ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘፀ. 16:16–18፣ ዘፀ. 20:8–11፣ ዘዳ. 5:12–15፣ ማቴ. 12:9–13፣ ዘሌዋ. 25:1–7።
መታሰቢያ ጥቅስ:-“ሰውሰንበት ስለ ሰው ተፈጥሮአል እንጂ ሰው ስለ ሰንበት አልተፈጠረም. 2፡ 27)።
እ
ግዚአብሔር በፍጥረት ሥራው ሣምንት መደምደሚያ ላይ ሰንበትን ፈጠረ።
እርሱ በሰባተኛው ቀን ማረፍ ብቻ ሳይሆን ለምድር መፈጠር መሰረታዊ
ክፍል የሆነውንም እረፍት እንደ ፈጠረ ሲነገር ይደመጣል። ሰንበት
ከእግዚአብሔር ጋር ብሎም እርስ በርሳችን ትስስር እንድንፈጥር ሆነን የመፈጠራችን
ማሳያ ነው።
እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያቀደውና ከትእዛዛቶቹ አንዱ የሆነው ሰንበት፤ ጥንት አዲስ
ሆኖ የተቋቋመው የእስራኤል ሕዝብ እንደጠበቀው መመልከት ብዙም ላያስገርም
ይችላል። ሰንበት በቀደሙት ዕብራውያን ህይወት ቁልፍ ሚና ነበረው።
ብዙውን ጊዜ ሰንበትን አስመልክቶ ስናወራ--እንዴት እንጠብቀው? የሚለው
ሃሳብ ፈጥኖ ይንጸባረቃል። ማድረግ የሌለብን ነገሮች ምንድን ናቸው? ያለብንስ?
ምንም እንኳ እነዚህ ጥያቄዎች አስፈላጊ ቢሆኑም፤ የአምላካዊው ጸጋና ስጦታ
ተምሳሌት የሆነው ሰንበት--በዓለምና በእግዚአብሔር ሕዝቦች ህይወት የራሱ ሚና
እንዲሚኖረው ሆኖ የተነደፈበትን መሰረታዊ ዕቅድ ማስተዋል ይኖርብናል።
የሱስ እንደተናገረው ሰባተኛው ቀን ሰንበት የተፈጠረው ዘር ቀለም ሳይል ለሁሉም
ሰብዓዊ ፍጡራን ነው። የሰንበትን ቀን በእውነት ስናስብ በሣምንቱ እያንዳንዱ ቀን
የተለወጥን እንሆናለን። የሱስ እንዳሳየው--ሌሎችን መባረኪያ መንስኤ መሆንም
ይችላል።
እስራኤላውያን የማይፈልጉትን እንዲቀበሉ ከተገደዱባቸው አያሌ ትውልዶች
ካለፉበት የባርነትና የማኅበራዊ ዝቅታ ዘመን በኋላ--እግዚአብሔር ይህን አዲስ
የነፃነት ባለቤት የሆነ ሕዝብ ወደ ተሻለ የአኗኗር ዘይቤ እያመላከተና ምርጥ የሆኑ
ሕግና ደንቦችን እየሰጠ ወደ ወደ ከፍታ የማምጣት ምኞት አደረበት። ይህ ሂደት
እውን ከሆነባቸው የመጀመሪያ ክፍሎች አንዱ ተግባራዊ ማስተማሪያ ዘዴዎችን
የተከተለ ነበር።
እስራኤላውያን ለቀጣዮቹ 40 ዓመታት በምድረ በዳ ባደረጉት መንከራተት
ያለፉባቸው የህይወታቸው ክፍል፤ ማለትም በገሃድ የተመለከቱት አምላካዊ
እርዳታና ራስ ወዳድ ያልሆነ ፍቅር--የእስራኤል ማኅበረሰብ ባህል አካል መሆን
በቻለ ነበር። እስራኤላውያን ባረፉባቸው ሰፈሮች ሁሉ ሁሌም ማለዳ ላይ የሚበሉት
መና ይወርድላቸው ነበር።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፀ. 16፡16-18። እያንዳንዱ ሰው የተወሰነ መጠን ያለው መና
እንዲያገኝ አጽንኦት መሰጠቱ ለምን ይመስሎታል
ሐዋርያው ጳውሎስ በ2ቆሮ. 8፡10-15 መልእክቱ ክርስቲያኖች እንዴት ሊሰጡ
እንደሚገባ አስመልክቶ ይህንኑ ታሪክ ይጠቅሳል፡ “በአሁኑ ጊዜ የእናንተ ትርፍ
የእነርሱን ጉድለት ያሟላል፤ የእነርሱም ደግሞ በተራው የእናንተን ጉድለት ያሟላል።
በዚህም ያላችሁን እኩል ትካፈላላችሁ” (ቁ. 14)።
እግዚአብሔር ለሕዝቡ እና ለፍጥረታቱ በለጋስነት መስጠቱ ለእስራኤላውያን
ብሎም ለእኛ የቀረበ ትምህርት ነው። የሚያስፈልገንን ብቻ ወስደን ትርፍ የሆነውን
ለሌሎች ለማካፈል ዝግጁ ከሆንን የሚራብም ሆነ የሚጠማ አይኖርም። ሕዝቡ
ለዕለቱ የሚያስፈልገውን በቂ መጠን ብቻ መውሰዱ በቀጣዩም ቀን ሌላ ተጨማሪ
አለ ብሎ መተማመን እንዲያድርበት ያደርጋል። ልክ እንደ እስራኤላውያን በባርነት
ቀንበር ውስጥ ያለፉ ሕዝቦች ትኩረታቸው የተቃኘው ከገዛ ህልውናቸው አኳያ ብቻ
ነው። እግዚአብሔር ግን የመታመን፣ የለጋስነትና የማካፈል ሕይወት ሊያሳያቸው
ወደደ።
ለእስራኤላውያን ይወርድ ከነበረው መና ጋር በተያያዘ ሌላም አስደናቂ ክስተት
የነበረ ሲሆን፤ ይኸውም በየሣምንቱ ዓርብ ከሌላው ቀን እጥፍ መጠን የነበረው
መና ለእነዚህ ሕዝቦች መውረዱ ነው። በመሆኑም በዚያ ቀንና በዚያ ቀን ብቻ-ሕዝቡ ለሰንበት ዝግጅት ያደርግ ዘንድ ከተለመደው እጥፍ መና ይሰበስብ ነበር።
ሰንበትን አስመልክቶ የተሰጣቸው ልዩ ደንብ በሚያስፈልጋቸው ሁሉ በጌታ
መታመንን የሚማሩበትን ተጨማሪ ዕድል ከፈተላቸው። ይህ የአምላካዊው ጸጋ
አካል የሆነው ተጨማሪ መና፤ በሰባተኛው ቀን ሰንበት በማረፋቸው እግዚአብሔር
ቃል የገባላቸውን ደስታ ይበልጥ በሙላት እንዲያገኙ አስቻላቸው።
እግዚአብሔር በሰጠን ሰንበት በተሻለ ሐሴት ማድረግ እንችል ዘንድ
በዋዜማው አርብ፤ ምን ማከናወን ይኖርብናል?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፀ. 20፡8-11፣ ዘዳ. 5፡12-15። እነዚህ ስለ አራተኛው ትእዛዝ የሚናገሩ ሁለት ሐተታዎች እርስ በርስ ያላቸው ዝምድና ምን ይመስላል?
እግዚአብሔር ፈጣሪያችንና አዳኛችን የመሆኑ ሐቅ ላይ ማዕከል ያደረገውን
የቀደመ ግንኙነት ማስታወስ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ዳግመኛ ለመመስረት
ለፈለገው ግንኙነት አንዱና በእጅጉ አስፈላጊው ክፍል ነው። ሁለቱም ሚናዎች
በሁለቱ ሐተታዎች በቀረበው አራተኛው ትእዛዝ የታዩ ሲሆን፤ ይኸውም ከሰንበት
እና አጠባበቁ ጋር በቅርበት የተሳሰረ ነው።
ስፍር ቁጥር የሌላቸው አማልክት ከሚመለኩበት ምድረ ግብፅ ተጽእኖ
የወጡት እስራኤላውያን እውነተኛው አምላክ እንደ ፈጣሪነቱ ስለሚኖረው ሚና
እንዲያስታውሱ መደረግ ነበረባቸው። እስራኤላውያን በየሣምንቱ አርብ ከሌሎቹ
ቀናት እጥፍ መና እንዲቀበሉ የተደረጉበት ዐውድ--የፈጣሪነቱ ብርቱ ምሳሌ የሆነው
ሰንበት ትውስታን ለማምጣት እጅግ ወሳኝ ነበር። በዘፀ. 20 በቀረበው የአራተኛው
ትእዛዝ ሐተታ እግዚአብሔር እንደ ፈጣሪ እጅግ ግልጽ በሆነ መንገድ ተገልጦአል።
እነዚህ ሕዝቦች ከባርነት ቀንበር ነፃ መውጣታቸው፣ መዋጀታቸውና መዳናቸው
የአራተኛው ትእዛዝ ትኩረት ስለመሆኑ ከዘዳ. 5 ጋር በማነጻጸር መመልከት
እንችላለን። ይህ እስራኤላውያን በተለይ በየሣምንቱ ሰንበት መልሰው፣ መላልሰው
ሲያወሩት የሚኖሩት ታሪክ ነበር። ቀዳሚውና ከአፋቸው የማይጠፋው፤ ከግብፅ
ባርነት በተጨባጭ፣ በአካል የወጡበት ታሪክ ሲሆን--ስለ እግዚአብሔርና አዳኝነቱ
ያላቸው መረዳት በጎለበተ መጠን፤ ሰንበትም እንዲሁ ሣምንታዊ ምልክትና
የመንፈሳዊ ደኅንነታቸው ክብረ በዓል ሆነላቸው።
ስለ ሰንበት የተጻፉት የእነዚህ ሁለት ሐተታዎች ሰበበ ድርጊት በእግዚአብሔርና
በሕዝቡ መሃል ያለውን ግንኙነት ወደ ቀደመው ንጽህና መመለስ ነበር፡ “ ‘ “ደግሞም
እኔ እግዚአብሔር እንደ ቀደስኋቸው ያውቁ ዘንድ፣ በእኔና በእነርሱ መካከልም
ምልክት እንዲሆን ሰንበቴን ሰጠኋቸው” ’ ” (ሕዝ. 20፡13)። ቀደም ብለን እንደ
ተመለከትነው ትእዛዙ የተሰጠው ለእነዚህ ሕዝቦች ብቻ አልነበረም። ይልቁንም
በዚህ የግንኙነት መሰረት ከእነርሱ ውጪ ለሆነው ሕዝብ መልካም፣ ለመላው ዓለም
ደግሞ በረከት የሆነ በዓይነቱ ልዩ ማኅበረሰብ መመስረት ነበረባቸው።
“ ‘ስለዚህ አምላክህ እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ታከብረው ዘንድ አዘዘህ’ ” (ዘዳ.
5፡15)። ሰንበት የተፈጠርንበትና የተዋጀንበት ምልክት መሆኑን እያስታወስን ከጌታ
ጋር ብቻ ሳይሆን በዙሪያችን ካሉ ወገኖች ጭምር ግንኙነት እየፈጠርን ማደጋችንን
መቀጠል እንችላለን። እግዚአብሔር ለእኛ ቸር፣ ለጋስና መሐሪ እንደሆነ ሁሉ እኛም
ለሌሎች ተመሳሳይ ባህሪ እናሳይ።
ሰንበት መጠበቃችን በተሻለ ለሌሎች መልካም፣ ጥንቃቄ የሚያደርግና
ርኅሩኅ ህዝብ የሚያደርገን እንዴት ነው?
በዘፀ. 20 እና ዘዳ. 5 የቀረቡትን ዐሥርቱን ትእዛዛት ላይ ላዩን ገረፍ ስናደርግ ከሌሉቹ ይልቅ ለአራተኛው ትእዛዝ ሰፋ ያለ ዝርዝር መረጃ መሰጠቱን እንረዳለን። ምንም እንኳ ከዐሥርቱ ትእዛዛት መካከል አንዳንዶቹ በሁለት ቃላት (በዕብራይስጥ በቀረበው) ብቻ መገለጥ ቢችሉም፤ አራተኛው ትእዛዝ ግን ለምን፣ እንዴት እና ማን ሰንበትን ማስታወስ እንዳለበት አስመልክቶ ተጨማሪ ሀሳብ ይሰጣል። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፀ. 20፡8-11። ስለ ቤት ውስጥ ወንድም ሆነ ሴት ሠራተኞች፣ ስለ እንግዶች እንዲሁም ስለ እንስሳት ሳይቀር ምን ይላል? ምን ለማለት ነው የተፈለገው?
ስለ ሰንበት ከተሰጡት ዝርዝሮች ወስጥ በቤት ውስጥ ስለሚያገለግሉ ወገኖች
የቀረበው ትኩረት ልዩ አጽንኦት የሚሰጠው ነው። ይህ ዓይነቱ ትእዛዝ በዓለም ዙሪያ
ካሉ ባህሎች በእጅጉ የተለየ ነው ሲሉ ሲግቭ ኬ. ቶንስታድ ይሞግታሉ። “በጀመሪያ
ለደካሞችና ለጉዳት ተጋላጭ የማኅበረሰቡ አባላት ቅድሚያ የሚሰጠው የሰንበት
ትእዛዝ፤ ከላይ ወደታች ሳይሆን ከታች ወደ ላይ ሲወጣ ይታያል። ሌት ተቀን በሥራ
ተጠምደው የሚኖሩትና በእጅጉ እረፍት የሚያሻቸው ባሮች፣ በእንግድነት የተጠጉ
ሰዎች እንዲሁም መደበኛውን የሸክም አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ የጋማ ከብቶችና
ሌሎች አገልጋይ እንስሳት በተለየ ለተጠቀሰ ጉዳይ እንዲያርፉ ተደርገው ነበር።”—
The Lost Meaning of the Seventh Day (Michigan: Andrews University
Press, 2009), pp. 126, 127.
ሰንበት እያንዳንዱ ሰው የሚያርፍበትና ሐሴት የሚያደርግበት ዕለት በመሆኑ ዙሪያ
ትእዛዙ ልዩ ትኩረት ያደርጋል። እኛ ሁላችን በሰንበት ብርሃን ስንታይ እኩል ነን።
ለምሳሌ እርስዎ በሣምንቱ ውስጥ ሥራ የሚሠሩ ሠራተኞችን የሚቀጥሩ ቢሆኑ፤
የቀጠሯቸውን ሰዎች በቅዳሜ ቀን የማሠራት ሥልጣን ሊኖርዎት አይችልም። ይህ
የሆነበት ምክንያት እግዚአብሔር ለእነርሱም የሚያርፉበትን ቀን ስለ ሰጣቸው
ነው። ምናልባት እርስዎ ተቀጥረው የሚሠሩ ወይም ከነጭራሹ ባሪያ ቢሆኑ ደግሞ-ከሁሉም ሰው ጋር በእኩል የተፈጠሩና በእግዚአብሔር የተዋጁ መሆንዎን የሰንበት
ዕለት ያስታውሶታል። ከሌሎቹ በሥራ ኃላፊነት ተጠምደው ከሚያሳልፏቸው
የሣምንቱ ቀናት ይልቅ በዚህኛው ሐሴት እንዲያደርጉ እግዚአብሔር ግብዣ
ያቀርብሎታል። ትእዛዙ ሰንበትን ከሚጠብቁ ውጪ ያሉትን ሕዝቦች ጨምሮ “በግቢ
ያለ መጻተኛም” (ዘፀ. 20፡10) ከሰንበት ተጠቃሚ ሊሆኑ ይገባል።
ይህ ጽንሰ ሃሳብ ከባርነት እና ዝቅ ተደርጎ የመፈረጅ ተሞክሮ ገና በቅጡ
ባልወጡት እስራኤላውያን አመለካከት ላይ አስደናቂ ለውጥ ማምጣት ነበረበት።
በአዲሲቱ ምድር ለመቋቋም በቅርብ ሂደት ላይ የነበሩት እስራኤላውያን፤ የቀድሞ
ጨቋኞቻቸውን አስከፊ ልማድ የራሳቸው አድርገው እንዲቀጥሉበት የእግዚአብሔር
አምላክ ፍላጎት አልነበረም። ጌታ ለማኅበረሰባቸው ዝርዝር ሕጎችን ከመስጠቱ
በተጨማሪ ሁላችንም በፊቱ እኩል መሆናችንን የሚያስታውሰንን የሣምንቱን
አስተዋሽ ሕግ (ለእነርሱ ብቻ ሳይሆን ለእኛም ጭምር) ሰጠ።
ሰንበትን እንዴት ለማኅበረሰብዎ ማካፈል ይችላሉ? ማለትም--ሌሎች
ከእርስዎ ሰንበት ጠባቂነት እንዴት መጠቀም ይችላሉ?
የቀደመው የሰንበት እይታ ብሎም የሰንበት አጠባበቅ ሰፊና ሁሉን አካታች የነበረ
ቢሆንም፤ ነገር ግን የሱስ ወደዚህ ምድር በመጣ ጊዜ ሰንበት ለብዙ የኃይማኖት
መሪዎች ከቀደመው ድንጋጌ በእጅጉ የተለየ ገጽታ እንዲይዝ ተደርጎ ነበር። ዕለቱ
የነፃነትና የእኩልነት ቀን በመሆን ፋንታ--የሰው፣ የባህላዊ ወጎችና የክልከላ መሣሪያ
ሆነ። የሱስ በምድር ይመላለስ በነበረ ጊዜ ከእንዲህ ዓይነቱ መንፈስ በተቃራኒ ቆሞ
ነበር--በተለይ በሌሎች ላይ ከሚቆለል ጫና!
የሱስ በሰንበት ቀን ብዙ ፈውሶችን በማድረግ ያን የቀደመ ጽንሰ ሃሳብ ሲያንጸባርቅ
መመልከት በእጅጉ ደስ ያሰኛል። የሱስ ስለ ሰንበት የተሸሸገውን ነገር ለማሳየት
በመፈለግ ከሌሎቹ ቀናት በተቃራኒ ሆነ ብሎ በሰንበት እነዚህን ታምራቶች
ማድረጉን ለማስተዋል ብዙም አያዳግትም። እርሱ በሰንበት ቀን መፈወሱ ተገቢ
መሆኑን አስመልክቶ በታሪኮቹ በተደጋጋሚ አስተያየት መስጠቱ የተመለከተ ሲሆን፤
ፈሪሳውያንም እነዚህኑ ንግግሮቹን የሱስን ለመግደል ለጠነስሱት ሤራ እንደ ግብአት
ተጠቅመውባቸዋል።
የሱስ በሰንበት የፈወሰባቸውን ታሪኮች ያንብቡ፡ ማቴ. 12:9–13፣ ማር. 1:21–26፣
3:1–6፣ ዮሐ. 9:1–16። በታሪኮቹ ያስተዋሏቸው የላቀ ትርጉም ያዘሉ ነገሮች ምንድን
ናቸው?
የሱስ ሰንበትን ስለ ማክበር አስፈላጊነት ማረጋገጫ ሰጥቶአል። የሰንበትን ቀን በተለየ
መንገድ ለመጠበቅና ይህን ሣምንታዊ ጊዜ ከእግዚአብሔር አምላክ፣ ከቤተሰባችን፣
ከቤተ ክርስቲያናችንና ከማኅበረሰባችን ጋር ያለንን ግንኙነት ለማሳደግ መጠቀም
እንድንችል በሰንበት መግቢያና መውጫ ላይ ትኩረት ማድረግ ይኖርብናል።
ደግሞም የሰንበትን ቀን ስለ ራሳችን ብቻ በማሰብ በራስ ወዳድነት ማክበር የለብንም።
ይልቁንም የሱስ እንዳለው “‘በሰንበት ቀን በጎ ማድረግ ተፈቅዶአል’ ” (ማቴ. 12፡12)።
ብዛት ያላቸው የቤተ ክርስቲያን አባላት ለሌሎች ጥንቃቄ የማድረግ መጠነ ሰፊ
ሥራ ይሠራሉ። ሆኖም ከዚህ በላቀ መሥራት እንዳለብን ብዙዎቻችን ይሰማናል።
እግዚአብሔር ለተጎዱ፣ ለተጨቆኑ ወይም ለተዘነጉ እንደሚጠነቀቅ የምናውቅ
እንደመሆኑ እኛም ይህንኑ ማድረግ ይኖርብናል። በሰንበት መደበኛ ሥራችንን
ከመሥራት ታቅበንና ከሥራ ጫና ነጻ ሆነን፤ ዕለቱን በእውነተኛ መንገድ
ከምናከብርባቸው መንገዶች አንዱ ለሌሎች ያለንን ተቆርቋሪነት በማሳየት ነው።
“በአራተኛው ትእዛዝ እንደቀረበው ሰንበት ከሌሎቹ የሣምንቱ ቀናት ተለይቶ
ለዕረፍትና ለመንፈሳዊ አምልኮ እንዲውል ታስቦ ተሰጥቶአል። ሁሉም ዓለማዊ
ሥራዎች በዕለቱ እንዳይሠሩ ሲከለከሉ--ከጌታ ተግባር ጋር አብረው የሚሄዱት
የምኅረትና የቸርነት ሥራዎች ይኸውም . . . ሥቃይን ማስታገስና ያዘኑትን ማጽናናት-ለእግዚአብሔር ቅዱስ ቀን ክብር የሚሰጥ የፍቅር ሥራ ነው።”—Ellen G. White,
Welfare Ministry, p. 77.
በሰንበት ቀን ለሌሎች ምን ዓይነት መልካም ተግባሮች ያደርጋሉ?
ሰንበት ሥር የሰደደ የእስራኤል ሕዝብ የሕይወት ዑደት አንዱ ክፍል መሆኑን ቀደም
ብለን ተመልክተናል። ሆኖም የሰንበት መርኅ በሣምንት አንድ ቀን ከሚመጣው ዕለት
ጋር ብቻ የተቆራኘ አልነበረም። ይልቁንም በሰባት ዓመት አንዴ የሚመጣውንም
የተለየ ዕረፍት ያካትት የነበረ ሲሆን፤ መደምደሚያው ግን ሰባት ጊዜ ሰባት ተባዝቶ
ከሚገኘው አርባ ዘጠኝ ዓመት በኋላ ያለው 50ኛ ዓመት ወይም የኢዮቤልዩ ዓመት
ነበር።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘሌዋ. 25፡1-7። እንዲህ ዓይነቱን መመሪያ አስደናቂ የሚያደርገው
ምንድን ነው? ይህ ዓይነቱን መርኅ ከህይወትና ከሥራዎ ጋር ማቆራኘት የሚችሉት
እንዴት ነው?
የሰንበት ዓመት የእርሻው መሬት ለአንድ ዓመት ጦም እንዲያድር የሚፈቅድ
ድንጋጌ ነበር። ይህ ዓይነቱ መሬቱን የመመገብ አስደናቂ ተግባር እና የእርሻ ጥበብ
በብዙዎች ዘንድ በስፋት ሲታወቅ ኖሮአል።
ሰባተኛው ዓመት ለባሮችም ቢሆን ታላቅ ትርጉም ነበረው (ዘፀ. 21፡ 1-11)።
ማንኛውም በእዳ ተዘፍቆ ራሱን የሸጠ እስራኤላዊ ሰባተኛው ዓመት ላይ ነጻ ይሆን
ነበር። በተመሳሳይ ከፍተኛ መጠን የነበራቸው ዕዳዎች በሰባተኛው ዓመት መጨረሻ
ይሰረዙ ነበር (ዘዳ. 15፡1-11)።
እስራኤላውያን በምድረ በዳ ጉዞአቸው እግዚአብሔር መና እንዳወረደላቸው ሁሉ፤
አሁንም ምንም ዓይነት ዘር ሳይዘሩና መከር ሳይሰበስቡ ካለፈው ዓመት የተትረፈረፈ
ምርትና በዚህ የሰንበት ዓመት ምድሪቱ በራሷ ባበቀለችው ነገር ላይ ተስፋ በማድረግ፤
እግዚአብሔር በበቂ ሁኔታ ይመግበናል ብለው በእርሱ ላይ ያላቸውን መተማመን
የሚያሳዩበት ወቅት ነበር። በተመሳሳይ ባሮችን አርነት ማውጣትና ዕዳቸውን መሰረዝ
በራሱ የምኅረት ተግባር ቢሆንም፤ በተጨማሪ እግዚአብሔር የሚያስፈልገንን ሁሉ
ያሟላል ብሎ በአምላካዊው ኃይል ላይ እምነት መጣል ነው።
የሰንበት ጽንሰ ሃሳቦችና ንድፎች ከአጠቃላዩ የእስራኤል ማኅበረሰብ መዋቅር ጋር
የቅርብ ትስስር እንዲኖራቸው የተቃኙ ነበሩ። በተመሳሳይ የዛሬው ሰንበት አጠባበቅ
ሌሎቹን ቀኖቻችንን በሙሉ በሚለውጥ መንፈሳዊ ግብረገብነት የተሞላ መሆን
ይጠበቅበታል። ሰንበት በቅድሚያ አምላካዊውን መንግሥት መሻት እንዳለብን
አስመልክቶ የሱስ የሰጠውን መመሪያ በተግባር የምናሳይበት መሣሪያ ነው፡ “‘የሰማዩ
አባታችሁም እነዚህ ሁሉ ለእናንተ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል… እነዚህ ሁሉ
ይጨመሩላችኋል’” (ማቴ. 6፡32-33)።
ሰንበትን መጠበቃችን በሌሎቹ ስድስት የሥራ ቀናት ላይ ምን ዓይነት
ልዩነት ማምጣት ይኖርበታል? ለነገሩ ከእሁድ እስከ አርብ--ስስታም፣
ራስ ወዳድና ለሌሎች ግድ የማይሎት ሆነው ሰንብተው ሲያበቁ፤
በሰንበት ከዚህ በተቃራኒ መሆንዎ ፋይዳው ምንድን ነው?
Read Ellen G. White, “From the Red Sea to Sinai,” pp.
295–297, in Patriarchs and Prophets; “The Sabbath,” pp. 281–289,
in The Desire of Ages; Sigve K. Tonstad, “The Social Conscience of the
Seventh Day,” pp. 125–143, in The Lost Meaning of the Seventh Day.
“በሥቃይ ያሉ ሰዎችን መከራ የማስታገስ ሥራ ከሰንበት ሕግ ጋር በተጓዳኝ
እንደሚሄድ ጠቅሶላቸው ነበር። በሥቃይ ያለውን ሰብዓዊ ፍጡር ለማገልገል ሁሌም
በሰማይና በምድር ከሚመላለሱ መላእክት ሥራ ጋር ለዛ ያለው ውህደት የፈጠረ
ነበር…
“ሰውም እንዲሁ በዚህ ዕለት የሚያከናውነው ተግባር ተሰጥቶታል። በሰንበት
ለህይወት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ሊታዩ፣ የታመሙ ተገቢውን እንክብካቤ ሊቸሩ፣
በድኽነት ያሉ ወገኖችም የጎደላቸው ሊሟላ ይገባል። የተቀደሰው የእግዚአብሔር
የእረፍት ቀን ለሰዎች የተሠራ እንደመሆኑ፤ የምኅረት ሥራ ከእቅዱ ጋር ፍጹም
ስምምነት አለው። በሰንበትም ሆነ በሌላ ቀን ፈውስ ማግኘት በሚችል ህመም
ፍጡራኑ ለአንድ ሰዓት እንኳ ይሠቃዩ ዘንድ አምላካዊው ፈቃድ አይደለም።”—Ellen G. White, The Desire of Ages, pp. 206, 207.
1.ሰንበትን በእግዚአብሔር ላይ ያሎት መታመን ማሳያ አድርገው
የተጠቀሙባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው? በጌታ ላይ ላሳዩት
መታመን በምላሹ እግዚአብሔር መና የመገቦት አጋጣሚዎች አሉ? ካለ
በዚህ ዙሪያ የተማሩትን ለክፍሉ ያካፍሉ።
2.በዘፀ. 20፡8-11 እና ዘዳ. 5፡12-15 በቀረበው አራተኛ ትእዛዝ
እግዚአብሔር የተለያዩ ገጽታዎች ለነበሯቸው ሰንበቶች አጽንኦት ሰጥቶ
ነበር። እርስዎ የተለየ ስፍራ የሚሰጡት አንዱ የሰንበት ገጽታ የትኛው
ነው?
3.የሰንበትን በረከቶችና ጥቅሞች ለማኅበረሰብዎ ማካፈል በሚችሉባቸው
መንገዶች ዙሪያ በግልዎም ሆነ በክፍል ተወያዩ።
4.ሰንበት በሕይወትዎ ለውጥ እንዲመጣ ካደረገባቸው ነገሮች መሃል
አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው? የሰንበት ንድፎችና መርኅዎች መደበኛ
ተጽእኖ ሊያሳርፉባቸው የሚገቡ ሌሎች የህይወትዎ ክፍሎች ይኖሩ
ይሆን?
ማጠቃለያ፡ እግዚአብሔር የፍጥረት ሥራንና መዋጀታችንን
እንድናስታውስ ሰንበትን ቢሰጠንም፤ ሌሎች ብዛት ያላቸው
ተጨባጭ ጥቅሞችም አሉ። ሰንበት በሚያስፈልገን ሁሉ
በአምላካዊው ቸርነት ላይ እንድንታመን ያስተምረናል።
እኩልነትን
እንድንለማመድ
በማስተማር--መላውን
ግንኙነታችንን መለወጥ የሚችል መንፈሳዊ ግብረገብ መሆንም
ይችላል። የሱስ በሽተኛውን በመፈወስ ሰንበት በዕጦት ያሉ ሁሉ
የሚያተርፉበት ዕለት መሆኑን አሳየ።