የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

በክርስቶስ ማረፍ


3ኛ ሩብ ዓመት 2021

ከሐምሌ 24 - 30

6ኛ ትምህርት

Jul 31–Aug 6




በቤተሰባዊ ትስስር ውስጥ ዕረፍት ማግኘት



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘፍ. 34፣ ዕብ. 11:17–22፣ ዘዳ. 4:29፣ 1ዮሐ. 3:1-2፣ ዘፍ. 39፣ ኤፌ. 6:1–13።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ ”እንግዲህ ወዳጆች ሆይ፤ ይህን አስቀድማችሁ ስላወቃችሁ፣ ጸንታችሁ ከቆማችሁበት መሠረት በዐመፀኞች ስሕተት ተስባችሁ እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ። ነገር ግን በጌታችንና በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ዕውቀት እደጉ፤ ለእርሱ አሁንም፣ ለዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።” (2ጴጥ. 3፡17)።

ብ ላቴናው አድማሱን በጥንቃቄ ቃኘ። እናም በመጨረሻ አያቸው። ወንድሞቹን ለብዙ ቀናት ሲፈልግ ከርሟል። እጆቹን እያወዛወዘና እየተጣራ እየቀረባቸው ሲመጣ እነዚያ አስፈሪ ገጽታ የተላበሱ ስብስቦች ሞቅ ያለ አቀባበል አደረጉለት። የገዛ ወንድሞቹ በእርግጠኝነት ሊገድሉት ፈልገዋል። ሮቤል የተለየ ሀሳብ ባያመነጭ ኖሮ ስለ ብላቴናው የሚነገር አንዳችም ታሪክ ባልኖረ ነበር። ሮቤል ጥቂት አንገላትተው ወደ ደረቅ የውሃ ጉድጓድ ውስጥ እንዲጥሉት አሳመናቸው። በመቀጠል ይሁዳ እርሱን ለማስወገድ የሚያስችል የላቀ ዕቅድ ይዞ ከተፍ አለ--ብላቴናውን ለመንገደኛ ባሪያ ፈንጋዮች ሸጦ ገንዘብ ማግኘት! የከሸፈ ዓይነት አባላት የሚገኙበትን ቤተሰባዊ ሁናቴ የሚያሳይ እንዴት ያለ ብርቱ ምሳሌ ነው!

በሕይወታችን አያሌ ነገሮችን መምረጥ ብንችልም--ነገር ግን ይኸ ው ምርጫችን ቤተሰባችንን አይጨምርም። ፍጹም የሆነ ማንም የለም፤ በመሆኑም ማናችንም ብንሆን ፍጹም ቤተሰብም ሆነ ፍጹም ቤተሰባዊ ግንኙነት የለንም። አንዳንዶቻችን የእግዚአብሔርን ፍቅር በሚያንጸባርቁ ወላጆች፣ በወንድም እህቶችና ሌሎች የቤተሰብ አባላት የተባረክን ብንሆንም፤ ነገር ግን ብዙዎች ምሳሌ መሆን ከሚችለው ዓይነት በታች ባለ ግንኙነት ስር መኖር ይጠበቅባቸዋል። ቤተሰባዊ ግንኙነቶች ብዙውን ጊዜ ዕረፍት ዐልባ የሚያደርጉ፣ የሚጎዱ፣ እኛም በሌሎች ላይ የምንቆልላቸውን ስሜታዊ ጫናዎች የሚያስከትሉ ከመሆናቸው በተጨማሪ ውስብስብና ሥቃይ የሚያስከትሉ ናቸው።

በዚህ የሕይወታችን ገጽታ አምላካዊውን ዕረፍት ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? በዚህ ሳምንት ወደ ዮሴፍ እና ቤተሰቡ ግንኙነት ታሪክ ፊታችንን መለስ በማድረግ፣ የከሸፈ ቤተሰባዊ ግንኙነት ባለበት ሁኔታም እንኳ እግዚአብሔር ፈውስ ለማምጣት በሥራ ላይ መሆኑን እንመለከታለን።

ሐምሌ 25
Aug 1

የቤተሰብ መክሸፍ


ዮሴፍ ስለ ከሸፉ የቤተሰብ አባላት ያውቅ ነበር። ጉዳዩ የጀመረው አያቶቹ በነበሩት አብርሃም እና ሣራ ነበር። ሣራ መካን መሆኗን ስትገነዘብ አገልጋይዋ ወደ ነበረችው አጋር እንዲሄድ አብርሃምን አሳመነችው። አጋር እንደጸነሰች ቅናትና ባላንጣነቱ ተጀመረ። በዚህ ድባብ ውስጥ ያደጉት እስማኤል እና ይስሐቅ ውጥረቱን ወደገዛ ቤተሰቦቻቸው ወሰዱ። ይስሃቅ ኤሳውን ለመጥቀም የሚያስችለውን ዘዴ ሲቀይስ፤ ያዕቆብ ደግሞ የአባቱን ፍቅር እና አክብሮት ለማግኘት ሕይወቱን ሙሉ ለፋ። ከጊዜ በኋላ ያዕቆብ ልጅ ለመውለድ እርስ በርስ የሚፎካከሩ ሁለት እህትማማቾችን ተታልሎ አገባ። የሚገርመው ልጅ ለመውለድ ይደረግ የነበረው ሩጫ፤ የእህትማማቾቹ ደንገጡሮች ሳይቀሩ ከያዕቆብ እንዲያረግዙ እስከ ማድረግ የዘለቀ ነበር።

በዘፍ. 34 በዝርዝር የተገለጸውን ሁኔታ ይገምግሙ። ይህ ሁሉ ክስተት በአጠቃላይ እንደ ቤተሰብ እና በብላቴናው ዮሴፍ ላይ ምን ዓይነት ስሜታዊ እና ቤተሰባዊ ተጽእኖ ሊኖረው ይችላል?



በእናቶቹ መካከል የነበረው የባላንጣነት ስሜት ለጠብ ዝግጁ ሆነው ባደጉት ልጆች ላይ ተጽእኖ ማሳደሩ እሙን ነው። የዮሴፍ ታላላቅ ወንድሞች በወጣትነታቸው የሴኬም ከተማ ወንዶች ልጆችን በሙሉ ጨፍጭፈዋል። በወንድሞቹ መካከል የበላይነት ያሳይ የነበረውና ለአባቱ ያልተበገረው፣ ትምክህተኛ ታላቅ ወንድማቸው ሮቤል፤ የራሔል ደንገጡር ከነበረችውና ለያዕቆብ ብዙ ልጆች ከወለደችለት ባላ ጋር ተኝቷል (ዘፍ. 35፡22)። ይህ በእንዲህ እንዳለ የዮሴፍ ወንድም ይሁዳ፤ መበለት የሆነችውን ምራቱን በስህተት እንደ ጋለሞታ በመቁጠር አብሯት በመተኛቱ ከእርሷ መንታ ልጆች ወለደ (ዘፍ. 38)።

ያዕቆብ ከልጆቹ መሃል ዮሴፍን ውድ በሆነ ህብረ ቀለማት ያጌጠ እጀ ጠባብ በማልበስ ግልጽ አድልዎ በማድረጉ በዚህ ሁሉ ቤተሰባዊ ውጥረት ላይ ቤንዚን አርከፈከፈ (ዘፍ. 37፡3)። የከሸፈ ቤተሰብ በነበረበት ሁሉ--በኃይማኖት አባቶች ቤተሰብ መሃል የጦፈ ፉክክር አይጠፋም ነበር። አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ ብልሹ ቤተሰባዊ ግንኙነት ቢኖራቸውም፤ በዕብ. 11፡17–22 ከእምነት ጀግኖች ጎራ የተዘረዘሩት ለምን ይመስሎታል?



የእምነት ጀግኖች ብዙውን ጊዜ ራሳቸው ካሰቡትም ሆነ እግዚአብሔር ከሚጠብቃቸው ከፍታ ሳይደርሱ ሲቀሩ ይታያሉ። እነዚህ ወገኖች በዕብ. 11 የተዘረዘሩት ከቤተሰባቸው ጋር ከነበራቸው የተበላሸ ዝምድና አኳያ ሳይሆን ከግል ስብዕናቸው አኳያ ነው። እነዚህ ሰዎች ከእንዲህ ያለው ቤተሰባዊ ጉዳይ ጋር እየታገሉ እምነትን፣ ፍቅርን እና በእግዚአብሔር ላይ መታመንን አስቸጋሪ በሆነ መንገድ ተምረዋል።

ምን ዓይነት የከሸፈ ይዘት ያለው ቤተሰብ ወርሰዋል? ራስዎን ለጌታ እና ለእርሱ መንገድ አሳልፈው መስጠትዎ ቢያንስ ለወደፊቱ ይህን ሁኔታ ለመስበር እንዴት ይረዳልዎታል?

ሐምሌ 26
Aug 2

አዲስ አቅጣጫ መምረጥ


ዮሴፍ ለባርነት ወደሚሸጥበት ወደ ግብፅ ሲጓዝ ህመም፣ ግራ የተጋባ ቤተሰባዊ ግንኙነትና ጭንቀት አልተለየውም ነበር። ይህ ጉዞ ከእንባው ጋር እየታገለ ለነበረው ዮሴፍ እጅግ አስጨናቂ ነበር። “ይህ በእንዲህ እያለ ዮሴፍ ከገዥዎቹ ጋር ወደ ግብፅ ጉዞ ላይ ነበር። ነጋዴዎቹ ወደ ከነዓን ድንበሮች በስተደቡብ ሲጓዙ ታዳጊው ልጅ ከርቀት ያባቱ ጎጆዎች ያሉባቸውን ተራሮች ለማስተዋል ችሎ ነበር። ያንን የሚወደውን አባቱን ጥሎ ለብቸኝነትና መከራ የመጋለጡ ሀሳብ በምሬት አስለቀሰው።

በድጋሚ በዶታይን የተፈጸመው ተግባር ከፊቱ ላይ ድቅን አለበት። የተበሳጩ ወንድሞቹንና በእርሱ ላይ የነደደውን የቁጣ ፊት ተመልክቷል። ያቀርብላቸው ለነበረው ልመና ይመልሱለት የነበረው አጸያፊ ስድብ እና ዘለፋ በጆሮዎቹ ውስጥ ያንቃጭሉበት ነበር። በፍርሀት በተሞላ ልብ ወደፊት መመልከት ጀመረ። ምን ዓይነት አስገራሚ ለውጥ ነው። ከሚወደድ ልጅነት ወደሚጠላና ረዳት የለሽ ባሪያነት ተቀየረ። ብቻውን ያለማንም ጓደኛ በሚሄድበት ባእድ አገር የሚኖረው ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል? ለተወሰነ ጊዜ ያህል ዮሴፍ ከቁጥጥሩ ውጭ የሆነ ሐዘን እና ፍርሀት ተሰማው።

“ከዚያም ሀሳቡ ወደ አባቱ አምላክ ወደ እግዚአብሔር ዞረ። በልጅነቱ እግዚአብሔርን መውደድና መፍራት ተምሯል። በአባቱ ድንኳን ውስጥ እያለ ያዕቆብ በስደተኛነት ከቤቱ በሸሸበት ወቅት ያየው የራእይ ታሪክ ሲወራ ሰምቷል።… እነዚህ ድንቅ የሆኑ ትምህርቶች በሙሉ ከፊት ለፊቱ ጥርት ብለው ታዩት። የአባቶቹ አምላክ እግዚአብሔር የእርሱም አምላክ እንደሆነ ዮሴፍ ያምን ነበር። እርሱም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እራሱን ለጌታ ሙሉ በሙሉ አሳፎ የሰጠ ሲሆን የእስራኤል ጠባቂ በእርሱ የስደት ምድር ላይ ከጎኑ እንዳይለይ ፀለየ።”—የኃይማኖት አባቶች እና ነቢያት ገጽ፡ 237-238።

አንዳንድ ባህሎች ማኅበረሰብ በግለሰብ ላይ የሚኖረውን ሚና ሲያጎሉ፤ ሌሎች ባህሎች ደግሞ ግለሰብ በማኅበረሰብ ላይ የሚጫወተውን ሚና ማጉላት ይቀናቸዋል። በቅዱሳት መጻሕፍት በእነዚህ ሁለቱ መካከል ሚዛናዊነት እንዳለ ብናውቅም፤ በግለሰብ ደረጃም ሆነ በማኅበረሰብ አቀፍ--ለእግዚአብሔር ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ ጥሪ አለ። ዮሴፍ እግዚአብሔርን ለመከተል የግል ውሳኔ ማድረጉን ተከትሎ በግንኙነቱ ዕረፍት ማግኘት ጀመረ። የግል ቃል ኪዳንን አስመልክቶ የሚከተሉት ጥቅሶች ምን ያስተምሩናል? (ዘዳ. 4፡29. ኢያ. 24፡15፣ 1ዜና 16፡11፣ መዝ. 14፡2፣ ምሳ. 8፡10፣ ኢሳ. 55፡6)



ዕረፍት ለማግኘት እያንዳንዳችን ጌታን ለመከተል የሚያስችል የግል ውሳኔ ላይ መድረስ አለብን። አባቶቻችን የግዙፍ እምነት ባለቤት የነበሩ ቢሆንም፤ ይህ እምነት እና መንፈሳዊነት በዘር ሀረግ አይተላለፍም። እግዚአብሔር ልጆች ብቻ እንጂ የልጅ ልጆች እንዳልነበሩት እዚህ ላይ ማስታወሱ ተገቢ ነው። በየቀኑ፣ እንደውም በየሰዓቱ ራስዎን ለእግዚአብሔር ለመስጠት መምረጥዎ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ይህን ከማድረግ ሲቆጠቡ ምን ይከሰታል?

ሐምሌ 27
Aug 3

እውነተኛውን የራስ ዋጋ ግምት ማግኘት


ዮሴፍ ምናልባት እንዴት ከነጋዴዎቹ አምልጦ ወደ አገሩ እንደሚመለስ ተስፋ ሊያደርግ ቢችልም፤ ግብፅ ከደረሱ በኋላ ለአንድ ታዋቂ ቤተሰብ እንደገና ተሸጠ። “ከፈርዖን ሹማምንት አንዱ የሆነውም የዘበኞች አለቃ፤ ግብፃዊው ጲጥፋራ ወደዚያ ከወሰዱት እስማኤላውያን ነጋዴዎች እጅ ገዛው” (ዘፍ. 39፡

1)። ወጣቱ በድንገት እንግዳ የሆነ አዲስ ቋንቋና ባሕል ውስጥ ገባ። ለራሳችን ያለንን ግምት ለማሳደግ ቤተሰቦቻችንና የቅርብ ግንኙነቶቻችን ወሳኝ ናቸው። ያዕቆብ እጅግ ከሚወዳት ሚስቱ የመጀመሪያ ፍሬ የሆነው ዮሴፍ ከሁሉ የተለየ ልጅ እንደሆነ እያሰበ ነው ያደገው (ዘፍ. 37፡3-4)። በአባቱ ይበልጥ ተወዳጅ እና በኅበረ ቀለማት ያጌጠች ውብ ኮት ባለቤት የነበረው እርሱ ብቻ ነበር (ዘፍ. 37፡3-4)። አሁንስ ማን ሆነ? ማንም እንደ ፈቀደ ሊገዛው ወይም ሊሸጠው የሚችል ባሪያ! አጠቃላይ ማንነቱ እንዴት በፍጥነት እንደ ተለዋወጠ ይመልከቱ። ሕይወት በምን ያህል ፍጥነት ፊቷን እንዳዞረችበት ልብ ይበሉ።

ዮሴፍ እኛ ሁላችን ልንማር የሚገባውን ትምህርት መማሩ እሙን ነው። የእኛን ማንነት ዋጋ ሌሎች እንዲነግሩን ሀሳባችንን በእነርሱ ላይ የምንጥል ከሆነ፤ አስቸጋሪ ብሎም የከፋ ግራ መጋባት ውስጥ እንወድቃለን። ምክንያቱም የእኛን ማንነት ወይም ምንነት ሁሉም አያደንቅም። ይልቁንም አሁን ባለን ሚና ሳይሆን--እግዚአብሔር ለእኛ በሚያስብልንና እኛን በሚያይበት መንገድ ለራሳችን የምንሰጠውን ዋጋ መፈለግ ይኖርብናል። እግዚአብሔር እያንዳንዳችንን የሚመለከትበት መንገድ ምን ይመስላል? (ኢሳ. 43:1፣ ሚል. 3:17፣ ዮሐ. 1:2፣ ዮሐ. 15:15፣ ሮሜ 8:14፣ 1ዮሐ. 3:1-2)



እግዚአብሔር እያንዳንዳችንን በጸጋ በተሸፈኑ መነጽሮች ይመለከታል። እርሱ ፈጽሞ ልንገምት የማንችለውን ችሎታ፣ ውበትና ተሰጥኦ በእኛ ውስጥ ያያል። እኛ በመጀመሪያ የተፈጠርንበትን ለመሆን የሚያስችለንን ዕድል እናገኝ ዘንድ በመጨረሻ፤ ሊሞትልን ዝግጁ ነበር። ምንም እንኳ መስቀሉ ኃጢአተኝነታችንን እና እኛን ለመዋጀት ያስከፈለውን ከፍተኛ ዋጋ ቢያሳየንም--ምን ያህል ለእግዚአብሔር የከበረ ዋጋ እንዳለንም ያሳያል። ሌሎች ስለ እኛ የሚያስቡት ወይም እኛ ስለ ራሳችን የምናስበው ምንም ይሁን ምን--እግዚአብሔር ይወደናል፤ አሁን ካለው የኃጢአት ኃይል ብቻ ሳይሆን ወደፊትም ከሚያስከትለው ዘላለማዊ ሞት ሊቤዠን ይፈልጋል።

ዋናው ጥያቄ ሁሌም አንድ ዓይነት ነው፡ በየሱስ ክርስቶስ በተጨባጭ ለተገለጠው አምላካዊ ፍቅር ምን ዓይነት ምላሽ አለን? ራሳችንን ባለንበት ሁናቴ እንድንወድና ያለ ምንም ነቀፋ እንድንቀበል የሚነግሩን አያሌ ቡድኖችና ግለሰቦች አሉ። ይህ በእርግጥ ራስን ማታለል የሆነው ለምንድን ነው? የእኛ ማንነት የከበረ ዋጋ የሚመነጨው እኛን ከፈጠረና እውነተኛ አቅማችንን ከሚያውቅ--ከራሳችን ውጪ ከሆነ አካል የሆነው ለምንድን ነው?

ሐምሌ 28
Aug 4

ግንኙነቶችን በአምላካዊው መንገድ መመስረት


መጀመሪያ ላይ በምድረ ግብፅ የተስተዋለው የዮሴፍ ታሪክ አዎንታዊ ገጽታ የተስተዋለበት ነበር። ዮሴፍ ራሱን ለእግዚአብሔር በአደራ ሲሰጥ፤ ይህ አምላክ ደግሞ በጲጥፋራ ቤተሰብ ውስጥ ሊገምተው የማይችለው ከፍተኛ ደረጃ ላይ በማድረስ ባረከው። አምላካዊው በረከቶች በዮሴፍ ሕይወት መገለጥ የቻሉባቸው ተጨባጭ መንገዶች የትኞቹ ነበሩ? ዮሴፍ ከሰዎች ጋር የነበረው የግል ግንኙነት ምን ይመስላል? ዘፍ. 39፡1-6።



ምንም እንኳ ዮሴፍ ከጲጥፋራ እንዲሁም ከቤቱ እና እርሻው ሠራተኞች ጋር መልካም ግንኙነት የነበረው ቢመስልም--ጉድ እየፈላ ነበር። በቤት ውስጥ ከሚኖሩ መሃል፣ በአንድ ሰው ላይ ዕረፍት የለሽ መቅበዝበዝ መታየት ጀምሯል። ዮሴፍ ምን ዓይነት ግንኙነት ነክ ችግር እየገጠመው ነው? ይህን ሁኔታ ለመቆጣጠር የመረጠበት መንገድ ምን ይመስላል? ዘፍ. 39:7–10።



ዮሴፍ ከጲጥፋራ ሚትስ ጋር በተያያዘ ችግር ገጥሞታል። ምናልባት ቃሉን፡ የጲጥፋራ ሚስት ችግር አለባት--ብለን ብናስተካክለው የተሻለ ይሆናል። ይህች ሴት ሌሎችን የምትመለከተው እንደ ልቧ እንደምትጠቀምበት “ቁስ” ነው። በመሆኑም ዮሴፍን “ልትጠቀምበት” ፈለገች። ስለ ዮሴፍ ከተሰጠው ዘገባ እንደምንረዳው “ጥሩ ቁመና ያለውና መልከ መልካም ነበር” (ዘፍ. 39፡ 6)። መጽሐፍ ቅዱስ ሰብዓዊውን ተክለ ሰውነትና ማማር አስመልክቶ ብዙም አይናገርም--ምክንያቱም “ ‘እግዚአብሔር የሚያየው፣ ሰው እንደሚያየው አይደለም። ሰው የውጭውን ገጽታ ያያል፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል’ ” (1 ሳሙ. 16:7)።

ከዚህ አኳያ የዮሴፍ ዐይነ-ግቡነት አምላካዊውን መርኅ በንጽህና እና በታማኝነት ለመከተል የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ከማገዝ ይልቅ እንቅፋት ሲሆንበት ይስተዋላል። ምንም እንኳ ይህች ክፉ ሴት አጥብቃ ብትነዘንዘውም፤ ዮሴፍ ግን ተቃራኒ ውጤት ሊያስከትል የሚችል ድርጊት ፈጸመ። ዮሴፍ የጲጥፋራ ሚስትን ጨምሮ ለሁሉም ዓይነት ግንኙነቶች መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርኅዎችን ይተገብር ነበር። የኃጢአት መዘዝ የደረሰበት ማንኛውም ሰው ምስክር መሆን እንደሚችለው--ሰብዓዊ ግንኙነቶችን አስመልክተው የቀረቡ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርኅዎች ዛሬም ቢሆን ጊዜ ያለፈባቸው አይደሉም።

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚተርክልን ፈተናው አንዴ ብቻ የተከሰተ አልነበረም። የጲጥፋራ ሚስት በተደጋጋሚ ጎትጉታዋለች (ዘፍ. 39፡10)። ዮሴፍ እንዲህ ያለው ውሳኔ ላይ ለመድረስ ያነሳሳውን መንስዔ ሊያብራራላት ቢሞክርም (ዘፍ. 39፡8-9) ሀሳቡ ተቀባይነት ያገኘ አይመስልም። ዮሴፍ የሌሎችን ምርጫ መቆጣጠር እንደማይችል ተገንዝቧል። ይሁን እንጂ በዙሪያው ከነበሩት ሰዎች ጋር እግዚአብሔርን በሚያስከብር አኳኋን ለመኖር፣ እነርሱን ለመውደድና ለመቅረብ ወስኗል።

ዮሴፍ በእግዚአብሔር ፊት እንዴት መመላለስ እንዳለበት ተምሯል። ይህ ዕውቀት ፈተናዎችን እንዲቋቋም እረድቶታል። ሌላው ሰው “ፍትሃዊ ሁናቴ--እርስዎ በሁሉም መርኅዎችን ለመተግበር መኖር አስፈላጊ የሆነው ጨዋታ” የማይጫወት በሚመስልበት ግንኙነት ነክ ዘርፎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሞክረዋል? ማቴ. 5፡43-48። እንዲህ ለምንድን ነው?

ሐምሌ 29
Aug 5

ቅርባችን ያሉትንም ሆነ ግላዊ ማንነታችንን የሚነካው-ታላቁ ውዝግብ


ከታሪኩ እንደምንረዳው (ዘፍ. 39፡11-20) በመርኅ ላይ የተመሠረተው የዮሴፍ ውሳኔ ሥቃይ አስከትሎበታል። ዮሴፍ ወደ ወኅኒ ተወረወረ። እንደ ጲጥፋራ ንብረትነቱ፣ ዮሴፍ ክሱ እንደ ቀረበበት ያለ አንዳች ጥያቄ ወዲያውኑ መገደል ይችል ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ ጲጥፋራ ሚስቱን አላመናትም፤ ሆኖም እርምጃ በመውሰድ ዝናውን መጠበቅ ግን ነበረበት። ምንም እንኳ ያ ሁሉ አሰቃቂ ግፍ በዮሴፍ ላይ ቢደርስም፤ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው “እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበር” (ዘፍ. 39፡21)።

ምድራዊው ሕይወት ፍትሐዊ አይደለም። መልካም ነገር ተገቢውን ካሳ ሰርክ አያገኝም። ክፋትም ሁሌም ወዲያውኑ አይቀጣም። ሆኖም አንድ የምሥራች አለ፡ ዮሴፍ በእስር ቤት ቢሆንም ሕሊናው ዕረፍት አለው። ምክንያቱም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበር። ዮሴፍ በእስር ቤት ቆይታው ዘወትር ስለ ደረሰበት ግፍ እያሰላሰለ ከእግዚአብሔር ገሸሽ ሊል፤ አልፎ ተርፎም እምነቱን ሊተው ይችል ነበር።

ዮሴፍ በእስር ቤት ቆይታው ምን ያደርግ ነበር? በዙሪያው ካሉ ሰዎች ጋር የነበረው ግንኙነት ምን ይመስላል? ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 39፡21-40፣ 22



ዮሴፍ በእስር ቤት ከተጨባጭ እውነታ ጋር ዝምድና ካለው ነገር አኳያ ይሠራ ነበር። ምንም እንኳ በእስር ቤት ከሰዎች ጋር የነበረው ግንኙነት እርሱ ከሚያስበው እጅግ የራቀ ቢሆንም፤ የግንኙነት መረቦችን በመዘርጋት ሌሎችን ይረዳ ነበር። ዮሴፍ የሌሎችን እርዳታ ከመጠየቅ በላይ አልነበረም--ለአደጋ ተጋላጭ ሊሆን እንደማይችልም አላሰበም። የመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ ያየውን ሕልም ለዮሴፍ በነገረው ጊዜ፤ ዮሴፍ ፍቺውን በመስጠት የእርሱን እርዳታ ጠይቋል።

ጳውሎስ በግንኙነት ዙሪያ በኤፌ. 6፡1-13 ያቀረበው ምልከታ ከፍ ያለው ትኩረት ምንድን ነው?



ከሰዎች ጋር ያሉን ግንኙነቶች በአምላክና በሰይጣን መካከል ለዘመናት እየተፋፋመ ያለው ታላቅ ውዝግብ ጥቃቅን ነጸብራቆች ናቸው። ይኸውም-ፍጹም የሚባሉ ግንኙነቶች የሉም ማለት ነው። እያንዳንዱ ግንኙነት ዕድገት ማስመዝገብ የሚጠበቅበት ቢሆንም፤ ሰይጣን ግን ዓላማውን ለማሳካት ሲል ግንኙነቶቻችንን ተጠቅሞ እግዚአብሔር ለሕይወታችን ያለውን ፈቃድ በመጉዳትና በማጨናገፍ ትርፍ የማግኘት ግላዊ ምክንያት አለው--በተለይ ለእኛ በጣም ቅርብ በሆኑት። እነዚህን ውጊያዎች በራሳችን እንድንዋጋ ብቻችንን ባለመተዋችን አመስጋኞች ልንሆን እንችላለን።

የእግዚአብሔር ቃል ለግንኙነቶቻችን ይበጃሉ ያላቸውን መርኅዎች ያስቀምጣል። ጥበብ እንደሚሰጠን (ያዕ. 1፡5) የተወልን የተስፋ ቃል ለግንኙነቶቻችንም እንዲሁ ጠቃሚ ነው። እርሱ ከዮሴፍ ጋር እንደነበረ ሁሉ፤ ግንኙነታችን ውስብስብ ሲሆን፣ ከእኛም ጋር እንደሚሆን እነሆ ቃል ገብቶልናል። እግዚአብሔር በያዕ. 1፡5 ስለ ሰጠው የተስፋ ቃል እያሰቡ፤ በግንኙነቶችዎ ዙሪያ ጥበብ ይሰጥዎ ዘንድ ጊዜ ወስደው ይጸልዩ። ከሰዎች ጋር ግንኙነት ለመፍጠር በሚያደርጉት እንቅስቃሴ፤ ራስዎን ለመንፈስ ቅዱስ ጉትጎታ ክፍት ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?

ሐምሌ 30
Aug 6


ተጨማሪ ሀሳብ


ከጲጥፋራ ሚስት ጋር በተያያዘ በዮሴፍ ላይ የደረሰውን ሁኔታ ኤለን ኋይት እንደሚከተለው ጽፋለች፡ “በምድር ላይ ለሚኖሩ ትውልዶች ሁሉ የተተወ ምሳሌ ይህ ነው።… በእንዲህ ያለው ወቅት እግዚአብሔር ረዳት፣ መንፈሱም ጋሻ ይሆናል። ምንም እንኳ በጣም ከባድ በሆኑ ፈተናዎች ብንከበብም፤ ፈተናዎቹን መቋቋም የሚያስችለን የብርታት ምንጭ አለ። በዮሴፍ ሥነ ምግባር ላይ የተፈጸመው ጥቃት ምንኛ ከባድ ነበር! ጥቃቱ የተሰነዘረው ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ የመምራት አጋጣሚያቸው ሰፊ ከሆኑ ተጽእኖዎች በአንደኛው ነበር። ሆኖም በአፋጣኝ ብሎም ጽኑ በሆነ አቋም ተቋቋመ። ስሙንና ፍላጎቱን አሳልፎ በእግዚአብሔር እጆች ውስጥ አኖረ።

ምንም እንኳ እርሱን ለታላቅ ሥልጣን ብቁ አድርጎ ለማዘጋጀት ለተወሰነ ጊዜ መከራ ቢደርስበትም፤ በክፉ ከሳሽ የጠለሸ ስሙን በአስተማማኝ ሁኔታ ጠብቆ በራሱ መልካም ጊዜ እንዲያንጸባርቅ አደረገ። እግዚአብሔር የእስር ቤት ቆይታውን እንኳ ሳይቀር ወደ ከፍታ የሚወጣበት መንገድ አድርጎለት ነበር። በጎነት በጊዜ ሂደት የራሱን ሽልማት ያስገኛል። የዮሴፍን ልብ የሸፈነው ጋሻ እግዚአብሔርን መፍራት ሲሆን፤ ይህም ለጌታው ጲጥፋራ ታማኝ እና ቅን፣ ለእግዚአብሔር ደግሞ እውነተኛ እንዲሆን አስችሎት ነበር። ምንም እንኳ ጌታው እውነቱን በጭራሽ ላያውቅ ቢችልም፤ በእርሱ ላይ የነበረውን እምነት እንዲያጎድፍ ሊያደርግ የሚችለውን ውለታ ቢስነት አበክሮ ናቀ።”—Ellen G. White, The Spirit of Prophecy, vol. 1, p. 132.


የመወያያ ጥያቄዎች



፡ 1.በስመ ክርስቲያን መሆን ወይም ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂ ተብሎ ለወጉ መጠራት ብቻውን በግንኙነታችን ውስጥ ዕረፍት እንድናገኝ አይረዳንም። በወግ እና ልማድ የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂነት እና በእውነተኛ አማኝ መካከል ያሉ ልዩነቶች ምንድን ናቸው?

2.እህት እገሊት ገና ቤተ ክርስቲያንን መቀላቀሏ ነው። ባሏ አማኝ አይደለም። ባሏን የምትወደው ቢሆንም፤ በእርሷ ውስጥ የተመለከተውን ለውጥ ግን አልወደደውም። በመጽሐፍ ቅዱስ መርኅዎች ላይ ተመርኩዘው ለአዲሷ የቤተክርስቲያንዎ አባል የሚሰጡት ምክረ ሀሳብ ምን ሊሆን ይችላል?

3.ታዋቂው ሩሲያዊው ደራሲ ሊዮ ቶልስቶይ “ደስተኛ የሆኑ ቤተሰቦች በሙሉ ተመሳሳይ ናቸው። ደስተኛ ያልሆነ እያንዳንዱ ቤተሰብ ደግሞ በገዛ ራሱ መንገድ ደስተኛ አይደለም።” ሲል ጽፏል። ሁሉም ቤተሰብ ኃጢአተኛ እንደመሆኑ የየራሱን መክሸፍ ወደ ቤተሰባዊው ግንኙነት ይዞ ይመጣል። በዚህም መጠኑ ይለያይ እንጂ የመክሸፍ ችግር ይከሰታል። እኛ እያንዳንዳችን በእግዚአብሔር ጸጋ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርኅዎች የሆኑትን-ፍቅር፣ ይቅርታ፣ የሌላውን ሸክም መሸከም እና የመሳሰሉትን ተጠቅመን ለቤተሰባዊ ግንኙነታችን ፈውስ ማምጣት የምንችለው እንዴት ነው?

4.ቤተሰባዊው ህይወት በመልካም ሁኔታ እየሄደ እያለ ድንገተኛ አሳዛኝ ነገር ይከሰታል። እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ሲገጥም በአምላካዊው ቃል ውስጥ የታቀፉትን ተስፋዎች አጥብቀን መያዛችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? በተለይ በመልካም ጊዜያት ወቅት--መጥፎውም ሊከሰት እንደሚችል በማሰብ መንፈሰ ጠንካራ ሆነን መዘጋጀት የሚኖርብን ለምንድን ነው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL