የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የተስፋው ቃል፡ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ኪዳን


2ኛ ሩብ ዓመት 2021

ከሰኔ 5 – 11

12ኛ ትምህርት

Jun 12 - Jun 18




የቃል ኪዳን እምነት



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ገላ 6:14; ሮሜ. 6:23; I ዮሐ 5:11, 13; ሮሜ. 4:1-7; ዘሌ. 7:18; ዘሌ. 17:1-4; ሮሜ. 5:1.


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “ጻድቅ በእምነት ይኖራል ስለ ተባለ ማንም በእግዚአብሔር ፊት በሕግ እንደማይጸድቅ ግልጽ ነው” (ገላ. 3፡11)

ከ ክርስቶስ ልደት ሰባት መቶ ዓመታት በፊት ገደማ የነበረው ገጣሚው ሆሜር ኦዲሴይ የተባለውን የታላቁን ተዋጊ የኦዲሴስን ታሪክ የጻፈ ሲሆን-በትሮጃን ጦርነት ውስጥ የትሮይን ከተማ ከለቀቀ በኋላ ወደ ትውልድ አገሩ ኢታካ ለመመለስ ዐሥር ዓመት የፈጀውን ጉዞ ጀመረ። የመርከብ መሰባበር፣ የባሕር ላይ ደፈጣ ወጊያ፣ ማዕበል፣ ዐውሎ ነፋስ እና ሌሎች መሰናክሎች ተደማምረው ጉዞው ረጅም ጊዜ እንዲወስድና እቅዱን እንዳይተገብር አደረጉት። በመጨረሻ ኦዲሴየስ በበቂ ሁኔታ መሠቃየቱን አማልክቱ ከተመለከቱ በኋላ፤ በድካም የዛለው ተዋጊ ወደ ቤቱ እና ቤተሰቡ እንዲመለስ ተስማሙ። ኦዲሴየስ ያለፈባቸው ብርቱ የፈተና ጊዜያቶች ለስህተቶቹ በቂ ማስተሰሪያ ናቸው ሲሉ ተስማሙ።

በአንድ በኩል ወደ ቤታችን ከምናደርገው ረጅም ጉዞ አኳያ እኛ እንደ ኦዲሴየስ ነን። በመሀላችን ያለው ወሳኝ ልዩነት--ወደ ቀደመው ንጽህና ለመመለስ፣ ከኦዲሴየስ በተቃራኒ “በበቂ ሁኔታ” ልንሠቃይ አንችልም። ስህተታችንን ይቅር ለማለት በሰማይና ምድር መካከል ያለው ርቀት በጣም ግዙፍ ነው። ወደ ቤት ከተመለስን በእግዚአብሔር ቸርነት ብቻ መሆን አለበት።

ሣምንቱ በጨረፍታ፡ ደኅንነት ሰጦታ መሆን ያለበት ለምንድን ነው? ለነፍሳችን ቤዛ መሆን የሚችለው ከእግዚአብሔር ጋር አንድ የሆነ ሰው ብቻ የሆነው ለምንድን ነው? ጽድቁ ለእኛ “ተቆጠረልን” ስንል ምን ማለታችን ነው? በመስቀል ላይ የተገኙትን ተስፋዎች እና የተስፋ ቃሎች የራሳችን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?



ሰኔ 6
Jun 13

የቀራኒዮ ነጸብራቆች


በብሉይ ኪዳን የሙሴ ኪዳን ስር የሚገኘው የመዳን መንገድ በአዲሱ ቃል ኪዳን ስር ከሚገኘው የአዲስ ኪዳን የደኅንነት መንገድ እምብዛም የሚለይ አይለይም። በብሉይም ይሁን በአዲስ ኪዳን፣ በአሮጌው ወይም በአዲሱ ኪዳን--መዳን የሚገኘው በእምነት ብቻ ነው። ነገር ግን እንደ ሥራ ባሉ ሌሎች ነገሮች ቢሆን ኖሮ--መዳን የሚከፈለን፣ ፈጣሪ ለእኛ የመስጠት ግዴታ የነበረበት በሆነ ነበር። የኃጢአትን ከባድነት የማይረዱ ብቻ እግዚአብሔር እኛን ለማዳን የተወሰነ ግዴታ ውስጥ ገብቷል ብለው ሊያምኑ ይችሉ ነበር። በተቃራኒው አንድ ብቻ ግዴታ ሊኖርብን የሚችል ሲሆን፤ ይኸውም ለተጣሰው ሕግ የምንፈጽመው ክፍያ ነበር። እኛ በእርግጥ ያንን ግዴታ መወጣት አልቻልንም። እንደ መታደል ሆኖ ግን የሱስ ስለ እኛ ከፍሎልናል።

“ወንዶችና ሴቶች በሰው ዘር ምትክ በመሞት በሰማይ ንጉሥ የተከፈለውን ታላቅ መሥዋዕትነት በበለጠና በተሟላ ሁኔታ መረዳት ሲችሉ፣ ያኔ የመዳን እቅድ ይጎላል፣ የቀራኒዮ ነጸብራቆች በክርስቲያኑ ልብ ውስጥ በፍቅር የተሞሉ፣ የተቀደሱና ጉልበት የሚሰጡ ጥልቅ ስሜት ይፈጥራሉ። ልቦቻቸውና ከናፍሮቻቸው ዘወትር ለእግዚአብሔር እና ለበጉ ምስጋና ያቀርባሉ። የቀራኒዮ ትዕይንት ትውስታ ዘወትር ከልቦቻቸው በማይጠፋ ወገኖች ውስጥ መታበይ እና እኔነት ሊሰፍን አይችልም።… መላው የዓለም ሐብትና ንብረቶች ለአንድ የጠፋ ነፍስን እንኳ ቤዛ የመሆን በቂ ዋጋ የላቸውም። ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተቸንክሮ ስለ ኃጢአተኛ ሰዎች እየተሰቃየ ለጠፋው ዓለም የተሰማውን ፍቅር ማን ሊለካ ይችላል? ይህ ፍቅር የማይሰፈር፣ የማይለካ ነበር።

“ክርስቶስ፤ ፍቅሩ ከሞት የበለጠ ጠንካራ መሆኑን አሳይቷል። እርሱ የሰውን ማዳን እያከናወነ በነበረበት ወቅት ምንም እንኳ ከጨለማ ኃይላት ጋር እጅግ አስፈሪ ግጭት ውስጥ የነበረ ቢሆንም፤ በዚህ ሁሉ ውስጥ ፍቅሩ እየጠነከረና እየበረታ ይሄድ ነበር። አባቱ ፊቱን ከእርሱ ሲያዞር ‘አምላኬ፣ አምላኬ ለምን ተውኸኝ?’ ብሎ እስከ መጮኸ ያደረሰውን ጭንቀት ተቋቁሞ ክንዶቹ ደኅንነት አስገኙ። ሰውን መዋጀት የሚያስችለው ዋጋ መከፈሉን ተከትሎ፤ በፍጥረት ሥራ መደምደሚያ ተሰምተው የነበሩት እነዚያ የተባረኩ ቃላት፣ እነሆ በመጨረሻው የነፍስ ግብግብ ዳግመኛ ተደመጡ፡ “ተፈጸመ!”

“የቀራኒዮ ትዕይንቶች ጥልቅ ስሜት ውስጥ ይከታሉ። በእነዚህ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የተለየ ቅንአት ውስጥ የሚገቡ ከሆነ፤ ይቅርታ አሎት። እጹብ ድንቅ እና ንጹህ የሆነው የሱስ አእምሮአችን ፈጽሞ ሙሉ በሙሉ ሊያስተውል የማይችለውን የዓለም ኃጢአት መሸከም እና ብርቱ ህመም ያለውን ሞት መሞት ነበረበት። እንዲህ ዓይነቱን አስገራሚ ፍቅር ርዝመት፣ ስፋት፣ ቁመት እና ጥልቀት መገመት አንችልም። ይህን ወደር የማይገኝለትና ጥልቀት ያለውን አዳኝ ፍቅር ማሰላሰል አእምሮን ሊሞላ፣ ነፍስን ሊነካ፣ ልብን ሊያቀልጥ፣ ፍቅርን ሊያጎለብትና መላውን ባህሪ ሙሉ ለሙሉ ሊለውጥ ይገባል።”—Ellen G. White, Testimonies for the Church, vol. 2, pp. 212, 213.

ከላይ የቀረቡትን ጽሑፎች በጸሎት መንፈስ ሆነው ያንቧቸው። ጸሑፎቹን በአእምሮዎ እንደያዙ ገላ. 6፡14 ያንብቡና በክርስቶስ መስቀል መመካት የምችለው እንዴት ነው--ብለው ራስዎን ይጠይቁ።



ሰኔ 7
Jun 14

ቃል ኪዳኑ እና መሥዋዕቱ


“ከቀድሞ አባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከንቱ ከሆነ ሕይወት የተዋጃችሁት በሚጠፋ ነገር፣ በብር ወይም በወርቅ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ፤ ነገር ግን እናንተ የተዋጃችሁት ነውርና እንከን እንደ ሌለበት በግ ደም፣ በክርስቶስ ክቡር ደም ነው።” (ጴጥ. 1፡1819)። ጴጥሮስ የተዋጃችሁት ሲል ምን ማለቱ ነው?



ጴጥሮስ ስለ ክርስቶስ የመስቀል ሞት ሲናገር የጠቀሰው “መዋጀት” ወይም ዋጋ ነክ ጽንሰ ሃሳብ፤ ስለ አንድ ግዞተኛ ባሪያ ተገቢው ዋጋ ከተከፈለ በኋላ (ብዙውን ጊዜ በዘመድ አማካይነት) ባሪያውን ከእስር ነፃ የማድረግ ጥንታዊ አሠራርን ያስታውሳል። በአንጻሩ ክርስቶስ ከኃጢአት ባርነት እና የመጨረሻ ፍሬው ከሆነው ሞት ነፃ አውጥቶናል። ሆኖም እርሱ ይህን ያደረገው በ “ክቡር ደሙ” ይኸውም በቀራኒዮ ለሰብዓዊው ዘር ምትክ ሆኖ በፈቃደኝነት በመሞቱ ነው። አሁንም፣ ይህ የቃል ኪዳኖች ሁሉ መሠረት እንደመሆኑ ያለዚህ--ቃል ኪዳኑ ዋጋ የሌለውና የማይጸና ይሆናል። ምክንያቱም እግዚአብሔር በእርሱ በኩል ያለውን ለሚያምኑ ሁሉ የተሰጠ የዘላለም ሕይወት ስጦታ ውል ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መፈጸም አይችልም። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሮሜ 6፡23፣ 1ዮሐ. 5፡11-13። ጥቅሶቹ በጋራ የሚያስተላልፉት መልእክት ምንድን ነው?



እኛ ያ የዘላለም ሕይወት ተስፋ አለን ምክንያቱም መጀመሪያ ያንን የዘላለም ሕይወት እንድናጣ ያደረገንን ጥሰት ሊያስተካክለው የሚችለው የሱስ ብቻ ነው። እንዴት? ምክንያቱም የፈጣሪ ጽድቅ እና ማለቂያ የሌለው ዋጋ በተጣሰው ሕግ ላይ ያለብንን ዕዳ ሊሽር ስለሚችል ነው። ይህ በኃጢአት ምክንያት የተፈጠረው ጥሰት ምን ያህል ሰፊ እንደነበር ያሳየናል። ለመሆኑ ለሕጉ መጣስ አንዳንድ ዘላቂ፣ ጊዜአዊ እና የተፈጠሩ አካላት ዋጋ መክፈል ቢችሉ ስለ አምላካዊው ዘላለማዊ ግብረገብ ሕግ ጽኑነት ምን ይላል? ከሕግ ዕዳ አርነት ለመውጣት የሚያስፈልገንን ቤዛ ሊከፍል የሚችለው ከራሱ ከእግዚአብሔር ጋር እኩል የሆነ፣ ሕይወቱን ከሌላ አካል ያልተበደረ፣ የሌላ አካል ውጤት ያልሆነ እና ዘላለማዊነት ያለው ብቻ ነው። ሁሉም የቃል ኪዳኑ ተስፋዎች ፍጻሜ የሚያገኙት፣ የዘላለም ሕይወት ተስፋ የሚኖረን እንዲሁም ከኃጢአትና ከሞት የተዋጀነው በዚሁ መንገድ ነው።

በአንድ የኪነ ጥበብ ሙዚየም ከወላጁ ጋር የመጣ ህጻን በቀለም የተሞላ ፊኛ በከበረ ጥንታዊ ሥዕል ላይ ቢወረውርና ሥዕሉ ሙሉ ለሙሉ ቢበላሽስ? ሥዕሉ ብዙ ሚሊዮኖች ዋጋ ያለው በመሆኑ፤ ወላጆች ያላቸውን ንብረት ሁሉ ቢሸጡ እንኳ ዕዳውን ለመክፈል ጥቂት እንኳ ቀረብ ማለት የማይችሉ ናቸው እንበል። ምሣሌው የኃጢአት ጥሰት ምን ያህል ከባድ እንደ ሆነ እንድንረዳ፣ ምን ያህል አቅመ ደካሞች እንደሆንን እንድንገነዘብና ዕዳውን መክፈል የሚችለው ራሱ ጌታ ብቻ መሆኑን እንድናስተውል የሚያግዘን በምን መልኩ ነው?



ሰኔ 8
Jun 15

የአብርሃም እምነት፡ ክፍል 1


“ ‘አብራም እግዚአብሔርን አመነ፤ እርሱም ጽድቅ አድርጎ ቆጠረለት’ ” (ዘፍ. 15:6) ይህ ቁጥር በሁሉም የቅዱሳት መጻሕፍት ከምናገኛቸው እጅግ ጥልቅ መግለጫዎች አንዱ ነው። ወሳኝ የሆነውን ጽድቅ በእምነት ብቻ--መጽሐፍ ቅዱሳዊ ኃይማኖት መሠረት ለመጣል የሚረዳን ሲሆን፤ ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ ስለዚህ ጉዳይ ከመጻፉ አያሌ መቶ ዓታት አስቀድሞ በአምላካዊው ቃል ተወስቶ እንመለከታለን። ከኤደን ጀምሮ ያለው ሁሉ፣ ደኅንነት በተመሳሳይ መንገድ ለመምጣቱ ማረጋገጫ እንድናገኝ ይረዳናል።

እግዚአብሔር ወንድ ልጅ እንደሚያገኝ የሰጠውን ተስፋ የማይቻል የሚያደርጉ የሚመስሉ አካላዊ ማስረጃዎች ቢኖሩም፣ የአብራም እምነት ምን ያህል ታላቅ እንደነበረ--የጥቅሱ ዐውደ ሀሳብ እንድንገነዘብ ይረዳናል። ለአብርሃም መታዘዝ ያስገኘለት እምነት፡ የራሱን ፍጹም አቅመ ቢስነት የሚገነዘብ፣ ራስን ሙሉ በሙሉ አሳልፎ መስጠትን የሚጠይቅ እና ለጌታ ሙሉ በሙሉ መገዛት የሚጠይቅ እምነት ነው። ይህ የአብራም እምነት ነበር እናም ለእርሱ “ጽድቅ አድርጎ” ቆጠረለት። መጽሐፍ ቅዱስ ጽድቅ አድርጎ “ቆጠረለት” የሚለው ለምንድን ነው? አብርሃም ራሱ እንደ እግዚአብሔር ዓይነት “ጽድቅ” ነበረው? እግዚአብሔር ጻድቅ ብሎ በይፋ ተናግሮለት ብዙም ሳይቆይ ያደረገው ነገር እርሱ ራሱ በትክክል ከነበረው ማንነት በተቃራኒ ይህ ጽድቅ ለምን እንደተሰጠው እንድናስተውል እንዴት ይረዳናል?

የሆነው ሆኖ፤ አብርሃም ፍጹም እምነትና መታዘዝ ባይኖረውም፤ በአመዛኙ የእምነት እና የመታዘዝ ሕይወት ነበረው። አልፎ አልፎ በሁለቱም በኩል ድክመት አሳይቶ ነበር። (ይህ ሁኔታ ከሆነ የሚያውቁት ሰው ጋር ይመሳሰላል?) እነዚህ ሁሉ ወደ አንድ ወሳኝ ነጥብ ይመሩናል፡ እኛን የሚያድነን ጽድቅ የተሰጠን ወይም የተቆጠረልን ጽድቅ--ወደ መሆኑ። ምንም እንኳ በደለኞች ብንሆንም በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ሆነን እንቆጠራለን ማለት ነው። እኛ ባንሆንም፤ የሰማይ አምላክ እንደ ጻድቅ ይቆጥረናል ማለት ነው። እርሱ ለአብርሃም ያደረገው ይህንኑ እንደመሆኑ፤ በአብርሃም እምነት (ሮሜ 4፡16) ወደ እርሱ ለሚመጡ ሁሉ ተመሳሳዩን ያደርጋል። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሮሜ 4፡1-7። ጳውሎስ ዘፍ. 15፡6 የተጠቀመበትን ዐውድ ይመልከቱ። በእነዚህ ጥቅሶች ዙሪያ ይጸልዩና ስለ እኔ ይናገራሉ ብለው የሚያምኑትን ሀሳብ በወረቀት ላይ ያስፍሩ።





ሰኔ 9
Jun 16

የአብርሃም እምነት፡ ክፍል 2


ወደ ዘፍ. 15፡6 እንደገና ስንመለከት “ቆጠረለት” ለተሰኘው ቃል (በዕብራይስጥ፡ ሃሳብ) ወይም “ታሰበለት”፣ “በሃሳብ ያዘ” በሚል የቀረቡ የተለያዩ ዓይነት ፍቺዎችን መመልከት እንላለን፡ ይኸው ቃል በሙሴ መጻሕፍት ሌሎች ጽሑፎችም ይሠራል። የሆነ ሰው ወይም ነገር እንዳልሆነ ተደርጎ “ተቆጠረ” ወይም “ታየ”። ለምሣሌ በዘፍ. 31፡15 ራሔል እና ሊያ ምንም እንኳ የአባታቸው ሴቶች ልጆች ቢሆኑም ነገር ግን እኛን “የሚያየን” ወይም “የሚመለከተን” እንደ ባዕድ ነው ብለው በጽኑ ሲናገሩ እንመለከታለን።

ስለ ሌዋውያን አሥራት ሲናገር ነገሩ እንዲያ ባይሆንም--ከአውድማ እንደገባ እህል ወይም ከመጭመቂያ እንደ ወጣ ወይን “ይቆጠርላችኋል” ይላል (ዘኁ. 18፡27፣30)። አሰበ ወይም አድርጎ ቆጠረ የተሰኘው ይህ ጽንሰ ሀሳብ በመሥዋዕቶች ዐውደ ጽሑፍ እንዴት ይገለጻል? (ዘሌዋ. 7:18፣ ዘሌዋ. 17፡ 1–4)።



ኪንግ ጀምስ በመባል የሚታወቀው የመጽሐፍ ቅዱስ ሀተታ ወይም እትም “ሃሳብ” የተሰኘውን የዕብራይስጥ ቃል ለመተርጎም “ተቆጠረ” የሚል ፍቺ ይሰጣል። አንድ በዓይነቱ ልዩ የሆነ መሥዋዕት (“የሰላም መባ”) በሦስተኛው ቀን ከተበላ አይሠምርም፤ ላቀረበው ሰው የተጠላ ይሆንበታል እንጂ ቁርባን ሆኖ “አይቆጠርለትም” (ዘሌዋ. 7፡18 /1962 ትርጉም/)። ኃጢአተኛው ጻድቅ ሆኖ በእግዚአብሔር ፊት ይቆም ዘንድ የሚያቀርበው መሥዋዕት ስለ እርሱ ጥቅም “ይቆጠራል” ሲል ዘሌዋ. 7፡1-4 ይናገራል። ምንም እንኳ የግለሰቡ አመጸኛነት እርግጥ ቢሆንም እግዚአብሔር ኃጢአተኛውን እንደ ጻድቅ እየቆጠረ እንደሆነ እንመለከታን። ምንም እንኳ ጥፋተኞች ብንሆንም፤ በእግዚአብሔር ፊት እንደ ጻድቅ ልንቆጠር ወይም ልንታይ በምንችልበት በዚህ አስደናቂ እውነት ዙሪያ ጥቂት ጊዜ ወስደው ያሰላስሉ። ይህ ምን ማለት እንደሆነ የተረዱትን በራስዎ ቃላት ይጻፉ።

ጻድቅ ሆነን የተቆጠርንበት ታላቁ እውነት--እኛ ማድረግ በምንችለው አንዳች ተግባር ሳይሆን፤ ክርስቶስ ባደረገልን ነገር ላይ በሚኖረን እምነት ብቻ--ይኸውም “ጽድቅ በእምነት” ነው። ሆኖም እምነታችን እራሱ ጻድቅ ያደርገናል ማለት ሳይሆን፤ ይልቁንም እምነት የጽድቅ ስጦታ የምናገኝበት ልዩ መሣሪያ ነው። ይህ በመሠረቱ የክርስትና ውበት፣ ምስጢር እና ክብር ነው። እኛ እንደ ክርስቲያን አማኝነታችንና እንደ ክርስቶስ ተከታይነታችን በዚህ አስደናቂ ጽንሰ ሀሳብ ውስጥ አንድ ወሳኝ መሠረት እናገኛለን። በእምነት በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ሆነን ተቆጥረናል። ይህን ተከትሎ መታዘዝ፣ መቀደስ፣ የባሕሪ መሻሻል፣ ፍቅር--ከዚህ ወሳኝ እውነት መመንጨት ይኖርባቸዋል።

ክርስቲያን ለመሆን አጥብቆ እየፈለገ ነገር ግን “ጻድቅ እንደሆንኩ አይሰማኝም” ለሚል ሰው ምላሽዎ ምንድን ነው



ሰኔ 10
Jun 17

በተስፋዎች ላይ ማረፍ


ካርዲናል ቤላርማይን በመባል ስለሚታወቅ ዝነኛ የካቶሊክ ጳጳስ የተነገረ ታሪክ አለ። ግለሰቡ በተቆጠረልን ጽድቅ ብቻ ጻድቅ ተደርገናል ከተሰኘው መልእክት ጋር ህይወቱን ሙሉ ሲፋለም ኖሯል። ታዲያ ለሞት በተቃረበበት ወቅት፤ ከመሞቱ በፊት ዋስትና እንዲያገኝ እንዲረዱት በሚል መስቀሎች እና የቅዱሳን ብቁ ሥራ ገድሎች አመጡለት። ቤልማይን ግን “እነርሱን ዞር አድርጉ። በክርስቶስ መልካም ሥራዎች ላይ እምነት መጣል ይበልጥ አስተማማኝ እንደሆነ አስባለሁ።” አላቸው። ብዙ ሰዎች የሕይወታቸው ፍጻሜ ሲቃረብ ወደ ኋላ መለስ ይሉና ተግባሮቻቸውም ሆኑ ሥራዎቻቸው በሙሉ ቅዱስ በሆነው አምላክ ፊት ደኅንነት ለማስገኘት ምን ያህል ከንቱ፣ ዋጋ ቢስ፣ ጥቅም የማይሰጡ መሆናቸውንና የክርስቶስ ጽድቅ ምን ያህል እንደሚያስፈልጋቸው ይመለከታሉ።

ሆኖም መልካም የሆነው የምሥራች፤ አሁን በጌታ አስተማማኝ ሁናቴ ላይ መገኘት እየቻልን ሞት እስኪመጣ መጠበቅ የለብንም። ቃል ኪዳኑ በሙሉ የተመሠረተው በአሁን የእግዚአብሔር አስተማማኝ ተስፋ ላይ ነው። ተስፋዎቹ ሕይወታችንን አሁን የተሻለ ሊያደርጉ የሚችሉ ናቸው። ከዚህ በታች የቀረቡትን ጥቅሶች ይመልከቱና ከእግዚአብሔር ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን ከማዳበር፣ ከመጠበቅና ከማጠንከር አኳያ ጥያቄዎቹን ይመልሱ። መዝ. 34፡8 (የእግዚአብሔርን መልካምነት እንዴት መቅመስ ይችላሉ?)



ማቴ. 34፡8፡ (ይህ ቀንበር ይቀል ዘንድ ክርስቶስ ያደረገልን ነገር ምንድን ነው?)



ሮሜ 5፡1፡ (ጽድቅ ከሰላም ጋር ምን ያገናኘዋል)



ፊልጵ. 2፡7-8፡ (ከክርስቶስ ተሞክሮ ምን ገበዩ?)



በጸሎት ሕይወትዎን ይመርምሩና እንዲህ ብለው ራስዎን ይጠይቁ፡ ከእግዚአብሔር ጋር ያለኝን ግንኙነት የሚያጠናክሩልኝ ምን ዓይነት ነገሮች እያደረኩ ነው? ምን ዓይነት ለውጦች ማድረግ ያስፈልገኛል?

ሰኔ 11
Jun 18


ተጨማሪ ሀሳብ


“ኃጢአተኛው ጽድቅ የሚያገኝበት ብቸኛው መንገድ እምነት ነው። የክርስቶስን የጽድቅ ሥራዎች በእምነት ወደ እግዚአብሔር ማምጣት ይችላል። በዚህም እግዚአብሔር የልጁን መታዘዝ ለኃጢአተኛው ይቆጥርለታል። የክርስቶስ ጽድቅ በግለሰቡ ውድቀት ምትክ ተቀባይነት ስለሚያገኝ፤ እግዚአብሔር ተነሣሒውን አማኝ ነፍስ ጻድቅ አድርጎ በመመልከት ልጁን እንደሚወደው ይወደዋል፣ ይቀበለዋል፣ ይቅር ይለዋል ደግሞም ያጸድቀዋል። እምነት እንደ ጽድቅ የሚቆጠረው በዚህ መንገድ ነው።”—Ellen G. White, Selected Messages, book 1, p. 367.

“በንስሐ እና በእምነት ክርስቶስን እንደ አዳኛችን ስንቀበል ጌታ ኃጢአታችንን ይቅር ይላል፤ ሕጉን በመተላለፋችን የሚደርስብንን ቅጣት ያስቀራል። በዚህ ጊዜ ኃጢአተኛው እንደ ጻድቅ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ይቆማል። በሰማይ ፊት ሞገስ ያገኛል፤ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ከአብ እና ከወልድ ጋር ሕብረት ይኖረዋል። “ከዚህ ሌላ ሊከናወን የሚገባው ተጨማሪ ሥራም እንዲሁ ያለ ሲሆን፤ ይኸውም ታዳጊ ተፈጥሮን ይመለከታል። ነፍስ በእውነት አማካይነት ልትቀደስ ይገባል። ይህ ደግሞ በእምነት ክንውን ያገኛል። ባህሪ መለወጥ የሚችለው በእምነት በተቀበልነው የክርስቶስ ጸጋ ብቻ ነው።”—Ellen G. White, Selected Messages, book 3, p. 191.


የመወያያ ጥያቄዎች



፡ 1.በሕያው እና ሙት እምነት መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? ጳውሎስ ሕያው የሆነን እምነት እንዴት ይገልጸዋል? (ሮሜ 16፡26)። እምነት የሚያካትተውን ለመግለጽ የሚረዳ ቁልፍ ቃል ምንድን ነው?

2.የዳንነው በውስጣችን በሚኖረው ሳይሆን በተቆጠረልን ጽድቅ ብቻ ከሆነ፤ የምናደርገው ነገር የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም--በሚል ለሚነሡ የሙግት ሀሳቦች ምላሽዎ ምንድን ነው?

3.በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት ማግኘታችን የሚረጋገጠው በተወዳጁ ልጁ አማካይነት ብቻ እንደመሆኑ፤ መልካም ሥራ የእርሱ ኃጢአትን ይቅር የሚል ፍቅር ውጤት ነው። ከዚህ ውጪ ሥራችን ለእኛ የሚያስቆጥርልን ምንም ነገር የለም። መልካም ሥራችንን ተገን በማድረግ ለነፍሳችን መዳን የምናበረክተው አንዳች ድርሻም የለንም። … እርሱ [አማኙ] ለነፍሱ መዳን ስለ መልካም ሥራዎቹ ልመና ማቅረብ አይችልም።”—Ellen G. White, Selected Messages, book 3, p. 199. ይህንን በአእምሮዎ እንደ ያዙ--መልካም ሥራዎች ለክርስትና ተሞክሮ ወሳኝ አካል ናቸው?

ማጠቃለያ፡ አሮጌው ቃል ኪዳንም ሆነ አዲሱ ቃል ኪዳን፡ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ሆነን እንቆም ዘንድ ሕጉ የሚጠይቀውን ዕዳ እነሆ የሱስ ከፍሎታል!




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL