“ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ…”
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 3ኛ ሩብ ዓመት 2019

ከሰኔ 29-ሐምሌ 5

2ኛ ትምህርት

Jul 06 - Jul 12




የተሻለ ዓለም ለማምጣት የሚያስችል ንድፍ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘፀ. 3:7፣ ማቴ. 22:37–40፣ ዘፀ. 22:21–23፣ ዘዳ. 14:22–29፣ 26:1–11፣ ዘሌዋ. 25:9–23።


መታሰቢያ ጥቅስ:- “ ‘ወገንህን አትበቀል፤ ወይም ምቀኛ አትሁንበት፤ ነገር ግን ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ’ ” (ዘሌዋ. 19:18)።

እ ግዚአብሔር ሁሌም ቢሆን በምኅረት ከተሞላ ማንነቱ ጋር በዓይነቱ ልዩ የሆነውን የግንኙነት መስመር እንደ ጠበቁ የቆዩ ሕዝቦች ነበሩት። የእነ ሔኖክ፣ ኖህ፣ አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብና ሌሎች ወገኖች ታሪክ እግዚአብሔር ከሰብዓዊው ፍጡር ጋር የነበረውን የተበላሸ ግንኙነት ዳግም ለመመስረት የነበረውን መናፈቅ ያሳያል። ነገር ግን በግንኙነቱ መስመር መታደስ የቱሩፋቱ ተጠቃሚዎች እነዚህ ጥቂት ግለሰቦችና ቤተሰቦቻቸው ብቻ እንዳልነበሩ መመልከት እንችላለን። ይልቁንም እነዚህ ወገኖች ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት መስርተው በእርሱ ሲባረኩ-ይህን በረከት ለሌሎች ማስተላለፍ የግዙፉ ዕቅድ አካል ነበር። “‘ ታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ፤ ደግሞም እባርክሃለሁ፤ ስምህን ገናና አደርገዋለሁ፤ ለሌሎች በረከት ትሆናለህ. . . በምድር የሚኖሩ ሕዝቦች በአንተ አማካይነት ይባረካሉ’ ” (ዘፍ. 12:23)። እርሱ ሲባረክ ለሌሎችም በረከት መሆን ይችላል። ይህ በረከት በእስራኤል ሕዝብ አማካይነት መምጣት የነበረበት ሲሆን፤ ውሎ አድሮ መሲህም ከዚያው ሕዝብ መምጣቱ የታወቀ ነበር። እስራኤላውያን እንደ ሕዝብ ከተመሰረቱ በኋላ እግዚአብሔር የሚሠራው በጣት ከሚቆጠሩ ግለሰቦች ጋር ሳይሆን ከመላው ሕዝብ ጋር ሆነ። ይህን ተከትሎ እነዚህ በእግዚአብሔር የተባረኩ ሕዝቦች ለሌሎችም በረከት ይሆኑ ዘንድ የሚተዳደሩባቸውን ሕጎች፣ ደንቦችና የሚያከብሯቸውን በዓላትና ወግ ልማዶች ሰጣቸው። ይህ መርኅ ዛሬም የሚሠራ ለመሆኑ አፋችንን ሞልተን መናገር እንችላለን።

ሰኔ 30
Jul 07

የሚሰማው አምላክ


“ ‘በግብፅ አገር የሚኖሩትን የሕዝቤን መከራ አይቻለሁ፤ ከአሠሪዎቻቸው ጭካኔ የተነሳ የሚያሰሙትንም ጩኸት ሰምቻለሁ፤ ሥቃያቸውንም ተረድቼአለሁ’ ” (ዘፀ. 3:7)። እየተቀዛቀዘ ሳይሆን እየጋመ ይሄድ ለነበረ ጭካኔ የተሞላበት የባርነት ዘመን--አራት መቶ ዓመት መጠበቅ እጅግ ረጅም ጊዜ ነው። እግዚአብሔር ወደ ሕዝቡ ተመልሶ ከግብፅ እንደሚያወጣቸውና ወደ ለምለሚቱ ምድር እንደሚመራቸው የተስፋ ቃል ሰጥቶአቸው የነበረ ቢሆንም፤ ትውልድ ሄዶ ትውልድ ቢተካም የጨቋኞቹን ጣዖት አምላኪ ጌቶቻቸውን ሐብትና ክብር እንዲገነቡ ተተዉ። እግዚአብሔርም ጸጥ ያለ መሰለ።

ከዚያም እግዚአብሔር ልዩ በሆነ መንገድ ራሱን ገለጠ። ጭው ባለ ምድረ በዳ-በሚነድ ቁጥቋጦ ውስጥ ለአንድ ትሁት ኮብላይ ልዑል እና የበጎች እረኛ ጌታ ራሱን ገለጠ። እግዚአብሔር በወቅቱ ዳተኛ ለነበረው ሙሴ የሚሠራውን ሥራ ሰጠው። እስራኤላውያን ወደ ነበሩበት ግብፅ ተመልሶ በመሄድ እግዚአብሔር ጭቆናቸውን ማየቱንና መስማቱን የሚገልጥ መልእክት መላክ ለሙሴ የተሰጠው የመጀመሪያው ክፍል ኃላፊነት ነበር። ይህ ደግሞ እግዚአብሔር በእርግጥ ለሕዝቡ እንደሚጠነቀቅ ያሳየ ክስተት ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ ሕዝቡ የሚገኝበትን ሁናቴ ለመለወጥ ጌታ አንድ አስደናቂ ለውጥ ማድረግ ነበረበት።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፀ. 3፡16-17። እግዚአብሔር በዓይነቱ ልዩ የሆነውን ይህን እቅድ ለእነዚህ ሕዝቦች አውጥቶ መሥራት እንዲጀምር ያስፈለገው ለምንድን ነው? ከዚህ አምላካዊ መግለጫ ይበልጥ ትኩረትዎን የሳበው የትኛው ክፍል ነው?



ሆኖም እግዚአብሔር በዚህ አልቆመም። የእግዚአብሔር እቅድ ሕዝቡ የተሻለ ምድር ባለቤት ሆኖ እንዲወጣ ብቻ ሳይሆን ከግብፅ ባዶ እጁን፣ በድኽነት እንዳይወጣም ጭምር ነበር። እነዚህ ወገኖች ላለፉት አራት መቶ ዓመታት ለግብፅ ሕዝብና መንግሥት ብልጽግና ይሄ ነው የማይባል ከፍተኛ የኤኮኖሚ አስተዋእጾ አበርክተዋል። ፈርኦን ሕዝቡን በቀላሉ እንደማይለቅ እግዚአብሔር አስቀድሞ ተመልክቶ የነበረ ቢሆንም፤ እስራኤላውያን ለዘመናት ለሠሩት ከባድ ሥራ ተመጣጣኝ ማካካሻ ይዘው እንደሚወጡ እግዚአብሔር ለሙሴ አረጋግጦለት ነበር። “ይህ ሕዝብ በግብፃውያን ዘንድ የመወደድን ጸጋ እንዲያገኝ ስለማደርግ በምትወጡበት ጊዜ ባዶ እጃችሁን አትሄዱም” (ዘፀ. 3፡21)። እስራኤላውያን አስከፊውን የጭቆና ገፈት ከቀመሱባቸው ዘመናት በኋላ እግዚአብሔር ከእነዚህ የቀድሞ ባሮች ጋር በዓይነቱ አዲስ የሆነ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ዕድሉን ተጠቀመበት። ሕዝቡ ከተለመደው የአኗኗር ዘይቤ ወጥቶ በተለየ መንገድ እንዲኖርና በዘላቂነት ራሱን ችሎ የሚያድግ ማኅበረሰብ ለመመስረት የአምላካዊው ፍላጎት ነበር። ይህ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ማኅበረሰብ ለአጎራባች ሕዝቦችና መንግሥታት ሞዴል በመሆን ልክ እንደ አብርሃም እነርሱም ከእግዚአብሔር የሚቀበሉት በረከት መላውን ዓለም ይባርክ ዘንድ አምላካዊው ዕቅድ ነበር። እግዚአብሔር አምላክ በዓለም ያሉ ሕዝቦችን ሥቃይና መከራ የሚመለከትና ልቅሶአቸውን የሚሰማ አምላክ መሆኑን መገንዘብዎ ለእርስዎ ምን ዓይነት ትርጉም አለው? ታሪኩ ስለ እግዚአብሔር ምን ይነግሮታል? ይህን ጥቅስ በድጋሚ ይመልከቱ--ዘፀ. 4፡31።

ሐምሌ 1
Jul 08

ዐሥርቱ ትእዛዛት


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማቴ. 22፡37-40፣ ዘፀ. 20፡1-17። ዐሥርቱን ትእዛዛትን ሲያነቡ የሱስ ስለ እነዚህ ትእዛዛት የሰጠው የማጠቃለያ ሃሳብ ይበልጥ እንዲያስተውሉአቸው የሚረዳዎ እንዴት ነው?



ዐሥርቱ ትእዛዛት ልክ እንደ ሕገ መንግሥት ይነበባሉ። እነዚህ መግለጫዎች መሰረት ስላደረጉበት ነገር አጠር ያለ መግቢያ--ማለትም እግዚአብሔር ሕዝቡን የመታደጉ እውነታ እና አገሪቱ የተመሰረተችባቸውን ዐበይት መርኅዎች ሰነዱ በዝርዝር ያቀርባል። እዚህ ላይ ፍቅር ለእግዚአብሔር እና ፍቅር ለሰው በሚል መርኅ ሰብዓዊ ፍጡራን ምርጥ በሆነ ፍቅር አምላካቸውንም ሆነ እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱ የቀረቡ ልዩ ትእዛዞች ነበሩ። ክርስትናን በቅርስነት የያዙ የአያሌ አገራት ሕጎች መሰረት ከእነዚህ መርኅዎች መመዘዛቸው ብዙም የሚገርም አይሆንም።

ከእነዚህ መግለጫዎች አብዛኞቹ አጠር ብለው ቢቀርቡም የተጽእኖአቸውን ወርድና ስፋት ዝቅ አድርገን መመልከት የለብንም። መግለጫዎቹ ማለትም ዐሥርቱ ትእዛዛት እንደ ሕይወት ሕግጋትነታቸው ያላቸውን ጠቅላይ ባህሪ መዘንጋት የለብንም። ለምሳሌ “አትግደል” (ዘፀ. 20፡13) የሚለው አሥረኛው ትእዛዝ “ህይወትን የሚያሳጥር ማንኛውም ዓይነት ኢፍትሐዊነት… የተቸገረውን ወይም በሥቃይ ያለውን ችላ የሚል ራስ ወዳድነት” (የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት ገጽ 346) በሚል አጠር ያለ ፍቺ ቀርቦአል። በተመሳሳይ መስረቅ የሚከለክለው ሕግ (ዘፀ. 20፡15) “የባርነት ንግድ መፈጸምና ሰዎችን በጦርነት ወርሮ መያዝን ያወግዛል።” እንዲሁም “የሠራተኞችን ክፍያን መክፈል፤ የወሰድነውም ብድር ቢኖር በአግባቡ መመለስ እንዳለብን ይነግረናል።” በተጨማሪ “ለግል ጥቅም ሲባል የሌሎችን--አለማወቅ፣ ደካማነት ወይም እጦት ተገን በማድረግ” ማጭበርበር የለብንም።--(የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት ገጽ 346-347)። መጥፎ ሰዎች እንዳልሆን በቀላሉ ለራሳችን መንገር እንችል ይሆናል። ለምሳሌ በአንድ ግድያ ወይም የስርቆት ወንጀል ላይ ተሳታፊዎች ባለመሆናችን ራሳችንን እንደ ጻድቅ እንቆጥር ይሆናል። ነገር ግን የሱስ ስለ ትእዛዛቱ ሲናገር ከትእዛዛቱ የተወሰኑት በመጠበቃቸው ብቻ ሕጉ ተከብሮአል ማለት እንዳልሆነ ግልጽ አድርጎ አስቀምጦአል። ይልቁንም አስተሳሰባችን፣ ተነሳሽነታችን--ከዚያም አልፎ ማድረግ እንዳለብን የምናውቀውን ነገር አለማድረጋችን በራሱ አምላካዊውን ሕግ ሊጥስ ይችላል (ማቴ. 5፡ 21-30)።

እያንዳንዱ የዐሥርቱ ትእዛዛት ሕጎች በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ በጽኑ ገቢራዊ ቢሆኑና ከሰዉ ህይወት ጋር ብርቱ ቁርኝት ቢኖራቸው ምን ሊፈጠር እንደሚችል በዐይነ ህሊናዎ ለመሳል ይሞክሩ። እያንዳንዱ ሰው ፍቅሩን በጋለ መንፈስ ለሰው እንዲሁም ለእግዚአብሔር የሚገልጽ፣ ለሌሎች እንክብካቤ የሚያደርግ፣ ንቁና ደስተኛ ማኅበረሰብ በሆነ ነበር።

እጅግ የገዘፉትንና ለህይወታችን ጠቃሚ የሆኑትን የዐሥርቱን ትእዛዛት አንደምታዎች ችላ እያልን “ጠባብ” በሆነ እይታ ማንበብ የሚቀናን ለምንድን ነው? ጠባቡን የንባብ ስልት መከተል ቀላል የሆነው ለምንድን ነው?

ሐምሌ 2
Jul 09

ባሮች፣ መበለቶች፣ አባት የሌላቸው ህፃናትና መጻተኞች


ጥቅሱን ያንብቡ፡ ዘፀ. 23፡9። እዚህ ላይ እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን የሰጠው መልእክት ምንድን ነው?



ከባርነት ነፃ ለመውጣት አዲስ የነበሩት እስራኤላውያን--ጭቆና፣ ብዝበዛና እጅግ ዝቅ ተደርጎ መታየት ምን ማለት እንደሆነ ጠንቅቀው ያውቁ ነበር። ነፃነታውቸን ሲያከብሩ ከየት እንደመጡ፣ ዝቅ ተደርጎ መፈረጅ ምን ይመስል እንደነበርና እግዚአብሔር እነርሱን ነጻ ለማውጣት ያደረገውን በጎነት እንዳይረሱ ጌታን አሳስቦት ነበር። በመሆኑም እነዚህ ሕዝቦች ያለፉበትን ታሪክ “ከባርነት ምድር ከግብፅ እግዚአብሔር በኃያል ክንዱ አወጣን” (ዘፀ. 13፡14) ብለው ለልጅ ልጆቻቸው ይነግሩ ዘንድ እግዚአብሔር እንደ መታሰቢያ አድርጎ የፋሲካን በአል ሰጣቸው። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፀ. 22፡21-23። እስራኤላውያን በመሰረቱት አዲስ ማኅበረሰብ ውስጥ ድኾችንና መጻተኞችን እንዴት መመልከት እንዳለባቸው በባርነት ያለፉበት ትውስታ ምን ያህል ሊረዳቸው ይችላል?



ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ተጨማሪ ጊዜያቶችን እንዲያሳልፍ በቀረበለት ጥሪ መሰረት ግዙፎቹን ዐሥርቱን ትእዛዛት እና ዝርዝር መመሪያዎችን ከእርሱ ተቀበለ። እግዚአብሔር የመገናኛ ድንኳኑን ስለ መገንባት መመሪያ ከመስጠቱ አስቀድሞ-አብዛኞቹ እስራኤላውያን ካለፉባቸው ተሞክሮዎች በተቃራኒ ባሮችን ተገቢ በሆነ መንገድ ስለመያዝ የሚናገሩ ሦስት ምዕራፍ ያሏቸውን ሕጎች ሰጥቶአቸው ነበር። እነዚህ ሕጎች ስለ ከባድ ወንጀሎች፣ ሐብት ስለ ማፍራት፣ ስለ የዕለቱ አኗኗር የሚናገሩ ከመሆናቸው በተጨማሪ ሕጎቹን ተግብሮ ፍትሕን በማስፈኑ ረገድ--የፍርድ ሸንጎዎችን ለማቋቋም የሚያስችሉ መርኅዎችንም ያካተቱ ነበሩ (ዘፀ. ምዕ. 21 እስከ 23)። በዚህ በዓይነቱ አዲስ የሆነ የእስራኤል ማኅበረሰብ፤ ለዜጎች መድረስ እንዲሁም ለመጻተኞችና ለአደጋ ተጋላጮች አለኝታ መሆን በጉልህ ከቀረቡት ሕጎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። እነዚህ ሰዎች ከምንም ዓይነት ብዝበዛ የተጠበቁ ነበሩ። የሚበሉትን በተመለከተ ለስብእናቸው ተገቢውን ክብር በሰጠ መልኩ ከማንኛውም ሰው እርሻ ዙሪያ ቃርሚያ መልቀም የሚችሉበት መብት ጭምር ተችሮአቸው ነበር። እንዲህ ዓይነቱ “መጻተኞችን” የመንከባበከብ ተግባር በጥንቱ ዓለም የተለመደ አልነበረም። እንዴት ለሌሎች አለኝታ መሆን እንዳለብን የሚነግሩን በእጅጉ አስፈላጊ የግብረገብ መርኅዎች እነሆ ዛሬም በአንዳንዶች የተዘነጉ ይመስላሉ። በሌሎች ላይ በሚደርሱ ሥቃዮችና የፍትሕ መጓደሎች ይበልጥ እንዲራሩ የሚያደርግዎ ምን ዓይነት ትውስታ አሎት?

ሐምሌ 3
Jul 10

የአሥራት አሥራት (ሁለተኛ አሥራት)


አያሌ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አሥራት የሚሰጠውን ትእዛዝ በሙሉ ልባቸው አምነው በመቀበል አሥራታቸውን ይመልሳሉ። በሚልክ. 3፡10 በቀረበው ቀላል ቀመር መሰረት አማኞች ከገቢያቸው አንድ አሥረኛውን ይመልሳሉ። ወይም ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን ለማሰራጨት የምትሠራውን ሥራ በመደገፍ በዚያ ላይ አክለው ይሰጣሉ። የምዕመኑን አሥራት አደራ የተቀበሉት ቤተ ክርስቲያኖች ስለ ገንዘቡ አጠቃቀም ጥብቅ መመሪያ ያላቸው ሲሆን፤ ለወንጌል አገልግሎት ቀጥተኛ ድጋፍ ቅድሚያ ይሰጣሉ።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘዳ. 14፡22-29። በቀረቡት መመሪያዎች መሰረት አሥራት የመመለስ ተቀዳሚው ዓላማ ምንድን ነው?



ከአሥር አንድ በመመለስ አሥራታችንን ስንከፍል የሚፈለግብንን እንዳሳካን አድርገን በማሰብ እንፈተናለን። ነገር ግን ለእስራኤላውያን የተሰጡት መመሪያዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ አሥር ከመቶው መነሻ ነጥብ ነው። ጥናቶች እንደሚያሳዩት በዘሌዋውያን ሕግና ደንቦች መሰረት ይኖሩ የነበሩ የጥንት እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር ሥራ፣ ካህኑንና ቤተ መቅደሱን ለመደገፍ እንዲሁም ድኾችን ለመደገፍ ከዓመቱ ገቢያቸው ከእሩብ እስከ አንድ ሦስተኛ የሚሆነውን በመደበኛ ይሰጡ ነበር።

አንዳንድ የሥነ መለኮት ምሑራን፤ በተለይ መጻተኞችን፣ ወላጅ የሌላቸውን ህፃናትና ባሏ የሞተባትን መበለት ለመደገፍ ይውል የነበረውን ስጦታ እንደ ሁለተኛ አሥራት አድርገው ይገልጹታል። ሕዝቡ በሥራው ውጤትና በሰበሰበው ምርት ሞገስ ማግኘቱና ደስ መሰኘቱ እሙን ነው። እስራኤላውያን በተለይ በአዲሱ ምድራቸው እግዚአብሔር እንደሚባርካቸው ቃል ገብቶላቸው የነበረ ቢሆንም፤ እነርሱ ግን የተሰጣቸው በረከት ሁሌም በእጃቸው እንደሚሆን በማሰብ ዝቅ አድርገው ተመለከቱት።

በመደበኞቹ ዓመታት ከሰበሰቡት ምርት የተጠቀሰው መጠን ለቤተ መቅደሱ እንዲገባ ይደረግ ነበር። ሆኖም በየሦስት ዓመቱ ግን ያገኙትን በረከት ለገዛ ማኅበረሰባቸው የማጋራት ልዩ ትኩረት ይደረግ ነበረ። መከር የሚሰበሰብባቸው የፌሽታ ጊዜያቶች በቀላሉ ችላ ሊባሉ ወይም ሊዘነጉ የሚችሉ ወገኖች ላይ ልዩ ትኩረት ይደረግ ነበር፡ “የአሥራት ዓመት የሆነውን የሦስተኛውን ዓመት ምርት አንድ ዐሥረኛ ለይተህ ካወጣህ በኋላ በየከተሞችህ ውስጥ በልተው እንዲጠግቡ ለሌዋዊው፣ ለመጻተኛው፣ አባት ለሌለውና ለመበለቲቱ ስጣቸው” (ዘዳ. 26፡12)።

እግዚአብሔር በሰጠው መመሪያ መሰረት እስራኤላውያን ከሚሰጡት ስጦታ ቢያንስ የተወሰነው ክፍል የገንዘብና ሌሎች ተጨባጭ ድጋፎች ለሚያስፈልጓቸው ወገኖች እንዲውል ይደረግ ነበር። አሁንም ቢሆን ይህ ችሮታ እግዚአብሔር ምን ያህል ለእነርሱ መሐሪና ጻድቅ እንደሆነ አድናቆታቸውን የሚገልጡበትን ትውስታ መሰረት ያደረገ ነበር።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘዳ. 26፡1-11። ጌታ ምን እያላቸው ነው? በችግር ላሉ ስለ መስጠት አስመልክቶ ይህን ለየራሳችን መተግበር የምንችለው እንዴት ነው?

ሐምሌ 4
Jul 11

የኢዩቤልዩ ዓመት


የገዛ ራሳቸው መኖሪያ ቤት የሌላቸው፣ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመድረስ ይጠባበቁ የነበሩ እስራኤላውያን እንደ ሕዝብ አዲሱ ማኅበረሰባቸው በከነዓን የመቋቋሙን አስፈላጊነት እግዚአብሔር ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። በኢያሱ መሪነት እንደ የጎሳቸውና ቤተሰባቸው ምድሪቱን ሥርዓት ባለው አመዳደብ ይከፋፈሉ ዘንድ እግዚአብሔር ተገቢውን የቁጥጥር ሥራ ሠርቶ ነበር።

እንዲሁም ከመሬት ስሪት ጋር በተያያዘ ሐብት፣ ምቹ ሁናቴዎችና ብልጽግና በጥቂት ሰዎች እጅ ሊወድቅ እንደሚችልም እንዲሁ እግዚአብሔር ያውቅ ነበር። በቤተሰብ ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮች፣ የጤና እክል፣ ደካማ ምርጫና ውሳኔ--እንዲሁም አንዳንዶች ለአጭር ጊዜ ጥቅም ወይም ለጊዜያዊ ችግር መፍቻ ብለው ይዞታቸውን ይሸጣሉ። ታዲያ ይህ እንደ ዋዛ የሚደረግ ውል ቤተሰቡን ለተከታታይ ትውልዶች ከርስት የመንቀል አደጋ ያስከትላል።

መሬት ፍጹም እንዳይሸጥ መደንገግ አምላካዊው መፍትሔ ነበር። ሆኖም መሬት እስከ ቀጣዩ “የኢዮቤልዩ ዓመት” ብቻ እንዲሸጥ ተወስኖ የነበረ ሲሆን፤ በዚህ ወቅት ተሸጦ የነበረ ርስት ወደ ቀድሞው ቤተሰብ ይመለስ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ርስቱን የሸጠ ግለሰብ በማንኛውም ጊዜ ይዞታውን ዋጅቶ ማስመለስ ወይም የቅርብ ዘመዱ መሬቱን ሊዋጅለት ይችል ነበር። “መሬት ለዘለቄታ አይሸጥ፤ ምክንያቱም ምድሪቱ የእኔ ናት፤ እናንተም መጻተኞችና እንግዶች ናችሁ” (ዘሌዋ. 25፡23)። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘሌዋ. 25፡8-23)። እነዚህ መርኅዎች ጥቅም ላይ ቢውሉ ኖሮ ማኅበረሰቡ ከዛሬው ምን ያህል የተለየ ሊሆን ይችል ነበር ብለው ያስባሉ? በተለይ አንዱ ሌላውን አይጨቁን ከሚለው አባባል አኳያ?

“እግዚአብሔር እነዚህን ደንቦችና መተዳደሪያዎች የቀየሰው ማኅበራዊ እኩልነትን ለማስፈን ነው። የሰንበት ዓመትና ኢዮቤልዩ--በህዝቡ ማኅበራዊና ፖለቲካ ኢኮኖሚ የተፈጸሙ ልዩነቶችን ለማስወገድ የተቀየሱ ማስተካከያዎች ናቸው።” (የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት ገጽ 613 /አማርኛው ትርጉም/) እነዚህ በተደጋጋሚ የሚከሰቱ የምጣኔ ሐብትና ማኅበራዊ ጉዳዮች ምን ያህል ሙሉ ለሙሉ በሥራ ላይ መዋላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ምሑራን እርግጠኞች አይደሉም (2ዜና 36፡21)። ሰዎች የእግዚአብሔርን ሕጎች ሙሉ ለሙሉ ተከትለው ቢሆን ኖሮ ዓለም ምን ትመስል እንደ ነበር በውልብታም ቢሆን በእነዚህ መሳጭ ደንቦች ማየት እንችላለን። በተጨማሪ እግዚአብሔር ለድኾችና ዝቅ ተደርገው የሚታዩ ወገኖች ስላለው ስጋት አጽንኦት ይሰጣሉ። እንዲሁም ሚዛናዊነት በዓለማችን በተጨባጭ እንዲታይ ያለውን ጭንቀትም ያሳያል።

ሐምሌ 5
Jul 12

ተጨማሪ ሀሳብ


Read Ellen G. White, “The Law Given to Israel,” pp. 303–314; “God’s Care for the Poor,” pp. 530–536, in Patriarchs and Prophets. “እስራኤላውያን የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ከተቀበሉና እንደ ፈቃዱ መመላለስ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ሙሴ እንዳዘዘው ድሖችን ከማሰብና ለእነርሱ የርኅራኄና የእንክብካቤ መንፈስ ከማሳየት የላቀ ነገር የለም። ምንም እንኳ እግዚአብሔር ህዝቡን አብልጦ ለመባረክ ቃል ቢገባም፤ ነገር ግን ድህነትን ሙሉ ለሙሉ ሳያውቁ ይቀሩ ዘንድ እቅዱ አልነበረም። በመሆኑም ከምድሪቱ ድሖች ፈጽሞ እንዲጠፉ እንደማይፈልግ ገልጾአል። ቸርነት፣ ለጋስነትና ድጋፍ የሚጠብቁ ወገኖች በሕዝቦቹ መካከል መኖራቸው ይቀጥላል። ያን ጊዜም እንደ ዛሬው በሰዎች ላይ መጥፎ ዕድል፣ ህመምና ድህነት ይደርስ ነበር። ሆኖም የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ተከትለው እስከኖሩ ድረስ በመካከላቸው ለማኞች ወይም ምግብ አጥቶ የሚቸገር አልነበረም።” (የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት ገጽ 609 /አማርኛው ትርጉም/) “እነዚህ ደንቦች የተቀየሱት ባለጸጋውን ከድኻው ባላነሰ ለመባረክ ነው። ስስትና ራስን ከፍ የማድረግ አባዜ እንዲታቀብ በማድረግ የደግነትን ታላቅ መንፈስ ይቀርጻሉ። በሁሉም መደቦች መካከል ቅን ልቦናና መተማመን እንዲፈጠር በማድረግ አገርን የሚያረጋጋ ማኅበራዊ ሥርዓት ያዳብራሉ። ሁላችንም የተሠራነው በታላቁ ሰብዓዊነት ድርና ማግ እንደመሆኑ ሌሎችን ለመጥቀምና ለማንሳት የምናደርገው ተግባር በረከት ሆኖ በላያችን ያንጸባረቃል።” (የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት ገጽ 614 /አማርኛው ትርጉም/)


የመወያያ ጥያቄዎች




1.ሙሴ እና የእስራኤል ሕዝቦች ስለሚመሰርቱት ማኅረሰብ እግዚአብሔር ከሰጣቸው ንድፍ ውስጥ የእርስዎን ትኩረት የሳበው የትኛው ሕግ፣ ደንብ ወይም መመሪያ ነው? (በዚህ ሣምንት ትምህርቱ ከቀረበው ወይም እርስዎ በተጨማሪ ሲያነቡ ካገኙት)

2.እግዚአብሔር ለሕዝቡ ከሰጠው ሕጎች ውስጥ ትኩረቱ ለጉዳት ተጋላጭ ወገኖች ላይ የሆነው ለምን ይመስሎታል?

3.ዛሬ እነዚህን ሕጎች እንዴት ማስተዋልና ከራሳችን ጋር ማዛመድ እንችላለን? ከእነዚህ መካከል ከዛሬው የእኛ ሁኔታ ጋር ሊሠሩ የሚችሉትንና የማይችሉትን መምረጥ የምንችለው እንዴት ነው? እስራኤላውያን ማኅበረሰባውንና ህይወታቸውን በሥርዓት ከመሩባቸው ከእነዚህ በዝርዝር ከቀረቡ መመሪያዎች የምንማረው በጣም አስፈላጊ ነገር የትኛው ነው?

ማጠቃለያ፡ በምድረ ግብፅ በባርነት ሥቃይ ውስጥ የነበሩትን እስራኤላውያን የልቅሶ ድምጽ የሰማው እግዚአብሔር እነሆ ሊያድናቸው ጣልቃ ገባ። ምንም እንኳ እሰራኤላውያን የተረሱ፣ ከሌላው ሕዝብ በእኩል የማይታዩና ደካሞች ቢመስሉም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር በዓይነቱ ልዩ የሆነ የኪዳን ግንኙነት ለመመስረትና ለሁሉም በረከት የሚሆን አዲስ ማኅበረሰብ ለመፍጠር አብሮአቸው መሥራት ተመኘ።