ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ሮሜ 8:20–23፣ ዮሐ. 3:16-17፣ ማቴ. 9:36፣ ኤፌ. 2:8–10፣ 1ዮሐ. 3:16-17፣ ራእ. 14:6, 7፡፡
መታሰቢያ ጥቅስ:--“በእምነት፣ በጸጋ ድናችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ማንም እንዳይመካ በሥራ አይደለም፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀልንን መልካም ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ የተፈጠርን የእግዚአብሔር እጅ ሥራዎች ነን፡፡” (ኤፌ. 2፡8-10)፡፡
ስ
ለ እግዚአብሔር ትእዛዞች፣ መመሪያዎች ወይም በአጠቃላይ እርሱ ከእኛ
ስለሚፈልጋቸው ነገሮች ተነጋግረን ብዙም ሳንቆይ ሥራችን ለደኅንነታችን
አስተዋጾ እንደሚኖረው ወይም በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ እንደሚያስገኝልን በማሰብ
ራሳችንን ለፈተና እያጋለጥን እንሰጣለን፡፡ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ
እንደሚነግረን እኛ ኃጢአተኞች ስንሆን የዳንነው በአምላካዊው ጸጋ ይኸውም
በመስቀል ላይ ቤዛ ሆኖ በሞተልን በየሱስ ነው፡፡ ለመሆኑ በዚህ ላይ ምን መጨመር
እንችላለን? “አንድ ሰው በሰብዓዊው ፍጡር ውስጥ ሊኖር የሚችለውን ማንኛውንም
መልካም፣ ቅዱስ፣ የከበረና ተወዳጅ የተባለ ነገር ሁሉ በአንድነት ሰብስቦ የሰውን
ነፍስ ሊያድን ይችል እንደሆን ጉዳዩን በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ቢያቀርብ
ሀሳቡ እንደ ክህደት ተቆጥሮ ተቃውሞ ይገጥመዋል፡፡”—Faith and Works, p. 24.
በመሆኑም በችግርና በእጦት ለሚገኙ ወንድም እህቶቻችን የምናደርገው የምኅረትና
የርኅራኄ ተግባር በራሱ ሕግን የመጠበቅ አካል ተደርጎ መስተዋል የለበትም፡፡
በተቃራኒው በክርስትና ህይወታችን እየጎለመስን፣ የደኅንነትን ምስጢር እያስተዋልንና
እያደነቅን በመጣን ቁጥር፤ በእግዚአብሔር ፍቅር እና እርሱ ለድኾችና ለተጨቆኑ
ባለው መቆርቆር መሃል ያለው ትስስር--የፍቅሩ ተቀባዮች ወደ ሆንነው ወደ እኛ
ይተላለፋል፡፡ በነጻ እንደ ተቀበልን ሁሉ በነጻ እንሰጣለን፡፡ እግዚአብሔር ምን ያህል
እንደ ወደደን መመልከት ስንችል እርሱ ሌሎችንም በምን ያህል ፍቅር እንደ ወደደና
እኛም እነርሱን እንድንወድ ያቀረበልንን ጥሪ ለመረዳት ብዙም አንቸገርም፡፡
“እግዚአብሔር… ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና” (ዮሐ. 3፡16)፡፡ ጥቅሱ የተወሰደው
kosmos ከተሰኘ የግሪክ ቃል ሲሆን “የተቀናበረውን የፍጥረት ሥራ፣ አንድነት
ያለውን አካል” የሚል ፍቺ አለው፡፡”—The SDA Bible Commentary, vol. 5, p.
929. ጥቅሱ ስለ ሰብዓዊው ፍጡር ደኅንነት የሚናገር ሲሆን፤ አምላካዊው የደኅንነት
ዕቅድ አንደምታ ግን ለመላው የፍጥረት ሥራ ጭምር ነው፡፡
ጥቅሱን ያንብቡ፡ ሮሜ 8፡20-23፡፡ በደኅንነት እቅድ እጅግ ሰፊ ስለሆኑት ጉዳዮች
ይህ ምን ያስተምረናል?
በእርግጥ በአንድ በኩል ደኅንነት እያንዳንዳችን ከጌታ ጋር በግል ባለን ግንኙነት
ላይ አጽንኦት ቢሰጥም ነገር ግን ጉዳዩ ከዚያም የላቀ አንደምታ አለው፡፡ መጽደቅ
ኃጢአታችን ተረሳልን እንደ ማለት ብቻ ሳይሆን ይልቁንም ጌታ በየሱስ እና በመንፈስ
ቅዱስ ኃይል አማካይነት አምላካዊውን ቤተሰብ የመፍጠሩ፣ ይቅር የመባላችንና
የመዳናችን ማረጋገጫ ማግኘታችን እንዲሁም ከሌሎች ነገሮች ጎን ለጎን በመልካም
ተግባሮቻችን ጭምር ለዓለም ምስክር መሆናችን ነው፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዮሐ. 3፡16-17፡፡ ቁ. 17--በቁጥር 16 የቀረበውን ሀሳብ በስፋት
እንድናስተውል አስተዋጾ የሚያደርገው እንዴት ነው?
እኛ ሌሎችን ከምንወደው በላቀ እግዚአብሔር ሰዎችን የመውደዱን እውነታ
መቀበል እንችላለን፡፡ እኛ የሚወዱንን እንወዳለን፤ በዚህም በእጅጉ ደስተኞች
ነን። በተጨማሪ እርሱ አምላካዊውን ፍቅር ለማካፈል የምንተጋላቸውን ወገኖችም
መውደዱና እኛም ለዚህ እውነት እውቅና መስጠታችን ወደ እነርሱ ለመድረስ
መበረታቻ ምክንያታችን ነው፡፡ ሆኖም ለእኛ ብዙም የማይመቹንን--እንደውም
የምንፈራቸውን ሳይቀር እርሱ ይወዳል፡፡ እግዚአብሔር በየትኛውም ስፍራ
የሚገኙትንም ሆነ በተለይ ልንወዳቸው የምንቸገርባቸውን ሳይቀር ይወዳል፡፡
ፍጥረት ይህ ተገልጦ ማየት የምንችልበት አንዱ መንገድ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ
ስለ እግዚአብሔር መልካምነት ያለማቋረጥ በዙሪያችን ያለውን ዓለም በማስረጃነት
ያሳየናል፡ “ ‘እርሱ ፀሐዩን ለክፉዎችና ለደጎች ያወጣል፤ ዝናቡንም ለኃጢአተኞችና
ለጻድቃን ያዘንባል’ ” (ማቴ. 5፡45)፡፡ ህይወት ራሷ ከእግዚአብሔር የተቸረች ስጦታ
ናት፡፡ አንድ ሰው ለእግዚአብሔር የሚሰጠው ምላሽ ወይም የሚኖረው አመለካከት
የቱንም ዓይነት ሊሆን ቢችልም፤ እያንዳንዱ ሰው የዚያ ስጦታ ተቀባይ ነው፡፡
ሌሎችም በእግዚአብሔር የተፈጠሩና የተወደዱ መሆናቸውን በጥልቅ
ማስተዋላችን በእነርሱ ላይ ያለንን አመለካከት የሚለውጠው እንዴት ነው?
ውሁድ ባህሪ ያላቸው የደህንነትና እልህ አስጨራሾቹ የታላቁ ተጋድሎ ታሪኮች
የዓለማችንንም ሆነ የራሳችንን መሰረታዊ እውነታ በጥልቀት አስተውለንና አምነን
እንድንቀበል ጥሪ የሚያደርጉልን ሲሆን፤ ይኸውም እኛም ሆንን ዓለማችን የወደቅን፣
የተበላሸንና ኃጢአተኞች የመሆናችንን ሐቅ ነው፡፡ ዓለማችን የተፈጠረችው
በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ እንድትወድቅ አልነበረም፡፡ እኛም የፈጠረንን አምላካዊ
አምሳል ብንይዝም የብልሹው ዓለም አካል ነን፡፡ በእኛ ውስጥ ያለው ኃጢአት
በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ ህመም፣ ጭቆና እና ብዝበዛ ካስከተለው ክፋት ጋር ተመሳሳይ
ተፈጥሮ ይጋራል፡፡
ስለዚህ ከምንገኝበት ነባራዊ ሁኔታ አኳያ በዓለምም ሆነ ዙሪያችንን ባሉ ሰብዓዊ
ወገኖች ላይ ጉዳት፣ ጉስቁልና፣ እጦትና ሐዘን መመልከት የሚጠበቅ ይሆናል፡፡
በዚህ ህይወት ላይ እየደረሰ ያለው ህመም እንዳይሰማን ሮቦቶች መሆን አለብን፡፡
በመዝሙረ ዳዊት የቀረቡ የልቅሶ ድምጾች፣ የኤርምያስ ሰቆቃና የሌሎችም ብሎም
የየሱስ እንባና ርኅራኄ ለዓለምና ለክፋቷ የእንዲህ ዓይነቱን ምላሽ ተገቢነት ያሳያሉ-በተለይ በክፉው ተደጋጋሚ የጉዳት ገፈት ቀማሾች!
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማቴ. 9:36፣ 14:14፣ ሉቃ. 19:41-42፣ ዮሐ. 11:35፡፡ በእነዚህ
በቀረቡት በእያንዳንዱ ጥቅሶች የየሱስ ልብ አጥብቆ የተነካባቸው ትእይንቶች
የትኞቹ ነበሩ? በዙሪያችን ላሉ ህመምና ሥቃዮች የሚራራ ልብ ሊኖረን የሚችለው
እንዴት ነው?
እንዲሁም ኃጢአትና የክፉው ሀሳብ ከእኛ ተነጥሎ በባይተዋርነት የተቀመጠ ነገር
ወይም የሌላው ውድቀት ውጤት አለመሆኑን አንዘንጋ፡ “ኃጢአት የለብንም ብንል
ራሳችንን እናስታለን፣ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም” (1ዮሐ. 1፡8)፡፡ እንደ መጽሐፍ
ቅዱስ ነቢያት መረዳት ከሆነ ኃጢአት አሳዛኝ ክስተት የሆነው ገና መጀመሪያ የሆነ
ሰው “ሕጎቹን” በመጣሱ ሳይሆን ነገር ግን ኃጢአት በእግዚአብሔርና በፍጡሮቹ
መካከል የነበረውን ግንኙነት በመበጠሱ እና የእኛ ኃጢአት ሌሎችን በመጉዳቱ
ነው። ምናልባት መጠኑ ሊያንስ ወይም ሊበዛ ቢችልም ክፉው ግን ያው ክፉ ነው፡፡
የዓለም የክፋት ተግባራት የሆኑት የኢፍትሐዊነት፣ የድኽነትና የጭቆና ሥረ
መሰረቶች--ራስ ወዳድነት፣ ስስት፣ ርኩሰት፣ ጭፍን ጥላቻ እንዲሁም ስለ ሌላው
ግድ አለማለት ናቸው፡፡ ይህን የክፉው ተግባር ለመቋቋም ተቀዳሚው ተግባር
ኃጢአተኝነታችንን መናዘዝ እና የእግዚአብሔር ፍቅር ባለ መብት የሆነበትን
ስፍራ ይኸውም ልባችንን እንዲወስድ መፍቀድ ይሆናል፡ “ኃጢአታችንን ብንናዘዝ
ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን፣ ከአመፃ ሁሉ ሊያነጻን እርሱ ታማኝና ጻድቅ ነው” (1ዮሐ.
1፡9)፡፡
እስቲ ወደ ራስዎ ይመልከቱ፡፡ እርስዎ በተለይ ሊቋቋሙት የሚገባ የትልቁ
ችግር አካል የሆነው የክፉ ተግባር የትኛው ነው? ለዚህ ብቸኛውን መልስ
ከወዴት ያገኛሉ? ሊሄዱ የሚገባውስ ብቸኛው ስፍራ?
ጥቅሶቹን ያንብቡና ሀሳቡን በራስዎ ቃላት ለመጻፍ ይሞክሩ፡ ኤፌ. 2፡8-10፡፡ በጸጋ እና በመልካም ሥራ መካከል ስላለው ግንኙነት ምን ይነግሩናል?
እኛ ሌሎች ነገሮችን ጨምሮ እግዚአብሔርን እንድናመልክ እና ሰብዓዊውን ወገን
እንድናገለግል መፈጠራችንን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ ይህ ማንነት ኃጢአት
በሌለበት ሁኔታ ምን ሊመስል እንደሚችል በዐይነ ህሊናችን ብቻ ለማየት መሞከር
እንችላለን፡፡
እኛ አሁን የምናውቀው በኃጢአት ምክንያት የፈረሰውንና የወደቀውን ዓለም
ብቻ ነው፡፡ ስለ ዓለም ኃጢአት ሲባል በየሱስ መሥዋዕትነት የተገለጠውና በተግባር
የታየው የእግዚአብሔር ጸጋ የይቅርታና የፈውስ ጎዳና ከፈተ፡፡ በእንዲህ ያለው
የፈረሰ ህልውና ውስጥ ሆነንም እንኳ ህይወታችን በአመዛኙ አምላካዊውን አሠራር
ሲከተል፤ በሌሎች ህይወት ላይ የደረሰውን ውድመትና ጉዳት ለመፈወስና ወደ ቀድሞ
ሁኔታው ለመመለስ ከእርሱ ጋር አንድነት እንድንፈጥር ይጠቀምብናል (ኤፌ. 2፡
10)፡፡ “በነፃ የተቀበሉ በነፃ ሊሰጡ የተገባ ነው፡፡ እርዳታ የሚሹ ጥሪዎች ከእያንዳንዱ
አቅጣጫ እየመጡ ነው፡፡ ሰዎች ሰብዓዊ ወገኖቻቸውን በደስታ ያገለግሉ ዘንድ እነሆ
እግዚአብሔር ጥሪ ያቀርባል፡፡”—Ellen G. White, The Ministry of Healing,
p. 103.
ለመጽደቅ ወይም ከእግዚአብሔር ጋር ለመቆም ብለን ደኻውን የመጎብኘት፣
የተጨቆኑትን ቀና የማድረግና የተራበውን የማብላት ሥራ አንሠራም፡፡ ይልቁንም
በክርስቶስ ላይ ባለን እምነት የተነሳ ሁሌም ከእግዚአብሔር ጋር መቆምን እንሻለን፡፡
ምንም እንኳ ራሳችንን እንደ ኃጢአተኛና የኃጢአት ሰለባ ብንቆጥርም፤ በእግዚአብሔር
የተወደድንና የተዋጀን ነን፡፡ በእርግጥ ዛሬም ከራስ ወዳድነትና ከስስት ጋር ግብግብ
ላይ ብንሆንም፤ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ የሰጠው ትሑቱ አምላካዊ ጸጋ ማንነታችንን
የሚለውጥ አዲስ ህይወትና የተትረፈረፈ ፍቅር ይሰጠናል፡፡
ወደ መስቀሉ ቀና ብለን ስለ እኛ የተደረገውን ታላቅና ፍጹም መሥዋዕትነት
ስንመለከት፤ በክርስቶስ በተደረገልን ነገር ላይ አንዳችም ነቁጥ ማከል እንደማንችል
እንገነዘባለን፡፡ በእርግጥ በክርስቶስ ለተበረከተልን ነገር ምንም ዓይነት አጸፋዊ ምላሽ
መስጠት የለብንም ማለት አይደለም፡፡ ምላሽ መስጠታችንማ የግድ ነው፡፡ ለእኛ
ያሳየንን ያንን አቻ የማይገኝለት ፍቅር ለሌሎች ከማሳየት ውጪ ምን የተሻለ ምላሽ
የምንሰጥበት መንገድ ይኖራል?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 1ዮሐ. 3፡16-17፡፡ ለመስቀሉ ልንሰጥ የሚገባውን
ምለሽ አስመልክቶ ጥቅሶቹ በብርታት የያዙት ሀሳብ ምን ይመስላል?
የሱስ በአገልግሎቱም ሆነ በአስተምህሮው ሁሉንም ሰብዓዊ ማንነት ላካተተው
ሥር ነቀል አምላካዊ ጥሪ አጽንኦት ሰጥቶ ነበር፡፡ አጉል ስም የነበራት ሴት ብትሆን
ወይም ቀረጥ ሰብሳቢ፣ በለምጽ የተመቱ ወይም ሳምራውያን፣ የሮም መቶ አለቆች
ወይም የኃይማኖት መሪዎች ወይም ደግሞ ህጻናት--የእርሱን ትኩረት በቅንነት እስከ
ሻቱ ድረስ ከልብ የመነጨውን ጥንቃቄና በጎ አቀባበል አድርጎላቸዋል፡፡ የጥንቷ ቤተ
ክርስቲያን በብርቱ የለውጥ ጎዳና ላይ በነበረችባቸው በእነዚያ ቀናት ይህ ስር ነቀል
ለውጥ የአምላካዊው የደኅንነት ስጦታ አካል ሆኖ ተካትቶ ነበር፡፡
የቀደሙት አማኞች ቀስ በቀስ የወንጌልን ሁሉን አካታችነት እየተገነዘቡ
በመጡ ቁጥር ሌሎች መልካሙን ሥራ ብቻ እንደ “ጥሩ” ነገር አክለው እንዲይዙ
አላበረታቱም፡፡ ሐዋርያት በየሱስ ህይወት፣ አገልግሎትና ሞት በነበራቸው ተሞክሮ
ይህ ወንጌልን የማስተዋላቸው--የልብ ትርታ ለመሆን በቃ፡፡ በጊዜው ይነሱ ከነበሩ
አወዛጋቢ ነጥቦችና ጥያቄዎች ጋር ያደርጓቸው በነበሩ ትግሎች መጀመሪያ እንደ
ጳውሎስና ጴጥሮስ ዓይነቶቹ መሪዎች--በግል (ሐዋ. 10፡9-20)፤ በመቀጠል እንደ
ቤተ ክርስቲያን አካል በየሩሳሌም ጉባዔ (ሐዋ. 15)--ይህ መልካም የምሥራች ይዞ
የመጣውን የእግዚአብሔርን ፍቅርና ሁሉን አካታች አስገራሚ ለውጥ መገንዘብ
ጀመሩ፡፡ እንዲሁም እርሱን ለመከተል የሚሹ እንዴት በህይወታቸው ሊተገብሩትና
ሊኖሩት እንደሚገባም ተረዱ፡፡
የሚከተሉት ጥቅሶች ሰብዓዊ ማንታችን ስለሚጋራቸው ነገሮች ምን ያስተምሩናል?
እያንዳንዱ ጽንሰ ሀሳብ በሌሎች ላይ በሚኖረን አመለካከት ዙሪያ ተጽእኖ ማሳደር
የሚችለውስ እንዴት ነው?
ሚልክ. 2:10
ሐዋ. 17:26
ሮሜ 3:23
ገላ. 3:28
በገላ. 3፡28 የቀረበው ነጥብ የሱስ ስለ መልካሙ ሳምራዊ የተናገረው ታሪክ ሥነ
መለኮታዊ ማጠቃለያ ሀሳብ ነው፡፡ ማንን የማገልገል ሞራላዊ ግዴታ ነው ያለብን
እያልን ሙግት ከማንሳት ይልቅ ወጥተን ማገልገልና ምናልባትም ያገለግሉናል ብለን
የማንጠብቃቸው ሊያገለግሉን እንደሚችሉም እንጠብቅ፡፡ የዓለማቀፉ ሰብዓዊ
ቤተሰብ የጋራ ባህሪ--በወንጌል፣ ወደ አንድነት በሚጠራን በአዳኙ አምላካዊ ፍቅርና
በእርሱ አማካይነት በአንድ በተሳሰሩ ተራ ሰዎች ከፍ ባለ ደረጃ እውን ሆኖ መታየት
ችሎአል፡ “አይሁድ ወይም የግሪክ ሰዎች ብንሆን፣ ባሪያ ወይም ነፃ ሰዎች ብንሆን፣
እኛ ሁላችን አንድ አካል እንድንሆን በአንድ መንፈስ ተጠምቀናልና” (1ቆሮ. 12፡13)፡፡
ወንጌል “ለሕዝብ፣ ለነገድ፣ ለቋንቋና ለወገን” (ራእ. 14፡6) እንዲሰበክ ሥር ነቀል ለውጥ ያመጣው ግብዣና ተማጽኖ የመላው ክርስትና ታሪክ አካል ሆኖ ኖሮአል፡፡ የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ ስለ የሱስ የቀረቡትን መልካም የምሥራቾች ከመጨረሻው ዘመን ትዕይንት ጋር አጣምሮ በአዲስ ዓይነት እወጃ ይገልጻቸዋል፡፡ ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 14፡6-7፡፡ በቁ. 7 በግልጽ የቀረበው የመልአኩ መልእክት ታክሎበት--በተለይ በዮሐ. 3፡16 ከቀረበው መልእክት አኳያ የተለመደው የወንጌል አረዳድ ምን ይመስላል?
እግዚአብሔር ስለ ክፉው፣ ስለ ድኽነትና ጭቆና አብዝቶ ግድ እንደሚለው
እስካሁን በመላው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ግንዛቤ ያገኘንባቸውን ሦስት ዋና ዋና
ነጥቦች ራእ. 14፡7 በአንድነት ያቀርብልናል፡፡
ፍርድ፡ በዘመናት በጭቆና ገፈት ውስጥ ያለፉ ሰብዓዊ ወገኖች ትክክለኛውን ፍርድ
እንዲያገኙና ፍትሕ እንዲሰፍን ተደጋጋሚ ተማጽኖ ሲቀርብ ኖሮአል፡፡ እንደ እድል
ሆኖ እግዚአብሔር በሥቃይ ውስጥ ያሉትን የልቅሶ ድምጾች የሚሰማ አምላክ አድርጎ
መጽሐፍ ቅዱስ ይስልልናል፡፡ በመዝሙር መጽሐፍ በተደጋጋሚ እንደተገለጠው
ለምሳሌ በደል የደረሰባቸው ፍትሕን እንደ መልካም የምሥራች ይመለከቱታል፡፡
አምልኮ፡ የዕብራውያን ነቢያት የአምልኮን ርዕሰ ጉዳዮች ከመልካም ሥራ
ጋር እያስተሳሰሩ በተደጋጋሚ በጽሑፎቻቸው አቅርበዋል--በተለይ ራሳቸውን
የእግዚአብሔር ሕዝቦች ብለው የሚጠሩ በአምልኮአቸው ይፈጽሟቸው የነበሩትንና
በዚያው የጸኑባቸውን አጉል ድርጊቶች እያወዳደሩ አቅርበዋል፡፡ ለምሳሌ በኢሳ. 58
እግዚአብሔር አብልጦ የሚሻው አምልኮ ለድኾችና ለችግረኞች በጎነት ማሳየትና
ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ መሆኑ በግልጽ ቀርቦአል (ኢሳ. 58፡6-7)፡፡
ፍጥረት፡ ቀደም ብለን እንደ ተመለከትነው ከእግዚአብሔር የፍትሕ ጥሪ መሰረታዊ
ባህሪያት አንዱ የሰው ልጅ በአንድ የሚጋራው ሰብዓዊ ቤተሰብነት ነው፡፡ እኛ
ሁላችን በእርሱ አምሳል የተፈጠርን፣ የተወደድንና በፊቱ የከበረ ዋጋ ያለን እንደ
መሆናችን ማንም በኢፍትሐዊው ስግብግብነት ሌላውን ሊበዘበዝ ወይም ሊጨቁን
አይገባም፡፡ ይህ ሰፊና እጅግ ብዙ ዐውዶችን ያካተተ የፍጻሜው ጊዜ የወንጌል እወጃ
የወደቀው ሰብዓዊ ዘር መዳን፣ መቤዠትና ወደ ቀድሞ ንጽህና መመለስ እንዲያገኝ
የቀረበለት አምላካዊ ጥሪ ነው፡፡ የእውነተኛና ሐሰተኛ አምልኮ ጉዳዮች ገንነው
በሚወጡባቸውና የክፉው ተግባር አስጨናቂ በሚሆንበት ስደት መሃል (ራእ. 14፡
8-12) እግዚአብሔር ለእውነት፣ ለአምላካዊው ትእዛዛትና ለየሱስ እምነት የሚቆሙ
ሕዝቦች ይኖሩታል፡፡
በችግር ያሉ ሰብዓዊ ወገኖችን እያገለገልን የሦስቱን መላእክት መልእክት
ተስፋዎችና ማስጠንቀቂያዎች ማካፈል የምንችልበትን መንገድ ማግኘት
የምንችለው እንዴት ነው?
Read Ellen G. White, “ ‘God With Us,’ ” pp. 19–26,
The Desire of Ages; “Saved to Serve,” pp. 95–107, in The Ministry of
Healing.
“እግዚአብሔር ምድር የእርሱ የወይን ቦታ መሆኗን ይናገራል፡፡ ምንም እንኳ ያላግባብ
ዙፋኑን በያዘው እጅ ብትወድቅም እርሷ ግን የእግዚአብሔር ናት፡፡ በመፍጠርም
ሆነ በመዋጀት እነሆ የእርሱ ናት፡፡ ክርስቶስ ስለ ዓለም ራሱን መሥዋዕት አድርጎ
ሰጥቶአል--‘እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና’
(ዮሐ. 3፡16)፡፡ በዚያ በአንዱ ስጦታ ሁሉም ሰው ተካፋይ ሆነ፡፡ መላው ዓለም
በየዕለቱ ከላይ ከአርያም የሚላከውን በረከት ይቀበላል፡፡ እያንዳንዱን የዝናብ
ጠብታም ሆነ የብርሃን ጸዳል ለእኛ ለምስጋና ቢሶቹ ሰብዓዊ ዝርያዎች ይሰዳል፡፡
እያንዳንዱ ለምለም ቅጠል፣ አበባና ፍራፍሬ የእግዚአብሔርን ረጅም ትዕግሥትና
ታላቅ ፍቅር ይመሰክራል፡፡”—Ellen G. White, Christ’s Object Lessons, pp.
301, 302.
“በክርስቶስ አይሁድ ወይም ግሪክ ወይም ደግሞ ባሪያና ነጻ ሰው የሚባል የለም፡፡
ሁሉም በከበረ ደሙ ወደ እርሱ መቅረብ ስለቻሉ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ናቸው
(ገላ. 3፡28፣ ኤፌ. 2፡13)፡፡
“በሰዎች መካከል የቱንም ዓይነት የኃይማኖት ልዩነት ቢኖርም የሰብዓዊው ወገን
የድረሱልኝ ድምጽ መሰማቱና ምላሽ ማግኘቱ የግድ ነው. . .
“የእኛ ርኅሩኅ ቃላትና እርዳታ የሚያሻቸው አያሌ ድኾችና ፈተናቸው የበዛ ነፍሳት
በዙሪያችን አሉ፡፡ ስሜታቸውን ልንጋራና የእርዳታ እጆቻችንን ልንዘረጋላቸው
የሚገቡ ባላቸውን በሞት የተነጠቁ ወይም ያለ ባል አለኝታ አሰቃቂ ኑሮ የሚገፉ
ባልቴቶች አሉ፡፡ ክርስቶስ ወላጆቻቸውን በሞት ያጡ ህጻናትን እንደ እግዚአብሔር
አደራ ተቀብለው ያሳድጉ ዘንድ ተከታዮቹን አዞአል፡፡ ሆኖም ይህ ሁኔታ አዘውትሮ
ችላ ሲባል ይታያል፡፡ ምናልባት እነዚህ ህጻናት ባብዛኛው የተጎሳቆሉ፣ የታረዙና
ብዙዎች የሚጠየፏቸው ዓይነት ሊሆኑ ቢችሉም፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ንብረቶች
ናቸው፡፡ በዋጋ የተገዙና በእርሱ ዐይን የከበሩ ናቸው፡፡ የታላቁ አምላካዊ ቤተሰብ
አባላት እንደ መሆናቸው መጋቢ ክርስቲያኖች ኃላፊነት አለባቸው፡፡”—Ellen G.
White, Christ’s Object Lessons, pp. 386, 387.
1.መልካም ሥራ ለመሥራትና ሌሎችን ለመርዳት ካለን መሻት አኳያ-ሥራችን የተሻልን ሰዎችና በእግዚአብሔር ፊት ይበልጥ ሞገስ እንደሚሆነን
በማሰብ ሊመጣ የሚችልን ፈተና እንዴት መቋቋም እንችላለን?
2.የአጥቢያ ቤተ ከርስቲያንዎ ማኅበረሰብ ልዩነት የማያደርግ በክርስቶስ አንድ
የሆነ ምዕመን ነው? አብልጦ ወደዚህ አቅጣጫ መምጣት የሚቻለው እንዴት
ነው? ቤተ ክርስቲያንዎ ምን ያህል ሌሎችን አካታች ነው?
3.በችግር ያሉትን እየረዳንና እግረ መንገዳችንን የወንጌልን እውነት እያካፈልን
ትክክለኛውን ሚዛን ጠብቀን መጓዝ የምንችለው እንዴት ነው? እነዚህን ሁለት
ነገሮች በተጓዳኝ ማድረግ የምንማረው እንዴት ነው? ሁለቱንም ጎን ለጎን
ማስኬድ ሁሌም የተሻለ የሆነው ለምንድን ነው?
ማጠቃለያ፡በደኅንነት እቅድ እንዲሁም በየሱስ መሥዋዕትነትና
ህይወት የተገለጸው የእግዚአብሔር ፍቅር--ይቅርታ፣ ህይወትና
ተስፋ ይሰጠናል፡፡ እንደ ጸጋው ተቀባይነታችን ይህን ለሌሎች
ለማካፈል የምንመኘው ለመዳን ብለን ሳይሆን የተፈጠርነውና ዳግም
የተወለድነው ይህንን ለማድረግ በመሆኑ ነው፡፡ እንዲሁም ወንጌል
የግንኙነትን ዐውድ በመቀየር ወደ አገልግሎት ይመራል--በተለይም
እርዳታ ወደ ሚፈልጉት፡፡