የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ጌታ እስኪመጣ ድረስ የእርሱን ንብረት ማስተዳደር


የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 1ኛ ሩብ ዓመት 2023

ጥር 6-12

3ኛ ትምህርት

Jan 14 - 20




አስራት የመመለስ ውል (ስምምነት)



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ትምህርት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ዘፍጥረት 14፡ 18-20፤ ሚልኪያስ 3፡10፤ ዘዳግም 12፡5-14፤ ዘሌዋውያን 27፡30፤ 1ኛ ነገስት 17፡9-16፤ 1ኛ ቆሮ. 4፡1፣2።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ“በቤቴ ውስጥ መብል እንዲሆን አሥራቱን ሁሉ ወደ ጎተራ አግቡ የሰማይንም መስኮት ባልከፍትላችሁ፥ በረከትንም አትረፍርፌ ባላፈስስላችሁ በዚህ ፈትኑኝ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር” (ሚልክያስ 3:10)።

በ ዘፍጥረት ምዕራፍ 14 ላይ አብርሐም የወንድሙን ልጅ ሎጥን፣ የሎጥን ቤተሰብ እና ሌሎች ከሶዶም የተወሰዱ ሰዎችን ካዳነበት ውጤታማ የሆነ ምርኮኛን የማስመለስ ተልዕኮ ተመልሶአል። የሶዶም ንጉሥ ሕዝቡን ስላዳነ እጅግ በማመስገን በጦርነቱ የተገኘውን ምርኮ በሙሉ ለአብርሃም ሰጠው። አብርሃም ስጦታውን መቀበልን እምቢ ማለት ብቻ ሳይሆን ካለው ሁሉ ለመልከጼዴቅ አሥራት ሰጠ።

ከአብርሃም አሥራት የመመለስ ልምምድ በኋላ ወዲያውኑ እግዚአብሔር እንዲህ አለ፡- “ አብራም ሆይ፥ አትፍራ እኔ ለአንተ ጋሻህ ነኝ፤ ዋጋህም እጅግ ታላቅ ነው” (ዘፍ. 15:1)።እግዚአብሔር ለአብርሃም “አትጨነቅ። እኔ ለአንተ ጠባቂና ሰጭ እሆናለሁ›› እያለው ነበር። ከብዙ ጊዜ በኋላ የእሥራኤል ልጆች ወደ ከነዓን ምድር ለመግባት ተቃርበው ሳለ ሙሴ እንዲህ አላቸው፡- “ከእርሻህ በየዓመቱ ከምታገኘው ከዘርህ ፍሬ ሁሉ አሥራት ታወጣለህ።ሁልጊዜ አምላክህን እግዚአብሔርን መፍራት ትማር ዘንድ፥ ስሙ እንዲጠራበት በመረጠው ስፍራ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት የእህልህን የወይን ጠጅህንም የዘይትህንም አሥራት የላምህንና የበግህንም በኵራት ብላ” (ዘዳግም 14:22፣ 23)።

ኤለን ጂ ኋይት እንዲህ በማለት ጽፋለች፡- “ለሙሴ ግልጽ የሆነ የስጦታ ሥርዓት ከመሰጠቱ ረዥም አመታት በፊት በአዳም ዘመን እንኳን ወንዶች ለኃይማኖታዊ ተግባሮች ለእግዚአብሔር ስጦታን እንዲያቀርቡ ይጠበቅባቸው ነበር።”—Testimonies for the Church, vol. 3, p. 393. ይህ ሁሉ ዛሬ ለእኛ ምን ማለት ነው? *የዚህን ሳምንት ትምህርት ለጥር 13 ሰንበት ለመዘጋጀት አጥኑ።

ጥር 7
Jan 15

አሥራት ከአሥር አንድ ነው


መዝገበ ቃላት አሥራትን ‹‹የአንድ ነገር አሥረኛው ክፍል›› ወይም ‹‹ከመቶ አሥር›› ብለው ይተረጉማሉ። ይህ ትርጉም የተወሰደው ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ሳይሆን አይቀርም። አሥራት ከገቢያችን ወይም ከትርፋችን ከመቶ አሥሩን ለእግዚአብሔር መመለስ ነው፡ በመጀመሪያ ደረጃ ያለን ነገር ሁሉ የእርሱ መሆኑን እንረዳለን። ለእሥራኤላውያን በሲና ተራራ የተሰጠው የአሥራት ህግ አሥራት ቅዱስና የእግዚአብሔር መሆኑን ይጠቁማል (ዘሌ. 27፡30፣ 32ን ይመልከቱ)። እግዚአብሔር የሚጠይቀው የእርሱ የሆነውን ከመቶ አሥሩን እጅ ብቻ ነው። የምስጋና ስጦታዎቻችን ከአስራት ውጭና ተጨማሪ ናቸው። አሥራት ለክርስቲያናዊ መሰጠታችን ዝቅተኛው ምስክርነት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በየትኛውም ክፍል ቢሆን የእግዚአብሔር ድርሻ ከመቶ አሥር እጅ በታች መሆኑን የሚገልጽ ነገር አናገኝም።

ዘፍጥረት 14፡18-20ን እና ዕብራውያን 7፡1-9ን ያንብቡ። አብርሃም መልከጼዴቅን ባገኘው ጊዜ የሰጠው ምላሽ ምን ነበር? ይህ ልምምድ በታሪክ ዘመን ምን ያህል ወደ ኋላ ርቆ እንደሚሄድ ምን ያስተምረናል?



በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አሥራት ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰው በዘፍጥረት ምዕራፍ 14 ሲሆን ይህ ክፍል መልከጼዴቅ አብርሃምን ያገኘበትን ታሪክ ይነግረናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ አሥራት የተጠቀሰው የመጨረሻው ክፍል ያንኑ ግንኙነት የሚያስታውስ ሲሆን ‹‹አንድ አሥረኛ›› የሚለው ቃልና ‹‹አሥራት›› የሚለው ቃል እየተቀያየሩ በጥቅም ላይ ውለዋል (ዕብራውያን 7፡ 1-9ን ይመልከቱ)። በዕብራውያን ታሪክ ውስጥ መልከጼዴቅም ሆነ ክርስቶስ ከሌዊ ወገን አለመሆናቸውን ልብ ይበሉ፤ ስለዚህ አሥራትን መመለስ የሌዋውያንን ለአገልግሎት መለየት የሚቀድምና የሚከተል ነው። አስራት መመለስ የአይሁዶች ባህል ብቻ አይደለም፤ ከዕብራውያን ጋር በሲና የተጀመረም አይደለም። ዘፍጥረት 28፡13፣ 14፣ 20-22ን ያንብቡ። እግዚአብሔር ለያዕቆብ ሊያደርግለት ቃል የገባለት ነገር ምን ነበር? ያዕቆብ ለእግዚአብሔር የሰጠው መልስ ምን ነበር?



ያዕቆብ ከተናደደው ወንድሙ ከኤሳው ለመሸሽ ቤቱን ትቶ ሲወጣ አንድ ሌሊት ከምድር እስከ ሰማይ የተዘረጋ መሰላል የሚያሳይ ሕልም አለመ። በመሰላሉ ላይ መላእክት ሲወጡና ሲወርዱ ነበር። እግዚአብሔር ከመሰላሉ ጫፍ ቁሞ ከያዕቆብ ጋር እንደሚሆንና አንድ ቀን ወደ ቤቱ እንደሚመልሰው ቃል ገባለት። ይህ ላጤ ወጣት እውነተኛ የሆነ የመለወጥ ልምምድ ከመለማመዱ የተነሳ እንዲህ አለ፡- “ ወደ አባቴ ቤትም በጤና ብመለስ፥ እግዚአብሔር አምላኬ ይሆንልኛል፤…. ከሰጠኸኝም ሁሉ ለአንተ ከአሥር እጅ አንዱን እሰጥሃለሁ።” (ዘፍጥረት 28:21፣ 22)።

አሥራት፣ ልክ እንደ ሰንበት፣ ከጥንታዊው የእሥራኤላውያን የህግ ወይም ኃይማኖታዊ ሥርዓት የመነጨ አለመሆኑን መረዳት አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድር ነው? እኛ ከክርስቶስ ስቅለት ወዲህ ያለን ከዚህ እውነት መውሰድ ያለብን መልእክት ምንድር ነው?

ጥር 8
Jan 16

ጎተራው የት ነው?


ሚልክያስ 3፡10ን ያንብቡ። ከዚህ ጥቅስ አሥራታችን የት መሄድ እንዳለበት ምን መማር እንችላለን?



በጥቅሱ ውስጥ ዝርዝር መመሪያዎች ባይሰጡም ‹‹ጎተራ›› የሚለው ቃል ምን ማለት እንደሆነ የእግዚአብሔር ሕዝብ ማወቁ እርግጥ ነው። እግዚአብሔር በሰጠው መመሪያው ውስጥ ‹‹በቤቴ መብል ይሆን ዘንድ›› የሚለውን ሀሳብ አካትቶአል። በመጀመሪያ የእግዚአብሔር ቤት ቤተ መቅደሱ--በሲና ተራራ ከእግዚአብሔር በተሰጡ ግልጽ መመሪያዎች የተገነባው ድንኳን እንደነበር ሕዝቡ አስተውለዋል። ከዚያ በኋላ እሥራኤላውን በተስፋይቱ ምድር ሲኖሩ ማዕከላዊ ቦታ የነበረው መጀመሪያ ሴሎ ሲሆን ቀጥሎም በቋሚነት ያገለገለው በኢየሩሳሌም የነበረው ቤተ መቅደስ ነበር።

ዘዳግም 12፡5-14ን ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች የእግዚአብሔር ልጆች አሥራታቸውን የት ማስገባት እንዳለባቸው የራሳቸውን ውሳኔ መጠቀም እንዳለባቸው አያመለክቱም። ዛሬ ከእነዚህ ጥቅሶች ለራሳችን ምን መርሆዎችን መውሰድ እንችላለን?



እንደ እግዚአብሔር ቤተሰብ አባሎች አሥራታችንን ምን ማድረግ እንዳለብን በተመለከተ የእርሱን ፈቃድ መረዳትና መተግበር እንፈልጋለን። በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ የእግዚአብሔር ሕዝብ በዓመት ሶስት ጊዜ--በፋሲካ፣ በጴንጤቆስጤ ቀንና በዳስ በዓል (ዘጸ. 23፡14-17)፣ አሥራታቸውንና ሥጦታዎቻቸውን በግላቸው ለእግዚአብሔር ለማቅረብ፣ እርሱን ለማወደስና ለማምለክ ወደ ኢየሩሳሌም ይጓዙ ነበር። አሥራቱን ሌዋውያን በመላው የእሥራኤል ምድር ለሚኖሩ ወንድሞቻቸው ያከፋፍሉ ነበር (2ኛ ዜና 31፡11-21፤ ነህምያ 12፡44-47፤ ነህምያ13፡ 8-14ን ይመልከቱ)። ከዚህ ማዕከላዊ ከሆነው መጽሐፍ ቅዱሳዊ የጎተራ መርህ ጋር በተጣጣመ ሁኔታ የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን፣ ዓለም አቀፋዊ ቤተ ክርስቲያንን እንዲወክሉ አጥቢያ ኮንፍራንሶችን፣ ሚስዮኖችንና ዩኒየኖችን እንደ ጎተራ የሰየመች ሲሆን ከዚህ ጎተራ ለአገልግሎት ይከፈላል።

ምንም እንኳን አንዳንዶች አሥራታቸውን ኦንላይን ቢከፍሉም፣ ለቤተ ክርስቲያን አባላት እንዲመች ሲባል፣ አባላቱ አሥራታቸውን እንደ አምልኮ ልምምዳቸው አካል አድርገው ወደ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ያመጣሉ። የአጥቢያው ሂሳብ ሹሞች አሥራቱን ወደ ኮንፍራንስ (ወደ ሰበካው) ጎተራ ይልካሉ። ይህ በእግዚአብሔር የተቀመረና የታዘዘ የአሥራት አስተዳደር ሥርዓት የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን በዓለም ላይ ዓለም አቀፋዊና የሚያድግ ተጽእኖ እንዲኖራት አድርጓል። እያንዳንዱ ሰው አሥራቱን ለአድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን በመመለስ ፋንታ ራሱ ለመስጠት ለፈለገው ሰው ለመስጠት ቢወስን ኖሮ ምን ሊሆን እንደሚችል ያስቡ። ቤተ ክርስቲያናችን ምን ትሆን ነበር? ያ ልምምድ መጥፎ ሀሳብና ከመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ተቃራኒ የሆነው ለምንድር ነው?

ጥር 9
Jan 17

አሥራትን የመመለስ ዓላማ


ዘሌዋውያን 27፡30ንና ዘሁልቁ 18፡21፣24ን ያንብቡ። አሥራት ለምን ተግባር እንዲውል ነው እግዚአብሔር ሀሳብ የሚያቀርበው?



እግዚአብሔር የሁሉም ነገር ባለቤት ስለሆነ (መዝሙር 24፡1) እርሱ ገንዘብ እንደማያስፈልገው ግልጽ ነው። ነገር ግን አሥራት የእርሱ ስለሆነ የወንጌልን አገልግሎት ለመደገፍ ጥቅም ላይ እንድናውል ይነግረናል። ስለዚህ የእግዚአብሔር አሥራት የአገልጋዮችን የኑሮ ፍላጎት ለማሟላት ጥቅም ላይ ይውላል። በብሉይ ኪዳን ውስጥ የወንጌል አገልግሎት ኃይል የሆኑት የሌዊ ነገድ እንደ ሌሎቹ የእስራኤል ነገዶች ታላላቅ ርስቶች አልተሰጡአቸውም ነበር። የሌዊ ነገድ የመማጸኛ ከተሞችን ጨምሮ ለራሳቸው አትክልት የሚያሳድጉት በቂ መሬት ያለባቸው አንዳንድ ከተሞች ተሰጥተዋቸው ነበር። ሌዋውያን በአሥራት የሚደገፉ ሲሆን እነርሱም ከገቢያቸው አሥራት ያወጡ ነበር። የሐዋርያት ሥራ 20፡35ን ያንብቡ። እዚህ ላይ ያለው መልእክት ምንድር ነው? ይህ ከአሥራት ጥያቄ ጋር የሚገናኘው እንዴት ነው?



አሥራትን መመለስ ከእግዚአብሔር ጋር የመተማመን ግንኙነት ለመፍጠር ስለሚረዳ አስፈላጊ ነው። ከገቢአችሁ አንድ አሥረኛውን ወስዳችሁ መስጠት (ምንም እንኳን መጀመሪያውኑ የእግዚአብሔር ቢሆንም) የእምነት ተግባር ሲሆን እምነታችሁ ሊያድግ የሚችለው በሥራ ሲገለጥ ብቻ ነው። በራዕይ 13-14 ላይ እንደተገለጸው (11ኛውን ሳምንት ትምህርት ይመልከቱ) ታማኞች መግዛትና መሸጥ ስለማይችሉበት ስለመጨረሻው ጊዜ እስኪ ያስቡ። ዓለም በሙሉ እኛን በመቃወም የተነሳብን በሚመስልበት ጊዜ በእግዚአብሔር፣ በእርሱ መልካምነት፣ ኃይልና ፍቅር ላይ መታመንን ማጎልበት ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል። በታማኝነት አሥራትን መመለስ ያንን መታመን ለማጎልበት በእርግጠኝነት ይረዳል። ከዚያም በፊት፣ ያለንበት ሁኔታ ምንም ቢሆን፣ በእግዚአብሔር መታመንን መማር ለሁላችንም ምንኛ ወሳኝ ነው።

በገንዘብ ታማኝ መሆን ከሚያስፈልግባቸው ምክንያቶች ሁለተኛው ትልቅ ምክንያት ቃል የተገባውን ተጨባጭ ተስፋ ለማግኘት ነው። እንደ አስራትን ለመመለስ የተገባው ውል አካል ለመቀበል በቂ ቦታ እስከማይኖር ድረስ ታላላቅ በረከቶችን ሊሰድልን እግዚአብሔር ቃል ገብቷል። ከእኛ በተረፈው ሌሎችን እና የእግዚአብሔርን ሥራ በስጦታችን መርዳት እንችላለን። እርስዎ‹‹ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጠጥ የበለጠ የተባረከ ነው›› የሚለውን ታላቅ እውነት በምን መንገዶች ተለማምደውታል?

ጥር 10
Jan 18

አሥራት መመለስ ያለብን ከአጠቃላይ ገቢያችን ነው


ወይስ ከተጣራው ገቢያችን ነው? `በሰዓት ወይም በደሞዝ የሚከፈለን ከሆነ አስራታችንን የምናሰላው ‹‹ከገቢያችን›› ሲሆን ራሳችንን የቀጠርንና የራሳችን የንግድ ሥራ የምንሰራ ከሆንን ‹‹ከትርፋችን›› እናሰላለን። በብዙ አገሮች መንግስት እንደ ጥበቃ፣ መንገድና ድልድዮች፣ የሥራ አጥ ጥቅማ ጥቅሞች፣ ወዘተ. የመሳሰሉ ለሕዝብ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ወጪ ለመሸፈን ከሰራተኞች ደሞዝ ግብር ይቆርጣል። አጠቃላይ ወይም የተጣራ ገቢ የሚለው ጥያቄ የሚመለከተው አሥራት የምንመልሰው የዚህ ዓይነት ግብሮች ከመቆረጣቸው በፊት ወይም በኋላ በመሆኑ ላይ ነው። ሥራ ፈጥረው ራሳቸውን የቀጠሩ ሰዎች የግል ግብሮቻቸው ከመቆረጣቸው በፊት ትክክለኛ ትርፋቸውን ለመወሰን ንግዱን የሚያንቀሳቅሱበትን ወጪ በሕጋዊ መንገድ መቀነስ ይችላሉ። የአባላትን የመስጠት ልማድ ለማወቅ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት አብዛኞቹ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች አሥራት የሚከፍሉት ከአጠቃላይ ገቢያቸው ነው። ይህ ማለት የተለያዩ ግብሮች ከመቆረጣቸው በፊት ማለት ነው።

1ኛ ነገሥት 17፡9-16ን ያንብቡ። ኤልያስ ወደ ባልቴቷ ከመምጣቱ በፊት የእሷ ሁኔታ ምን ይመስል ነበር? ባልቴቷ ለራሷና ለልጇ ምግብ ከማዘጋጀቷ በፊት አስቀድማ ምን እንድታደርግ ነበር ነቢዩ የጠየቃት? አሁን እየተጠየቀ ስላለው ጥያቄ ከዚህ መረጃ ምን መማር እንችላለን?



የእግዚአብሔር ሰው ሊያገኛት እየመጣ እንደሆነ እግዚአብሔር ለሰረፕታዋ ባልቴት ነግሮአት ነበር (1ኛ ነገሥት 17፡9)። ኤልያስ ወደ እሷ ሲደርስ ያለችበትን አስከፊ ሁኔታ ነገረችው። እርሱም መጀመሪያ ውኃ እንድትሰጠው ከጠየቀ በኋላ በመቀጠል እንዲህ አላት፡- “አትፍሪ ይልቅስ ሄደሽ እንዳልሺው አድርጊ፤ አስቀድመሽ ግን ከዱቄቱ ለእኔ ታናሽ እንጎቻ አድርገሽ አምጭልኝ፥ ከዚያም በኋላ ለአንቺና ለልጅሽ አድርጊ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ በምድር ላይ እግዚአብሔር ዝናብ እስከሚሰጥበት ቀን ድረስ፥ ዱቄቱ ከማድጋ አይጨረስም፥ ዘይቱም ከማሰሮው አይጎድልም” (1ኛ ነገሥት 17:13፣ 14)። በእርሱ በኩል የተጠየቀው ይህ ጥያቄ ራስ ወዳድነት ነበር ወይስ እምነቷን እንድትለማመድ በመፍቀድ እምነቷን እየፈተነ ነበር? መልሱ ግልጽ ነው።

አሥራትን ከአጠቃላይ ወይም ከተጣራ ገቢ የመክፈሉን ጉዳይ መወሰን ያለብን እኛ ነን። ምን ማድረግ እንዳለብን ቤተ ክርስቲያን አታስገድድም፣ መሆንም የለበትም። በመጨረሻ እያንዳንዳችን የራሳችንን ምርጫ ማድረግ ያለብን ሲሆን ምንም ብናደርግ ከእኛ በተለየ መንገድ የሚያከናውኑ ሰዎች ላይ መፍረድ የለብንም። ለምርጫዎቻችን እያንዳንዳችን በግላችን ለእግዚአብሔርና ለእግዚአብሔር ብቻ መልስ እንሰጣለን። “እያንዳንዱ ሰው ራሱን እንዲያጠናና በልቡ እንዳሰበ እንዲሰጥ ተፈቅዶለታል።”—Ellen G. White, Testimonies for the Church, vol. 4, p. 469.

አስራትን መልሶ ለማያውቅ ሰው ከመመለስ ስለሚገኙ በረከቶች እንዴት ያስረዳሉ? እነዚያ በረከቶች ምንድር ናቸው? አስራትን መመለስ እምነትዎን የሚያጠነክረው እንዴት ነው?

ጥር 11
Jan 19

እውነተኛ ወይም ታማኝነት ያለበት አሥራት


1ኛ ቆሮ. 4፡1፣ 2ን ያንብቡ። እንደ እግዚአብሔር ልጆችና የበረከቶቹ መጋቢዎች ምን ዓይነት ሰዎች እንድንሆን ነው የተጠየቅነው?



ስለዚህ በአሥራታችን ታማኝ መሆን ማለት ምን ማለት ነው? በዚህ ሳምንት አሥራት የሚያካትታቸውን በርካታ ነገሮች ከልሰናል፡- 1. መጠን--አንድ አሥረኛ ወይም ከገቢያችን ወይም ከትርፋችን ከመቶ አሥር እጅ። 2. ወደ ጎተራ ማስገባት--ከጎተራው እየተወሰደ የወንጌል አገልጋዮች የሚከፈሉበት ቦታ 3. ከገቢያችን በኩራት እግዚአብሔርን ማክበር 4. ለትክክለኛ ዓላማ ጥቅም ላይ ማዋል--አገልግሎቱን ለመደገፍ እንደ ቤተ ክርስቲያን አባላት የመጀመሪያዎቹን ሶስት ነገሮች መደገፍ ሀላፊነታችን ነው። የአሥራት ገቢ በትክክል ጥቅም ላይ መዋሉን የመቆጣጠር ኃላፊነት የግምጃ ቤቱ አስተዳዳሪዎች ሥራ ነው።

ከስጦታዎቻችን በተቃራኒ አሥራት በእኛ የሚወሰን ነገር አይደለም። አንድ አሥረኛውና ግምጃ ቤቱ (ጎተራው) የእኛ ኃላፊነት አካሎች ናቸው። እኛ መስፈርቶችን አናስቀምጥም፤ እግዚአብሔር ግን ያስቀምጣል። ከገቢዬ ከመቶው አሥር እጅ በሙሉ ካልመለስኩ በትክክል አሥራት እየመለስኩ አይደለሁም። ከመቶው አሥር እጅ ያጣሁትን አሥራት ወደ ‹‹ጎተራው›› ካላመጣሁ አሁንም በትክክል አሥራት እየመለስኩ አይደለሁም።

ማቴ. 25፡19-21ን ያንብቡ። እግዚአብሔር በእጃችን ያደረገውን ገንዘብ እንዴት እንዳስተዳደርን መልስ እንድንሰጥ የምንጠራው መቼ ነው? በገንዘብ አያያዝ ታማኝ ለሆኑት ምን ተባለላቸው?



“‘አሥራትን ሁሉ ወደ ጎተራው አምጡ’ (ሚልክያስ 3:10)የሚለው የእግዚአብሔር ትዕዛዝ ነው። እየቀረበ ያለው የምስጋና ወይም የልግስና ተማጽኖ አይደለም። ይህ የታማኝነት ጉዳይ ነው። አሥራት የእግዚአብሔር ነው፤ የራሱ የሆነውን እንድንመልስለት እያዘዘን ነው ያለው። ”—Ellen G. White, Education, p. 138. የእግዚአብሔርን ንብረት በአግባብ ማስተዳደር የተለየ ዕድልና ሀላፊነትም ነው።

እርሱ ይባርከናል፣ የሚያስፈልገንንም በመስጠት ከአሥር አንድ እንድንመልስለት ይጠይቀናል። ከዚያ በኋላ አሥራቱን በጥንቷ እሥራኤል ዘመን ለሌዊ ወገን እንዳደረገው ለወንጌል አገልጋዮች እንዲጠቀሙበት ይጠቀመዋል። አንዳንድ ሰዎች የአሥራት ገንዘባቸው ጥቅም ላይ እየዋለ ያለበትን ሁኔታ ስለማይወዱ አሥራታቸውን አይመልሱም ወይም ገንዘባቸውን ወደ ሌላ ቦታ ይልካሉ። ነገር ግን ‹‹አሥራትን ወደ ጎተራዬ የምታመጡት ጎተራው በትክክል እንደሚጠቀመው እርግጠኛ ስትሆኑ ብቻ ነው›› ብሎ እግዚአብሔር የተናገረው የት ነው?

ጥር 12
Jan 20


ተጨማሪ ሀሳብ


:- ኤለን ጂ ኋይት ስለ አሥራት የጻፈችውን እጅግ ሰፊ የሆነ ሰነድ ቴስቲሞኒስ ፎር ዘ ቸርች በሚለው መጽሐፍ 9ኛው ቅጽ ላይ ከገጽ 245252 ያለውን ያንብቡ። ምክረ መጋቢነት በሚለው መጽሐፍ ውስጥ ክፍል ሶስት ገጽ 65-107ን ያጥኑ። “የሕዝባችን አሥራት በሙሉ መሆን በሚገባው ሁኔታ ወደ እግዚአብሔር ግምጃ ቤት ቢፈስ ኖሮ ለቅዱስ ዓላማ የሚውሉ መክሊቶችና ስጦታዎች አሥር እጥፍ በተባዙና በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያሉ የመተላለፊያ መስመሮች ክፍት በሆኑ ነበር።”—Ellen G. White, Testimonies for the Church, vol. 4, p. 474. ይህ አስደናቂ የሆነ አረፍተ ነገር ነው። ሁላችንም ታማኝ አሥራት መላሾች ብንሆን ኖሮ ሥጦታዎቻችንን ከመቶ አንድ ሺህ እጅ መጨመር እስክንችል ድረስ እግዚአብሔር በገቢ ይባርከን ነበር።

“በሚልክያስ ሶስተኛው ምዕራፍ ውስጥ እግዚአብሔር ከሰው ጋር የገባው ውል (ስምምነት) አለ። በዚህ ቦታ ለእርሱ አሥራትንና ስጦታን በታማኝነት በሚመልሱ ላይ የእርሱን ታላቅ ስጦታዎች በመስጠት የሚጫወተውን የራሱን ሚና ጌታ በግልጽ አስቀምጦአል።”— Ellen G. White, Review and Herald, December 17, 1901. “እግዚአብሔር በእኛ ላይ ባለው የይገባኛል ጥያቄ ሥር ማንኛውም ሌላ የይገባኛል ጥያቄ እንደሚካተት ሁሉም ማስታወስ አለባቸው። እርሱ በልግስና ስለሚሰጠን ከሰው ጋር የፈጸመው ስምምነት ከንብረቱ አንድ አሥረኛውን ለእግዚአብሔር እንዲመልስ ነው።

እግዚአብሔር ለመጋቢዎቹ ሀብቱን በልግስና ይሰጣል፣ ነገር ግን አንድ አሥረኛው የእኔ ነው ይላል። እግዚአብሔር ንብረቱን ለሰው በሰጠው ልክ ሰው ከሀብቱ ሁሉ ለእግዚአብሔር በታማኝነት አሥራት መመለስ አለበት። ይህ ግልጽ የሆነ ስምምነት የተዘጋጀው በራሱ በኢየሱስ ክርስቶስ ነው።”—Ellen G. White, Testimonies for the Church, vol. 6, p. 384.


የውይይት ጥያቄዎች



:1.አሥራትን የመመለስ ልምምድ መነሻው የጥንቷ እስራኤል አይደለችም በሚለው ሀሳብ ላይ የበለጠ ትኩረት አድርጉ። ይህ እውነታ በእግዚአብሔር ፊት ያለብንን የዚህን ግዴታ ዘላቂነት እንድናስተውል እንዴት ሊረዳን ይችላል?

2.በሰኞው ዕለት ጥናት ላይ የተነሳውን ጥያቄ በክፍላችሁ ተወያዩበት። ሰዎች አስራታቸውን ወደ ሌላ ቦታ ለመላክ ቢወስኑ ኖሮ ምን ሊሆን እንደሚችል ያስቡ። ቤተ ክርስቲያናችን ምን ይገጥማት ይሆን? ቤተ ክርስቲያን ትኖረን ይሆን? አሥራቴ ከሌሎች ነገሮች ጋር ሲነጻጸር እጅግ ትንሽ ስለሆነ ምንም ማለት አይደለም የሚለው አመለካከት ችግሩ ምንድር ነው? ሁሉም ሰው እንደዚህ ቢያስብ ምን ሊከሰት ይችላል?

3.አሥራትን መክፈልን በተመለከተ እርስዎ የተማሩትንና የተለማመዱትን ከሌሎች ጋር ይጋሩ። ስለ ልምምዱ ሌሎችን ምን ማስተማር ይችላሉ?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL