የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ኢሳ. 7:1–9፣ ኢሳ. 7:10–13፣ ኢሳ. 7:14።
የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡- “‘እንግዲህ በእምነታችሁ ካልጸናችሁ፣ ፈጽሞ መቆም አትችሉም’ ”(ኢሳ. 7:9)።
ኮ
ኒ እና ሮይ በአንድ ሰንበት ዕለት ከቤተ ክርስቲያን መልስ በግቢያቸው
የመኪና ማቆሚያ ሊደርሱ ጥቂት ሲቀራቸው፤ አንድ የበረገገች ዶሮ በፍጥነት
መንገዳቸውን አቋርጣ ስታልፍ ተመለከቱ። የሆነ ችግር ሳይፈጠር እንዳልቀረ ገመቱ።
ይህች ዶሮ ከማንኛውም ክፉ ነገር አስተማማኝ ከለላ እንድታገኝ ተብሎ ከተሠራው
የዶሮ ቤት አምልጣለች። በወቅቱ አንድ አሳዛኝ ክስተት በሂደት ላይ እንደ ነበር
ለመገመት አስቸጋሪ አልነበረም። የዶሮ ቤቱን ነድሎ ዶሮዋ እንድታመልጥ ያደረገው
በመጠን አነስ ያለው የጎረቤት ውሻ ነበር።
ከኮኒ እና ሮይ መኖሪያ ቤት አካባቢ
ወደሚገኝ መለስተኛ ሀይቅ ያመራው ይኸው ውሻ፤ ሌላዋን ዲይዚ የተባለች ዶሮ
በጥርሶቹ መሃል ነክሶ እንደ ያዘ ነው። ዴይዚ ነጭ ላባ ያላት ውብ እንቁላል ጣይ ዶሮ
ነበረች። ኮኒ ተሯሩጣ ዲይዚን ከውሻው አፍ ብታስጥላትም፤ በጣም ዘግይታ ነበር።
አንገቷን የተጨመቀችው ይህች ተወዳጅ ለማዳ ዶሮ ብዙም ሳትቆይ በኮኒ እጆች ላይ
ክምብል አለች። በግቢዋ አንድ ጥጋት ቁጭ ብላ የሞተችውን ዶሮ የታቀፈችው ኮኒ፤
እንባዋ በጉንጮቿ ኩልል ብሎ ሲወርድ ተሰማት።
ዋድሌስዎርዝ የሚባል አንድ ሌላ ዳክዬ በጣም ተረብሾአል። እጇ ላይ የሞተችውን
ዴይዚ እንደ ታቀፈች ኮኒን የተመለከተው ይህ እንደ ወተት የነጣ ዳክዬ፤ ኮኒ ዲይዚን
ገድላታለች ብሎ ደምድሟል። በዚህ የተነሳ ለቀጣዮቹ ጥቂት ሣምንታት--ዳክዬው
ዋድሌስዎርዝ ኮኒን ባያት ቁጥር በዚያ ጠንካራ መንቁሩ እየተከታተለ ይወቅራት
ጀመር። አንዳንዴ ወዳጅን ከጠላት ለይቶ መገንዘብ አዳጋች ሊሆን ይችላል።
በዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ተመሳሳይ ችግር የነበረውን የይሁዳ
ንጉሥ በመመልከት የተሳሳቱ ምርጫዎች ያደረገባቸውን ምክንያቶች ለመረዳት
ጥረት እናደርጋለን።
አካዝ ገና ወደ ንግሥና በመጣበት ለጋ ዘመኑ የገጠመው አስፈሪ ቀውስ ምን ነበር? 2ነገሥ. 15:37-38፣ 2ነገሥ. 16:5-6፣ ኢሳ. 7:1-2.
የሰሜናዊው እስራኤል መንግሥት (ኤፍሬም) እና ሶሪያ (አራም) ግንባር ፈጥረው
በደቡብ በኩል የምትገኘውን አነስተኛ አገር፤ ይሁዳን ሊወጉ ወጡ። ይህ የሆነው ይሁዳ
በኤዶማውያን እና ፍልስጤማውያን በደረሰባት ጥቃት በተዳከመችበት ወቅት ነበር።
ቀደም ባለው ጊዜ ይሁዳ እስራኤልን በውጊያ ብትገጥምም፤ የእስራኤል እና ሶርያ የጦር
ኅብረ ስምምነት ግን ሊቋቋሙት የማይችሉትን አደጋ ማምጣቱ አይቀሬ ነው። በወቅቱ
በፍጥነት እየተስፋፋ የነበረው ገናናው የአሦር ንጉሥ ቴልጌልቴል-ፌልሶር 3ኛ (2ነገሥ.
15፡19) በነዚህ አገሮች ላይ ከፍተኛ ዛቻና ማስፈራሪያ እያደረሰ ነበር።
ስለዚህ እስራኤል
እና ሶሪያ ይሁዳን አስገድደው የእነርሱ የጦር የኃይል ጥምረት አካል ለማድረግ የፈለጉ
ይመስላል። እስራኤል እና ሶርያ ለረጅም ጊዜ በመሃላቸው ሰፍኖ የኖረውን ሽኩቻ ወደ ጎን
በማለት፤ አሁን ትኩረታቸውን ከፊታቸው ወደ ተደቀነው ታላቅ አደጋ አደረጉ። ይሁዳን
አሸንፈው አሻንጉሊት መሪ ካስቀመጡ (ኢሳ. 7፡5-6) የአገሪቱን አንጡራ ሀብትም ሆነ
የሰው ኃይል እንዳሻቸው መመዝበር ይችላሉ።
ዓለም እየተደፋችበት የነበረው የአካዝ የመፍትሄ ሀሳብ ምን ነበር?
2ነገሥ. 16:7–9፣ 2ዜና 28:16።
አካዝ እርሱንም ሆነ አገሩን ሊታደግ ይችል ለነበረው ብቸኛው እግዚአብሔር አምላክ
ወዳጅነት እውቅና በመስጠት ፋንታ፤ የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው እንዲሉ--የጠላቶቹ
ጠላት ከሆነው ቴልጌልቴል-ፌልሶር 3ኛ ጋር ወዳጅነት ለመመስረት ሞከረ። የአሦር ንጉሥ
ይሁዳን በመርዳት በሶርያ እና እስራኤል ላይ እንዲነሳ የቀረበለትን ጥሪ በደስታ ነበር
የተቀበለው። ቴልጌልቴል-ፌልሶር 3ኛ ከአካዝ ሞቅ ያለ እጅ መንሻ ብቻ አልተቀበለም፤
ነገር ግን በትክክለኛው ሰዓት ሶርያን የራሱ ለማድረግ የሚያስችለውን ጥሩ ምክንያትም
እንዲሁ አገኘ (2ነገሥ. 16፡9)። የሶርያ--እስራኤል ኅብረ ጦር ስምምነት ውሃ በላው።
አካዝም ይሁዳን በአቋራጭ ያዳነ መሰለ።
ይህ በአካዝ የተደረገ ውሳኔ ብዙም የሚያስገርም ሊሆን አይችልም። እስከዚያ ዘመን
ድረስ ይሁዳን ከመሩ ነገሥታት ሁሉ እርሱ እጅግ የከፋው እንደ ነበር እሙን ነው።
(2ነገሥ. 16:3-4፣ 2ዜና. 28:2–4)።
አካዝ ምን ዓይነት ሰው እንደ ነበር ስናነብ፤ ያን ዓይነት አደጋ ያለው አካሄድ ለምን እንደ
መረጠ ለማስተዋል አያዳግትም። ከታሪኩ በግል ልናገኝ የምንችለው ትምህርት ምንድን
ነው? ጌታን ዛሬ ባንታዘዝም፤ እውነተኛው አስቸጋሪ ሁኔታ ሲከሰት በእርሱ እንድንታመን
የሚያስችል እምነት እንደምናገኝ አድርገን እንድናስብ የሚያደርገን ምንድን ነው? (ያዕ.
2፡22፣ ኤር. 12፡5)።
አካዝ ከእስራኤል እና ሶሪያ በኩል ለተጋረጠበት አስፈሪ አደጋ አሉኝ ያላቸውን
ፖለቲካዊ አማራጮች እየመረጠና እየመዘነ በነበረበት ወቅት፤ እርሱ ያላስተዋላቸውን
አንዳንድ ነገሮች እግዚአብሔር ያውቅ ነበር። እዚህ ላይ ችግር እንዲመጣበት
የፈቀደው እርሱን ለማረም እና ወደ ኅሊናው እንዲመለስ የፈለገው አምላክ እንደ
ነበር ሊጤን ይገባል (2ዜና 28፡5፣19)። በተጨማሪ ምንም እንኳን ቴልጌልቴልፌልሶር እንዲረዳው ያቀረበው ተማጽኖ ከሰብዊው አመለካከት አኳያ ተገቢና ማራኪ
ቢመስልም፤ የይሁዳ ዳዊታዊ ሥርወ መንግሥት ሊያንሰራራ በማይችል የባዕዳን
ቁጥጥር ስር እንዲወድቅ የሚያደርግ መዘዝ ማስከተሉን ግን እግዚአብሔር ያውቅ
ነበር።
ሊከተል የሚችለው አደጋ እጅግ አስደንጋጭ ነበር። ስለዚህ አካዝ የአሦርን ንጉሥ
እንዳይገናኘው ለማሳመን ጌታ ኢሳይያስን ላከው (በወቅቱ ንጉሡ ለጦርነት ከበባው
በሚያደርገው ዝግጅት የየሩሳሌምን የውሃ አቅርቦት እየፈተሸ ነበር)።
ኢሳይያስ ልጁን ሽአር ያሹብ ከእርሱ ጋር ይዞ እንዲሄድ ጌታ የነገረው ለምን
ነበር (ኢሳ. 7፡3)?
ኢሳይያስ ለአካዝ ሰላምታ አቅርቦ የስሙ ፍቺ “ትሩፋን ይመለሳሉ” የሚባል ልጁን
ሲያስተዋውቀው አካዝ መሸበሩ አይቀርም። የማን ትሩፋን? ከየት ይመለሳሉ?
የልጁ አባት ነቢይ ከመሆኑ አኳያ--ወደ ግዞት ስለሚሄዱ ሕዝቦች ከእግዚአብሔር
የተሰጠ ማስጠንቀቂያ አዘል መልእክት ያለው ስያሜ ይመስላል።
ወይስ በንስሐ ወደ
እግዚአብሔር ስለ መመለስ ይናገራል? (“መመለስ” የሚለው ግስ ንስሐ የሚል ፍቺ
መያዙንም ልብ ይሏል።) ከእግዚአብሔር ወደ አካዝ የመጣው መልእክት፡ ፍቺው አንተ
እንደ ተረጎምከው ይሆናል! የሚል አንደምታ ነበረው። ከኃጢአትህ ተመለስ ወይም ወደ
ግዞት ሂድ። ትሩፋን ከግዞት ይመለሳሉ። ውሳኔው የራስህ ነው!
አምላካዊው መልእክት ንጉሡ የሚገኝበትን ሁናቴ የተናገረበት መንገድ ምን
ይመስላል? ኢሳ. 7፡4-9
ከሶርያ እና እስራኤል የሚሰነዘሩ የጥቃት ዘመቻዎች ከሽፈው ይሁዳ ከአደጋው
ትተርፋለች። ለአካዝ ዐይኖች ገዝፈውና የሚፋጅ የእሳት ረመጥ ሆነው የታዩት
እነዚህ ኃይላት--ከእሳት ተርፈው የሚጤሱ ሁለት የእንጨት ጉማጆች (ኢሳ. 7፡4)
እንደመሆናቸው፤ አካዝ ለእርዳታ ወደ አሦር መሄድ ባላስፈለገው ነበር።
አካዝ ትክክለኛውን ውሳኔ መወሰን ይችል ዘንድ በጌታ እና እርሱ በሰጠው ተስፋ መታመን
ነበረበት።
በእምነቱ ጸንቶ መቆም ይችል ዘንድ ማመን ነበረበት (ኢሳ. 7፡9)። “ማመን”
እና “መቆም” የተሰኙት ቃላት መሰረታቸው ተመሳሳይ የዕብራይስጥ ስርወ ቃል ሲሆን፤
በተጨማሪ “እውነት” (ሊታመን የሚችል) እና አሜን (እውነት/ሊታመን የሚችል
ለመሆኑ ማረጋገጫ ይሰጣል)። አካዝ በእርግጠኝነት ጸንቶ ለመቆም እርግጠኛ መሆን
ነበረበት። በሚመካበት ላይ ለመጽናትም እንዲሁ የተመካ መሆን ነበረበት።
በኢሳ. 7፡9 የቀረበውን ጥቅስ የመጨረሻ ክፍል ይልከቱ። ጸንቶ ለመቆም-እምነት እጅግ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? በምን ላይ ጸንተን ልንቆም
ይገባል? ይህ መርኅ በክርስትና ህይወት መተግበር የሚችለው እንዴት
ነው?
አካዝ እምነት እንዲኖረው በኢሳይያስ ለቀረበለት ጥሪ ምላሽ ሳይሰጥ ቀረ። ሆኖም
“ከጥልቁ ጥልቅ ወይም ከከፍታው ከፍታ” (ኢሳ. 7፡11) ምልክት እንዲሰጠው
እግዚአብሔርን ይጠይቅ ዘንድ በምህረት የተሞላው አምላክ ለንጉሡ ሌላ ዕድል
ሰጠው። ለሰብዓዊው ፍጡር ከቀረቡ ታላላቅ የእምነት ግብዣዎች አንዱ እነሆ በዚህ
ክፍል ቀርቦአል። እግዚአብሔር እንደ ሎተሪ ወይም ቶምቦላ ዕጣ አንዳች ወሰን ወይም
ገደብ አላስቀመጠም። ደግነታቸው የመጨረሻው ጥግ ላይ ሲደርስ፤ የመንግሥታቸውን
እኩሌታ እስከ መስጠት ቃል እንደሚገቡ ሰብዓዊ ነገሥታት እንኳ እግዚአብሔር
ስጦታውን ውሱን አላደረገም (አስቴ. 5:6፣ 7:2፣ ማር. 6:23)። ይህ ዕቡይ ንጉሥ
ቢያምን ብቻ--ለእርሱ ሲል መላውን ሰማይ እና ምድር ባዶ ለማድረግ ዝግጁና ፈቃደኛ
ነበር! አካዝ የተቆለለ የወርቅ ተራራ ወይም መቆጠር የማይችል የሜድትራኒያን ያህል
የባሕር አሸዋ ሰራዊት በምልክትነት ቢጠይቅ በተሰጠው ነበር።
አካዝ ለምን በዚያ መልኩ ምላሽ ሰጠ (ኢሳ. 7:12)?
አካዝ የሰጠው ምላሽ ላይ ላዩን ሲታይ ቀና እና በአክብሮት የተሞላ ይመስላል።
እስራኤላውያን ከመቶዎች ዓመታት በፊት እንዳደረጉት፤ እግዚአብሔርን መፈታተን
(ዘፀ. 17፡2፣ ዘዳ. 6፡16) አልፈልግም ሲል ነበር የተናገረው። ነገር ግን ይሄኛው ጉዳይ
የተለየ ነበር። ምክንያቱም ንጉሡ እግዚአብሔርን እንዲፈትን ራሱ እግዚአብሔር አምላክ
ግብዣ አቅርቦለት ነበር (ያስተያዩ፡ ሚል. 3፡10)። አምላካዊውን ትዕግሥት ሳይፈታተኑ-ሞልቶ የተትረፈረፈ ለጋስ ስጦታውን መጠየቅ ያስደስተዋል እንጂ አያስከፋውም። አካዝ
ግን ራሱ እግዚአብሔር እንዲያምን እንዲረዳው ለመፍቅድ እንኳ ፈቃደኛ አልነበረም።
እምነትን ከውስጡ አንጠፍጥፎ አውጥቶ የልቡን ጓዳ ከረቸመ።
ጥቅሱን ያንብቡ፡ ኢሳ. 7፡13። ኢሳይያስ ምን እያለ ነው?
እግዚአብሔርን ለመፈተን ፈቃደኛ አለመሆኑ--ላይ ላዩን ሲታይ እግዚአብሔርን
ከማድከም ለመቆጠብ ሲል ያደረገው ቢመስልም፤ እውነታው የሚያሳየው አካዝ
እግዚአብሔርን እያደከመው እንደ ነበር ነው--ሲል ኢሳይያስ ግልጽ ድርጎ ያስቀምጣል።
በኢሳ. 7፡11 ነቢዩ--ከእግዚአብሔር “አምላኬ” ሳይሆን “ከአምላክህ” የሚለውን ቃል
ተጠቅሞ ንጉሡ ምልክት እንዲጠይቅ ያደረገው ጥሪ አብልጦ ውስጥን የሚነካ አቀራረብ
ነው። አካዝ የቀረበለትን መለኮታዊ ስጦታ ለመቀበል እንቢታውን ሲያሳይ፤ ጌታ አምላኩ
እንዳይሆን አደረገ። እግዚአብሔር የኢሳይያስ እንጂ የአካዝ አምላክ አልነበረም።
የዛሬው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን እኛን ሁላችንንም ወደ ደኅንነት
በማምጣት ረገድ ስለ እግዚአብሔር ትዕግሥት እና ፈቃደኝነት ምን
ያስተምረናል? በተጨማሪ ሰብዓዊው ልብ ሙሉ ለሙሉ ለጌታ ሳይገዛ ሲቀር
ስለሚታይበት መታወር እና መደንደን ምን ያስተምረናል? በመጨረሻ፤
እግዚአብሔር አካዝ የፈለገውን ምልክት ሰጥቶት እንኳን ቢሆን አካዝ ያምን
የነበረ ይመስሎታል? መልስዎን ያብራሩ።
“ከጥልቁ ጥልቅ ወይም ከከፍታው ከፍታ” (ኢሳ. 7፡11) የሚል ምልክት ከተሰጠም
በኋላ ቢሆን አካዝ ከያዘው አቋም ንቅንቅ አላለም። ሆኖም፤ እርሱ ራሱ ከምልክት ጋር
ይመጣል (ኢሳ. 7፡14) ብሎ እግዚአብሔር ሲናገር፤ ይህ በመለኮታዊው ምናብ ብቻ
ሊፈጠር የሚችል አስገራሚ ትዕይንት እንደሚሆን እንጠብቃለን (ኢሳ. 55፡9፣ 1ቆሮ.
2፡9)።
እነሆ ያልታሰበ ነገር! ምልክቱ ወንድ ልጅ ነው። ነገር ግን አንዲት ወጣት ድንል ሴት-ልጅ ወልዳ ስሙን “አማኑኤል” ብላ መጥራቷ ለዚህ ተመጣጣኝ መጽሐፍ ቅዱሳዊ
ምልክት መሆን የሚችለው እንዴት ነው?
ለመሆኑ ይህች ሴት ማን ናት? ልጇስ ማነው?
ለሌሎች ሰዎች ማለትም እንደ ጌዲዮን (መሳ. 6፡36-40) ለመሳሰሉት ምልክት በመስጠት
ክንውን ቢታይም፤ ብሉይ ኪዳን የዚህን አስፈላጊ ምልክት ፍጻሜ በየትኛውም ስፍራ
አያመለክትም። ስለዚህ በብሉይ ኪዳን ላይ ብቻ ተመስርተው ሊሆኑ ከሚችሉ ነጥቦች
መካከል አንዳንዶቹ እንደሚከተለው ቀርበዋል።
1.“ድንግል” የተሰኘው ቃል ለጋብቻ የደረሰችን ወጣት ዕንስት ማመላከቱን ተከትሎ
ብዙዎች በየሩሳሌም የምትኖር ባለ ትዳር አድርው ይህችን ሴት ያስቧታል-ምናልባትም የኢሳይያስ ሚስት አድርገው። ኢሳይያስ ከ “ነቢይቱ” ወንድ ልጅ እንደ
ተወለደለት በኢሳ. 8፡3 ተጠቅሷል (ትንቢታዊው መልእክት ስለ ሚስቱ እና ልጆቿ
የሚናገር መሆኑን፤ ጥቅሶቹን በማስተያየት ይመልከቱ፡ ኢሳ. 7፡3፣ 8፡18።) ይህ ሕፃን
ማኸር-ሻላል-ሃሽ-ባዝ (ኢሳ. 8፡1-4) በሚል ተጠራ እንጂ አማኑኤል አልነበረም።
ሆኖም ሁለቱም ልጆች ክፉና ደግ ማመዛመን የሚችሉበት ዕድሜ ላይ ሳይደርሱ
ሶርያ እና ሰሜን እስራኤል ላይ የጦርነት ውድመት መድረሱ ያመሳስላቸዋል (ኢሳ.
7፡16፣ 8፡4)።
2.አንዳንዶች አማኑኤል ቀጣዩ ንጉሥ የሆነው የአካዝ ልጅ ሕዝቅያስ ነው ይላሉ። ግን
አማኑኤል የሚለው ስም እርሱን አስመልክቶ ጥቅም ላይ አልዋለም።
3.አምላካዊውን አብሮነት በሚያሳይ መልኩ “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር” በሚል
ፍቺ የሚታወቀው ይህ ምስጢራዊ አንደምታ ያለው አማኑኤል--በኢሳ. 9 እና
11 ከተተነበየው ልዩ ህፃን ጋር ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል። እንዲያ ከሆነ፤ ከፍ ባለ
መለኮታዊ ባህሪ (ኢሳ. 9፡6) እና “የእሴይ ሥር” (ኢሳ. 11፡10) የቀረበው ይህ ህፃን፤
መልካም ንጉሥ ከተባለው ሕዝቅያስም ሆነ ከማንም የላቀና አቻ የማይገኝለት
ይሆናል።
4.አንድ ዕድሜዋ ለጋብቻ የደረሰ ወጣት ትዳር ሳትመሰርት ተልከስክሳ ማርገዟ፤ከሕግ
ውጪ የሚወለድ ህፃን ወይም ዲቃላ ያስከትላል (ዘዳ. 22፡20-21)። እግዚአብሔር
እንዲህ ዓይነቱን ህፃን እንደ እምነት ማነሣሻ ምልክት ለምን ይጠቅሳል?
በተቃራኒው የሱስን አማኑኤል በሚል ስያሜ ለይቶ የሚያስቀምጠው አዲስ ኪዳን
(ማቴ. 1፡21-23)፤ ካላገባች ነገር ግን ታጭታ ከነበረች ንጽህትና ድንግል ሴት በተዓምር
መወለዱን ይነግረናል። በተጨማሪ የሱስ መለኮታዊ ሕፃን (ኢሳ. 9፡6፣ ማቴ. 3፡17)
እንዲሁም “የእሴይ ሥር” እና “ዘር” ነው (ኢሳ. 11፡1፣ ራእ. 22፡16)። ቀደም ሲል የቀረበውና
የአካዝን የትንቢታዊ ፍፃሜዎች ተገቢነት ያሳየው “አማኑኤል” ምናልባት ከፊት እንደ
ተላከ የክርስቶስ መልእክተኛ አገልግሎ ይሆናል። በእርግጥ ይህን አናውቅም።
ነገር ግን
አብሮነቱን ሊገልጽልን የወደደው አምላክ “የተወሰነው ጊዜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር
ከሴት የተወለደውን ልጁን እንደ ላከ” ማወቅ እንዳለብን ግን እናውቃለን (ገላ. 4፡4)።
ክርስቶስ ሰብዓዊውን ሥጋ ለብሶ ወደ ምድር በመጣበት ሐቅ ዙሪያ ትኩረት
ያድርጉ። ምንም እንኳ ይህ ዓለም በራድ፣ ሰቆቃ የበዛበትና ግፈኛ ቢሆንም፤
የክርስቶስ መወለድ ሐቅ ምን ዓይነት መጽናኛ ሊሰጠን ይችላል?
የኢሳይያስ ልጆች ስም (“ሽአር ያሹብ” “ትሩፋን ይመለሳሉ” እና “ማኸር-ሻላል-ሃሽ-ባዝ”
“ምርኮ በቶሎ ይሆናል፣ ብዝበዛው ይፈጥናል”) የሚል ፍቺ እንዳለው ሁሉ፤ አማኑኤል
“እግዚአብሔር ከእኛ ጋር” የሚል ቀጥተኛ ትርጉም አለው። ሆኖም “እግዚአብሔር
ከእኛ ጋር” በሚል የቀረበው የተለመደ ፍቺ፤ እየተገለጸ ያለው በዕብራይስጥ ባለመሆኑ፤
የግስ እጦት እንዳለባቸው እንደ ሌሎቹ የዕብራይስጥ ስሞች ሁሉ ለዚህም “የመሆን”
ግስ ማካተት የግድ ይሆናል። ስለዚህ አማኑኤል በሚል የቀረበው ስያሜ “እግዚአብሔር
ከእኛ ጋር” በሚል መተርጎሙ የግድ ይሆናል (ኢሳ. 8፡10)--ልክ የሱስ ለተሰኘው ስም
“ጌታ ድነት ነው” የሚል ግስ እንደ ተጨመረለት።
“አማኑኤል” የተሰኘው ቃል ረቂቅና ግልጽነት የጎደለው መግለጫ አልያዘም። ይልቁንም፤
አሁን “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር” ስለ መሆኑ የተሰጠው ተስፋ፤ ፍጻሜ ያገኘበት
የማረጋገጫ ቃል ነው!
እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እንደሚሆን የተሰጠው የተስፋ ቃል አንደምታው
ምንድን ነው?
ከዚህ የበለጠ ጠንካራ ማረጋገጫም ሆነ መጽናኛ የለም። እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር
አብሮ እንደሚሆን ከመናገር ውጪ በመከራና ሥቃይ ውስጥ አያልፉም የሚል ቃል
አልወጣውም። ባለ መዝሙሩ እንዲህ ይላል፡ “በሞት ጥላ ሸለቆ ውስጥ ብሄድ እንኳ
አንተ ከኔ ጋር ስለሆንህ፣ ክፉን አልፈራም፤ በትርህና ምርኩዝህ እነርሱ ያጽናኑኛል”
(መዝ. 23፡4)።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡ “በውሃ ውስጥ በምታልፍበት ጊዜ፣ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤
ወንዙን ስትሻገረው፣ አያሰጥምህም፤ በእሳት ውስጥ ስትሄድ፣ አያቃጥልህም፤ ነበልባሉም
አይፈጅህም።” (ኢሳ. 43፡2)።
“ባቢሎናውያን ሦስቱን የዳንኤል ጓደኞች አስረው እሳት ውስጥ ሲጥሏቸው ጌታ የት
ነበር? (ዳን. 3፡23-25)። ደግሞስ ያዕቆብ እስኪነጋ በታገለበት የመከራው ወቅት ጌታ
የት ነበር? (ዘፍ. 32፡24-30)።
“ጌታ በአካል በዚህ ምድር ባይገለጥም፤ በመንፈስ ግን ሁሌም ከሕዝቡ ተሞክሮ ጋር
አብሮ ይኖራል። እስጢፋኖስ ላይ የደቦ እርምጃ ሲወሰድ ጌታ የት ነበር? ‘በእግዚአብሔር
ቀኝ ቆሞ’ ነበር (ሐዋ. 7፡55)። ነገር ግን የሱስ ወደ ሰማይ እንዳረገ ‘በሰማያት በግርማው
ቀኝ ተቀመጠ’ (ዕብ. 1፡3)። ታዲያ እስጢፋኖስ በድንጋይ ተወግሮ የመገደል ብርቱ አደጋ
በተጋረጠበት በዚያ ወቅት፤ ጌታ ለምን ቆመ? ሰባኪ፣ መምህርና ደራሲ የሆኑት ሞሪስ
ቬንደን እንደተናገሩት ‘የሱስ ቁጭ ማለት አላስፈለገውም ነበር!’” —Roy Gane, God’s
Faulty Heroes (Hagerstown, Md.: Review and Herald Pub. Assn., 1996), p.
66.
ምንም እንኳን “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር” የሚል የተስፋ ቃል ቢሰጠንም፤
ዛሬም አስከፊ ፈተና እና ሥቃይ ከመጋፈጣችን አኳያ የቃላቱ ፋይዳ ምንድን
ነው? የእርሱን አብሮነት ማወቃችን የሚያስገኝልን በጎ ነገር ምንድን ነው?
መልስዎን ያብራሩ።
“ ‘ስሙንም አማኑኤል ይሉታል… ትርጓሜውም እግዚአብሔር
ከእኛ ጋር ነው የሚል ነው’ የእግዚአብሔር የግርማው ብርሃን በየሱስ ፊት ላይ ይታያል።
ከዘለዓለም ጀምሮ ጌታ የሱስ ክርስቶስ ከአብ ጋር ነበረ። እርሱም የእግዚአብሔር
አምሳያ ነበር። የታላቅነቱና የግርማው አምሳያና የክብሩ አንጸባራቂ ነበር። ይህን ክብር
አጉልቶ ለመግለጽ ወደ ዓለማችን መጣ። በኃጢአት ወደ ጨለመችው ዓለም የመጣው
የእግዚአብሔርን ፍቅር ለመግለጽና እግዚአብሔር ከአኛ ጋር ይሆን ዘንድ ነው። ስለዚህ
ስሙ ‘አማኑኤል ይባላል’ ተብሎ ቀደም ሲል ተተነበየ።” የዘመናት ምኞት ገጽ 9።
“አካዝ ይህን ከሰማይ የተላከ መልእክት ተቀብሎ ቢሆን ኖሮ ለይሁዳ መልካም
በሆነ ነበር። ነገር ግን በሥጋ ክንድ መታመን በመምረጥ ከአሕዛብ እርዳታ ጠየቀ።
ከዚያም በተስፋ መቁረጥ ስሜት ወደ አሦር ንጉሥ ቴልጌልቴል-ፌልሶር እንዲህ ሲል
መልእክተኞች ላከ፡ “እኔ አገልጋይህም ልጅህም ነኝ፤ ስለዚህ መጥተህ ከሚወጉኝ
ከሶርያ ንጉሥና ከእስራኤል ንጉሥ እጅ አድነኝ’ (2ነገሥ. 16:7)። ልመናው ከንጉሡ እና
ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ግምጃ ቤት በተወሰደ ገጸ በረከት የታጀበ ነበር።”—Ellen
G. White, Prophets and Kings, p. 329.
1.ውሳኔ ለመወሰን በሂደት ላይ ባሉበት ወቅት እግዚአብሔርን ምልክት
መጠየቅ ተገቢ ነው? እንዲህ ያለው ነገር ምን ዓይነት አደጋ ሊያስከትል
ይችላል?
2.የሰዎች እርዳታ መኖር መልካም ቢሆንም፤ ግን ገደቡን እንዴት ያውቃሉ?
3.ሩሲያዊው ደራሲ ሊዮ ቶልስቶይ የሚከተለውን ለጓደኛው ጽፎ ነበር፡
“ሞት የማንኛውም ነገር መጨረሻ መሆኑን ሰው አንዴ ከተገነዘበ፤ ከሕይወት
የበለጠ የከፋ ነገር የለም።” “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር” የሚለው የአምላካዊ
ቃል ዕውቀት ለእንዲህ ዓይነቱ አባባል መልስ የሚሰጠው እንዴት ነው?
ማጠቃለያ፡ እግዚአብሔር እምነት የለሹን አካዝ ከባድ ውሳኔ መወሰን ወዳለበት
ሁናቴ አመጣው። ጥያቄው--ማመን ወይም አለማመን ነበር። ምንም እንኳ ጌታ
የማሰብ ችሎታው ሊፈቅድ ይችል የነበረውን ማንኛውንም ዓይነት ምልክት ሊሰጠው
ዝግጁ የነበረ ቢሆንም፤ እርሱን ለምን ማመን እንዳበት ምክንያቱን ለእግዚአብሔር
ማሳየት አልፈቀደም። ከዚያ ይልቅ የአሦርን ንጉሥ “ወዳጅ” አድርጎ መረጠ።