ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ራእ. 1:1–8፣ዮሐ. 14:1–3፣ዘዳ. 29:29፣ዮሐ. 14:29፣ሮሜ 1:7፣ፊልጵ. 3:20፣ዳን. 13 7፣ 14፡፡
መታሰቢያ ጥቅስ :- “ዘመኑ ቀርቦአል፤ እንግዲህ ይህን የትንቢት ቃል የሚያነብ ብፁእ ነው፤ የሚሰሙትና የተጻፈውንም የሚጠብቁ ብፁዓን ናቸው፡፡” (ራእ. 1፡3)፡፡
የ
ራእይ ትንቢት ለሐዋርያው ዮሐንስ የተገለጠለት ከአስራ ዘጠኝ መቶ ዓመታቶች
ቀደም ብሎ ሲሆን ይኸውም በኤግያን ባሕረ ሰላጤ ፍጥሞ በሚል ስያሜ
ትታወቅ በነበር አንዲት አነስተኛ ደሴት በግዞት ይኖር በነበረበት ወቅት ነው (ራእ.
1፡9)፡፡ ይህ መጽሐፍ በቤተ ክርስቲያን እንዲነበብ ራእ. 1፡3 ያበረታታል፡፡ ይህን
መጽሐፍ የሚያነብ፣ የሚያዳምጥም አምላካዊውን በረከት ይቀበላል የሚል የተስፋ
ቃል ተሰጥቶአል፡፡ የሚሰሙት--በሚል ጥቅም ላይ የዋለው ቃል የቤተክርስቲያንን
ጉባዔ ይወክላል፡፡ ሆኖም አማኙ በረከት የሚያገኘው እንደው እንደ ዋዛ መጽሐፉን
በመሸምደዱ ወይም ሲነበብ በመስማቱ ሳይሆን ቃላቶቹን በመታዘዙ ነው
(ራእ. 22፡7)፡፡
የራእይ ትንቢቶች እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያለውን ጥንቃቄ የሚያሳዩ ጥልቅ
መገለጫዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ትንቢቶች ምድራዊው ህይወት ምን ያህል ተሰባሪና
አጭር መሆኑን ከማሳየታቸው በተጨማሪ በየሱስ የሚገኘውን ደኅንነትና ወንጌልን
እንድናሰራጭ የመጠራታችንን እውነታ ያመላክቱናል፡፡
መጽሐፍ ቅዱሳዊዎቹ ትንቢቶች ጨለማን ሰንጥቆ እንደሚያልፍ የብርሃን ጨረር
ናቸው (2ጴጥ. 1፡19)፡፡ ለዛሬው ሕይወታችን ምሪት እንዲሰጡና የወደፊቱን ደግሞ
በተስፋ እንዲሞሉ ታቅዶ የተበረከቱ ናቸው፡፡ ክርስቶስ ዳግም እስከሚገለጥና
የእግዚአብሔር መንግሥት እስከሚመሰረት ይህን ትንቢታዊ ምሪት እንሻለን፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 1፡1-2፡፡ የመጽሐፉ ርዕስ ሙሉ ትርጓሜ ምንድን ነው? መጽሐፉ በትክክል ስለ ማን እንደሚናገር አስመልክቶ ርዕሱ ምን ያስተምረናል?
ራእ. 1፡1 የመጽሐፉን ርዕስ “የኢየሱስ ክርስቶስ ራእይ” በማለት ያስቀምጣል፡፡
ራእይ የተሰኘው ቃል የተወሰደው አፖካሉፕሲስ ከሚል የግሪክ አቻው ሲሆን፤ ቃሉ
“መግለጥ” ወይም “ይፋ ማድረግ” የሚል ፍቺ አለው፡፡ በመሆኑም አፖካሉፕሲስ
ከየሱስ እና ስለ የሱስ የተሰጠ የየሱስ ክርስቶስ መገለጥ ነው፡፡ ይህ በየሱስ ክርስቶስ
አማካይነት ከእግዚአብሔር የመጣ ራእይ (ራእ. 22፡16)፤የራእዩ አስኳል የሱስ
መሆኑንም ይመሰክራል፡፡ አፖካሉፕሲስ እርሱ ራሱን ለሕዝቡ የገለጠበት ራዕይ እና
ለእነርሱ ያለው ጥበቃና ጥንቃቄ መግለጫ ነው፡፡
የሱስ የራእይ መጽሐፍ ማዕከላዊ አካል ወይም አስኳል ነው፡፡ መጽሐፉ በእርሱ
ተጀምሮ (ራእ. 1፡5-8) በእርሱ ይደመደማል (ራእ. 22፡12-16)፡፡ “ትንቢተ ዳንኤል
ይናገር፣ የራእይ መጽሐፍም ይናገር--እውነት የሆነውን አውሩ፡፡ ነገር ግን ማንኛውም
የዚህ መልእክት ክፍል ሲቀርብ--የሁሉም ተስፋ የሆነውን ‘የዳዊት ሥርና ዘር፣
የሚያበራ የንጋት ኮከብ’ የሱስን ከፍ አድርጉ፡፡”—Ellen G. White, Testimonies
to Ministers and Gospel Workers, p. 118.
ደግሞም የራእይ መጽሐፉ የሱስ የአራቱ ወንጌሎች የሱስ ነው፡፡ መጀመሪያ ላይ
በወንጌላት እንደ ተወሳው የራእይ መጽሐፍ የሱስንና እርሱ ስለ ሕዝቡ የሠራውን
የደኅንነት ሥራ መግለጹን ይቀጥላል፡፡ የራእይ መጽሐፍ በየሱስ አብሮነትና
በአገልግሎቱ ልዩ ልዩ ገጽታዎች ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡ በመሰረቱ መጽሐፉ
የሚጀምረው ከወንጌል የመጨረሻ ጽሑፍ በመቀጠል ይኸውም ከየሱስ ትንሣኤና
ዕርገት አንስቶ ነው፡፡ የራእይ መጽሐፍ ከዕብራውያን መልእክት ጋር በማበር
ስለ የሱስ ሰማያዊ አገልግሎት አጽንኦት ይሰጣል፡፡ የሱስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ
በሰማያዊው መቅደስ በንጉሣዊና ካኅናዊ አገልግሎቱ መክበሩን ያሳያል፡፡ ያለ ራእይ
መጽሐፍ (እና ዕብራውያን) የሱስ ስለ እኛ በሰማያዊው መቅደስ እየሰጠ ስለሚገኘው
አገልግሎት ይኖረን የነበረው ዕውቀት ውሱንና ስውር ሆኖ በተከደነ ነበር፡፡ ደግሞም
የራእይ መጽሐፍ ከዕብራውያን ጋር ባለው ኅብር የሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ እየሰጠ
ስላለው አገልግሎት በዓይነቱ ልዩ የሆነ ምልከታ ይሰጠናል፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዮሐ. 14፡1-3፡፡ በጥቅሱ የቀረበው ሰፊ የተስፋ
ቃል የሱስ በአሁኗ ሰዓት ስለ እኛ በሰማያዊው መቅደስ እያደረገ
ስላለው ነገር በተሻለ ማስተዋል እንድንችል እንዴት ይረዳናል? ከዚህ
አስገራሚ የተስፋ ቃል ብሩህ የሆነውን መጻኢ ጊዜ መሳል የምንችለው
እንዴት ነው?
የራእይ መጽሐፍ የተጻፈበት ዓላማ መጽሐፉ ራሱ ከተጻፈበት ጊዜ አንስቶ በተከታታይ
ገቢራዊ የሚሆኑ ክስተቶችን ለማሳየት እንደሆነ ራእ. 1፡1 ይነግረናል፡፡ ከራእይ
መጽሐፍ ጋር ቅርበት ያለው ማንኛውም ሰው ይህ መጽሐፍ በአብዛኛው የተሞላው
ከእኛ ኋላ በነበሩ ዘመኖች ፍጻሜ ባገኙ ክስተቶች እንዲሁም የወደፊቱን ጊዜያቶች
የሚጠባበቁ ትንቢቶችን መያዙን ለማስተዋል አይቸገርም፡፡ የራእይ መጽሐፍ
የመጀመሪያው አጋማሽ (ከምዕ. 1-11) ከመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን እስከ ዘመን
መጨረሻ ባሉ ክስተቶች ላይ ትኩረት ሲያደርግ፤ ሁለተኛው አጋማሽ ግን (ከምዕ. 1222) ወደ ዳግም ምጽአቱ የሚመሩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡
የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ተቀዳሚ ዓላማ ነገ የቱንም ዓይነት ያልተለመደ ነገር
ይዞ ከተፍ ሊል ቢችል--ሁሉም ነገር በእግዚአብሔር ቁጥጥር ስር ለመሆኑ ማረጋገጫ
መስጠት ነው፡፡ የራእይ መጽሐፍ ተግባር ይኸው ነው--የሱስ ክርስቶስ በዚህ
ዓለም ታሪክ ውስጥ እና በወደፊቱ አሳሳቢ ሁኔታ ከሕዝቡ ጋር ለመሆኑ ማረጋገጫ
መስጠት፡፡ በዚህ የተነሳ የራእይ ትንቢቶች ሁለት ተጨባጭ ዓላማ አላቸው፡--ዛሬን
እንዴት መኖር እንዳለብን ማስተማር እና ለወደፊቱ ማዘጋጀት፡፡
ጥቅሱን ያንብቡ፡ ዘዳ. 29፡29፡፡ አንዳንድ ነገሮች ለምን እንዳልተገለጡልን ማስተዋል
እንድንችል ጥቅሶቹ እንዴት ይረዱናል? በጥቅሱ መሰረት ለእኛ የተገለጡት ነገሮች
ዓላማ ምንድን ነው? ስለ ምን ተነገሩን? (ራእ. 22፡7)
የራእይ የመጨረሻ ጊዜ ትንቢቶች የተገለጡልን እንደው ስለ ወደፊቱ እያሰብን
በፍርሃትና መብሰልሰል እንዳንኖር ለመጠበቅ አይደለም፡፡ መጽሐፉ አሁን
ለእኛ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ብቻ ይገልጥልናል፡፡ የመጪውን ጊዜ ከባድነት
አስተውለን ከወዲሁ በእግዚአብሔር ላይ መተማመን--ይኸውም እርሱን መታዘዝ
እንደሚኖርብን መገንዘብ እንችል ዘንድ እነሆ ትንቢቶቹ ተገልጠውልናል፡፡
የመጨረሻዎቹን ዘመናት ክስተቶች አስመልክቶ አያሌ መላ ምቶች እንደውም
የተዋጣላቸው ስሜት ተኮር ግምቶች ለምዕተ ዓመታት ሲስተናገዱ ኖረዋል፡፡
ምዕመናን የመጨረሻው መቃረቡን እንናገራለን በሚሉ ትንቢት ተናጋሪ ነን ባይ ቀበኛ
የቤተ ክርስቲያን መሪዎች መጨረሻው ደርሶአል በሚል ማስፈራሪያ ታልበዋል፡፡
ሆኖም ማስፈራሪያው እንደ ማንኛውም ቀን ያለ አንዳች ልዩ ክስተት መጥቶ ሲሄድ-በቁም ቅዠት ውስጥ የነበሩ ሰዎች በብርቱ ተስፋ መቁረጥ ሲወድቁ በተደጋጋሚ
ተስተውለዋል፡፡ ከእግዚአብሔር የተቀበልናቸው አያሌ በጎ ነገሮች አሉታዊ ተግዳሮት
እንደሚገጥማቸው ሁሉ በተመሳሳይ ትንቢትም በተሳሳተና ተገቢ ባልሆነ መንገድ
ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 13፡1፣ ዳን. 7፡1-3፣ ሕዝ. 1፡1-14፡፡ ሁሉም ራእዮች በጋራ የያዙት አንድ ነገር ምንድን ነው?
የራእይ መጽሐፍ ስለ መልእክቱ ተጨማሪ ማብራሪያ ሲሰጥ “መልአኩን ልኮ
ለአገልጋዩ ለዮሐንስ ገለጠለት” ይላል (ራእ. 1፡1 )፡፡ ይህ ሃረግ የመልእክቱ በጣም
አስፈላጊ ክፍል ነው፡፡ በጥቅሱ ገለጠለት በሚል ጥቅም ላይ የዋለው ቃል የተወሰደው
ሴማይኖ ከሚል የግሪክ አቻው ሲሆን “በምሳሌያዊ ምልክቶች አሳየው” የሚል ፍቺ
አለው፡፡ እንዲሁም ይህ ቃል በግሪክ ቋንቋ በተጻፈው የብሉይ ኪዳን ትርጉም “ወደ
ፊት የሚሆነውን” (ዳን. 2፡45) በሚል ዳንኤል ለንጉሡ ናቡከደነጾር ከወርቅ፣
ከብር፣ ከነሐስ እና ከብረት ስለ ተሠራው ምስል ሲያብራራለት ቀርቦ እንመለከታለን፡
፡ ዮሐንስ በተምሳሌታዊ አቀራረብ የተሞሉት ክስተቶችና ትዕይንቶች በራእይ እንደ
ተገለጡለትተመሳሳይ ቃል ተጠቅሞ ይነግረናል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ይመራ የነበረው
ዮሐንስ በተምሳሌታዊ አቀራረብ የተመለከታቸውን እነዚህን ራዕዮች በታማኝነት
አስፍሮአል (ራእ. 1፡20)፡፡
የራእይ ትንቢቶች የተገለጡበት ቋንቋ ውስጠ ወይራ እንደመሆኑ ቃል በቃል
መተርጎም የለበትም፡፡ በአጠቃላይ መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ (ጥቅሱ ራሱ ወደ
ተፈለገው ተምሳሌታዊው አቀራረብ ካላመለከተ በቀር) ፊት ለፊት የተቀመጠውን
ቀጥተኛ ትርጉም መውሰዳችን እርግጥ ነው፡፡ ሆኖም የራእይ መጽሐፍን ስናነብ ጥቅሱ
ቀጥተኛውን ትርጉም ካላመላከተ በቀር በተምሳሌታዊ መንገድ ፍቺ መስጠታችን
ተገቢ ነው፡፡ እነዚህ በትንቢት የቀረቡ ትዕይንቶች እና ድርጊቶች ተጨባጭ ቢሆኑም
ነገር ግን አቀራረባቸው በተምሳሌታዊ ቋንቋ ነው፡፡
የራእይ መጽሐፍ በአብዛኛው ተምሳሌታዊ ጸባይ የተላበሰ መሆኑን ከግምት
ማስገባታችን ትንቢታዊውን መልእክት አዛብተን ከማቅረብ እንድንጠበቅ ይረዳናል፡
፡ በመጽሐፉ ጥቅም ላይ የዋሉ ምሳሌያዊ አቀራረቦችን ፍቺ ለመወሰን በምናደርገው
ሙከራ ሰዋዊውን እሳቤ እንዳንጭን ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል፡፡ ይልቁንም ወደ
ራሱ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ በማምራት በሌሎች ገጾች የሚገኙ ምሳሌያዊ አቀራረቦችን
እየቃኘን በራእይ መጽሐፍ የምናገኛቸውን ተምሳሌታዊ አቀራረቦች በአግባቡ
ማስተዋል ተገቢ ይሆናል፡፡
በራእይ መጽሐፍ የምናገኛቸውን ምሳሌያዊ አቀራረቦች ለመፍታት በምናደርገው
ሙከራ አብዛኞቹ የተወሰዱት ከብሉይ ኪዳን መሆኑን ማስታወስ የግድ ይሆናል፡፡
የወደፊቱ የማዳን ሥራው ካለፈው ጋር አንድ ዓይነት የሆነው እግዚአብሔር አምላክ
እነዚያን የቀደሙ ቋንቋዎች ተጠቅሞ የወደፊቱን በማሳየት አእምሮአችንን ለማነቃቃት
ፍላጎቱ ነው፡፡ እርሱ ቀደም ባለው ዘመን ለሕዘቡ ያደረገውን እነሆ ወደፊትም
ያደርጋል፡፡ የራእይ መጽሐፍን ተምሳሌቶች እና ምስሎች ለመፍታት በምናደርገው
ሙከራ ከወዲሁ ለብሉይ ኪዳን ትኩረት መስጠት መጀመር ይኖርብናል፡፡
የራእይ መጽሐፍ ከጳውሎስ መልእክቶች በተመሳሳይ በሰላምታ ይጀምራል፡፡
ሲጀመር፤መጽሐፉ በዮሐንስ ዘመንለነበሩ ሰባቱየእስያ አብያተ ክርስቲያናት የተላከ
ደብዳቤ ቢሆንም (ራእ. 1፡11)፤ የራእይ መጽሐፍ የተጻፈው ለእነርሱ ብቻ ሳይሆን
በዘመናት ለነበሩ፣ ላሉና ለሚኖሩ ክርስቲያኖች ጭምር ነው፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 1፡4-5፣ ሮሜ 1፡7፡፡ ሁለቱ መልእክቶች የሚጋሩት ሰላምታ
ምንድን ነው? ሰላምታው የተሰጠው ከማን ነው?
የራእይም ሆነ የጳውሎስ መልእክቶች “ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን” የሚል
ደብዳቤያዊ ሰላምታ ያቀርባሉ፡፡ ይህ ኃረግ የግሪኮችን ሰላምታ ቻሪስ (ጸጋ) እና
የዕብራውያኑን ሻሎም (ሰላም፣ ደኅና መሆን) በአንድ ይዞአል፡፡ ጸጋና ሰላም ሰጪ
እግዚአብሔር አብ፣ እግዚአብሔር ወልድ እና እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አንድ
አምላክ መሆኑን ከእነዚህ ጥቅሶች ተነስተን መመልከት እንችላለን፡፡ እንደ ቀሪው
የመጽሐፉ ክፍል ሁሉ እነዚህ ሦስት ባህሪያትም በተምሳሌታዊ ቋንቋ ተለይተው
ቀርበዋል፡፡ እግዚአብሔር አብ “ያለውና የነበረው፣ የሚመጣውም” (ራእ. 1፡8፣
4፡8) በሚል የቀረበ ሲሆን፤ ይህ አነጋገር “እኔ፣ ያለሁና የምኖር ነኝ” (ዘፀ. 3፡14)
የሚለውን የዘላማዊውን እግዚአብሔር ህልዎት ይወክላል፡፡
መንፈስ ቅዱስ “ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስት” በሚል ተጠቅሶአል (ራእ. 4፡
5፣ 5፡6)፡፡ ሰባት ቁጥር ሙላትን ያሳያል፡፡ “ሰባቱ መናፍስት” መንፈስ ቅዱስ
ከሚሠራባቸው ሰባቱ ቤተ ከርስቲያኖች ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ ይህ ገጽታ በዘመናት
የእግዚአብሔር ሕዝቦች የተጠሩበትን ከፍጻሜ ለማድረስ የሚያስችላቸውን
ዓለማቀፋዊ ገጽታ ያለውን የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ያሳያል፡፡
የሱስ ክርስቶስ “ታማኝ ምስክር፣ ከሙታን በኩርና የምድር ነገሥታት ገዥ”(ራእ. 1፡5)
በሚሉ ሦስት ስያሜዎች ቀርቦአል፡፡ ስያሜዎቹ የመስቀል ላይ ሞቱን፣ ትንሣኤውንና
ሰማያዊ ንግሥናውን ያሳያሉ፡፡ ከዚያም “ለወደደንና ከኃጢአታችንም በደሙ ነጻ
ላወጣን፣ አምላኩንና አባቱን እንድናገለግልም መንግሥትና ካኅናት ላደረገን” (ራእ.
1፡5-6) በማለት የሱስ ያደረገውን ዮሐንስ ይጠቅሳል፡፡
“ለወደደን” የሚለው ቃል በመጀመሪያው የግሪክ ቋንቋ--ያለፈውን፣ የአሁኑንና
የወደፊቱን በአንድ ያቀፈው የክርስቶስ ፍቅር የማያባራ መሆኑን ይገልጻል፡፡ እኛን
የወደደው፣ እርሱ በደሙ ከኃጢአታችን ነፃ አድርጎናል፡፡ በግሪኩ ትርጉም፣ አባባሉ
ያለፈው ድርጊት ፍጻሜ ማግኘቱን ይጠቅሳል፡፡ የሱስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ-እኛን ተከታዮቹን ከኃጢአታችን ለዘላለም ነፃ አወጣን፡፡
የተዋጁ ወገኖች በትንሣኤ ተነስተው በሰማያዊው ስፍራ ከየሱስ ጋር
እንደሚቀመጡ--ኤፌ.2፡6 እና ፊልጵ.3፡20 ይገልጻሉ፡፡ ለመሆኑ ይህ
ምን ማለት ነው? ዛሬ በዚህ በኃጢአት የተረገመ ምድር እየተመላለስን
ይህን በክርስቶስ “መንግሥትና (ነገሥታትና) ካኅናት” ስለ መሆናችን
በክብር የተሞላ ማንነት ሐሴት የምናደርገው እንዴት ነው? አውነታው
በዚህ ህይወት ምን ዓይነት ተጽእኖ ሊኖረው ይገባል?
የራእይ መጽሐፍ መግቢያ አጠቃላይ ገጽታ መጽሐፉ ሙሉ ለሙሉ ትኩረት
የሚያደርግበትን-- ይኸውም በኃይልና በግርማ እውን ወደሚሆነው የየሱስ
ዳግም ምጽአት ያመላክታል፡፡ የክርስቶስ ዳግም ምጽአት የተስፋ ቃል በመጽሐፉ
መደምደሚያ ላይ ሦስት ጊዜ ተደጋግሞ ቀርቦአል (ራእ. 22፡7፣ 12፣ 20)፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ--ራእ. 1፡7-8፡፡ የዚህ ጥቅስ አጻጻፍ ወይም የቃላት አጠቃቀም
ግኝት ብዛት ያላቸው ትንቢቶች ናቸው፡ ዳን. 7፡13-14፣ ዘካ. 12፡10፣ ማቴ. 24፡30፡፡
ጥቅሶቹ ዳግም ምጽአቱ የተረጋገጠ ስለመሆኑ ምን ይነግሩናል?
በራእይ መጽሐፍ እንደ ተመለከተው የክርስቶስ ዳግም ምጽአት የታሪክ ሁሉ
መደምደሚያ ነው፡፡ የዚህን ዓለም ታሪክ ፍጻሜና የአምላካዊውን መንግሥት
ጅማሮ የሚያመለክተው ዳግም ምጽአት--የክፉ፣ የጣር፣ የህመምና የሞትን ፍጻሜ
ያበስራል፡፡
ራእ. 1፡7--እንደ ሌሎቹ የአዲስ ኪዳን መልእክቶች ሁሉ ግላዊ ብሎም ልክ እንደ
ተባለው ገቢራዊ ወደ ሚሆነው፣ ንጉሣዊና ባለ ታላቅ ግርማ የክርስቶስ ዳግም
ምጽአት ያመላክቱናል፡፡ እያንዳንዱ ሰብዓዊ ፍጡር እንደውም “የወጉት እንኳ
ሳይቀሩ” የዳግም መገለጡ ምስክር ይሆናል፡፡ ይህ አባባል የክርስቶስ ዳግም ምጽአት
ገቢራዊ ከመሆኑ ጥቂት ቀደም ብሎ እርሱን የወጉ ሰዎችን ጨምሮ በተለየትንሳኤ
የሚነሱ መኖራቸውን ይጠቁማል፡፡ በዳግም ምጽአቱ እርሱን ለሚጠባበቁ ደኅንነት-ለፍቅሩና ምኅረቱ ዘለፋዊ ምላሽ ለሰጡ ደግሞ ፍርድ ይዞ ይመጣል፡፡
የተረጋገጠው የክርስቶስ ዳግም ምጽአት “አዎ፤ አሜን!” በተሰኙ ቃላት የጸና ነው
(ራእ. 1፡7)፡፡ እነዚህ አዎ እና አሜን የተሰኙ ቃላት--ሁለቱም አዎንታዊ ወይም
አዎንታን ይዘዋል (ራእ. 22፡20)፡፡
“በቅርቡ በሰማያት ደመና በሚገለጠው የሰው ልጅ መምጣት ላይ ጽኑ እምነት
እስካለ ድረስ--ተራና መናኛ የሆነው ምድራዊ ነገር እውነተኞቹን ክርስቲያኖች
ቸልተኛና ግዴለሽ አያደርግም. . . ትክክለኝነታቸው፣ ታማኝነታቸውና ሐቀኝነታቸው
በአላፊ ምድራዊ ነገሮች ይፀናል፣ ይረጋገጥማል፡፡”—Ellen G. White, Testimonies for the Church, vol. 4, p. 309.
አንድ የተስፋ ቃል ሲሰጥ--የተስፋ ሰጪው ቃል ጥንካሬ የሚለካው
ቃሉን ጠብቆ መዝለቅ በመቻሉ ሐቀኝነትላይ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ
ቀደም ሰጥቶ የነበረውን የተስፋ ቃል በሙሉ በጠበቀው በእግዚአብሔር
የተቸረን የዳግም ምጽአቱ የተስፋ ቃል ሐቅ--ክርስቶስ በተናገረው
መሰረት ዳግም ስለ መመለሱ ምን ዓይነት ማረጋገጫ ይሆንዎታል?
Read Ellen G. White, “The Study of the Books of Daniel
and the Revelation,” pp. 112–119, in Testimonies to Ministers and Gospel Workers.
“ቤተ ክርስቲያን በዘመናት ምሪትና መጽናናት ታገኝ ዘንድ እነሆየራእይ መጽሐፍ
ተሰጠ. . . ራእይ--የተገለጠ የሚል ፍቺ አለው፡፡ በዚህ መጽሐፍ የቀረቡትን ምስጢሮች
ጌታ ራሱ ለአገልጋዩ የገለጠ ሲሆን፤ መጽሐፉን ለሚያጠኑ ሁሉ መልእክቱን የተከፈተ
አድርጎአል፡፡ መጽሐፉ የያዛቸው እውነቶች የዮሐንስን ዘመን ብሎም በምድር ታሪክ
መደምደሚያ የሚኖሩ ሕዝቦችን ዒላማ ያደረገ ነው፡፡ በዚህ ትንቢት የቀረቡት
አንዳንድ ትዕይንቶች ቀደም ባሉት ዘመናት ፍጻሜ ያገኙ፣ በምድር ታሪክ መጨረሻ
ገቢራዊ የሚሆነውን የጨለማውን ኃይልና የሰማይን ልዑል ውዝግብ የሚያስቃኙ
እንዲሁም በጸጋው የዳኑ አሸናፊዎች በአዲሲቱ ምድር የሚኖራቸውን ደስታና ፍስሐ
የሚገልጡ ናቸው፡፡
“መጽሐፉ የያዛቸውን እውነቶች ፍቺ ለማወቅ በምናደርገው ጥረት፤ ለእያንዳንዱ
ተምሳሌታዊ አቀራረብ ትርጓሜና ማብራሪያ ባለመሰጠቱ፤ መጽሐፉን መመርመር
ዋጋ እንደሌለው አድርገን ልንቆጥር አይገባም፡፡ እነዚህን ምስጢሮች ለዮሐንስ
የገለጠለት ጌታ፤ እውነትን ለማወቅ ለሚሹ ትጉሃን የሰማዊውን ነገር ምሳሌ
ይገልጥላቸዋል፡፡ እውነትን ለመቀበል ልቦቻቸው ክፍት የሆኑ ወገኖች አስተምህሮውን
የሚያስተውሉበት ኃይል ይሰጣቸዋል፡፡`ይህን የትንቢት ቃል የሚያነብ ብፁዕ ነው፤
የሚሰሙትና የተጻፈውንም የሚጠብቁ ብፁዓን ናቸው’ በሚል የቀረበው በረከትና
የተስፋ ቃል ባለቤት ይሆናሉ፡፡”—Ellen G. White, The Acts of the Apostles,
pp. 583–585.
1.ራእይ የተሰኘው ቃል በየሱስ ክርስቶስ የተገለጠ የሚል ፍቺ ቢኖረውም
ነገር ግን ብዙዎች አሉታዊ ከሆነ የዓለም ፍጻሜ፣ ከአሰቃቂ ክስተትና
አስፈሪ የፍርድ ቀን አኳያ ይመለከቱታል፡፡ መጽሐፉ በአብዛኛው
የክርስትና እምነት ተከታዮች እንዴት እንደሚታይ አስመልክቶ ይህ
ምን ይነገረናል?አስፈሪ የተሰኘው ቃል ተደጋግሞ የቀረበው ለምንድን
ነው?
2.ባለፉት 20 ዓመታት ብቻ ስለ ዓለም ፍጻሜ እንዲሁም ስለ
የሱስ ዳግም ምጽአት በአንዳንዶች ተነግረው ፍጻሜ ሳያገኙ ስለቀሩ
ትንቢቶች አሰብ ያድርጉ፡፡ ትንቢቶቹ ከየትኛውም እሳቤ አኳያ ሊሰጡ
ቢችሉም፤ሳይሰምሩ የመቅረታቸው አሉታዊ ውጤት ምን ሊያስከትል
ይችላል? ትንቢቶቹን አምነው በተቀበሉ ላይ ምን ዓይነት ስሜት
ይፈጥራል? ሳይሰምሩ የቀሩት ትንቢቶች ለአጠቃላዩ ሕዝበ ክርስቲያን
ምን ዓይነት ገጽታ ያሰጣሉ? እኛ ትንቢትን አምነን የምንቀበልና ወደ
መጨረሻው የሚያደርሱ ምልክቶችን በጥንቃቄ የምንመለከት ሕዝቦች
እንደ መሆናችን፤ ትንቢትን በማስተዋሉና ለሌሎች በማስተማሩ ረገድ
ትክክለኛውን ሚዛን ጠብቀን መጓዝ የምንችለው እንዴት ነው?