የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ጌታ እስኪመጣ ድረስ የእርሱን ንብረት ማስተዳደር


የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 1ኛ ሩብ ዓመት 2023

ጥር 27- የካቲት 3

6ኛ ትምህርት

Feb 4 - 10




በሰማይ ሀብት መሰብሰብ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ:- ዘፍ. 6:5–14፣ ዕብ. 11:8– 13፣ 2 ቆሮ. 4:18፣ ዘፍ. 13:10–12፣ ዘፍ. 32:22–31፣ ዕብ. 11:24–29።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? ሰውስ ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል?” (ማርቆስ 8:36፣ 37)።

ኢ የሱስ “ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ፤ ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ” (ማቴ. 6:19፣ 20) በማለቱ በዓለም ላይ ከሁሉ የሚበልጠውን ሀብት የማፍሰስ ስልት ሰጥቶናል። ኢየሱስ ሀብት ሥራ ላይ የማዋሉን ስልት እንዲህ በማለት ይደመድመዋል፡- “መዝገብህ ባለበት ልብህ ደግሞ በዚያ ይሆናልና” (ማቴ. 6:21)። በሌላ አገላለጽ ገንዘብህን በምን ላይ እንደምታውል አሳየኝና ልብህ የት እንደሆነ አሳይሃለሁ ማለት ነው። ገንዘባችሁን የትም ሥራ ላይ ብታውሉ ልባችሁ በእርግጠኝነት ይከተለዋል፤ ያም የሚሆነው አስቀድሞውኑ እዚያ ቦታ ከሌለ ነው።

ልባችሁ በእግዚአብሔር መንግስት እንዲሆን ትፈልጋላችሁ? ፍላጎታችሁ ይህ ከሆነ ገንዘባችሁን የዘላለም ሽልማቶችን በሚያጭድበት ቦታ አስቀምጡ። ጊዜያችሁን፣ ገንዘባችሁንና ጸሎታችሁን በእግዚአብሔር ሥራ ላይ አድርጉ። እንደዚህ ካደረጋችሁ በሥራው ከበፊቱ የበለጠ ፍላጎት ያድርባችሁና ልባችሁም ያንኑ ይከተላል። በዚህ ሳምንት ሀብትን በሰማይ እንዴት እንደምናካብትና በመጨረሻም ዘላለማዊ ሽልማትን እንዴት እንደምናጭድ የሚያሳዩንን ጥቅሶችና ማብራሪያዎች እንከልሳለን።

*የዚህን ሳምንት ትምህርት ለየካቲት 4 ሰንበት ለመዘጋጀት አጥኑ።

ጥር 28
Feb 05

ኖህና ጸጋ


ሰማያዊ ሀብት የሚሹ ሰዎች እዚህ ምድር ላይ እያሉ ዋና የሕይወት ለውጦችን እንዲያደርጉ እግዚአብሔር በየጊዜው እንደሚጠራቸው ልብ ማለት አስፈላጊ ነው። አስፈላጊ ከሆነ ተመሳሳይ ነገርን ለመጋፈጥ ተዘጋጁ። ዘፍጥረት 6:5–14ን ያንብቡ። ኖህ እግዚአብሔርን ከመታዘዙ የተነሣ ምን ዋና ለውጦች ተከሰቱ? ስለማይቀረው ጥፋት ማስጠንቀቂያ ሊሰጠው በሚገባ ዓለም ውስጥ በዚህ ቦታ ለራሳችን ምን መርሆዎችን ማግኘት እንችላለን?



ኖህ ለራሱ ቤት እየሰራ ጊዜውንና ሀብቱን ሊያባክን ይችል ነበር፣ ነገር ግን በሕይወቱ መሰረታዊ ለውጥ ለማድረግና የእግዚአብሔርን ጥሪ በመከተል መርከብን ለመስራት 120 ዓመታትን ለማሳለፍ መረጠ። ዛሬ ብዙ ተጠራጣሪዎች የውኃ ጥፋትን ታሪክ በስፋት ተቀባይነት ያገኘ ሀሰተኛ እምነት፣ ስለሚታወቁት የተፈጥሮ ሕግጋት በሳይንሳዊ ግምቶች ላይ የተመሰረተ ሀሳብ የሚያቀርብ እንደሆነ ይናገራሉ። ይህ አዲስ ነገር አይደለም። “ከውኃ ጥፋት በፊት የነበረው ዓለም ለብዙ መቶ ዓመታት የተፈጥሮ ሕግ የማይለዋወጥ ነው፤ ወቅቶች ጊዜያቸውን ጠብቀው ይመጣሉ፤ እስከ ዛሬ ድረስ ዝናብ ዘንቦ አያውቅም፤ መሬትን የሚያጠጣው ጉም ወይም ጤዛ ነው፤ ወንዞች ከገደባቸው በፍጹም አልፈው አያውቁም፣ ነገር ግን የያዙትን ውኃ ያለ አንዳች ችግር ወደ ባህር ያደርሳሉ፤ የማይቀያየር አዋጅ ውኃዎች ከገደባቸው አልፈው እንዳይፈሱ አድርጓል ብሎ ያምን ነበር።”—Ellen G. White, Patriarchs and Prophets, p. 96.

እውነታውን በተሳሳተ ሁኔታ ከመረዳት የተነሳ ከጥፋት ውኃ በፊት የነበሩ ሰዎች የውኃ ጥፋት በፍጹም አይመጣም ብለው ይከራከሩ ነበር። ከጥፋት ውኃ በኋላም እውነታውን በተሳሳተ መልክ ከመረዳታቸው የተነሣ መጀመሪያውኑ የውኃ ጥፋት አልተከሰተም ብለው ይከራከራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “ከፀሐይ በታች ምንም አዲስ ነገር የለም” (መክ. 1:9)። ሰዎች ስለ ውኃ ጥፋት እንደተጠራጠሩ ሁሉ ስለ መጨረሻው ዘመን ክስተቶችም ተጠራጣሪ እንደሚሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል ( 2ኛ ጴጥሮስ 3፡3-7ን ይመልከቱ)። ታዲያ ስለሚመጣው ጥፋት እንዴት መዘጋጀት እንችላለን? ‹‹የዘገየ ፍላጎትን ማሟላት›› የሚባል ታስቦበት የሚወሰን ውሳኔ አለ።

በመሰረታዊነት ይህ ማለት ወደ ፊት የሚመጣውን ባለ ግርማ ሽልማት ተስፋ በማድረግ የእግዚአብሔርን ሥራ በትዕግስት መስራት አለብን ማለት ነው። ክርስቶስ መቼ እንደሚመለስ አናውቅም። ይህ ምንም ልዩነት አያመጣም። ልዩነት የሚያመጣው፣ መሰረታዊ የሆነ የሕይወት ለውጥ የሚያስከትል ቢሆንም፣ ኖህ እንዳደረገው እግዚአብሔር እንድንሰራ የሚጠይቀንን ነገር ማድረጋችን ነው። ልክ ኖህ ያደረገውን ነገር እንድታደርግ ብትጠራ ኖሮ በሕይወትህ መሰረታዊ ለውጥ ለማድረግ ምን ያህል ዝግጁ ነህ? (ፍንጭ:- ሉቃስ 16:10ን ይመልከቱ)።

ጥር 29
Feb 06

አብርሃም፣ የታማኞች አባት


እግዚአብሔር አብርሃምን ከአገሩና ከዘመዶቹ ተለይቶ እርሱ ወደሚያሳየው አገር እንዲሄድ ጠራው። የመሲሁ የዘር ግንድ እዚህ ተጀመረ። ዝርዝር ሀሳቦች ባይሰጡም አብርሃም የተወለደበትንና የቀድሞ አመታትን የኖረበትን አገር ትቶ መውጣት ነበረበት። ውሳኔው ቀላል አልነበረም፣ ይህን ለማድረግ አንዳንድ ምድራዊ ድሎቶችንና ምቾቶችን እንደተወ ምንም ጥርጥር የለም። ዘፍጥረት 12፡1-3ን ያንብቡ። ከዚህ ተስፋና ተስፋውን ከመቀበሉ የተነሣ ‹‹የምድር ወገኞች ሁሉ የተባረኩት›› እንዴት ነው?



ይህ ለአብርሃምና ለቤተሰቡ ሕይወትን የሚለወጥ አብይ ክስተት ነበር። “አብርሃም የተባለው ርስት አድርጎ ሊቀበለው ወዳለው ስፍራ ለመውጣት በእምነት ታዘዘ፥ ወዴትም እንደሚሄድ ሳያውቅ ወጣ።” (ዕብ. 11:8)። “አብርሃም አንዳች ጥያቄ ሳያነሳ መታዘዙ በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙ አስደናቂ የእምነት ማስረጃዎች መካከል አንዱ ነው።”—Ellen G. White, Patriarchs and Prophets, p. 126.

አብዛኞቻችን የትውልድ አከባቢያችንን፣ ወዳጆቻችንን እና የቤተሰብ አባሎቻችንን ለመተው ፍላጎት አይኖረንም። ነገር ግን አብርሃም ይህንን አደረገ። እግዚአብሔር ባስቀመጠው ቦታ መቀመጥ ለአብርሃም እርካታ ሰጥቶት ነበር። ያልተለመደ ነገር ቢመስልም አብርሃም፣ ይስሃቅና ያዕቆብ በሕይወት ዘመናቸው የተስፋውን ምድር አልተቀበሉም ነበር፤ ነገር ግን ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆነው ቆዩ። ዕብ. 11፡8-13ን ያንብቡ። በዚህ ቦታ ለእኛ የሚገጥም መልእክት ምንድን ነው?



አብርሃም በዙሪያው በሚኖሩ ሰዎች ዘንድ እንደ ልዑል ይታወቅ ነበር። በልግስናው፣ በድፍረቱ፣ በእንግዳ ተቀባይነቱና ከሁሉ የሚበልጥ አምላክ በማምላኩ ይታወቅ ነበር። ለእግዚአብሔር ያለው ምስክርነቱ ምሳሌ መሆን የሚችል ነበር። በእግዚአብሔር ፀጋ እኛም የአብርሃም ወራሾች ነን። “እንዲሁ አብርሃም በእግዚአብሔር አመነና ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት። እንኪያስ ከእምነት የሆኑት እነዚህ የአብርሃም ልጆች እንደ ሆኑ እወቁ” (ገላ. 3:6፣ 7)። “እናንተም የክርስቶስ ከሆናችሁ እንኪያስ የአብርሃም ዘር እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ” (ገላ 3:29)።

በኖህ ታሪክ እንደተመለከትነው ሁሉ በአብርሃም ታሪክም የምናየው ነገር ቢኖር እግዚአብሔርን ከመታዘዝ የተነሳ ይህ ሰው ሕይወትን የሚቀይር አብይ ውሳኔ ሲፈጽም ነው። 2ኛ ቆሮ. 4፡18ን ያንብቡ። የዚህ ጥቅስ መልእክት ምን ዓይነት መንፈሳዊ ውሳኔዎችን መወሰን እንዳለብን ተጽእኖ ማሳደር ያለበት እንዴት ነው? ሙሴና አብርሃም ያንኑ መርህ መከተል የቻሉት እንዴት ነበር?

ጥር 30
Feb 07

የሎጥ መጥፎ ውሳኔዎች


አብርሃም ለእግዚአብሔር ጥሪ ምላሽ በመስጠት ከአገሩ በወጣ ጊዜ የወንድሙ ልጅ የሆነው ሎጥ አብሮት ለመውጣት ወሰነ። አብርሃም “በከብት በብርና በወርቅ” እጅግ እስኪበለጽግ ድረስ እግዚአብሔር እንደባረከው ዘፍጥረት ምዕራፍ 13 መዝግቦ ይዟል(ዘፍ. 13:2)። ሎጥም ደግሞ “የላምና የበግ መንጋ ድንኳንም ነበረው።” (ዘፍ. 13:5)። ሁለቱም በከብት ብዛት እጅግ ስለበለጸጉ አብረው መኖር አልቻሉም ነበር። በእረኞቻቸው መካከል ጠብ እንዳይፈጠር በማለት ሎጥ መኖር የሚፈልግበትን እንዲመርጥ አብርሃም እድል ሰጠው። እንደ እውነቱ ከሆነ አብርሃም በዕድሜ ስለሚበልጠውና ሀብትም ማፍራት የቻለው ከእርሱ ጋር ካለው ግንኙነት የተነሣ ስለሆነ ሎጥ አብርሃምን መስማት ነበረበት። ነገር ግን እስካሁን የረዳውን አብርሃምን በማመስገን ፋንታ በእርሱ ግምት ከሁሉ የተሻለ ነው ብሎ ያሰበውን መሬት በራስ ወዳድነት መውሰድ ፈለገ። ዘፍጥረት 13:10–12ን ያንብቡ። ሎጥ የወሰነውን ውሳኔ እንዲወስን ያደረጉት አሳማኝ ምክንያቶች ምን ነበሩ?



ሎጥ ወደ ከተማው ለመሄድ ለወሰነው ውሳኔ በቀላሉ ምክንያቶችን ማቅረብ ቢችልም እዚያ ሲደርስ ነገሮች ቀላል አልሆኑለትም። አብርሃም በሎጥ ላይ የደረሰበትን ነገር ሲሰማ ‹‹እንግዲህ ሎጥ ሆይ፣ መጥፎ ነገር ገጥሞሃል። የዘራኸውን አጭደሃል›› አላለውም። ይልቁንም እርሱን ለማዳን እርምጃ ወሰደ። (ዘፍጥረት ምዕራፍ 14ን ይመልከቱ)። አንዳንድ ጊዜ የበለጠውን ለማግኘት በምናደርገው ጥያቄ በበቂ ሁኔታ ትምህርት ሳናገኝ እንቀራለን። ሎጥ ወደ ሶዶም አቀና። ነገር ግን ሎጥና ቤተሰቡ በእነዚህ ከተሞች ላይ ሊደርስ ስላለው ጥፋት እንዲያውቁ እግዚአብሔር የሚያስጠነቅቁ መልእክተኞችን ላከ።

ዘፍጥረት 18:20–33ን ያንብቡ። እግዚአብሔር ምድሪቱን የጎበኘበት ምክንያት ምን እንደሆነ ነበር እግዚአብሔር ለአብርሃም የነገረው? እግዚአብሔር እነዚህን ኃጢአተኛ ከተሞች ሊያጠፋቸው ዕቅድ እንዳለው ሲነግረው የአብርሃም ምላሽ ምን ነበር?



አብርሃም ለሎጥና ለቤተሰቡ ግድ ስላለው በከተማዎቹ ውስጥ ጻድቃን ሰዎች ከተገኙ እንዳያጠፋቸው ከእግዚአብሔር ጋር ተከራከረ። በ50 ሰው ጀምሮ እስከ 10 ሰው ድረስ ሄደ። ከፍቅር ባህርዩ ጋር በተጣጣመ ሁኔታ አብርሃም ጥያቄውን እስኪያቆም ድረስ እግዚአብሔር ምህረት ማድረጉን አላቆመም ነበር። እግዚአብሔርና ሁለቱ መላእክት ሎጥን፣ ሚስቱንና ሁለቱን ሴት ልጆቻቸውን በግላቸው አወጡአቸው። ነገር ግን ሚስቱ ወደ ኋላ ተመለከተችና የጨው አምድ ሆና ቀረች። ሎጥ ወደ ሶዶም ሲገባ ሀብታም የነበረ ሲሆን ከዚያ ሲወጣ ግን ባዶ እጁን ነበር። የምንወስናቸውን ውሳኔዎች በተመለከተ፣ በተለይም ትልቁን ስዕል ሳናይ የአጭር ጊዜ ትርፍን በማሰብ የምንወስናቸውን ውሳኔዎች በተመለከተ ምን ያህል ጥንቁቅ መሆን ይጠበቅብን ይሆን! (ማርቆስ 8፡36፣ 37ን ይመልከቱ)።

የካቲት 1
Feb 08

ከአታላይ ወደ ልዑል


ያዕቆብ እግዚአብሔርን የሚወድና የሚፈራ ወጣት ቢሆንም አባቱን አታልሎ በረከቱን ለመቀበል ከእናቱ ርብቃ ጋር ለማሴር ራሱን ዝቅ አደረገ። ከዚህ የተነሣ ቤቱን ለቆ በመኮብለል ወይም ያለ ዕድሜው በመሞት ምርጫ ውስጥ በመውደቅ የጎልማሳነት ሕይወቱን በተሳሳተ መንገድ ላይ ጀመረው። ርብቃ ያዕቆብን “ወደ ላባ ሂድ፤ የወንድምህ ቍጣ እስኪበርድ ድረስ በእርሱ ዘንድ ጥቂት ቀን ተቀመጥ፥ከዚያ በኋላ እኔ አስልኬ አስመጣሃለሁ” አለችው (ዘፍ 27:43-45)። ያዕቆብ ከቤት ከኮበለለ 20 ዓመታት ያለፉበት ሲሆን የእናቱን ፊት ዳግመኛ አላየም ነበር።

ዘፍጥረት 32:22-31ን ያንብቡ። ያዕቆብ ምን ደረሰበት? ከዚህ ታሪክ፣ የተሳሳቱ ውሳኔዎችን ስንወስን እንኳን፣ ስለ እግዚአብሔር ፀጋ ምን መንፈሳዊ ትምህርት እናገኛለን?



“ይህ ኃጢአተኛና ተሳሳች ሟች ሰው በንስሃ፣ ራሱን በማዋረድና አሳልፎ በመስጠት ከሰማይ ንጉስ ጋር አሸነፈ። እየተንቀጠቀጠ የእግዚአብሔርን ተስፋ አጥብቆ ያዘ። ከዚህ የተነሣ ዘላለማዊ ፍቅር የሆነው አምላክ ልብ የኃጢአተኛውን ልመና ችላ አላለም። ያዕቆብ ብኩርናን አጭበርብሮ በመውሰድ ኃጢአት እንዲሰራ የመራው ስህተት አሁን በፊቱ በግልጽ ተቀምጦአል። በእግዚአብሔር ተስፋዎች አልታመነም፣ ነገር ግን እግዚአብሔር በምንም መንገድ ቢሆን በራሱ ጊዜ ሊፈጽም የሚችለውን ነገር በራሱ ጥረት ለመፈጸም ፈለገ። …ያዕቆብ ነፍሱ ለረዥም ጊዜ ስትናፍቀው የነበረውን በረከት ተቀብሏል። የቀማኛነትና የአታላይነት ኃጢአቱ ይቅር ተብሎለታል።”—Ellen G. White, Patriarchs and Prophets, pp. 197, 198.

ዘፍጥረት 49:29-33ን ያንብቡ። ያዕቆብ በከነዓን ምድር ምንም ርስት ባይኖረውም ቀብሩን በተመለከተ ለልጆቹ ምን መመሪያዎችን ነበር የሰጠው? በዚያ ዋሻ ውስጥ እነማን ተቀብረው ነበር ? ያዕቆብ ይህን ጥያቄ ለምን አቀረበ ብለው ያስባሉ?



ሶስቱም አባቶችና ሚስቶቻቸው በሙሉ በዚያ ዋሻ ውስጥ እንደተቀበሩ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ያዕቆብ በእግዚአብሔር ላይ የነበረው መታመን ጠንካራ ስለነበር በምድር ላይ ራሱን ይመለከት የነበረው እንግዳና ተጓዥ እንደሆነ ነበር (ዕብራውያን 11፡13ን ይመልከቱ)። ምንም እንኳን ስህተት ቢሰራም ከከነዓን ሲወጣ ባዶ እጁን የወጣ ሲሆን ወደ ካናዓን ሲመለስ ግን በልጽጎ ነበር።

ስህተተኞች ብንሆንም እንኳን እግዚአብሔር ሊባርከን ይችላል። ነገር ግን ከስህተት መራቅ ምን ያህል የተሻለ በረከት ያስገኝ ይሆን! አሁን ከፊትዎ የተቀመጡት ምርጫዎች ምንድር ናቸው? የስህተት ምርጫን ከመምረጥ መራቅ የሚችሉት እንዴት ነው?

የካቲት 2
Feb 09

ሙሴ በግብጽ


የሙሴ ባህርይ የቅዱስ ታሪክ ቀደምት ዓመታትን ተቆጣጥሮ ነበር። እግዚአብሔር ድርድር በምታውቅ እናትና ተጠንቃቂ በሆነች እህት አማካይነት በሰራው በእግዚአብሔር ልዩ መሰናዶ በሕይወት እንዲኖር ተደረገ። የፈርዖን ሴት ልጅ ሙሴን በውኃ ላይ በሚንሳፈፍ ቅርጫት ውስጥ ባገኘችው ጊዜ ዕብራዊቷ እናቱ እንድትጠነቀቅለትና ለእሷ እንድታሳድግላት ደሞዝ ከፈለች። ስደተኛና ባርያ ለሆነች ወጣት እንዴት ያለ የተባረከ ግድድሮሽ ነው! ዮካቤድ ልጇን መጸለይን፣ በእግዚአብሔር መታመንን እና እርሱን ማክበርን ለማስተማር፣ እንዲሁም ባህርዩን ለአገልግሎት ሕይወት ለመቅረጽ የነበራት ጊዜ 12 ዓመት ብቻ ነበር። ሙሴ በግብጽ ቤተ መንግስት ውስጥ ለዓመታት ሥልጠና ወስዷል። “ሙሴም የግብፆችን ጥበብ ሁሉ ተማረ፥ በቃሉና በሥራውም የበረታ ሆነ” (የሐዋ. ሥራ 7:22)። ሙሴ ወደ ብስለት ዕድሜ ሲደርስ ሕይወቱንና የታሪክን መንገድ የቀየረውን ውሳኔ አስቦበት ወሰነ።

ዕብራውያን 11:24–29ን ያንብቡ። ሙሴ ከኋላው ስለተወውና በዚያ ፋንታ ሊጋፈጥ ስላለው ነገር አስቡ። እርሱ ምርጫውን ከመምረጡ በፊት በነበረው በእርሱ ቦታ ሆናችሁ ነገሩን ለመመልከት ሞክሩ። እየተወ የነበረው ነገርና ከመተው የተነሣ ለመቀበል እየመረጠ ያለው ነገር ምን ነበር?



በዚያን ጊዜ ግብፅ ብቸኛዋ ታላቅ አገር ባትሆን እንኳን በጥንቱ ዓለም ከነበሩ ታላላቅ ኃይላት አንዷ ነበረች። የአባይ ወንዝ ለም መሬትን ስለፈጠረላት ግብጽ በእህል ከመሞላቷ የተነሣ ኃብታምና ኃይለኛ መንግስት ነበረች፤ ሙሴ ደግሞ በዚህች መንግስት ቁንጮ ላይ መሆን ይችል ነበር። የዓለም ማታለያ፣ የግብፅ ዓለምና ሀብቷ በሙሉ በዕድሜው ቀደምት ዓመታት ምን ያህል ፈታኝ እንደነበሩ ለማሰብ አይከብድም። ሰዎች በሚሰጡት አክብሮት፣ ምቾትና ሀብት መፈተኑ እርግጥ ነበር። ዕጣውን ከተናቁ ባሪያዎች ጋር ከመጣል ይልቅ ምንም በማያሻማ ሁኔታ በግብጽ ለመቆየት በቀላሉ ምክንያት ማቅረብ ይችል ነበር።

ግን ምን ሆነ? መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው “ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ፤ ብድራቱን ትኵር ብሎ ተመልክቶአልና” (ዕብ. 11:25)። ስለ መከራዎቹስ ተናገረ? የዘጸአት መጽሐፍ አብዛኛው ክፍል የሚያወራው ስለ ሙሴ ትግሎችና ፈተናዎች ሲሆን በእነዚያ ትግሎችና ፈተናዎች ውስጥ ካለፈ በኋላም ወደ ተስፋይቱ ምድር መሻገር አልቻለም ነበር። (ዘሁልቁ 20:12ን ይመልከቱ)። ሆኖም በመጨረሻ አንዳንድ ጊዜ ትክክለኛ ምርጫ ስለማድረጉ ጥርጣሬ ቢገባበትም ትክክለኛ ምርጫ ማድረጉን ሁላችንም እናውቃለን።

ከዓለማዊ ዕይታ ስናይ ሙሴ በግብፅ መቆየት ነበረበት። ነገር ግን እንደ ክርስቲያኖች ከዚህ ዓለም ባሻገር ስለሚወስደን እውነታ እይታ ተሰጥቶናል። ዓለም ሲፈትነን ሁልጊዜ በፊታችን ትልቁን ምስል ማስቀመጥ የምንችለው እንዴት ነው? እንዲህ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድር ነው?

የካቲት 3
Feb 10


ተጨማሪ ሀሳብ


:- እግዚአብሔር አብርሃምን በመባረክ የገባውን ቃል ኪዳን የራሱን ድርሻ አክብሮአል። አብርሃምም ሀብትን በዚህች ምድር ላይ ባለመሰብሰብ እግዚአብሔርን አከበረ። “እግዚአብሔር ለሕዝቡ ቃል የገባው ውርስ በዚህች ዓለም ላይ አይደለም። አብርሃም በምድር ላይ ሀብት አልነበረውም፤ የእግሩን ጫማ የሚያሳርፍበት ቦታ እንኳን አልነበረውም።’ የሐዋ. ሥራ 7:5። ትልቅ ሀብት የነበረው ሲሆን ሀብቱን ለእግዚአብሔር ክብርና ለሰው ልጆች ጥቅም ተጠቀመበት፤ ነገር ግን ይህን ዓለም መኖሪያ ቤቱ አድርጎ አልተመለከተውም። የካናዓንን ምድር ዘላለማዊ ርስት አድርጎ እንደሚሰጠው ቃል በመግባት ጣዖት አምላኪ የሆኑ የአገሩን ሰዎች ትቶ እንዲወጣ እግዚአብሔር ጠራው። ሆኖም እርሱም ሆነ ልጁ ወይም የልጁ ልጅ ተስፋውን አልተቀበሉም ነበር።

አብርሃም ሬሳውን መቅበር ሲፈልግ ከከነዓናውያን መሬት መግዛት ነበረበት። በተስፋይቱ ምድር ላይ የነበረው ብቸኛው ርስት በማክፌላህ የነበረው ከዓለት የተፈለፈለ መቃብር ነበር።”—Ellen G. White, Patriarchs and Prophets, p. 169. በሕይወት ስንኖር አንዳንድ ጊዜ ሀብትና ምቾት ለመፈለግ እንፈተናለን። የራስን ፍላጎት ማርካትን ማዘግየት ጠንካራ እምነት ይጠይቃል። “የፈርዖን ውብ ቤተ መንግስትና የንጉሡ ዙፋን ለሙሴ በማታለያነት ቀርበውለት ነበር፤ ነገር ግን ሰዎች እግዚአብሔርን እንዲረሱ የሚያደርግ በኃጢአት የሚገኝ ደስታ በነገሥታት ቤተ መንግስት ውስጥ እንዳለ አወቀ።

ከተንቆጠቆጠው ቤተ መንግስትና ከንጉሡ ዘውድ ባሻገር በኃጢአት ባልተበከለው መንግስት ለልዑል ቅዱሳን የሚሰጠውን ታላቅ ክብር ተመለከተ። የሰማይ ንጉሥ በአሸናፊዎች ራስ ላይ የሚጭነውን የማይጠፋ ዘውድ በእምነት ተመለከተ። ይህ እምነት ከምድራዊ መሳፍንት እንዲለይና ኃጢአትን ከማገልገል ይለቅ እግዚአብሔርን ለመታዘዝ የመረጡትን ትሁት፣ ድሃና የተናቀ ሕዝብ እንዲቀላቀል መራው።”—Patriarchs and Prophets, p. 246.


የውይይት ጥያቄዎች



1.ኢየሱስ ሲመጣ ሀብታችን ምን ይሆናል? (2ኛ ጴጥ. 3:10ን ይመልከቱ)። ኢየሱስ ከመምጣቱ በፊትም ቢሆን ሀብታችን ምን ሊሆን ይችላል? (ማቴ. 6:20ን ይመልከቱ)። ሁልጊዜ ነገሮችን በትክክለኛ ቦታቸው ማስቀመጥ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድር ነው?

2. ኢየሱስ ስለ ‹‹ሀብት አታላይነት›› አስጠንቅቋል (ማር. 4፡19)። ስለ ምንድር ነው እየተናገረ ያለው? ሀብት እንዴት ሊያሳስተን ይችላል?

3.ሙሴ ከተወሰኑ ባሪያዎች ጋር ወደ ምድረ በዳ ለመኮብለል ሁሉን ትቶ ከመውጣት ይልቅ በግብፅ ለመቆየት ሊያቀርባቸው ስለሚችላቸው ምክንያቶች በክፍል ውስጥ ተወያዩ። በመጨረሻ ያደረገውን ነገር ለማድረግ እንዲወስን ያደረገው ነገር ምን ይሆን?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL