የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ጌታ እስኪመጣ ድረስ የእርሱን ንብረት ማስተዳደር


የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 1ኛ ሩብ ዓመት 2023

ጥር 20-26

5ኛ ትምህርት

Jan 28 - Feb 3




የዕዳ አያያዝ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ዘዳ. 28፡1፣2፣ 12፤ ማቴ. 6፡ 24፤ 1ኛ ዮሐ. 2፡15፤ ምሳሌ 22፡7፤ ምሳሌ 6፡1-5፤ ዘዳ. 15፡1-5።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “ባለጠጋ ድሆችን ይገዛል፥ ተበዳሪም የአበዳሪ ባሪያ ነው።” (ምሳሌ 22:7)።

የ ዕዳ አንዱ ትርጉም ‹‹ወደ ፊት አገኛለሁ ብለህ በምትጠብቀው ነገር ዛሬን መኖር ነው።›› ዛሬ ዕዳ የኑሮ ዘይቤ ይመስላል፣ ነገር ግን ለክርስቲያኖች ይህ ልማድ መሆን የለበትም። መጽሐፍ ቅዱስ ዕዳን አያደፋፍርም። በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ቢያንስ 26 ስለ ዕዳ የተነገሩ ማጣቀሻዎች ያሉ ሲሆን ሁሉም አሉታዊ ናቸው። ገንዘብን መበደር ኃጢአት ነው አይልም፣ ነገር ግን ብዙ ጊዜ መበደር ስለሚያመጣቸው መጥፎ መዘዞች ይናገራል። ገንዘብን የሚመለከቱ ግዴታዎችን በተመለከተ ጳውሎስ እንዲህ በማለት መክሮአል፡- “ለሁሉ የሚገባውን አስረክቡ፤ ግብር ለሚገባው ግብርን፥ ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን፥ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፥ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ። እርስ በርሳችሁ ከመዋደድ በቀር ለማንም ዕዳ አይኑርባችሁ፥ ሌላውን የሚወድ ሕግን ፈጽሞታልና” (ሮሜ 13:7፣ 8)።

ዕዳ በሁሉም ደረጃ--በግል፣ በጋራ እና በመንግሥት ደረጃ--ዓለም አቀፋዊ መቅሰፍት የሆነው ለምንድር ነው? እያንዳንዱ ማህበረሰብ፣ ሁልጊዜ፣ ቢያንስ አነስተኛ መጠን ያለው ዕዳ ነበረበት። ነገር ግን ዛሬ አብዛኛው ሕዝብ ባለዕዳ ሲሆን ዕዳውም በፍጹም ጥቅም የማያስገኝ ዕዳ ነው። በዚህ ሳምንት ሰዎች ባለ ዕዳ የሚሆኑባቸውን ምክንያቶችና ዕዳን እንዴት መያዝ እንዳለብን እንመለከታለን። እርስዎ ከዕዳ ነጻ ሊሆኑ ይችላሉ፣ ነገር ግን ይህ መረጃ ሊጠቅማቸው ለሚችል የቤተሰብ አባላትና ጓደኞች መረጃውን ማካፈል ይችላሉ። *የዚህን ሳምንት ትምህርት ለጥር 27 ሰንበት ለመዘጋጀት ያጥኑ።

ጥር 21
Jan 29

የዕዳ ችግሮች


ዘዳግም 28:1፣ 2፣ 12ን ያንብቡ። ዕዳን በተመለከተ እግዚአብሔር ለልጆቹ እንዲሆን የሚመኝላቸው ነገር ምንድር ነው? እግዚአብሔር ወደሚመኝላቸው ሀሰብ መድረስ የሚችሉት እንዴት ነው? ይህ አውድ ከእኛ አውድ እጅግ የተለየ ቢሆንም ከዚህ አውድ አውጥተን አሁን ለእኛ በሚሆን ሁኔታ ለመጠቀም ምን መርሆዎችን መውሰድ እንችላለን?



ሰዎች በገንዘብ ችግር ውስጥ የሚገቡባቸው ሶስት ግንባር ቀደም ምክንያቶች እንዳሉ ጥናቶች ያሳያሉ። ከሚያሳዩት ድግግሞሽ አንጻር ከዚህ በታች ከትልቅ ወደ ትንሽ ተዘርዝረዋል። የመጀመሪያው አለማወቅ ነው። ብዙ ሰዎች፣ የተማሩ ሰዎች እንኳን፣ ገንዘብን በተመለከተ ዕውቀት የላቸውም። የገንዘብ አያያዝን በተመለከተ ከመጽሐፍ ቅዱሳዊውም ሆነ ከዓለማዊው መርሆዎች ጋር ትውውቅ የላቸውም። ነገር ግን ተስፋ አለ! ይህ ትምህርት የእነዚህን መርሆዎችና እንዴት ሥራ ላይ ማዋል እንደሚቻል ቀለል ያሉ ዋና ዋና ሀሳቦች ይሰጣል።

በገንዘብ አያያዝ ችግር እንዲፈጠር የሚያደርገው ሁለተኛው ምክንያት ስስት ወይም ራስ ወዳድነት ነው። ለማስታወቂያና ለግል ፍላጎት ምላሽ በመስጠት ሰዎች ከገቢያቸው በላይ ይኖራሉ። በገንዘባቸው ልክ ለመኖር፣ ለመንዳት ወይም ለመልበስ ፈቃደኞች አይደሉም። ከእነዚህ ሰዎች አብዛኞቹ ድሃ ስለሆኑ አሥራት መመለስ እንደሌለባቸው ይሰማቸዋል። ከዚህ የተነሣ እግዚአብሔር ሊሰጣቸው ቃል የገበላቸውን ጥበብና በረከት ሳያገኙ ይኖራሉ (ሚልኪያስ 3፡10፣ 11፤ ማቴ. 6፡33ን ይመልከቱ)። ለእነዚህ ሰዎችም ተስፋ አለ፣ ነገር ግን የልብ ለውጥ፣ ያለኝ ይበቀኛል የሚል መንፈስ ይጠይቃል።

ሰዎች ራሳቸውን በገንዘብ ችግር ውስጥ የሚያገኙበት ሶስተኛው ምክንያት የግል መጥፎ አጋጣሚ ነው። በቂ የጤና መድህን ሳይኖራቸው ከባድ ህመም ገጥሞአቸው ሊሆን ይችላል። አባካኝ የሆነ የትዳር አጋር ክዶአቸው ሊሆን ይችላል። የተፈጥሮ አደጋ ንብረታቸውን በሙሉ ጠራርጎ ወስዶባቸው ሊሆን ይችላል። ወይም እጅግ አስከፊ በሆነ ድህነት ውስጥ ተወልደው አድገው ሊሆን ይችላል። ለእነዚህ ሰዎችም ተስፋ አለ። ምንም እንኳን መንገዳቸው ከባድ ቢሆንም ችግሮቻቸውን ማሸነፍ ይችላሉ። ክርስቲያን ወዳጆች በሚያደርጉት ድጋፍ፣ እግዚአብሔርን የሚፈሩ አማካሪዎች በሚሰጡት ምክር ወይም ድጋፍ፣ በጥሩ ትምህርት በተደገፈ ጠንካራ ሥራ እና በእግዚአብሔር በረከትና መሰናዶ ለውጥ ሊመጣ ይችላል። ባለ ዕዳ የሆነበት ምክንያት ምንም ቢሆን፣ የግለሰቡ የራሱ ስህተት እንኳን ቢሆን፣ ዕዳ ሊወገድ ይችላል። ነገር ግን በዕዳ ውስጥ ያሉ ሰዎች በአኗኗራቸው፣ በገንዘብ አጠቃቀማቸውና ቅድሚያ በሚሰጡአቸው ነገሮች ላይ አንዳንድ ለውጦችን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

1ኛ ጢሞ. 6:6–9ን ያንብቡ። እዚህ ላይ ጳውሎስ ሁላችንም መስማት የሚገባንን ምን እየነገረን ነው? እነዚህ ቃላት ለእርስዎ ምን ትርጉም ይሰጣሉ? ቃሉ እዚህ ላይ እያስተማረን ያለውን ነገር በምን መንገዶች ነው በተሻለ ሁኔታ መከተል የሚችሉት?

ጥር 22
Jan 30

ከእግዚአብሔር የሆነ ምክርን መከተል


እኛ ቁሳዊ ፍጡራን ስንሆን አንዳንድ ጊዜ እጅግ አታላይ በሆነ ቁሳዊ ዓለም ውስጥ እንኖራለን። የቁሳዊ ሀብትና የሀብት ፍላጎት አታላይነት እንዳይሰማህ ከፈለግክ መሰራት ያለብህ ከሥጋና ከደም ሳይሆን ከማይዝግ ብረትና ከብረት ቀለም መሆን አለበት። በሆነ ጊዜ ሀብታም ለመሆን ወይም ሎተሪ ለማሸነፍ ያላሳበ (ያልተመኘ) ሰው ማን ነው?

ሁላችንም የምንጋፈጠው ነገር ቢሆንም ጥሩ ሕይወት ለመኖር ወይም ሀብታም ለመሆን ጠንክሮ መስራት በራሱ ምንም ስህተት ባይኖርበትም ማናችንም ገንዘብን፣ ሀብትንና ቁሳዊ ንብረትን ጣዖቶች በማድረግ ወጥመድ ውስጥ መግባት የለብንም። ትክክል መሆኑን ለምናውቀው ነገር ታማኝ ሆነን መቆየት እንድንችል መለኮታዊ ኃይል እንደሚሰጠን ቃል ተገብቶልናል። የሀብትና ቁሳዊ ንብረት ፈተና የብዙ ነፍሳትን ጥፋት ስላስከተለ ይህ እጅግ አስፈላጊ ነው።

ማቴዎስ 6:24ን እና 1ኛ ዮሐንስ 2:15ን ያንብቡ። ምንም እንኳን የተገለጸው በተለያየ መንገድ ቢሆንም በሁለቱ ጥቅሶች ውስጥ ያለው የጋራ የሆነ ዋና ሀሳብ ምንድር ነው?



እንደ አለመታደል ሆኖ የዓለም ፍቅር እጅግ ጠንካራ ከመሆኑ የተነሣ ሰዎች ያንን ፍቅር ለማርካት ሲሉ ወይም እናረካለን ብለው ተስፋ በማድረግ ዕዳ ውስጥ ይገባሉ። (ይህ በፍጹም ትክክል አይደለም፤ መክብብ 4፡8ን ይመልከቱ)። ዕዳ ሰይጣን ነፍሳትን ለማጥመድ ካዘጋጃቸው ወጥመዶች አንዱ ስለሆነ እግዚአብሔር ደግሞ ልጆቹ ከዕዳ ነጻ እንዲሆኑ መፈለጉ ትርጉም ይሰጣል። ከገንዘብ ባርነት ነጻ ወደመሆን የሚመራንን ምክር በመጽሐፍ ቅዱስና በትንቢት ስጦታ አማካይነት ሰጥቶናል።

መዝሙር 50:14፣ 15ን ያንብቡ። የእግዚአብሔር ሕዝብ ከምን ዓይነት አመለካከት ጋር ነው መኖር ያለባቸው? “መሃላህን ፈጽም ማለት ምን ማለት ነው?



ወደ ቤተ ክርስቲያን አባልነት የምንገባው ለፈጠረንና ላዳነን አምላካችን ውዳሴና ምስጋና በማቅረብ ነው። የጥምቀት ቃል ኪዳን መግቢያ ላይ ከ13 ነጥቦች ውስጥ ዘጠነኛው ነጥብ ላይ ‹‹በቤተ ክርስቲያን ድርጅት ታምናለህን? እግዚአብሔርን ማምለክና በአሥራትህና በስጦታዎችህ፣ እንዲሁም በግል ጥረትህና ተጽእኖህ ቤተ ክርስቲያንን መደገፍ ዓለማህ ነውን?›› የሚል ጥያቄ ተጠይቀናል። እንደ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ሁላችንም አዎን ብለን መልሰናል። ስለዚህ ይህ ጥቅስ (መዝሙር 50፡14፣ 15) ለእግዚአብሔር ምሥጋናን ለሚያቀርቡና የገቡትን መሃላ በታማኝነት ለሚፈጽሙ የተሰጠ ተስፋ ነው።

ምርጫዎቻችሁ የዓለምን ማታለያ እንዴት እንደምትይዙአቸው ምን ይነግራሉ? ጥሩ ኑሮ ለመኖር ተግቶ መሥራት ሀብትን ወይንም ገንዘብን ጣዖት ከማድረግ ጋር የማይመሳሰለው እንዴት ነው? ልዩነቱን እንዴት ማወቅ እንችላለን?

ጥር 23
Jan 31

ከዕዳ እንዴት መውጣት እንደሚቻል


ምሳሌ 22:7ን ያንብቡ። የአበዳሪያችን ባሪያ የምንሆነው በምን መልኩ ነው?



ከዚህ መጥፎ ክስተት ለማምለጥ ምን ማድረግ ይቻላል? ባለ ዕዳ ከሆንክ የሚቀጥለው አጠር ያለ ዝርዝር ዕዳን የማስወገድ ሂደትን እንድትጀምር ይረዳሃል። ዕቅዱ ቀላል ነው። መነሻ ሀሳብና ሶስት ደረጃዎች አሉት። መነሻ ሀሳቡ የእግዚአብሔርን ጥበብና በረከት ለማግኘት የእርሱን የተቀደሰ አሥራት በመመለስ ታማኝ ለመሆን የሚገባ ቃል ኪዳን ነው። እርሱ የሚታዘዙትን ለመባረክ ይፈልጋል። የመጀመሪያው ደረጃ ተጨማሪ ዕዳ ውስጥ ላለመግባት ዕገዳ መጣል ነው፤ ይህ ማለት ተጨማሪ በክሬዲት እየወሰዱ መጠቀምን ማቆም ማለት ነው። ገንዘብን የማትበደሩ ከሆነ ተጨማሪ ዕዳ ውስጥ አትገቡም።

በሁለተኛው ደረጃ እግዚአብሔር ሲባርካችሁ፣ ከዚያች ነጥብ በመጀመር በተቻለ ፍጥነት ዕዳችሁን ትከፍላላችሁ። እግዚአብሔር በገንዘብ ሲባርካችሁ ያንን ገንዘብ ሌሎች ተጨማሪ ቁሳቁሶችን ለመግዛት ሳይሆን ዕዳችሁን ለመቀነስ ተጠቀመበት። ይህ እርምጃ ምናልባትም እጅግ ወሳኝ እርምጃ ሊሆን ይችላል። ብዙ ሰዎች ያልጠበቁትን ገንዘብ ሲቀበሉ ዝም ብለው ያባክኑታል። እንደዚህ አታድርጉ፤ ይልቁን ይህን ገንዘብ ዕዳችሁን በመቀነስ ዕቅድ ውስጥ አስገቡት።

ሶስተኛው ደረጃ የተግባር ሥራ የምትሰሩበት ክፍል ነው። ዕዳዎቻችሁን ከትልቁ አንስቶ እስከ ትንሹ ድረስ በቅደም ተከተል ዘርዝሩ። ለብዙ ሰዎች የቤት ብድር ከላይ ሲሆን በክሬዲት ካርድ የተበደሩት ወይም የግል ዕዳ ከሥር ይሆናል። በየወሩ ቢያንስ በትንሹ ዕዳዎቻችሁን መክፈል ጀምሩ። በመቀጠል በምትችሉት መንገድ ሁሉ በዕዳ ዝርዝራችሁ ከታች ያሉትን ለመክፈል ክፍያችሁን ዕጥፍ አድርጉ ወይም ከፍ አድርጉ። እነዚያን ትናንሽ ዕዳዎች እንዴት በፍጥነት ማስወገድ እንደምትችሉ ስታዩ በመደነቅ ትደሰታላችሁ። ከታች ያሉትን ዕዳዎቻችሁን እየጨረሳችሁ ስትሄዱ፣ ቀጥሎ ባለው ደረጃ ላይ ያለውን ዕዳ ለመክፈል፣ ከታች ስትከፍሉ የነበራችሁትን የገንዘብ መጠን ከላይ ያለውን በምትከፍሉበት ዋና ክፍያ ላይ ጨምሩ። ከፍተኛ ወለድ ያለባቸውን ትናንሽ ዕዳዎች ከፍላችሁ ስትጨርሱ ቀጥለው ባሉ ከፍ ያሉ ዕዳዎች ላይ ለመጨመር ብዙ ገንዘብ ነጻ ታደርጋላችሁ።

በዕዳ ውስጥ እንድንሆን እግዚአብሔር እንደማይፈልግ ግልጽ ነው። ብዙ ቤተሰቦች ቃል ኪዳኑን ከፈጸሙ በኋላ እግዚአብሔር ባልተጠበቀ መንገዶች ሲባርካቸውና ዕዳቸውም ከጠበቁት በላይ በፍጥነት ሲቀንስ ይመለከታሉ። እነዚህን ሶስት ቀላል ደረጃዎች በመከተል ብዙ ቤተሰቦች ከዕዳ ነጻ ሆነዋል። እርስዎም ነጻ መሆን ይችላሉ! እግዚአብሔርን በማስቀደም እርሱ የሰጣችሁን ነገሮች በአግባቡ ለመያዝ ከእርሱ ጥበብና በረከት ትቀበላላችሁ።

“አካሄዳችሁ ገንዘብን ያለ መውደድ ይሁን፥ ያላችሁም ይብቃችሁ፤ እርሱ ራሱ፦ አልለቅህም ከቶም አልተውህም ብሎአልና” (ዕብ. 13:5)። እነዚህን ቃላት ሥራ ላይ ማዋል ሰዎች ዕዳ ውስጥ እንዳይገቡ እንዴት በከፍተኛ ደረጃ ይረዳቸው ይሆን?

ጥር 24
Feb 01

ዋስትናና ቶሎ ሀብታም የመሆን ዕቅዶች


እግዚአብሔር ልጆቹ በሌሎች ሰዎች የዕዳ ግዴታ ውስጥ እንዲገቡ እንደማይፈልግ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል። በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ ዋስትና እንዳንገባ--ለሌላ ሰው ዋስ ለመሆን እንዳንፈርም እግዚአብሔር አስጠንቅቆናል። ምሳሌ 6:1–5፣ ምሳሌ 17:18 እና ምሳሌ 22:26ን ያንብቡ። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ የተላለፈው መልእክት ምንድር ነው?



ዋስትና የሚከሰተው በቂ ገንዘብ የሌለው ሰው ከአበዳሪ ተቋም ብድር ሲፈልግና ለመበደር ብቁ ሳይሆን ሲቀር ነው። የብድር ተቋሙ ሀላፊ ለመበደር ብቁ ያልሆነውን ሰው በዋስትና የሚፈርምለትን ጥሩ ገንዘብ ያለው ጓደኛ የሚያገኝ ከሆነ ባንኩ ብድር እንደሚሰጥና ተበዳሪው መክፈል ካቃተው በዋስትና የፈረመውን ሰው ተጠያቂ እንደሚያደርገው ይነግረዋል። አንዳንድ ጊዜ የቤተ ክርስቲያናችሁ አባል የሆነ ሰው መጥቶ ዋስትና እንድትፈርሙለት ይጠይቃችኋል። መልሳችሁ ‹‹ይህን ማድረግ እንደሌለብኝ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግራል›› የሚል መሆን አለበት። መጽሐፍ ቅዱስ ችግረኞችን እንድንረዳ እንደሚያደፋፍር፣ ነገር ግን ለእነርሱ ዕዳ እኛ ሀላፊነት እንዳንወስድ እንደሚያበረታታ አስተውሉ።

አንዳንድ ጊዜ ለጋ ወጣቶች የመጀመሪያ መኪናቸውን ለመግዛት ወላጆቻቸው በዋስትና እንዲፈርሙላቸው ይጠይቃሉ። ወይም ጎልማሳ ልጆች ንግድ ለመጀመር ወላጆቻቸው በዋስትና እንዲበደሩላቸው ይጠይቃሉ። ለእነዚህ ጥያቄዎችም የሚሰጠው መልስ ተመሳሳይ ነው። እርግጠኛ የሆነ ችግር ካለ ሌሎችን መርዳት ተገቢ ነው፣ ነገር ግን ለሌሎች ሰዎች ዕዳ ዋስ አትሁኑ። ለሌሎች ዋስ ከሆኑ ሰዎች መካከል 75% የሚሆኑት ዕዳውን ራሳቸው ለመክፈል እንደሚገደዱ ጥናቶች ያመለክታሉ!

ምሳሌ 28:20 እና 1ኛ ጢሞ. 6:9፣ 10ን ያንብቡ። እዚህ የተሰጠው ማስጠንቀቂያ ምንድር ነው?



ቶሎ ሀብታም የመሆን ዕቅድ ገንዘብን የሚመለከት ሌላኛው ወጥመድ ነው። በእነዚህ ወጥመዶች ውስጥ የሚገቡ ሰዎች በገንዘብ ውድመት ውስጥ የመግባት ዋስትና አግኝተዋል ማለት ይቻላል። አንድ ነገር ለማመን እስከሚከብድ ድረስ ጥሩ ሲመስል እንደዚያው ነው ማለት ነው። ብዙ ሰዎች በስሜትም በገንዘብም ተጎድተዋል። የእነዚህ የማይታመኑ ዕቅዶች ሌላ መጥፎ ገጠመኝ ግለሰቦች ከእነርሱ ጋር ለመሳተፍ በመጀመሪያ ደረጃ ገንዘብ መበደር አለባቸው። ቶሎ ሀብታም የመሆን ዕቅዶች ብዙ ሕይወቶችንና ቤተሰቦችን አጥፍተዋል። ለዚህ ምክንያቱ ዕቅዱን የሚነድፉ ተዋኒያን በእነርሱ ወጥመድ ውስጥ በሚወድቁ ሰዎች ኪሳራ ሀብታም ስለሚሆኑ ነው። ጓደኛችሁ ወይም የምትወዱት ሰው ከእነዚህ ዕቅዶች ወደ አንዱ ጎትቶ ሊያስገባችሁ ሲሞክር ሽሹ። አትራመዱ። እስከሚቻላችሁ ድረስ ሽሹ።

ጥር 25
Feb 02

የጊዜ ገደቦችና የብድር ነጥቦች


ዘዳግም 15:1–5ን ያንብቡ። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ እንደተገለጠው እግዚአብሔር ከሕዝቡ የሚጠይቀው ምንድር ነው?



ከሌሎች የሰባት ዓመት ሕግጋት/ደንቦች ጋር በተጣጣመ ሁኔታ (ዘጸ. 21፡2፤ ዘሌ. 25፡3፣ 4) ቁጥጥር የሚደረግባቸው ባርያዎች ወይም አገልጋዮችና መሬት ብቻ ሳይሆን አበዳሪዎችም ጭምር ናቸው። አበዳሪዎች ምንም ዓይነት ዕዳ መተው ስላልፈለጉ አንድ ሰው በዕዳ የሚያዝበት ረጅሙ ጊዜ ሰባት ዓመት ነው። ከእነዚህ ጥቅሶች መማር የምንችለው ነገር ቢኖር እግዚአብሔር ለእንደዚህ ዓይነቶቹ ገንዘብ ነክ ነገሮች ፣በተላይም እሥራኤላውያንን በተመለከተ፣ ግድ እንደሚለው ነው። እነዚህ ጥቅሶች የሚያሳዩት ሌላኛው ነገር ዕዳ ምንም ያህል ክፉ ቢሆንም ያለ ነገር መሆኑን ነው። በተቻለ መጠን ዕዳን መሸሽ እንደሚያስፈልግም አጽንዖት ሰጥቷል።

ከዚህ በተቃራኒ፣ ዛሬ፣ በብዙ የዓለም ክፍሎች ቤት ለመግዛት ለ30 እና 40 ዓመታት ብድር ተዘጋጅቷል። ቤቶች እጅግ ብዙ ዋጋ ከሚያወጡባቸው ምክንያቶች አንዱ ቤቶችን ለመግዛት ብድር መዘጋጀቱ ሳይሆን አይቀርም። ብዙ ሰዎች፣ ወላጆችና ተማሪዎች ለትምህርት ገንዘብ በመበደራቸው ይገረማሉ። እንደ ደንብ ስንመለከት የኮሌጅ ድግሪ ማግኘት በቀሪው የሕይወት ዘመን በሙሉ የግለሰቡን ገንዘብ የማግኘት ችሎታ ከፍ ያደርጋል። አንዳንድ ሰዎች ለትምህርታቸው ለመክፈል ገንዘብ መበደር ሊያስፈልጋቸው ይችላል፣ ነገር ግን እነዚህን ነገሮች በአእምሮአችሁ ያዙ። የተበደራችሁትን ገንዘብ የምትከፍሉት በወለድ ነው። ማግኘት የምትችሉአቸውን ስጦታዎችና ነጻ የትምህርት ዕድሎች ለማግኘት ሞክሩ። የምትችሉትን ሁሉ ሰርታችሁ ለትምህርት ቤት ክፍያ ቆጥቡ።

ሥራን ወደማግኘት የሚመሩአችሁን ኮርሶች ብቻ ውሰዱ። የወላጆችን እገዛ አግኙ። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ልጆች የራሳቸውን መተዳደሪያ እንዲያፈሩ ወላጆች የእርሻ መሬት ይሰጡአቸው ነበር። ዛሬ ልጆች ራሳቸውን ችለው መኖር እንዲችሉ የሚሰጣቸው ያ ‹‹ውርስ›› ትምህርት ነው። እንዲሆንልን በምንመኘው ዓለም መበደርና ማበደር አይኖርም። ነገር ግን እንዲሆንልን በምንመኘው ዓለም ውስጥ ስለማንኖር መበደር አስፈላጊ የሚሆንባቸው ጊዜያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ስለዚህ እስከሚቻላችሁ ድረስ በጥሩ ሁኔታ ተደራደሩ፣ ወለዱም ከሌሎች የተሻለ መሆኑን አረጋግጡ። ከዚያ በኋላ የሚያስፈልጋችሁን ያህል ብቻ ተበደሩ፣ የወለድ ወጪን ለመቀነስ በተቻለ ፍጥነት ብድራችሁን ክፈሉ። ነገር ግን በመርህ ደረጃ በሰብአዊ አቅም እስከሚቻል ድረስ ዕዳ ውስጥ ላለመግባት መሻት አለብን፤ በየዕለቱ ሕይወታችን መጽሐፍ ቅዱሳዊ የገንዘብ መርሆዎችን በመከተል አለአስፈላጊ ዕዳንና በእኛና በቤተ ሰቦቻችን ላይ የሚያሳድረውን አሰቃቂ ጭንቀት ለማስወገድ ረዥም መንገድ መጓዝ እንችላለን።

ገንዘብን ለሰዎች አበድረው ከሆነ ከእነርሱ ጋር በሚያደርጉት ግንኙነት ምን ያህል ታማኝ፣ ፍትሃዊና ቸር ነዎት? ለእነዚህ ግንኙነቶችዎ መልስ ሲሰጡ በእግዚአብሔር ፊት የሚጓዙት እንዴት ነው? (መክብብ 12:14ን ይመልከቱ) ።

ጥር 26
Feb 03


ተጨማሪ ሀሳብ


:- ዕዳን የማስወገጃ ሶስት ደረጃዎች ያሉት ሂደት በኤለን ጂ ኋይት ጽሁፎች ውስጥ በአንድ ገጽ ውስጥ አለ። ነጥቦቹን ለማጉላት ሲባል ለቃላቶቹ አጽንዖት ተሰጥቶባቸዋል። “ሌላ ዕዳ ውስጥ ላለመግባት ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። በዕዳ ውስጥ ከምትገባ የሚያስፈልጉህን ሺህ ነገሮች ተው። በዕዳ ውስጥ መግባት የህይወትህ እርግማን ሆኖ ቆይቷል። ፈንጣጣን እንደምትሸሽ ዕዳን ሽሽ። “በእርሱ በረከት ዕዳዎችህን እንድትከፍልና ገንፎንና ዳቦን እየተመገብክ የምትኖር እንኳን ቢሆን የማንም ዕዳ እንዳይኖርብህ ከእግዚአብሔር ጋር ጽኑ ቃል ኪዳን ፈጽም።…..አታቅማማ፣ ተስፋ አትቁረጥ ወይም ወደ ኋላ አትመለስ። የምግብ ጣዕምን ካድ፣ የምግብ ፍላጎትን ማሟላትን ካድ፣ ሳንቲሞችን ቆጥብና ዕዳህን ክፈል።

“በተቻለ ፍጥነት ሰርተህ ዕዳህን ክፈል። የማንም ዕዳ ሳይኖርብህ እንደገና ነጻ ሰው ሆነህ መቆም ስትችል ትልቅ ድል ተቀዳጅተሃል ማለት ነው።”—Counsels on Stewardship, p. 257. ከዕዳ ነጻ ለመሆን ተጨማሪ እርዳታ የምትፈልግ ከሆነ የሚከተሉትን ነጥቦች ሞክር፡- ባጄት መስራት። ወጪዎችህንና ገቢዎችን መዝግበህ በመያዝ ቀላል ባጀት አዘጋጅ። ወጪህ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ለሸመትካቸው ነገሮች ያወጣሃው ገንዘብ ነው። ብዙ ሰዎች አስፈላጊ ላልሆኑ ነገሮች ምን ያህል ገንዘብ እንዳወጡ ሲረዱ ይደነቃሉ።

የክሬዲት ካርዶችን አጥፋ። ቤተሰብን ዕዳ ውስጥ ከሚያስገቡ ዋና ነገሮች መካከል የክሬዲት ካርድ አንዱ ነው። ክሬዲት ካርዶች ለመጠቀም እጅግ ቀላልና ለመክፈል እጅግ ከባድ ናቸው። በየወሩ በክሬዲት ካርድ የወሰድካቸውን ዕዳዎች በሙሉ እየከፈልክ አለመሆንህን ከተረዳህ፣ ወይም የክሬዲት ካርድ ባይኖር ኖሮ የማትገዛቸውን ነገሮች ሁሉ እየገዛህ መሆንህን ከተገነዘብክ እነዚህ ካርዶች አንተን ወይም ትዳርህን ወይም ሁለቱንም ከማጥፋታቸው በፊት እነርሱን አጥፋቸው።

ኢኮኖሚያዊ መቆጣጠሪያዎችን ጀምር። ስለምንገዛቸው አንዳንድ ትንንሽ ነገሮች ጥንቃቄ በማድረግ ከወርሃዊ ወጪዎቻችን ምን ያህል ማዳን እንደምንችል አንዳንድ ጊዜ አናውቅም። እነዚህ የምናድናቸው ትንንሽ ነገሮች እየተደመሩ በፍጥነት ያድጋሉ።


የውይይት ጥያቄዎች



: 1. ብዙ አገሮችና ግለሰቦች በላያቸው ተሸክመው ያሉት የዕዳ መጠን ጭንቅላት የሚያዞር ነው። ዕዳ ለራስዎና ለሌሎች ሰዎች ከፈጠራቸው ችግሮች ጋር የእርስዎ ልምምድ ምን ነበር?

2 የቤተ ክርስቲያን አባላት ዕዳን ወይም ገንዘብን የሚመለከቱ ጉዳዮችን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው ለመርዳት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያንዎ ምን ማድረግ ትችላለች?

3. ዓለም ማታለያና ስስት ከሚያመጣው ከገንዘብ አደጋ ራስዎን መጠበቅ እንዲችሉ የሚረዱ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋዎች ምንድር ናቸው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL