ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ራእ. 2፡8-11፣ 3:7– 11፣ 2:12–17፣ 14:12፣ 2:18–29፣ 3:1–6፣ 3:14–22፣ ኢሳ. 61:10፡፡
መታሰቢያ ጥቅስ :- “ ‘መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ’ ” (ራእ. 3፡22)፡፡
የ
ሱስ ፍጥሞ በነበረው ዮሐንስ በኩል ሰባት መልእክቶች የያዘውን መልእክት
ለሕዝቡ ላከ፡፡ ምንም እንኳ የመልእክቶቹ ቀዳሚ ጭንቀት በዮሐንስ ዘመን
በእስያ የነበሩት አብያተ ክርስቲያናት ቢሆኑም፤ መልእክታቸው እስከ ምድር ታሪክ
መደምደሚያ የሚኖሩ ክርስቲያኖችን ያካትታል፡፡
መልእክቶቹ እርስ በርስ ሲመሳከሩ ሁሉም አንድ ዓይነት አወቃቀር መከተላቸውን
እንመለከታለን፡፡ በሁሉም መልእክቶች መግቢያ የሱስ እያንዳንዱን ቤተ ክርስቲያን
በስም ይጠራል፡፡ በቀጣይ ደግሞ “ ‘ “እንዲህ ይላል…” ’ ” የሚል ሃረግ ይከተላል፡፡ የሱስ
ገላጭ ባህሪዎችን ተጠቅሞ ራሱን ለእያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን የሚያስተዋውቅበት
መንገድ በምዕራፍ አንድ ይገኛል፡፡ እነዚህ የሱስ የተጠቀማቸው መግለጫዎች
የእያንዳንዱን ቤተ ክርስቲያን ጉድለት ማሳየታቸውና በትክክል ገጣሚ መሆናቸው፤
የተለያዩ የዕለት ከዕለት ትግልና አስቸጋሪ ሁናቴዎችን ለመፍታት ያለውን ክህሎት
ያመላክታል፡፡
በመቀጠል የሱስ ቤተ ክርስቲያኗ የምትገኝበትን ሁናቴ ካመዛዘነ በኋላ
እንዴት ከገጠማት አስቸጋሪ ሁናቴ መውጣት እንደምትችል ምክረ ሃሳብ ይለግሳል፡
፡ በመጨረሻ፤ ቤተ ክርስቲያን መንፈስ የሚያቀርብላትን ተማጽኖ እንድትሰማ
ጥሪ በማድረግ እና ለአሸናፊዎች በተሰጠው የተስፋ ቃል--እያንዳንዱ መልእክት
ይደመደማል፡፡
መልእክቶቹን ለማጤንና ለመመርመር ስንሞክር ቤተ ክርስቲያን በየትኛውም
ሁናቴ ውስጥ ብትገኝ፤ የሱስ እያንዳንዱን ችግሯን የመረዳትና መፍትሔ የማምጣት
ክህሎት እንዳለው እንመለከታለን፡፡ እርሱ በእርግጥ ዛሬ እየገጠሙን ላሉ ችግሮችም
ሆነ ተግዳሮቶች መፍትሔ አለው!
የሱስ በሁለተኛና በስድስተኛ ቅደም ተከተል የላካቸው መልእክቶች በቀዳሚነት
የተላኩት ለስምርኔስ እና ፊላደልፊያ አብያተ ክርስቲያናት ነበር፡፡ እነዚህ ሁለት ቤተ
ክርስቲያኖች ከየሱስ የተቀበሉት ግሳጼ አልነበረም፡፡
ሰምርኔስ ውብና ባለጠጋ ከተማ ከመሆኗ በተጨማሪ ለንጉሠ ነገሥቱ አምልኮ
የሚቀርብባት ማዕከላዊ ስፍራ ነበረች፡፡ ይህን በገዢው መደብ የተደነገገ የአምልኮ
ሕግ መቃወም ለስደት ብሎም ሰማዕትነት ሞት ይዳርግ ነበር፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡--ራእ. 2፡8-11፡፡ የሱስ ራሱን ለዚህች ቤተ ክርስቲያን ያቀረበበት
መንገድ ከተቋሟ ሁናቴ ጋር እንዴት ይዛመዳል? ቤተ ክርስቲያኒቱ ትገኝበት የነበረው
ሁናቴ ምን ይመስላል? እየመጣ ስለነበረው ነገር ለዚህች ቤተ ክርስቲያን የሰጠው
ማስጠንቀቂያ ምን ነበር?
በሰምርኔስ ለነበረችው ቤተ ክርስቲያን የተሰጠው መልእክት ክርስቲያኖች
አሰቃቂውን የስደት ገፈት የቀመሱበትን ድኅረ ሐዋርያት ዘመን ያመለክታል፡፡ በራእ.
2፡10 “ዐሥር ቀን” በሚል የተጠቀሰው ሃረግ በዲዮክሊታን ትእዛዝ 303 ዓ.ም. ላይ
ተጀምሮ እስከ 313 ዓ.ም. የዘለቀውን የዐሥር ዓመት የስደት ጊዜ የሚያመለክት
ሲሆን፤ ትእዛዙ የተሻረው ታላቁ ቆስጠንጢኖስ የሚላን ዐዋጅ በሚል መጠሪያ
የሚታወቀውንና ለክርስቲያኖች የኃይማኖት ነፃነት የሰጠበትን ድንጋጌ ባጸደቀበት
ወቅት ነበር፡፡
ከየሱስ መልእክት የተላከባት ስድስተኛዋ ቤተ ከርስቲያን የምትገኘው በፊላድልፍያ
(“ወንድማማቻዊ ፍቅር”) ነበር፡፡ ከተማዋ የታነጸችው በንጉሠ ነገሥታዊው የንግድ
ጎዳና ሲሆን መላውን ምስራቃዊ ክፍል ከምዕራባዊው አውራጃ ጋር የምታስተሳስር
ነበረች፡፡ የተቆረቆረችውም በሊዲያ እና ፍሪግያ አካባቢዎች የግሪክን ቋንቋና ባህል
ለማበልጸግ በሚል እሳቤ ነበር፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 3፡7-13፡፡ የሱስ ራሱን በዚህ መልእክት ውስጥ የሚያቀርብበት
መንገድ ከዚህች ቤተ ክርስቲያን ሁናቴ ጋር ያለው ዝምድና ምን ይመስላል? የሱስ
“ኀይልህ ትንሽ እንደ ሆነ ዐውቃሁ” (ራእ. 3፡8) ብሎ መናገሩ ቤተ ክርስቲያኒቱ
ስለምትገኝበት ሁናቴ ምን ይነግረናል? የሱስ ለዚህች ቤተ ክርስቲያን የሚሰጠው
የተስፋ ቃል ምንድን ነው?
ለዚህች ቤተ ክርስቲያን የተሰጠው መልእክት በዐሥራ ስምንተኛውና ዐሥራ
ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከተስተዋለው ታላቅ የተሐድሶ እንቅስቃሴ ጋር ገጣሚ
ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች በእርግጥም የነበራቸውን ብርሃን ሰጥተዋል፤ ቃሉንም
ጠብቀዋል (ራእ. 3፡8)፡፡ በዚህ ዘመን የነበረችው ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን ለዓለም
ለማዳረስ ከልብ በመነጨ ቅንአት መገፋፋቷን ተከትሎ--ከጴንጤቆስጤ አንስቶ
ያልታየ ግዙፍ የወንጌል ስርጭት ገቢራዊ መሆን ቻለ፡፡
ጴርጋሞን “አዳኝ” በሚል ስያሜ የሚጠራውንና በእባብ የሚወከለውን
አስሊፒየስ--የግሪክ የፈውስ አምላክ ጨምሮ የአያሌ የቤተ ጣዖት አምልኮ ማዕከል
ነበረች፡፡ ብዙዎች ፈውስ ፍለጋ የተቀደሰ ብለው ወደሚጠሩት አስሊፒየስ ይጎርፉ
ነበር፡፡ እንደ ስምርኔስ ሁሉ ጴርጋሞን ለንጉሠ ነገሥቱ ይቀርብ ለነበረው የግዳጅ
ሥርዓተ አምልኮ የመሪነቱን ሚና ትጫወት ነበር፡፡ በጴርጋሞን ከተማ ይኖሩ የነበሩ
ክርስቲያኖች “የሰይጣን ዙፋን ባለበት” እንደሚኖሩ በጥቅሱ መቅረቡ ከዚህ አኳያ
እምብዛም የሚገርም አይሆንም፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 2፡14-15፡፡ የሱስ ራሱን ለዚህች ቤት ክርስቲያን ያቀረበበት
መንገድ ምን ይመስላል? ቤተ ክርስቲያኒቱ ስለምትገኝበት መንፈሳዊ ሁኔታ
ያቀረበውስ ቅኝት?
በባዕድ አምልኮና በታላላቅ ቤተ ጣዖቶቿ ተከብባ በነበረችው በጴርጋሞን
ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖች ከቤተ ክርስቲያን ውጪም ሆነ በራሷ በቤተ ክርሰቲያኗ
ውስጥ የሚነሱ ብርቱ ፈተናዎችን መጋፈጥ ግድ ሆኖባቸው ነበር፡፡ ምንም እንኳ
አብዛኞቹ ክርስቲያኖች በታማኝነታቸው ቢጸኑም ነገር ግን ኒኮላይቲያንስ በመባል
ይጠሩ የነበሩ ጥቂቶች ሊደርስባቸው ከሚችል ስደት ለመጠበቅ ከአረማዊ አምልኮ
አራማጆች ጋር ሊያስታርቁ የሚችሉ ሀሳቦችን ያቀነቅኑ ነበር፡፡በተጨማሪ ከበለዓም
በኋላ በመባል ይታወቅ ከነበረ ሌላ ውጉዝ ቡድን ጋር ትስስር ፈጥረው ነበር፡፡
በለዓም እስራኤላውያን ወደ ተስፋው ምድር ያደርጉ በነበረው ጉዞ ለከፉ ሥራው
ያባበለ ግለሰብ ነበር (ዘኁ. 31፡16)፡፡ እነዚህ ሁለት ቡድኖች ምቾት ነሺውን ስደት
ለማስወገድ በማሰብ ከባዕድ አምልኮ አራማጆች ጋር ስምምነት በመፍጠሩ ዙሪያ
ያቀነቅኑ ነበር፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 2፡16-17፡፡ አማኞች የሚገኙበትን መንፈሳዊ ሁናቴ
ለማሻሻል ማድረግ በሚኖርባቸው ነገሮች ዙሪያ የሱስ ቤተ ክርስቲያንን አጥብቆ
ያሳሰበው ነገር ምንድን ነው? ምን ዓይነት ተስፋዎች ሰጣቸው?
ለጴርጋሞን ቤተ ክርስቲያን የተሰጠው መልእክት ተቋሟ ከ313 ዓ.ም. በኋላ
ትገኝበት የነበረውን ሁናቴ በተገቢው መንገድ ይገልጣል፡፡ ምንም እንኳ ክርስትና
ከባዕድ አምልኮ ጋር የነበረውን ትግል በአሸናፊነት ቢወጣም፤ ብዙዎች የቤተ
ክርስቲያን ሰዎች ግን ከአረማውያን ጋር ስምምነት መፍጠር ጀመሩ፡፡
በእርግጥ
አንዳንዶች በወንጌል ላይ የነበራቸው አቋም የማያወላዳና ለቃሉ ታማኝ ቢሆኑም
በእነዚያ በአራተኛው እና በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመኖች መንፈሳዊ ቁልቁለትና
ክህደት ተስተውሎአል፡፡
“በእኔ ያለህን እምነት
ማለቱ ነው? አባባሉ ወደ
እንደ ሞት ያሉ አስፈሪ
ብሎም አምነትን አጥብቆ
አልካድክም” (ራእ. 2፡13፣ 14፡12) ሲል ምን
ስምምነት እንድናመራ ተጽእኖ ሊያደርጉ የሚችሉ
ፈተናዎች ቢገጥሙን እንኳ--ስለ እምነት ጅማሮ
ስለመያዝ ቅዱስ የውዴታ ግዴታ ምን ይነግረናል?
ትያጥሮን ከሌሎቹ ከተሞች ጋር ስተወዳደር በዘመኗ እዚህ ግባ የሚባል ፖለቲካዊም
ሆነ ባህላዊ ግዝፈት ባይኖራትም በንግድ ቀጠናነት ግን ትታወቅ ነበር፡፡ ሰዎች ገቢ
የሚያስገኝ ሥራ ለመሥራት ከንግድ ጋር ቁርኝት ያላቸው ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች
ማድረግ ነበረባቸው፡፡ አባላት በልዩ ልዩ ማኅበራዊ ፌስቲቫሎችና ባብዛኛው
ግብረገብነት በጎደላቸው የቤተ ጣዖት ሥርዓቶች መሳተፍ ይጠበቅባቸው ነበር፡
፡
በእነዚህ ተግባራት ለመሳተፍ ፈቃደኞች የማይሆኑ ከማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች
የመገለልና የኢኮኖሚ ዕቀባ ይጠብቃቸዋል፡፡ በከተማዋ ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖች
ከሰጥቶ መቀበል እና ለወንጌል ታማኝ ሆኖ ከመዝለቅ አንዱን መምረጥ ነበረባቸው፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 2፡18-29፡፡ የሱስ ራሱን ለእነዚህ ሕዝቦች ያቀረበበት
መንገድ ምን ይመስላል? (ዳን. 10፡6) የሱስ ንጽህናቸው እንዲጠበቅ ለቤተ ክርስቲያን
አደራ ያላቸው ነገሮች ምን ነበሩ? ይህን ጉዳይ ያናወጠውስ ጉዳይ ምን ነበር?
እንደ ጴርጋሞን ቤተ ክርስቲያን ሁሉ በትያጥሮን የደረሰው አስጊ ሁናቴ መንስዔ
ከባዕድ አምልኮ ጋር የተደረሰ የልከክልህ እከክልኝ መታረቂያ ሃሳብ ነበር፡፡ “ኤልዛቤል”
በመባል የሚታወቀው ስያሜ እስራኤልን ወደ ክህደት የመራችውን የንጉሥ አክዓብን
ሚስት ይወክላል (1ነገሥ. 16፡31-33)፡፡ የሱስ በመንፈሳዊ ግልሙትና የሚስላትን
ኤልዛቤል ትምህርት እንደ ዋዛ የሚያልፉ ከእርሷ ጋር መንፈሳዊ ምንዝር ይፈጽማሉ፡፡
በትያጥሮን ቤተ ክርስቲያን የተገለጸው አጠቃላይ ሁናቴ በመካከለኛው ዘመን
የነበረውን የቤተ ክርስቲያን ገጽታ ይወክላል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ላይ ይረሰው አደጋ
የመጣው ከውጪ ሳይሆን ሥልጣናቸውን ከእግዚአብሔር እንደ ተቀበሉ ይናገሩ
በነበሩ የኃይማኖት መሪዎች ነው፡፡ በዚያን ወቅት መጽሐፍ ቅዱሳዊው እውነት በወግ
እና ልማድ ተተካ፡፡
ሰብዓዊ ክኅነት እና ቅዱሶቹ ኃይማኖታዊ ጉዳዮች የክርስቶስን
ክኅነት ተክተው ወሰዱ፡፡ ሥራ እንደ ደኅንነት ማግኛ መንገድ ታየ፡፡ የተቋማዊውን
ቤተ ክርስቲያን ብልሹ ተጽእኖ ለመቀበል ፈቃደኞች ያልሆኑ ስደት፣ ከዚያም አልፎ
ሞት ደረሰባቸው፡፡ በዚህ የተነሳ ወንጌል ለአያሌ ምዕተ ዓመታት (ዳን. 7፡25)
ተዳፍኖ ኖረ፡፡
ስለነዚህ ቃላት አሰብ ያድርጉ፡ “ ‘ብቻ እኔ እስክመጣ ድረስ ያላችሁን
አጥብቃችሁ ያዙ’ ” (ራእ. 2፡25)፡፡ ቃላቶቹ በጋራም ሆነ በግል ምን
ትርጉም አላቸው? ይህ አጥብቀን ልንይዘው የሚገባ ከየሱስ ያገኘነው
ነገር ምንድን ነው?
ሰርዴስ የድንቅ ታሪክ ባለቤት የነበረች ቢሆንም--በሮማውያን የግዛት ዘመን
የቀደመውን ክብርና ሞገስ አጣች፡፡ ከተማዋ የነበራት ሐብት ባይመክንም ነገር ግን
ክብርና ዝናዋ ከዚያን ወቅት ይልቅ በቀደመው ታሪኳ ውስጥ እንደ ተቀበረ ቀረ፡፡ ከተማዋ
የተገነባቸው በከፍታ ስፍራ ስለነበር በቀላሉ የምትቀመስ አልነበረችም፡፡
በዚህ የተነሳ
የከተማዋ ቅጥር እንደ ነገሩ ቢጠበቅ እንኳ ነዋሪዎች የደኅንት ስሜት ይሰማቸው ነበር፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 3፡1-6፣ ማቴ. 24፡42-44፣ 1ተሰ. 5፡1-8፡፡ የሰርዴስ
ክርስቲያኖች ይገኙበት ለነበረው መንፈሳዊ ሁናቴ ፈውስ ያገኙ ዘንድ አጥብቆ
ያሳሰባቸው ሦስት ነገሮች ምን ነበሩ? የሱስ “ንቃ” ሲል የሰጠው ማስጠንቀቂያ
ከከተማዋ ታሪካዊ ዳራ አኳያ እንዴት ይስማማል?
ምንም እንኳ የሱስ በሰርዴስ ለነበሩ ጥቂት ክርስቲያን ታማኞች ዕውቅና ቢሰጥም፤
አብዛኞቹ የመንፈሳዊ ሞት ሰለባ ነበሩ፡፡ በእርግጥ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከገጠማት
መንፈሳዊ ልፍስፍስነት በቀር የትኛውም ዓይነት ግልጽ ኃጢአት ክስ አልቀረባትም
(እንደ ጴርጋሞን እና ትያጥሮን)፡፡
ተቋሟ ትገኝበት በነበረው መንፈሳዊ ሁኔታ የነበራት እርካታ እንዲሁም ቀስ በቀስ
ወደ ሕይወት ዐልባ ቅርጻዊነት አዘቅት እያሽቆለቆለች መሄዷ፤ በሰርዴስ ለነበረችው
ቤተ ክርስቲያን የተሰጠውን መልእክት ከፕሮቴስታንት ድኅረ ተሐድሶ ሁኔታ ጋር
በትክክል ገጣሚ ያደርገዋል፡፡ አስተሳሰብ በምክኒያት እንጂ በእምነት ላይ መመስረት
የለበትም የሚለውና--መንፈሳዊ አስተሳሰብ በሕዝብ ላይ ተጽእኖ ሊኖረው አይገባም
የተሰኘው ሙግት ያስነሳው ተጽእኖ፤ የወንጌልን አዳኝ ጸጋ እንዲሁም ለክርስቶስ
ሊኖር የሚገባ ቁርጠኝነት እንዲዳከምና እንዲጠፋ አደረገው፡፡ ምንም እንኳ በዚህ
ዘመን የነበረችው ቤተ ክርስቲያን ሕይወት ያላት ብትመስልም፤ ተጨባጩ እውነታ
ያመላክት የነበረው በተቃራኒ መገኘቷን ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ደብዳቤው ከእያንዳንዱ ክርስቲያን ትውልድ ጋር ገጣሚና አግባብ
አለው፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያቶች ስለ ክርስቶስ የነበራቸውን ቅንአትና መንፈሳዊ
ህይወት ቢያወሩ የማይጠግቡ ክርስቲያኖች አሉ፡፡ ሆኖም የዛሬውን ተሞክሮ እንደ
ቀድሞው መናገር አለመቻላቸው ግን በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ ምንም እንኳ የቀደመውን
እውነት ባይለቁም ለወንጌል የነበራቸው ከልብ የመነጨ ቁርጠኝነት ግን ደብዝዟል፡፡
መዳን በክርስቶስ ላይ ባለን እምነት ብቻ እንደሆነ የሚገልጽውን ታላቅ
እውነት ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ጠብቀን መጓዛችን አማራጭ ባይኖረውም፤
ሥራችን በእግዚአብሔር ፊት “ፍጹም” ሆኖ አልተገኘም ልንል የምንችለው
እንዴት ነው? ይህ ምን ማለት ነው? ሥራችንን በፊቱ “ፍጹም” ማድረግ
የምንችለውስ እንዴት ነው? ማቴ. 5፡44-48፡፡
የሱስ መልእክት የላከባት የመጨረሻዋ ቤተ ክርስቲያን ሎዶቅያ ስትሆን፤ ይህች
ባለጸጋ ከተማ በዋንኛ የንግድ መስመር ላይ ትገኝ ነበር፡፡ የሱፍ ጨርቅ ምርቷ፣
ከባሕር ዳርቻዎቿ ይታፈስ የነበረው መጠነ ሰፊ የወርቅ ማዕድን እንዲሁም በህክምና
ትምህርት ቤት ይመረት የነበረ የዐይን መድኃኒት ስሟን ገናና አድርገውት ነበር፡፡
ይህ ሐብት ዜጎች በኢኮኖሚ ራሳቸውን የሚችሉበትን አቅም ፈጠረላቸው፡፡ በ60
ዓ.ም. ገደማ በከተማዋ ላይ የደረሰው ርዕደ መሬት ዜጎች በሮም ድጋፍና እርዳታ
ሥር እንዲወድቁ መንስዔ ሆኖ ነበር፡፡ ከተማዋ የመጠጥ ውሃ ችግር ስለነበረባት
ሔራፖሊስ በመባል ከሚታወቅ አካባቢ በቦይ እንዲደርሳት ተደርጎ ነበር፡፡ ታዲያ
ውሃው ይገኝ የነበረበት ስፍራ ሩቅ ስለነበር ሎዶቅያ ሲደርስ የቀድሞ ይዞታውን
አጥቶ ለብ ይል ነበር፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 3፡14-17፣ ሆሴ. 12፡8፡፡ ከተማዋ በነበራት ታሪካዊ ባህሪ
እና ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያኑን በገመገመበት አካሄድ መሃል ያሉ ተዛማጅ ሁናቴዎችን
ለይተው ለማውጣት ይሞክሩ፡፡ ከተማዋ ትገኝበት ከነበረው የኤኮኖሚ ሁኔታ አኳያ
በነዋሪዎች ላይ ይነበብ የነበረው መንፈስ፤ በሎዶቅያ ክርስቲያኖች ላይ የታየበት
መንገድ ምን ይመስላል?
የሱስ በሎዶቅያ የነበሩ ክርስቲያኖችን እንደ የሐሰት አስተምህሮ ወይም ክህደት
ዓይነት ከባድ ኃጢአት ውስጥ ወድቃችኋል ሲል አልገሰጻቸውም፡፡ ይልቁንም
የእነርሱ ችግር ወደ መንፈሳዊ ልፍስፍስነት ሊያመራ የሚችል የእርካታ ስሜት ነበር፡
፡ በራድ ወይም ትኩስ ሳይሆኑ ልክ ወደ ከተማዋ ይደርስ እንደ ነበረው የመጠጥ
ውሃ ለብ ያሉ ነበሩ፡፡ ራሳቸውን ሐብታም አድርገው ስለሚቆጥሩ ምንም ነገር
እንደማያስፈልጋቸው አድርገው ያስቡ ነበር፡፡ ነገር ግን--ድኻ፣ የተራቆተና የታወረ
መንፈሳዊ ህይወት ነበራቸው፡፡
በሎዶቅያ የነበረችው ቤተ ክርስቲያን በምድር ታሪክ መደምደሚያ የምትኖረውን
ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ሁኔታ በትክክል ትወክላለች፡፡ የሎዶቅያዋና የመጨረሻዋ
ዘመን ቤተ ክርስቲያን ትስስር በራእ. 16፡15 ጠንከር ባሉ ቃላት የተገለጸ ሲሆን፤
በዚህም ቤተ ክርስቲያኒቱ በዚያ አስከፊ ወቅት ሊደረግ ከሚገባ ዝግጅት አኳያ
ለመጨረሻው ዘመን እንደ ምሳሌ ቀርባለች፡፡ በምድር ታሪክ መዝጊያ የምትገኘው
ቤተ ክርስቲያን የቀደመው ትውልድ አይቶም ሆነ ሰምቶ የማያውቀው ዓይነት
ፖለቲካዊ፣ ኃይማኖታዊም ሆነ ዓለማዊ ነውጥ መሃል የምትገኝ ትሆናለች፡፡
ይህም ሆኖ ይህች ቤተ ክርስቲያን በራሷ የምትመካና ከሐቀኝነቷ ጋር የምትታገል
ትሆናለች፡፡ ይህ ክርስቶስ የሰጣት ማስጠንቀቂያ የእርሱ የመጨረሻው
ዘመን ቤተ ክርስቲያን አካል ለሆኑ ሁሉ እጅግ የላቀ አንደምታ አለው፡፡
ሎዶቅያን እንደሚወዳትና በእርሷ ተስፋ እንደማይቆርጥ ማረጋገጫ የሰጠው
የሱስ (ራእ. 3፡19) በማሕልየ ማሓልይ 5፡2-6 ከደጃፍ ቆሞ በሩን በሚያንኳኳና
ለመግባት በሚለምን አፍቃሪ ተማጽኖ መልእክቱን ይደመድማል፡፡ የሱስ በሩን
ከፍቶ ከሚያስገባው ከማንኛውም ሰው ጋር አብሮ እራት እንደሚበላ የተስፋ ቃል
ሰጥቶአል፡፡ ይህ ጥሪ ምላሽ ሳይሰጠው ፈጽሞ መቅረት የለበትም፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 3፡18-22፡፡ የሱስ ለሎዶቅያ ቤተ
ክርስቲያን ምዕመን የሰጠው ምክረ ሀሳብ ምን ነበር? ወርቅ፣ ነጭ
ልብስ እና ኩል ምን ይወክላሉ--(1ጴጥ. 1:7፣ ኢሳ. 61:10፣ ኤፌ.
1:17-18)? ራሳችንን እንደ ሎዶቅያ ቤተ ክርስቲያን ለምንመለከት
ለእኛ ለሰባተኛ ቀን አድቬንተስቶች ያላቸው መልእክት ምንድን ነው?
Read Ellen G. White, “The Revelation,” pp. 578–592, in
The Acts of the Apostles.
ለቤተ ክርስቲያኖቹ የተላኩት ሰባት መልእክቶች በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት
የተከሰተውን የመንፈሳዊነት መውረድ ያሳያሉ፡፡ ምንም እንኳ በኤፌሶን የነበረችው
ቤተ ክርስቲያን የቀደመ ፍቅሯን ብታጣም፤ በታማኝነቷ ጸንታ ቀጥላለች፡፡
ሰምርኔስ፣ ጴርጋሞን እና ፊላድልፊያ አብያተ ክርስቲያናትን በተመለከተ--ጥቂት
አኻዝ የነበራቸው አመጸኞች ብቻ ታማኝነታቸውን አጉድለው ነበር፡፡ ትያጥሮን
ለክርስቶስ የነበራት ታማኝነት በሁለት የተከፈለ ነበር፡፡ በሰርዴስ የነበረችው ቤተ
ክርስቲያን በከፋ ሁናቴ ውስጥ ትገኝ ነበር፡፡ ከዚህች ቤተ ክርስቲያን ምዕመን መሃል
ጥቂቶች ብቻ ታማኝ ሲሆኑ አብላጫው ሕዝበ ክርስቲያን ከወንጌል ጋር ውህደት
አልነበረውም፡፡ በሎዶቅያ የነበረችው ቤተ ክርስቲያን የምትገኘው መልካም ሊባልላት
በማይችል ሁናቴ ውስጥ እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡
የሱስ ለአብያተ ክርስቲያናቱ በሰጠው በእያንዳንዱ መልእክት ድምዳሜ፤ ምክረ
ሀሳቡን ለሚቀበሉ ሁሉ የተስፋ ቃል ይሰጣል፡፡ በየአብያተ ክርስቲያናቱ የተከሰተውን
የመንፈሳዊነት አዘቅት ቀልብሶ ዳግም እንዲያንሰራራ የሚያደርግ ተስፋ መሰጠቱን
ማንም አንባቢ በተጨባጭ ሊያስተውል ይችላል፡፡ ለየአብያተ ክርስቲያናቱ
የተሰጠውን የተስፋ ቃል ስንመለከት--የመጀመሪያዋ ማለትም ኤፌሶን የተቀበለችው
ተስፋ አንድ ብቻ ሲሆን፤ በዚህም የኋለኞቹ ከመጀመሪያዋ የላቀ ተስፋ መቀበላቸውን
እንመለከታለን፡፡ በመጨረሻው ቅደም ተከተል የምትገኘው ሎዶቅያም እንዲሁ
አንድ ብቻ የተስፋ ቃል ቢሰጣትም፤ የምትቀበለው ግን የላቀውን ነው--የዙፋኑ ተጋሪ
ያደርጋታል (ራእ. 3፡21)፡፡
1.እነዚህ እየጨመሩ የሚሄዱ የተስፋ ቃሎች ከየአብያተ ክርስቲያናቱ
በተጓዳኝ ከተስተዋለው የመንፈሳዊነት መውረድ አኳያ ኃጢአት
በጨመረ ቁጥር ጸጋው አብልጦ የመትረፍረፉን አባባል እንዴት
ያንጸባርቃሉ (ሮሜ 5፡20)? “ቤተ ክርስቲያን የቱንም ያህል ድካምና
ጉድለት ሊደርስባት ቢችል እንኳ በዚህ ምድር የክርስቶስ ከፍ ያለ
ጥበቃ ያላት ብቸኛ ተቋም ናት፡፡ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ያለማቋረጥ
በብቸኝነት በዐይኖቹ ይጠብቃታል፣ ይጨነቅላታል፣ በመንፈስ ቅዱስም
ያበረታታል፡፡”—Ellen G. White, Selected Messages, book
2, p. 396.
2.በኢንዱስትሪና በንግድ በበለጸጉ ታላላቅ ከተሞች ክርስትናንን
ጠብቆ መጓዝ አስቸጋሪ እንደሆነ አንዳንዶች ሲናገሩ ይደመጣሉ፡
፡ በእስያ በሐብት የበለጸጉ ከተሞች--ዙሪያ ገባውን በቤተ ጦዖቶች
ተከብበው ይኖሩ ከነበሩና ለወንጌል ታማኝ ሆነው አረማዊውን ተጽእኖ
ተቋቁመው ከዘለቁ ክርስቲያኖች ምን እንማራለን? እነዚያን በእስያ
የነበሩ ክርስቲያኖች የሱስ በዮሐ. 17፡15-19 በጸለየው ጸሎት ብርሃን
አሰብ ለማድረግ ይሞክሩ፡፡
በዓለም ውስጥ እየኖሩ ነገር ግን ከዓለም
ሳይሆኑ የመኖር ጽንሰ ሃሳብ በዛሬዎቹ ክርስቲያኖች ላይ መሥራት
የሚችለው እንዴት ነው? በተለይ--በታላላቅ ከተሞች የሚኖሩ አማኞች?
3.እኛ እንደ አድቬንቲስት ለሎዶቅያ የተሰጡትን መልእክቶች
አክብረንና በጥንቃቄ አስተውለን መራመድ የምንችለው እንዴ ነው?