የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ወቅታዊ እውነት በኦሪት ዘዳግም


4ኛ ሩብ ዓመት 2021

ከጥቅምት 13 – 19

5ኛ ትምህርት

Oct 23-Oct 29




በግቢህ ያለ መጻተኛ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ማር. 12:29–31፣ ዘዳ. 10:1–19፣ መዝ. 146:5–10፣ ማቴ. 7:12፣ ዘዳ. 27:19፣ ያዕ. 1:27–2:11።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ“ ‘ስለዚህ እናንተም በግብፅ ምድር መጻተኞች ነበራችሁና መጻተኛን ውደዱ’ ” (ዘዳ. 10፡19)።

ባ ለፈው ሳምንት ጥናታችን “ ‘ከትእዛዛት ሁሉ የሚበልጠው የትኛው ነው’ ” (ማር. 12፡28) ሲል አንድ ጸሐፍት ለየሱስ ላቀረበለት ጥያቄ፤ የሱስ--እግዚአብሔር አንድ አምላክ መሆኑን አጽንኦት ከሰጠ በኋላ፡ “ ‘ “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህና በፍጹም ኀይልህ ውደድ’ ” (ማር. 12፡3) ሲል እንደመለሰለት ተመልክተናል። የሱስ ንግግሩን በመቀጠል “ ‘ሁለተኛውም ይህ ነው’ ” (ማር. 12:31) ይላል-ጸሐፍቱ ያልጠየቀውን እያነሣ። የሆነው ሆኖ ይህ ነጥብ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ የሚያውቀው የሱስ፡ “ ‘ሁለተኛውም ይህ ነው፤ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ’ ከዚህም የሚበልጥ ትእዛዝ የለም።” (ማር. 12፡31)። ከዚህም የሚበልጥ ትእዛዝ የለም? የሱስ እግዚአብሔርን መውደድ እና ባልንጀራን መውደድ በአንድ ትእዛዝ ውስጥ በማስተሳሰር፣ ትእዛዛዙ ከሁሉ የበለጠ ነው ሲል ይናገራል።

የሱስ አይሁዳውያን ከዚያ በፊት ሰምተውት የማያውቁትን አዲስ ነገር ይዞ እየመጣ አልነበረም። ይልቁንም እርሱን አስበልጠን እንድንወድ ያቀረበው ይህ ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር የምንገልጽበት--ባልንጀራችንን እና ሌሎች ሰዎችን እንድንወድ የተጠራንበት ጽንሰ ሀሳብ የተወሰደው በእርግጥም ከዘዳግም መጽሐፍ ነው።

ጥቅምት 1
Oct 1

የልባችሁን ሸለፈት ግረዙ


የዘዳግም ምዕራፍ 9 ቀጣይ የሆነው ምዕራፍ 10፣ እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር የገባውን ኪዳን በድጋሚ ያረጋገጠበት ክፍል ነው። በእርግጥ የዚህ መጽሐፍ አብዛኛው መልእክት የኪዳን መታደስን ያመለክታል። ማለትም-ሙሴ ለጥቂት ጊዜ ከአጠገባቸው ዞር ባለበት ቅጽበት በጣኦት አምልኮ ወድቀው በኮሬብ አስከፊ የተባለውን ኃጢአት ከሠሩ በኋላም እንኳ ጌታ አሁንም አልተዋቸውም ነበር። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘዳ. 10፡1-11። እግዚአብሔር የሕዝቡን ኃጢአት ይቅር ብሎ ከእነርሱና ከአባቶቻቸው ጋር የገባውን ኪዳን ዳግመኛ ማጽናቱን እንድናስተውል ጥቅሶቹ እንዴት ይረዱናል?



ሙሴ አሥርቱ ትእዛዛት የተቀረጹባቸውን ሁለቱን ጽላቶች አሽቀንጥሮ በፊታቸው መሰባበሩ የቃል ኪዳኑ መፍረስ ምልክት ነበር (ዘዳ. 32፡19)። “ቁጣው የነደደው ሙሴ ሕዝቡ ለሠራው የወንጀል ድርጊት ያለውን ጥላቻ ለመግለጽ ጽላቶቹን ከእጁ ወረወራቸው። መላው ሰው እየተመለከተ ከተራራው ግርጌ ወድቀው ተሰባበሩ። የምስክር ጽላቶቹ መሰባበር --እነርሱ የእግዚአብሔርን ኪዳን እንደሰበሩ ሁሉ እግዚአብሔርም ከእነሱ ጋር የገባውን ኪዳን መስበሩን ያሳያል።” (የኃይማኖት አባቶች እና ነቢያት፡ ገጽ 361)።

ሙሴ “እንደ መጀመሪያዎቹ ያሉ” ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ቀርጾ የመጀመሪያዎቹ ላይ ተጽፈው የነበሩትን ቃላት መልሶ በእነዚህኞቹ ላይ እንዲጽፍ እግዚአብሔር ሲነግረው፤ ጌታ ሕዝቡን ይቅር ማለቱንና በዚያን ጊዜም እንኳ፣ ከእነርሱ ጋር የነበረው ግንኙነት እንዳላበቃለት ያሳያል። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘዳ. 10፡14-16። እግዚአብሔር ምን እያላቸው ነው? ጌታ በዚህ ስፍራ ጥቅም ላይ ያዋላቸው የቃላት ስያሜ ትርጓሜ ምንድን ነው?



ሸለፈት፣ ልብ፣ አንገት--የሆነው ሆኖ ለማመልከት የተፈለገው ነጥብ ግልጽ ነው። ግርዘት የኪዳኑ ምልክት ቢሆንም፣ ነገር ግን ውጫዊ ምልክት ብቻ ነበር። እግዚአብሔር የፈለገው ልባቸውን ማለትም--አእምሮአቸውን፣ መውደዳቸውንና ፍቅራቸውን ነበር። አንገተ ደንዳናነታቸውን አስመልክቶ የቀረበው መግለጫ፣ ጌታን ለመታዘዝ ምን ያህል ግትር እንደነበሩ ይጠቁማል። ጌታ በዚህም ሆነ በየትኛውም ስፍራ የተከፋፈለውን ማንነት እርግፍ አርገው ትተው በሙሉ ልባቸውና ነፍሳቸው እርሱን እንዲያገለግሉ እየነገራቸው ነበር። ጌታ በደል መተላለፍዎን ያለማቋረጥ ይቅር እያለ ይገኛል። እስቲ ስለዚህ ጉዳይ አሰብ ያድርጉ። ስለ ጸጋው ምን ሊነግርዎ ይገባል?

ጥቅምት 1
Oct 1

መጻተኛን ውደዱ


በእነዚህ ምክርና ተግሳጾች መሃል ሙሴ-“ ‘ሰማያት፣ ሰማየ ሰማያት፣ ምድርና በእርሷም ያለው ሁሉ የአምላክህ የእግዚአብሔር ነው’ ” (ዘዳ. 10፡14) ሲል ያውጃል። ይህ በሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍልም እንዲሁ የሚገኝ ጽንሰ ሀሳብ፣ የጌታን ሉዐላዊ አምላክነት የሚገልጥ ብርቱ አባባል ነው፡ “ምድርና በእርሷ ያለው ሁሉ፣ ዓለምና በውስጧ የሚኖር ሁሉ የእግዚአብሔር ነው።” (መዝ. 24፡1)። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘዳ. 10፡17-19። ሙሴ ስለ ጌታ የሚሰጠው ሌላ መግለጫ ምንድን ነው? ይህን መግለጫ ተከትሎ እግዚአብሔር ምን አድርጉ ሲል ሕዝቡን ያዛል?



ያሕዌ የሰማይና ምድር ሉዐላዊ አምላክ ብቻ አይደለም “የአማልክት አምላክ የጌቶች ጌታ” (ዘዳ. 10፡17) ጭምር እንጂ! ይህ ማለት በእስራኤላውያን ዙሪያ የነበሩ አረማውያን ሕዝቦች ያመልኳቸው የነበሩ ዓይነት ዝቅ ያለ ደረጃ የነበራቸው ሌሎች አማልክትም አሉ ማለት አይደለም። ይልቁንም እርሱ ብቸኛ አምላክ መሆኑን የሚናገርበት መንገድ ነው፡ “ ‘ “እኔ ራሴ እርሱ እንደሆንሁ እዩ፤ ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ የለም” ’ ” (ዘዳ. 32፡39)። በሰማይም ሆነ በምድር፣ በሁሉም ኃይላት ላይ ሙሉ ልዕልና እንዳለው ጥቅሱ ያረጋግጣል። በተጨማሪ--“የአማልክት አምላክ፣ የጌቶች ጌታ፣ ታላቅ አምላክ፣ አድልዎ የማያደርግ፣ መማለጃም የማይቀበል” መሆኑን ጥቅሱ ይናገራል። ይህ ሁሉ የታላቁ መልእክት ክፍል ነው፡ ያህዌ አምላክህ ነው፣ አንተ ሕዝቡ ደግሞ ልትታዘዘው ይገባል።

በዚህ ስፍራም እንዲሁ ብርቱ ንጽጽር ቀርቦ እንመለከታን። አዎን--ያህዌ የአማልክት አምላክ፣ የጌቶች ጌታ፣ ሉዓላዊ ገዥና የፍጥረቱ ደጋፊ (ቆላ. 1፡ 16-17) ከመሆኑ በተጨማሪ አባት ለሌላቸው፣ ለመበለቲቱና ለመጻተኞችም የሚያስፈልጋቸውን በማሟላት ይጠነቀቅላቸዋል። አንዲት ድንቢጥ እንኳ በምድር ላይ ስትወድቅ የሚያውቀው አምላክ (ማቴ. 10፡29) ማኅበራዊ መገለል የደረሰባቸው ግፉአን የሚገኙበትን አሳዛኝ ሁኔታ ይገነዘባል። በሌላ አነጋገር-አዎ ምናልባት አናንተ የተመረጣችሁ፣ የተለያችሁ ሕዝቦች በመሆናችሁ እወዳችኋለሁ፤ ነገር ግን በመካከላችሁ ያሉትን ችግረኞች እና ረዳተ ቢሶችም እንዲሁ እወዳለሁ--እያለ ለሕዝቡ እየነገረ ነበር። እኔ እነርሱን እንደምወዳቸው እናንተም ልትወዷቸው ይገባል። ይህ ከቃል ኪዳን ግዴታዎቻችሁ ውስጥ አንዱና አስፈላጊው ነው።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ መዝ. 146፡5-10። እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ የሚናገረውን የሚያንጸባርቀው የትኛው የመጽሐፈ መዝሙር መልእክት ነው? እንደ ክርስቲያን ይህ ለእኛ ምን ትርጉም ሊኖረው ይገባል?





ጥቅምት 1
Oct 1

እናንተም በግብፅ ምድር መጻተኞች ነበራችሁ


“ ‘ስለዚህ እናንተም በግብፅ ምድር መጻተኞች ነበራችሁና መጻተኞችን ውደዱ’ ” (ዘዳ. 10፡19)። ለጥንት እስራኤላውያን በዚህ ስፍራ የቀረበው መልእክት ምንድን ነው? ለእኛስ ምን ፋይዳ ሊኖረው ይገባል?



በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት አስቀድሞ ጌታ አብርሃምን እንዲህ ብሎት ነበር፡ “ ‘ዘርህ በባዕድ አገር ስደተኛ እንደሚሆን በእርግጥ ዕወቅ፤ አራት መቶ ዓመታት በባርነት ተረግጦ ይገዛል’ ” (ዘፍ. 15፡13 በተጨማሪ፡ ዘፍ. 17፡8፣ ሐዋ. 13፡17)። ይህ በእርግጥ የተከሰተ ነገር ነው። በዘፀአት የመጀመሪያዎቹ ምዕራፎች የቀረቡት በትዕይንት የተሞሉ ከግብፅ ምድር የመዋጀታቸው (ዘፀ. 15፡13) እና የመዳናቸው (ዘፀ. 14፡13) ታሪኮች--ይኸውም በክርስቶስ የሱስ የተሰጠን ቤዛነትና ማዳን ለትውልድ ምልክትና ምሳሌ ሆነው ተመዝግበዋል። በዚህ ጥቅስ ጌታ የት እንደነበሩና ምን እንደነበሩ እንዲያስታውሱ ይፈልጋል። አዎ--በባዕድ ምድር ይኖሩ የነበሩ መጻተኛ ሕዝቦች ነበሩ።

በሌላ አነጋገር--ማኅበራዊ መድሎና መገለል የደረሰብህ፣ አልፎ ተርፎም ባሪያ እንደነበርክ አስታውስ። ከአንተ በበረቱና ጉዳት ሊያደርሱብህ በሚችሉ፣ በእርግጥም ባደረሱብህ ፈቃዳቸው ስር እንደነበርክ አትዘንጋ--እያላቸው ነበር። ምንም እንኳ እስራኤል በእግዚአብሔር የተመረጠ፣ የተጠራ እና “የመንግሥት ካህናት” (ዘፀ. 19፡6) ሕዝብ ከመሆኑ አኳያ በእነርሱና በመካከላቸው በነበሩ ሕዝቦች መካከል በተለይ ኃይማኖታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ልዩነቶች ቢኖሩም--“ሰብዓዊ መብቶችን” አስመልክቶ እስራኤላውያን ከጌቶቻቸው ይጠብቁት የነበረው ዓይነት ቅንነትና ፍትሐዊነት ለመጻተኛው፣ ለመበለቲቱና ለወላጅ ዐልባው ማሳየት ነበረባቸው።

ጥቅሱን ያንብቡ፡ ማቴ. 7፡12። የጥንት እስራኤላውያን በመካከላቸው የነበሩትን ደካሞች እንዴት ማስተናገድ እንደ ነበረባቸው ጌታ ይነገራቸው የነበረውን፣ ጥቅሱ አጠቃልሎ ያቀረበበት መንገድ ምን ይመስላል?



እስራኤላውያን የማኅበረሰባዊ መገለል ሰለባ ለሆኑት መጻተኞች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ይህ ምክርና ተግሰጽ በተሰጣቸው በዚያ የጥንቱ ዓለም-መጻተኞች ከእንስሳ እንኳ በተሻለ ተለይተው አይታዩም ነበር። ከዚህ አኳያ ማስጠንቀቂያው ፈጽሞ ሊታሰብ የማይችልና ያልተለመደ ነበር። በተቃራኒው እስራኤል የተለየች እና በመንግሥታት ፊት ብርሃን መሆን ነበረበት። እርግጥ ነው--ልዩነቱ በሚያመልኩት አምላክ፣ በአምልኮ ሥርዓታቸው እና እግዚአብሔር በሰጣቸው አጠቃላይ ኃይማኖታዊ ሥርዓት እውነት ውስጥ ይገኛል። እነርሱ መገለል የደረሰባቸውን ወገኖች የሚያዩበት በጎ ዐይን፣ የሚያመልኩትን ታላቅ አምላክ እና እምነታቸውን በመግለጽ ለጥንቱ ዓለም ግዙፍ ምስክር መሆን ይችል ነበር።





ጥቅምት 1
Oct 1

ፍትሐዊ ዳኝነት


እንደ አማኝ፣ የእግዚአብሔርን ባህሪ እንድናንጸባርቅ ተጠርተናል። “የምወዳችሁ ልጆቼ ሆይ፤ ክርስቶስ በውስጣችሁ እስኪቀረጽ ድረስ ስለ እናንተ እንደገና ምጥ ይዞኛል” (ገላ. 4፡19)። ለነገሩ እኛ በመጀመሪያ የተፈጠርነው “በእግዚአብሔር መልክ” (ዘፍ. 1፡27) ነበር። ሆኖም ኋላ ላይ ኃጢአት ይህን መልክ አበላሽቶታል። ቀደም ብለን እንደ ተመለከትነው ሙሴ ስለ እግዚአብሔር ኃያልነትና ልዕልና ሲናገር፤ እርሱ አንዳች እጅ መንሻ ወይም ጉቦ የማይቀበል፣ ስለ ደካማው እና ስለ ተገለለው የሚጠነቀቅ አምላክ መሆኑን ሰምተናል። እግዚአብሔር ይህን እንዳደረገ ሁሉ እኛም የእርሱን አርአያ መከተል ይኖርብናል። የሚከተሉት ጥቅሶች ያንብቡ። የመልእክቶቹ የጋራ ጭብጥ ምንድን ነው? ዘዳ. 1:16________________________________________________



ዘዳ. 16:19_______________________________________________



ዘዳ. 24:17_______________________________________________



ዘዳ. 27:19_______________________________________________



ጉዳዩ--ገንዘብ፣ ሥልጣን እና ዝምድና ያላቸው የሚያገኙትን “ፍትሕ”-ደካሞች፣ ድኾች እና መድሎ የሚደረግባቸው ወገኖች ከአብዛኞቹ የፍትሕ አካላት አለማግኘታቸው የታወቀ መሆኑን ያወሳል። በየትኛውም አገር፣ ዘመን ወይም ባሕል ቢሆን፤ ወይም ደግሞ በየትኛውም ዓይነት ሕገ መንግሥት ወይም ሕግ ውስጥ የፍትሕ እና እኩልነት መርኅዎች ገዝፈው ቢደነገጉ እንኳ-መሬት ላይ ያለውን እውነታ አይለውጡም፡ ደኻው፣ ደካማው፣ የተገፋው ሌሎች የሚያገኙትን ፍትሕ አያገኝም ብሎ ደፍሮ መናገር ይቻላል። ጌታ ራሱ እዚህ ላይ እየተናገረ የነበረው ነገር በእጅጉ አስገራሚ ነው። ይህ በየትኛውም አገር ይተገበር የነበረ ኢፍትሐዊነት እርሱን በዓለም ፊት በሚወክሉትና ሕዝቦቹ በሆኑት እስራኤላውያን መሃል መደረግ አልነበረበትም። በሌላ አነጋገር የዘመኑን ቋንቋ ስንጠቀም፡ ጥንት ሁሉም እስራኤላውያን “በሕግ ፊት እኩል የሚዳኙበት” አሠራር እንዲሰፍን ጌታ ፈለገ።

ይሁን እንጂ ይህ ጉዳይ ከፍትሕ አካል የበለጠ ጥልቀት ያለው ነው። “ ‘ “እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” ’ ” (ዘሌዋ. 19፡2)። አዎን፤ እውነተኛው አምላክ ማን እንደ ነበር አውቀዋል። በዚህም የትክክለኛው አምልኮ ቅርጽ ነበራቸው፣ ትክክለኞቹን ዓይነቶች ሥጦታዎችም ይዘው ቀርበዋል። ይህ ሁሉ መልካም ነበር። ሆኖም በመጨረሻ፣ በመካከላቸው የነበሩትን ደካሞች እና ድኾች የሚበድሉ ከሆነ የዚህ ሁሉ ፋይዳው ምንድን ነው? ጌታ የእስራኤልን ድኾችና በእጦት ያሉ ወገኖች በሚጨቁኑ ላይ፣ በነቢያቱ አማካይነት በተደጋጋሚ አምርሮ ይናገራል። እርስዎ በተመሳሳይ ወቅት “ቅዱስ” እና ሌሎችን የሚበድል ሰው መሆን የሚችሉት እንዴት ነው? ትክክለኞቹን ኃይማኖታዊ ምግባሮች አጥብቀው እስከያዙ ድረስ ይህ የማይሆን ነገር ነው።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ አሞጽ 2:6፣ አሞጽ 4:1፣ አሞጽ 5:11፣ ኢሳ. 3:14-15፣ ኢሳ. 10:1-2፣ ኤር. 2:34። ጌታ የጥንቷን እስራኤል ያስጠነቀቀበትን ጉዳይ አስመልክቶ ትንቢቶቹ ምን ይላሉ? ቃላቶቹ ዛሬ ለእኛ ያላቸው ትርጉም ምንድን ነው?

ጥቅምት 1
Oct 1

በእግዚአብሔር ፊት ንጹህና ነውር የሌለበት ሃይማኖት


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘዳ. 24፡10-15። በስራችን ያሉ ወገኖችን እንዴት መያዝ እንዳለብን አስመልክቶ ምን ዓይነት ጠቃሚ መርኅዎች ተገልጸዋል?



አሁንም ቢሆን ጌታ መሠረታዊ የሆነው ሰብዓዊ ክብር እንደሚያሳስበው እንመለከታለን። አንድ ሰው የሆነ ነገር ቢበደሮትና ያን ያበደሩትን ነገር የሚቀበሉበት ጊዜ ቢደርስ--ለግለሰቡ መጠነኛም ቢሆን አክብሮት መስጠትም ሆነ ክብሩን መጠበቅ እንዳለብዎት አይዘንጉ። ከዚህ ውጪ ያለበት ድረስ ሄደው ኃይለ ቃል አይናገሩ። በዘዳ. 24፡ 12-13 እንደ ቀረበው፡ አንድ ደኻ ነፍስ ልብሱን “በማያዣነት” ሲሰጥዎ ማታ ለብሶት እንዲያድር ቢያንስ ጸሐይ ሳትጠልቅ ይመልሱለት። ሌሎቹ ጥቅሶች ደግሞ አንድ ሰው የሚሠራለትን ምስኪን ሰው እንዴት ከጭቆና ጠብቆ መያዝ እንዳለበት ይናገራሉ።

በእርስዎ ስር ያሉ ሰዎችን አይጨቁኑ። ምክንያቱም ይህን ማድረግ በእግዚአብሔር ዐይን ከኃጢአትም የከፋ ኃጢአት ነው።እስራኤል በስሕተት፣ በጣዖት አምልኮ፣ በክፋትና በኃጢአት ከተዘፈቀው ዓለም በተቃራኒ ምስክር እና በእውነት የሚመላለስ ቅዱስ ሕዝብ እስከ ሆነ ድረስ፣ በመካከላቸው ለነበሩ እጅግ ደካሞች እና አብልጠው የተገለሉ ወገኖች መልካም መሆን ይጠበቅበታል። ያለበለዚያ ግን ምስክርነታቸው ከንቱ ይሆናል።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ያዕ. 1፡27-2፡11። ጌታ በዘዳግም መጽሐፍ ለሕዝቡ የነገረውን ያዕቆብ መልሶ የሚያንጸባርቅበት መንገድ ምን ይመስላል? ያዕቆብ በድኾች ላይ የሚደርሰውን በደል ከአሥርቱ ትእዛዛት ጋር ማዛመዱ ምን ትርጉም አለው?



ምንም እንኳ በዐሥርቱ ትእዛዛት ውስጥ ሐብታሞች በድኾች ላይ የሚፈጽሙትን አድልዎ በቀጥታ የሚያሳይ ነገር ባይኖርም፣ ሕጉቹን በጽኑ እጠብቃለሁ እያሉ ድኾችን ወይም ችግረኞችን በግፍ መበደልና አማኝ ነኝ ማለት--በእምነት መቀለድ ነው። ባልንጀራን እንደ ራስ መውደድ ከሁሉ የላቀው የአምላካዊ ሕግ መገለጫ ነው። ይህ እንደ ያዕቆብ ዘመን እንዲሁም እስራኤላውያን በቅድስቲቱ ምድር ድንበር ላይ ሆነው ሙሴ እንደተናገራቸው እንደዚያች ሰዓት--እነሆ ዛሬም ወቅታዊ እውነት ነው።

እኛ ሕጉን በጽኑ እንደሚጠብቁ እንደ ሰባተኛ ቀን የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂነታችን፤ የያዕቆብን እና የዘዳግም መልእክቶችንም በቁም ነገር የምንመለከተው ለምንድን ነው? በያዕቆብ መጽሐፍ በቀረበው ነጥብ መሠረት፣ ሕጉን በመጠበቅ ዙሪያ የሚኖረን እምነት በመካከላችን ያሉ ድኾችንና ችግረኞችን ለመርዳት ያለንን ቁርጠኝነት ብቻ የሚያጠነክርልን ለምንድን ነው?





ጥቅምት 1
Oct 1


ተጨማሪ ሀሳብ


አስራኤላውያን በዳዊት እና በሰሎሞን አገዛዝ ሥር በነበሩባቸው በእነዚያ ምርጥ ጊዜያቶች አገሪቱ አብልጣ በእግዚአብሔር ልትባረክ ትችል የነበረ ቢሆንም፤ በመካከላቸው የነበሩትን ድኾች፣ ችግረኞች እና መጻተኞች ይጨቁኑ እንደ ነበር ለመገመት አያዳግትም። “እናንተ ደኻውን ትረግጣላችሁ፤ እህል እንዲሰጣችሁም ታስገድዱታላችሁ፤ ስለዚህ በተጠረበ ድንጋይ ቤት ብትሠሩም፣ በውስጡ ግን አትኖሩም፤ ባማሩ የወይን ተክል ቦታዎች ወይን ብትተክሉም፣ የወይን ጠጁን ግን አትጠጡም፤ ኃጢአታችሁ ምንኛ ታላቅ እንደ ሆነ፣ በደላችሁም የቱንም ያህል እንደ በዛ እኔ ዐውቃለሁና። ጻድቁን ትጨቁናላችሁ፤ ጉቦም ትቀበላላችሁ፤ በፍርድ አደባባይም ድኻውን ፍትሕ ትነጥቃላችሁ።” (አሞጽ 5፡ 11-12)። “እግዚአብሔር፣ ከአለቆችና ከሕዝቡ ሽማግሌዎች ጋር እንዲህ ሲል ይፋረዳል፤ ‘የወይኔን ቦታ ያጠፋችሁ እናንተ ናችሁ፤ ከድኾች የዘረፋችሁትም በቤታችሁ ይገኛል’ ” (ኢሳ. 3፡14)።


የመወያያ ጥያቄዎች



1.እስራኤላውያን በግብፅ “መጻተኞች” እንደነበሩ ማስታወስ የነበረባቸው አንዱ ምክንያት፣ እነርሱ በግብፅ መጻተኞች በነበሩበት ወቅት ጌቶቻቸው እንዲያደርጉባቸው የማይወዱትን እነሱም በመካከላቸው በሚገኙ መጻተኞች እና በተገለሉ ሰዎች ላይ እንዳያደርጉ ነው። ይህ እውነት በየሱስ ደም ከኃጢአት ባርነት ነጻ መውጣታችንን ከሚያበስረው የወንጌል ጽንሰ ሀሳብ ጋር እንዴት ይዛመዳል? የሱስ ለእኛ ያደረገልን ነገር--እኛ ሌሎችን እንዴት መያዝ እንዳለብን፣ በተለይም በዙሪያችን ካሉ ረዳተ ቢስ ወገኖች ጋር ከሚኖረን አግባብ ጋር ያሉ ቀጥተኛ ተዛምዶዎች የትኞቹ ናቸው?

2.በትክክለኛው ቀን አምልኮ ልናደርግ፣ የሞትን ተጨባጭ እውነታ፣ ስለ ገሐነም፣ ስለ አውሬው ምልክት እና የመሳሰሉት ልናስተውል እንችላለን። ይህ መልካም ነው። ነገር ግን ሌሎችን የምናስተናግድበት መንገድ የሚያጸይፍ ከሆነ ወይም በመካከላችን ያለውን ደካማ የምንጨቁን ከሆነ ወይም ደግሞ በአንድ ሁኔታ ላይ ፍርዳችንን እንድንሰጥ ስንጠየቅ ፍትሕን በቅንነት የማናገለግል ከሆነስ? በተለይ ካለን እውነት አኳያ በይበልጥ ጠንቃቆች ልንሆን የሚገባው ለምንድን ነው? እውነትን ጠንቅቀን እንድናውቅ ብቻ ነው እግዚአብሔር የሚፈልገው? ይህ ለእኛ አደገኛ ወጥመድ የሆነው ለምንድን ነው?

3.እምነታችን በተለምዶ “ሰብአዊ መብቶች” ተብለው የሚጠሩትን ጽንሰ ሀሳቦች መረዳት እንድንችል ምን ሚና ሊኖረው ይችላል?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL