የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘዳ. 6:4-5፣ ዘዳ. 10:12፣ ኤፌ. 2:1–10፣ ራእ. 14:6-7፣ ዘዳ. 4:37፣ ዘዳ. 11:1፣ ማር. 12:28–30።
የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “ ‘አምላክህ እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህ ውደድ’ ” (ዘዳ.6፡5)።
በ
አይሁድ እምነት በጣም አስፈላጊ ከሚባሉ ጸሎቶች አንዱ የተወሰደው
ከዘዳ. ምዕ. 6 ነው። ጸሎቱ “ሽማ” (በአማርኛ--ስማ) በመባል
የሚታወቅ ሲሆን የመጀመሪያውን የዕብራይስጥ የጸሎት ቃል መሠረት
ያደረገ ነው። ስርወ ቃሉ “ሽማ” ሲሆን ይኸውም “ስማ”፣ “መስማት” ከዚያም
አልፎ “መታዘዝ” የሚል ፍቺ አለው። ይህ ቃል በዘዳግም ብቻ ሳይሆን
በመላው ብሉይ ኪዳን ተደጋግሞ ይታያል።
የሽማ ጸሎት የመጀመሪያው መስመር እንደሚከተለው ይነበባል፡-
ሽማ ኢስራኤል አዶናይ ኤሎሂኑ አዶናይ ኤሃድ
ትርጉሙ፡ “ ‘እስራኤል ሆይ ስማ፤ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ
እግዚአብሔር ነው’ ” (ዘዳ. 6፡4) የሚል ነው። ብዙ ጊዜ አይሁዶች ሲጸልዩ
ዓይኖቻቸውን ይሸፍናሉ፤ ይህ ደግሞ ስለ እግዚአብሔር ከማሰብ ምንም
ነገር እንዳያስተጓጉላቸው ከማድረግ የመነጨ ነው። ይህ የሽማ የመጀመሪያ
መስመር አዶናይ ኤሎሂኑ “አምላካችን እግዚአብሔር” አንድ አምላክ መሆኑን
የሚያረጋግጥና የእስራኤል ታማኝነት ለሌሎች “አማልክት” ሳይሆን ለእርሱ
ብቻ ሊሆን እንደሚገባ አጽንኦት ይሰጣል።
ይህ አንድ መስመር--የእስራኤል ልጆች ወደ ተስፋይቱ ምድር ሊገቡ ሲሉ
ሙሴ ያደረገው የመጀመሪያ ንግግር አካል ነው። ያንን የመክፈቻ መስመር
ተከትሎ የሚመጣው ብርቱ የእውነት መግለጫ እንደዚያን ጊዜ ሁሉ ዛሬም
ወሳኝ ነው።
ሙሴ ለእስራኤል ልጆች ታሪካቸውን ከነገራቸው በኋላ ምድሪቱን ለመውረስና
በምድሪቱ ላይ ዕድገት ለማስመዝገብ ምን ማድረግ እንዳለባቸው መመሪያ
መስጠት ጀመረ። በእርግጥ አብዛኛው የዘዳግም መጽሐፍ ይህንኑ ነው
የሚያትተው ብሎ አንድ ሰው ሊሞግት ይችላል፡ ጌታ ከአባቶቻቸው ጋር
የገባውን ኪዳን ይፈጽም ዘንድ በጸጋው ከእነርሱ ጋር ለገባው ውል ታማኝ
ለመሆን ምን ማድረግ እንዳለባቸው ለሕዝቡ እየነገረ ነበር።
ዘዳግም ምዕ. 6 እንደሚከተለው ይጀምራል፡ “ ‘ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ
በምትወርሷት ምድር እንድትጠብቁት አስተምራችሁ ዘንድ አምላካችሁ
እግዚአብሔር የሰጠኝ ትእዛዝ፣ ሥርዐትና ሕግ ይህ ነው፤ ይኸውም፣
የምሰጣችሁን ሥርዐቱንና ትእዛዛቱን ሁሉ በመጠበቅ፣ ዕድሜያችሁ እንዲረዝም
አንተ፣ ልጆችህና ከእነርሱ በኋላ የሚመጡት ልጆቻቸው በሕይወት ዘመናችሁ
ሁሉ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትፈሩት ዘንድ ነው’ ” (ዘዳ. 6፡1-2)።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘዳ. 6፡4-5። ጌታ እግዚአብሔር በቁ. 5
ለእስራኤል ልጆች የሰጠው ትዕዛዝ ምንድን ነው?
አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ ውደድ…? በእነዚያ ሁሉ ሕጎች፣
ማስጠንቀቂያዎች፣ ደንቦች እና ድንጋጌዎች መሃል ሕዝቡ እግዚአብሔርን
እንዲወድ ጥሪ መቅረቡ ምንኛ አስደሳች ነው? እንደው ድደደው ብቻ ሳይሆን
ነገር ግን “ ‘በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህ” በሚል
መቅረቡ የዚህን ፍቅር በፍጽምና የተሞላ ተፈጥሮ አመላካች ነው።
እግዚአብሔርን በፍጹም ልብ፣ በፍጹም ነፍስ፣ በፍጹም ኀይል መውደድ
ማለት ለእርሱ የሚኖረን ፍቅር ከማንኛውም ነገርም ሆነ አካል የላቀ መሆን
አለበት የሚል አንደምታ አለው። ምክንያቱም እርሱ የሕልውናችንም ሆነ
የማንኛውም ነገር መሠረት ነው። ለእርሱ የሚኖረን ፍቅር ሌላውን ሁሉ
በተገቢ መንገድ እንድንወድ ሊያደርገን ይገባል።
በዕብራይስጥ፡ በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህ--የሚለው
ሀረግ የቀረበው በነጠላ ነው። እግዚአብሔር በአጠቃላይ ለሕዝቡ እየተናገረ
የነበረ ቢሆንም ነገር ግን የአጠቃላዩ ጥንካሬ የእያንዳንዱ ድምር ውጤት
መሆኑ እሙን ነው። እያንዳንዳችን የግዙፉ አካል ክፍል ብንሆንም፤ በተናጠል
ለእርሱ ታማኝ እንድንሆን ጌታ ይፈልጋል። የታማኝነታችን መሠረት--ለእርሱ
ካለን ፍቅር፣ ከማንነቱና ለእኛ ካደረገልን ነገር ሊመነጭ ይገባል።
እግዚአብሔርን በፍጹም ልብ፣ በፍጹም ነፍስ፣ በፍጹም ኀይል
መውደድ ምን ማለት ነው?
የእስራኤል ልጆች ባሏቸው ነገሮች ሁሉ እግዚአብሔርን እንዲወዱት ሙሴ ነግሯቸው ነበር። ሆኖም ከጥቂት ቁጥሮች ቀደም ብሎ፡ “ ‘እግዚአብሔርን ትፈሩት ዘንድ’ ” (ዘዳ. 6፡2) የሚል ሌላ ትእዛዝ ሰጥቷቸው ነበር። ጥቅሱን ያንብቡ፡ ዘዳ. 10፡12። በዚህ ጥቅስ ፍቅርንና ፍርሃትን አስመልክቶ ምን ይላል? እንዴትስ እንረዳዋለን?
በአንድ ጥቅስ ውስጥ እግዚአብሔርን እንዲፈሩ እና እርሱን እንዲወዱ ተነግሯቸዋል። “ፍርሃት” በተሰኘው ቃል ዙሪያ ካለን የጋራ ግንዛቤ አኳያ ሀሳቡ የሚቃረን ሊመስለን ቢችልም--አይቃረንም። ይልቁንም እግዚአብሔርን መፍራት--በማንነቱ፣ በሥልጣኑ፣ ኃያልነቱ፣ ፍትሐዊነቱና ጻድቅነቱ የተነሣ የሚሰማን አክብሮታዊ ፍርሃት--በተለይ ከኃጢአተኝነታችን፣ ደካማነታችን እና ሙሉ ለሙሉ በእርሱ ላይ የተደገፍን ከመሆናችን ጋር ስናነጻጽረው ተፈጥሮአዊ ምላሽ ሊሆን ይችላል። እኛ የወደቅን፣ የእግዚአብሔርን ሕግ የጣስን--ከጸጋው የተነሣ ባይሆን ኖሮ የዘላለም ሞት የሚገባን ፍጡራን ነበርን። ጥቅሱን ያንብቡ፡ ኤፌ. 2፡1-10። እነዚህ ጥቅሶች እግዚአብሔርን በተመሳሳይ ጊዜ እንዴት መፍራት እና መውደድ እንደምንችል እንድናስተውል እንዴት ሊረዱን ይችላሉ?
ምንም እንኳ “የቁጣ ልጆች” ብንሆንም (ለዚህ ነው እርሱን መፍራት ያለብን)
ክርስቶስ ለእኛ ሞቶ በእርሱ አዲስ ሕይወት አጎናጸፈን። ይህ ደግም ያለፈው
ኃጢአት እና ኩነኔ ላይ ነጻነት መቀዳጀትን ያካትታል (ለዚህ ነው እርሱን
መውደድ ያለብን)። ይህ ዛሬ ለእኛ እውነት የሆነውን ያህል፣ ይኸው መርኅ
በጥንቷ እስራኤል ላይም እንዲሁ ተፈጻሚነት ነበረው፡ ለግብፅ ባርነትና ጭቆና
የተኮነኑ ምርኮኛ ሕዝቦች የነበሩ ቢሆንም፤ ለታላቅ መቤዠት የዳረጋቸው
እግዚአብሔር ለእነርሱ የነበረው ፍቅርና ቸርነት ብቻ ነበር። “ ‘በግብፅ ሳለህ
አንተም ባሪያ እንደ ነበርህ፣ ከዚያም አምላክህ እግዚአብሔር በጸናች እጅና
በተዘረጋ ክንድ እንዳወጣህ አስታውስ።’ ” (ዘዳ. 5፡15)።
ከዚህ አኳያ እነዚህ
ሕዝቦች እግዚአብሔርን በተመሳሳይ ጊዜ ቢፈሩና ቢወዱ ብዙም የሚደንቅ
አይሆንም። እነርሱ ይህን ማድረግ ከነበረባቸው፣ የሱስ ስለ እኛ በመስቀል
ላይ የመሞቱ እውነት ያለን ወገኖች ይህን ምን ያህል በላቀ ማድረግ ይኖርብን
ይሆን?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 14፡6-7። “እግዚአብሔርን ትፈሩት
ዘንድ” የሚለው ትእዛዝ ጌታ ስለ መጨረሻዎቹ ቀናት ለዓለም
የሰጠው ቀዳሚ መልእክት ለምን ሊሆን እንደቻለ የምናስተውለው
እንዴት ነው? በዓለም ላይ ስለሚመጣው ነገር የምናውቀውን
ከግምት ውስጥ ስናስገባ--ያ ትዕዛዝ አብልጦ ትርጉም የሚሰጠው
ለምንድን ነው?
በዘዳግም መጽሐፍ ለአይሁድ ሕዝብ በተሰጡ ሕጎች እና መመሪያዎች
እንዲሁም ተግሳጾች እና ማስጠንቀቂያዎች መሃል ሕዝቡ አምላካዊውን
“ትእዛዛዝ፣ ሥርዓትና ሕግ” የግድ መጠበቅ የነበረበት ቢሆንም፤ ከሁሉም
በፊትና ከሁሉም በላይ ግን እግዚአብሔርን በፍጹም ልባቸው፣ ነፍሳቸውና
ኃይላቸው መውደድ ይጠበቅባቸው ነበር። ያን ለማድረግ ደግሞ በቂ ምክንያት
ነበራቸው።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘዳ. 4፡37፣ ዘዳ. 7፡7-8፣ 13፣ ዘዳ. 10፡
15፣ ዘዳ. 23፡5፣ ዘዳ. 33፡3። ጥቅሶቹ እግዚአብሔር ለሕዝቡ
ስላለው ፍቅር ምን ያስተምራሉ?
እግዚአብሔር ምን ያህል አባቶቻቸውን እና እነርሱን እንደሚወድ ሙሴ
በተደጋጋሚ በዘዳግም መጽሐፍ ተናግሯል። ደግሞም ከቃላት በላይ ጌታ
ይህን ፍቅር በድርጊቶቹ ገልጧል። ምንም እንኳ ጉድለት፣ ውድቀትና በደል
ቢገኝባቸውም--እግዚአብሔር ለእነርሱ የነበረው ፍቅር በብርቱ የተገለጠና
ጽኑ ነበር።
“እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና” (1ዮሐ. 4፡19)። ጥቅሱ እግዚአብሔርን ለምን
መውደድ እንዳለብን ማስተዋል እንድንችል እንዴት ይረዳናል?
እግዚአብሔር እኛን የወደደው ገና ከመፈጠራችን አስቀድሞ ስለ ነበር፣ እነሆ
የደኅንነትን እቅድ “ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ” አወጣ (ኤፌ. 1፡4)።
“ስለ መዳናችን የተነደፈው ዕቅድ ቀደም ብሎ የተሰጠበት እንጂ አዳም
ከወደቀ በኋላ የተጠነሰሰ አይደለም። ‘ምስጢር በመግለጽ ከጥንት ጀምሮ
ተሰውሮ የነበረውን’ ይላልና፤ ሮሜ 16፡25። ይህም ዘላለማዊ የሆነውን
የእግዚአብሔርን ዙፋን መርኅዎች ለማሳወቅ ነው።” የዘመናት ምኞት ገጽ 12
እግዚአብሔር በእርግጥም የፍቅር አምላክ በመሆኑ ስለ እኛ ራሱን መሥዋዕት
አድርጎ ወደ መስቀሉ አመራ “ራሱን ዝቅ አደረገ፤ አስከ ሞት፣ ያውም በመስቀል
ላይ እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ” (ፊልጵ. 2፡8)። ስለዚህ እኛ ዛሬ
ምናልባትም የእስራኤል ልጆች ፈጽሞ ሊገምቱት ያልቻሉት የእግዚአብሔር
ፍቅር መገለጥ አለን።
እግዚአብሔር ፍቅር ከመሆን ይልቅ በጥላቻ የተሞላ ወይም ግድ
የማይሰጠው አምላክ ቢሆን ኖሮስ? ይህ ዓለም ምን ዓይነት ሊሆን
ይችል ነበር? ለእኛ የተገለጠው አምላካዊ ፍቅር በእርግጥም
ሐሴት ልናደርግበት የሚገባ የሆነው ለምንድን ነው?
ባጠቃላይ እስራኤላውያን እንደ ሕዝብ እግዚአብሔርን እንዲወዱ ጥሪ ቀርቦላቸው ነበር። ይሁን እንጂ ጥሪው ገቢራዊ መሆን የሚችለው በእያንዳንዱ ግለሰብ ደረጃ ነበር። ለእያንዳንዱ ሰው የመምረጥ ነጻነት በተሰጠው መሠረት፣ ማንኛውም እስራኤላዊ እግዚአብሔርን ለመውደድ መምረጥ ነበረበት። ይህን ፍቅር ማሳየት የሚችሉት ደግሞ እርሱን በመታዘዝ ነበር። የሚከተሉትን ጥቅሶች ምን ያመሳስላቸዋል? በመካከላቸው ያለው የጋራ ጭብጥ ምንድነው? ማለትም ዘዳ. 5:10________________________________________________
ዘዳ. 7:9_________________________________________________
ዘዳ. 10:12_______________________________________________
ዘዳ. 11:1________________________________________________
ዘዳ. 19:9________________________________________________
የእግዚአብሔር ቃል ከዚህ በላይ እንዴት ግልጽ መሆን ይችላል?
እግዚአብሔር ፍቅሩን የገለጸልን በቃላት ብቻ አይደለም--በድርጊት ጭምር
እንጂ! በተመሳሳይ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ፍቅራቸውን በድርጊት ይገልጹ
ዘንድ ተጠርተዋል። በመሆኑም ከላይ በቀረቡት ጥቅሶች እንደተመለከተው፣
እግዚአብሔርን መውደድ እርሱን ከመታዘዝ ጋር የማይነጣጠል ነው።
ስለዚህ ዮሐንስ፡ “እግዚአብሔርን መውደድ ትእዛዛቱን መፈጸም ነውና”
(1ዮሐ. 5፡3) ብሎ ሲጽፍ ወይም የሱስ፡ “ ‘ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ’
” (ዮሐ. 14፡15 /1962 ትርጉም/) ብሎ ሲናገር--ጥቅሶቹ ይህን መሠረታዊ
አስተምህሮ እየገለጹ ነው። እግዚአብሔርን መውደድ ሁሌም ቢሆን እርሱን
በመታዘዝ መገለጥ አለበት። ይህ የነበረና ወደፊትም የሚኖር ሐቅ ነው።
ይህ ለእግዚአብሔር መታዘዝ ለሕጉ ማለትም አራተኛውን የሰንበት ትእዛዝ
ለሚጨምረው ዐሥርቱ ቃላት መታዘዝ ነው። አራተኛውን ትእዛዝ መጠበቅ
ሌሎቹን ዘጠኝ ትእዛዛት ከመጠበቅ ባለፈ ሕጋውያን ሊያሰኝ አይችልም።
ምንም እንኳ ከትእዛዛቱ አንዱንም ለመጠበቅ መሞከር ሕጋውያን ሊያሰኝ
ቢችልም፤ ነገር ግን ለእግዚአብሔር ሊኖር ከሚችል ፍቅር ውጪ እንደዚያ
ዓይነቱ መታዘዝ ሊኖር አይችልም። እግዚአብሔርን በተለይ በክርስቶስ የሱስ
ባደረገልን ነገር ከልባችን ስንወደው እርሱን መታዘዝ እንፈልጋለን--ምክንያቱም
እንድናደርግ የሚጠይቀን ይህንኑ ነው።
እስራኤላውያን ከግብፅ ከተዋጁ በኋላ እግዚአብሔርን እንዲወዱና
እንዲታዘዙ ሙሴ በተደጋጋሚ ይነግራቸው ነበር። በዚህም ፍቅራቸውና
መታዘዛቸው እግዚአብሔር ለሰጣቸው መቤዠት ምላሽ ነበር። እነዚህ
ሕዝቦች በጌታ ተዋጅተዋል። እንግዲህ ትእዛዛቱን በታማኝነት በመጠበቅ
ምላሽ ይሰጣሉ። ታዲያ ይህ ሁኔታ ከዛሬው በምን ይለያል?
እግዚአብሔርን የመታዘዝ ግላዊ ተሞክሮዎ ምን ይመስላል?
እግዚአብሔርን እንዲታዘዙ የሚያደርጎት ምክንያቶች ምንድን
ናቸው? ለእርሱ ከሚኖር ፍቅር ውጪ ሊታሰብ የማይችለው
ለምንድን ነው? እዚህ ላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊው ፍርሐት ምን
ሚና ሊኖረው ይችላል?
አንዳንድ ክርስቲያኖች በተለያዩ ምክንያቶች ብሉይ ኪዳንን ከአዲስ ኪዳን
ለመነጠል ቢጥሩም፤ የአዲስ ኪዳን እውነተኛ ትርጉም--ትርጉም ዐልባ
እንዲሆን ከማድረግ ውጪ የሚፈይዱት አይኖርም። አዲስ ኪዳን ስለ የሱስ
ሕይወት፣ ሞት፣ ትንሣኤ እና የሊቀ ካህንነት አገልግሎት ባቀረበው መገለጥና
ሥነ መለኮታዊ ማብራሪያ አያሌ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች መፈጸማቸውን
ያመላክታል። ብሉይ ኪዳን በብዙ መንገዶች የአዲስ ኪዳንን ታሪካዊ ዳራ፣
ዐውድ እና መሠረት ይሰጠናል። ሁለቱም ኪዳኖች የእግዚአብሔርን ርኅራኄ
እና ፍቅር ይገልጻሉ።
የሱስን ጨምሮ ብዙዎች አዲስ ኪዳንን ደጋግመው የሚጠቅሱበት አንዱ
ምክንያት ይኸው ነው።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማር. 12፡28-30። ከሁሉ ስለሚበልጠው
ትእዛዝ የተጠየቀው ጥያቄ ምን ነበር? የሱስ ምን ዓይነት ምላሽ
ሰጠ? መልሱን ከየት ጠቀሰ?
ሕግን ለመረዳት እና ሕጉ እንዴት ሥራ ላይ መዋል እንዳለበት ለማወቅ
ህይወቱን ያዋለ አንድ ጸሐፍት እንዲህ ያለውን ጥያቄ መጠየቁ ትኩረት
ይስባል። እነዚህ ሰዎች ልንታዘዛቸው ይገባል ብለው ያመኑባቸው አያሌ ሕጎች
(በኋለኛው የአይሁድ ወግ መሠረት 613 ሕግጋት) የነበሯቸው ከመሆኑ አኳያ-እነዚህ ሁሉ በአንድ ጥያቄ እንዲጠቃለሉ ቢፈልጉ አያስገርምም።
ታዲያ የሱስ ምን አደረገ?
በቀጥታ ወደ ዘዳ. 6 አምርቶ፡ “ ‘እስራኤል ሆይ ስማ፤ አምላካችን እግዚአብሔር
አንድ እግዚአብሔር ነው!’ ” (ዘዳ. 6፡4) ይልና እግዚአብሔርን በፍጹም
ልብ፣ ነፍስ እና ኃይል ስለ መውደድ የሚናገረውን ጥቅስ ይጠቅሳል። ጌታ
ብቸኛው አምላካቸው መሆኑን የሚያረጋግጠውን ቁልፍ ነጥብ ካመላከታቸው
በኋላ፤ በዚያ ታላቅ እውነት መሠረት እርሱን ከሁሉ አስበልጠው እንዲወዱ
መጠራታቸውን ይጠቁማቸዋል።
ከዚህ ትእዛዝ የላቀ ምን ዓይነት “ወቅታዊ እውነት” ሊኖር ይችላል?
በምድር መጨረሻዎቹ ቀናት የፍጻሜዎቹ ክስተቶች ሲገለጡና እያንዳንዱ
ሰው በየትኛው ጎራ መሰለፍ እንዳለበት በአስደናቂ ትዕይነት የተሞላ ጥሪ
ሲቀርብለት፤ የእግዚአብሔር ሕጎች (ራእ. 14፡12) ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ።
በመጨረሻ፣ ስደት ተጋርጦብን እንኳ የምንመርጠው ጎራ እግዚአብሔርን
በእውነት መውደድ፣ አለመውደዳችን ላይ የተመሠረተ ይሆናል። ያ ውሳኔ
የሚጠይቅ ጉዳይ እንደመሆኑ--በፍጹም ልባችን፣ ነፍሳችንና ኃይላችን
እግዚአብሔርን ወደ መውደድ መምጣት የምንችልበት ብቸኛው መንገድ
ርኅራኄውን፣ ፍቅሩን እና ጸጋውን ለራሳችን ማወቃችንና መለማመዳችን ነው።
አንድ ሰው፡ በግል አይተው የማያውቁትን አምላክ እንዴት
መውደድ ይችላሉ--ብሎ ቢጠይቆት ምን ይመልሳሉ? መልስዎን
በክፍል ውስጥ ያቅርቡ።
በክርስቶስ መስቀል የተዋጁት ወገኖች ዘላለማዊ ሳይንስ
እና መዝሙር ይሆናል። በከበረው ክርስቶስ ውስጥ የተሰቀለውን ክርስቶስ
ይመለከታሉ። በኃይሉ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ዓለማት የፈጠረውና ሁሉንም
በግዙፉ ሕዋ ውስጥ ደግፎ የያዘው የተወደደው አምላክ፣ የሰማይ ንጉሥ፣
ኪሩቤል እና አንጸባራቂው ሱራፌል ሊሰግዱለት የሚወዱት ጌታ--የወደቀውን
ሰብዓዊ ፍጡር ከፍ ለማድረግ ሲል ራሱን ትሑት ማድረጉ ፈጽሞ የሚዘነጋ
አይሆንም። እነሆ እርሱ የኃጢአትን በደል እና ሐፍረት ተቀበለ፣ የአባቱ ፊት
ከእርሱ ተሸሸገ፣ የጠፋው ዓለም ወዮታ ልቡን ሰብሮ ሕይወቱን በቀራኒዮ
ቀጠፈ። የዓለማት ሁሉ ፈጣሪና ዳኛ ክብሩን ትቶ ስለ ሰው ልጆች ፍቅር ሲል
ራሱን ማዋረዱ፣ ሁሌም በዩኒቨርስ በአድናቆትና ከበሬታ ሲፈጥር ይኖራል።
የዳኑት ወገኖች ይህን የዋጃቸውን ጌታ እና በገጽታው ላይ የሚያበራውን የአብ
ዘላለማዊ ክብር ሲመለከቱ፤ ከዘላለም እስከ ዘላለም ያለውን ዙፋኑን ሲያዩና
መንግሥቱ መጨረሻ እንደሌለው ሲያውቁ፣ እጅግ ደስ በሚያሰኝ ታላቅ ድምጽ
እንዲህ ሲሉ አዜሙ፡ ‘የታረደው በግ ክብርና ሞገስ ይገባዋል፣ እነሆ በከበረው
ደሙ ለእግዚአብሔር ዋጅቶናልና!’ ”—Ellen G. White, The Great Controversy, pp. 651, 652.
1.ከላይ የቀረበውን የኤለን ጂ. ኋይት መግለጫ ያንብቡ።
ለእግዚአብሔር የሚኖረን ፍቅር ከሁሉ የላቀ ሊሆን እንደሚገባ
እንድንገነዘብ እንዴት ይረዳናል? “ስፍር ቁጥር የሌላቸውን
ዓለማት የፈጠረውና ሁሉንም በግዙፉ ሕዋ ውስጥ ደግፎ የያዘው”
አምላክ ስለ እኛ ወደ መስቀል መሄዱ ምን ማለት እንደሆነ ያስቡ።
ይህ እውነት ከእግዚአብሔር ጋር ላለን ግንኙነት መሠረት ሊሆን
የሚገባው ለምንድን ነው?
2.እግዚአብሔርን መውደድ እና መፍራት በሚለው ጽንሰ ሀሳብ
ላይ ቆይታ ያድርጉ። ሁለቱንም ጉን ለጎን ማስኬድ የምንችለው
እንዴት ነው? ለምን?
3.ነገሮች በሕይወታችን በመልካም ሁኔታ ክንውን ሲያገኙ
እግዚአብሔርን ብንወድ ብዙም ላያስገርም ይችላል። አሳዛኝ
ሁናቴዎች ሲከሰቱስ? ከበጎዎቹ ጊዜያቶች ይልቅ በእንዲህ
ዓይነቶቹ ወቅቶች እግዚአብሔርን አብልጦ መውደድ በእጅጉ
አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
4.በሐሙስ ትምህርት መጨረሻ የቀረበውን ጥያቄ ይመልከቱ።
እግዚአብሔርን መውደድ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ለማያምን
ሰው ማብራራት የሚችሉባቸው የተለያዩ ዘዴዎች የትኞቹ ናቸው?
እኛ ሰዎች በአካል አይተን የማናውቀውን ሰው እንዴት ልንወደው
እንችላለን? ቢያንስ በአካል አይተነው አለማወቃችን ምን ችግር
አለው?