ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ራእ. 13፣ ራእ. 17:8፣
ዳን. 7:24፣ 2ተሰ. 2:2–12፣ ራእ. 12:14–16፣ 1ነገሥ. 18:38፡፡
መታሰቢያ ጥቅስ :- “ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ ተቆጣ፤
ከቀሩት ልጆቿም ጋር ሊዋጋ ሄደ፤ እነርሱ የእግዚአብሔርን
ትእዛዛት የሚጠብቁና የኢየሱስን ምስክር አጥብቀው
የያዙ ናቸው” (ራእ. 12፡17)፡፡
ራ
እ. ምዕ. 12 በንዴት የጦዘው ሰይጣን የከርስቶስን ታማኝ ሕዝቦች ለመውጋት
ዝግጅት እያደረገ እንደሆነ በመንገር ይደመደማል፡፡ ምዕ. 13 ደግሞ ሰይጣን
ለመጨረሻው ውጊያ በሚያደርገው ዝግጅት በክፉ አውሬነት የተሳሉትን ሁለት
አበሮቹን አጋዡ አድርጎ ያሰልፋል፡፡ ይህ በሦስት አካላት የተዋቀረ ቅድስና የጎደለው
ሐሳዊ ሥላሴ (ራእ. 1፡4-6) እንዲህ ያለውን ኅብረት የፈጠረው ለሰብዓዊው ዘር
ደኅንነት የማምጣት ኃይል ያለውን አምላካዊውን ኃይል ለመቃወምና ሰዎችን
ለዓለም ታማኝ አድርጎ ለማሸነፍ ነው፡፡
በእስካሁኑ ጥናታችን ቀደም ባሉት ዘመናት ፍጻሜ ያገኙ ትንቢቶችን ተመልክተናል፡
፡ በመቀጠል ሙሉ ለሙሉም ባይሆን ነገር ግን አብዛኛው ምልከታችን ትኩረት
የሚያደርገው ወደፊት ፍጻሜ በሚያገኙ ትንቢቶች ላይ ይሆናል፡፡ በምድር ታሪክ
መዝጊያ ወቅቶች ገቢራዊ የሚሆኑ ክስተቶችን እግዚአብሔር አስቀድሞ የሚያሳየን
ጊዜው ሲደርስ ያልታሰቡ እንዳይሆኑብን በማሰብ ነው፡፡
ትንቢቶቹ በመጨረሻው ጊዜ እውን የሚሆኑትን ነገሮች ቢነግሩንም ነገር ግን
መቼ እና በትክክል እንዴት ፍጻሜ እንደሚያገኙ የሚሉት ነገር የለም፡፡ ይህን
ደግሞ ሁሌም ማስታወስ ከእኛ ይጠበቃል፡፡ ስለዚህ ከትንቢት ባሻገር የሚሰነዘሩ
መላ ምቶችን ከመቀበል ብሎም ከማስተላለፍ መቆጠብ የግድ ይሆናል፡፡ የራእይ
ትንቢቶች ተጨባጭ አንደምታ እንዳላቸው እናስታውስ፡--ዛሬን እንዴት መኖር
እንዳለብን ማስተማር እና ለወደፊቱ እንድንዘጋጅ ማድረግ፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 13፡1-4፣ 8፣ 17፡8፡፡ የዚህ አውሬ ልዩ ባህሪያት ምንድን
ናቸው? የሕልውናው የዕድገት ደረጃስ?
ዮሐንስ አንድ አስፈሪ አውሬ ከባሕር ሲወጣ ተመልክቶአል፡፡ አውሬ ፖለቲካዊ
ሥልጣንን የሚወክል እንደመሆኑ፤ ከባሕር የወጣው አውሬ የተገለጸበት መንገድ
ኃይማኖታዊ እና ፖለቲካዊ ሥልጣን ያለውን ኃይል ያመለክታል፡፡ ባሕር የሮም ልዕለ
ኃያል አገዛዝ ውድቀትን ተከትሎ የተከሰተው ጽንፈኛ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሁናቴ
ተምሳሌት ነው (ዳን. 7፡2-3፣ 23-24)፡፡
ዮሐንስ አስፈሪ ሲል የገለጸው አውሬ ከባሕር ሲወጣ መመልከቱን ተናግሮአል፡
፡ አውሬው ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶች የነበሩት ሲሆን--በራእ. 12፡3 ከቀረበው
ዘንዶ ጋር ያለው ተመሳሳይነት በሁለቱ መካከል ያለውን ግንኙነት ያሳያል፡፡ በራሶቹ
ላይ የስድብ ስሞች፣ በቀንዶቹ ላይ ደግሞ ዘውዶች ደፍቶአል፡፡ የአውሬው ራሶች
ሰይጣን በዘመናት የእግዚአብሔርን ሕዝቦች ለማሳደድ የሚጠቀምባቸው ኃይሎች
ናቸው (ራእ. 17፡9-11)፡፡ የስድቡ ስም አውሬው አለኝ የሚለውን መለኮታዊ ማዕረግ
ይወክላል፡፡ ወደ ዳን. 7፡24 የሚያመላክቱት ዐሥሩ ቀንዶች የልዕለ ኃያሉን ሮም
አስተዳደር መክሰም ተከትሎ የወጡት መንግሥታት ተምሳሌቶች ናቸው፡፡
አውሬው ከውሃ ሲወጣ--የነብር፣ የድብ እና የአንበሳ የሚመስል ገጽታ ይዞ ነበር፡፡
ይህ ደግሞ አውሬው በዳን. 7፡2-7 የተጠቀሰውንና (የዓለም መንግሥታት ተምሳሌት
የሆነውን) የአራት አውሬዎችን መለያ ባህሪያት በአንድ አጣምሮ መያዙን ያሳያል፡፡
መንግሥታቱ--ባቢሎን፣ ሜዶንና ፋርስ፣ ግሪክ እና ሮም (ዳን. 7፡17) ናቸው፡፡ ሆኖም
ዮሐንስ የሚያስቀምጣቸው ቅደም ተከተላቸውን ጠብቆ ሳይሆን በተገላቢጦሽ ነው፡
፡ ይህ ደግሞ ከባሕር የወጣው አውሬ የሮም ንጉሠ ነገሥታዊ ግዛት ከሆነው ከዳን. 7
አራተኛው አውሬ ጋር ያለውን ዝምድና ያሳያል፡፡ ዘንዶው ኃይሉን፣ ዙፋኑንና ታላቅ
ሥልጣን ለአውሬው ሰጥቶታል፡፡ አብ ዙፋኑን እንዲሁም ሥልጣን ሁሉ ለክርስቶስ
እንደ ሰጠ (ራእ. 2፡27) በተመሳሳይ ዘንዶውም የምድር አጋር፣ ገዢና ወኪሉ አድርጎ
ይሰጠዋል፡፡ ከባሕር የወጣው አውሬ የሦስትዮሹ ሰይጣናዊው ኅብረት ሁለተኛው
አካል ሲሆን ይህ ደግሞ የሱስ ክርስቶስን ከሰብዓዊው ልብ ለማውጣት የሚደረግ
ሙከራ ነው፡፡
አውሬው በሥልጣን የሚሠራባቸው ጊዜያቶች 42 ትንቢታዊ ወራት ወይም 1,260
ቀናት (ዓመታት) መሆናቸው ተገልጾአል፡፡ ከአውሬው ራሶች በአንደኛው ላይ ለሞት
የሚያደርስ ጊዜያዊ ቁስል በደረሰበት ጊዜ ይህ ምዕራፍ ይደመደማል፡፡ ሆኖም ቁስሉ
በተፈወሰለት ጊዜ አውሬው ዳግም በሕይወት ያንሰራራል፡፡ ይህ ሁናቴ በዓለም
ከፍተኛ አድናቆት እንዲገኝ የሚያስችል በመሆኑ ብዙዎች ለዘንዶውና ለአውሬው
ይሰግዳሉ፡፡
ራእ. 15፡5 በአንድ የተወሰነ ወቅት ስለሚደርስ ስደት መናገሩን በትናንቱ ጥናታችን
ተመልክተናል፡፡ የአውሬው ለ42 ወራት በሥልጣን መቆየት ከራእ. 12፡14--የ1,260
ቀናት የሴቲቱ (የቤተ ክርስቲያን) የስደት ዘመን ጋር እኩል ነው፡፡ ተምሳሌታዊዎቹ
ትንቢታዊ ቀናት ገሃዱን ዓመታት ይወክላሉ፡፡ 538 ዓ.ም.--የትንቢታዊው ምዕራፍ
ጅማሮ ሲሆን፤ ይኸውም ጳጳሳዊውን ሥርዓት የበላይ አድርጋና ራሷን በክርስትና
ተቋም ኃይልነት ሰይማ፣ በመካከለኛው ዘመን ምዕራቡን ዓለም በበላይነት
የተቆጣጠረችው የሮም ቤተ ክርስቲያን መነሳት ነው፡፡ የፈረንሳይ አብዮት ሲፈነዳ
ይዞት የመጣው ነውጥ በ1798 ዓ.ም. አውሬው ክፉኛ እንዲቆስል መንስዔ ሆነ፡
፡ በዚህም ቤተ ክርስቲያን የነበራት ጨቋኝ ሚና እና የመንግሥት ቀኝ የነበረው
ኃይማኖታዊ ተቋም ለጊዜውም ቢሆን ያከተመለት መሰለ፡፡
ጥቅሶቹን ያስተያዩ፡ ራእ. 13፡5-8፣ ዳን. 7፡24-25፣ 2ተሰ. 2፡2-12፡፡ ከባሕር የወጣው
አውሬ ተግባራት ስለ ትንሹ ቀንድ እና ስለ ዐመፅ ሰው የቀረበውን መግለጫ በተሻለ
የሚያንጸባርቁት እንዴት ነው?
በ1,260 ትንቢታዊ ቀናት ውስጥ የተስተዋለው የአውሬው እንቅስቃሴ የስድብ
ቃል በሚል አነጋገር ተወስቶአል፡፡ የስድብ ቃል--ከእግዚአብሔር ጋር እስተካከላለሁ
እንደ ማለት ነው ሲል አዲስ ኪዳን ይነግረናል (ዮሐ. 10፡33፣ ማቴ. 26፡63-65፣ ማር.
2፡7)፡፡ ከባሕር የወጣው አውሬ የስድብ ቃላት የሚያነጣጥሩት ወደ እግዚአብሔር
ነው፡ “እርሱም እግዚአብሔርን ለመሳደብ እንዲሁም ስሙንና ማደሪያውን፣
በሰማይም የሚኖሩትን ለመሳደብ አፉን ከፈተ” (ራእ. 13፡6)፡፡ የእግዚአብሔር
ማደሪያ ክርስቶስ ስለ እኛ ደኅንነት አገልግሎት የሚሰጥበት ሰማያዊው መቅደስ
ነው፡፡ የደኅንነት ሥራን የመቆጣጠርና የመምራት እንዲሁም ኃጢአትን ይቅር
የማለት መብት እንዳለው የሚናገረው ከባሕር የወጣው አውሬ ድርጊት፤ ከክርስቶስ
የማማለድ ሥራ ጋር የሚጻረረው የዚህ የስድብ ቃል ትክክለኛ ፍቺ ነው፡፡
ራእ. 13 በጳጳሳዊው ሥርዓት የበላይነት የምዕራቡ ዓለም ቤተ ክርስቲያንና
መንግሥት በሮም ጥበቃና ምሪት ስር የዋለባቸውንና፤ ጳጳሱ ከእግዚአብሔር ልዩ
መብትና ጥቅም እንደ ተቀበለ ተደርጎ የታመነበት ይህ የበላይነት--በቤተ ክርስቲያን
ላይ መሰረታዊ ክህደት የተፈጸመባቸውን ዘመኖች ያመላክታል፡፡ ሰብዓዊውን
ዘር የሚዋጀው ሰማያዊው የክርስቶስ አገልግሎት በቤተ ክርስቲያን ክኅነት ተተካ፡
፡ ለሮም ቤተ ክርስቲያን ታማኝ ያልሆኑ ስደት ደረሰባቸው፣ የሰማዕትነት ሞትም
ተቀበሉ፡፡ ምንም እንኳ ዛሬ እንደነዚህ ዓይነቶቹ አነጋገሮች እንደ ጨካኝና ፍጹም
አክራሪ ድርጊት ቢታዩም፤ ነገር ግን የዛሬው ሁኔታ የትናንቱን ታሪክ ፈጽሞ ሊፍቅ
አይችልም፡፡
የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ አስመልክቶ ለትንቢት ታማኝ መሆን ያለብን
እንዴት ነው? በተጨማሪ እነዚህን እውነቶች ለሌሎች ስናቀርብ
ደግነትና ጥንቃቄ እንዳይለየን መዘንጋት የለብንም፡፡
የራእይ ምዕ. 13 የመጀመሪያው ግማሽ በ1,260 ትንቢታዊ ቀናት/ ዓመታት
በጉልህ የታየውን የመካከለኛውን ዘመን የቤተ ክርስቲያን ዐምባ ገነንነት ይገልጻል፡
፡ በፈረንሳይ ተቀጣጥሎ የፈነዳው አብዮት በዚህ ኃይማኖትንና ፖለቲካን በአንድ
አጣምሮ በያዘ ተቋም ላይ ለሞት የሚያደርስ ቁስል አደረሰ፡፡ ሆኖም ውሎ አድሮ
ለሞት የሚያደርሰው ቁስል ሻረና ሥርዓቱ ወደ ቀድሞ ህልውናው ተመለሰ፡፡ ይህ
ለሞት ያደረሰው ቁስል ፈውስ--እንዴት ገቢራዊ እንደሚሆን የምዕራፉ ሁለተኛ
አጋማሽ ይገልጽልናል፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 13፡11፡፡ የሁለተኛው አውሬ ባህሪያት ምንድን ናቸው? በራእ.
12፡14-16 መሰረት የዚህ አውሬ ከምድር መውጣት አንደምታ ምንድን ነው?
ዮሐንስ ሌላ አውሬ ከምድር ሲወጣ እንደተመለከተ ይናገራል፡፡ ይህ ከምድር የወጣ
አውሬ አስፈሪ ገጽታ ከነበረው ከመጀመሪያው አውሬ በተቃራኒ “እንደ በግ ሁለት
ቀንዶች” የነበሩትና ጉዳት የሌለው ዓይነት ነበር (ራእ. 13፡11)፡፡ በራእይ መጽሐፍ በግ
ክርስቶስን በብቸኝነት ይወክላል፡፡ ስለዚህ ይህ በዘመን መጨረሻ ላይ የሚነሳ ኃይል
የክርስቶስ ዓይነት ገጽታ ይኖረዋል፡፡
ይህ ከቤተ ክርስቲያን ጋር ወዳጃዊ ሆኖ በበግ የተመሰለው አውሬ ኃይል የተነሳው
ሴቲቱን ወይም ቤተ ክርስቲያንን በ1,260 ቀናት መደምደሚያ (ራእ. 12፡14-16) ላይ
ከዘንዶው የጎርፍ ውሃ ከተከላከላት ግዛት ነው፡፡ ከባሕር የወጣው አውሬ በፈረንሳይ
አብዮት ለሞት የሚያደርስ ቁስል ከደረሰበት በኋላ የዓለም ልዕለ ኃያል ሆኖ ብቅ ያለ
የመጨረሻው ዘመን ትዕይንት አዲስ ተዋናይ መሆኑ እርግጥ ነው፡፡
ሆኖም ይህ በበግ የተመለሰለ ኃይል ውሎ አድሮ እንደ ራሱ እንደ ዲያብሎስ
ማለትም እንደ ዘንዶ መናገር እንደሚጀምር ከጥቅሱ እንመለከታለን፡፡ ይህ
የመጨረሻው ዘመን ኃይል መላው ዓለም ለሞት የሚያበቃ ቁስል ደርሶበት ለነበረው
የመጀመሪያው አውሬ እንዲሰግድ ለሚደረገው እንቅስቃሴ ቁልፍ መሣሪያ ይሆናል፡
፡ በድኅረ መካከለኛው ዘመን፤ በአንድ ወቅት ለቤተ ክርስቲያን መጠጊያ በመሆን
ደኅንነቷን ያስጠበቀው ይህ ግዛት፤ በመጨረሻው ዘመን ገቢራዊ በሚሆኑ ክስተቶች
የማሳደድ ሚና እንደሚጫወት ከዚህ እንመለከታለን፡፡
“ብርቱ እና ታላቅ እንደሚሆን የተስፋ ቃል የተሰጠውና የዓለምን ትኩረት እየሳበ
በ1798 በአዲሱ የዓለም ሥርዓት ወደ ሥልጣን የመጣው የትኛው መንግሥት ነው?
የተምሳሌቱ አተገባበር አንዳችም ጥያቄ የሚያስነሳ አይደለም፡፡ የዚህን ትንቢት
ዝርዝር መመሪያ በብቸኝነት የሚያሟላ አንድ እና አንድ ብቻ አገር ሲሆን ይኸውም
ዩናይትድ ስቴስ ኦቭ አሜሪካ ነው፡፡”—Ellen G. White, The Great Controversy, p. 440.
አሜሪካ የትንቢቱ ፍጻሜ በመሆን ተለይታ በተቀመጠችበት ወቅት
ዛሬ በዓለም ዙሪያ ካላት ልዕለ ኃያልነት ጫፉ የሚደርስ ኃይልም ሆነ
ተጽእኖ አልነበራትም፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ በዚህ ትንቢት የቀረበችበት
ይህ የልዕለ ኃያልነቷ ሐቅ፤ አገሪቱ የትንቢቱን መስፈርት ማሟላቷን
አጽንተን እንድንይዝ እንዴት ሊረዳን ይችላል?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 13፡12-13፡፡ እሳት ከሰማይ እስከ ማውረድ ታላቅ ታምራት
የሚያደርገውን የዚህን አውሬ ተፈጥሮ ማስተዋል እንድንችል 1ነገሥ. 18፡38 እና
ሐዋ. 2፡3 እንዴት ይረዱናል?
በመጨረሻው ዘመን በግ የሚመስለው አውሬ የመጀመሪያውን አውሬ ሥልጣን
መለማመድ የሚጀምር ሲሆን፤ የእርሱ ድርጊትም ሆነ እንቅስቃሴ ከመንፈስ
ቅዱስ ተግባርና ኃላፊነት ጋር ይመሳሰላል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ሰዎችን ወደ ክርስቶስ
በማመላከት (ዮሐ. 15፡26) ስለ ክርስቶስ ሥልጣን ምስክርነት እንደሚሰጥ ሁሉ፤
ይህ ምድራዊ ኃይልም ከባሕር የወጣው አውሬ ላለው ሥልጣን ምስክርነቱን ለሕዝብ
ይሰጣል፡፡
በግ መሳዩ አውሬ ለመጀመሪያው አውሬ እጅግ ከፍ ያለ ክብር በመስጠት የምድር
ሕዝቦች የመጀመሪያውን አውሬ እንዲያመልኩ መንስዔ ይሆናል፡፡ ይህ ሁናቴ ለሞት
ከሚያደርስ ቁስል ከተፈወሰው አውሬ ጋር ዝምድና እንዳለው ጥቅሱ ያሳየናል።
ለመሆኑ በግ የሚመስለው አውሬ ዓለም ከባሕር ለወጣው አውሬ እንዲሰግድ
የሚያደርገው እንዴት ነው? በመጀመሪያ--ታምራቶችንና ምልክቶችን በማድረግ
(ራእ. 13፡13-14) በቀጣይ--በማስገደድ (ራእ. 13፡15-17)፡፡
ከባሕር የወጣው አውሬ ለሞት ያደርስ የነበረ ቁስል መፈወስ የመካከለኛው ዘመን
ኃይማኖታዊ ሥርዓት ወደ ቀድሞው ሁናቴ መመለሱን ያሳያል፡፡ በግ የሚመስለው
አውሬ ለሞት የሚያደርስ ቁስል ለደረሰበት አውሬ ምስል በማቆም ታምራቶችን
ተጠቅሞ የምድርን ሕዝቦች ማሳት የሚቻለው ይሆናል፡፡
ምስል የአንድ ተጨባጭ ነገር ግልባጭ ነው፡፡ ዓለም የቀደመውን አምሳያ፤ ይኸውም
የመካከለኛውን ዘመን ኃይማኖታዊ ሥርዓት ለመፍጠር የሚገፋፋ ይሆናል።
ሕዝቦች አሳቾቹን ታምራቶች የመለኮታዊ ኃይል መገለጫ አድርገው የሚቀበሉ
ይሆናሉ፡፡ ሕዝባዊና ፖለቲካዊ ኃይላት ኃይማኖትን በሕዝቡ ላይ ለመጫን ዓለምን
እየመሩ ከሚገኙ ኃይማኖታዊ ተቋማት ጋር በሚሰለፉበት ወቅት የአውሬው ምስል
ይፈጠራል፡፡
ራእ. 13፡14-15 ያንብቡና ከዘፍ. 2፡7 የወጣው ቋንቋ--የአውሬው ምስል ለመሥራት
የሚያስችለው እስትንፋስ እንዴት እንደተሰጠው የሚገልጽበትን አካሄድ ለማስተዋል
ይሞክሩ፡፡
በግ የሚመስለው አውሬ--የአውሬው ምስል እግዚአብሔር ሰውን ከፈጠረበትና
ሕይወት ከሰጠበት ሂደት በተመሳሳይ እንዲሠራ ያደርጋል ሲል ይኸው ትንቢት
በዘፍ. 2፡7 የቀረበውን ቋንቋ ተጠቅሞ ይነግረናል፡፡ ይህን ማስገደድን ጫና አድርጎ
የተከተለ የማሳመን ሥራ ተከትሎ፤ የዓለም ሕዝቦች ለአውሬው ሥልጣን እውቅና
ለመስጠት እና እርሱን ለመቀበል ይገፋፋሉ፡፡
በመጨረሻው ቀውስ ወቅት በግ የሚመስለው አውሬ የመሪነቱን ሚና እንደሚጫወት
ራእ. 13 ይጠቁመናል፡፡ ይህ የዓለም ልዕለ ኃያል--የሕዝቦችን የማምለክ ነፃነት
ለመቆጣጠር እንዲቻለው የመካከለኛው ዘመን ክርስትናን ነጸብራቅ በዓለማቀፋዊ
ሕግና አሠራር ያቋቁማል፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 13፡16-17፣ ዘዳ. 6፡4-8፡፡ በግምባር ላይ እና በቀኝ እጅ
ላይ ምልክት ማስቀመጥ ከእግዚአብሔር ሕግ ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት አለው?
ሐብታም ደኻ ሳይል ሁሉም የዓለም ሕዝቦች የአውሬውን ምልክት በግምባራቸውና
እና በቀኝ እጃቸው እንዲቀበሉ ይገደዳሉ፡፡ ይህን ምልክት መቀበል ከአውሬው ጋር
ማበር ይሆናል፡፡ አምላካዊው ማኅተም የእግዚአብሔር የሆኑት መለያ እንደመሆኑ
(ራእ. 14፡1)፤ የአውሬው ምልክት ደግሞ ለእርሱ የሚሰግዱ የሚለዩበት ይሆናል፡፡
የአውሬው ምልክት በዐይን ተለይቶ የሚታይ ነገር አይደለም፡፡ ምልክቱ በቀኝ
እጅ ወይም በግምባር ላይ ማረፉ እስራኤላውያን የእግዚአብሔርን ሕግ በእጆቻቸው
ላይ ምልክት አድርገው እንዲያስሯቸውና በግምባራቸውም ላይ እንዲሆኑ (ዘዳ. 6፡
8) ሙሴ የሰጣቸውን መመሪያ መሰረት ያደረገ ነው፡፡ በዚህም የምልክቱ በግምባር
ላይ መሆን የእግዚአብሔር ሕግ በአእምሮ ላይ ያለውን ተጽእኖ ሲገልጽ፤ በቀኝ እጅ
መሆኑ ደግሞ የሰዎችን የሥራ ባህሪ ያሳያል፡፡
አምልኮ እና የእግዚአብሔርን ትእዛዛት እየጠበቁ እርሱን መታዘዝ፤ ዋንኛው
የመጨረሻው ቀውስ ወቅት ጉዳይ ይሆናል (ራእ. 14፡12)፡፡ በተለይ ሰንበትን
እንድንጠብቅ የተሰጠው ትእዛዝ--ሕዝቦቹ ለእግዚአብሔር ያላቸው ታማኝነትና
መታዘዝ የሚፈተንበት ይሆናል፡፡ ሰንበት የእግዚአብሔር ታማኝ ሕዝቦች እርሱን
የመታዘዛቸው ግልጽ ምልክት ሲሆን (ሕዝ. 20፡12)፤ የአውሬው ምልክት ደግሞ
አውሬውን የመታዘዝ መለያ ይሆናል፡፡ የአውሬው ምልክት የእግዚአብሔርን
ትእዛዝ በሰብዓዊው ትእዛዝ በመተካት በአራተኛው ትእዛዝ ላይ ቀጥተኛ ጥቃት
ይፈጽማል፡፡ የዚህ ተጨባጭ እውነታ ግዙፍ ማስረጃ በመጽሐፍ ቅዱስ በተሰየመው
በሰባተኛው ቀን ቅዳሜ ሰንበት ምትክ እሁድ የአምልኮ ቀን ሆኖ በሰው መቋቋሙ
ነው (ዳን. 7፡25)፡፡
ጌታን በፈጣሪነቱ የምናመልከው ሲሆን፤ ሰባተኛው ቀን ሰንበት
ደግሞ ከምድር መፈጠር አንስቶ የእውነተኛ አምላክነቱ ምልክት ሆኖ እንደ ጸና
ይገኛል፡፡ የእግዚአብሔርን የመፍጠር ምልክት በሌላ ቀን ለመቀየር መሞከር የራሱን
የእግዚአብሔርን ሚና እና ኃይል መቀማት ይሆናል፡፡
በጥቅሶቹ የቀረቡትን ትዕይንቶች ያስተያዩ፡ ራእ. 13፡14-18፣ ዳን.
3፡1-7፡፡ በታሪኩ ምን ዓይነት ተመሳሳይነት ያላቸውን ሁናቴዎች
ማግኘት እንችላለን? በዘመን መጨረሻ ምን ይከሰታል?
ሰንበት በምድር ታሪክ መደምደሚያ ላይ የመታዘዝ
ምልክት እንደሚሆን የራእይ መጽሐፍ ያስገነዝበናል፡፡ ሆኖም ዛሬ እሁድን
መጠበቅ የአውሬውን ምልክት መቀበል አለመሆኑን ማስታወስ ተገቢ ነው፡
፡ ልዩ ልዩ ማደናገሪያዎችና ማታለያዎች መኖራቸው እሙን ቢሆንም፤ እሁድን
መጠበቅ “የአውሬው ምልክት” የሚሆነው ሰዎች አምልኮ የሚያደርጉበትን ቀን
መመምረጣቸውን ተከትሎ የሚመጣውን አንገብጋቢ ጉዳይ በግልጽ አስተውለው
እግዚአብሔርን ወይም ከእርሱ በተቃራኒ የተሰለፈውን ኃይል ሲመርጡ ብቻ ነው፡፡
ሆኖም ያ ዕለት ገና አልደረሰም፡፡
“እስካሁን የአውሬውን ምልክት የተቀበለ ሰው የለም፡፡ የመፈተኛውም ጊዜ
ቢሆን ገና አልደረሰም፡፡ ከሮም ጳጳሳዊው ሥርዓት ጋር ኅብረት የሌላቸው አያሌ
ክርስቲያኖች በብዙ ቤተ ክርስቲያኖች አሉ፡፡ በሰባተኛው ቀን ዙሪያ ብርሃን
እስኪቀበሉና የአራተኛውን ትእዛዝ አስገዳጅነት እስኪያስተውሉ አንዳቸውም
ውግዘት የለባቸውም፡፡ ነገር ግን የሐሰተኛው ሰንበት አስገዳጅ ዐዋጅ ሲወጣ እና
ሰዎች ለአውሬውና ለምስሉ እንዳይሰግዱ የሚያስጠነቅቀው የሦስተኛው መልአክ
ተማጽኖ ዳር እስከ ዳር ሲያስተጋባ፤ ያኔ በሐሰተኛውና በእውነተኛው አምልኮ
መሃል ያለው ልዩነት ግልጽ ሆኖ ይሰመራል፡፡ በዚህ ወቅት አምላካዊውን ትእዛዝ
በመተላለፍ የሚጸኑ የአውሬውን ምልክት ይቀበላሉ፡፡”—Ellen G. White, Evangelism, p. 234.
የእሁድ አምልኮ ዛሬ ማንንም ለጥፋት እንደማይዳርግ ሁሉ፤ በተቃራኒው ቅዳሜ
ማንንም ሊያድን እንደማይችል እናስታውስ፡፡ ሆኖም “የአውሬው ምልክት” የነገሮች
ሁሉ ማዕከላዊ ጉዳይ የሚሆንበትና የአምልኮ ቀን መምረጥ የታማኝነት መፈተኛ
ሆኖ ብቅ የሚልበት ጊዜ እየመጣ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝቦች እውነትን ለማወቅ
በሚሻ መንፈስ ልባቸውን ከፍተው የአምላካዊውን ቃል ትንቢቶች ለግላቸው
እንዲያጠኑና፣ ይህን የክርስቶስ ወንጌል ወዳላገኙ ለመድረስ ማንኛውንም ጥረት
ያደርጉ ዘንድ የራእይ መጽሐፍ ተማጽኖውን ያቀርባል፡፡
1.ከዛሬው የዓለም ሁኔታ አኳያ በኃይማኖታዊውና በፖለቲካው አድማስ
ወደ ራእ. 13 ትንቢት ፍጻሜ ሊያመሩ የሚችሉ ምን ዓይነት አካሄዶችን
ይመለከታሉ?
2.መጨረሻውን እየተጠባበቅን እያለን፣ በሌሎች የኃይማኖት ድርጅቶች
በሚገኙ ክርስቲያኖች ላይ የሚኖረን አመለካከት ምን ሊሆን ይገባል?
ስለሚከተለው ምክረ ሃሳብ አሰብ ያድርጉ፡ “አገልጋዮቻችን ሌሎች
አገልጋዮችን ለመቅረብ ጥረት ማድረግ አለባቸው፡፡
ክርስቶስ
እየማለደላቸው ለሚገኝ ለእነዚህ ሰዎች ይጸልዩ እንዲሁም ከእነርሱ ጋር
አብረው ልመና ያቅርቡ፡፡ እነሆ የተከበረ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ እኛ
እንደ ክርስቲያን መልእክተኝነታችን ለእነዚህ የመንጋ እረኞች ጥልቅና ቅን
ፍላጎት ማሳየት ይኖርብናል፡፡”—Ellen G. White, Testimonies
for the Church, vol. 6, p. 78.
አልፎ አልፎ በሌሎች የክርስትና ድርጅቶች በሚገኙ ክርስቲያኖች ላይ
የምንገልጠውን ክርስቲያናዊ ያልሆነ መንፈስ ማስወገድ የምንችለው
እንዴት ነው? ያመንናቸውን እውነቶች ለድርድር ሳናቀርብ ለእነርሱም
ሆነ ለግል እምነታቸው አክብሮት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?