የሕይወት ምዕራፎች
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 2ኛ ሩብ ዓመት 2019

ከሚያዝያ 12-18

4ኛ ትምህርት

Apr 20 - Apr 26




ብቸኝነት ሲከሰት



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ መክ. 4:9–12፣ ፊልጵ. 4:11–13፣ 1ቆሮ. 7:25–34፣ ማቴ. 19:8፣ ዘፍ. 37:34፣ ኢሳ. 54:5።


መታሰቢያ ጥቅስ:- “ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ ሰው ብቻውን መሆኑ መልካም አይደለምና የሚስማማውን ረዳት አበጅለታለሁ አለ።” (ዘፍ. 2፡18)።

ከ ዓመታት በፊት ከወደ አሜሪካ የተሰማው ወሬ እጅግ አስገራሚና ሰቅጣጭ ነበር። አንዲት በሃያዎቹ መጀመሪያ ዕድሜ የነበረች ሴት በመኖሪያ አፓርታማዋ ሞታ መገኘቷ በራሱ አሳዛኝ ዜና ቢሆንም፤ አስከሬኗ ሲገኝ ዐሥር ዓመት ያለፈው መሆኑ ግን ጉዳዩን ይበልጥ ልብ የሚሰብር አድርጎት ነበር። በጣም ብዙ ሰዎች በሚኖሩበት ከተማና ሰዎች በቀላሉ ሊገናኙ የሚችሉባቸው ብዙ መንገዶች እያሉ ተመልካች እንደ ሌለው የጎዳና ተዳዳሪ ማንም ሳያውቅ ይህን ያህል ዘመን አስቆጠረች? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነበር።

በእርግጥ ታሪኩ ብዙም ያልተለመደ ቢሆንም ነበር ግን ብዙዎች በብቸኝነት መሰቃየታቸው የዕለት ከዕለት ክስተት ነው። በጎርጎሮሳውያኑ ቀመር 2016 ታዋቂው ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ “Researchers Confront an Epidemic of Loneliness.” በሚል ርዕስ የወጣው ጽሑፍ ችግሩን በተጨባጭ ያመላከተ ነበር።

እኛ ገና ከመጀመሪያው በብቸኝነት እንድንኖር ሆነን አልተፈጠርንም። ይልቁንም ከኤደን ገነት አንስቶ ይብዛም ይነስም ከሰዎች ጋር ኅብረት ፈጥረን እየኖርን እንገኛለን። በእርግጥ ኃጢአት ጣልቃ በመግባቱ የተነሳ ከዚያን ጊዜ አንስቶ አንዱም ነገር እንደ ታቀደው መሄድ ሳይችል ቀርቶአል። በዚህ ሣምንት ጥናታችን በተለያዩ የህይወት ምዕራፎች ምናልባትም ብዙዎቻችንን ሊያጋጥሙ በሚችሉ፤ በአብሮነትና ብቸኝነት ዙሪያ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመልከት እንሞክራለን።

ሚያዝያ 13
Apr 21

አብሮነት


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 4፡9-12። እዚህ ላይ የምናገኛቸው መሰረታዊ ጽንሰ ሃሳቦች ምንድን ናቸው? በአጠቃላይ ሲታይ ምን ዓይነት የህይወት መርኅዎች ቀርበዋል?



የብቸኝነት ነገር ለብዙዎቻችን አይሆንልንም። ብቸኛ ብንሆንና ይህንኑ ብቸኝነታችንን የምንወደው ቢሆንም እንኳ ወዲያውኑ ወይም ዘግየት ብለን አብሮነትን መሻት ብቻ ሳይሆን ነገር ግን የግድ እንደሚያስፈልገን ይሰማናል--በተለይ ሰው በሚያስፈልገን ወቅት። በእርግጥ እኛ እንደ ማህበረሰብ ኅብረት እንዲኖረን ሆነን ተፈጥረናል። በተለይ አስፈላጊ በሚሆንበት ሰዓት ላይ አንዱ ለሌላው መጽናናትና ድጋፍ የሚያደርግበት ቤተሰብ እንዴት ዕድለኛ ነው።

የሚያሳዝነው በቤተ ክርስቲያን፣ በሥራ ቦታ እንዲሁም በመኖሪያ አካባቢያችን በሰዎች ብንከበብም ነገር ግን ከሰዎች ጋር አጽናኝ ምክረ ሀሳቦችን መለዋወጡ ቀርቶ የረባ ነገር እንኳ ሳንባባል ብርድ ብርድ እንዳለን ቀኑ ይገባደዳል። ብቸኝነት በማንኛውም ጊዜ ሊመጣ ይችላል። አንድ ትዳር ያልመሰረተ ሰው እንዲህ ሲል ተደምጦአል “በሣምንቱ ቀናት በሰዎች እንደ ተከበብኩ በሥራ አሳልፋለሁ። ሰንበት ላይ ሰዎችን በቤተ ክርስቲያን አያለሁ። እሁድ ቀን ግን ብቻዬን ስለማሳልፍ ለእኔ ከባዱ ቀን እሱ ነው።”

በተለይ በብቸኝነት ጊዚያቶች ውስጥ ስናልፍ ከሚከተሉት ጥቅሶች ምን ዓይነት መርኅዎች መማር እንችላለን? ዮሐ. 16፡32-33፣ ፊልጵ. 4፡11-13።



እንደ ክርስቲያን የአምላካዊውን ተጨባጭ ነባራዊ ማንነት ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ከእርሱ ጋር አምልኮ ማድረግ የመቻልንም እውነታ እንጋራለን። ከእርሱ ጋር ባለን አብሮነት ደግሞ መጽናናት እናገኛለን። እግዚአብሔር በኤደን የአትክልት ስፍራ ከአዳም ጋር የነበረው ቀረቤታ “ሰው ብቻውን መሆኑ መልካም አይደለም” (ዘፍ. 2፡18) እንዳይል አላደረገውም። በመሆኑም በኃጢአት ጉዳት ባልደረሰበት ዓለም ይኖር የነበረው አዳም ከእግዚአብሔር ጋር ሕብረት ኖሮት ቢመላለስም ሰብዓዊ ወዳጅ ያስፈልገው ነበር። ነገሩ እንዲህ ከሆነ እኛ የተቀረነው ከዚህ በላቀ ሰው እንደሚያስፈልገን ለመገመት ብዙም አያዳግትም።

ዙሪያ ገባው በሰዎች ተከብቦ እንዴት አንድ ሰው ብቸኝነት ሊሰማው ይችላል ብለን ከማሰብ መጠንቀቅ ይኖርብናል። በታላላቅ ከተሞች በብቸኝነት ከሚኖሩት መሃል አንዳንዶቹ ከሰዎች ጋር መስተጋብር ያላቸው ናቸው። አንድ ሰው ከሌሎች አካላት ጋር አብሮ መሆኑ ብቸኛና የተነጠለ ሆኖ እንዳይሰማውና ጓደኝነት እንዳያስብ ያደርገዋል ለማለት አያስደፍርም።

ብቸኛውን፣ ከሌሎች የተነጠለውንና ተቀባይነት ያጣውን እና ሰው እንደሚያስፈልገው ሆኖ የሚሰማውን ሰው ለማወቅ ብሎም ለማናገር ሁሌም ቀላል አይደለም። በዚህ ሁኔታ ውስጥ የወደቀው ሰው ማንም ይሁን ማን--ስሜትዎትን በተጨባጭ ማጋራት የሚችሉት እንዴት ነው?

ሚያዝያ 14
Apr 22

ትዳር ያልመሰረተው ህይወት


በትዳር ያለመጣመር ያለውን ጥቅም አስመልክታ አንዲት ወጣት ስትናገር “ከአንዴም ሁለቴ ለመስክ አገልግሎት የዝውውር ጥሪ ሲቀርብልኝ ምላሽ ለመስጠት ምንም አላመነታሁም ነበር” ብላለች። በተቃራኒው በጋብቻ የተጣመረና ቤተሰብ የመሰረተ ሰው ውሳኔው ግለሰቡን ብቻ ሳይሆን የትዳር ጓደኛንና ልጆችን ስለሚነካ እንዲህ ያለው ውሳኔ ላይ ለመድረስ ብዙ ጊዜ ሊፈጅበት ይችላል።

ጳውሎስ እንደሚለው ሳያገቡ ለመቅረት እንደ መልካም ምክንያት መቆጠር የሚችሉ ነጥቦች የትኞቹ ናቸው? 1ቆሮ. 7፡25-34



ብዙዎች እንደሚያስቡት ትዳር መመስረት የሚቻለው እግዚአብሔር ሲፈቅድ ብቻ ነው። በእርግጥ እርሱ ራሱ “‘ሰው ብቻውን መሆኑ መልካም አይደለም’” ሲል ቢናገርም፤ ታላቁ ምሳሌያችን የሆነውን የሱስን ጨምሮ ትዳር ያልመሰረቱ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች አሉ።

ነቢዩ ኤርምያስ ከነበረበት ታሪካዊው ሁነት አኳያ እንዳያገባ ተነግሮት ነበር (ኤር. 16፡1-3)። ይህ ዕገዳ ተነስቶለት እንደሆን የምናውቀው ነገር ባይኖርም፤ ነገር ግን ሳያገባ የዘለቀው ኤርምያስ ታላቅ ነቢይ እንደነበር ግልጽ ነው።

እንዲሁም የሕዝቅኤል ሚስት በድንገት ብትሞትም የእርሱ በጋብቻ ተሳስሮ የመኖር ሁናቴ እምብዛም አጽንኦት ሲሰጠው አይስተዋልም። ይህ ነቢይ ጌታ በሰጠው አገልግሎትና ተልዕኮ ከመሰማራት ውጪ ለደረሰበት ሐዘን እንዲቀመጥ እንኳ አልተፈቀደለትም ነበር (ሕዝ. 24፡15-18)። ነቢዩ ሆሴዕ የጋብቻ መፍረስ ቢገጥመውም ነገር ግን በአገልግሎቱ መግፋት ችሎ ነበር። ታሪኩ እንግዳ ሊሆንብን ቢችልም ሆሴዕ በሌላ ሰው የምትለውጠውን አንዲት ሴተኛ አዳሪ እንዲያገባ እግዚአብሔር ሲነግረው እንመለከታለን (ሆሴ. 1-3)። ነገሩን ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንቃኝ እግዚአብሔር ለእስራኤል የነበረውንና ለእኛ ያለውን በአንድ ጎን ያዘነበለ ፍቅር ለማሳየት መጣሩን መገንዘብ ብንችልም ነገር ግን ጉዳዩ በተጨባጭ መማሪያ ለሆነው ሆሴዕ ብርቱ ሥቃይ ማስከተሉን ለመገመት አይከብድም።

በእነዚህ በሁለቱም ምሳሌዎች የጋብቻ ሁናቴ ያን ያህል አሳሳቢ ጉዳይ አልነበረም። እግዚአብሔር ይፈልግ የነበረው የግለሰቡን ሐቀኝነት፣ ታዛዥነትና ጌታ የነገረውን የማስተላለፍ ክህሎት ነበር። ሕይወታችን በጋብቻ ሁኔታችን ሊገለጽ እንደማይችል እርግጠኞች ልንሆን ይገባል። ካላገባን ወይም ትዳር ካልመሰረትን በቀር ሙሉ ሰው አለመሆናችንን የሚገልጹ አያሌ ድምፆች በጆሮአችን ሽው ይላሉ። ለዚህ አባባል ጳውሎስ ምላሽ አለው፡ “ሰውነታችሁን ቅዱስና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕያው መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ… እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ” (ሮሜ. 12፡ 1-2)።

የቤተ ክርስቲያን አባል ለሆኑ እንዲሁም ላልሆኑ ትዳር ያልመሰረቱ ወገኖች አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉባቸው ተጨባጭ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

ሚያዝያ 15
Apr 23

ጋብቻ በፍቺ ሲያከትም


ኃጢአት በሁሉም አቅጣጫ ሰብዓዊው ፍጡር ላይ ውድመት አስከትሎአል። መተላለፍ አካላዊ ሥቃይና ሞት ከማስከተሉ በዘለለ በቤተሰብ ላይ ሊያደርስ ከሚችለው የጥፋት መጠን በላይ ምን ሊኖር ይችል ይሆን? ለመሆኑ ቤተሰብ እንደሚገባው መሥራት ወይም መቀጠል የሚሳነው ምን ሲሆን ነው?

ከሞት ባሻገር በቤተሰብ ላይ ከሚደርሱ የከፉ ችግሮች አንዱ ፍቺ ነው። በዚህ አስከፊ ተሞክሮ የሚያልፉ ይሄ ነው የማይባል የልብ መሰበር ይገጥማቸዋል። መጠንና ደረጃው እንደየሰዉ የሚለያየው የበረታ ሐዘንና የልብ መሰበር ለወራት ብሎም ለዓመታት የሚዘልቅ ሊሆን ይችላል።

አንዳንዶች ከዚህ ቀደም በማያውቁት ፍርሐት ውስጥ የሚወድቁ ሲሆን የገቢ ምንጭ መድረቅ ስጋትና ነገሮችን ተቋቁሞ ማለፍ ያለመቻል ፍርሐት ዋንኞቹ ናቸው። በዚህ የተነሳ በድብርት ወይም ድባቴና ብስጭት እንዲሁም በእርግጠኝነት በብቸኝነት ውስጥ ማለፋቸው የታወቀ ነው። ፍቺን አስመልክቶ ከሚከተሉት ጥቅሶች ምን ዓይነት ሰፋ ያሉ መርኅዎችን እናገኛለን? ሚልክ. 2:16፣ ማቴ. 5:31- 32፣ 19:8፣ 1ቆሮ. 7:11–13።



“የቤተ ክርስቲያን አባሎች በክርስትና ተሞክሮአቸው ያድጉና ይበለጽጉ ዘንድ ቤተ ክርስቲያን እንደ ክርስቶስ ቤዛ ወኪልነቷ በሚያስፈልጋቸው ሁሉ ማገልገል ይኖርባታል--በተለይ መላውን የሕይወታቸውን ክፍል ዘልቆ የሚነካውን እንደ ጋብቻ ያሉ ውሳኔዎችንና ፍቺ ዓይነቱን አስጨናቂ ተሞክሮ ሲጋፈጡ። የባልና ሚስት የትዳር ህይወት የመፍረስ አደጋ ሲገጥመው የቆሰለው ግንኙነት ወደ ቀድሞው ሁኔታ እንዲመለስና እርቅ እንዲወርድ በቅርብ አጋሮችና በቤተ ክርስቲያን ወይም በቤተሰብ ጉባዔ ከመለኮታዊው መርኅዎች አኳያ አገልግሎት የመስጠት ጥረት ሊደረግ ይገባል (ሆሴ 3:1–3፣ 1ቆሮ. 7:10-11፣ 13:4–7፣ ገላ. 6:1)።

“ጠንካራ ክርስቲያናዊ ቤተሰብ ለማነጽ በሚደረገው ሂደት አስተዋጽዖ ሊያደርጉ የሚችሉ መረጃዎችን ከቤተ ክርስቲያን ማግኘት ይቻላል። እነዚህ መረጃዎች የሚከተሉትን ያካትታሉ፡ (1) ወደ ጋብቻ ለሚያመሩ ጥንዶች ገለጻና አቅጣጫ ማስያዝ የሚያስችሉ መርኀ ግብሮች (2) ባለትዳሮችንና ቤተሰባቸውን የሚያካትት ትምህርት የመስጠት መርኅ ግብር (3) የትዳር መፍረስ ለገጠመው ቤተሰብና በፍቺ ለተለያዩ ጥንዶች ድጋፍ የማድረግ መርኅ ግብር ማካሄድ ናቸው።”—The Seventh-day Adventist Church Manual, 19th edition (Nampa, Idaho: Pacific Press Publishing Association, 2016), p. 161. እርስዎ በፍቺ ውስጥ የሚያልፉ ወገኖችን ሊረዱ የሚችሉባቸው ከፍረጃ የተጠበቁ ተጨባጭ አካሄዶች የትኞቹ ናቸው?

ሚያዝያ 16
Apr 24

ሞትና ብቸኝነት


ሞትን አስመልክቶ የሚነሱ ብዙ ጥያቄዎች አሉ። ለመሆኑ በሰዎችና በጫጩቶች መሃል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? ሲል አንድ ሰው ለጠየቀው ጥያቄ--ሟች የሆኑት ሰዎች መሞታቸውን ከማያውቁት ጫጩቶች በተቃራኒ መሞታቸውን ማወቃቸው እንደ መልስ መወሰድ ይችላል። ይህ ሁኔታ ስለ አይቀሬው ሞታችን ያለን ዕውቀት በአኗኗራችን ላይ ብርቱ ተጽእኖ እንዲኖረው ያደርጋል።

ጋብቻን ጨምሮ ሁሉም ዓይነት ግንኙነቶች በታላቁ ጠላታችን ሞት አማካኝነት አንድ ቀን እንደሚያከትም ሁላችንም እንገነዘባለን። የቱንም ዓይነት ነፋስ ገብቶበት የማያውቅ የትዳር ህይወት ቢኖረን፣ እጅግ ብንዋደድ፣ ጥልቅ ወዳጅነት ብንመሰርትና ብዙ ጊዜዎችን አብረን ብናጠፋ--እንደ ሰው የየሱስ ዳግም ምጽአት ጣልቃ ካልገባ በቀር ውሎ አድሮ መተሳሰራችን በሞት እንደሚፈታ እናውቃለን (ከጫጩቶች በተቃራኒ)።

ከአዳምና ሔዋን ማናቸው ቀድመው በሞት እንደተለዩ መጽሐፍ ቅዱስ ባይነግረንም፤ ሐዘኑ በተለይ ለቀሪው እጅግ መሪር ሊሆን እንደሚችል ለመገመት አይከብድም። ሲጀመር ሞት የህይወት ክፍል ይሆናል ብሎ ማን አስቦት? ቀደም ባለው ትምህርታችን የአንድ ቅጠል መጠውለግ የአዳምና ሔዋንን ልብ በሐዘን ከሰበረ የትዳር አጋርን ማጣት ምን ማለት ሊሆን እንደሚችል ማን ሊገምት ይችላል?

ሞትን እጅግ ከመለማመዳችን የተነሳ እምብዛም ትኩረት እየሰጠነው አለመሆኑ በራሱ ትልቅ ችግር ነው። ሆኖም ጉዳዩ እኛ ሰብዓዊ ፍጡራን እንደተለማመድነው ዓይነት መሆን አልነበረበትም። በዚህ የተነሳ እነሆ እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ በተደጋጋሚ ያልሆነልንን ትርጓሜ ለመስጠት እየታገልን እንገኛለን። ሰዎች ስለ ሞት እና ከሞት ጋር እያደረጉ ስለሚገኙት ትግል የሚከተሉት ጥቅሶች ምን ያስተምሩናል? ኢሳ. 57:1፣ ራእ. 21:4፣ 1ተሰ. 4:17-18፣ ማቴ. 5:4፣ 2ሳሙ. 18:33፣ ዘፍ. 37:34።



ራሳችን አንድ ቀን እንደምንሞት ብንገነዘብም ነገር ግን የምንወዳቸውንም ሆነ የቅርብ ወዳጆቻችንን ሞት መጋፈጣችን አጠያያቂ አይደለም። በመሆኑም ውሎ አድሮ ሞት በሚያስከትለው ጦስ ብቸኝነትን መጋፈጣችን አይቀሬ ይሆናል። ምንም እንኳ ሐዘኑ በእጅጉ ልብ የሚሰብርና የሚጎዳ ሊሆን ቢችልም አምላካዊውን የተስፋ ቃል መማጸን የግድ ይሆናል። ለነገሩ ከዚህ ኃጢአት፣ ሥቃይና ሞት ከነገሠበት ዓለም ሌላ ምን የረባ ነገር ሊጠበቅ ይችላል?

የሚወዱትን በሞት አጥተው በከባድ የብቸኝነት ልብ ስብራት ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን ቤተ ክርስቲያንዎ የምትደግፍበት መንገድ ምን ይመስላል?

ሚያዝያ 17
Apr 25

ነጠላ መንፈሳዊ ህይወት


በትዳር ሰባት ዓመታት ያስቆጠረችውና ገና በወጣትነት ዕድሜ ያለችው ወይዘሮ ናታሊ በአንዲት ጓደኛዋ ግብዣ የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን የወንጌል ጉባዔ ላይ መታደም ችላ ነበር። ወጣቷ ወይዘሮ ባገኘችው እውነት በመነካቷ ልቧን ለክርስቶስ ሰጥታ በጥምቀት አዲስ ፍጥረት ሆና ተወለደች። ምንም እንኳ በባሏ፣ በወላጆቿ፣ በባሏ ቤተሰቦች ይባስ ብሎ በጎረቤቶቿ ሳይቀር ከባድ ተቃውሞ ቢገጥማትም ናታሊ ግን የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን አባል ሆነች።

የአኗኗር ዘይቤዋንም በተቻላት አዲስ ካገኘችው እምነቷ አኳያ አስተካከለች። ማንም ሊገምት እንደሚችለው ወጣቷ ወይዘሮ ብርቱ ተግዳሮት ገጠማት። ሁኔታዎችን እጅግ ፈታኝ ካደረጉባት ቀዳሚው “ስንጋባ የፈረምኩት የጋብቻ ሰነድ ለዚህ ዓይነቱ ማንነት አይደለም። አንቺ ፍጹም አዲስ ሰው ሆነሻል። እኔ የምፈልጋት ያቺን የበፊቷን ናታሊ ነው” እያለ ባለቤቷ ነጋ ጠባ ይነዘንዛት ጀመር። ናታሊያ ለዓመታት የእምነት ህይወት ለመኖር እየታገለች ትገኛለች። ያገባች ቢሆንም ነጠላ በመባል የሚታወቀውን ዓይነት መንፈሳዊ ህይወት ትመራለች። ነጠላ መንፈሳዊ ህይወት ለሚመሩ ወገኖች ምን ዓይነት ማበረታቻዎች ከሚከተሉት ጥቅሶች ማግኘት እንችላለን? ኢሳ. 54:5፣ ሆሴ. 2:19-20፣ መዝ. 72:12።



በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ቤተ ክርስቲያኖቻችን አያሌ ናታሊያዎች አሉ። ባልና ሚስት በጋብቻ ተሳስረው ቢኖሩም ነገር ግን ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመጡት ከሁለት አንዳቸው ብቻ ወይም ልጆቻቸውን አስከትለው ነው። ምናልባት ከመጀመሪያው ጋብቻ የመሰረቱት ከእምነታቸው ውጪ ከሆነ ሰው ጋር ሊሆን ይችላል። ወይም ከተጋቡ በኋላ አንዳቸው ወደ ጌታ ሲመጡ ሌላው ወገን ሳይሆንለት ቀርቷል። ወይም ደግሞ ሁለቱም አማኞች ሆነው ተጋብተው መኖር ከጀመሩ በኋላ ከሁለት አንዳቸው ቤተ ክርስቲያን መምጣት ያቆሙና ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በእምነቱ ላይ ጥላቻ እያዳበሩ መጥተው ሊሆን ይችላል።

በመሆኑም ባልና ሚስት ከሁለት አንዳቸው ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥተው አምልኮ ያደርጋሉ፤ ከአገልግሎት በኋላም ሊኖር በሚችል የምሳ ቆይታ እንዲሁም የጉብኝት መርኀ ግብር ብቻቸውን ይካፈላሉ። የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት በገንዘብ የመደገፍ ፍላጎት ቢኖርም በጉዳዩ የትዳር ጓደኛ ላይስማማ ይችላል ወይም ላትስማማ ትችላለች። ባልና ሚስቱ በትዳር ተሳስረው እየኖሩ ቢሆንም ከመንፈሳዊ ህይወታቸው አንፃር የትዳር ጓደኛቸው በሞት እንደ ተለያቸው ሆኖ ይሰማቸዋል።

እኛ ሁላችን እንደነዚህ ዓይነቶቹን ወገኖች በቤተ ክርስቲያን የምንገናኝበት አጋጣሚ ሊኖር ከመቻሉ አኳያ ፍቅራችንና ድጋፋችን እንደሚያሻቸው አንዘንጋ። እንደ አንድ የቤተ ክርስቲያን ቤተሰብ በመካከላችን ነጠላ መንፈሳዊ ህይወት ለሚመሩ ወገኖች ምን ዓይነት ተጨባጭ ነገሮችን ማድረግ እንችላለን?

ሚያዝያ 18
Apr 26

ተጨማሪ ሀሳብ


: “ሔኖክ በንቃትና በቅልጥፍና ይሠራ በነበረበት የብርታት ዘመኑ ከእግዚአብሔር ጋር ጽኑ ግንኙነት መሰረተ። ሥራውን በሙሉ አቅሙ በሠራ ቁጥር ጸሎቱም ያን ያህል የማያወላውልና ታማኝ ነበር። ሆኖም ሔኖክ የሆነ ሰዓት ላይ ራሱን በተወሰነ ደረጃ ከማኅበረሰቡ መነጠል ጀመረ። በዚህም ሔኖክ ለተወሰነ ጊዜ ከሕብረተሰቡ ጋር ተቀላቅሎ ለሰዎች መሻሻልና ጥቅም ካገለገለና መልካም ምሳሌ ሆኖ ከሠራ በኋላ--የመለኮታዊ ዕውቀት ረሃቡንና ጥማቱን ለማስታገስ ከእግዚአብሔር ጋር በብቸኝነት ወደሚገናኝበት የተነጠለ ስፍራ ያመራ ነበር።

ሔኖክ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን ሕብረት ለማጎልበት በተጋ መጠን አብልጦ መለኮታዊውን አምሳል ማንጸባረቅ ቻለ። በፊቱ ገጽታ ይስተዋል የነበረው ቅዱስ ጸዳል በየሱስ ላይ እንደነበረው ደማቅ፣ ብሩህና አንጸባራቂ ነበር። ሔኖክ ከመለኮታዊው ሕብረት ቆይታው ተመልሶ ወደ ሕብረተሰቡ ሲቀላቀል በክህደት ያሉ ሳይቀሩ የገጽታውን ሰማያዊ ተጽእኖ በታላቅ አክብሮትና በፍርሃት ይታዘቡ ነበር።”—Ellen G. White, Gospel Workers, p. 52.

ምንም እንኳ ይህ የሔኖክ ታሪክ አበረታችና በብቸኝነት ከጌታ ጋር ለመገናኘት ለሚመርጡ ወገኖች ብርቱ መልእክት ሊሆን ቢችልም፤ ነገር ግን ብዙዎች በማይፈልጉት የብቸኝነት ድባብ ውስጥ ለመውደቅ ሲገደዱ ይስተዋላሉ። በእርግጥ በማንኛውም ስፍራ መገኘት ከሚችለው ጌታ ጋር ሁሌም አስደሳች ኅብረት ሊኖረን ቢችልም አንዳንዴ ሰብዓዊውን ወዳጅነትና አብሮነት መናፈቃችን ግን እሙን ነው።

እኛ እንደ ቤተ ክርስቲያን በከባድ የብቸኝነት ወቅት ላይ ሊገኙ የሚችሉ፣ በየሣምንቱ ሰንበት ጠኋት ከጎናችን የሚቀመጡ ወገኖች ጋር ለመድረስ አብልጠን ዝግጁ ልንሆን ይገባል። ይህ በእንዲህ እንዳለ እርስዎ ተመሳሳይ ስሜት እየተጋሩ ከሆነ አንድ የሚያምኑት ሰው ጉዳዩን እንዲያውቅ ያድርጉ። ብዙውን ጊዜ አንድን ሰው በመመልከት ብቻ በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንዳለፈ መናገር አይቻልም። ስለዚህ ራስን በጭምብል መሸሸግ ለአንዳንዶች ብዙም ከባድ ላይሆን ይችላል።


የመወያያ ጥያቄዎች




፡ 1.ቤተ ክርስቲያንዎ በብቸኝነት ማዕበል ለሚዋትቱ ዙሪያችን ላሉ ወገኖች ጥንቁቅና ምላሽ ሰጭ መሆንን መማር የምትችለው እንዴት ነው?

2.“ይህን የምለው ስለ ቸገረኝ አይደለም ምክንያቱም በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ያለኝ ይበቃኛል ማለትን…ተምሬአለሁ” (ፊልጵ. 4፡ 11-12)። እዚህ ላይ የቀረበውን ሙሉውን የጳውሎስ መልእክት ያንብቡ። እነዚህን መርኅዎች በህይወታችን ተግባራዊ ማድረግ መማር የምንችለው እንዴት ነው? በተመሳሳይ እነዚህን ጥቅሶች በጣም ለተጎዳ ሰው ስንጠቅስ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?

3.እርስዎ ስላለፉባቸው አስቸጋሪ የብቸኝነት ጊዜያቶች በክፍል ውስጥ ተወያዩ። በምን ዓይነት እርዳታ ማለፍ ቻሉ? የጎዳዎት ነገር ምን ነበር? ለሌሎች ትምህርት መሆን የሚችል--ምን አገኙ?