የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የተስፋው ቃል፡ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ኪዳን


2ኛ ሩብ ዓመት 2021

ከግንቦት 28 – ሰኔ 4

11ኛ ትምህርት

Jun 05 - Jun 11




የአዲስ ኪዳን ቤተ መቅደስ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘፀ. 25:8፣ ኢሳ. 53:4–12፣ ዕብ. 10:4፣ ዕብ. 9:14፣ ዕብ. 8:1–6፣ 1ጢሞቴ. 2:5-6።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “ስለዚህ… ክርስቶስ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው፤ በመጀመሪያው ኪዳን ሥር በነበሩበት ጊዜ ከሠሩት ኃጢአት ነጻ ለማውጣት ቤዛ ሆኖ ሞቶአልና” (ዕብ. 9፡15)፡፡

በ ዚያ ምሽት ጨረቃ አልወጣችም። ሰማዩ ጥቁር ቀለም የፈሰሰበት ይመስላል። ፍራንክ በዚያ ጥቅጥቅ ያለ ጨለማ በከተማው ጎዳና እየተራመደ ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ--ከበስተ ኋላው ኮቴ ሰማ። በዚያ ጨለማ ውስጥ አንድ ሰው እየተከተለው ነበር። ከዚያም ይኸው ሰው አጠገቡ ደርሶ “ፍራንክ አታሚው?” አለው።

“አዎ፤ ነኝ። ግን እንዴት አወቅከኝ?” “በእርግጥ አላውቅህም።” በማለት እንግዳው ሰው ከመለሰ በኋላ ንግግሩን በመቀጠል “ወንድምህን ግን በሚገባ አውቀዋለሁ። በጨለማ ውስጥ እንኳ ሥነ ምግባርህ፣ አረማመድህ፣ ገጽታህ ሁሉ እርሱን በሚገባ ያስታውሱኛል። ስለዚህ ወንድሙ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት ነበረኝ፤ ደግሞም አንድ ወንድም እንዳለው ነግሮኝ ነበር” ይህ ታሪክ ስለ እስራኤል የቤተ መቅደስ አገልግሎት ብርቱ እውነት ይገልጥልናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የእውነተኛይቱ--ጥላ፣ ምሣሌና ምስል ነበር። ሆኖም በምስሉ ሊወክሉ የሚገባቸውን፡ የክርስቶስን ሞት እና የሰማያዊ ሊቀ ካህንነት አገልግሎት እውነታዎች በጉልህ ለማሳየትና ለመወከል በቂ ነበሩ።

ሣምንቱን በጨረፍታ፡ እስራኤላውያን መቅደስ ይሠሩ ዘንድ እግዚአብሔር ለምን ፈለገ? ክርስቶስ ምትካችን ስለ መሆኑ ቤተ መቅደሱ ምን ያስተምረናል? የሱስ እንደ ወኪላችን ሆኖ በሰማይ ምን ያደርጋል?



ግንቦት 29
Jun 6

ግንኙነቶች


“ማደሪያዬን በመካከላችሁ አደርጋለሁ፤ ነፍሴም አትጸየፋችሁም። በመካከላችሁ እመላለሳለሁ፤ አምላካችሁ እሆናለሁ፤ እናንተም ሕዝቤ ትሆናላችሁ” (ዘሌዋ. 26፡ 11-12) አሁን አንድ ነጥብ ግልጽ መሆን አለበት፡ በአሮጌው ቃል ኪዳንም ሆነ በአዲሱ ቃል ኪዳን--ጌታ ከሕዝቡ ጋር የጠበቀ የፍቅር ግንኙነት ይፈልጋል። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ቃል ኪዳኖቹ ለግንኙነቱ የሚበጁ “ደንቦች” ለመፍጠር ይረዳሉ።

ግንኙነት በማንኛውም ጊዜ ወይም ዐውድ ለቃል ኪዳኑ ወሳኝ ናቸው። ሆኖም ለግንኙነት መኖር መስተጋብር መፍጠር፣ መናበብ፣ መገናኘት በተለይ ኃጢአተኛና ተጠራጣሪ ለሆነው ሰብዓዊ ፍጡር ወሳኝ ነው። ይህን በሚገባ የሚያውቀው ጌታ ከእርሱ ጋር ትርጉም ያለው ዝምድና እንፈጥር ዘንድ፣ በውድቀት ለተገደብነው ለእኛ ራሱን ለመግለጥ ቀዳሚውን ተነሳሽነት ወሰደ። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፀ. 25፡8። ጌታ እስራኤላውያን ቤተ መቅደስ እንዲሠሩለት ትእዛዝ ሰጣቸው። ይህን እንዲያደርጉ የፈለገበትን ምክንያት ሲገልጽ ምን አላቸው?



በእርግጥ የዚህ ጥያቄ መልስ--ጌታ በሕዝቡ መካከል ለማደር የፈለገለው ለምንድን ነው? የሚል ሌላ ጥያቄ ያስነሳል። እውነታው፣ ምናልባት ከላይ በተዘረዘሩት የዛሬ ጥናት ጥቅሶች ላይ መገኘት ይችላል። ጌታ ማደሪያውን “በመካከላቸው” እንደሚያደርግ በመናገር “ነፍሴም አትጸየፋችሁም” ሲል ይቀጥላል። ከዚያም “በመካከላችሁ እመላለሳለሁ” በማለት አምላካቸው እንደሚሆን፣ እነርሱም ሕዝቡ እንደሚሆኑ ይገልጻል (ዘሌዋ. 26፡1112)። በጥቅሶቹ የቀረቡትን ባህሪያት ይመልከቱ። ግንኙነታዊ ገጽታ አሁንም በጣም ግልጽ ሆኖ እንደመጣ ይታያል።

ጥቂት ጊዜ ወስደው--ዘሌዋ. 26፡11-12 እና ዘፀ. 25፡8 ላይ የቀረቡ ጽንሰ ሀሳቦችን ለማብላላት ይሞክሩ። በጥቅሱ የሰፈሩ የተለያዩ ባህሪያት ጌታ ከህዝቡ ጋር ግንኙነት ይፈልጋል ከሚለው አስተሳሰብ ጋር እንዴት እንደሚጣጣሙ ይፃፉ። በተለይ ጌታ “ነፍሴም አትጸየፋችሁም” ሲል በተናገረው ሀረግ ላይ ትኩረት ያድርጉ። የወደቀው፣ ኃጢአተኛ ሰብዓዊ ፍጡር በጌታ ተቀባይነት እንዲያገኝ መንገዱን የሚያመቻቸው ቤተ መቅደሱ በራሱ ምንድን ነው? ደግሞስ ቃል ኪዳን ለማቋቋም ሂደት ያን ያህል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?





ግንቦት 30
Jun 7

ኃጢአት፣ መሥዋዕት እና ተቀባይነት (ዕብ. 9፡22)


በብሉይ ኪዳን ዘመን ኃጢአተኛው ራሱን ከመተላለፍ እና ከበደል እንዲያነጻ በመለኮት የተደነገገው መንገድ የእንስሳ መሥዋእትነት ነበር። የእስራኤላውያን የመሥዋዕት ሥርዓት ዝርዝር ዘሌዋ. ምዕ. 1-7 ቀርቧል። በተለያዩ ዓይነት መሥዋዕቶች-የደም አጠቃቀም እና አወጋገድ ላይ የተለየ ጥንቃቄ ይደረግ ነበር። በእርግጥም በመሥዋዕታዊ ሥርዓቶች ውስጥ የደም ሚና፤ የእስራኤላውያን መሥዋዕቶችን በአንድ ከሚያስተሳስሯቸው ባህሪያት አንዱ ነው። ኃጢአት የሠራና የቃል ኪዳኑን ግንኙነት ሕግ የጣ

ሰ ሰው፤ ከእግዚአብሔር እና ከሰው ጋር ወደ ሙሉ ሕብረት መመለስ የሚችለው በእርሱ ምትክ የሚታረድ የእንስሳ መሥዋዕት በማቅረብ ነበር። መሥዋዕቶች፣ ከነአምልኮ ሥርዓቶቻቸው--ከኃጢአት እና በደል ለመንጻት እግዚአብሔር የደነገጋቸው ዘዴዎች ነበሩ። እነዚህ ኃጢአተኛውን ለማንጻት የተቋቋሙ ዘዴዎች--በሚረጨው የእንስሳው ደም እያንዳንዱን የግለሰቡን ኃጢአትና በደል ወደ መቅደሱ በማስተላለፍ፤ ተነሳሒውን የግል አምላኩ ከሆነው አዳኝ ጌታ ጋር የንስሐ እና ኪዳናዊ ኅብረት እንደገና ለመመስረት የሚያስችሉ ነበሩ። እነዚህ ከላይ የተገለጹ ጽንሰ ሀሳቦች በትናንቱ ጥናት መጨረሻ የቀረቡ ጥያቄዎችን ለመረዳት እንዴት ይረዱናል? በእንስሳው መሥዋእት ውስጥ ምን ዓይነት ትንቢታዊ አንደምታ ነበር? (ኢሳ. 53:4–12፣ ዕብ.10:4)



የብሉይ ኪዳን ዘመኑ የእንስሳ መሥዋዕቶች፤ ኃጢአተኛውን ከኃጢአት እና ከበደል ለማንጻት የተደነገጉ መለኮታዊ ዘዴዎች ነበሩ። ኃጢአተኛው የሚገኝበትን የበደለኝነት እና የሞት ፍርደኝነት ሁናቴ ዳግም በአምላክ--ሰው ኪዳን ላይ የተመሠረተ ይቅርታ ወደ መቀበል ይቀይራሉ። ነገር ግን የእንስሳ መሥዋዕቶች ትንቢታዊ ተፈጥሮ ነበራቸው። የትኛውም እንስሳ ለሰው ልጆች ኃጢአትና ጥፋት ማስተሰሪያ የሚሆን በቂ ምትክ አልነበረም። ይህን አስመልክቶ የዕብራውያን መጽሐፍ ደራሲ የሚከተለውን በብዕሩ አስፍሯል፡ “ምክንያቱም የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን ማስወገድ አይችልም” (ዕብ. 10፡4)። ስለሆነም የእንስሳት መሥዋእትነት ለዓለም ኃጢአት ምትክ የሚሞተውን፣ መለኮት--ሰው የሆነውን የእግዚአብሔር አገልጋይ መምጣት የሚያመለክት ነበር።

እንግዲህ ኃጢአተኛው ይቅር የሚባለው፣ በጌታ ተቀባይነት የሚያገኘውና የቃል ኪዳናዊው መሠረት የሚጸናው በዚህ ሂደት አማካይነት ነበር። ራስዎን--በብሉይ ኪዳን ዘመን እንስሳት በቤተ መቅደሱ በሚሠዉበት ዘመን ላይ ያስቀምጡ። እንስሳት ለእነዚያ ሕዝቦች ምጣኔ ሐብት፣ ባህልና አጠቃላይ የኑሮ ዘይቤ ምን ያህል አስፈላጊ እንደ ነበሩ በማስታወስ፤ ኃጢአት ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍል እነዚህ መሥዋዕቶች ያስተምሯቸዋል ተብሎ ይታሰባል?



፡ ሰኔ 1
Jun 8

ምትክ


“እንደ አምላካችንና እንደ አባታችን ፈቃድ ከዚህ ክፉ ዓለም ያድነን ዘንድ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ” (ገላ. 1፡4) ከአዲስ ኪዳን ቁልፍ ጭብጦች አንዱ የሱስ ክርስቶስ ለዓለም ኃጢአት መሥዋዕት ሆኖ መሞቱ መሆኑ ላይ ምንም ጥያቄ የለም። ይህ እውነት የአጠቃላዩ ደኅንነት እቅድ መሠረት ነው። የክርስቶስን ደም ሥርየት የሚክድ ማንኛውም ኃይማኖታዊ አስተምህሮ የክርስትናን ልብና ነፍስ ይክዳል። የሚያስተሰርይ ደም የሌለው መስቀል ማንንም ሊያድን አይችልም።

በዛሬው ጥናት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ ማሰላሰል ካደረጉ በኋላ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ይመልሱ፡ የሱስ ለመሞት ፈቃደኛ ነበር? ለማን ነበር የሞተው? ሞቱ ምን ዓይነት ክንውን አመጣ?



ምትክ--የአጠቃላዩ የደኅንነት እቅድ ቁልፍ ነው። በኃጢአታችን ምክንያት ሞት የሚባን ነን። ክርስቶስ ለእኛ ካለው ፍቅር የተነሳ “ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ” (ገላ. 1፡4)። እኛ የሚገባንን ሞት እርሱ ሞተ። የኃጢአተኞች ምትክ የሆነው የክርስቶስ ሞት፤ የሌሎች ሁሉ እውነቶች መነሾ ታላቅ እውነት ነው። ወደ ቀድሞው ንጽህና የመመለሳችን፣ የነፃነታችን፣ ይቅር የመባላችንና የኤደን ዘላለማዊ ሕይወት ተስፋችን የሚያርፈው የሱስ ራሱን ለኃጢአታችን በመስጠት ለእኛ በሠራው ሥራ ላይ ነው። ያለዚህ እምነታችን ትርጉም የለሽ ይሆናል። ምናልባት ተስፋችንንና መታመናችንን ከዓሣ ቅርጽ ለተሠራ ሐውልት ልናደርግ ብንችል እንኳ፤ ነገር ግን ደኅንነት የሚገኘው በደም--ይኸውም በክርስቶስ ደም ብቻ ነው።

ጥቅሶቹን ይመልከቱ፡ ማቴ. 26:28፣ ኤፌ. 2:13፣ ዕብ. 9:14፣ 1ጴጥ. 1:19። ስለ ደሙ ምን ይሉናል? ታዲያ ደም በመዳን እቅድ ውስጥ ምን ዓይነት ሚና ይጫወታል?



“ኃጢአተኛ እና ብቁ ስላልሆንኩ እግዚአብሔር አይቀበለኝም በሚል ፍርሐት ራስን ማሰቃየት አምላካዊ ፈቃድ አይደለም።… ‘እኔ ኃጢአተኛ እንደሆንኩ አውቃለሁ፤ ለዚህም ነው አዳኝ የሚያስፈልገኝ …መዳን ይገባኛል እንድል የሚያስችለኝ አንዳችም በጎነት ወይም መልካምነት የለኝም፤ ነገር ግን የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ ነውር የሌለበት፣ ከበደል ሁሉ የሚያነጻው የእግዚአብሔር በግ ደም ፊት ራሴን አቀርባለሁ።

ይህ ብቸኛው ልመናዬ ነው።’ ”—Ellen G. White, The Faith I Live By, p. 100. ከዚህ በላይ በትምህርተ ጥቅስ የቀረበውን የኤለን ኋይት ጽሑፍ ልብ ብለው ይመልከቱ። ሀሳቡን በራስዎ ቃላት እንደገና ይጻፉ። የግል ፍርሃቶችዎን እና ህመምዎን በዚያ ውስጥ ያኑሩ። ከዚያም እነዚያ የተካተቱ ነጥቦች ለእርስዎ የሚሰጦትን ተስፋዎች ይጻፉ። በአዲሱ ቃል ኪዳን ደም--ምን ተስፋ አሎት?

ሰኔ 2
Jun 9

የአዲሱ ቃል ኪዳን ሊቀ ካህናት


እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር አብሮ ለመኖር የመረጠው ምድራዊ መቅደስ የእንስሳትን መሥዋዕት ያማከለ ነበር። ሆኖም አገልግሎቱ በእነዚህ ፍጥረታት ሞት አላበቃም። መሥዋዕት የሚሆነው እንስሳ ከተገደለ በኋላ ካህኑ ስለ ኃጢአተኛው በቤተ መቅደሱ የደም አገልግሎት ይሰጥ ነበር። ይህ ሁሉ ምድራዊ የቤተመቅደስ አግልግሎት ክርስቶስ ለዓለም የሚያደርገው ነገር ጥላ እና ምሣሌ ብቻ ነበር። ስለሆነም ጥላ የነበሩት (የቤተ መቅደሱ አገልግሎት) በእንስሳው ሞት እንዳላበቁ ሁሉ፤ በተመሳሳይ ክርስቶስ ለእኛ የሚሠራውም ሥራ በመስቀል ላይ ሞቱ አላበቃም።

ለዛሬ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እነዚህን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዕብ. 8፡ 1-6። በጥቅሶቹ እየተባለ ስላለው ነገርና ይህን ማወቃችን አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት ጌታ እንዲረዳዎ ይጠይቁት። በተጨማሪ ጥቅሶቹ አዲሱን ኪዳን ለማስተዋል እንዴት እንደሚረዱን ራስዎን ይጠይቁ።



በብሉይ ኪዳን ስር ምድራዊ መቅደስ፣ ክህነት እና አገልግሎት እንደነበረ ሁሉ በአዲሱ ቃል ኪዳን ደግሞ ሰማያዊ መቅደስ፣ ሰማያዊ ክህነት እና ሰማያዊ አገልግሎት አለ። በአሮጌው ኪዳን--ምሣሌና ጥላ (ዕብ. 8፡5) ብቻ የነበሩት፤ በአዲሱ ኪዳን ተጨባጭ እውነታ ሆኑ።

ደግሞም ስለ እኛ ምትክ የሚሆነው እንስሳ ሳይሆን፤ ይልቁንም ኃጢአት የሌለበት የሱስ አለን። ከእንስሳ ደም ይልቅ የክርስቶስ ደም አለን፣ “በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች፣ እውነተኛ ድንኳን ቤተ መቅደስ” (ዕብ. 8፡2) አለችን፣ ኃጢአተኛና ስህተት የማያጣው ሰብዓዊ ካህን ሳይሆን ስለ እኛ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ሊቀ ካህን የሱስ አለን። እነዚህን በልብዎ እንደያዙ ጳውሎስ እንደሚከተለው ስለ ጻፋቸው ቃላት ያስቡ፡ “እኛስ እንዲህ ያለውን ታላቅ ድነት ቸል ብንል እንዴት ልናመልጥ እንችላለን? (ዕብ. 8፡2)

የሱስ ለእርስዎ ሲል ኃጢአት ዐልባ ሕይወት ኖረ፣ ስለ እርስዎ ሞተ፣ አሁን ደግሞ በሰማያዊው መቅደስ ስለ እርስዎ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። ይህ ሁሉ የተደረገው እርስዎን ከአስፈሪው የኃጢአት የመጨረሻ ውጤት ለማዳን ሲባል ነው። በቀጣዮቹ ቀናት ይህን ግሩም የምሥራች መስማት ይኖርበታል ለሚሉት ሰው ለማጋራትና ለመወያየት እቅድ ያውጡ። በዛሬው ጥናት ላይ በመመርኮዝ ስለሚያካፍሉት ሀሳብ ከወዲሁ ይዘጋጁ።





ሰኔ 3
Jun 10

ሰማያዊ አገልግሎት (ዕብ. 9፡24)


ክርስቶስ ስለ እኛ ከተቀበለው መሥዋዕታዊ ሞት በኋላ እየሰጠ ካለው ሰማያዊ አገልግሎት ዐውድ--ይህን ጥቅስ፡ ዕብ. 9፡24 ያጥኑ። ምንም እንኳ ብዙ ማለት ቢቻልም፤ ክርስቶስ አሁን ለእኛ በእግዚአብሔር ፊት ተገልጧል በሚለው በስተ መጨረሻ የሚገኝ ሀረግ ላይ እናተኩራለን። ይህ ምን ማለት እንደሆነ ያስቡ። እኛ የወደቅን ኃጢአተኞች ነን፤ እኛ እግዚአብሔርን አሁን ብናይ ከክብሩ ነጸብራቅ የተነሣ እንጠፋለን፤ እኛ የቱንም ያህል መጥፎዎች የነበርን ወይም የእግዚአብሔርን ቅዱስ ሕግ በድፍረት የጣስን ብንሆንም--ስለ እኛ በእግዚአብሔር ፊት የሚታይ አለን። በእኛ ምትክ በአብ ፊት የሚቆም ተወካይ አለን። ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት ምን ያህል አፍቃሪ፣ ይቅር ባይና ሁሉን የሚቀበል እንደነበረ ያስቡ። ይኸው ሰው እነሆ አሁን በሰማይ አማላጃችን ነው? ይህ ሌላው የዚሁ መልካም የምሥራች ክፍል ነው። የሱስ የኃጢአታችንን መቀጮ ብቻ አልከፈለም። ነገር ግን በመስቀል ላይ ተሸከመው (1ጴጥ. 2፡24)። አሁን ግን በሰው እና በመለኮት መሃል የሰማይና የምድር አስታራቂ ሆኖ በእግዚአብሔር ፊት ቆሟል።

ይህ ፍጹም የሆነ ትርጉም ይሰጣል። አምላክ እና ሰው የሆነው የሱስ (ኃጢአት ዐልባው ፍጹም ሰው) በሰው እና በእግዚአብሔር መሀል ያለውን ክፍተት ድልድይ ሆኖ ማገናኘት የሚችል እርሱ ብቻ ነው። በዚህ ሁሉ ውስጥ ለማስታወስ ወሳኝ የሆነው ነጥብ፤ በማንኛውም ነገር እንደ እኛ የተፈተነና (ዕብ. 4፡14-15) ህመማችንን የሚያውቀው እርሱ እኛን በአብ ፊት እየወከለን የሚገኝ መሆኑ ነው። “አንድ እግዚአብሔር አለና፤ ደግሞም በእግዚአብሔርና በሰዎች መካከል አንድ አስታራቂ አለ፤ እርሱም ሰው የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ ራሱንም ለሰዎች ሁሉ ቤዛ አድርጎ ሰጠ፤ ይህም በትክክለኛው ጊዜ ተመስክሮለታል።” (1ጢሞቴ. 2፡5-6)። ጥቅሱ የሱስን በሁለት ሚናዎች ውስጥ ያስቀምጠዋል--ምንድን ናቸው? እነዚህ ሚናዎች በምድራዊው መቅደስ አገልግሎት ውስጥ ተለይተው ተቀምጠው የነበሩት እንዴት ነው?

ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞች ከየሱስ የተነሣ አሁን በአብ ፊት በሰማይ እየወከላቸው የሚገኝ መኖሩ የአዲሱ ቃል ኪዳን ታላቅ የምሥራች ነው። እነርሱ በራሳቸው ፈጽሞ ሊያገኙት የማይችሉትን ፍጹም ጽድቅ እና በእግዚአብሔር ፊት ሊቆም የሚችለውን ብቸኛ ጽድቅ አስገኝቶላቸዋል። የሱስ ሥቃይ ተቀብሎ ባስገኘው በዚያ ፍጹም ጽድቅ (ዕብ. 2፡10) የኃጢአት ይቅርታ እንድንቀበልና በኃጢአት ላይ ኃይል እንድናገኝ በእግዚአብሔር ፊት እየታየ ይገኛል። ያለዚህ አሁንም ሆነ በፍርድ ወቅት ተስፋ ባልኖረን ነበር።

በኃጢአት የመፈተን ተሞክሮ ያለው አንድ ሰው በሰማያዊው አምላክ ፊት በመቆሙ ጽንሰ ሀሳብ ዙሪያ ጸሎት እና ማሰላሰል ያድርጉ። ይህ ለእርስዎ በግልዎ ምን ማለት ነው? ምን ዓይነት ተስፋ እና ማበረታቻ ያመጣል?



ሰኔ 4
Jun 11


ተጨማሪ ሀሳብ


“ታላቅ የተባለ በሰማይ የሚገኝ መልአክ ለአንዲት የጠፋች ነፍስ ቤዛ የመሆን ኃይል አልነበረውም። ኪሩቤል እና ሱራፌል የእርሱ ፍጥረት እንደመሆናቸው የተሰጣቸው ክብር ብቻ ነው ያላቸው። በአምላክ እና በሰው መካከል የሚደረገው እርቅ ክንውን ማግኘት የሚችለው ከዘላለማዊው አምላክ ጋር እኩል በሆነው፣ ክብሩን በሚያንጸባርቁ እና ብቁ አድርገው በሚገልጹት ባህሪዎች ተካፋይ በሆነው፣ ሰውን በሚወክለው እና እግዚአብሔርን ለወደቀው ዓለም ለሚያሳየው አማላጅ ብቻ ነበር። እርሱ ከሚወክለው ሰብዓዊው ቤተሰብ ጋር ግንኙነት ለመመስረት እንደ እግዚአብሔር አምባሳደርነቱ መለኮታዊውን ተፈጥሮ መውሰድና ከዘላለማዊው ጋር ትስስር መፍጠር ነበረበት። እግዚአብሔርን ለዓለም ለማሳየትና በእግዚአብሔርና በሰው መካከል አማካይ ለመሆን የሰው ምትክ እና ዋስ-የሰው ተፈጥሮ ሊኖረው ይገባ ነበር።”—Ellen G. White, Selected Messages, book 1, p. 257.

“በመቀጠልም የሱስ በሰዎች ፊት ከመሰከራችሁልኝ እኔም በእግዚአብሔርና በቅዱሳን መላእክት ፊት እመሰክርላችኋለሁ አላቸው። እናንተ በምድር ላይ የእኔ ምስክሮችና ዓለምን የሚፈውሰው ጸጋዬ የሚተላለፍባችሁ መሣሪያዎቼ ናችሁ አለ። እንደዚሁም እኔ በሰማይ የእናንተ ወኪል ነኝ። አብ የሚያየው የረከሰ ባህሪያችሁን ሳይሆን የተጎናጸፋችሁትን የእኔን ፍጽምና ነው። የሰማይን በረከት የምታገኙት በእኔ አማካይነት ነው። እኔ ለጠፉት ነፍሳት የከፈልሁትን መሥዋዕትነት በማጋራት የሚመሰክርልኝ ሁሉ የዳኑት ነፍሳት የሚያገኙትን ክብርና ደስታ የሚጋራ መሆኑ ይመሰከርለታል” የዘመናት ምኖት ገጽ 361


የመወያያ ጥያቄዎች



1. ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሮሜ 5፡2፣ ኤፌ. 2፡18፣ ኤፌ. 3፡12። በየሱስ በኩል ወደ አብ መድረስ እንደምንችል እንድናስተውል እንዴት ይረዱናል?

2. ከላይ የቀረበውን ሁለተኛውን የኤለን ጂ. ኋይት ጥቅስ ይመልከቱ። የአማላጅነትን ሚና እንዴት እንደምትገልጽ ልብ ይበሉ። አብ ወደ እኛ ሲመለከት የክርስቶስን ፍጹም ባህሪ እንጂ የእኛን የተሳሳተ ማንነት አያይም። ይህ ምን ማለት እንደሆነ ጠለቅ ብለው ለመመልከት ይሞክሩ። በክፍል ውስጥም ተወያዩበት።

3. በዚህ ሣምንት ያጠናነውን በመመልከት፤ ይህን ጥያቄ እንዴት እንደሚመልሱ ራስዎን ይጠይቁ፡ “እሺ፤ ክርስቶስ የሚገኘው በሰማያዊው መቅደስ ውስጥ ነው። ከዛ ምን? ከየዕለቱ ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ ይህ ምን ማለት ነው?

ማጠቃለያ፡ የቀድሞው የብሉይ ኪዳን የመሥዋዕት ሥርዓት በአዲሱ ተተክቷል። በምድራዊው መቅደስ ውስጥ በኋጢአተኛ ካህናት እጆች በሚታረዱ እንስሶች ፋንታ፤ አሁን ፍጹም የሆነው መሥዋዕታችን የሱስ አለን። የአዲሱ ቃል ኪዳን እና የተስፋዎቹ መሠረት በሆነው፣ በሰማይ ባለው መቅደስ በአብ ፊት እኛን ይወክለናል።




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL