ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ራእ. 1:9–18፣ ሐዋ. 7:54–60፣ ማቴ. 12:8፣ ዘፀ. 20:11፣ ዳን. 10:5-6፣ ራእ. 1:20፣ ራእ. 2:1–7፡፡
መታሰቢያ ጥቅስ :- “ ‘እኔ ድል ነስቼ ከአባቴ ጋር በእርሱ
ዙፋን ላይ እንደ ተቀመጥኩ፣ ድል የሚነሳውንም ከእኔ ጋር
በዙፋኔ ላይ እንዲቀመጥ አደርገዋለሁ’ ” (ራእ. 3፡21)፡፡
መ
ዝ. 73-- በዐመፀኞች ስኬት ግራ ስለ ተጋባው ባለ መዝሙር ገለጻ
ያደርጋል፡፡የእነዚህ ሰዎች ኑሮ ከጻድቃን በተቃራኒ በብልጽግና
የተሞላ ከመሆኑ በተጨማሪ፤ በብዙዎች የሚደርሰው ጣጣ አያውቃቸውም፡
፡ይህ ኢፍትሐዊነት በጉዳዩ እየተብሰለሰለ ወደ ቤተ መቅደስ ያመራውን
(መዝ. 73፡16-17) ባለ መዝሙር አብልጦ ቢረብሸውም፤ ሆኖም
በእግዚአብሔር ፊት በቆመ ጊዜ--ስለ ጉዳዩ ጥልቅ ማስተዋል አገኘ፡፡
ይህ ከሆነ ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ አንድ ዕድሜ የተጫጫነው ሐዋርያ ስለ
ታማኝ ምስክርነቱ ራሱን በዐለታማ የግዞት ደሴት መሃል እንዲያገኝ ተገድዶ ነበር፡
፡ በዚያ አስጨናቂ ሁናቴ ውስጥ የነበረው ይህ ሐዋርያ በእርሱ ጥንቃቄ ስር የነበሩ
ቤተ ክርስቲያኖች በአስቸጋሪ ሁናቴ የመውደቃቸውን ወሬ ሰማ፡፡ ሆኖም በዚያ
ወሳኝ ወቅት--በትንሣኤ የተነሳውን ክርስቶስ በሰማያዊው ቤተ መቅደስ የመመልከት
ተሞክሮ ማግኘት ችሎ ነበር፡፡
ቀደም ሲል ከባለ መዝሙሩ ጋር የነበረው ጌታ
አንዳንድ የዚህን ህይወት ዕንቆቅልሾችና ተግዳሮቶች በተመሳሳይ ለዮሐንስ
ሲገልጥለት ይታያል፡፡ የዚህ ምድር ታሪክ እስኪደመደም ረጅሞቹን ምዕተ ዓመታት
አቋርጦ በሚያልፈው የክርስትና ትውልድ መሃል የክርስቶስን ሕልዎት፣ ጥንቃቄና
ጥበቃ በቤተ ክርስቲያን ላይ የመኖሩን አዎንታዊ የምስራች ለመግለጥ--እነሆ የቤተ
መቅደሱ ትዕይንት ለዮሐንስ ተሰጠ፡፡
ጥቅሱን ያንብቡ፡ ራእ. 1፡9፡፡
ዮሐንስ ራእዩን ስለ ተቀበለበት ሁናቴ ምን ይለናል?
በሜዲቴራንያን ባሕረ ሰላጤ ኤግያን ባሕር (በግሪክና በዛሬዋ ቱርክ መሃል)
የምትገኘው ዐለታማዋ ፍጥሞ ደሴት 16 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 9.6 ኪሎ ሜትር
የጎን ስፋት ነበራት፡፡ ፍጥሞን ጨምሮ ዙሪያ ገባውን ደሴቶች በቅኝ ግዛት ያስተዳድሩ
የነበሩት የያኔዎቹ ልዕለ ኃያል ሮማውያን የፖለቲካ ወንጀለኞች ያሏቸውን ወደ እነዚህ
ደሴቶች በግዞት ይልኩ እንደ ነበር የታሪክ ድርሳናት ያረጋግጣሉ፡፡ የዮሐንስ ለወንጌል
ታማኝ መሆን በሮም ባለ ሥልጣናት ትእዛዝ ወደ ግዞት እንዲላክ መንስኤ እንደነበር
መጽሐፉ በተጻፈበት ዘመን አካባቢ የነበሩ ቀደምት ክርስቲያን ጸሐፊዎች በአንድ
ይስማማሉ፡፡ አዛውንቱ ሐዋርያ በፍጥሞ ህይወቱ ሁሉንም ዓይነት የሮማውያን
የእስር ጉስቁልና ማለፉ እሙን ነው፡፡
ምናልባትም እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ በእግር
ብረት እንዲታሠር፣ በቂ ምግብ እንዳያገኝና በእነዚያ ርኅራኄ ያልፈጠረባቸው ጨካኝ
የሮም ዘቦች ጅራፍ ከባድ የጉልበት ሥራ እንዲሠራ ሳይገደድ እንዳልቀረ ይታመናል፡፡
“ዐለታማና ጠፍ ደሴት የሆነው ፍጥሞ፤ ወንጀለኞች እንዲጋዙበት በሮም መንግሥት
ቢመረጥም--ተስፋ አስቆራጩና የጨገገው ስፍራ ለእግዚአብሔር አገልጋይ የሰማይ
ደጃፍ መመልከቻ ሆነ፡፡
ከተለመደው በውጥረት የተሞላ ባተሌ የዕለት ከዕለት
ህይወቱ ብሎም ከንቁ አገልጋይነቱ ፍጹም የተቆራረጠው ሐዋርያ--ከእግዚአብሔር፣
ከክርስቶስና ከሰማያዊ መላእክት ጋር አብሮነት በመፍጠር እስከ ምድር ታሪክ
መዝጊያ ላለችው ቤተ ክርስቲያን የሚበጅ መመሪያ ተቀበለ፡፡”—Ellen G. White,
The Acts of the Apostles, pp. 570, 571.
ለእግዚአብሔር ባላቸው ታማኝነት በአስቸጋሪ ሁናቴ እንዲያልፉ የተገደዱ ሌሎች
የመጽሐፍ ቅዱስ መሪ ተዋናይ እነማን ናቸው? ዳን. 3:16–23፣ ሐዋ. 7:54–60፡፡
የክርስቶስ ተከታዮች ራሳቸውን በየትኛውም እንደ ዮሐንስ ባለ አስቸጋሪ ሁናቴ
ውስጥ ሊያገኙ ቢችሉ ብቻቸውን አለመተዋቸውን ፈጽሞ መርሳት የለባቸውም፡፡
ዮሐንስ በፍጥሞ በነበረበት ፈታኝ ሰዓት የተስፋና የማጽናኛ ቃል ይዞ ወደ እርሱ
የመጣው የሱስ፤ ሕዝቡ አስቸጋሪ ሁናቴ ሲገጥመው ለመደገፍ ብሎም ለመርዳት
በመካከላቸው ይሆናል፡፡
ስለ ክርስቶስ ሥቃይ በመቀበል እና የራሳችንን የተሳሳተ ምርጫ
ጨምሮ በሌላ ምክንያት ሥቃይ በመቀበል መካከል ያለውን ልዩነት
ማስተዋል የምንችለው እንዴት ነው? ወይስ ለማንኛውም ነገር ሥቃይ
መቀበል መልካም ጎን የለው ይሆን? በእያንዳንዱ ሁናቴ ጌታን መታመን
መማር የምንችለው እንዴት ነው?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 1፡10፣ ዘፀ. 31፡13፣ ኢሳ. 58፡13፣ ማቴ. 12፡8፡፡
በጥቅሶቹ
መሰረት የጌታ ቀን በሚል በግልጽ የተቀመጠው የትኛው ቀን ነው? ዮሐንስ
ባሳለፋቸው በእነዚያ የመከራ የግዞት ዘመናት ዕለቱ ምን ያህል ለእርሱ ትርጉም
ነበረው?
“የክብር ጌታ በግዞት ለነበረው ሐዋርያ የተገለጠው በሰንበት ዕለት ነበር፡፡ ዮሐንስ
በይሁዳ ከተሞችና መንደሮች ይሰብክ እንደ ነበረው በፍጥሞ ሰንበትን በቅድስና
ይጠብቅ ነበር፡፡ ዮሐንስ ስለዚያ ቀን የተሰጠውን የከበረ ተስፋ ሙሉ ለሙሉ አምኖ
የተቀበለ ሰው ነበር፡፡
”—Ellen G. White, The Acts of the Apostles, p. 581.
ሐዋርያው ዮሐንስ ራእዩን በሰባተኛው ቀን ሰንበት ስለ መቀበሉ ጥቅሱ ራሱ
በግልጽ ይናገራል፡፡ ምንም እንኳ ራእዩ እስከ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት ያሉ የወደፊት
ክስተቶችን አሻግሮ ቢቃኝም (ራእ. 1፡7) ነገር ግን ዮሐንስ የሚጠቅሰው እርሱ ራሱ
የወደፊቱን ክስተት የሚገልጸውን ራእይ የተቀበለበትንና በተጨማሪ “የጌታ ቀን”
(ኢሳ. 13፡6-13፣ 2ጴጥ. 3፡10) በሚል የሚታወቀውን የሰንበት ዕለት ነው፡፡
ዮሐንስ በዚያ አስከፊ ሁናቴ ውስጥ ሆኖ ከዳግም ምጽአቱ በኋላ እርሱና በዘመናት
ታማኝ ሆነው የኖሩ ወገኖች የሚኖሩትን ራእይ በሰንበት መመልከቱ፤ በመጠኑም ቢሆን
ከሥቃይ ነጻ የሆነውን ህይወት እንዲያጣጥም መርዳቱ እሙን ነው፡፡ እርግጥ ነው
ሰንበት በአይሁዳውያን እሳቤ የመጪው ዓለም ኦላምባ ወይም ቅድመ ልምድ ነው፡፡
“እግዚአብሔር በኤድን ገነት ያቋቋመው የሰንበት ቀን… በሰው ዐልባዋ ደሴት
ለነበረው ዮሐንስ የከበረ ዕለት ነበር፡፡
“በክርስቶስ ዐይን ሁሌም የከበረውና አሁን ደግሞ በዚህ ትዕይንት ተጨማሪ
ሞገስ ያገኘው ሰንበት--ብቸኝነት ያንከላውሰው ለነበረው ዮሐንስ እንዴት ያለ ዕለት
ሆኖለት ይሆን! ከዚያ በፊት እንዲህ ዓይነት ዕውቀት ስለ የሱስ ኖሮትም ሆነ ይህን
እውነት ሰምቶ አያውቅም፡፡”—Ellen G. White Comments, The SDA Bible
Commentary, vol. 7, p. 955.
በአራተኛው ትእዛዝ ዙሪያ በዘፀ. 20፡11 እና ዘዳ. 5፡15 የቀረቡትን ሁለቱን ሐተታዎች
ያመሳክሩ፡፡ ጥቅሶቹ እግዚአብሔር ፈጣሪያችንና ቤዛችን መሆኑን እያወሱ የፍጥረት
ብሎም የመዋጀታችን መታሰቢያ የሆነውን ሰባተኛውን ቀን ያስታውሱናል፡፡
እግዚአብሔር ፈጣሪያችንና አዳኛችን መሆኑን በተጨባጭ ተገንዝበን
እያንዳንዱን ሰንበት በተሻለ መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው? እግዚአብሔር
ፈጣሪያችን ከመሆን ውጪ አዳኛችን ባይሆን ኖሮ መልካምነቱ እንዴት
መገለጥ ይችል ነበር?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 1፡12-18፡፡
ዮሐንስ ክርስቶስን ያሳየበትን መንገድ በዳን. 10፡
5-6 ከቀረበው መለኮታዊ ባህሪ ጋር ያመሳክሩ፡፡ የሱስ በራእዩ የቀረበበት መንገድ
ምን ይመስላል? ምን እያደረገ ነው?
ዮሐንስ በልብሰ ተክኅኖ የተሸለመውን የሱስ በመቅረዞቹ መካከል ተመለከተ፡፡ ራእዩ
መቅረዞች ብርሃን የሚፈነጥቁበትን የጥንቱን የእስራኤል መቅደስ ያሳያል (1ነገሥ.
7፡49)፡፡ የሱስ በመቅረዞቹ መካከል መራመዱ እግዚአብሔር አምላካቸው ሆኖ
በመካከላቸው እንደሚመላለስ ለጥንት እስራኤላውያን የገባውን ኪዳን ያመለክታል
(ዘሌዋ. 26፡12)፡፡
በራእይ መጽሐፍ የቀረቡት መቅረዞች መልእክቱ በቀዳሚነት
የተጻፈላቸውን በእስያ ይገኙ የነበሩ ሰባቱን አብያተ ክርስቲያናት ይወክላሉ (ራእ.
1፡20)፡፡ የየሱስ በመቅረዞቹ መካከል መራመድ፡ ሕዝቡን ወደ ዘላለማዊው ቤት
እስኪያመጣ ድረስ ሁሌም ከእነርሱ ጋር እንደሚሆን ለእስራኤል የሰጠውን የተስፋ
ቃል ፍጻሜ ያመለክታል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የየሱስ በመቅረዞቹ መካከል መራመድ ከየሩሳሌም ቤተ መቅደስ
አምልኮአዊ ሥርዓት ጋር ትስስር አለው፡፡ መቅረዙ በቅዱሱ ስፍራ ፍንትው ብሎ
እንዲበራ ጥንቃቄ ማድረግ የካኅኑ ዕለታዊ ተግባር እንደ መሆኑ እያንዳንዱን
መቅረዝ በሚገባ አያስተካከለና ዘይት እየሞላ ብርሃን መስጠታቸው እንዳይቋረጥ
ይተጋል፡፡ ይህም ካህኑ የእያንዳንዱን መቅረዝ ሁናቴ በሚገባ እንዲያስተውል
ያስችለዋል፡፡ በተመሳሳይ የሱስ በእነዚያ አብያተ ክርስቲያናት ብቻ ሳይገደብ-ሁሉም የሚያስፈልጋቸውን ነገርም ሆነ የሚገኙበትን ሁናቴ በግል ያውቃል፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 2፡2፣9፣13፣19፣ 3፡1፣8፣15፡፡ “ዐውቃለሁ” የተሰኘው
ቃል የሱስ በእነዚህ አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ስላሉበት
ሁናቴም ሆነ ስለሚያስፈልጋቸው ነገር ዕውቀት እንዳለው ምን ይነግረናል?
የሱስ በእግዚአብሔር መገለጫ ማዕረግ የሚታወቀውን ሃረግ ራሱን ሲገልጥበት
ይስተዋላል “የፊተኛውም እኔ ነኝ፤ የኋለኛውም እኔ ነኝ” (ኢሳ. 44፡6፣ 48፡12)፡
፡ “የኋለኛው” የሚለው ቃል በግሪክኛው ኢሻቶስ “የዘመን መጨረሻ” የሚል
ፍቺ አለው፡፡ አባባሉ የመጨረሻው ዘመን ትኩረት--በመጨረሻዎቹ ክስተቶች
ላይ የመጨረሻ ቃል ባለቤት የሆነው የሱስ ክርስቶስ መሆኑን ያሳየናል፡፡
እርሱ
“ሕያው” ነው “የሞትና የሲኦል መክፈቻም” በእጁ ነው (ራእ. 1፡18)፡፡ ቁልፍ-የኃይልና የሥልጣን ተምሳሌት ነው፡፡ የጠፉት እንኳ በእርሱ ጥበቃና ጥንቃቄ ስር
እንደመሆናቸው የጌታ ታማኝ ተከታዮች አንዳችም ፍርሃት ሊያድርባቸው አይገባም፡
፡ እርሱ ለሙታን እንዲያ ከሆነ ታዲያ ለሕያዋን ምን ያህል የላቀ ይሆን! (ማቴ. 22፡
32)፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 1፡11፣ 19-20፡፡
እንዲሁም የሱስ በዮሐንስ አማካይነት በእስያ
ለነበሩት ሰባት ቤተ ክርስቲያኖች የተለየ መልዕክቶች ሰጥቶ ነበር፡፡ በአውራጃው
ከሰባት በላይ አብያተ ክርስቲያናት የመኖራቸው ሐቅ መልእክቱ በአጠቃላይ
ለክርስቲያኖች ያለውን ተምሳሌታዊ አንደምታ ምን ያደርገዋል?
ዮሐንስ ለሰባቱ ቤተ ክርስቲያኖች እንዲልክ በየሱስ የተሰጡት መልእክቶች በምዕ.
2እና 3 የሚገኙ ሲሆን ትርጉማቸውም በሦስት ቅደም ተከተሎች መተግበር ይችላል፡፡
ታሪካዊ አንደምታ፡ መልእክቶቹ በቅድሚያ የተላኩት በመጀመሪያው መቶ ክፍለ
ዘመን በእስያ ለነበሩ በምጣኔ ሐብት የበለጸጉ ከተሞች ነበር፡፡ በዚያ ይኖሩ የነበሩ
ክርስቲያኖች ብርቱ ተግዳሮቶች ገጥመዋቸዋል፡፡ ሕዝቡ ለሮም ልዕለ ኃያል መንግሥት
ታማኝነቱን ያሳይ ከነበረባቸው አስገዳጅ ሥርዓቶች አንዱና ዋንኛው በአረማውያን
ቤተ አምልኮ ለንጉሡ ይደረግ የነበረ ስግደት ነበር፡፡
በተጨማሪ ዜጎች በሕዝባዊ
ሥነ ስርዓቶችና በአረማውያን የባዕድ አምልኮ መርኅ ግብሮች ተሳትፎ ማድረግ
ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ ሆኖም አያሌ ክርስቲያኖች በዚህ አምልኮ ሥርዓት ተካፋይ
ለመሆን በመቃወማቸው ሥቃይ ይደርስባቸዋል፣ አልፎ አልፎም የሰማዕትነት ሞት
ለመቀበል ይገደዱ ነበር፡፡ እነዚህ ወገኖች ይገጥሟቸው ለነበሩ ፈታኝ ሁኔታዎች እገዛ
ይሆን ዘንድ በክርስቶስ የታዘዘው ዮሐንስ ሰባቱን መልዕክቶች ጸፈ፡፡
ትንቢታዊ አንደምታ፡ የራእይ መጽሐፍ ትንቢታዊነት እሙን ቢሆንም ነገር ግን
እነዚህን መልእክቶች እንዲቀበሉ የተመረጡት ሰባት ቤተ ክርስቲያኖች ብቻ ነበሩ፡
፡ ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ይገኙበት የነበረው መንፈሳዊ ሁናቴ በተለያዩ ዘመናት
ከኖሩ የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያኖች ጋር ስምሙ ነው፡፡ ሰባቱ መልእክቶች-በሰማያዊው ዕይታ ከመጀመሪያው ክፍለ ዘመን አንስቶ እስከ ምድር ታሪክ መዝጊያ
ያለውን የክርስትና ሁናቴ አጠቃላይ ቅኝት ለማሳየት ቀርበዋል፡፡
ዓለማቀፋዊ አንደምታ፡ ምንም እንኳ መልእክቱ በቀዳሚነት የተላከው በእስያ ለነበሩ
አብያተ ክርስቲያናት ቢሆንም፤ እነዚህ ሰባት መልእክቶች በተለያዩ ዘመናት ለሚገኙ
ክርስቲያኖች መተግበር የሚችሉ ትምህርቶችን ይዘዋል፡፡ በየቤተ ክርስቲያኖቹ እንደ
አንድ ደብዳቤ እንዲነበቡ ሆነውም ተልከዋል (ራእ. 1፡11)፡፡
በዚህ መልኩ በተለያዩ
ቦታዎችና ጊዜዎች የሚኖሩ የተለያዩ ክርስቲያኖችን ይወክላሉ፡፡ ለምሳሌ የዚህ ዘመኑ
ክርስትና አጠቃላይ ባህሪ በላውዶቅያ የሚጠቃለል ቢሆንም የአንዳንድ ክርስቲያኖች
መለያ ግን ከዚህ ውጪ ነው፡፡ የትኛውም ዓይነት መንፈሳዊ ሁናቴ ላይ ልንገኝ
ብንችል እንኳ ሰብዓዊው ፍጡር በሚኝገበት ሁኔታ እግዚአብሔር የሚገናኘው
መሆኑ መልካም የምስራች ነው፡፡”—Ellen G. White, Selected Messages,
book 1, p. 22.
ጌታ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያንዎ እየገጠሟት ስለሚገኙ ተግዳሮቶችና
መንፈሳዊ ሁናቴዋ ደብዳቤ ቢጽፍ የመልእክቱ ይዘት ምን ሊሆን ይችላል?
በዋንኛ የንግድ መናኸሪያ መስመር ላይ ትገኝ የነበረችው ኤፌሶን በሮም ስር
ትተዳደር የነበረችው የእስያ አውራጃ መዲና ነበረች፡፡ በእስያ ቀዳሚ የባህር ወደብ
መሆኗ ቁልፍ የንግድና የኃይማኖት ማዕከል አድርጓት ነበር፡፡ ከተማዋ በነዋሪዎቿ
ቤቶች፣ ቴያትር ቤቶች፣ ጂምናዚየሞች፣ መታጠቢያ እና ግልሙትና ቤቶች የተሞላች
ነበረች፡፡ ኤፌሶን በአስማት እና በሥነ ጥበብ የታወቀች ነበረች፡፡ በተጨማሪ
ከተማዋ የብልሹ ሥነ ምግባር አጉል ስምና ዝና ቢኖራትም፤ የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን
በአውራጃው ብርቱ ተጽእኖ ነበራት፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 2፡1-4፣ ኤር. 2፡2፡፡ የሱስ ራሱን ለዚህች ቤተ ክርስቲያን
ያቀረበበት መንገድ ምን ይመስላል? ምስጋናውን እንዲቸር ያደረገው ላቅ ያለ ተግባር
ምንድን ነው? ሥጋቱስ?
ቀደም ባሉት ቀናት ኤፌሶናውያን በታማኝነታቸውና በፍቅራቸው ይታወቁ ነበር
(ኤፌ. 1፡15)፡፡ ምንም እንኳ ከቤተ ክርስቲያን ውጪም ሆነ ከውስጥ ጫና እና
ግፊት ቢበረታባቸውም እነርሱ ግን በጽናትና በታማኝነት መዝለቅ ችለው ነበር፡፡
የኤፌሶን ክርስቲያኖች ጠንካራ ሠራተኞችና ያልተበረዘውን ኃይማኖታዊ አስተምህሮ
የሚከተሉ እንደመሆናቸው በሐሰተኛ ምሁራንን ላይ የነበራቸው አቋም ጽኑ ነበር፡፡
ሆኖም አግባብ ላለው አስተምህሮ አጽንኦት የሚሰጡና ለቀጥተኛው እምነት ብሎም
አስተሳሰብ ገጣሚ ባህሪ ቢኖራቸውም፤ ለክርስቶስ እና ለእምነት ተጓዳኞቻቸው
የነበራቸው ፍቅር ግን እየተዳከመ መሄድ ጀመረ፡፡ ምንም እንኳ ሕዝቡ በእምነቱ
ጥብቅና ታማኝ ቢሆንም፤ ያ ፍቅር የሌለበት ሥራቸው ቀዝቃዛና ሕግ ጠባቂ ብቻ
አድርጎአቸው ቀረ፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 2፡5-7፡፡ የዚህች ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን የቀደመው
የእርስ በርስ ፍቅራቸውና ለክርስቶስ የነበራቸው ታማኝነት ዳግም ሕይወት ይዘራ
ዘንድ የሱስ አጥብቆ ያስገነዘባቸው ሦስት ነገሮች ምንድን ናቸው? እነዚህ ሦስት
ነጥቦች እንደየ ቅደም ተከተላቸው ያላቸው ዝምድና ምንድን ነው?
ከትንቢቱ አኳያ በኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን የተስተዋለው ሁናቴ በመጀመሪያው
ክፍለ ዘመን ከነበረችው ቤተ ክርስቲያን አጠቃላይ መንፈሳዊ ገጽታ ጋር ተመሳሳይ
ነው፡፡ የቀደመችው ቤተ ክርስቲያን በፍቅሯና ለወንጌል በነበራት ታማኝነት ትታወቅ
ነበር፡፡ ሆኖም በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ ቤተ ክርስቲያኗ
ከወንጌል ንጽህናና ግልፅነት እየራቀች በመሄዷ የቀደመውን የሞቀ ፍቅሯን ማጣት
ጀመረች፡፡
ፍቅሩ እየደበዘዘና እየተዳከመ ይሄድ እንደ ነበረው የዚያ ጉባዔ አባል
አድርገው ራስዎን ያስቡ፡፡ በእርግጥ አባላት ምንም ዓይነት የሚታወቅ
ወይም ግልጽ ኃጢአት ላይሠሩ ይችላሉ፡፡ በአንድ በኩል ትክክል የነበረውን
ነገር እያደረጉ ቢሆንም በሌላ በኩል ግን ቀዝቃዛና ፊደላውያን ብቻ የመሆንን
ቁልቁለት ተያይዘውት ነበር፡፡ የሱስ በዚህ ቦታ የሰጠው ምክረ ሃሳብ ቤተ
ክርስቲያንን ከዚህ ሁናቴ ነፃ ማድረግ የሚችለው እንዴ ነው?
Read Ellen G. White, “Patmos,” pp. 568–577, in The Acts
of the Apostles.
“በዮሐንስ ላይ የደረሰው ስደት የአምላካዊው ጸጋ ዓይነተኛ መንገድ ለመሆን በቃ
፡፡ የትንሳዔ ባለቤት የሆነው የአዳኙ ክብር ፍጥሞን አንጸባራቂ አደረጋት፡፡ ዮሐንስ-የእጆቹና የእግሮቹ ጠባሳ ክብሩ የሆነውንና ለዘላለም አብሮት የሚኖረውን ክርስቶስ
ቀደም ብሎ ተመልከቶት እንደ ነበር ሁሉ፤ አሁን ደግሞ ሰብዓዊው ዐይኖች እርሱን
ተመልክተው በሕይወት መቀጠል የሚችሉትን ያህል ክብር የተጎናጸፈውን የትንሳዔ
ባለቤት ጌታውን እንዲመለከት ተፈቀደለት፡፡
“ለዮሐንስ የተገለጠውና በተጨባጭ የቀረበው ከሞት የተነሳው ክርስቶስ ማስረጃ
ለሐዋርያው ብቻ ሳይሆን ለመላው አማኝም ሆነ ኢአማኒ ሊሆን ይገባል፡፡
ለቤተ ክርስቲያን ሕያው ኃይል ሊያጎናጽፋት ይገባል፡፡ አንዳንዴ ጭቆናና ስደት
የእግዚአብሔርን ሕዝቦች ከምድረ ገጽ የሚያጠፋቸው እስኪመስል ድረስ በድቅድቅ
ጨለማ ደመናዎች እስከ መዋጥ የደረሱባቸው ጊዜያቶች ነበሩ፡፡ ሆኖም በእነዚህ
ጊዜያቶች ውስጥ በዓይነታቸው ልዩ የሆኑና አማኞችን የሚያንጹ ትምህርቶች
ተሰጥተዋል፡፡ ክርስቶስ በተደጋጋሚ ወህኒ እየገባ ራሱን ለተመረጡ ወገኖች
ገልጦአል፡፡ ወደ እሳት የመጣል አደጋ ሲገጥማቸው አብሮአቸው አለ፡፡ የከዋክብት
ብርሃን ድቅድቁን ሌሊት ወገግ እንደሚያደርግ ሁሉ፤ ጨፍጋጋ በሆነው ሁናቴ እጅግ
ደማቅ አምላካዊ ጨረሮች ተገልጠዋል፡፡ ሰማዩ በጨለመ ቁጥር የትንሣኤው አዳኝ
የጽድቅ ፀሐይ ጨረሮች አብልጠው ግልጽና መሳጭ ይሆናሉ፡፡”—Ellen G. White,
The Youth’sInstructor, April 5, 1900.
1.ባለ ራእዩ ዮሐንስ በፍጥሞ የተመለከተውንና የሰማውን ለአንባቢዎቹ
ያጋራል፡፡ እርስዎ በራእ. 1፡12-20 የሚመለከቱትና የሚሰሙት ነገር
ምንድን ነው? በዚህ ከተገለጠ መልእክት ምን ዓይነት የመጽናኛ ቃላት
ማግኘት ይችላሉ?
2.በመጨረሻው ዘመን የሚገኙ የምድር ሕዝቦች “ሰማይንና ምድርን፣
ባሕርንና የውሃ ምንጮችን ለፈጠረው” ይሰግዱ ዘንድ የመጀመሪያው
መልአክ በራእ. 14፡7 አጥብቆ ያስገነዝባል፡፡ ይህ አነጋገር ከዘፀ.
20፡11 የተወሰደ ነው፡፡ በራእይ መጽሐፍ በተገለጠው መሰረት
ይህ በመጨረሻው ዘመን ስለ ሰንበት በተሰጠው አጽንኦት ዙሪያ ምን
ይነግረናል?
3.አያሌ ክርስቲያኖች እየተጋፈጡት ያለ ዕንግዳ ምጸታዊ ነገር ያለ ሲሆን
ይኸውም ሰዎች በቤተ ክርስቲያን በቆዩ ቁጥር እምነታቸው እየመነመነ
ይሄዳል ወይም ከነአካቴው ይጠፋል፡፡ ይህ በእርግጥ መሆን የነበረበት
በተቃራኒው ነበር፡፡ ከየሱስ ጋር አብልጠን በተጓዝን ቁጥር ስለ እርሱ
አብልጠን ልንማርና ለእኛ ያለውን ፍቅር ልናውቅ የግድ ነው፡፡ ታዲያ
የእምነት እሳት መንደድ ብቻ ሳይሆን ይበልጥ እየተንቀለቀለ እንዲሄድ
ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?