“ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ…”
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 3ኛ ሩብ ዓመት 2019

ከጳግሜ 2 - መስከረም 2

11ኛ ትምህርት

Sep 07 - Sep 13




በዳግም ምጽአቱ ተስፋ መኖር



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ራእ. 15:1፣ 7:1–3፣ 14:9-10፣ 16:1–12፣ 17:1፣ ዳን. 5፣ ራእ. 16:16፣ 2ተሰ. 2:9–12፡፡


መታሰቢያ ጥቅስ:-"ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፤ ጸንታችሁ ቁሙ፤ በምንም ነገር አትናወጡ፡፡ ለጌታ ሥራ ዘወትር የምትተጉ ሁኑ፤ ምክንያቱም ለጌታ የምትደክሙት በከንቱ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ" (1ኛ ቆሮንቶስ 15:58)።

የ እግዚአብሔርን መንግሥት ዛሬ ልንወርሰው የምንችል ተጨባጭ እውነታ አድርጎ የሱስ አስታውቆናል፡፡ ይህንኑ መልእክት እያበሰሩ፣ ወንጌልን እየሰበኩና ሌሎችን እያገለገሉ መንግሥቱን ያውጁ ዘንድ ደቀ መዛሙርቱን ላከ፡፡ ያም ማለት በነጻ አንደ ተቀበሉ በነጻ ይሰጡ ነበር (ማቴ. 10፡5-8)፡፡

የሱስ የእርሱ መንግሥት ከተለመደው የተለየ ስለ መሆኑ “የእኔ መንግሥት ከዚህ ዓለም አይደለም” በማለት በግልጽ ተናግሮአል (ዮሐ. 18፡36)--በሙላት ሊመጣ ያለ እንጂ! ሥጋ በመልበሱ፣ በአገልግሎቱ፣ በሞቱና በትንሣኤው እነሆ የእግዚአብሔር መንግሥት ተቋቋመ፡፡ ነገር ግን የእርሱ መንግሥት የዚህን ዓለም መንግሥት ሙሉ ለሙሉ የሚተካበትንና የእግዚአብሔር ንግሥና ፍጹም ሆኖ ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ የሚያስተጋባበትን ጊዜ አሻግሮ ይመለከታል፡፡

አድቬንቲስት ወይም የክርስቶስን ዳግም ምጽአት የሚጠባበቁ የተሰኘው ስያሜ-ተስፋ የሚያደርጉ ሕዝቦች የሚል ፍቺ አለው፡፡ በእርግጥ ይህ ተስፋ ወደፊት የሚመጣውን አዲስ ዓለም ብቻ ያማከለ አይደለም፡፡ ተስፋ የወደፊቱን አሻግሮ እንደሚመለከት ሁሉ የአሁን ሁኔታንም ይቀይራል፡፡ በዚህ ተስፋ ዛሬን እየኖርን የወደፊቱንም እንጠባበቃለን፡፡ ዓለም አንድ ቀን ምን ሊሆን እንደሚችል ተስፋ ከምናደርገው ጋር የተጣጣመ ለውጥ ለማምጣት አሁን መሥራት እንጀምራለን፡፡

ጳግሜ 3
Sep 08

“ጌታ ሆይ፤ እስከ መቼ?”


ብዛት ባላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች የአምላካዊውን ጣልቃ ገብነት የሚጠይቁ ከእግዚአብሔር ሕዝቦች የቀረቡ ተደጋጋሚ ጥሪዎች አሉ--በተለይ በባርነት፣ በግዞት፣ በጭቆና፣ በድኽነት ወይም በሌሎች ኢፍትሐዊ ወይም አሳዛኝ ሁኔታዎች ውስጥ ከነበሩ ህዝቦች፡፡ በግብፅ ባርነት እና በባቢሎን ግዞት ስር ወድቀው የነበሩ እስራኤላውያንን ጨምሮ ሌሎች አያሌ ወገኖች እግዚአብሔር ሥቃያቸውን እንዲሰማ፣ እንዲመለከትና የተበላሸውን እንዲያቃና የጩኸት ድምጾቻቸውን አሰምተዋል፡፡ እግዚአብሔር እነዚህን ሕዝቦቹን ለማዳንና ወደ ቀድሞው የተሻለ ሁኔታ ለመመለስ፤ እንደውም አንዳንዴ ጨቋኞቻቸውንና ጠላቶቻቸውን እስከ መበቀል የደረሰባቸውን አጋጣሚዎች መጽሐፍ ቅዱስ በምሳሌ ያስነብበናል፡፡

ነገር ግን ብዙውን ጊዜ እነዚህ የመታደግ ሥራዎች ለአጭር ጊዜ ብቻ ዕድሜ ያላቸው እንደመሆናቸው፤ ነቢያት እግዚአብሔር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የክፉው ዘመን አክትሞ የተገፉትን ከፍ ከፍ የሚያደርግበትን ጊዜ አሻግረው መመልከታቸውን ቀጥለዋል፡፡ በተጨማሪ እነዚህ ነቢያት “ጌታ ሆይ እስከ መቼ ነው?” ብለው ማንባታቸውንም አላቆሙም፡፡ ለምሳሌ የእግዚአብሔር መልአክ ስለ እሰራኤላውያን የግዞት ዘመን እንዲህ ብሎ ጠይቆአል “እግዚአብሔር ጸባኦት ሆይ… የማትምራቸው እስከ መቼ ነው” (ዘካ. 1፡12)፡፡

መዝሙረ ዳዊት ኃጥአን በግልጽ እየበለጸጉና የመልካም ዕድል ባለቤት እየሆኑ ጻድቃን ግን የጉዳት፣ የብዝበዛና የድኽነት ሰለባ መሆናቸውን እያነሳ ብርቱ የሰቆቃ ድምጽ ያሰማል፡፡ እግዚአብሔር ጣልቃ እንዲገባ በተደጋጋሚ ጥሪውን እያቀረበና ምድር በእግዚአብሔር በተፈጠረች ጊዜ ዛሬ ያላትን ሁኔታ እንዳልያዘች ወይም እንድትይዝ አምላካዊው ፈቃድ እንዳልነበር እየገለጸ “ጌታ ሆይ እስከ መቼ?” ሲል እርሱም የነቢያቱንና የተጨቆኑትን የልቅሶ ድምጽ ያሰማል (መዝ. 94፡3-7)፡፡

ለሰዎች ሁሉ ፍትሕ የሚመኝ የፍትሕ አምላክ በሚመለክበት እምነት ውስጥ ኢፍትሐዊነትን ተቀብሎ መኖር ይበልጥ አስቸጋሪ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝቦች በዓለም በሰፈነው ክፉው ላይ ሁሌም ቢሆን ትዕግሥት አይኖራቸውም፡፡ ደግሞም ብዙም ሳይቆይ ገቢራዊ ሊሆን የሚችለው አምላካዊ ፍርድ--ሌላው ትዕግሥት የለሽ የሚያደርጋቸው ምክንያት ነው፡፡ ስለዚህ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ለእርዳታ እየተጣራሁ አንተ የማትሰማው እስከ መቼ ነው? ‘ግፍ በዛ’ ብዬ እየጮኽሁ፣ አንተ የማታድነው አስከ መቼ ነው?” (ዕንባ. 1፡2) የሚሉ ጥብቅ ጥያቄዎችን አልፎ አልፎ ነቢያት ይጠይቃሉ፡፡

ፍጥረት ራሱ የሚቃትትበትና እግዚአብሔር እንዲታደገው ተማጽኖ የሚያቀርብበት ተመሳሳይ የልቅሶ ድምጽ በአዲስ ኪዳን ቀርቦአል (ሮሜ 8፡19-22)፡፡ በራእ. 6፡ 10 “ጌታ ሆይ፤ እስከ መቼ?” በሚል የቀረበው የልቅሶ ድምጽ በእግዚአብሔር ላይ ባላቸው እምነት የተነሳ ሰማዕት ስለ ሆኑት ቅዱሳን የቀረበ ነው፡፡ ሆኖም ስለ ተጨቆኑና ስለ ተሰደዱ ሕዝቦች የእግዚአብሔርን ጣልቃ ገብነት ከሚማጸን የሰቆቃ ድምጽ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሉቃ. 18፡1-8፡፡ ሕዝቦቹ እግዚአብሔር እንዲደርስላቸው በተደጋጋሚ ያቀርቡ ለነበረው ልቅሶ እና ጸሎት አምላካዊ ምላሽ አስመልክቶ የሱስ ምን እያለ ነው? ይህ ሁኔታ እምነት አስፈላጊ ከመሆኑ ጋር እንዴት ይተሳሰራል?

ጳግሜ 4
Sep 09

የሆነ ዓይነት ተስፋ


ኃይማኖት ዛሬ በዚህ ምድር አማኞች የሚኖሩትን ህይወት ችላ ብለው ከህይወት በኋላ ወዳለ የተሻለ የሚመስል ህይወት የመውሰድ አዝማሚያ አለው የሚል ትችት በተደጋጋሚ ይሰነዘራል፡፡ የሰዎችን ትኩረት ወደ ሌላ ዓይነት ግዛት የሚወስደው የአማኙ የመናኝ ዓይነት የተቀደሰ ህይወት፤ ከምድራዊው ነገርም ሆነ ከማኅበረሰቡ ተጠቃሚ የሚያደርገውን ምላሽ በቅጡ እንዳይሰጥ መንስኤ ይሆናል--የሚል ነው ትችቱ፡፡ አልፎ አልፎ አማኞች ራሳቸውን ለእንዲህ ያለው ትችት ክፍት ሲያደርጉ ሌላ ጊዜ ደግሞ እያለሙ፣ እየሰበኩና እንዲህ ዓይነቱን አመለካከት እየተለማመዱ ኖረዋል፡፡

የሱስ ዳግም ተገልጦ ሁሉም ነገር ትክክለኛ ገጽታውን እስኪይዝ ደኻውና የተጨቆነው በዚህ ምድር የገጠመውን አሳዛኝ ዕጣ ፈንታ ተቀብሎ እንዲኖር የሚነግሩ በኃላፊነት የተቀመጡ አስደንጋጭ ምሳሌዎች አሉ፡፡ ዓለማችን መውደቋ፣ መፍረሷና አሳዛኝ ስፍራ መሆኗ እርግጥ ከመሆኑ አኳያ እግዚአብሔር ኢፍትሐዊነትን፣ ህመምንና ሐዘንን ወደ ፍጻሜ አምጥቶ የዛሬውን ምስቅልቅል በታላቅ ክብር በተሞላና ጻድቅ መንግሥት ተክቶ የጠፋውንና የተመሰቃቀለውን ወደ ቀድሞው ንጽህና እንዲመልሰው መናፈቅ በራሱ ስህተት የለውም፡፡ ለነገሩ ያ አለኝታ ባይኖረን ኖሮ እንደው ያለ ተስፋ በቀረን ነበር፡፡ የሱስ ስለ ምድር መጨረሻ የተናገረበትን ስብከት (ማቴ. 24 አና 25) የመጀመሪያ ክፍል አጋማሽ ያዋለው በዓለም ላይ ከሚከሰት መከራ ስለ ማምለጥ አስፈላጊነት በመዘርዘር ነው፡፡ እንደውም በቀጥታ ወደ ዋናው ሀሳብ በመግባት “‘ቀኖቹ ባያጥሩ ኖሮ ሥጋ ለባሽ ሁሉ ባልተረፈ ነበር’” (ማቴ. 24፡22) ይላል፡፡ ሆኖም ይህ ስለ አምላካዊው ተስፋ ምንነት የሚሰጠው ማብራሪያ የመግቢያ ክፍል ነው፡፡ የወደፊቱ የክርስቲያኖች ተስፋ “ማምለጥ” በሚለው ቃል ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያደርግ ወይም ተቀዳሚውን ስፍራ እንዲወስድ ማድረግ፤ የሱስ ያስተማራቸውን አንዳንድ ጥልቀት ያላቸውን ነጥቦች ማጉደል ይሆናል፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ ማቴ. ምዕ. 24 እና 25፡፡ ከየሱስ የተራራው ስብከት ንባብዎ በእጅጉ አስፈላጊ ያሏቸው ነጥቦች የትኞቹ ናቸው? ዳግም ምጽአቱን እየተጠባበቅን እንዴት መኖር እንዳለብን አስመልክቶ የሱስ የሰጣቸውን መመሪያዎች እንዴት ጠቅለል አድርገው ያቀርቧቸዋል?



ስለ ወደፊቱ የሚኖረን እምነት ለዛሬው አኗኗራችን ጠቃሚ አንደምታ አለው፡፡ እግዚአብሔር ለዓለማችን የወደፊት ሁናቴ ባለው አስተሳሰብ ላይ የሚኖር ጤነኛ መተማመን፤ ጥብቅ ለሆነው ቁርጠኝነት ለውጥ የሚያመጣ፣ ለከበረውና ጥልቅ ትርጉም ላለው ህይወት የብርሃን ብልጭታ የሚፈነጥቅና በሌሎች ላይ ልዩነት የሚፈጥር ሊሆን ይገባል፡፡

የየሱስ ዳግም ምጽአት ተስፋና ኪዳን በተለይ በችግር ውስጥ ያሉትን ከመርዳት አኳያ በዛሬው አኗኗራችን ላይ ተጽእኖ ማምጣት የሚችለው እንዴት ነው?

ጳግሜ 5
Sep 10

የኤፍራጥስ ወንዝ መድረቅ


ክርስቲያኖች በየሱስ ዳግም ምጽአት ላይ ያላቸው ተስፋ ብሩህ የሆነውን መጻኢ ነገር አሻግሮ በማየት ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ የቀደሙት ክርስቲያኖች የሱስ በአካል ወደ ሰማይ ሲያርግ መመልከታቸው ስለ ዳግም ምጽአቱ ተጨባጭ ተስፋ ሰጥቶአቸው ነበር፡፡ ደቀ መዛሙርት ምስክር የሆኑበትን--ሞትን አሸንፎ እስከ ተነሳ ድረስ ኃጢአትንና ውጤቱን አስወግዶ ዓላማውን እስከ መጨረሻው ሊያሳካና ምድርን አዲስ ሊያደርግ እነሆ በእርግጠኝነት ይመጣል (1ቆሮ. 15፡22-23)፡፡ ትንሣኤ ለሐዋርያው ጳውሎስ በቅርብ የሚገለጠው ተስፋ ቁልፍ ነገር ነበር፡፡ እርሱ የስብከቱን ሁሉ ተአማኒነት በዚህ ከሁሉ የላቀ የየሱስ ታሪክ ታምራት ላይ ለማዋል ዝግጁ ነበር፡ “ክርስቶስም ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ነው” (1ቆሮ. 15፡17)። የክርስቶስ ዳግም ምጽአት ተስፋ ለምናደርጋቸው ነገሮች ሁሉ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አሰብ ያድርጉ፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 1ቆሮ. 15፡12-19፡፡ የትንሣኤው እውነት ለዳግም ምጽአቱ ወሳኝ ስለ መሆኑ አማኝ ላልሆነ ሰው እንዴት ይገልጹታል?



የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት ለየሱስ ትንሣኤ ምስክር መሆን ህይወታቸው እንዲለወጥ አደረገ፡፡ ቀደም ብለን እንደ ተመለከትነው ደቀ መዛሙርቱ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዲያውጁ ተልከው (ማቴ. 10፡5-8) የነበረ ቢሆንም፤ ነገር ግን የየሱስ ሞት ወኔያቸውን ሰልቦ ተስፋቸውንም አጨልሞ ነበር፡፡ ከሞት በተነሳው የሱስ (ማቴ. 28፡18-20) እና በልዩ ሁኔታ በወረደው የመንፈስ ቅዱስ ኃይል (ሐዋ. 2፡1-4) እንዲያከናውኑ የተሰጣቸው ቀጣይ ተልዕኮ ዓለምን መለወጥ በሚያስችል ጎዳና ላይ አስቀምጦ የሱስ መስርቶት በነበረው መንግሥት ላይ አጸናቸው፡፡

ከሞት ኃይልና ፍርሃት ነጻ የሆኑት የቀደሙት አማኞች በየሱስ ስም በብርታት እየተመላለሱ ቃሉን ያካፍሉ ነበር (1ቆሮ. 15፡30-31)፡፡ ሞት የሚያስከትለው ክፉው-የሥቃይ፣ የፍትሕ መጓደል፣ የድኽነትና የተለያየ ዓይነት ጭቆና መንስዔም ነው። ሆኖም በየሱስ እና እርሱ በሞት ላይ ባለው አሸናፊነት የተነሳ ይህ ሁሉ አንድ ቀን ያከትማል፡፡ “የሚደመሰሰውም የመጨረሻው ጠላት ሞት ነው” (1ቆሮ. 15፡26)፡፡ “ዛሬ የትኛውንም ሰው ብናግዝና ብንረዳ ውሎ አድሮ አንድ ቀን ሞት አይቀርም፡፡ ሌሎች በየሱስ ሞት እና ትንሣኤ ውስጥ የሚገኘውን ተስፋ እንዲያውቁ መርዳት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ከዚህ ከባድ እውነት ምን እንማራለን?

ጳግሜ 6
Sep 11

የፍርድ ተስፋ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ መክ. 8፡14፡፡ በዚህ ስፍራ የተጻፈውን ጽኑ እና ብርቱ እውነታ በምን ዓይነት መንገድ ይመለከቱታል?



ሰብዓዊውን ሥቃይ፣ ጭቆና እና አሳዛኝ ክስተት በራሱ ተቋቁሞ መዝለቅ እጅግ አስቸጋሪ ቢሆንም፤ በማናለብኝ የሚፈጸም አካላዊ ጉዳት ወይም ስድብ ደግሞ ጉዳቱ ይበልጥ የከፋ ነው፡፡ በሰብዓዊው ወገን ላይ ሊደርስ የሚችል ቅጥ ያጣ፣ ትርጉም የለሽ ሐዘን ከቀደመው ቀንበር በከፋ ለመቋቋም ከባድ ነው፡፡ ተግባሩ በመዝገብ መስፈር ያልቻለ ወይም በመጨረሻ ፍትሐዊ ብይን የማያገኝ ዓለም ድምዳሜው ጨካኝና ትርጉም ዐልባ ነው፡፡ የሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን የዝግመተ ለውጥ አራማጅ ጸሐፊዎች እነርሱ ያመኑበት ሰብዓዊ ሁኔታ “ዘበት” እንደሆነ በማውሳት ቢያላዝኑ ብዙም አይደንቅም፡፡ ዓለማችን የፍትሕ ተስፋ ከሌላት፣ አንድ ቀን የፍርድ ጸሐይ የማይወጣላትና ነገሮች እንደተመሰቃቀሉ የሚቀሩ ከሆነ፤ በእርግጥም ትርጉም ዐልባ ዘበት ናት፡፡

በመክ. 8፡14 የቀረበው የልቅሶ ድምጽ የታሪኩ መጨረሻ አለመሆኑን ልብ ይሏል። ሰለሞን የተቃውሞ ሀሳብ ካነሳ በኋላ በመጨረሻ ድንገት ይመለሳል፡፡ በእርግጥ ሰለሞን ስለ ከንቱነት ከጠቃቀሳቸው የሰቆቃ ቃላት መሃል እግዚአብሔር ፍርዱን ስለሚሰጥ ማንኛውም ነገር ትርጉም የለሽ አይደለም፤ በመሆኑም አሁን ማንኛውም ነገርም ሆነ እያንዳንዱ ሰው ትርጉም አለው የሚል ዐውድ እናገኛለን፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ መክ. 12፡13-14፡፡ እያንዳንዱ የምናደርገው ነገር ምን ያህል አጽንኦት እንደሚሰጠው አስመልክቶ ይህ ምን ይነግረናል?



የፍርድ ተስፋ አንድ ሰው ስለ እግዚአብሔር ባህሪ፣ ስለ ህይወትና ስለምንኖርባት ዓለም ከሚኖረው እምነት ይመነጫል፡፡ እኛ እየኖርን ያለነው እግዚአብሔር በሚወዳትና በፈጠራት ምድር ውስጥ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ አጽንኦት ሰጥቶ ይነግረናል፡፡ ሆኖም ይህች ምድር በተሳሳተ አቅጣጫ መንጎዷን ተከትሎ እግዚአብሔር በልጁ በየሱስ ህይወትና ሞት እነሆ ዳግም ሊፈጥራት እየሠራ ይገኛል፡፡ አምላካዊው ፍርድ ምድራችንን ዳግም ወደ ቀናው ጎዳና የሚመልስበት ቁልፍ ክፍል ነው፡፡ ለተገፉ፣ የጭካኔ ተግባር ለተፈጸመባቸው፣ ለተጨቆኑና ለተበዘበዙ ሁሉ የፍርድ ተስፋ በእርግጥም መልካም የምሥራች ነው፡፡

አሁን አጥብቀን የምንናፍቀው ፍትሕ በመጨረሻ አንድ ቀን ልንገምት በማንችለው መንገድ መምጣቱ ለእርስዎ ምን ዓይነት ትርጉም አለው? ከዚህ የተስፋ ቃል--ተስፋ መጨበጥ የምንችለው እንዴት ነው?

መስከረም 1
Sep 12

ከዚህ በኋላ እንባ ወይም ህመም አይኖርም


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 21፡1-5፣ 22፡1-5፡፡ በጥቅሶቹ የተገለጠው ህይወት ምን ሊመስል እንደሚችል በዐይነ ህሊናዎ ለመመልከት ይሞክሩ፡፡ ህይወትን ከኃጢአት፣ ከሞት፣ ከህመምና ከዕንባ ውጪ ለማሰብ የሚከብደው ለምንድን ነው?



መጽሐፍ ቅዱስ ከኃጢአት በኋላ ስላለው ህይወታችን የሚሰጠው መግለጫ አስገራሚና በክብር የተሞላ ከመሆኑ አኳያ የሚጠብቀንን ነገር ፍንትው አድርጎ ማቅረቡ ብዙም የሚደንቅ አይደለም፡፡ ሌላው ቀርቶ በእነዚህ ጥቅሶች የቀረቡት መግለጫዎች ራሳቸው የሚዳስሱት በዚያ ያሉትን ሳይሆን የሌሉትን ነው፡፡ እኛ የምናውቀው ይህን ዓለም ብቻ እንደ መሆኑ፤ ህይወትን ከህመም፣ ከሥቃይ፣ ከሞትና ፍርሀት፣ ከኢፍትሐዊነትና ድኽነት ውጪ ለማሰብ ይከብደናል፡፡

ጥቅሱ የሚናገረው ከዚህ በኋላ እነዚህ ነገሮች በዚያ ስፍራ አለመኖራቸውን ብቻ ሳይሆን ግላዊ መነካትንም በማከል “እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል” ይላል (ራእ. 21፡4)፡፡ በዘመናት በሥቃይ ውስጥ ስላለፉት ምስኪኖች--የእግዚአብሔር ርኅራኄ በዚህ አንድ ዐርፍተ ነገር ከፍ ወዳለ ደረጃ ተሸጋግሮ እንመለከታለን፡፡ እርሱ ለሥቃያቸው ፍጻሜ ማምጣት ብቻ ሳይሆን ዕንባቸውንም ያብሳል፡፡

ዓለም በኃጢአት ህይወት፣ በኢፍትሐዊነትና አሳዛኝ ክስተቶች የተጎሳቆለና የተደናገጠ ቢሆንም፤ የኃጢአት ሰለባዎች ለሆንነው ለእኛ ለሁላችን የፈውስ ሂደት ፍንጮችን በተለያዩ መንገዶች ከራእይ መጽሐፍ መመልከት እንችላለን፡፡ በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ስለሚገኘው የህይወት ዛፍ ዮሐንስ ሲያብራራ “የዛፉም ቅጠሎች ሕዝቦች የሚፈወሱባቸው ነበሩ” ይላል (ራእ. 22፡2)፡፡ በድጋሚ እግዚአብሔር ሰውን እንደሚያስተውል፣ ለሰው እንደሚራራ፣ ሰው መሆን ያለውን ስሜት፣ ትርጉሙን፣ ተሞክሮውን፣ ምስክርነቱን ከዚያም አልፎ የዓለም ክፋት ተጋሪነቱን እንደሚረዳ ያሳየናል፡፡ ምድራችንን ዳግም የመፍጠር እቅዱ እኛን ወደ ቀድሞው ንጽህና መመለስና መፈወስን ያካትታል፡፡

ምንም እንኳ የእኛን ችሮታ ለሚሹ በዙሪያችን ያሉ ወገኖች የምናበረክተው አገልግሎት በማቅማማት የታጀበና እጅግ አነስተኛ ሊሆን ቢችልም፤ ነገር ግን እስከዚያው የድርሻችንን እያበረከትን በክርስቶስ መሆን የምንችለውን ሁሉ ለመሆን የተቻለንን ጥረት ለማድረግ ምኞታችን ነው፡፡ አገልግሎታችን የቱንም ዓይነት ሊሆን ቢችል ማለትም--በበጎ ቃላት የመንፈስ ልዕልና መፍጠር፣ ለተራበው ማብላት፣ የህክምና እርዳታ መስጠት፣ የታረዘውን ማልበስ ወይም የምክር አገልግሎት መስጠት ሊሆን ቢችል--ሁሉም የሱስ በዚህ ምድር በነበረበት ወቅት ባሳየን ዓይነት ራስን ዝቅ በማድረግ፣ ራስን በመካድና ራስን ለሌላው መሥዋዕት ባደረገ ፍቅር ሊተገበር ይገባል፡፡

ምንም እንኳ የተቻለንን ጥረት ከማድረግ ባንቦዝንም ዓለም ከመቼውም ይልቅ እየከፋችና ነገሮች እየተባባሱ መሄዳቸው እርግጥ ነው፡፡ ይህ እንደሚሆን ያውቅ የነበረውን የሱስ እውነታው ከማገልገል እንዳልገታው ሁሉ፤ በተመሳሳይ እኛንም ሊገታ አይገባም፡፡

መስከረም 2
Sep 13


ተጨማሪ ሀሳብ


Read Ellen G. White, “Called to Reach a Higher Standard,” pp. 309–322, in The Acts of the Apostles; “Desolation of the Earth,” pp. 653–661, in The Great Controversy. “የእግዚአብሔር ድምጽ የሕዝቦቹን ምርኮ ሲመልስ፤ በታላቁ የህይወት ተጋድሎ ሁሉንም አምላካዊ ነገር ያጡ በጣም አስፈሪና አስደንጋጭ በሆነ ሁኔታ ይነቃሉ፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝቦች የሚፈተኑበት ጊዜ በቀጠለ ቁጥር ዐይኖቻቸው በሰይጣን ማታለያ ተሸብበውና የኃጢአት መንገዳቸውንም አጽንተው ይዘው ነበር፡፡ ሀብታሞች የእግዚአብሔርን ሕግ ጥሰው በሰበሰቡት ሀብት በድኾች ላይ ታበዩ፡፡

የተራበውን ለማብላት፣ የታረዘውን ለማልበስ፣ በቅንነት ለማስተናገድና ምኅረትን ለመውደድ ችላ አሉ. . . ለምድራዊው ተድላና ፍስሐ ነፍሳቸውን ከመሸጥ ውጪ በእግዚአብሔር ፊት ባለጸጋ ለመሆን አልተመኙም፡፡ በውጤቱ ህይወታቸው በውድቀት፣ ደስታቸው በከባድ ሐዘን፣ ሐብታቸውም በንቅዘት ተበላ፡፡”—Ellen G. White, The Great Controversy, p. 654. “ታላቁ ተጋድሎ ፍጻሜ አግኝቶአል፡፡ የኃጢአትና ኃጢአተኞች ጉዳይ አክትሟል። መላው ጽንፈ ዓለም ወደ ቀደመ ንጽህናው ተመልሶአል፡፡ በመላው ፍጥረት ውስጥ አንድ ዓይነት ስምምነትና ውህደት ሰፍኖአል፡፡ ወሰን በሌለው ግዛት ሁሉን ከፈጠረው ከእርሱ--ህይወት፣ የብርሃን ጸዳልና የደስታ ፍስሐ ይፈሳል፡፡ ኢምንት ከሆነው አቶም እስከ ግዙፉ ዓለም፣ ህይወት ያለው ወይም ግዑዙ--አንዳችም ጥላ ባላጠላበት ውበትና ፍጹም ደስታ እግዚአብሔር ፍቅር መሆኑን ያውጃሉ፡፡”—Ellen G. White, The Great Controversy, p. 678.


የመወያያ ጥያቄዎች




1.በዚህ ሣምንት ባጠናነው መሰረት ምድራዊ ማንነትዎ ያንኛውን ሕይወት እንዴት እንደሚያሳይ ያብራሩ፡፡ እግዚአብሔር ይህን ምድር አጥፍቶ ሁሉም ነገር እንደገና ከአዲስ ስለሚጀምር ስለዚህ ምድርም ሆነ ህይወት መጨነቅ የለብንም ከሚለው እምነት ጋር መልስዎን ያመሳክሩ፡፡ ይህን የአዲስ ፍጥረት ተስፋ እውነት በችግር ያሉትን ችላ ሳንል ጥቅም ላይ ለማዋል ጥንቃቄ ማድረግ ያለብን እንዴት ነው? ይህን እውነት ሌሎችን ለመበዝበዝ ጥቅም ላይ ላለማዋላችን እርግጠኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

2.የየሱስ ዳግም ምጽአት በተቃረበ ቁጥር የክፉው አሠራር፣ ችግርና ሥቃይ እየጨመረ ይሄዳል ብላ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን--ከመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት አኳያ የዚህን እውነት ገቢራዊነት ትጠባበቃለች፡፡ እነዚህ ነገሮች እያየሉ በሄዱ ቁጥር በተደጋጋሚ ከምናደርጋቸው ነገሮች አንዱ ማቴ. 24ን ማንበብ ነው፡፡ አሳዛኞቹን ክስተቶች ከማቴ. 25 አኳያ እንዴት እናስተውላቸዋለን? ማጠቃለያ፡ ክፉው መጨረሻ ለሌለው ዘመን ተንሰራፍቶ እንዲኖር አምላካችን አይፈቅድም፡፡ የሱስ ለክፉው ፍጻሜ፣ ለኢፍትሐዊነት ፈውስ በማምጣት የቀደመ ንጽህናዋን የያዘች አዲስ ምድር ዳግመኛ ሊፈጥር ዳግም ይገለጣል። ይህ ታላቁ የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ነው። በየሱስ ዳግም ምጽአት ላይ የተገነባው ይህ ተስፋ ዛሬ እኛን በመለወጥ ዳግም ምጽአቱን እየተጠባበቅን ለእግዚአብሔርና ለሌሎች ለምንሰጠው አገልግሎት ወኔ ይሆነናል፡፡