የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ኢሳይያስ፡ “ሕዝቤን አጽናኑ”


1ኛ ሩብ ዓመት 2021

ከታህሳስ 24- 30

2ኛ ትምህርት

Jan 02 - Jan 08




የአመራር ቀውስ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ኢሳ. 6:1–4፣ ኢሳ. 6:5–7፣ ኢሳ. 6:8፣ ኢሳ. 6:9–13።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡- “ንጉሥ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን ከፍ ባለና በከበረ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት፤ የልብሱም ዘርፍ ቤተ መቅደሱን ሞልቶት ነበር።” (ኢሳ. 6፡1)።

መ ልካም አስተዳደር ማካተት ስለሚገባው መሰረታዊ ነገሮች ኮንፊሸስ ተጠይቆ እንደሚከተለው መልሶ ነበር፡ “ ‘በቂ ምግብ፣ በቂ የጦር መሣሪያ እና የተራው ሕዝብ በራስ መተማመን።’ “‘ነገር ግን’ አለ ደቀ መዝሙሩ ሲጠይቀው ‘ምናልባት ከእነዚህ ከሦስቱ አንዱን ከመተው ውጪ ሌላ ምንም አማራጭ ባይኖርህ የትኛውን ትተዋለህ?’ “‘የጦር መሣሪያ’ ሲል መለሰ ኮንፊሸስ።

“‘ደቀ መዝሙሩ መጠየቁን አላቆመም፡ ‘ምናልባት ከተቀሩት ሁለቱ አንዱን ለመተው ብትገደድስ?’ “ኮንፊሸስ እንዲህ አለ፡ ‘ምግብ። ከጥንት ጀምሮ ረሀብ የሁሉም ሰው ዕጣ ፈንታ ሆኖ ኖሮአል፤ በሚመራው አካል ላይ መተማመን የሌለው ሕዝብ ግን በእርግጥ የጠፋ ነው’ ”—Edited by Michael P. Green, 1500 Illustrations for Biblical Preaching (Grand Rapids, Mich.: Baker Books, 1989), p. 215. በእርግጥ ሰዎች ጠንካራና ተአማኒነት ያለው አመራር ይፈልጋሉ። አንድ ወታደር ለሁለተኛ ጊዜ ግዳጅ ለመሄድ ቅጽ ሲሞላ የተመለከተው የሠራዊቱ ምልመላ ክፍል ኃላፊ ለምን ይህን እንደሚያደርግ ቢጠይቀው፡ “የሲቪል ህይወትን ሞከርኩ፤ ነገር ግን ይሄ ነው የሚባል ቆፍጣና አመራር ማግኘት አልቻልኩም” ሲል መለሰለት ይባላል። በዚህ ሣምንት ጥናታችን በይሁዳ የተከሰተውን የአመራር ቀውስ እና መዘዙን እንመለከታለን።

ታህሳስ 25
Jan 03

ንጉሡ ሞቷል። ንጉሥ ለዘላለም ይኑር!


ኢሳ. ምዕ. 2 ስለ ንጉሥ ዖዝያን ሞት ይናገራል። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 2ዜና ምዕ. 26። የንጉሥ ዖዝያን ሞት አንደምታው ምንድን ነው? የንጉሡን ሞት አስመልክቶ የተለያዩ አመለካከቶች ሊንጸባረቁ ይችላሉ። 1. ምንም እንኳ የዖዝያን ንግሥና ዘመን ረጅምና በብልጽግና የታጀበ ቢሆንም “ዖዝያን ከበረታ በኋላ ግን ዕብሪቱ ለውድቀት ዳረገው” (2ዜና 26፡16) የውድቀቱ መንስኤ በዕጣን መሰዊያው ላይ ዕጣን ለማጠን መሞከሩ ነበር። ለእግዚአብሔር ካህናት እንዲሆኑ ከተገባቸው የአሮን ዘሮች ውጪ እርሱ ይህን የማድረግ ሥልጣን እንደ ሌለው ካህናቱ ሲነግሩት (2ዜና 26፡18) እርሱ ግን በጣም ተቆጣ። የቀረበለትን ግሳጼ ለመቀበል የተቃወመውን ይህን ንጉሥ ወዲያውኑ ጌታ በለምጽ መታው። “ንጉሥ ዖዝያን እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ለምጻም ነበረ። ለምጻም በመሆኑም ከቤተ መቅደስ ተወግዶ ነበርና በተለየ ቤት ተቀመጠ።” (2ዜና 26፡21)። ይህ በለምጽ ምክንያት ንጽህና የጎደለው ሰብዓዊ ንጉሥ በሞተ በዚያው ዓመት ኢሳይያስ--ሕያው እና መለኮታዊ የሆነውን ንጉሥ በቤቱ (በቤተ መቅደሱ) በራእይ መመልከቱ በእርግጥም ምጸታዊ ነው!

2. በዖዝያን እና በኢሳይያስ መካከል ደማቅ ልዩነት አለ። ዖዝያን በተሳሳተ አመክንዮ (በትዕቢት) እና ግብዝ አስተሳሰብ ራሱን ቅዱስ ለማድረግ የሄደበት መንገድ-ኃይማኖታዊው ሥርዓት ጭራሽ እርኩስ አድርጎ እንዲቆጥረው እና ከቅድስና ጋር ፍጹም እንዲቆራረጥ አደረገው። በሌላ በኩል ኢሳይያስ አምላካዊው ቅድስና ወደ እርሱ ይደርስ ዘንድ ፈቀደ። ደካማነቱን በትህትና በመቀበል ግብረገባዊውን ልዕልና ናፈቀ፤ አገኘም (ኢሳ. 6፡5-7)። የሱስ በተናገረው ተምሳሌታዊ ታሪክ ቀረጥ ሰብሳቢው በእግዚአብሔር ፊት እንደ ጻድቅ ተቆጥሮ ወደ ቤቱ እንደ ተመለሰ፤ እርሱም እንዲሁ ሆነለት “ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይላልና፤ ራሱን ዝቅ ዝቅ የሚያደርግ ግን ከፍ ይላል” (ሉቃ. 18፡14)።

3. ለምጽ በወጣበት የዖዝያን አካል እና በሕዝቡ ግብረገባዊ ሁናቴ መሃል አስገራሚ መመሳሰል ነበረ፡ “…ከእግር ጥፍራችሁ እስከ ራስ ጠጉራችሁ ጤና የላችሁም ቁስልና ዕባጭ እንዲሁም እዥ ብቻ ነው” (ኢሳ. 1፡6)።

4. ከክርስቶስ ልደት በፊት 740 ላይ የተከሰተው የዖዝያን ሞት በእግዚአብሔር ሕዝቦች አመራር ኃላፊነት ላይ ብርቱ ቀውስ አስከተለ። ማንኛውም ፍጹም የበላይ ሆኖ ሲያስተዳድር የኖረ ገዥ ሲሞት በሥልጣን ሽግግር ወቅት አገሪቱ አደጋ ላይ ልትወድቅ የምትችልበት ዕድል ሰፊ ነው። ከጥቂት ዓመታት ቀደም ብሎ ማለትም ከክ.ል.በ. 745 ላይ የአሦሩ ቴልጌልቴልፌልሶር 3ኛ ወደ ዙፋን እንደ መጣ አገሩን በጦር ኃይል የማይበገርና ልዕለ ኃያል በማድረግ፤ የጦርነትና ጠብአጫሪነት ነጋሪት መጎሰሙ የቅርብ ምስራቅ አገራት ሉዓላዊ ህልውና ላይ ስጋት አስከተለ። በዚህም ይሁዳ የተለየ አደጋ ያንዣበበባት አገር ሆነች። ሆኖም በዚህ የቀውስ ወቅት ሁሉም ነገር እንደ ቀድሞው በእርሱ ቁጥጥር ስር መሆኑን በማሳየት እግዚአብሔር ኢሳይያስን አበረታታው።

ጥቅሶቹን በጥንቃቄ ያንብቡ፡ 2ዜና 26፡16። እኛ እያንዳንዳችን ራሳችንን በተመሳሳይ ሁናቴ ውስጥ ልናገኝ የምንችልበት ዕድል ሊኖር የሚችለው እንዴት ነው? በመስቀሉ መኖራችን ከእንዲህ ያለው ወጥመድ እንዴት ሊጠብቀን ይችላል?

ታህሳስ 26
Jan 04

“ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ” (ኢሳ. 6፡1-4)


በኢሳ. ምዕ. 6 የመጀመሪያዎቹ አራት ቁጥሮች እየሆነ የነበረውን ነገር በጥንቃቄ ለመመልከት ይሞክሩ። ንጉሡ የሞተው የፖለቲካው ትኩሳት እያጋመ መጥቶ ይሁዳን የሚወጉ ኃይላት የሚወጡበት ጊዜ የተቃረበበት አካባቢ መሆኑን ልብ ይሏል (ሦርያውያን የጦርነት ነጋሪት እየጎሰሙ ለውጊያ እየወጡ ነበር)። ወቅቱ ድል አድርጎ የሚቆጣጠረው ማን ሊሆን እንደሚችል እርግጠኛ ላልነበረው ኢሳይያስ አስፈሪ ሳይሆን እንዳልቀረ ይገመታል።

ከዚያስ--ምን ተከሰተ? በራእይ የተወሰደው ኢሳይያስ በአንጸባራቂ ክብር ከፍ ባለ ዙፋኑ የተቀመጠውን እግዚአብሔር ተመለከተ። በብርሃን የተሞሉ ሱራፌል “ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ” እያሉ ከፍ ባለ ድምጽ ከሚያቀርቡት ሕብረ ዝማሬ የተነሣ የመድረኩ መሰረት ሲናወጥና ቤተ መቅደሱም በጢስ ሲሞላ አየ። ነቢዩ ሰማይ ምድሩን የሚያዞር ድንቅ ውበት እንደ ተመለከተ ለመገመት አይከብድም። ከውጪያዊ ክስተቶች በተቃራኒ--ኢሳይያስ ልዕለ ኃያሉ ማን እንደ ሆነ አሁን በእርግጠኝነት አውቋል። በራእዩ ጌታ የቀረበው በየትኛው ስፍራ ነው? (ኢሳ. 6:1 ይመልከቱ)። ጌታ ከሌላ ስፍራ ይልቅ ራሱን በዚህ ስፍራ ለኢሳይያስ ለምን ገለጠ? ዘፀ. 25:8፣ ዘፀ. 40:34–38።



ሕዝቅኤል፣ ዳንኤል እና ዮሐንስ--አምላካዊውን ራእይ የተቀበሉት በግዞት በነበሩበት ወቅት ነበር (ሕዝ. 1፣ ዳን. 7፡9-10፣ ራእ. 4-5)። ዙሪያ ገባው ቢጨልምባቸውም፤ ሁሉም ነገር በእግዚአብሔር ቁጥጥር ሥር መሆኑን የሚያመላክት በዓይነቱ ለየት ያለ መጽናናት እና መበረታታት አስፈልጓቸው ነበር--እንደ ኢሳይያስ። (ዳንኤል እና ሕዝቅኤል በምድራቸው ላይ ውድመት ባደረሱ ወራሪ ባዕዳን ግዞት ስር ወድቀው የነበረ ሲሆን፤ ዮሐንስ ደግሞ በጥላቻ የተሞላ ፖለቲካዊ ኃይል--ሰው በማይኖርበት ደሴት በግዞት ወርውሮት ነበር።) አስከፊ ቀውስ በተከሰቱባቸው ወቅቶች፤ እነዚህ ራእዮች በታማኝነት እንዲዘልቁ የረዷቸውን ነገሮች በመስጠት ድጋፍ እንደሆኗቸው ለመገመት አይከብድም።

“ኢሳይያስ ከፍ ባለ ክብር የተሞላውን ንጉሥ በዙፋኑ ሲመለከት፤ ከአምላካዊው ንጽህና እና ቅድስና የተነሳ ስሜቱ ክፉኛ ተነካ። በፈጠረው አምላክ ወደር የለሽ ፍጽምና እና ራሱን ጨምሮ የኃጢአት አቅጣጫ ተከትለው በሚጓዙ ከረጅም ዘመን አንስቶ በተመረጡ የእስራኤልና የይሁዳ ህዝቦች መሃል ያለው ልዩነት እንዴት ሰፊ ነው!”—Ellen G. White, Prophets and Kings, p. 307. በኢሳይያስ ራእይ አጽንኦት የተሰጠው ከተለመደው ባሻገር የሚገኝ አምላካዊ ቅድስና የመልእክቱ መሰረታዊ ክፍል ነው። ቅዱስ የሆነው እና ሕዝቡም ቅዱስ እንዲሆን የሚጠይቀው ይህ አምላክ--ሕዝቡ ከክፉ መንገዱ ከተመለሰ፣ ንስሐ ከገባና በእምነት እና በመታዘዝ ራሱን ካስረከበ ብቻ ይህን ቅድስና ይሰጠዋል።

እኛ ሁላችን--ውጪያዊው ሁኔታችን መጥፋታችንን በሚያሳይ መልኩ ተስፋ አስቆራጭ ሁናቴ ውስጥ የምንገኝ ሕዝቦች ሆነናል። ምናልባት እርስዎ እንደ ኢሳይያስ “የእግዚአብሔርን ክብር” በራእይ ባይመለከቱም፤ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ጌታ እርስዎን እና እምነትዎን ጠብቆ ማቆየቱን ደግመው ደጋግመው ይንገሩ። ለሌሎች ሊያጋሩ ከሚችሏቸው ከእነዚህ ተሞክሮዎች ምን ተማሩ?

ታህሳስ 27
Jan 05

አዲስ ስብዕና (ኢሳ. 6፡5-7)


በስርየት ቀን የእግዚአብሔር ማደሪያ ወደ ሆነው ቅድስተ ቅዱሳን መቅረብ ይችል የነበረው ሊቀ ካህናቱ ብቻ ሲሆን፤ እርሱም ቢሆን በምስክሩ ላይ ካለው የስርየት መክደኛ ማለትም ከእግዚአብሔር ፊት በዕጣኑ ጢስ መሸፈን ነበረበት፤ ያለበዚያ ግን ይሞታል (ዘሌዋ. 16፡2፣12-13)። ኢሳይያስ ግን ሊቀ ካህናት ሳይሆን እና በዕጣኑ ጢስ ሳይሸፈን እነሆ እግዚአብሔርን ተመለከተ! የቤተ መቅደሱ በጢስ መሞላት (ዘሌዋ. 16፡2) በስርየት ቀን የእግዚአብሔር ክብር የሚገለጥበትን ደመና ያስታውሰናል (ዘሌዋ. 16፡2)። እጅግ መሳጭ ሁኔታ ውስጥ የወደቀውው የእርሱ ነገር፤ እስከ ወዲያኛው እንዳበቃለት ያሰበው ኢሳይያስ (ያስተያዩ፡ ዘፀ. 33:20፣ መሳፍ. 6:22-23) በስርየት ቀን ሊቀ ካህናቱ የሚያሰማውን የኃጢአት ኑዛዜ አስታውሶ (ዘሌዋ. 16፡21)፣ የእርሱን እና የሕዝቡን ኃጢአተኝነት አምኖ በመቀበል ጮኸ (ኢሳ. 6፡5)።

“በፍጹም ብርሃን የተሞላውን መለኮታዊ መገኘት በቤተ መቅደሱ ውስጠኛው ክፍል የተመለከተው ኢሳይያስ፤ ከነጉድለቱና የብቃት ማነሱ የሚተው ከሆነ፤ የተጠራበትን ተልዕኮ ፈጽሞ ከዳር ማድረስ እንደማይችል ተገነዘበ።”—Ellen G. White, Prophets and Kings, p. 308. ከሱራፌል አንዱ የኢሳይያስን ከንፈሮች ለማንጻት እየነደደ የነበረውን የእሳት ፍም ለምን ተጠቀመ? ኢሳ. 6፡6-7



የነቢዩ ከንፈሮች በመነካታቸው በደሉ እንደ ተወገደ ኃጢአቱም እንደ ተሰረየለት ሱራፌል ይገልጻል (ኢሳ. 6፡7)። የኃጢአቱ ዓይነት ተለይቶ ባይቀርብም፤ ከአንደበቱ በወጡ ከንቱ ንግግሮች ብቻ አለመወሰኑ ግን እሙን ነው። ለዚህ ምክንያቱ ከናፍር ንግግርን ብቻ ሳይሆን አጠቃላዩን የቃላቶቹን ባለቤት ስብዕና ማመላከታቸው ነው። ግብረገባዊውን ትብስህት የተቀበለው ኢሳይያስ አሁን በፍጹም ንጽህና የተሞላውን ምስጋና ለእግዚአብሔር ማቅረብ ቻለ።

እሳት ማንኛውንም ጉድፍ የማቃጠልና የማጥራት (የማንጻት) ባህሪ አለው (ዘኁ. 31፡ 23)። ነገር ግን ሱራፌል የተጠቀመው ከመሠዊያው ላይ የወሰደውን ቅዱስ የእሳት ፍም ሲሆን፤ ይኸውም በራሱ በእግዚአብሔር የተለኮሰና ምን ጊዜም የሚነድ ነበር (ዘሌዋ. 6፡12)። ይህን ተከትሎ ሱራፌል ኢሳይያስን ቅዱስ ብሎም ንጹህ አደረገው። ሌላም ተጨማሪ ነገር አለ። በቤተ መቅደስ ይካሄድ በነበረው አምልኮ ከመሠዊያው ፍም የሚወሰድበት ዋንኛ ምክንያት ዕጣን ለማጨስ ነበር። ሊቀ ካህናቱ ከመሠዊያው ላይ የሚወስደውን ፍም ጥናውን ሞልቶ ዕጣን ለማጨስ ይጠቀምበታል።

ይህን የሚገልጹትን እነዚህን ጥቅሶች ያስተያዩ፡ ዘሌዋ. 16፡12-13። ነገር ግን በኢሳ. 6 እንደ ቀረበው ሱራፌል ፍሙን ወስዶ በጥናው ላይ በማኖር ፋንታ የኢሳይያስን አፍ ሲነካበት ይስተዋላል። ዖዝያን ዕጣን ለማጠን ፈለገ፤ ኢሳይያስ ግን ራሱ እንደ ዕጣን ሆነ! ቅዱስ የሆነው እሳት ዕጣኑን በማቃጠል የእግዚአብሔር ቤት በመልካም መዓዛ እንዲሞላ ያደርግ እንደነበር ሁሉ፤ ነቢዩም ቅዱስ የሆነውን መልእክት ለሌሎች ያሰራጭ ዘንድ በዚሁ ፍም ተለኮሰ። በኢሳ. ምዕ. 6 ቀጣይ ቁጥሮች (ኢሳ. 6፡8 እና ቀጥሎ…) እግዚአብሔር ኢሳይያስን ወደ ሕዝቡ ሲልከው መመልከታችን አጋጣሚያዊ ክስተት አይደለም።

ኢሳይያስ እግዚአብሔርን ለተመለከተበት ራእይ የሰጠውን ምላሽ (ኢሳ. 6፡5) በጸሎት መንፈስ ያንብቡ። “‘ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ’” በሆነው አምላክ ተፈጥረው በዩኒቨርስ ውስጥ የሚኖሩ ኃጢአተኛ ሰዎችን ችግር መሰረታዊ መገለጫ በዚህ ውስጥ የምንመለከትበት ሁኔታ ምን ይመስላል? (ኢሳ. 6፡3) የክርስቶስ በመስቀል ላይ መዋል ብቸኛው የዚህ ችግር መልስ መሆን የቻለው ለምንድን ነው?

ታህሳስ 28
Jan 06

ታላቁ ንጉሣዊው ተልዕኮ (ኢሳ. 6፡8)


“ከዚያም የጌታ ድምፅ፤ ‘ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል?’ ሲል ሰማሁት። እኔም፣ ‘እነሆኝ እኔን ላከኝ’ አልሁ።” (ኢሳ. 6፡8)። መንጻት ያገኘው ኢሳይያስ እርሱን ወክሎ ለመሄድ ያለውን ቁርጠኝነት በመግለጽ ወዲያውኑ ለእግዚአብሔር ጥሪ ምላሽ ሰጠ። ኢሳይያስ በአዲስ ኪዳን ቢሆን ኖሮ ሐዋርያ ማለትም “የተላከ” የሚል መጠሪያ ሊኖረው በቻለ ነበር። የኢሳይያስ መጽሐፍ እንደ ሌሎች የነቢያት መጻሕፍት የነቢይነት ጥሪውን በመግለጽ አለመጀመሩ ልዩና አስገራሚ ያደርገዋል (ያስተያዩ፡ ኤር. 1:4–10፣ ሕዝ 1–3)።

በሌላ አነጋገር ከምዕ. 6 ክስተቶች አስቀድሞ የነብይነት ጥሪ ሳይደርሰው እንዳልቀረ ይታመናል። አገልግሎት ከተጀመረ በኋላም እንኳ የሚገለጥ መለኮታዊ መስተጋብር ለነብዩ ከፍተኛ መበረታታት እንደሚሰጥ መጽሐፍ ቅዱስ ያሳየናል (ሙሴ፡ ዘፀ. 34፣ ኤልያስ: 1ነገሥ. 19)። እንዲሁም ከሌሎች ምሳሌዎች በተለየ ነቢይ እንደሚሆኑ በእግዚአብሔር ሲነገራቸውና--በኢሳ. 6 እንደ ቀረበው ነቢዩ ልዩ የሆነውን ተልዕኮ ለመቀበል ፈቃደኛ ሲሆን እንመለከታለን። ኢሳይያስ ጥሪው በመጀመሪያ ሲቀርብለት በኢሳ. ምዕ. 1-5 በሁኔታዎች የሚወሰኑ ጉዳዮች መኖራቸውን እንመለከታለን። ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር በቤተ መቅደስ በሰጠው ማደፋፈር እና እርሱን የአምላካዊው ትንቢት ቃል አቀባይ አድርጎ ለመሾሙ ማረጋገጫ በመስጠት ተልዕኮውን እንዲጀምር ይሆናል።

እግዚአብሔር በቤተ መቅደሱ ኢሳይያስን አበረታታው። አምላካዊው ቤተ መቅደስ የማበረታቻ ስፍራ መሆኑን የሚገልጽ ሌላ ማስረጃ ማግኘት እንችላለን? መዝ. 73 (መዝ. 73:17)፣ ዕብ. 4:14–16፣ ዕብ. 10:19–23፣ ራእ 5። ጥቅሶቹ ምን ይነግሩናል?



ቤተ መቅደሱ የአስገራሚው አምላካዊ ኃይል ትርታ ብቻ ሳይሆን፤ የእንደኛ ዓይነቱ ደካማ እና እንከን የማያጣው ሕዝብ መማጸኛ ስፍራም ነው። እግዚአብሔር በሊቀ ካህናችን ክርስቶስ አማካይነት ለእኛ እየሠራ መሆኑን ማወቃችን ከጭንቀት ነጻ ሊያደርገንና ሰላም ሊሰጠን ይችላል። ስለ እኛ የሚታየውን የታረደ የመሥዋዕት በግ ክርስቶስ፤ ዮሐንስም እንዲሁ ተመልክቶታል (ራእ. 5፡6)። በእርግጥ ይህ ትዕይንት ዐይን የሚስብ ዓይነት አልነበረም። ምንም እንኳ ክርስቶስ ከሞት የተነሳና ወደ ሰማይ ያረገ ቢሆንም፤ የመስቀሉን ጉዳይ ግን ሁሌም እንደ ተሸከመ እንደሚኖር መግለጫው ያመለክታል።

ሰውን ሁሉ ወደ መሥዋዕቱ ይስብ ዘንድ እነሆ ዛሬም ከፍ ከፍ ብሎ ይገኛል። በእምነት፣ በጸሎት--ወደ አምላካዊው ሰማያዊ መቅደስ ገብተው መበረታታት ማግኘት የቻሉት እንዴት ነው? “ምሕረትን እንድንቀበልና በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ” ሲል ዕብ. 4፡16 ግብዣ ያቀርብሎታል። አምላካዊው ጸጋና ምህረት ባስፈለገዎት ጊዜ እንዴት ማግኘት እንደሚችሉ ቢጠየቁ መልስዎ ምን ይሆናል?

ታህሳስ 29
Jan 07

አስፈሪ ጥሪ (ኢሳ. 6፡9-13)


እግዚአብሔር ለኢሳይያስ በሰጠው ተልዕኮ እንዲህ ዓይነቱን ዕንግዳ መልእክት ወደ ሕዝቡ እንዲያደርስ ለምን ፈለገ (ኢሳ. 6:9, 10)? የሱስ ለምን በምሳሌ እንደሚያስተምር ሲያብራራ ከላይ የቀረበውን ጥቅስ ተጠቅሞ እንደ ነበር ልብ ይሏል (ማቴ. 13፡13-15)። ኢሳይያስ ወደ ይሁዳ ሕዝብ፣ የሱስ ደግሞ ወደ ዓለም የተላከበት መንገድ ማንም ይጠፋ ዘንድ አምላካዊው ፍላጎት አለመሆኑን (2ጴጥ. 3፡9) ጥሩ አድርጎ ይገልጻል።

የእግዚአብሔር ምኞት ሰብዓዊውን ፍጡር ለማጥፋት ሳይሆን ለዘላለም ለማኖር ነው። ነገር ግን አንዳንዶች ለጥሪው አዎንታዊ ምላሽ ሲሰጡ ሌሎች በተቃውሞ ይጸናሉ። ይህም ቢሆን ለጥሪው ምላሽ በመስጠት ወደ ንስሐ የሚያመጧቸውን የላቁ በሮች እና ዕድሎች መክፈቱን ይቀጥላል። ሆኖም ሰዎች ለአምላካዊው ጥሪ አብልጠው ጆሮአቸውን በደፈኑ ቁጥር ልባቸው እየደነደነ ይሄዳል። በዚህ ሁኔታ እግዚአብሔር ልባቸውን ቢያለሳልስ እያለ ለእነርሱ የሚያደርጋቸው ነገሮች፤ ልባቸውን ከማደንደን ያለፈ ፋይዳ ወደማይኖረው ደረጃ መሸጋገር ይጀምራሉ። እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ፍቅር አይለወጥም። ለዚህ አምላክ ፍቅር የምንሰጠው ግላዊ ምላሽ በእጅጉ ወሳኝ ነው።

የሙሴ፣ ኢሳይያስ፣ ሕዝቅኤል ወይም ራሱ የክርስቶስ ዓይነቱ የአገልጋይነት ሚና-ሰዎች መልእክቱን ቢቃወሙ እንኳ ጥሪ እና ተማጽኖ ማቅረብ ነው። እግዚአብሔር ሕዝቅኤልን እንዲህ ብሎት ነበር፡ “እነርሱ ዐመፀኛ ቤት ስለ ሆኑ፤ ቢሰሙም ባይሱም በመካከላቸው ነቢይ እንደ ነበር ያውቃሉ” (ሕዝ. 2፡5)። የሕዝቡ የመጨረሻ ምርጫ በጥፋትና ግዞት ሊያከትም ቢችል እንኳ (ኢሳ. 6፡11-13) የእግዚአብሔር እና አገልጋዮቹ ሚና በቂ ማስጠንቀቂያ እንዲያገኙ ማድረግና (ሕዝ. 3፡16-21) ሚዛናዊ ምርጫ መስጠት ነው።

ይህን ጽንሰ ሀሳብ በአእምሮአችን እንደ ያዝን፤ የፈርዖንን ልብ በማደንደን እግዚአብሔር የነበረውን ሚና መረዳት የምንችለው እንዴት ነው? በዘፀ. 4፡21 “ ‘እኔ ግን… ልቡን አደነድነዋለሁ።’ ” በማለት እግዚአብሔር ይናገራል። እግዚአብሔር የፈርዖንን ልብ እንደሚያደነድን ዘጠኝ ጊዜ ከተናገረው መሃል ይህ የመጀመሪያው ነው። በመሆኑም ፈርዖን ዘጠኝ ጊዜ ልቡን እንዳደነደነ በቀረቡት ጥቅሶች እንመለከታለን፡ (ለአብነት ያህል የሚከተሉትን ይመልከቱ፡ ዘፀ. 8:15፣ 32፣ ዘፀ. 9:34)።

እዚህ ላይ ፈርዖን የገዛ ራሱን ምርጫ ማድረጉን በግልጽ መመልከት እንችላለን። ይህ ባይሆንማ የገዛ ልቡን ማደንደን ባልቻለ ነበር። እግዚአብሔርም እንዲሁ የፈርዖንን ልብ ያደነደነበት ምክንያት እውነታው--ፈርዖን እግዚአብሔር የሰጠውን ምልክቶች በመቃወም ያደረገውን የገዛ ምርጫውን ተንተርሰው በተከሰቱ ሁናቴዎች ላይ የፈጠረለት መነሳሳት እንደ ነበር ያሳየናል። ፈርዖን ለእነዚህ ምልክቶች ራሱን ክፍት ቢያደርግ ኖሮ ልቡ በመደንደን ፋንታ በምልክቶቹ በተለሳለሰ ነበር።

እርስዎ ከጌታ ጋር ባለዎት የግል ተሞክሮ ልብዎ ለመንፈስ ቅዱስ ጥሪ የመደንደን ዓይነት ስሜት ተሰምቶት ያውቃል? ይህ እንዲሆን ያደረገው መንስኤ ምን ነበር? የጽንሰ ሀሳቡን ምንነት ማግኘት ካልቻሉ ጉዳዩ አስፈሪ ሊሆን ስለሚችል፤ አሁን ላይ እንዴት ይመለከቱታል? ከዚህ ዓይነቱ ሁናቴ ማምለጫ መንገዱስ ምንድን ነው? (1ቆሮ. 10፡ 13)።

ታህሳስ 30
Jan 08


ተጨማሪ ጥናት


“የረከሱ ተግባራት በሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች የተለመዱ ከመሆናቸው የተነሳ፤ ለእግዚአብሔር በታማንነት የዘለቁ ጥቂቶች በተደጋጋሚ ልባቸው እንዲዝልና በተስፋ አስቆራጭ ሁናቴ ውስጥ እንዲወድቁ ሆነው ተፈትነዋል። እግዚአብሔር ለእስራኤል የነበረው ዓላማ ውድቀት ደርሶበት አመጸኛው ሕዝብ የሶዶምና ጎሞራ ተመሳሳይ ውድመት ተጋሪ እንዲሆን ተፈልጎ ነበር። “በዖዝያን የንግሥና ዘመን የመጨረሻ ዓመት ላይ ኢሳይያስ የእግዚአብሔርን ማስጠንቀቂያ እና ግሳጼ መልእክት ለይሁዳ እንዲያደርስ ተጠርቶ የነበረ ቢሆንም እርሱ ግን ከኃላፊነቱ ሸርተት ያለበት እንዲህ ዓይነቱ ሁናቴ መግጠሙ ብዙ አይገርምም።

ኢሳይያስ ግትር ተቃውሞ ሊገጥመው እንደሚችል ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። በመሆኑም ሁኔታውን ለመጋፈጥ የሚያስችለውን የገዛ ራሱን የብቃት ጉድለት እና ሊሠራለት ያለውን ሕዝብ ግትርነትና አለማመን ሲገነዘብ፤ ሥራው ተስፋ አስቆራጭ ሆኖ ታየው። በተስፋ መቁረጥ ስሜት ወድቆና ከተልዕኮው ተገትቶ ይሁዳን ለጣዖቶቿ ይተዋት? የነነዌ አማልክትስ በሰማይ አምላክ ላይ ባላቸው እምቢተኝነት ምድርን መግዛት ነበረባቸው?”—Ellen G. White, Prophets and Kings, pp. 306, 307.


የመወያያ ጥያቄዎች



1. አንድ ተጠራጣሪ ወይም እምነት የለሽ ሰው “ሁሉም ነገር በሚያመልኩት አምላክዎ ቁጥጥር ስር መሆኑን እንዴት ማሳየት ይችላሉ?” ብሎ ቢጠይቆት መልስዎ ምን ይሆናል?

2. ሁሉም ነገር በእግዚአብሔር ቁጥጥር ስር ከሆነ ንጹሃን ለምን ይሰቃያሉ? በኢሳ. 1፡19-20 የቀረበው መልእክት፤ በዚህ ህይወት የእግዚአብሔር ታማኝ ሕዝቦች መልካም ነገሮች ይገጥሟቸዋል። መጥፎ ነገር የሚገጥማቸው መጥፎዎቹ ሕዝቦችን ብቻ ነው--የሚል አንደምታ አለው? ኢዮ. 1-2፣ መዝ. 37፣ መዝ. 73። ስለ እግዚአብሔር ባህሪ ያለንን አረዳድ በሰዎች ላይ ሊደርስ ከሚችሉ መጥፎ ክስተቶች ጋር ማስታረቅ እንችላለን? ያን ማድረግ ይኖርብን ይሆን?

3. ኢሳ. 6 ከስርየት ቀን ጋር ሰፊ ትስስር የኖረው ለምንድን ነው? ይህ ዓመታዊ የፍርድ ቀን እግዚአብሔር ታማኞችን (ዘሌዋ. 16፡30) ከኃጢአት አጥቦ ያነጻ የነበረበት እና ታማኝ ያልሆኑት (ዘሌዋ. 23፡2930) ተለይተው የሚጠፉበትን እውነታ (ማስተዋል ተገቢ ይሆናል። ማጠቃለያ፡ የማያስተማምን የሰላም ሁናቴ በሰፈነበትና በሰብዓዊው የአመራር ክህሎት ላይ ውድቀት በገሃድ በታየበት በዚያ ዘመን፤ የዩኒቨርስን ሉዐላዊ መሪ ገልጦ የሚያሳይ ታላቅ ራእይ ለኢሳይያስ ተሰጠው። በብቃት ጉድለቱ ሀሳብ ገብቶት የነበረው፤ ነገር ግን በአምላካዊው ምህረት የነጻውና በኃይል የተሞላው ኢሳይያስ--የእግዚአብሔር አምባሳደር ሆኖ በጥላቻ ወደ ተሞላው ዓለም ለመገስገስ ዝግጁ ሆነ!