የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ጌታ እስኪመጣ ድረስ የእርሱን ንብረት ማስተዳደር


የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 1ኛ ሩብ ዓመት 2023

ጥር 13-19

4ኛ ትምህርት

Jan 21 - 27




ለኢየሱስ የሚሰጡ ስጦታዎች



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ትምህርት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- 2ኛ ቆሮ. 9:6፣ 7፤ ዘዳግም 16:17፤ መዝሙር 116:12–18፤ 1ኛ ዜና 16:29፤ ማርቆስ 12:41–44፤ ማርቆስ 14:3–9።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “ ስላደረገልኝ ሁሉ ለእግዚአብሔር ምንን እመልሳለሁ? የመድኃኒትን ጽዋ እቀበላለሁ፥ የእግዚአብሔርንም ስም እጠራለሁ። በሕዝቡ ሁሉ ፊት ስእለቴን ለእግዚአብሔር እፈጽማለሁ” (መዝሙር 116:12–14)።

አ ስራት ከመመለስ ባሻገር ከመለስን በኋላ በእጃችን ከሚቀረው ዘጠና ፐርሰንት ላይ የምንሰጣቸው ስጦታዎች አሉ። ልግስና የሚጀምረው እዚህ ላይ ነው። የእግዚአብሔር ሕዝብ የሚያቀርቡአቸው የተለያዩ ዓይነት ሥጦታዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል ለእግዚአብሔር ጸጋ ምላሽ የሚሰጡ የኃጢአት ስጦታዎች ወይም ለእግዚአብሔር ጥበቃ፣ የጤና በረከቶች፣ ብልጽግና እና ደግፎ የማኖር ኃይሉ እውቅና ለመስጠት የሚቀርቡ የምስጋና ስጦታዎች በምሳሌነት የሚጠቀሱ ናቸው። ለድሆች የሚሰጡ ስጦታዎችና የአምልኮ ቤትን ለመገንባትና ለማደስ የሚሰጡ ስጦታዎችም አሉ። እግዚአብሔር የሰጠንን ስጦታዎች ግዝፈት ስንመለከት የእኛ ስጦታ የመኪና ማቆሚያን ከመጥረግ ወይም የመዘምራን ልብስ ከመግዛት እንደማይበልጥበልጥ ማየት እንጀምራለን። ስጦታዎቻችንን የምናመጣው እግዚአብሔር ላደረገልን፣ በተለይም በክርስቶስ ኢየሱስ ላደረገልን መስዋዕትነት ምላሽ እንዲሆን በማሰብ ነው። “እርሱ አስቀድሞ ስለወደደን እንወደዋለን” (1ኛ ዮሐንስ 4:19). ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን፣ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ወይም ኮንፍራንስ ወይም ዓለም አቀፋዊዋ ቤተክርስቲያን ብትሆን፣ የእግዚአብሔርን ሥራ ወደ ፊት ለማስቀጠል የእኛን ስጦታዎች ትጠቀማለች። በዚህ ሳምንት መጽሐፍ ቅዱስ በምድር ላይ የእግዚአብሔርን ሥራ የማስተዳደር አካል አድርጎ ስለ ስጦታዎች የሚለውን ነገር እንከልሳለን። *የዚህን ሳምንት ትምህርት ለጥር 20 ሰንበት ለመዘጋጀት አጥኑ።

ጥር 14
Jan 22

ለመስጠት ማነሳሻ


እግዚአብሔር አስቀድሞ ስለወደደን እንወደዋለን። እኛ የምንሰጠው እርሱ አስደናቂ የሆነውን ስጦታ፣ ኢየሱስን ስለሰጠን ነው። በርግጥ ‹‹እግዚአብሔር ሥጦታችንን እንደማይፈልግ ተነግሮናል። በስጦታዎቻችን እርሱን ባለጸጋ ማድረግ አንችልም። ባለ መዝሙሩ እንዲህ ይላል፡- ‹ሁሉ ከአንተ ነው፣ አንተ ከሰጠኸን መልሰን እንሰጥሃለን።› ሆኖም ራስን መስዋዕት በሚያደርግ ጥረት እግዚአብሔር ለእኛ ላደረገው ምህረት ያለንን አድናቆት ለሌሎች ተመሳሳይ ነገር በማድረግ እንድናሳይ እግዚአብሔር ይፈቅዳል። ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅርና ምስጋና ለመግለጽ የምንችልበት ብቸኛው መንገድ ይህ ነው።”—Ellen G. White, Counsels on Stewardship, p. 18. ገንዘባችንን ለኢየሱስ አሳልፈን ስንሰጥ ለእርሱና ለሌሎች ያለንን ፍቅር ያጠነክራል። ስለዚህ ገንዘብ ለመልካም ነገር ትክክለኛ ኃይል ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ከማንኛውም ነገር ይበልጥ ስለ ገንዘብና ሀብት እየተናገረ ብዙ ሰዓት አሳልፏል። በማቴዎስ፣ በማርቆስና በሉቃስ ወንጌላት ውስጥ ካሉ ስድስት ቁጥሮች ውስጥ አንዱ የሚናገረው ስለ ገንዘብ ነው። የወንጌል መልካሙ ዜና እግዚአብሔር ገንዘብን ያለ አግባብ ከመጠቀምና ከገንዘብ ፍቅር ነጻ ሊያወጣን እንደሚችል መግለጹ ነው። ማቴዎስ 6፡ 31-34ን እና ዘዳግም 28፡1-14ን ያንብቡ። እግዚአብሔር ከታዘዝነው ምን ሊያደርግልን ነው ቃል የገባልን? የእግዚአብሔር ተስፋዎች እንዲፈጸሙልን መጠየቅ ራስ ወዳድነት ነው ወይ?



ስጦታዎቻችን ራሳችንን ለእግዚአብሔር መስዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ ለመሆናችን ማስረጃ ናቸው። ሕይወታችንን ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር እንደ ጌታ አድርገን አሳልፈን የመስጠታችን መግለጫና ጥልቅ መንፈሳዊ ልምምድ ሊሆኑ ይችላሉ። የእንግሊዝኛ ምሳሌያዊ አነጋገር እንደሚለው ‹‹አፋችን ባለበት ገንዘባችንን ማስቀመጥ›› ነው። እግዚአብሔርን እወደዋለሁ ልትል ትችላለህ፣ ነገር ግን የልግስና ስጦታዎች ያንን ፍቅር ለመግለጽ ይረዳሉ ያጠናክራሉም። ስጦታ የሚመጣው ለፍላጎታችን መልካም ነው ብሎ በሚያስበው መንገድ ያለማቋረጥ በሚሰጥ ግላዊ አምላክ ከሚታመን ልብ ነው። ስጦታዎቻችን የሚያርፉት የድነት መተማመኛን በክርስቶስ ማግኘታችንን በማመን ላይ ነው። እግዚአብሔርን ለማስደሰት ወይም በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ከመፈለግ የሚደረግ ነገር አይደለም። ነገር ግን ስጦታዎቻችን የሚፈሱት ክርስቶስን እንደ ብቸኛና በቂ የጸጋና የመበዤት መንገድ አድርጎ በእምነት ከሚቀበል ልብ ነው። 2ኛ ቆሮንቶስ 9፡ 6፣7ን ያንብቡ። በዚህ ቦታ እግዚአብሔር ምን እያለን ነው? ሰው ‹‹በልቡ እንዳሰበ ይስጥ›› ማለት ምን ማለት ነው? በደስታ መስጠትን እንዴት ነው የምንማረው?

ጥር 15
Jan 23

ከገቢያችን ምን ያህሉን ለስጦታ ማዋል አለብን?


ዘዳግም 16፡17ን ያንብቡ። ስጦታችንን በተመለከተ በመቶኛ ከማስላት ይልቅ ምን ያህል መስጠት እንዳለብን መሰረት እንዲሆን እግዚአብሔር ያስቀመጠው መስፈርት ምንድር ነው?



ስጦታዎቻችን እግዚአብሔር አትረፍርፎ ስለሰጠን የሕይወት፣ የመበዤት፣ የመኖርና ብዙ ዓይነት ቀጣይነት ላላቸው በረከቶች እውቅና የመስጠትና የአመስጋኝነት መግለጫዎቻችን ናቸው። ከላይ ባለው ንባብ ላይ እንደተመለከትናው የምንሰጠው የስጦታ መጠን የተመሰረተው በተባረክነው ልክ ነው። “ብዙም ከተሰጠው ሰው ሁሉ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል” (ሉቃስ 12:48 N)። መዝሙር 116፡12-14ን ያንብቡ። በቁጥር 12 ላይ የተነሳውን ጥያቄ እንዴት ነው መመለስ ያለብን? ከመልሱ ጋር ገንዘብ የሚገጥመው እንዴት ነው?



እግዚአብሔር ለሰጠን በረከቶች ሁሉ መልሰን ልንከፍለው የምንችለው እንዴት ነው? ቀላሉ መልስ በፍጹም መክፈል አንችልም የሚለው ነው። ማድረግ የምንችለው ከሁሉ የተሻለ ነገር ቢኖር ለእግዚአብሔር ሥራ እና ሰብአዊ ፍጡራንን ለመርዳት በልግስና መስጠት ነው። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ለሚስዮናዊ ጉዞ ሲልካቸው እንዲህ አላቸው፡- “በነጻ ስለተቀበላችሁ በነጻ ስጡ” (ማቴዎስ 10:8)። ስጦታዎቻችን ክርስቶስን የመሰለ ባህርይ ለመገንባት አስተዋጽዖ ያደርጋሉ። ከዚህ የተነሣ ከራስ ወዳድነት ወደ አፍቃሪነት እንለወጣለን፤ ክርስቶስ እንዳደረገው ሁሉ እኛም ለሌሎችና ለእግዚአብሔር ሥራ ግድ የሚለን መሆን አለብን። ‹‹እግዚአብሔር …እንዲሁ ስለወደደ ሰጠ›› የሚለውን ሀሳብ ሁልጊዜ እናስታውስ (ዮሐ. 3፡16)። ከዚህ በተቃራኒ ቀን ሌሊትን መከተሉ እርግጠኛ የሆነውን ያህል አብዝተን ለራሳችን ባከማቸን ቁጥር በልባችን የበለጠ ራስ ወዳድ እየሆንን ስለምንመጣ የበለጠ ጎስቋላነታችን ይሰማናል። ምን ያህል መስጠት እንዳለብንና ለማን መስጠት እንዳለብን መወሰን ያለብን እኛ ነን። ነገር ግን ለጌታ ስጦታን ማምጣት መንፈሳዊና ግብረገባዊ አንደምታ ያለው ክርስቲያናዊ ተግባር ነው። ይህን ችላ ማለት ምናልባት መገንዘብ ከምንችለው በላይ ለራሳችን መንፈሳዊ ሕይወት ጉዳት ማምጣት ነው። ስጦታዎቻችሁና ስለ መስጠት ያላችሁ አመለካከት ከእግዚአብሔር ጋር ስላላችሁ ግንኙነት ምን ይላሉ?

ጥር 16
Jan 24

ስጦታዎችና አምልኮ


መጽሐፍ ቅዱስ አምልኮን በተመለከተ የአገልግሎት ቅደም ተከተል አይሰጠንም። ነገር ግን በአምልኮ አገልግሎት ውስጥ ቢያንስ አራት ነገሮች ያሉ ይመስላል። ይህ ዝርዝር በአዲስ ኪዳን ውስጥ ጥናትን/ስብከትን፣ ጸሎትን፣ ሙዚቃንና አሥራትና ስጦታን ያካትታል። የእሥራኤል ወንዶች (ቤተሰቦች) በዓመት ሶስት ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት በኢየሩሳሌም መታየት ነበረባቸው። “በእግዚአብሔር ፊት ባዶ እጃቸውን አይታዩ” (ዘዳ. 16:16) የሚል ትዕዛዝ ተሰጥቷል። በሌላ አነጋገር ገሚሱ የአምልኮ ልምምድ አስራትን መመለስና ስጦታዎችን መስጠት ነበር። የእግዚአብሔር ልጆች አስራታቸውንና ስጦታዎቻቸውን ለእግዚአብሔር ያመጡ የነበሩት በፋሲካ ጊዜ፣ በጴንጤቆስጤ ቀንና በዳስ በዓል ጊዜያቶች ነበር። ለእነዚያ በዓላት የሚመጣ ሰው ባዶ እጁን ስለመምጣቱ ሲታሰብ ይከብዳል።

በሌላ አገላለጽ ለጥንቶቹ እሥራኤላውያን አሥራትን መመለስና ስጦታዎችን መስጠት የአምልኮ ልምዳቸው እምብርት ነበር። አምልኮ፣ እውነተኛ አምልኮ፣ ለእግዚአብሔር ያለንን ምስጋና በቃላት፣ በዝማሬና በጸሎት መግለጽ ብቻ ሳይሆን ስጦታዎቻችንን ወደ እግዚአብሔር ቤት በማምጣት አመስጋኝነታችንና ምስጋናችንን መግለጽም ነው። እነርሱ ስጦታዎቻቸውን ያመጡት ወደ ቤተ መቅደሱ ነበር፤ እኛ ደግሞ የአምልኮ ተግባር ስለሆነ በሰንበት ቀን ወደ ቤተ ክርስቲያን እናመጣለን (ቢያንስ አሥራታችንን እና ስጦታዎቻችንን ከምንመልስባቸው መንደጎች እንደ አንድ መንገድ ስለሚያገለግል) ። 1ኛ ዜና 16፡29፤ መዝ. 96፡8፣9፤ መዝ. 116፡16-18ን ያንብቡ። እዚህ ላይ የተገለጹ መርሆዎችን ለራሳችን የአምልኮ ልምምድ መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?



በምድር ላይ ያለውን የእርሱን ሀብት እንድናስተዳድር ኃላፊነት የተሰጠን የእግዚአብሔር ልጆች እንደመሆናችን ስጦታዎቻችንን ለእርሱ ማምጣት ልዩ መብት፣ መልካም ዕድልና ሀላፊነታችን ነው። ልጆችን እንድናሳድግለት እግዚአብሔር ሰጥቶን ከሆነ አሥራትንና ስጦታን ወደ ሰንበት ትምህርትና የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የማምጣትን ደስታ ከእነርሱ ጋር መጋራት አለብን። በአንዳንድ ቦታዎች ሰዎች አስረቶቻቸውን በኦን ላይን ወይም በሌሎች መንገዶች ይመልሳሉ። በየትኛውም መንገድ ብናደርግ አሥራትንና ስጦታዎችን መመለስ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን የአምልኮ ልምምድ አካል ነው። እንደ አምልኮ ክፍል አሥራትንና ስጦታዎችን ከመመለስ ሚና ጋር የእርስዎ ልምምድ ምን ነበር? ልምምዱ ከእግዚአብሔር ጋር ባለዎ ግንኙነት ላይ ምን ተጽእኖ አሳደረብዎ?

ጥር 17
Jan 25

እግዚአብሔር ስጦታዎቻችንን መዝግቦ ይይዛል


ማርቆስ 12፡41-44ን ያንብቡ። ሀብታም ብንሆንም ባንሆንም ከዚህ ታሪክ ምን መልእክት መውሰድ እንችላለን? ይህ የሚያስተምረን መርህ ምንድር ነው? ለራሳችን የአምልኮ ልምምድ መጠቀም የምንችለውስ እንዴት ነው?



ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ የግምጃ ቤቱ ሳጥን ተቀምጦበት በነበረው የቤተ መቅደሱ ግቢ ውስጥ ነበሩ። ኢየሱስ ስጦታዎቻቸውን ያመጡ የነበሩ ሰዎችን ተመለከተ። አንዲት ባልቴት ሁለት የነሃስ ሳንቲሞችን ስትሰጥ መመልከት እስከሚችል ድረስ ቀረብ ብሎ ነበር። ያላትን ሁሉ ሰጠች። “ኢየሱስ የሰጠችበትን ውስጣዊ ምክንያት ተረዳ። የቤተ መቅደስ አገልግሎት እግዚአብሔር ያቋቋመው ሥርዓት እንደሆነ በማመን አገልግሎቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ ድርሻዋን ለመወጣት ጉጉት ነበራት። ማድረግ የምትችለውን አደረገች፤ ድርጊቷም በዘመናት ሁሉ እና ለዘላለም ደስታዋ መታሰቢያ የሚሆን ሀውልት ነው። ልቧ ከስጦታዋ ጋር ሄደ፤ ዋጋው የሚተመነው (የሚገመተው) ሳንቲሙ በሚያወጣው ዋጋ ሳይሆን ተግባሩን እንድትፈጽም ባደረጋት ለእግዚአብሔር ባላት ፍቅርና ለሥራው በነበራት ፍላጎት ነበር።”—Ellen G. White, Counsels on Stewardship, p. 175. ሌላኛው እጅግ ወሳኝ ነጥብ ቢኖር ኢየሱስ አድናቆቱን የገለጸለት ስጦታ ይህ ብቻ ነበር። ያውም በቅርቡ አልቀበል በማለት ልትክደው ላለችው ቤተ ክርስቲያን፣ ከጥሪውና ከተልዕኮው እጅግ ላፈነገጠች ቤተ ክርስቲያን የተሰጠ ስጦታ ነበር።

የሐዋ. 10፡1-4ን ያንብቡ። ሮማዊውን መቶ አለቃ ሰማያዊ መልአክ የጎበኘው ለምን ነበር? በሰማይ የተመዘገቡት (የተጻፉት) ሁለት ተግባራቱ ምን ነበሩ?



ግልጽ በሆነ ሁኔታ ስንገልጽ፣ ጸሎቶቻችን በሰማይ የሚሰሙ ብቻ ሳይሆን ስጦታዎቻችንን ለመስጠት የተነሳሳንበት ምክንያትም ይጻፋል። ቆርኔሊዎስ ለጋስ ሰው እንደነበር ንባቡ ይገልጻል። “መዝገባችሁ ባለበት ልባችሁ በዚያ ይሆናል” (ማቴ. 6:21)። የቆርኔሊዎስ ልብ ስጦታዎቹን ተከተለ። ስለ ኢየሱስ የበለጠ ለመማር ዝግጁ ነበር። ጸሎትና ምጽዋት መስጠት በቅርበት የተገናኙ ሲሆን ለእግዚአብሔርና ለሰዎች ያለንን ፍቅር--ሁለቱን ታላላቅ የእግዚአብሔር ሕግ መርሆዎች--የሚያሳዩ ናቸው። “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም ኃይልህም በፍጹም አሳብህም ውደድ፥ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ አለው” (ሉቃስ 10:27)። የመጀመሪያው በጸሎት የሚገለጽ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ምጽዋት በመስጠት የሚገለጽ ነው።

ጥር 18
Jan 26

ልዩ ፕሮጄክቶች፡- ትልቅ ገንቦ መስጠት


ሰዎች ካላቸው ንብረት 9 ፕርሰንት ብቻ በቀላሉ በገንዘብ የሚቀየር ስለሆነ በአጭር ጊዜ ማሳሰቢያ በስጦታ መልክ ሊሰጡ እንደሚችሉ ጥናቶች ያሳያሉ። በአጠቃላይ በእጅ ያለ ገንዘብ፣ ቼክ፣ የተቆጠበ ገንዘብ፣ የገንዘብ ገበያ ገቢዎች፣ ወዘተ…ወደ ገንዘብ ሊቀየሩ የሚችሉ ንብረቶች ተደርገው ይታያሉ (ቢያንስ እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ላሉአቸው ሰዎች)። አብዛኞቹ ንብረቶቻችን፣ ወደ 91 ፐርሰንት የሚጠጉት፣ እንደ ቤቶቻችንና ከብቶቻችን (በገጠር አከባቢ ላሉ ሰዎች) ባሉ ወይም በሌሎች ወደ ገንዘብ ሊቀየሩ በማይችሉ ነገሮች ላይ የፈሰሱ ናቸው።

ወደ ገንዘብነት በቀላሉ ሊቀየር በሚችልና በማይችል ንብረት መካከል ያለው ልዩነት ሊገለጽ የሚችለው 1000 ሳንቲሞችን በሁለት የተለያዩ የብርጭቆ ገንቦዎች ውስጥ በመጨመር ሲሆን 10 ሳንቲሞች እያንዳንዱን የፐርሰንቴጅ ነጥብ ይወከላሉ። ስለዚህ ወደ ገንዘብ ሊለወጥ የሚችለውን 9 ፐርሰንት ንብረት የሚወክለው ትንሹ ገንቦ 90 ሳንቲሞች የሚኖሩት ሲሆን ወደ ገንዘብነት በቀላሉ ሊለወጥ የማይችለውን 91 ፐርሰንት ንብረት የሚይዘው ትልቁ ገንቦ ደግሞ 910 ሳንቲሞች ይኖሩታል።

ብዙ ሰዎች ስጦታ የሚሰጡት ከትንሹ ገንቦ፣ከተንቀሳቃሽ ንብረታቸው ነው። በባንክ ደብተራቸው ወይም በኪስ ደብተራቸው ያለው ይህ ነው። ነገር ግን አንድ ሰው ስለ አንድ ነገር ልቡ በትክክል ከተነሳሳ ከትልቁ ገንቦ ይሰጣል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደዚህ ያሉ ብዙ ታሪኮችን ይነግረናል። ማርቆስ 14፡3-9ን እና ዮሐንስ 12፡2-8ን ያንብቡ። በስምዖን ቤት ግብዣ ላይ የነበሩ ዋና ገጸ- ባህርያት እነማን ነበሩ? የማርያም ስጦታ ዋጋ ምን ያህል ነበር? በዚህ ወቅት ኢየሱስን የቀባችው ለምን ነበር?



የማርያም ስጦታ 300 ዲናር የሚያወጣ ዋጋ የነበረው ሲሆን ይህ ገንዘብ የአንድ ሰው የዓመት ሙሉ ደሞዝ ነበር። ይህ ‹‹የትልቁ ገንቦ›› ሥጦታ ነበር ማለት ይቻላል። ይህን ክስተት ተከትሎ ይሁዳ ኢየሱስን ማርያም ከሰጠችው ስጦታ ከአንድ ሶስተኛ ትንሽ ለሚበልጥ ገንዘብ--‹‹የትንሹ ገንቦ›› ስጦታ፣ ለሰለሳ የብር ሳንቲሞች ሸጠ (ማቴ. 26፡15)። ከሀብታችን የትልቁን ገንቦ ስጦታዎች መስጠት እውነተኛ ፍቅርንና መሰጠትን ይጠይቃል። ነገር ግን እንደ ይሁዳ ስስታሞች ስንሆን ከምንም ለማይሻል ነገር ነፍሳችንን መሸጥ እንችላለን።

የባርናባስ ሥራና እንቅስቃሴዎች በአዲስ ኪዳን ውስጥ 28 ጊዜ ተጠቅሰዋል። እርሱን በዋነኛነት የምናውቀው እንደ ሐዋርያ ጳውሎስ ጓደኛና ታላቅ ሚስዮናዊ ነው። ነገር ግን የዚህ ሁሉ መሰረት የተጣለው ስሙ በተጠቀሰበት በመጀመሪያው ንባብ ላይ ነበር። በሐዋርያት ሥራ 4፡ 36ና 37 ላይ እርሱ ስለ ሰጠው ስጦታ፣ በርግጥም ‹‹የትልቁ ገንቦ›› ስጦታ እናነባለን። ‹‹መዝገባችሁ ባለበት በዚያ ልባችሁ ደግሞ ይሆናል›› ላለው ለኢየሱስ ቃላቶች ምንኛ ኃይለኛ ምሳሌ ነው (ማቴ. 6፡21)። መስዋዕትነት ያለበት ስጦታ ለሰጪዎችም ሆነ ለተቀባዮች በተመሳሳይ ደረጃ ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድር ነው?

ጥር 19
Jan 27


ተጨማሪ ሀሳብ


:- የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባላት በገንዘብ አያያዝ የሚያሳዩት ታማኝነት በሰማይ ባለው የመታሰቢያ መጽሐፍ ውስጥ ይጻፋል። “ለእግዚአብሔር ተቀድሶ የተሰጠውንና ወደ ግምጃ ቤት የተጨመረውን እያንዳንዱን ስጦታ፣ እንዲሁም የተሰጠው ገንዘብ ያስገኘውን የመጨረሻውን ውጤት መዝጋቢው መልአክ በታማኝነት ይመዘግባል። ለሥራው ተለይቶ የተሰጠውን እያንዳንዱን ሳንቲምና የሰጪውን ፈቃደኛነት ወይም ዳተኝነት የእግዚአብሔር ዓይኖች በደንብ ይመለከታሉ። ስጦታውን እንዲሰጥ ያነሳሳው ምክንያትም ይመዘገባል። እግዚአብሔር በሚጠይቃቸው መልክ የእርሱ የሆነውን ለራሱ መልሰው ለመስጠት ራሳቸውን የሰውና የቀደሱ ሰዎች እንደ ሥራቸው ዋጋቸውን ያገኛሉ።

ለእግዚአብሔር ሥራ ተቀድሶ የተለየው ገንዘብ ሰጪው ለሰጠበት አለማ፣ ለእግዚአብሔር ክብርና ለነፍሳት መዳን ሳይውል በተሳሳተ መልኩ ሥራ ላይ ቢውልም ዓይኖቻቸውን በእግዚአብሔር ክብር ላይ በማተኮር ከእውነተኛ ልባቸው መስዋዕትነት የከፈሉ ሰዎች ሽልማታቸውን ያገኛሉ።”—Ellen G. White, Testimonies for the Church, vol. 2, p. 518. “እግዚአብሔር ሥራው ወደ ፊት እንዲቀጥል ሰዎች እንዲጸልዩና እንዲያቅዱ ይሻል። ነገር ግን እንደ ቆርኔሊዎስ ጸሎትን ከመስጠት ጋር ማጣመር አለብን።

ጸሎቶቻችንና ምጽዋቶቻችን በእግዚአብሔር ፊት ለመታሰቢያነት መቅረብ አለባቸው። እምነት ያለ ሥራ የሞተ ነው፤ ያለ ሕያው እምነት እግዚአብሔርን ማስደሰት አይቻልም። ጸሎቶቻችን ፍጻሜ እንዲያገኙ ከፈለግን እየጸለይን መስጠት የምንችለውን ሁሉ፣ ጉልበታችንንም ሆነ ገንዘባችንን፣ መስጠት አለብን። እምነታችንን በሥራ ከገለጽን እግዚአብሔር አይረሳንም። እያንዳንዱን የፍቅርና ራስን የመካድ ተግባር ምልክት ያደርግበታል። እምነታችንን በሥራ የምንገልጽባቸውን መንገዶች ይከፍትልናል።”—Ellen G. White, Atlantic Union Gleaner, June 17, 1903.


የውይይት ጥያቄዎች



1.ጸሎትና መስጠት አብረው የሚሄዱት እንዴት ነው? ምን፣ መቼና ምን ያህል መስጠት እንዳለባችሁ እንድታውቁ ጸሎት እንዴት ሊረዳ ይችላል?

2. በአሜሪካ እጅግ ታዋቂ የሆነ መጽሔት ወል እስትሪት በሚባል ቦታ እጅግ ገንዘብ እያገኙ ጎስቋላና ባዶ ስለሆኑ እና በስጋትና በጭንቀት ስለተሞሉ ወጣት ባለሙያዎች ተናግሮአል። ከእነዚህ መካከል የሰራተኞችን የቅጥር ሁኔታ የሚቆጣጠር አንድ ሰው እንዲህ አለ፡- ‹‹የሥራዬ ሁኔታ መግለጫ መዝገብ ውስጥ ተጫማሪ አንድ ፐርሰንት ትርፍ ቢኖረኝ እኔ ከሞትኩ በኋላ ምን ይጠቅማል?” መስጠት፣ ራስን መስዋዕት የሚያደርግ መስጠት፣ ‹‹ከሀብት አታላይነት›› ነጻ ለመሆን ስለሚረዳ ለሰጪው በመንፈሳዊ ሕይወቱ ጠቃሚ ስለመሆኑ ከዚህ ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን? (ማቴ. 13፡22)።

3. ከላይ በተጠቀሰው የኤለን ጂ ኋይት ጥቅስ ውስጥ ገንዘብ ‹‹ያለ አግባብ ጥቅም ላይ መዋል›› የሚለውን ክፍል ልብ ይበሉ። እሷ የጠቀሰችውን ነጥብ በአእምሮአችን ውስጥ ለማቆየት ለምንሰጥ ለእኛ ይህ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድር ነው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL