የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

በክርስቶስ ማረፍ


3ኛ ሩብ ዓመት 2021

ከሐምሌ 3 - 9

3ኛ ትምህርት

Jul 10–Jul 16




የመቅበዝበዝ ሥረ መሰረቶች



ሰንበት ከሰዓት

፡ ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ማቴ. 10:34–39፣ ሉቃ. 12:13–21፣ ፊልጵ. 2:5–8፣ ሉቃ. 22:14–30፣ ማቴ. 23:1–13።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “ቅናትና ራስ ወዳድነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ሥራ ሁሉ ይገኛሉ” ያዕ. 3፡16)።

አ ስፐን ቁመቱ ከ15 እስከ 30 ሜትር የሚደርስ ውብ ዛፍ ነው። ቅዝቃዜ ባለው የክረምት ወቅት ጥሩ ሆኖ ያብባል። እንጨቱ ለቤት ውስጥ ቁሳቁሶች እንዲሁም ለክብሪትና ወረቀት መሥሪያ ያገለግላል። ቅርፊቱ ብዙ ንጥረ ነገሮችን ስለሚይዝ ብዙውን ጊዜ አጋዘን እና ሌሎች እንስሳት በክረምቱ ወቅት የአስፐን ቁጥቋጦዎችን ይመገባሉ። ከፍ ያለ የፀሐይ ብርሃን አብልጦ የሚሻው አስፐን በክረምት ወራትም እንኳ ሳይቀር ያብባል። ይህ ደግሞ በቀዝቃዛው የክረምት ወራት ለተለያዩ እንስሳት በጣም አስፈላጊ የምግብ ምንጭ ያደርገዋል።

ይሁን እንጂ አስፐን በዕጸዋት ዓለም በጣም የሚታወቀው በረጃጅም ሥሮቹ ነው። ሥሮቹ ከመሬት በታች እርጥበት እየሳቡ እዚህም እዚያም በሚፈሉ ቀንበጦች የሚዛመት ሲሆን፤ በአንጻራዊ ሲታይ በቶሎ መሰራጨት የሚችልና ሰፋፊ አካባቢዎችን በቀላሉ የመሸፈን አቅም ያለው ነው። እያንዳንዱ የአስፐን ዛፍ እስከ 150 ዓመት ሊኖር ቢችልም፤ ከመሬት በታች የሚገኘው ትልቅ የሚባል ተህዋስ ግን በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት ሊኖር ይችላል።

በዚህ ሳምንት ጥናታችን ዕረፍት አልባ የሚያደርጉንን አንዳንድ ነገሮች ለመዳሰስ እንሞክራለን። በየሱስ እውነተኛ ዕረፍት እንዳናገኝ ሊከለክሉን የሚችሉ ብዙ ነገሮች አሉ። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ግልጽ በመሆናቸው ብዙ ትኩረት አያስፈልጋቸውም። ሌሎቹ ለእኛ እምብዛም ግልጽ ላይሆኑ ይችላሉ፤ እናም ከምድር በታች እንደማይታዩት ግዙፍ የአስፐን ተህዋስያን እኛም ከአዳኛችን ለሚለየን ዝንባሌ እና ድርጊት ሁሌም ንቁ ላንሆን እንችላለን።

ሐምሌ 4
Jul 11

የሱስ መከፋፈልን ይዞ መምጣቱ


በጣም ጥቂት ሰዎች በግጭት ቢደሰቱም አብዛኞቻችን ግን ስምምነትና ሰላም ለማግኘት እንጓጓለን። በቤተ ክርስቲያናችን ወይም በተቋሞቻችን ስለ ሰላም መስፈን እና ግጭት አፈታት ሴሚናሮችን እንሰጣለን። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማቴ. 10፡34-39። የሱስ ሰይፍ እንጂ ሰላም ለማስፈን እንዳልመጣ የመናገሩ ፍቺ ምንድን ነው? እርሱ “የሰላም አለቃ” (ኢሳ. 9፡26) ከመሆኑ አኳያ ይህ ምን ማለት ነው?



የሱስ በማቴ. 10፡34–39 የተናገረው ሐሳብ ውስጠ ወይራ እንደመሆኑ በቀላሉ አይስተዋልም። በብርቱ ጠባቂዎች እንደ ተከበበ ንጉሥ ሳይሆን፤ ረዳት አልባ ህፃን ሆኖ ወደዚህ ምድር በመምጣት ለወዳጅም ሆነ ለጠላት ፍቅር የሰበከው አዳኝ፤ አሁን ደግሞ መከፋፈል እና ትግል እንደሚያመጣ ለተከታዮቹ ሲነግር ይደመጣል። ደቀ መዛሙርቱ እና አድማጮቹ ልክ እንደ እኛ ሳይደነቁ አልቀሩም። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?

ማቴ. 10፡35-39 ስለ ወዳጅነት እና ታማኝነት መናገሩ እሙን ነው። የሱስ ሚክ. 7፡6 በመጥቀስ አድማጮቹ ዘላለማዊውን ምርጫ ያደርጉ ዘንድ ፈታኝ ምርጫ ያቀርብላቸዋል፡ ልጅ ወላጆቹን መውደድና ማክበር ይኖርበታል። ሙሴ በተራራው ላይ የተቀበለው ሕግ የሚጠይቀው ይህን ነበር። ይህ እግዚአብሔር የሚጠይቀው አሠራር የነበረ ቢሆንም፤ ነገር ግን ይህ መውደድ አድማጩ ለየሱስ የሚኖረውን ቁርጠኝነት እንዲያቃልል የሚያደርግ ከሆነ ከባድ ውሳኔ ማድረግ ይጠበቅበታል። አባት እና እናት ልጆቻቸውን መውደድ እና መንከባከብ አለባቸው። ሆኖም ይህ መውደዳቸው ለየሱስ ከሚኖራቸው ቁርጠኝነት የሚልቅ ከሆነ፤ አስቸጋሪ ውሳኔ እንዲያደርጉ ይጠየቃሉ። ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮች ቅድሚያ ሊያገኙ ይገባል ሲል የሱስ በጥቅሱ ያስገነዝበናል።

የሱስ ይህን ምርጫ የገለጸው ሦስት ዓረፍተ ነገሮችን በአንድ በመቀመር ሲሆን፤ እያንዳንዳቸው የከበረ የሚለውን ቃል ይዘዋል። የከበረ መሆን ከፍያለውን ሥነ ምግባራዊ ልዕልና መሠረት ያደረገ--አልፎ ተርፎም ኃጢአትን ማሸነፍ አይደለም። የከበረ መሆን ከየሱስ ጋር በሚኖር ግንኙነት ላይ የተመሠረተ ነው። እናትን፣ አባትን ወይም ልጆችን ጨምሮ ከሁሉም በላይ እርሱን ስንመርጥ የከበርን እንሆናለን። የመስቀሉን መከራ መርጠን የሱስን እንከተላለን። “ወጣቶቻችን መስቀሉን ተሸክመው የሱስን እንዲከተሉ በሚመራቸው በዚያ ንጹህ ኃይማኖታዊ መንፈስ ተሞልተው ከማየት የላቀ ምኞት የለኝም።

በመርኅ የሚመሩ ወጣት የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የንጽህና እና ጽድቅ ሸማ ለብሰው ወደፊት ይገስግሱ። አዳኛችሁ አብልጦ ለችሎታችሁ ተስማሚ ወደ ሆነውና የላቀ ጥቅም ወደምትሰጡበት ስፍራ ይመራችኋል።”—Ellen G. White, Testimonies for the Church, vol. 5, p. 87. አንዳንዴ በራሳችን ምርጫ ባይሆንም መስቀሉን ለመሸከም እንገደዳለን፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ፈቃደኞች ሆነን መስቀሉን እንሸከማለን። ያም ሆነ ይህ፣ መስቀሉን በታማኝነት የመሸከም ቁልፉ ምንድን ነው?

ሐምሌ 5
Jul 12

ራስ ወዳድነት


እንደ አስፐን እና ትልቁ የመሬት ውስጥ ሥርዓት ሁሉ--ራስ ወዳድነት በየሱስ እውነተኛ ዕረፍት እንዳናገኝ ጠፍንጎ የሚይዘን “ኃጢአት” ተብሎ የሚጠራው ግዙፉ የምድር ሥርዓት አካል ነው። በሕይወታችን ውስጥ ካሉ የኃጢአት መገለጫዎች ሁሉ በቀላሉ የሚታየው ራስ ወዳድነት ይመስላል--አይደል? ለብዙዎቻችን ራስ ወዳድነት ልክ እንደ እስትንፋስ ተፈጥሮአዊ ነው። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሉቃ. 12፡13-21። በየሱስ ምሳሌ በጉልህ የቀረበውን ችግር ይግለጹ። ስለ ወደፊት ማቀድ ራስ ወዳድነትና የእግዚአብሔርን መንግሥት ዝቅ አድርጎ መመልከት ነው? ካልሆነ ታዲያ የሱስ ስለ ምን እያስጠነቀቀን ነው?



ይህ ምሳሌያዊ ንግግር የሚገኘው በሉቃስ ወንጌል ብቻ ሲሆን ከአንድ ማንነቱ ያልተገለጸ አድማጭ ለቀረበ ጥያቄ የተሰጠ ምላሽ ነው። ውርስን አስመልክቶ ለተጠየቀው ጥያቄ በወንድማማቾች መካከል የፈራጅ ወይም ዳኝነት ሚና እንደሌለው በመግለጽ የሚመልሰው የሱስ፤ ይልቁንም በትልቁ መሰረታዊ ችግር ማለትም በራስ ወዳድነት ላይ ትኩረት ለማድረግ ይመርጣል። የግለሰባዊ እርምጃዎቻችንን ሥረ መሰረት ለማሳየት ጠለቅ ብሎ ይቆፍራል።

ስለ ገዛ ሕይወትዎ ራስ ወዳድ መገለጫዎች ያስቡ። ራስ ወዳድነት ከእግዚአብሔር፣ ከትዳር አጋራችን፣ ከቤተሰባችን፣ ከቤተ ክርስቲያን ቤተሰቦች፣ ከጎረቤቶቻችን እና ከሥራ ባልደረቦቻችን ጋር ያለንን ግንኙነት እንዴት ያቃውሳል? በፊልጵ. 2፡5-8 ውስጥ ምን ቁልፍ ነገር ይገኛል?



ይህ በራሱ ፍላጎቶች እና ምኞቶች ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገ ማንነቱ ያልተገለጸ ሀብታም ሰው የማይታዩትን ሰማያዊ እውነታዎች ከግምት ማስገባት ዘነጋ። ከፍ ያሉ፣ የተሻሉና የተከማቹ የሚመስሉ--የሰማያዊው መንግሥት መሠረት አይደሉም። የሱስ የእኛን ቦታ ለመውሰድ ምን እንዳነሳሳው ጳውሎስ ፍንጭ ይሰጠናል።

ፊልጵ. 2፡5-8 ራስ ወዳድ ያልሆነውንና ራሱን ዝቅ አድርጎ ያዋረደውን ፍቅር ንድፍ ይሰጠናል። ለእግዚአብሔርና ለሌሎች ያለን ፍቅር ምርጫዎቻችንን እና ቅድሚያ የምንሰጣቸውን ነገሮች መምራት ካልቻለ፤ በዚህ ምድር ለራሳችን ብዙ ጎተራዎችን መገንባታችንንና በመንግሥተ ሰማይ አነስተኛ ሀብት ማኖራችንን እንቀጥላለን (ማቴ. 6፡20)። በሀብት እና ቁሳዊ ንብረት ምኞት ለመውደቅ በጣም ቀላል የሆነው ለምንድነው? ምንም እንኳ ሁላችንም ለመኖር የተወሰነ ገንዘብ ቢያስፈልገንም፤ የቱንም ያህል ቢኖረን ሁሌም የበለጠ የምንሻው ለምን ይሆን?





ሐምሌ 6
Jul 13

የማያባራ ምኞት


የሱስ ከመሰቀሉ አስቀድሞ የነበረውን የመጨረሻውን ሣምንት የምድር አገልግሎቱን ማጥናት ሁሌም የመበረታቻና የመነሳሻ ምንጭ ነው። በተጨማሪ ዕረፍት ዐልባነትና የማያባራ ምኞት ሰዎችን እንዴት ከንቱ ወደሆነው ነገር እንደሚነዳ በጉልህ ያቀርባል። ጥቅሱን ያንብቡ፡ ሉቃ. 22፡14-30--እና ደቀ መዛሙርቱ በዚህ የተከበረ የጌታ እራት ወቅት ከመካከላቸው ማን እንደሚበልጥ አስመልክቶ በመካከላቸው የተነሳውን ክርክር ሲሰማ የሱስ ስለ ተሰማው ስሜት አስቡ (ሉቃስ 22፡24)። ደቀ መዛሙርቱ ለዚህ ወሳኝ ወቅት ሊሰጡ የሚገባቸውን ትኩረት ነፍገው ምልከታቸውን በሰው ታላቅነት ዙሪያ ለምን አደረጉ?



በቤተ ክርስቲያናችን፣ በቤተሰባችን ወይም በሥራ ቦታችን ትልቁን ስፍራ የሚይዘው ማን ነው--ብለን ከሌሎች ጋር በግልጽ ለመወያየት ባንደፍርም፤ ጉዳዩ አብልጦ ሳያብሰለስለን እንዳልቀረ ይገመታል። ይህ ጥያቄ በየሱስ ተከታዮች መሃል ሲነሳ ለመጀመሪያ ጊዜ አልነበረም። ደቀ መዛሙርቱ ጥያቄውን ይበልጥ በረቀቀ መንገድ አቀናብረው ወደ የሱስ ማቅረባቸውን ማቴ. 18፡1 ይዘግብልናል፡ “ ‘በመንግሥተ ሰማይ ከሁሉ የሚበልጥ ማን ነው?’ ” የየሱስ መልስ ተጨባጭ የሆነ ትምህርት ያካተተ ነበር።

አንድ ህጻን ጠርቶ በመካከላቸው አቆመ። ዐይኖቻቸው ፈጠጡ፣ ቅንድቦቻቸውም ቆሙ። የየሱስ ድርጊት ማብራሪያ ይሻ ስለነበር መምህሩ በማቴ. 18፡3 ይህንም ጨምሮ ሰጣቸው፡ “ ‘እውነት እላኋለሁ፣ ካልተለወጣችሁ እንደ ህፃናትም ካልሆናችሁ ፈጽሞ ወደ መንግሥተ ሰማያት አትገቡም።’ ” መለወጥ በየሱስ ውስጥ እውነተኛ ዕረፍት ማግኛ መሠረት ነው። ውጪያዊ ዕርዳታ እንደሚያስፈልገን እንገነዘባለን። እኛ በራሳችን መመካት እንደማንችል፤ ይልቁንም በየሱስ መታመን እንደሚያስፈልገን በድንገት እንገነዘባለን።

በእሴቶቻችን እና ምኞቶቻችን ዙሪያ ለውጥ እንለማመዳለን። የሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ ይላቸዋል፡ ልክ እንደዚህ ህፃን በእኔ እመኑ፣ ተመኩም። እውነተኛ ታላቅነት መብትን ትቶ ሰማያዊ እሴቶችን በደስታ መቀበል ነው። የሚያሳዝነው--የሱስ የመጨረሻውን የጌታ እራት አብሯቸው ይበላ በነበረበት ወቅት ደቀ መዛሙርቱ ይህን ትምህርት ገና ያልተማሩ ይመስላሉ። ንትርክና ውዝግባቸው ፈጽሞ ሊደገም የማይችለውን ያን ወደር የለሽ የአንድነት ጊዜ አበላሸው።

ለዓመታት ከየሱስ ጋር አገልግለው፣ እግሮቹ ስር ተቀምጠው ቃሉን ሰምተውና ተምረው ሲያበቁ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? ሰብዓዊው ልብ ምን ያህል ብልሹነትን የሙጥኝ እንደሚል የሚያሳይ እንዴት ያለ አሳዛኝ ምሳሌ ነው! የትዕይንቱን አዎንታዊ ጎን አስመልክቶ ሁሌም ስለማይለየን አምላካዊ ጸጋ ያስቡ። በየሱስ ተከታዮች መካከል ይህ አሳዛኝ ውይይት ቢኖርም ጌታ ግን ስለ እነርሱ ተስፋ አልቆረጠም። በኃጢአት እንደመውደቃችን ሁላችንም ራስን የማመጻደቅ ምኞት ሰለባዎች ከመሆናችን አኳያ፤ ትኩረታችንን በተሰቀለው የሱስ ላይ ማድረጋችን ብርቱ መፍትሔ የሚሆነን ለምንድን ነው?





ሐምሌ 7
Jul 14

ግብዝነት


ግብዝ ማለት ያልሆነውን ሆኖ ለመታየት የሚሞክር ሰው ነው። ቃሉ የሱስ የአይሁድ እምነት አመራር ማዕከላት የነበሩትን ጸሐፍት እና ፈሪሳውያን በይፋ ለማሳፈር ባደረገው ንግግር፣ ማለትም በማቴ. 23 ሰባት ጊዜ ጥቅም ላይ ውሏል (ማቴ. 23፡17፣ 14፣ 15፣ 23፣ 27፣ 29)። የሱስ ለአመንዝራዎች፣ ለቀረጥ ሰብሳቢዎች፣ ለዝሙት አዳሪዎች እንዲሁም ነፍሰ ገዳዮች እንኳ ሳይቀር ጸጋ እና ይቅርታ እንደሰጠ ወንጌል የሚያሳየን ሲሆን፤ ለግብዞች ያሳየው ርኅራኄ ግን አነስተኛ ነበር (ማቴ. 6፡2፣ 5፣ 16፣ ማቴ. 7፡5፣ ማቴ. 15፡7-9፣ ማቴ. 22፡ 18)። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማቴ. 23፡1-13 እና በየሱስ የተጠቀሱትን አራት ዋና ዋና የግብዝነት ባህሪያት ይዘርዝሩ።



የሱስ አራት ባህሪያትን ከፀሐፍት እና ፈሪሳውያን ጋር ያዛምዳል። ከክርስቶስ ልደት በኋላ ባለው አንደኛው ክፍለ ዘመን የአይሁድ እምነት--ፈሪሳውያን ወግ አጥባቂውን ኃይማኖታዊ አንጃ ይወክላሉ። በጽሑፍ ለተላለፈውና እና ለአፋዊ ሕጎች የተለየ ፍላጎት የነበራቸው ከመሆናቸው በተጨማሪ ለሜዳዊው የመንጻት ሥርዓት አጽንኦት ይሰጡ ነበር። ሌላው የአይሁድ ጎራ ሰዱቃውያን ሲሆኑ፤ እነዚህ ቡድኖች በአብዛኛው ሀብት ያላቸው መሪዎች ናቸው። ብዙውን ጊዜ ከልሂቃኑ ካህናዊ መደብ ጋር ትስስር ነበራቸው። ግሪክኛ የሚናገሩ እና የግሪክ ፍልስፍና ቤተኞች ስለ ነበሩ በመጨረሻው ፍርድ ወይም በሙታን ትንሣኤ አያምኑም ነበር። እነርሱን እንደ ሊበራሎች እንገልጻቸዋለን። እነዚህ ሁለቱም ቡድኖች ግብዝነት ያጠቃቸው ነበር። በምንናገረው ካልኖርን፣ የኃይማኖት መመዘኛዎችን በሌሎች ላይ እየጫንን እኛ ግን ሳናከብረው ራሳችንን ገለል ስናደርግ፣ ስለ ኃይማኖተኝነታችን ግለት ሌሎች እንዲያጨበጭቡልን ስንፈልግ፣ ለሰማያዊ አባታችን ብቻ የሚገባውን ክብርና እውቅና ስንሻ--በየሱስ አነጋገር መሠረት ግብዞች ተብለን እንጠራለን።

የሱስ የተናገራቸው ቃላት የቱንም ያህል ስለታማና ቀጥተኛ ቢሆኑም፤ ግብዝ ብሎ ለጠራቸው ሰዎች--ፍጹም ፍቅር እና ተቆርቋሪነት ነበረው። “የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው የሱስ ንግግሩን ሲያዳምጡ የነበሩትን ሰዎችና ቤተ መቅደሱን በትካዜ እየተመለከተ ሳለ በፊቱ ላይ መለኮታዊ ሐዘኔታ ይታይበት ነበር። ልቡ ከማዘኑ የተነሣ እየቃተተና እንባ እየተናነቀው ‘እየሩሳሌም፤ እየሩሳሌም ሆይ! አንቺ ነቢያትን የምትገድይ! ወደ አንቺ የተላኩትንም በድንጋይ የምትወግሪ! ዶሮ ጫጩቶቿን በክንፎችዋ ሥር እንደምትሰበስብ እኔም የአንቺን ልጆች በአንድነት ልሰበስብ ስንት ጊዜ ወደድሁ!’” የዘመናት ምኞት ገጽ 646።

የሱስ በዚህ ስፍራ በግልጽ ያወገዘው ዓይነት ግብዝ የኃይማኖት መሪ መሆን የሌለቦት ለምንድን ነው? ምናልባት እንዲህ ዓይነቱ ግብዝነት በውስጣችን ቢኖር እንዴት ማየት እንችላለን? እንዴትስ ማስወገድ እንችላለን?

ሐምሌ 8
Jul 15

ዕረፍት ዐልባነትን ከሥሩ ነቅሎ ማስወገድ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዮሐ. 14፡1-6። የራሳችንን አለመረጋጋት አስመልክቶ ልባችን እንዳይረበሽ ምን ማድረግ እንችላለን? መለያየትን፣ ራስ ወዳድነትን፣ የማያባራ ምኞትንና ግብዝነትን ማሸነፊያውና እውነተኛ ዕረፍት ማግኛው ቁልፉ ምንድን ነው?



መቅበዝበዝን ማሸነፊያው መንገድ የሚጀምረው ሁሌም ቢሆን በየሱስ ነው። እርሱ መንገድ፣ እውነት እና ሕይወት ነው። በመገናኛ ብዙሃን እንቶፈንቶ በተጨናነቀው ምድረ በዳ ዓለም ውስጥ ዓላማ የለሽ ሆነን ለምንባዝነው ለእኛ የሚበጀውን ትክክለኛውን አቅጣጫ ያውቃል። መለኮታዊው ሕግ ሰጪ እርሱ ራሱ እውነት እንደመሆኑ መንፈሱ ወደ እውነት ሁሉ ይመራናል (ዮሐ. 16፡ 13)። ስንጎዳ፣ ስንደክም፣ ስንዝል፣ ስንታመም እና ተስፋ ስንቆርጥ እርሱ-ሕይወት ነው።

በእርግጥ የተትረፈረፈ ሕይወት እንደሚሰጠን ቃል ገብቶልናል (ዮሐ. 10፡10)። ይህ ደግሞ ዘላለማዊ ቤታችንን እና ዘላለማዊ ሕይወታችንን የሚያካትት ቢሆንም፤ በዚህ ምድር ለየት ያለ ምርጥ ሕይወት ባለቤት መሆናችንንም ይጨምራል። ፈጣሪ አሁንም ቢሆን ሊታሰብ ከሚችለው በላይ አትረፍርፎ መስጠት ይችላል። “ልባችሁ አይታወክ” የተሰኘው አባባል በመጠባበቅ እንድንኖር የቀረበልን ግብዣ ነው። ስናዝንና ተስፋ አስቆራጭ ሁናቴ ላይ ስንወድቅ ቀና ሊያደርገንና ወደ ከፍታ ሊያወጣን ይቻለዋል። ከጽልመትና ኃጢአት ጋር ስንታገል፤ እርሱ በእኛ ውስጥ መልካም የሆነውን ሥራ የሚጀምር ብቻ ሳይሆን የሚጨርስም ጭምር ነው (ፊልጵ. 1፡6)።

የቱንም ዓይነት መጥፎ ነገሮች ቢደርሱም (አዎ፤ መጥፎ ነገሮች ሊደርሱ ይችላሉ) በየሱስ የተሰጠንን የተስፋ ቃል ይመልከቱ። ህመማችን፣ ዕረፍት አልባነታችን እና ሥቃያችን ለዘላለም የሚወገድበት መኖሪያ “ስፍራ” እነሆ እያዘጋጀልን ይገኛል። ማንም ብንሆን፣ ምንም ዓይነት የኋላ ታሪክ ቢኖረንና ወራዳ ማንነት ልንሸከም ብንችል እንኳ፤ ይህ ተስፋ በክርስቶስ የሱስ ለሁላችንም ተሰጥቷል።

ድካም፣ ጉዳት፣ ጉስቁልና እና አጠቃላይ የወደቀ ማንነት ችግር ቢኖርብንም፤ ዋናው ቁልፍ ነገር እንደሚቀበለን አውቀን ወደ እርሱ መምጣታችን ነው። ጸጋ ማለት ይኸው ነው። በእምነት የፈለግነውን እንደ ተሰጠን ማመናችን የግድ የሚሆነው ለምንድን ነው? ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኤር. 3፡22። እግዚአብሔር ምን እንድናደርግ ይጠይቀናል? በምላሹስ ምን ያደርግልናል?



የሱስ ስለተናገራቸው የሚከተሉት ቃላት ያስቡ፡ “ ‘ሄጄም ስፍራ ካዘጋጀሁላችሁ በኋላ፣ እኔ ባለሁበት እናንተም ከእኔ ጋር እንድትሆኑ ልወስዳችሁ ዳግመኛ እመጣለሁ’ ” (ዮሐ. 14፡3)። የዳግም ምጽአቱ የተስፋ ቃል ወሳኝ መሆኑን አስመልክቶ ይህ ምን ሊነግረን ይገባል? በተለይ ለእኛ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች (የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂዎች)-ይህ የዳግም ምጽአቱ የተስፋ ቃል የከበረ የሆነው ለምንድን ነው?

ሐምሌ 9
Jul 16


ተጨማሪ ሀሳብ


“እኔነትን ባማከለ ሕይወት ውስጥ ዕድገትም ሆነ ፍሬያማነት ሊኖር አይችልም። ክርስቶስን የግል አዳኝዎ አድርገው ከተቀበሉ ራስዎን መርሳትና ሌሎችን ለመርዳት መሞከር አለብዎት። ስለ ክርስቶስ ፍቅር ያውሩ፣ ስለ መልካምነቱም ይናገሩ። በፊትዎ የቀረበውን እያንዳንዱን ግዴታ ያከናውኑ። የነፍሶችን ሸክም በልብዎ ይሸከሙ፤ የጠፋውን ነፍስ ለማዳን አቅምዎ የፈቀደውን ሁሉ ከማድረግ አይቆጠቡ።

ራስ ወዳድ ያልሆነውን የፍቅር መንፈስ እና ሌሎችን የሚያገለግለውን የክርስቶስ መንፈስ ሲቀበሉ-ያድጋሉ፣ ፍሬም ያፈራሉ። የመንፈስ ጸጋ ፍሬ በባህሪዎ ያፈራል፣ እምነትዎ ይጨምራል፣ ጥልቅ ይሆናል፣ ፍቅርዎም ፍጹምነትን ይላበሳል። ንጹህ፣ ጻድቅና ተወዳጅ የሆነውን የክርስቶስ ምሳሌ አብልጠው ያንጸባርቃሉ።”— Ellen G. White, Christ’s Object Lessons, pp. 67, 68. በቤተክርስቲያን አባላት መካከል ያሉ ጉዳዮችን አስመልክቶ፡ “ጉዳዩ በሚመለከታቸው አካላት መካከል ለሰዓታት የዘለቀ ውይይት ቢካሄድም ጊዜያቸውን በከንቱ ከማባከን ውጪ ውጤት ላይ ላይደርሱ ይችላሉ… ትዕቢትንና ራስ ወዳድነትን ወደ ጎን የሚተዉ ቢሆን ኖሮ አምስት ደቂቃዎች አብዛኛዎቹን ችግሮች ያስወግዳሉ።”—Ellen G. White, Early Writings, p. 119


የመወያያ ጥያቄዎች



፡ 1.ራስ ወዳድነትን በተጨባጭ ማሸነፍ ስለሚያስችሉ መንዶች በክፍል ተወያዩ። እነዚህ ጽንሰ ሀሳቦች እውን ይሆኑ ዘንድ ተጠያቂነትን እንዴት ማስፈን ይቻላል?

2.ምኞት በተፈጥሮ መጥፎ አይደለም። ሆኖም ምኞት የሚያስከትለው የስግብግብነት ወጥመድ ውስጥ ሳንገባ ታላላቅ ነገሮችን ከእግዚአብሔር ተስፋ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

3.አጉል ምኞት፣ ግብዝነት፣ ራስ ወዳድነት ወይም ምቀኝነት ብዙውን ጊዜ በውጫዊ ሁኔታችን አይታዩብንም። ውጪያዊ ደግነት ማሳየቱን አብልጠን ተክነነዋል። ሆኖም ልክ እንደ አስፐን ዛፍ ግዙፉ የሥር ሥርዓት፣ እነዚህ ሁሉ አሉታዊ ባህሪያት በውጪ ከሚታየው ገጽታችን ስር አድብተው ይገኛሉ። በመንፈስ የሚመራ የባህሪ መለወጥ በተጨባጭ ሲታይ ምን ይመስላል? የመቅበዝበዝን ሥረ መሰረት አሸንፈን በየሱስ እውነተኛ ዕረፍት ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

4.በዳግም ምጽአቱ አስፈላጊነት ዙሪያ በሐሙስ ጥናት የመጨረሻ ክፍል በቀረበው ጥያቄ ላይ በቂ ምልከታ ያድርጉ። ለነገሩ ያለዚህ ምን ተስፋ ይኖረን ነበር? ዳግም ምጽአቱ ባይኖር--የክርስቶስ የመጀመሪያ ምጽአት ምን መልካም ነገር ሊያደርግልን ይችል ነበር?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL