ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ራእ. 14:6–12፣ ማቴ.
24:14፣ መክ. 12:13-14፣ ዘፀ. 20:2–11፣ ኢሳ. 21:9፣ 34:8–10፡፡
መታሰቢያ ጥቅስ :-“የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁና ለኢየሱስም ታማኝ ሆነው በትዕግሥት የሚጸኑ ቅዱሳን የሚታወቁት በዚህ ነው”(ራእ.14፡12)።
በ
መጨረሻው ጊዜ ሰይጣን በማሳት ሥራው ውጤታማ እንደሚሆንና ዓለም
ለአውሬው ለመሥገድና ምልክቱን ለመቀበል እንደሚመርጥ የራእይ መጽሐፍ
ያሳየናል፡፡ ሆኖም እግዚአብሔር ከአብዛኛው የዓለም ሕዝብ በተቃራኒ ለጌታ
የሚቆሙ ትሩፋን እንደሚኖሩት ራእ. 14፡1-5 ይናገራል፡፡ ሰዎች ሁሌም አምልኮ
ቢያደርጉም ነገር ግን በመጨረሻ ላይ ማንን ማምለክ እንዳለባቸው ሊመርጡ የግድ
ይሆናል፡፡ ለአውሬው የሚሠግዱ በአእምሮአቸውና በድርጊታቸው ይህን ክህደት
የፈጸመ ሥርዓት ለማገልገል የመምረጣቸው ምሳሌ የሆነውን ምልክት በግምባራቸው
ወይም በቀኝ እጃቸው ይቀበላሉ፡፡
በተመሳሳይ ወቅት ከጴንጤቆስጤ ዕለት ወዲህ ታይቶም ሆነ ተሰምቶ ለማይታወቅ
የወንጌል ዕወጃ ዓለም ምስክር ይሆናል፡፡ አምላካዊው ፍርድ በዐመጸኛው ሰብዓዊ
ፍጡር ላይ ከመውረዱ አስቀድሞ እግዚአብሔር የማስጠንቀቂያ መልእክቱን
ይልካል፡፡ ሰይጣን ሥራውን በዓለማቀፍ ደረጃ እንደሚያፋፍም ሁሉ የመጨረሻው
ዘመን የወንጌል ዕወጃም እንደዚያው ይሆናል፡፡ የእግዚአብሔር ፍላጎት አንድም ሰው
እንኳ እንዲጠፋ ሳይሆን ነገር ግን ሁሉም እንዲድን በመሆኑ እነሆ ክርስቶስ ስለ
ሰብዓዊው ዘር መሥዋዕት ሆነ፡፡ ይህን ስጦታ ማን ይቀበላል ማንስ ይቃወማል-የሚለው ነው አንገብጋቢው ጉዳይ፡፡
የምድር መጨረሻ ሊደርስ ጥቂት ጊዜ ሲቀር እግዚአብሔር በሰማይ መካከል
በሚበሩት በሦስቱ መላእክት ተምሳሌት የቀረበውን የማስጠንቀቂያ መልእክቱን
ይልካል፡፡ በግሪክኛ መልአክ (angelos) የተሰኘው ቃል እንደ አማርኛው ሁሉ
“መልእክተኛ” የሚል ትርጉም አለው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ መልአክ መልእክተኛን
ወክሎ ሲቀርብ ይታያል (ሚልክ. 2፡7፣ ማቴ. 11፡10)፡፡ ሦስቱ መላእክት ለዓለም
የሚያካፍሉት የመጨረሻው ጊዜ መልእክት የተሰጣቸውን የእግዚአብሔር ሕዝቦች
እንደሚወክሉ ከራእይ መጽሐፍ የሚገኙ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 14፡6፣ ማቴ. 24፡14፡፡ የመጀመሪያው መልአክ መልእክት
“የዘላለም ወንጌል” (ራእ. 14፡6) በሚል ማጣቀሻ ቀርቦአል፡፡ ይህ ሁኔታ ስለ
መጀመሪያው መልአክ መልእክት ይዘትና ዓላማ ምን ይነግረናል? ይህ መልእክት
የሁሉም የእምነታችን ክፍል አስኳል የሆነው ለምንድን ነው?
የመጨረሻው ጊዜ--የመጀመሪያ መልእክት ወንጌል ነው፡፡ ወንጌል ሰብዓዊውን
ፍጡር በመስቀል ስላዳነው አምላክ--የሱስ ክርስቶስ የሚተርክ የምሥራች ነው።
የመጀመሪያው መልአክ መልእክት “ዘላለማዊ” ወንጌል የሆነበት ምክንያት፤
የወደቀውን ሰብዓዊ ዘር ወደ ቀድሞው ንጽህና ለመመለስ እየተደረገ ያለ
የእግዚአብሔር የማያቋርጥ ጥረት አካል በመሆኑ ነው፡፡ እንደውም ከመፈጠራችን
አስቀድሞ የተጠነሰሰ እቅድ ነው (2ጢሞቴ. 1፡9፣ ቲቶ 1፡2)፡፡ ወንጌል ደኅንነትን እና
ፍርድን በአንድ አካትቶ ይዞአል፡፡ ለሚቀበሉት የሚድኑበት መልካም የምሥራች፤
የሚሰጠውን ተስፋ ለሚቃወሙ ደግሞ የፍርድ ማስጠንቀቂያ ይዞአል፡፡
ሦስቱ መላእክት መልእክቱን “በታላቅ ድምፅ” ማወጃቸው ተገልጾአል (ራእ.
14፡7፣9)፡፡ የሰብዓዊውን ፍጡር ዘላማዊ መዳረሻ የሚወስነው ይህ መልእክት
አስቸኳይና እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ለሁሉም ጆሮ መድረሱ የግድ ይሆናል።
በዚህም ለሕዝብ፣ ለነገድ፣ ለቋንቋ እንዲሁም ለወገን መሰበክ ይኖርበታል፡፡
በመጨረሻው ዘመን አውሬው በሰይጣን ውክልና የተሰጠውን ሥልጣን በነገድ፣
በወገን፣ በቋንቋና በሕዝቡ ሁሉ ላይ (ራእ. 13፡7) እንደሚለማመድ ከተበረከተልን
ብርሃን አኳያ መመልክታችን በእጅጉ ወሳኝ ነው፡፡ የሰይጣን አሳች እንቅስቃሴዎች
በዓለም ዙሪያ ሲንሰራፉ የመጨረሻው ዘመን የወንጌል ዕወጃ ገቢራዊ ይሆናል፡፡
ከሰይጣናዊው ሦስትዮሽ ኅብረት (ሐሰተኛ ሥላሴ) አፍ የሚወጡትን እንቁራሪት
መሳይ እርኩሳን መናፍስት በመቃወም የሦስቱ መላእክት መልእክት በእግዚአብሔር
ሕዝቦች ይሰበካል (ራእ. 16፡13-14)፡፡ መልእክቶቻቸው ለሦስቱ መላእክት መልእክት
የተመቻቹ ሐሰተኛ የመልስ ምቶች ይሆናሉ፡፡ በዚህ የተነሳ በመጨረሻው ዘመን
ሕዝቦችን ለየራሳቸው ታማኝ ለማድረግ ባለሙ ኃይላት አማካይነት ዓለም የሁለት
ባላንጣዎች መልእክት ይቀርብላታል፡፡
እኛ እንደ ሰባተኛ ቀን የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂነታችን ዓለምን በወንጌል
እንድንደርስ ጥሪ ቀርቦልናል፡፡ ይህን ጥሪ ከዳር ለማድረስ እርስዎ ምን
እያደረጉ ነው? አሁን እያደረጉ ካለው በተጨማሪ ምን ማበርከት ይችላሉ?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 14፡7፣ መክ. 12፡13-14፡፡ “እግዚአብሔርን ፍሩ” ማለት
ትርጉሙ ምንድን ነው? እግዚአብሔርን የመፍራት ጽንሰ ሃሳብ ከወንጌል ጋር
እንዴት ይዛመዳል? ወንጌል የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ከመጠበቅ ጋር ያለው
ተዛምዶ ምንድን ነው? (ሮሜ. 7፡7-13)፡፡ እግዚአብሔርን በመፍራትና ለእርሱ ክብር
በመስጠት መካከል ያለው ግንኙነትስ እንዴት ይገለጻል?
“‘እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ክብርም ስጡት’” (ራእ. 14፡7) የተሰኘው ጥሪ የቀረበው
ከ “ዘላለማዊው ወንጌል” እወጃ ዐውድ ነው፡፡ ክርስቶስ ለእኛ መዳን ያደረገውን
መገንዘብ መቻላችን ለእርሱ አዎንታዊ ምላሽ ያስገኝለታል፡፡
በራእይ መጽሐፍ--እግዚአብሔርን መፍራትና ለእርሱ ክብር መስጠት ውሁድ ጽንሰ
ሀሳቦች ናቸው (ራእ. 11፡13፣ 15፡4)፡፡ የመጀመሪያው--ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖርን
ትክክለኛ ግንኙነት ሲያሳይ (ኢዮ. 1፡8) ቀጣዩ ደግሞ እርሱን መታዘዝ እንደሚገባ
ያመለክታል፡፡ እግዚአብሔርን ፍሩ ማለት--በሥጋትና በጥበት ኑሩ ከሚለው ሃሳብ
በተቃራኒ አምላካዊውን ጉዳይ እንደው በዋዛና በፈዛዛ ሳይሆን በጽኑ ወይም የምር
አርጋችሁ ያዙት፣ በሕይወታችሁም ሕጋዊ የባለቤትነት ስፍራ ስጡት--የሚል
አንደምታ አለው፡፡ የእግዚአብሔር የመጨረሻው ዘመን ሕዝቦች እርሱን የሚፈሩ
ይሆናሉ (ራእ. 11፡18፣ 19፡5)፡፡ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው እርሱን በመታዘዝ
(ዘዳ. 5፡29፣ መክ. 12፡13) እና ባህሪውን በማንጸባረቅ ያከብረዋል (ዘፍ. 22፡12)፡፡
እግዚአብሔርን እንድንፈራና ለእርሱ ክብር እንድንሰጥ የሚያነሳሳን የፍርዱ ሰዓት
መድረሱ ነው (ራእ. 14፡7)፡፡ እዚህ ላይ የቀረበው ፍርድ ከዳግም ምጽአቱ ቀደም
ብሎ ያለው ፍርድ ነው፡፡ የቅድመ ምጽአቱ ፍርድ ዓላማ እግዚአብሔርን በእውነት
እያገለገልን መሆን አለመሆኑን በመጨረሻው ምርጫችን ማሳየት ነው (በሥራችን
የምንገልጸው ምርጫ)፡፡ በፍርዱ መደምደሚያ የእያንዳንዱ ሰው የመጨረሻ መዳረሻ
ይወሰናል (ራእ. 22፡11)፡፡ ከዚያም የሱስ ለእያንዳንዱ ሰው እንደ ሥራው ሊከፍለው
ዳግም ይገለጣል (ራእ. 22፡12)፡፡
በራእ. 14 የቀረበው ፍርድ የወንጌል አካል ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር በትክክለኛ
ግንኙነት ላሉ ፍርድ ማለት--ነፃ መውጣት፣ መዳን እና ነፃነትን መቀዳጀት እንደ
መሆኑ ለእነርሱ መልካም የምስራች ነው፡፡ ሆኖም ታማኝ ላልሆኑት ግን መጥፎ ዜና
ነው፡፡ ከፊታችን ያለው የፍርድ መልእክት እነዚህ ወገኖች በንስሐ ወደ እግዚአብሔር
እንዲመለሱ የቀረበ ጥሪ ነው፡፡ ሁሉም በንስሐ እንዲመጡ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ
የእግዚአብሔር ፍላጎት ነው (2ጴጥ. 3፡9)፡፡
በፍርድ ወንበር ፊት ብቻዎን መቆም የሚችሉት እንዴት ነው?
ሥራዎችዎ ለየትኛው ፍርድ ዋስትና ሊሆንዎ ይችላሉ? መልስዎ
ስለ ወንጌል አስፈላጊነት ምን ይነግሮታል? ከመጀመሪያው መልአክ
መልእክት ጋር እንዲህ በቅርበት የተቆራኘው ለምንድን ነው?
የእግዚአብሔርን ትእዛዛት መጠበቅ በሚል እንደ ተገለጠው (ራእ. 14፡12) በምድር
ታሪክ መዝጊያ ለሚከሰተው ቀውስ ዋንኞቹ ጉዳዮች አምልኮ እና እግዚአብሔርን
መታዘዝ ይሆናሉ (ራእ. 14፡12)፡፡ የዓለም ሕዝቦች በሁለት ቡድን ይከፈላሉ፡
እግዚአብሔርን የሚፈሩና እርሱን የሚያመልኩ እንዲሁም እግዚአብሔርን የሚፈሩና
ለአውሬው የሚሰግዱ፡፡
የዐሥርቱን ትእዛዛት የመጀመሪያ ክፍሎች ደግመው ይቃኙና (ዘፀ. 20፡2-11)
በመቀጠል ወደ ራእ. 13 ያምሩ፡፡ አውሬው እንዲመለክ የሚጠይቅበት መንገድ (ራእ.
13፡15)፤ አውሬው የሚመለክበትን ምስል ማቆሙ (ራእ. 13፡14-15)፣ እግዚአብሔርንና
የእርሱን ስም መስደቡ (ራእ. 13፡5-6)፣ እንዲሁም ሰዎች የአውሬውን ምልክት
መቀበላቸው (ራእ. 13፡16-17)--እነዚህ ሁሉ ሰይጣን በመጀመሪያዎቹ አራት ትእዛዛት
ላይ የፈጸመውን ጥቃት እንዴት ያመላክታሉ?
የዐሥርቱ ትእዛዛት አካል የሆኑት የመጀመሪያዎቹ አራት ትእዛዞች ያላቸው ዝምድና
ከአምልኮ ጋር ነው፡፡ እነዚህ ትእዛዞች በመጨረሻው ቀውስ ወቅት ለእግዚአብሔር
የሚኖረን ታማኝነት መለኪያ እንደሚሆኑ የራእይ መጽሐፍ ይገልጥልናል፡
፡ በክርስቶስና በሰይጣን መካከል የሚደረገው የመጨረሻው ውዝግብ በግልጽ
የሚያጠነጥነው በአምልኮና በመጀመሪያዎቹ አራት ትእዛዛት ዙሪያ ይሆናል፡፡
በመጨረሻው ቀውስ ወቅት አጽንኦት የተሰጠው ቁልፍ ጉዳይ የመጀመሪያው
መልአክ መልእክት ልባዊ ምክር ነው፡፡ “‘ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንና የውሃ
ምንጮችን ለፈጠረው ስገዱ’” (ራእ. 14፡7) በሚል የቀረበው ጥሪ የዐሥርቱ ትእዛዛት
አካል የሆነውን አራተኛ ትእዛዝ በተዘዋዋሪ ይነካል (ዘፀ. 20፡11)፡፡ ፈጣሪ የሆነው
እግዚአብሔር አምላክ እንዲመለክ የቀረበው ጥሪ ሰንበትን በመጠበቅ ዐውድ
መሰጠቱን ከዚህ እንመለከታለን፡፡
በዐሥርቱ ትእዛዛት እንዲሁም በተቀረው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንደ ተወሳው፤
እውነተኛ አምልኮ ከትክክለኛው የአምልኮ ቀን ጋር ዝምድና አለው፡፡ ሰባተኛው
ቀን ሰንበት ከእግዚአብሔር ጋር ላለን ግንኙነት የተለየ ምልክት ነው (ዘፀ. 31፡13፣
ሕዝ. 20፡12)፡፡ በመጨረሻው ጊዜ የዓለም ሕዝቦች እውነተኛ ፈጣሪ ወደ ሆነው
አምላክ እንዲመለሱና የሕይወታቸውን የባለቤትነት ስፍራ እንዲሰጡት ጥሪ
እንደሚቀርብላቸው የመጀመሪያው መልአክ መልእክት ያሳየናል፡፡ ይህ መልእክት
ሰይጣን በመጨረሻው ጊዜ ዓለምን ወደ ሐሰተኛ ኃይማኖትና እውነት መሳይ አምልኮ
በመሳብ በሚሠራቸው የማታለያ ተግባራት ላይ ተግዳሮት ይኖረዋል፡፡ የዚህ ጉዳይ
አስኳል አራተኛው ትእዛዝ የሆነው ሰባተኛው ቀን ሰንበት ይሆናል፡፡
“ሐሰተኛውን ሰንበት ማክበር ከአራተኛው ትእዛዝ በተቃራኒ ከመንግሥታዊው
ሕግ ጋር እንድናብርና እግዚአብሔርን በመቃወም ለቆመው ኃይል ታማኝነትን
ማጽናት ይሆናል፡፡ የእግዚአብሔርን ሕግ በመታዘዝ እውነተኛውን ሰንበት
መጠበቅ፤ ለፈጠረን አምላክ ያለንን ታማኝነት የምናሳይበት ተጨባጭ ማስረጃ
ነው። አንደኛው አጋማሽ ራሱን ለምድራዊው ኃይል በማስገዛት የአውሬውን ምልክት
ሲቀበል፤ የተቀረው በመለኮታዊው ሥልጣን ስር በታማኝነት መዋልን በመምረጥ
የእግዚአብሔርን ማኅተም ይቀበላል፡፡”—Ellen G. White, The Great Controversy, p. 605.
የመጀመሪያው መልአክ ሰዎች እግዚአብሔርን እንዲፈሩና እውነተኛውን አምላክ
እንዲያመልኩ ጥሪ ሲያቀርብ፤ ሁለተኛው ደግሞ ሐሰተኛ ኃይማኖታዊ ተቋም
የሆነችውን ባቢሎን መጨረሻ ይፋ ያደርጋል፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 14፡8፣ 18፡1፣ ኢሳ. 21፡9፡፡ “ወደቀች” በሚል ሁለት ጊዜ
ተደጋግሞ የቀረበው ይህ ቃል የመጨረሻውን ጊዜ የባቢሎን ውድቀት እርግጠኝነት
ያመላክታል፡፡ ምንም እንኳ የባቢሎን ውድቀት ገና ወደፊት የሚጠበቅ ቢሆንም ነገር
ግን ተቋሟ ካሁኑ እንደ ወደቀች ሆና የቀረበችበት ምክንያት ምንድን ነው?
እዚህ ላይ ባቢሎን በታላቅ ከተማነት ቀርባለች፡፡ ለዚህ ምክንያቱ በራእይ መጽሐፍ
በምሳሌ የተጠቀሰችው ባቢሎን የተወሰደችው በታሪክ እግዚአብሔርን ስትቃወምና
ሕዝቡን ስትጨቁን የኖረችውን ከሐዲ ሥረ መሰረት ተከትሎ በመሆኑ ነው፡፡ ኢሳ.
14፡12-15 ባቢሎንን ከሰይጣን ጋር እኩል አድርጎ በማቅረብ ራሷን ከእግዚአብሔር
ጋር ለማስተካከል ያደረገችውን ሙከራ ያሳየናል፡፡
በዘመን መጨረሻ በራእይ
መጽሐፍ የተከሰተችው ባቢሎን ሐሰተኛውን ሥላሴ ከሌሎች ክህደት የፈጸሙ
ኃይማኖቶች ጋር አጣምራ ይዛለች (ራእ. 17፡5)፡፡ እነዚህ በክህደት ውስጥ የሚገኙ
ኃይማኖታዊ ተቋሞች ከእግዚአብሔር ሕዝቦች በተቃራኒ እየሠሩ ማንነታቸውን
ለሰይጣን አገልግሎት ያውላሉ (ራእ. 13፡11-18)፡፡ ክህደት የፈጸመው ኃይማኖታዊ
ኅብረት ራሱን ከእግዚአብሔር በላይ ከፍ ከፍ እያደረገና ጌታ በዚህ ምድር ያለውን
ስፍራ ለመውሰድ እየተመኘ የጥንቷን ባቢሎን ዕብሪተኝነት በይፋ ያሳያል፡፡ እንደ
ጥንቷ ባቢሎን ሁሉ ይህ የረከሰ አምልኮአዊ ተቋምም በተመሳሳይ እንደሚያከትምለት
የሁለተኛው መልአክ መልእክት ለእግዚአብሔር ሕዝቦች ማረጋገጫ ይሰጣል፡፡
ጥቅሶቹን በድጋሚ ያንብቡ፡ ራእ. 14፡8፣ 17፡2፣ 18፡3፡፡ ባቢሎን የምንዝሯን ወይን
ጠጅ ለዓለም የምታጠጣው እንዴት ነው? የዚህ ወይን አንደምታስ ምንድን ነው?
ባቢሎን የቁጣዋን ወይን ጠጅ ለምድር ነዋሪዎች በማጠጣቷ ተወንጅላለች፡፡ ሕዝቦች
ከባቢሎን የወይን ጠጅ እንደ ጠጡና እንደ ሰከሩ ኤርምያስ ይናገራል (ኤር. 51፡7)፡፡
የዘመን መጨረሻዋ ባቢሎን የምድር ሕዝቦችን በምንዝሯ ወይን ጠጅ የምታሰክርበትን
ትዕይንት ራእ. 17 ይሰጠናል (ራእ. 17፡2)፡፡ ይህ ደግሞ ሰይጣናዊው ሥላሴ የምድር
ሕዝቦች ለአውሬውና ለምስሉ እንዲሰግዱ (ራእ. 13፡11-18) ወደሚያባብልበት ራእ.
13 ይወስደናል፡፡
የባቢሎን የወይን ጠጅ በዚህች ክህደት የፈጸመች ኃይማኖታዊ ተቋም የሚሰጠውን
ሐሰተኛ አስተምህሮ እና ወንጌል ይወክላል፡፡ በስካር ውስጥ ያሉ ሰዎች ራሳቸውን
መቆጣጠር ስለሚሳናቸው በትክክል ማሰብ አይችሉም፡፡ ሰዎች በባቢሎን የወይን
ጠጅ መንፈሳዊ ስካር ስር ሲውሉ፤ ኅሊናቸው ለአውሬው ለመስገድም ሆነ
ምልክቱን ለመቀበል ይማልላል፡፡ የአስተሳሰብ አድማሳቸውን አነሁልሎ የነበረው
ስካር ሲለቃቸው፤ ውሳኔዎቻቸውንና ድርጊቶቻቸውን ለማጤን ቢሞክሩም ጊዜው
ረፍዶአል (ራእ. 17፡15-17)፡፡
አንድ ሰው የባቢሎንን ወይን ጠጅ ለመጠጣት ባቢሎን ውስጥ መኖሩ
የግድ ይሆናል? ለመሆኑ ከባቢሎን የወይን ጠጅ የሚጠጣው እንዴት
ነው?
የእግዚአብሔር ታማኝ ሕዝቦች በራእ. 14፡12 የቀረቡበት መንገድ ምን ይመስላል?
ከእነዚህ ሕዝቦች በተቃራኒ የእግዚአብሔርን ቁጣ ስለሚቀበሉ ሰዎች አስመልክቶ
ራእ. 14፡9-10 ማስጠንቀቂያ ይሰጣል፡፡ የእግዚአብሔርን ቁጣ የወይን ጠጅ ስለ
መጠጣት የሚገልጽ ተምሳሌታዊ አባባል በብሉይ ኪዳን ቀርቦአል (ኤር. 25፡15-16)፡
፡ ለአውሬው በሚሰግዱ ላይ የሚኖረው የፍርድ ጽናት--ምንም ያልተቀላቀለበትን
የእግዚአብሔር ቁጣ የወይን ጠጅ ጽዋ መጠጣት በሚል ተገልጾአል፡፡
በጥንት
ዘመን የወይን ጠጅ ሲጠነክር በውሃ ተበርዞ የማስከር ኃይሉ እንዲቀንስ ሲደረግ፤
በተቃራኒው የማስከር ኃይሉ እንዲጨምር ደግሞ ልዩ ልዩ እጸዋትና ቅመማ ቅመሞች
ጣል ይደረጉበት ነበር፡፡ በእግዚአብሔር ቁጣ የወይን ጠጅ የተሞላው ይህ ጽዋ
ምንም አልተቀላቀለበትም ማለት ምኅረቱ አልገባበትም የሚል ፍቺ አለው (መዝ.
75፡8)፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 14፡10-11፣ 20፡10-15፡፡ “ ‘የሥቃያቸውም ጢስ ከዘላለም
እስከ ዘላለም ወደ ላይ ይወጣል’ ” በተሰኘው አባባል ላይ ኢሳ. 34፡8-10 እና ይሁዳ
7 የሚፈነጥቁት ብርሃን ምን ይመስላል?
እሳት እና ዲን የሚካተቱበት መግለጫ አጠቃላይ ውድመትን ይጠቁማል፡፡ እሳት
እና ዲን ፍርድ የሚሰጥበት መንገድ ነው (ዘፍ. 19፡24፣ ኢሳ. 34፡8-10)፡፡ ወደ ላይ
እየተትጎለጎለ የሚወጣው የውድመት ጢስ በመጽሐፍ ቅዱስ የሚታወቅ ትዕይንት
ነው፡፡ ወደ ፊት በእሳት እና በዲን ስለሚደርሰው ውድመት አስመልክቶ ኢሳይያስ
እንዲህ ይላል “እሳቷ ሌሊትና ቀን አይጠፋም፤ ጢሷም ለዘላለም ይትጎለጎላል” (ኢሳ.
34፡10)፡፡ ይሁዳ ሰዶምና ገሞራ ስለደረሰባቸው ጽኑ ቅጣት ሲናገር “በዘላለም እሳት”
(ይሁዳ 7) ተቃጡ ይለናል፡፡ ዛሬ በዘላለም እሳት እየነደደ የሚገኝ ስፍራ እንደ ሌለ
ሁሉ እነዚህም ጥቅሶች ማብቂያ ስለሌለው ቃጠሎ አይናገሩም፡፡ ዘላለማዊ የሆነው
እሳቱ ሳይሆን ውጤቱ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ “ዘላለማዊ እሳት” ድምጥማጡን
ማጥፋት የሚል ፍቺ አለው፡፡ እሳት ለፈጀው ምን ይበጀው እንዲሉ የእሳቱ ቃጠሎ
ምንም ዓይነት ነገር ሳያስቀር ሁሉንም በልቶ ይጨርሳል፡፡
ምንም እንኳ የገሐነም እሳት የጠፉትን ለዘላለም ሲያሰቃይ አይኖርም
የሚለውን እውነት በማስተዋላችን አመስጋኝ ብንሆንም--ቅጣቱ እጅግ
አሰቃቂ ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም፡፡ ስለሚመጣው ፍርድ
ሌሎችን ማስጠንቀቅ እንደሚኖርብን አስመልክቶ በተጣለብን የተቀደሰ
ብርቱ ኃላፊነት ዙሪያ ይህ ምን ሊነግረን ይገባል?
Read Ellen G. White, “The Final Warning,” pp. 603–612,
in The Great Controversy.
የእግዚአብሔር ሕዝቦች የመጨረሻውን ጊዜ ወንጌል ለዓለም የሚያውጁበት
ተልዕኮ እንደተሰጣቸው የራእይ መጽሐፍ ያሳየናል፡፡ ከፊት ለፊታችን የሚጠብቀን
ሥራ ተስፋ አስቆራጭና የማይቻል ቢመስልም ነገር ግን አምላካዊው ተስፋ አለን፡፡
“ታላቁ የወንጌል ሥራ የወንጌል ዘር ሲዘራ ከተገለጠው አምላካዊ ብርቱ ኃይል ባነሰ
አይደመደምም…
“መልእክቱ ከእግዚአብሔር መንፈስ ጥልቅ መነካት ውጪ በክርክርና በጭቅጭቅ
የትም አይደርስም፡፡ ጭቅጭቁና ንትርኩ በጌታ እግር ስር እንዲውል ሆኗል፡፡ ዘሩ
እንደተዘራ ሁሉ እነሆ ጎልብቶ የሚያፈራበት ወቅት ላይ ደርሶአል፡፡”—Ellen G.
White, The Great Controversy, pp. 611, 612.
የአምላካዊው የመጨረሻ መልእክት እወጃ መደምደሚያ--የምድር ሕዝቦች ከሁለት
ጎራ እንዲከፈሉ መንስዔ ይሆናል፡--ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ያላቸው እና
አውሬውን ለመከተል የመረጡ፡፡ እንዲህ ያለው መለያየት በሁለቱ የምድር መከሮች
ተመልክቶአል፡ የስንዴው ወደ ጎተራ መግባት (ራእ. 14፡14-16) እና የወይኑ በወይን
መጭመቂያ መረገጥ (ራእ. 14፡17-20)፡፡ ይህ የራእ. 17-18 አበይት ርዕሰ ጉዳይ ነው፡፡
1.ከሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች ውጪ የሦስቱን መላእክት መልእክት
እየሰበከ የሚገኝ ተቋም ማነው? የዚህ ምላሽ ስለ ሥራችን አስፈላጊነት
ምን ይነግረናል? የተሰጠንን ተልዕኮ ምን ያህል የምር ይዘነዋል?
2.አምላካዊው ፍርድ በብዙ ክርስቲያኖች ዘንድ ገሸሽ የተደረገ ዓይነት
የሆነው ለምን ይመስሎታል? የቅድመ ምጽአቱ ፍርድ ጽንሰ ሃሳብ
ለዛሬዎቹ ክርስቲያኖች ምን ዓይነት አንደምታ አለው? ወዳጆችዎ
እውነተኛውን የቅድመ ምጽአቱ ፍርድ ጽንሰ ሃሳብ በተሻለ ማስተዋል
እንዲችሉ እንዴት ሊረዷቸው ይችላሉ?
3.
በሰንበት ዙሪያ የሚነሱን ጥያቄዎች ከመጨረሻው ጊዜ ቀውሶች
ዐውድ አሰብ ያደርጉ፡፡ መጀመሪያ ከፍጥረት ጊዜ አንስቶ የተቋቋመው
ሰባተኛው ቀን ሰንበት (ዘፍ. 2፡2-3) ይህን ያህል የጉዳዮች ማዕከል
የመሆን ሚና እንዲጫወት የላቀ ትርጉም የሰጠው ምን ይመስሎታል?
ጉዳዩ ለማን እንስገድ--“ሰማይንና ምድርን ለፈጠረው” (ራእ. 14፡
7) ወይስ ለአውሬው ሥልጣን--የሚል ከሆነና፤ ሰባተኛው ቀን ሰንበት
ጥንታዊ፣ እጅግ መሰረታዊና እግዚአብሔር “ሰማይንና ምድርን”
መፍጠሩን የሚያረጋግጥ ምልክት ነው ካልን፤ ታዲያ ለምን ይሆን
ሰንበት እንደ አንድ የእግዚአብሔር ሕግ (ራእ. 14፡12) እንዲህ በግልጽ
የሚታይ ሚና የማይጫወተው?