የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

በክርስቶስ ማረፍ


3ኛ ሩብ ዓመት 2021

ከሐምሌ 17 - 23

5ኛ ትምህርት

Jul 24–Jul 30




“ወደ እኔ ኑ…”



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ማቴ. 11:20–30፣ ማቴ. 5:5፣ ዘዳ. 18:15፣ ገላ. 5:1፣ ዘፀ. 18:13–22፣ ገላ. 6:2.


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “‘እናንት ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ’ ” (ማቴ. 11:28)፡፡

እ ናንት ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ--ይህ በየሱስ የተሰጠን የተስፋ ቃል እንዴት እጹብ ድንቅና አስደናቂ ነው! ከሥራ ጋር ብቻም ባይሆን ነገር ግን ሕይወት ራሱ በሚያመጣው ከባድ ጫና፣ አልፎ አልፎም ቢሆን ከመካከላችን ብርቱ ሸክም ያልተሰማው ይኖር ይሆን? አዎ--የሱስ እየነገረን ያለው ይህንኑ ነው። በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እያለፍን እንደሆን የሚያውቀው እርሱ--እኛ እስከፈቀድንለት ድረስ ሊረዳን ይችላል።

ከዚያም ቀንበሩን እንድንሸከም ከነገረን በኋላ እንዲህ ይላል፡ “ ‘ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀላል ነውና’ ” (ማቴ. 11፡30)። በሌላ አነጋገር ሸከማችሁንና ቀንበራችሁን አራግፋችሁ (ለእኔ ሰጥታችሁ) በምትኩ የእኔን ውሰዱ፤ የእኔ ቀላል ነው--እያለን ነው። የሱስ እየተናረ ያለውን ቀሪ ክፍል እንዴት ማየት እንችላለን? ለነገሩ እኛ እየኖርን ያለነው እግዚአብሔር አዳምን፡ “ ‘እንጀራህን በፊትህ ላብ ትበላለህ’ ”(ዘፍ. 3፡19) ብሎ በነገረው ከኃጢአት በኋላ ባለው ዓለም ውስጥ ነው። በመሆኑም ጥሮ ግሮ እና ለመቋቋም በእጅጉ አዳጋች የሚመስለውን ቀንበር ተሸክሞ መኖር--ቢያንስ ምን ማለት እንደሆነ እናውቀዋለን።

ሐምሌ 18
Jul 25

“ ‘እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ’


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማቴ. 11፡20-28። የሱስ “ ‘እናንት ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ’ ” ብሎ የተናገረበት ዐውደ ሀሳብ ምንድን ነው? እንዴት ይህን ዕረፍት ይሰጠናል?



እንደ ሁላችን ሁሉ፤ የሱስም ያለ ዐውደ ሀሳብ አይናገርም። እርሱን ለመረዳት እየተናገረ ያለውን ሀሳብ የከበበውን ዐውደ ንባብ መረዳት ይኖርብናል-በተለይ የሱስን በተሳሳተ መንገድ ከመረዳት ለመቆጠብ። ማቴ. 11--በማቴዎስ ወንጌል አዲስ ምዕራፍ ከፋች ገጽታ ይዞ ቀርቦአል። የገሊላ ዋና ዋና ከተሞችን የሚያወግዙት መግለጫዎች በወንጌል ከሰሙት ሁሉ ቆምጨጭ ያሉ ናቸው። የሱስ ሞገስ ለማግኘት አላሸረገደም፣ መተላለፍን ሳይገስጽ አላለፈም፣ በማኅበረሰቡ ተቀባይነት ካልነበራቸው ሰዎች ጋር ግንኙነት ነበረው (ማቴ. 9፡9-13)፣ ኃጢአትን ይቅር ማለት መቻሉ በኃይማኖት መሪዎች ዐይን ነውርና የሚያስቆጣ ነበር።

በእርግጥ የሱስ በውግዘት የተሞሉ አንዳንድ ብርቱ ቃላቶችን ለሕዝቡ ተናግሯል። እንደውም (ዛሬም) የክፋት ስፍራ ተደርጎ ይታይ ከነበረው ሰዶም ጋር እንዲህ በማወዳደር ተናግሯል፡ “ ‘ስለዚህ እልሻለሁ፤ በፍርድ ቀን ከአንቺ ይልቅ ቅጣቱ ለሰዶም ይቀልላታል’ ” (ማቴ. 11፡24)። ውጥረቶች ቢያሻቀቡም--ነገር ግን በዚህ ሁሉ መሃል የሱስ ማርሽ ቀይሮ እውነተኛውን ዕረፍት ሰጠ። እርሱ ይህን ማድረግ ይችላል። ምክንያቱም እንዲህ ሲል ተናግሮአል። “ሁሉ ነገር ከአባቴ ተሰጥቶኛል፤ ከአብ ሌላ ወልድን የሚያውቅ የለም፤ ከወልድና ወልድ ራሱ ፈቅዶ ከሚገልጥላቸው ሌላ አብን የሚያውቅ የለም’ ” (ማቴ. 11፡27)። የየሱስ ዕረፍት የመስጠት ችሎታ በመለኮታዊነቱ እና ከአብ ጋር ባለው አንድነት ላይ የተመሠረተ ነው።

ሸክሞቻችንን ለማራገፍ ከመምጣታችን አስቀድሞ ብቻችንን ልንሸከማቸው እንደማንችል መገንዘብ ይኖርብናል። እንዲያውም እውነተኛ ሁኔታችንን ካልተገነዘብን በቀር አብዛኞቻችን ልንመጣ አንችልም። የየሱስ ግብዣ በፍላጎት ላይ የተመሠረተ ነው። በማቴ. 11፡28 የተናገረው ሀሳብ የሚጀምረው መልእክቱ በመጀመሪያ በተጻፈበት የግሪክኛው ትእዛዛዊ ጽሑፍ ነው። “ ‘ኑ’ ” የሚለው ቃል በአማራጭነት የቀረበ አይደለም። ይልቁንም ዕረፍት የማግኘት ቅድመ ሁኔታን ይወክላል። “ ‘ኑ’ ”--ራሳችንን በቁጥጥሩ ስር ማዋል ያስፈልገናል የሚል አንደምታ አለው። ስማርት ስልኮቻችንን ተጠቅመን አያሌ ነገሮችን በበቂ ሁኔታ መቆጣጠር በምንችልበት በዚህ ወቅት ወደ የሱስ መምጣት ተፈጥሮአዊ አቅጣጫ አይሆንም። ራስን አሳልፎ መስጠት ወይም ማስገዛት ከባዱ የክርስትና ሕይወት ክፍል መሆኑ እሙን ነው።

እኛ እግዚአብሔር በክርስቶስ ስላደረገልን ነገሮች እንዲሁም እንዴት ራሳችንንና ሌሎችን ማዳን እንደማንችል ማውራት ይቀናናል። ይህ ሁሉ እውነት ነው። ይሁን እንጂ በመጨረሻ፣ ወደ የሱስ ለመምጣት ይኸውም ራሳችንን ለእርሱ ለማስገዛት በግንዛቤ ላይ የተመሠረተ ምርጫ ማድረግ ይኖርብናል። የመምረጥ ነፃነት በክርስትና ሕይወት ውስጥ ግንባር ቀደምና ማዕከል የሚሆነው በዚህ ቦታ ላይ ነው። ሸክሞችዎ ምንድን ናቸው? ሸክሞችዎን ለየሱስ በመስጠትና ብዙ ዋጋ ያስከፈለውን ያን እርሱ የሚሰጠውን ዕረፍት እንዴት መለማመድ ይችላሉ?

ሐምሌ 19
Jul 26

“‘ቀንበሬን ተሸከሙ’”


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማቴ. 11፡29-30። የሱስ ሸክማችንን እንድንሰጠውና እውነተኛ ዕረፍት እንድናገኝ ከጋበዘን በኋላ ቀንበሩን እንድንሸከም ያዘዘን ለምንድን ነው?



በማቴ. 11፡28 ከቀረበው የመጀመሪያ “ ‘ኑ’ ” ወሳኝ ቃል በኋላ ሁለት ተጨማሪ በጣም አስፈላጊ ቃላት ጥቅሱን ተከትለው ቀርበዋል። “ ‘ተሸከሙ’ ” እና “ ‘ተማሩ’ ” የአድማጮች (የአንባቢዎች) ትኩረት በየሱስ ላይ እንዲሆን ያደርጋሉ። ቀንበሩን ልንሸከምና ከእርሱ ልንማር ይገባል። በአብ እና በወልድ መካከል ያለው መለኮታዊ የጠበቀ ግንኙነት (ማቴ. 11፡2527) በእነዚህ ጥቅሶች ላይ የሚገኘውን የቀንበር ዘይቤ ለመግለጽ የሚያስችል ጠንካራ ምሳሌ ይዟል። አብም ሆነ ወልድ የሰው ልጆችን ለማዳን በአንድነት እየሠሩ ይገኛሉ። ቀንበር የመገዛት ተምሳሌት ቢሆንም (ኤር. 27) የተባበረ ዓላማን የሚያሳይ ተምሳሌትም ነው። ለቀንበሩ እየተገዛን በዙሪያችን ያሉትን ለመባረክ የሚሰጠንን ሥራ እንቀበላለን። እኛ የእርሱን ቀንበር አንሸከምም፤ ምክንያቱም ቀንበሩ “ ‘ልዝብ’ ” ሸክሙም “ ‘ቀላል’ ” (ማቴ. 11፡30) ነውና።

“ ‘ከእኔም ተማሩ’ ” በሚል የቀረበው ሁለተኛው ቁልፍ ነጥብ ይህንኑ ጽንሰ ሀሳብ ይደግማል። በግሪክኛ “መማር” የሚለው ግስ “ደቀ መዝሙር” ከሚለው ቃል ጋር ተዛማጅ ነው። ከየሱስ ስንማር በእርግጥም የእርሱ ደቀ መዛሙርት ነን። ታዛዥነት እና ቁርጠኝነት የደቀ መዝሙርነት ባህሪያት ናቸው። ሸክም የከበደው (ማቴ. 11፡28) በመሆን እና የእርሱን ቀንበር በመሸከም (ማቴ. 11፡29) መሃል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?



ቀንበር ከሕጉ ጋር በተያያዘ በአይሁድ እምነት የተለመደ ዘይቤ ነበር። ለምሳሌ ሐዋ. 15፡10 የግርዘትን ሕግ ሲያመለክት--ገላ. 5፡1 ደግሞ የሱስ የሚሰጠውን ነፃነት ከባርነት ቀንበር ጋር በማነጻጸር ሲያቀርብ ይታያል። ከየሱስ ጋር መጠመድ--ዱካውን በመከተልና በተልዕኮው ለመሳተፍ ለሚኖር ታዛዥነትና ቁርጠኝነት አጽንኦት ይሰጣል። የሱስ በመስቀል ላይ አሸናፊዎች ባደረገን የደኅንነት ሥራ ላይ አንዳች ነገር ለመጨመር ባይዳዳንም፤ የእርሱ አምባሳደሮች ሆነን በዙሪያችን ላሉ ወገኖች የምሥራቹን ማካፈል ግን እንችላለን። በተራራው ስብከት (ማቴ. 5–7) እንደተገለጸው--የሱስ ስለ ሕጉ የሰጠው ፍቺ ፈሪሳውያን ከሰጡት ይበልጥ ሥር ነቀል ነው። የልብ ቀዶ ጥገና ማድረግና አመለካከታችንን መቀየር ይፈለግብናል። የእርሱ ቀንበር ልዝብ ሸክሙም ቀላል ነው (ማቴ. 11፡ 30)።

እንዴት ያለ አስደናቂ ተስፋ ነው! እነሆ ለነፍሳችሁ እረፍት ታገኛላችሁ። እርስዎ በዚህ ዕረፍት ዙሪያ ያሎትን ተሞክሮ እንዴት ይገልጹታል? ምን ይመስላል? በየሱስ እና እርሱ በሚሰጠን ዕረፍት ላይ በማተኮር ያን ዕረፍት ማወቅ የምንጀምረው እንዴት ነው?

ሐምሌ 20
Jul 27

“ ‘እኔ በልቤ የዋህና ትሑት ነኝና’ ”


የዋህነት ዛሬ ዝቅተኛ ግምት የሚሰጠው ባህሪ ነው። ትህትና ወይም ገርነት ደግሞ መሳለቂያ ነው። ማኅበራዊ ሚዲያዎች ለሚጮኸው፣ ለሚለፈልፈው፣ ዕንግዳና አውሬ ለሆነው እንዲሁም ለብልጭልጩ ትኩረት እንድንሰጥ አስተምረውናል። እንደ እውነቱ ከሆነ ዓለም እንደ አቋም ከያዛቸው አመለካከቶች ውስጥ አብዛኞቹ እግዚአብሔር አስፈላጊና ዋጋ አላቸው ብሎ ካስቀመጣቸው በእጅጉ ተቃራኒ ናቸው።

“የእውነት ዕውቀት በዓላማ ንጽህናና ቅንነት ላይ መተማመን ያደርጋል እንጂ በማሰብ ችሎታ ጥንካሬ ላይ አጥብቆ አይመካም። ልቦቻቸውን ትሑት አድርገው መለኮታዊ መመሪያ ለመቀበል የሚሹትን የእግዚአብሔር መላእክት ይቀርቧቸዋል። የተትረፈረፈውን የእውነት ሐብት ይከፍትላቸው ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ይሰጣቸዋል።”—Ellen G. White, Christ’s Object Lessons, p. 59 ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማቴ. 5፡5፣ 1ጴጥ. 3፡4፣ ኢሳ. 57፡ 15። የዋህነትንና ትህትናን በእነዚህ ጥቅሶች መሠረት እንዴት ይገልጹአቸዋል?



ጳውሎስ በ2ቆሮ. 10፡1 ስለ “ክርስቶስ የዋህነትና ገርነት” ይጠቅሳል። የዋህነትና ገርነት በአቋማቸው ጸንተው መቆም የማይችሉ ሰዎችን የሚገልጡ አይደሉም። የሱስ ራሱ ተልዕኮው ገና ስላልተገባደደ ግጭት ሊያስከተል ከሚችል ማንኛውም ውዝግብ ራሱን ገሸሽ ያደርግ ነበር (ዮሐ. 4፡1-3)። ሆኖም እንዲህ ያለው ጉዳይ በቀጥታ ወደ እርሱ ሲመጣ ግን በድፍረት ይመልስ ነበር--ደግነት በተሞላው ድፍረት። ለምሳሌ ከመስቀል ጥቂት ቀደም ብሎ ስለ የሩሳሌም ማንባቱ መራገሙ ሳይሆን በእንባ በተሞሉ ቃላት ወደፊት የሚመጣውን ውድመት ማመላከቱ ነበር (ሉቃ. 19፡41-44)።

በአዲስ ኪዳን የሱስ ብዙ ጊዜ እንደ ሁለተኛው ሙሴ ተገልጧል። በተራራ ላይ ሆኖ የመንግሥቱን መርኅዎች ለሕዝብ አቅርቧል ማቴ. 14፡13-21)። ዘኍልቍ 12፡3 ሙሴን “ትሑት” ሲል የሚገልጠው ሲሆን ይኸው ቃል በማቴ. 11፡29 ሲያስተጋባ ይስተዋላል። የሱስ 5,000 ሕዝብ ሲመግብ እማኝ የሆኑ ሰዎች፡ “ ‘ወደ ዓለም የሚመጣው ነቢይ በእርግጥ ይህ ነው’ ” (ዮሐ. 6፡14) ማለታቸው--የዘዳ. 18፡15 እና የሙሴ ነቢይነት ሚና ማመሳከሪያ ነው። የየሱስ ትሕትና እና የዋህነት ከሙሴ የሚልቅ መሆኑ በግልጽ የሚታይ ነው። ደግሞስ እርሱ መለኮታዊ አዳኛችን አይደል! ሙሴ ሕዝቡ ይድን ዘንድ ራሱን መሥዋእት አድርጎ ቢሰጥ (ዘፀ. 32፡32) የእርሱ ሞት ምንም ውጤት ማምጣት አይችልም--ምክንያቱም እርሱ ራሱ ኃጢአተኛ እንደመሆኑ፣ በደሉን የሚከፍል ኃጢአት ተሸካሚ አዳኝ ያስፈልገው ነበር። ከሙሴና ከሕይወት ታሪኩ ትምህርት መቅሰም ብንችልም--ደኅንነት ማግኘት ግን አይታሰብም።

ከዚህ ይልቅ እንደ አማላጅ ሳይሆን እንደ ምትክ ሆኖ ሊቆምልን የሚችል አዳኝ ያስፈልገናል። አማላጅነት አስፈላጊ ቢሆንም ነገር ግን የኃጢአታችን ተሸካሚ ሆኖ በመስቀል ላይ የተቸነከረ፣ የኃጢአታችንን ቅጣት በራሱ የከፈለ እና ኃጢአታችን ከሚያስከትለው የሕግ ጥያቄ ሊያድነን የሚችል መለኮታዊ ባህሪ ያለው እርሱ ብቻ ነው። የሱስ ለእኛ ያሳየው ምሳሌነት የቱንም ያህል ታላቅ ቢሆንም ነገር ግን ያለ መስቀሉ እና ትንሣኤው ምንም የሆነው ለዚህ ነው።

ሐምሌ 21
Jul 28

“ ‘ቀንበሬ ልዝብ’ ” ነውና


ማቴዎስ በዚህ ክፍል “ቀንበር” የተሰኘውን ቃል ጥቅም ላይ ያዋለው--የአይሁድ እምነት እና ሌሎች የአዲስ ኪዳን ጥቅሶች ስለ ሕጉ ያላቸውን የተሳሳተ ግንዛቤ ለማስተጋባት እንደሆነ ቀደም ብለን አስተውለናል። በማቴ. 11፡30 “ልዝብ” ወይም “ ‘ቀላል’ ” በሚል የተተረጎመው ቃል--“ጥሩ”፣ “ደስ የሚያሰኝ”፣ “ጠቃሚ”፣ “ደግ” ተብሎ ሊተረጎምም ይችላል። በዙሪያችን ያሉ ብዙ ሰዎች የእግዚአብሔርን ሕግ እንደ ከባድ ሸክም፣ ለማክበር አስቸጋሪ እንደሆነና አንዳንድ ጊዜም ምንም ጥቅም እንደሌለው አድርገው ይቆጥሩታል። እነዚህ ወገኖች ሕጉ ምን ያህል ውብ መሆኑን እንዲገነዘቡና በሕግ ሰጪው ላይ ፍቅር እንዲያድርባቸው መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?



ወላጆች የጨቅላ ልጃቸውን የመጀመሪያ እርምጃ ሁሌም ያስታውሳሉ። የሚውተረተር የመጀመሪያ እርምጃ ላይ ሁለተኛው ይከተላል፣ ከዚያም ሦስተኛው፣ ሲቀጥል ባብዛኛው እንደሚስተዋለው ትንሽ መንገዳገድ፣ አሁንም መንገዳገድ ከዚያ… ዱብ! ይህን ተከትሎ ማልቀስ ከዚያም አለፍ ሲል ጥቂት ቁስለት ሊገጥም ይችላል። ነገር ግን ህፃኑ አንዴ የመንቀሳቀስ ስሜት ከተሰማው ብድግ ብሎ እንደገና መሞከሩን ይቀጥላል። መራመድ፣ መውደቅ፣ መነሣት፣ መራመድ፣ መውደቅ፣ መነሣት። ህፃናት አስተማማኝ በሆነ መንገድ መራመድ ከመጀመራቸው በፊት ይህን ቅደም ተከተል ብዙ ጊዜ ይደጋገማሉ። ሆኖም በመንገዳገድና መውደቅ መካከል፡ አባባ፣ እማማ--መራመድ እችላለሁ! የሚል ድምጸት ያለው አንድ ኩሩ፣ የድል አድራጊነት ትንሽዬ ገጽታ ይታይባቸዋል።

ከየሱስ ጋር መራመድ ሁሌም ቀላል ላይሆን ይችላል። ነገር ግን ሁል ጊዜ መደረግ ያለበት፣ መልካምና ትክክለኛ ነገር ነው። እንሰናከል ይሆናል፤ እንዲያውም ልንወድቅ እንችላለን። ይህም ቢሆን ከወደቅንበት ልንነሣ እና ከጎናችን ካለው ከእርሱ ጋር መጓዛችንን መቀጠል እንችላለን። ጳውሎስ በገላ. 5፡1 የሚከተለውን ጽፏል፡ “ክርስቶስ ነጻ ያወጣን በነጻነት እንድንኖር ነው። ስለዚህ ጸንታችሁ ቁሙ፤ ዳግመኛም በባርነት ቀንበር አትጠመዱ።” ይህ ምን ማለት ነው? ክርስቶስ እኛን ነጻ ያወጣን እንዴት ነው? ክርስቶስ እንድንሸከም በሚጠይቀን ቀንበር እና ጳውሎስ በሚያስጠነቅቀን “የባርነት ቀንበር” መካከል ያለው ልዩነት ምንድነው?



ጳውሎስ “የባርነት ቀንበር” ብሎ የተናገረበት መንገድ ምንም ይሁን ምን አምላካዊውን ሕግ ማለትም አሥርቱን ትእዛዛት መታዘዝን ማመልከቱ እንዳልሆነ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። በተቃራኒው ደኅንነታችን አስተማማኝ ሆኖ የተዋቀረው በእምነት ይኸውም እርሱን በመታዘዛችን መሆኑን እንረዳለን። ሕጉን መሠረት ባደረገ ሳይሆን እኛን በሚሸፍነን የክርስቶስ ጽድቅ። ይህ የእውነተኛ ዕረፍት እና ነጻነት ባለቤት እንድንሆን ያስችለናል። አምላካዊውን ሕግ እየታዘዙ መኖር ሕጉን ከመጣስ የላቀ ዕረፍት የሚሰጠው ለምንድን ነው?





ሐምሌ 22
Jul 29

“ ‘ቀንበሬ ቀላል’ ” ነውና


የሱስ በማቴ. 11፡30 የተናገረው የመጨረሻ ሐሳብ ሸክም የመሸከምን ገጽታ ይሰጣል፡ “ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀላል ነውና።” እስራኤላውያን ከግብፅ ወጥተው ባሕሩን ከተሻገሩ በኋላ ሙሴ አማቱን ዮቶር በማየቱ ተደስቶ ነበር። ጥቅሶቹን ያንብቡ ዘፀ. 18፡ 13-22። በዚህ ታሪክ የሌላውን ሸክም መሸከም ያለው አንደምታ ምን ይመስላል?



ሕዝቡ ፍርድ ፍለጋ ከጠዋት አንስቶ እስከ ማታ ወደ ሙሴ ይመጣ እንደ ነበር ዘፀ. 18፡13 ይነግረናል። የሙሴ አማት ይህን ሲመለከት፤ ሙሴ ትኩረቱን ከፍ ባሉ ጉዳዮች ላይ እንዲያደርግና ሌሎች የታመኑ ሰዎች ቀላሉን ጉዳይ የሚዳኙበት መዋቅር እንዲያቋቁም አጥብቆ ተማጸነው። ሙሴ የዮቶርን ምክረ ሀሳብ ሰምቶ እነዚያን ሕይወት ሰጭ ለውጦች ተግባራዊ ማድረጉን ቅዱሳት መጻሕፍት ይነግሩናል።

የሱስ የእርሱ ሸክም ቀላል መሆኑን ሲነግረን፣ የመጨረሻውን ሸክም በሚወስደው በእርሱ መታመን እንደምንችል ሊያስታውሰን ፈልጓል። እኛም ልክ እንደ ሙሴ ሸክማችንን የሚጋሩ ሌሎች እንደሚያስፈልጉን መማር አለብን። ጳውሎስ የክርስቶስን አካል ምሳሌ አድርጎ ባቀረበበት በ1ቆሮ. 12፡ 12-26 መልእክቱ--አንዱ የሌላውን ሸክም ስለ መጋራቱ አንደምታ ጥሩ ምሳሌ ይሰጠናል። ማንኛውንም ሸክም ለመሸከም ብቁ አካል ሊኖረን ይገባል። እግር፣ እጅ፣ ትከሻ፣ ጡንቻ፣ ጅማት መኖሩ ወሳኝ ነው።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ገላ. 6፡2። አንዳችን የሌላውን ሸክም መሸከማችን የክርስቶስን ሕግ ለመፈጸም እንዴት ይረዳናል?



የዚህ ጥቅስ ቀጥተኛ ዐውደ ንባብ አንዳች እገዛ ሊያበረክት ይችላል። አንድ ሰው በፈተና ቢወድቅ ያንን ሰው በገርነት መንፈስ መመለስ እንዳለብን ገላ. 6፡1 ይነግረናል (በማቴ. 11፡29 የሱስ የዋህና ትሑት እንደሆነ የተናገረውን ያስታውሱ) ። የሌላውን ሸክም መሸከም ማለት፣ አንድ ከመስመር የወጣ ግለሰብ መለኮታዊውን ጸጋ እንዲያይ በመርዳት መልሶ ማቋቋም ነው።

በተጨማሪ መከራ ሲደርስ እርስ በርስ መረዳዳት ማለት ነው። “ሸክም” በሚል የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ከባድ ክብደትን ወይም ድንጋይን ሊያመለክት ይችላል። ቃሉ ሁላችንም ሸክሞች እንዳሉብንና ሸክማችንን በመሸከም ሊረዱን የሚችሉ ወገኖች እንደሚያስፈልጉን ይጠቁማል። ሸክም መጋራት የዋህነትንና ትሕትና የሚጠይቅ በመለኮት የተደነገገችው ቤተክርስቲያን ተግባር ነው። ክፉኛ ሲደቁሶት የነበረውን ሸክም ስለ ተሸከመሎት ሰው ያስቡ። ያ ለእርስዎ ትልቅ ትርጉም የነበረው ለምንድን ነው? አሁን እርስዎ የማንን ሸክም በመሸከም ሊረዱ ይችላሉ?





ሐምሌ 23
Jul 30


ተጨማሪ ሀሳብ


“የሚሠሩት ሥራ ሲጠነክርብዎ፣ ስለ ደረሰብዎ ችግርና ፈተና ሲያጉረመርሙ፣ ፈተናን መቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ እንደሌሎት ሲናገሩ፣ በትዕግሥት ማለፍ ሲሳኖት እና በክርስትና ሕይወት መመላለስ ዳገት ሲሆንብዎ--የሌላውን ጌታ ቀንበር ተሸክመዋል ማለት ነው።”—Ellen G. White, Child Guidance, p. 267 “ዘወትር ነቅቶ መጠባበቅ፣ ከልብ የመነጨና በፍቅር የተሞላ አምልኮ ማድረግ ያስፈልጋል። ነፍስ በእምነት በእግዚአብሔር ኃይል ስትጠበቅ እነዚህ በተፈጥሮ ይመጣሉ። ለራሳችን ከፍ ያለውን ስፍራ በመስጠት አምላካዊውን ሞገስ ለማግኘት የምናደረገው ጥረት ከከንቱም ከንቱ ነው። በራሳችንም ሆነ በመልካም ሥራዎቻችን ላይ ፈጽሞ መታመን የለብንም። ነገር ግን እንደሚሳሳትና ኃጢአተኛ ፍጥረትነታችን ወደ ክርስቶስ ስንመጣ፣ በእርሱ ፍቅር ዕረፍት ማግኘት እንችላለን። በተሰቀለው ጌታ መልካም ሥራ ሙሉ ለሙሉ ታምነው ወደ እርሱ የሚመጡትን ሁሉ እግዚአብሔር ይቀበላቸዋል።

ፍቅር ከልባቸው ማህደር ይመነጫል። ምንም ዓይነት የፍንደቃ ስሜት ላይኖር ቢችልም ነገር ግን አምላካዊው አብሮነትና ሰላማዊ መታመን አለ። ክርስቶስ የሚጭነው ቀንበር ቀላል እንደመሆኑ እያንዳንዱ ሸክም ቀሊል ነው። የየዕለቱ ተግባር አስደሳች፣ የሚከፈለው መሥዋዕትነት ደግሞ ደስታ የሚሰጥ ይሆናል። ቀደም ሲል በጨለማ የተሸፈነ ይመስል የነበረው መንገድ ከጽድቅ ፀሐይ በሚወጡ የብርሃን ጨረሮች ብሩህ ይሆናል። ይህ እንግዲህ በብርሃን ውስጥ ካለው ክርስቶስ ጋር መመላለስ ነው።”—Ellen G. White, Faith and Works, pp. 38, 39.


የመወያያ ጥያቄዎች



፡ 1.ከየሱስ ጋር በነበሮት ጉዞ በመጨረሻ እንዴት እጆን እንደ ሰጡ ትዝ ይሎታል? ይህን ክስተት ለሰንበት ትምህርት ጥናት ቡድን አባላት ያካፍሉ። በተለይ ራሶን ለእርሱ ባስገዙበት ምክንያት ዙሪያ ትኩረት ያድርጉ።

2.በማቴ. 11፡25-27 የቀረበውን የየሱስ ጸሎት ያጥኑና እንዴት የጸጋ ዕውቀት ማግኘት እንደምንችል በክፍል ተወያዩ። እግዚአብሔር የመዳንን ዕቅድ (“እነዚህ ነገሮች”) ከጥበበኞች እና አስተዋዮች ሰውሮ ለህፃናት የሚገልጠው ለምንድን ነው?

3.ከሸክማቸው ጋር እየታገሉ ያሉ በዙሪያችን ያሉ ሰዎች ወደ የሱስ መጥተው ዕረፍት እንዲያገኙ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?

4.“የዋህ እና ትሑት” በሚለው ጽንሰ ሀሳብ ላይ በቂ ትኩረት ያድርጉ። አንድ ሰው ለራሱ ከፍ ያለ ግምት መስጠቱ ምን ያህል መጥፎ ነው? ስለ ራሳችን ጥሩ ስሜት ሊሰማን አይገባም? በተለይ በራሱ ላይ እምነት መጣል ያልቻለ ሰው ከሚያደርገው ግላዊ ትግል አኳያስ? የሱስ “የዋህ እና ትሑት” ስለ መሆን የተናገረውን ጽንሰ ሀሳብ ማስተዋል እንድንችል መስቀሉና መስቀሉ የሚወክለው ነገር እንዴት ይረዳናል? ይኸውም የዋህነት እና ትሕትና በመስቀሉ ፊት ብቸኛ ተጨባጭና ተገቢ ባህሪያት መሆን የቻሉት ለምንድን ነው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL