት በመንፈስ ከመቀደስ ውጪ ሌላ ምን ሊያፈራ ይችላል?
ይህ በአመኑትም ሆነ በአላመኑት ዐይን የጸጋው ታምራት ነበር፡፡”—Ellen G. White,
The Acts of the Apostles, p. 344.
እርስዎና ቤተ ክርስቲያንዎ ለሌሎች ለጋስ የመሆንን ጥቅም የተለማመዳችሁበት
መንገድ ምን ይመስላል? ማለትም--የቸርነት እጆቻቸውን ለሌሎች የሚዘረጉ ምን
ዓይነት በረከት ይወርድላቸዋል?
Ellen G. White, “Pentecost,” pp. 35–46, in 3 The Acts
of the Apostles.
“ይህ የአማኞች የለጋስነት ተግባር [ሐዋ. 2:44-45፣ 4:32–35] የመንፈስ ቅዱስ
መፍሰስ ውጤት ነበር፡፡ በወንጌል ኃይል የተለወጡ ወገኖች ‘በአንድ ልብ እና በአንድ
መንፈስ ነበሩ፡፡’ የተልዕኮው ስኬት ለሁሉም መሰጠቱ--አንድ ሁሉንም በጋራ የሳበና
የተቆጣጠረ ነገር ነበር፡፡ ይህን ተከትሎ ስስትም ሆነ ምቀኝነት በህይወታቸው ቦታ
አልነበረውም፡፡ ለወንድማቸውና ለዓላማቸው የነበራቸው ፍቅር ለገንዘብና ለቁሳዊው
ነገር ከነበራቸው የላቀ ነበር፡፡ ከምድራዊው ሀብት ይልቅ ለነፍሳት ከፍ ያለ ዋጋ
ለመስጠታቸው ሥራዎቻቸው ምስክር ነበሩ፡፡
“የእግዚአብሔር መንፈስ ሕይወታችንን ሲመራ የሚከሰተው ይኸው ነው፡፡
ልባቸው በክርስቶስ ፍቅር የተሞላ ወገኖች በእርሱ ጉስቁልና እኛ ባለጸጎች እንድንሆን
ስለ እኛ የደኸየውን ጌታ ምሳሌ ይከተላሉ፡፡ ገንዘብ፣ ጊዜ፣ ተጽእኖ--ከእግዚአብሔር
እጅ የተቀበሏቸው ስጦታዎች በሙሉ የወንጌልን ሥራ ለማፋጠን ብቻ ጥቅም ላይ
ይውላሉ፡፡ በዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን እንደሚታየው አባላት ምድራዊውን ብልጭልጭ
ነገር ከመውደድ ይልቅ መንፈስ ቅዱስ በሚሰጣቸው ኃይል ባልንጀራቸው ወንጌል
የሚሰማበትን መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኞች ሲሆኑ፤ በቀደመችው ቤተ ክርስቲያን
እንደ ሆነው በአምላካዊው ቃል የታወጁት እውነቶች በአድማጭ ልብ ብርቱ ተጽእኖ
ያገኛሉ፡፡”—Ellen G. White, The Acts of the Apostles, pp. 70, 71.
1.
የቀደመችው ቤተ ክርስቲያን ለተለማመደችው ኅብረት መምጣት መንስዔ
በመሆን እገዛ ያደረጉትን ነጥቦች ከዚህ ሣምንት ትምህርት ያንብቡ፡፡ እኛ ዛሬ እንደ
ቤተ ክርስቲያን ተመሳሳይ ተግባራት መፈጸም የምንችለው እንዴት ነው? በዚያን
ወቅት በነበሩ አማኞች መሃል የተተገበሩ እኛን ግን የሚጎድሉን ነገሮች ምንድን ናቸው?
2.
እነዚያ የቀደሙ የአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያኖች ከእነርሱ እጅግ ርቀው
በየሩሳሌም ይኖሩ ለነበሩ ድኾች እርዳታ ማድረጋቸው ለእኛ ምን ምሳሌ ይተውልናል?
ሌሎች ማኅበራዊ ጉዳዮችን በተመለከተስ? አጥቢያ ቤተ ክርስቲያኖች ድህነትን
በመቅረፍና ሌሎች መሰረታዊ ነገሮችን በማቅረብ ረገድ ማኅበረሰብ አቀፍ ተግባራቶች
ማከናወን የሚችሉት እንዴት ነው?
3.
ከአሳዛኙ የሐናንያ እና ሰጲራ ታሪክ ልንቀስም የምንችላቸው አንዳንድ
ትምህርቶች ምንድን ናቸው? የእነዚህን ሁለት ሰዎች ሞት ስለ ሰሙ ሲጠቀስ “ታላቅ
ፍርሐት ያዛቸው” (ሐዋ. 5፡5) በሚል የቀረበው ሀረግ አስፈላጊነት ምኑ ላይ ነው?
ማጠቃለያ፡
የየሱስ ደቀ መዛሙርት በታላቅ ኃይል እንደሚፈስ ተስፋ ለተሰጠው መንፈስ ቅዱስ
ራሳቸውን በማዘጋጀታቸው የቀደመችው ቤተ ክርስቲያን ፈጣን ዕድገት ማስመዝገብ
ቻለች፡፡ በእነርሱ የተስተዋለው ኅብረትና የጋራ መታመን መንፈስ ቅዱስ ልባቸውን
በበዓለ ኀምሳ ቀን ለማዘጋጀት እንዲጠቀምባቸው ምክንያት ነበሩ፡፡ አንዱ ለሌላው
ያሳይ ከነበረው ቸርነት እና ከተመዘገበው ፈጣን የቤተ ክርስቲያን ዕድገት አኳያ
መንፈስ ቅዱስ ከበዓለ ኀምሳ በኋላም ይህን አዲስ አማኝ ማኅበረሰብ የመለወጥ
ሥራውን ቀጠለ፡፡