የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ማሳደግ



2ኛ ሩብ ዓመት 2026


ሚያዝያ 3 - 9

3ኛ ትምህርት

Apr 11 - 17




ትዕቢት ወይስ ትህትና?



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ 1ኛ ዮሐንስ 2፡15-17፣ ሉቃስ 18፡9-14፣ 1ኛ ዮሐንስ 1፡9፣ ዕብ. 11፡24-26፣ ሉቃስ 22፡24-27፣ ፊልጵ. 2፡3-8።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፥ ራሱንም የሚያዋርድ ከፍ ይላል።” (ሉቃስ 14፡11)

ሁላችንም ከፍ ያለ ራስ ወዳድነት ያለባቸውን፣ ፈጽሞ እንደማይሳሳቱ የሚያስቡ ሰዎችን እናውቃለን። ምናልባት ደግሞ ሁሉንም ነገር ለመቆጣጠር የሚፈልግ፣ ለመማማር ወይም ለገንቢ ትችት ክፍት ያልሆነን ሰው ታውቁ ይሆናል። ወይም ዘወትር በግጭት ውስጥ ያለና ሌሎችን ዝቅ በማድረግ የተካነ ሰውን ታውቁ ይሆናል።

አእምሯችን ወዲያውኑ ስለ ሌሎች ሊያስብ ይችላል፤ ነገር ግን ትክክለኛው ጥያቄ፡- ስለ ራሳችንስ? ጣታችንን ወደ ሌሎች በመጠቆም እና በራሳችን ሕይወት ውስጥ ትዕቢት እንደሌለ በማሰብ ራሳችንን እናታልላለን። ሁላችንም ከትዕቢት ጋር ታግለናል። ሁላችንም በዙሪያችን ካሉት ሰዎች በተሻለ ሁኔታ ለመታየት፣ ለመምሰል፣ ለመናገር ወይም ቢያንስ በሆነ መንገድ ከእነሱ የተሻለ ሆኖ ለመታየት የምንፈልግባቸው ጊዜያት አጋጥመውናል፤ ምክንያቱም ቢያንስ በአንድ ነገር ከእነሱ የተሻልን ነን ብለን ስለምናምን ነው። አንድ ሰው በአንድ ወቅት ትዕቢት የሚመጣው ሕይወታችን ዋጋ እንዳለው ለማሳየት ካለው ፍላጎት ነው ብሏል። ሆኖም ግን በእግዚአብሔር ስለተፈጠርን እና ክርስቶስ ስለ እኛ ስለሞተልን ሕይወታችን ዋጋ እንዳለው ማወቅ አለብን። በዚህ ሳምንት ትዕቢት ከእግዚአብሔር እና ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ላይ ሊኖረው የሚችለውን ተጽእኖ እንመረምራለን፤ እና መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች ፊት በተለይ ደግሞ በእግዚአብሔር ፊት ስንቀርብ እንዴት መቅረብ እንዳለብን የሚያስተምረንን እንመለከታለን። *ለሚያዝያ 10 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያጥኑ።

ሚያዝያ 4
Apr 12

የትዕቢት ጥብቅ ጣቶች


ትዕቢት። ይህንን ቃል ስታስቡ፣ ትዕቢተኛ ፖለቲከኛ፣ ሀብታም ወይም ታዋቂ ሰው ወይም ፒኮክ ወደ አእምሮዎ ሊመጡ ይችላሉ። ትዕቢት ከሌሎች ሰዎች የበለጠ አስፈላጊ ወይም የተሻሉ እንደሆኑ የሚሰማ ስሜት ነው። በእርግጥም ትዕቢት ስሜት ነው - ሊታመን የማይችል እና የማይገባው ስሜት።

ትዕቢት መጀመሪያ የጀመረው ለእግዚአብሔር ቅርብና የሚጋርድ ኪሩብ በነበረው ሉሲፈር ውስጥ ነው። እነዚያ የራስ ወዳድነት ሀሳቦች መቼ ወይም እንዴት ወደ ልቡ እንደገቡ አናውቅም፣ ነገር ግን እነዚህ ሀሳቦች ዩኒቨርስን ወደ ታላቁ ተጋድሎ እንደገፋፉ እናውቃለን።

ሰይጣን የእግዚአብሔር ተቃራኒ መሆኑን እናያለን። (ኢሳይያስ 14:12-14 እና ፊልጵስዩስ 2:5- 11ን ያነፃፅሩ።) በውጤቱም ሰይጣን በአዳምና በሔዋን አእምሮ ውስጥ ጥርጣሬን በመዝራት ከእግዚአብሔር በላይ ራሳቸውን እንዲወዱና እንዲታመኑ ከፈተናቸው ጀምሮ ዓለማችን የኃጢአትን ውጤቶች ሲዋጋ ቆይቷል። 1ኛ ዮሐንስ 2:15-17ን ያንብቡ። ይህ ክፍል ስለ ትምክህትና ዓለምን ስለመውደድ የሚያስተምራቸው ሦስት ዋና ነጥቦች ምንድናቸው?



ትዕቢት(ትምክህት) አዎንታዊ ሊሆን ይችላል? ምናልባት ቃሉን በምናውቀው አውድ አዎንታዊ ሊሆን አይችልም፣ ሆኖም ስለ አንድ ሰው ስኬቶች ስንናገር ወይም አንድ ሰው ላደረገው ነገር ጥልቅ አድናቆት ሲኖረን የምንናገረው አነጋገር አለ (ኮርቼብሃለሁ!”)። ልቀትን መፈለግ እና እግዚአብሔር የሰጣችሁን ስጦታዎች እና ችሎታዎች እውቅና መስጠት እና ማድነቅ ማለት ትዕቢት እንዳልሆነ መረዳት አስፈላጊ ነው። በቅዱሳት መጻሕፍት መሠረት ተገቢ የሆነ ራስን የመውደድ ዓይነት አለ (በማርቆስ 12:31 ላይ ኢየሱስ የሰጠውን ትእዛዝ አስቡ፣ እሱም እኛ ራሳችንን እንደምንወድ ሌሎችን ውደዱ ይላል)፣ ነገር ግን ይህ ሁልጊዜ ለኔ ለኔ ብቻ የማይል ፍቅር ነው። በሕይወታቸው ውስጥ እግዚአብሔር ያላቸው እና ዓላማ ያለው ህይወት የሚመሩ ሰዎች አይታበዩም (1ኛ ጢሞ. 3:1ን ይመልከቱ)። ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ እግዚአብሔር ለሚያደርገው ነገር ክብር ሳይሰጡት ሲቀሩ እየታበዩ ነው። ሀብታችን፣ ችሎታችን እና ስኬቶቻችን ዋጋችንን እንደማይወስኑ ማስታወስ አለብን።

በምትኩ፣ ዋጋችን ሁልጊዜ ከእግዚአብሔር ሊሆን ይገባዋል፣ ምክንያቱም ያለን ሁሉ፣ ወደ ትዕቢት የሚፈትነን እንኳን፣ የሚመጣው ከእርሱ ብቻ ነው። ይህ ፈጽሞ ልንረሳው የማይገባን ነጥብ ነው። እኔ በእርግጥ ምን ያህል ትዕቢተኛ ነኝ? ብለው እራስዎን ይጠይቁ ትዕቢቴ(ትምክህቴ) ከእግዚአብሔር እና ከሌሎች ጋር ባለኝ ግንኙነት ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ያለው እንዴት ነው?

ሚያዝያ 5
Apr 13

እራስዎን ይወቁ


ሁለት ሰዎች ለመጸለይ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄዱ። አንደኛው የተከበረ ሽማግሌ ሲሆን በቤተክርስቲያኒቱ ፕሮግራም ከመጀመሩ በፊት ሰዎች እንዲያዩት በጉባኤው ከፊት የሚቀመጥ ነው። ጮክ ብሎ ይጸልያል፣ ስለ ራሱ መልካምነት እግዚአብሔርን ያመሰግናል።

ሌላኛው ሰው፣ በኅብረተሰቡ የሚናቀው ሰው በቤተክርስቲያኑ ጀርባ ቆሟል። በኃጢአቱና በጫንቃው ላይ ባለው ሸክም ምክንያት ዓይኖቹ በእንባ ፈዘዋል። በቤተክርስቲያኑ የኋላ ጥግ ላይ፣ በጉልበቱ ተንበርክኮ “ጌታ ሆይ፣ እባክህ፣ ኃጢአተኛ ነኝ፣ ማረኝ!” እያለ በተስፋ መቁረጥ ስሜት በሹክሹክታ እየፀለየ ነው። ሉቃስ 18:9-14ን ያንብቡ። ስለእነዚህ ሁለት ሰዎች ምን ያስባሉ? ኢየሱስ ምን አስቦ ነበር? እዚህ ላይ ለሁላችንም ምን ትምህርት እናገኛለን?



ራሳችንን ከፍ ማድረግ በጣም ቀላል ነው። አንዳንድ ጊዜ ለሌሎች ስኬቶቻችንን እና ምን ያህል መልካም ሰው እንደሆንን ማሳወቅ ለምደን ይሆናል። ነገር ግን እነዚህ ነገሮች፣ በራሳቸው፣ በሰማይ እይታ ላይ ምንም ለውጥ አያመጡም። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ከምናስበው ነገር ጋር ፈጽሞ የሚቃረን ነው፣ ምክንያቱም “ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል፣ ራሱንም የሚያዋርድ ከፍ ይላል” (ሉቃስ 18:14)። ኢየሱስም ዝቅተኛውን ቦታ እንድንይዝ እና አስተናጋጆች ከፈለጉ አስነስተውን ከፍ ወዳለው ስፍራ እንዲወስዱን ይመክረናል (ሉቃስ 14:8-10)። ኢየሱስ የሚያስተምረው መንግሥት እኛ ከምንጠብቀው ተቃራኒ ነው። “ክርስቶስ ሊያድነው የሚችለው ኃጢአተኛ መሆኑን የሚያውቀውን ብቻ ነው።”—ኤለን ጂ. ኋይት፣ የክርስቶስ ምሳሌያዊ ትምህርቶች፣ ገጽ 158። በመጀመሪያ ኃጢአተኝነታችንን እና ክርስቶስ እጅግ እንደሚያስፈልገን ስንገነዘብ፣ “በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው።” ብለን በልበ ሙሉነት ወደ እርሱ መምጣት እንችላለን (1 ዮሐንስ 1:9)። ወደ ክርስቶስ በቀረብን ቁጥር፣ ኃጢአተኛነታችንን እና ብቁ አለመሆናችንን እንገነዘባለን። “በአንድ መንገድ ብቻ ነው እውነተኛ የራስ እውቀት ማግኘት የሚቻለው።

እርሱም ክርስቶስን በትኩረት በማየት ነው። ሰዎች በጽድቃቸው ከፍ ከፍ የሚሉት እሱን ባለማወቃቸው ነው።”—የክርስቶስ ምሳሌያዊ ትምህርቶች፣ ገጽ 159። ስለዚህ፣ እግዚአብሔር ስለ ትዕቢተኞች ምን ያስባል? 1ኛ ጴጥሮስ 5:5 “እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ” ይላል። ከዚህ የበለጠ ግልጽ ሊሆን አይችልም። በሕይወትዎ የእግዚአብሔርን ጸጋ ለመጨረሻ ጊዜ የተለማመዱት መቼ ነው? (በእርግጥ፣ ይህንን ጸጋ በየቀኑ ልንለማመደው ይገባናል።) ለሌሎችም ጸጋ ማሳየት አለብን።

እግዚአብሔር በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ በኃይለኛ እጁ ስር ትሁት እንዲያደርጋችሁ አሁኑኑ በጸሎት ጊዜ አሳልፉ።

ሚያዝያ 6
Apr 14

ሙሴ፣ ትሑቱ አገልጋይ


የግብፅ ቤተ መንግሥት ታላላቅ አዳራሾች በብልጽግና፣ በደስታ እና በምቾት ይኩራሩ ነበር። “ ‘ሙሴም የግብፆችን ጥበብ ሁሉ ተማረ፥ በቃሉና በሥራውም የበረታ ሆነ።’” (የሐዋርያት ሥራ 7:22)። የስልጣን፣ የሀብት እና የታዋቂነት ህይወትን የራሱ ማድረግ ይችል ነበር፤ ሆኖም ሙሴ በጣም የተለየ ነገር መርጧል። “እንደ ታሪክ ጸሐፊ፣ ገጣሚ፣ ፈላስፋ፣ የሠራዊት ጄኔራል እና ሕግ አውጪ ለመሆን ቢፈልግ አቻ አልተገኘለትም ነበር። ሆኖም ግን ከፊቱ ባለው ዓለም፣ የሀብት፣ የታላቅነት እና የዝና ተስፋዎችን ውድቅ ለማድረግ የሞራል ጥንካሬ ነበረው፣ ‘ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ።’ ” ኤለን ጂ. ዋይት፣ የሐይማኖት አባቶች እና ነብያት፣ ገጽ 246 ዕብራውያን 11፡24–26 ሙሴ የተለየ መንገድ ለምን እንደ መረጠ እና ራሱን ለምን ዝቅ እንዳደረገ ምን ይነግረናል?



ኃያል እንደነበረ እና ከየት እንደመጣ ከግምት ውስጥ በማስገባት የሙሴ ትሕትና አስደናቂ ነው። ሆኖም፣ በግዴለሽ ኃጢአት (ዘጸ. 2፡12) እና በራስ መተማመን ምክንያት ብቃቱን አጣ። ሙሴ ተራሮች እንደ መማሪያ ክፍል እያገለገሉ እና ትዕቢቱም ተወግዶለት፣ ለ40 ዓመታት አንድን ሕዝብ ከባርነት ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመምራት ማወቅ የሚያስፈልገውን ሁሉ ከእግዚአብሔር ተማረ። ሙሴ ዘላለማዊው ላይ ስላተኮረ በግብፅ ውስጥ የተትረፈረፈ ሕይወት ሊሆን የሚችለው ኃይልና ሀብት ብዙም ትርጉም አልሰጠውም። እግዚአብሔር ለይቶ ጠራው፣ ሙሴም ተከተለው። ምናልባትም በዚህ ርዕስ ብርሃን በጣም ጉልህ በሆነ መልኩ፣ ዘኍልቍ 12:3 እንዲህ ይለናል፡ - “ሙሴ በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ነበር”። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከታላላቅ አባቶች አንዱ የሆነው ሙሴ በትሕትናው፣ በየዋህነቱ ይታወቅ ነበር። በሕይወቱ ውስጥ በእያንዳንዱ ትልቅ ክስተት ውስጥ ማለትም የቁጥቋጦው መንደድ ፣ የግብፅ መቅሰፍቶች፣ ቀይ ባሕርን መሻገር፣ ከሰማይ የወደቀው መና፣ ከእግዚአብሔር ጋር በቀጥታ መነጋገር፣ አሥርቱን ትእዛዛት መቀበል እና ዓለቱን ከመታ በኋላ የእግዚአብሔርን ቃል መስማት ከተከሰቱ በኋላ ትዕቢት አሳይቶ ቢሆን ኖሮ ሕይወቱና አመራሩ ምን ያህል የተለየ እንደሚሆን ያስቡት። ሕይወትዎን መለስ ብለው ያስቡ። አንድ ሰው ሊገልጽዎ ቢፈልግ፣ በዝርዝሩ ውስጥ “ትሑት” ወይም “ገር” ይካተቱ ይሆን? ከሆነ ለምን? ካልሆነስ ለምን? እውነቱ ግን በራሳችን ትሑት መሆን አንችልም። ኃጢአት የሕይወታችን አካል ነው፣ ኢየሱስ በጣም የሚያስፈልገን ለዚህ ነው። “የሱስ ይሻለናል” የሚለውን መዝሙር ያዳምጡ፤ እነዚህን ቃላት ከሙሴና ከእርስዎ ሕይወት ጋር በተያያዘ ያስቡባቸው።

ሚያዝያ 7
Apr 15

ታላቁ ጥፋት


የኢየሱስ ደቀ መዝሙር መሆንን ያስቡ። ከእርሱ ጋር ትጓዛላችሁ፣ ከእርሱ ጋር ትበላላችሁ፣ ከእርሱ አጠገብ ትተኛላችሁ፣ እና ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ህይወቶች፣ የእርስዎንም ጨምሮ፣ ሲለውጥ ከእርሱ መማርን ያስቡ። ሰዎች ወደ እርሱ ይጮኻሉ፣ እና እርሱ ከ12ቱ ወደ ራሱ ካቀረባቸው መካከል እንዲሆኑ መምረጡ ምን ያህል ልዩ እንደሆነ ይገነዘባሉ። ከዚያም እንዲህ ብለው ማሰብ ይጀምራሉ፡- በእርግጥ ከደቀ መዛሙርቱ ሁሉ የሚበልጠው ማነው? በሉቃስ 22፡24-27፣ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ታላቅነት ምን ማለት እንደሆነ ለተነሳው ክርክር የሰጠውን ምላሽ ያንብቡ። እዚህ ላይ የኢየሱስን መልእክት ልብ የያዘው አንድ አባባል ምንድን ነው?



ከኢየሱስ ጋር ይህን ሁሉ ጊዜ አብረው ከሆኑ በኋላ፣ ይህ ዓይነቱ መከራከሪያ በአእምሯቸው ውስጥ ሊመጣ የሚችል የመጨረሻው ነገር ነው ብላችሁ ታስቡ ይሆናል።

ግን የሆነው ያ አልነበረም። እነዚህ ሰዎች በጥሪያቸው ረክተው ከመቆየት ይልቅ እያንዳንዱ ሰው ከሌሎቹ የተሻለ እንደሆነ እስከሚያስብበት ደረጃ ድረስ በልባቸው ውስጥ ትዕቢት ተነሳ። እንደዚህ ያሉ ሀሳቦች አእምሯችንን እንዲቆጣጠሩ መፍቀድ ቀላል ነው። ነገር ግን “ለሰው ነፍስ እንደ ትዕቢትና እኔ ለራሴ እበቃለሁ የማለት ስሜት አደገኛና እግዚአብሔርን የሚያሳዝን ነገር የለም። ይህ ከኃጢአቶች ሁሉ እጅግ ተስፋ አስቆራጭ እና ለመፈወስ አስቸጋሪው ነው።” የክርስቶስ ምሳሌያዊ ትምህርቶች፣ ገጽ 154 ይህ ለእኛ በጣም ከባድ ነው። ትዕቢታችን እግዚአብሔርን ከማንኛውም ነገር በላይ ያሳዝነዋል፣ እና ብዙውን ጊዜ ስለማናስተውለው ለማሸነፍ አስቸጋሪ የሆነ ባህሪ ነው። እኔ ለራሴ እበቃለሁ በማለት ስሜታችን፤ ትዕቢታችን ስለ ነገሰብን ራሳችንን አለመገምገምን እንመርጣለን። ቆም ብለን ራሳችንን መመርመር እና እግዚአብሔር እውነተኛ ሁኔታችንን እንድንመለከት ዓይኖቻችንን እንዲከፍትልን መጠየቅ አለብን፣ ምክንያቱም ዛሬ ከእግዚአብሔር ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳናደርግ የሚያግደን ዋነኛው ምክንያት ትዕቢት ነው። እግዚአብሔር ብቻውን ከውስጥዎ ትዕቢትንና ራስ ወዳድነትን ማስወገድ እንደሚችል ከተገነዘቡ፣ ቆም ብለው ይህንን ጸሎት አሁኑኑ ይጸልዩ፡- “ጌታ ሆይ፣ ልቤን ውሰደው፤ እኔ ልሰጥህ አልችልምና። ንብረትህ ነው። ለአንተ ልይዘው አልችልምና ንፁህ አድርገህ ጠብቅልኝ። ደካማ፣ ክርስቶስን የማይመስል ማንነት ቢኖርብኝም አድነኝ። ፍቅርህ በነፍሴ ውስጥ ሊፈስ ወደሚችልበት ወደ ንፁህና ቅዱስ ድባብ አስገባኝ፣ አብጀኝም።” የክርስቶስ ምሳሌያዊ ትምህርቶች፣ ገጽ 159።

ሚያዝያ 8
Apr 16

እርሱን ተመልከቱ


ሉቃስ 22:27ን እንደገና ያንብቡ። እዚህ ጥቅስ ላይ ለሁሉም የክርስቶስ ተከታዮች ቁልፍ የሆነው መልእክት ምንድን ነው?



ደቀ መዛሙርቱ የበላይ ለመሆን ካላቸው ፍላጎት እና ከጎናቸው ካለው ሰው የተሻሉ እንደሆኑ ካመኑበት እምነት በተቃራኒ፣ የትሕትና የመጨረሻ ምሳሌ የሆነውን ኢየሱስን እናገኘዋለን። ኢየሱስ፣ “እኔ ግን በመካከላችሁ እንደ አገልጋይ ነኝ” (ሉቃስ 22:27) ብሎ ተናገረ። ኢየሱስ፣ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ሆነው ሕዝቡን ስላየና ስለራራላቸው በዙሪያው ላሉት ችግረኞች በየቀኑ የሚያስፈልጋቸውን ይሰጣቸው ነበር። ምንም እንኳን ጥቂቶች ይህንን ቀላል እውነት ቢገነዘቡም የሰው ልጅ በሕይወቱ ውስጥ ከማንኛውም ነገር በላይ እርሱ እንደሚያስፈልገው ያውቅ ነበር። ሰማይን ትቶ ለመሞት የመጣው ኢየሱስ ሰዎች የጸጋውን ተግባር እንዲረዱና ከእርሱ ጋር ግንኙነት እንዲፈጥሩ፣ ላቀረበላቸውም ግብዣ መልካም ምላሽ እንደሚሰጡ ተስፋ በማድረግ ነበር። ፊልጵስዩስ 2፡3-8ን ያንብቡ። ይህ በመስቀሉ ብርሃን እንዴት መኖር እንዳለብን ምን ይነግረናል?



ኢየሱስ ሁሉንም ነገር አድርጓል። ሁሉንም ነገር ተሸክሟል። በእውነት እና ንፁህ በሆነ መንገድ እርሱን ለማየት ጊዜ ወስደን ቆም ብለን ስናይ፣ ርኩሰታችንን፣ ቆሻሻችንን እና ዛሬ በሕይወታችን ውስጥ እርሱ ምን ያክል እንደሚያስፈልገን እንገነዘባለን። ወደ እርሱ ስንመለከት፣ ሌላው ነገር ሁሉ (በተለይም እኛነታችን እና የራሳችን ታላቅነት) ሙሉ በሙሉ ዋጋ ቢስ ይሆናል። የኢየሱስ ማንነት፣ ያደረገው እና ለፍጥረቱ ያለው ፍቅር ዋና ጉዳያችን ይሆናል። እርሱን ስንመለከት እኔነት በእርግጠኝነት ይጠፋል። ኢየሱስ። እንዴት ያለ ውብ፣ ኃያል ስም ነው። የትሕትና ዋናው ምሳሌ ነው። ክፍት ልባችን ስለ እርሱ ሲማር፣ ለእኛ ያደረገውን ስንረዳ፣ እና የሕይወት ቃሎቹ ወደ አእምሯችን እንዲገቡ ስንፈቅድ፣ ምን ያህል ትዕቢተኛና ጎስቋላ እንደሆንን እንገነዘባለን። ከእርሱ ጋር የኖሩትና የተማሩት የራሱ ደቀ መዛሙርት ከትዕቢት ጋር ከታገሉ፣ የተለየን ነን ብለን ራሳችንን ማታለል አንችልም።

በዋናነት፣ ከኢየሱስ ጋር ባለን ግንኙነት ውስጥ ማደግ የምንችለው ትሑት ስንሆን ብቻ ነው። አሁን ከእርሱ ጋር ተጨማሪ ጊዜ ያሳልፉ። መጽሐፍ ቅዱስዎን፣ ብዕርዎን፣ ማስታወሻዎን ወይም ወረቀትዎን ይውሰዱና ጸጥ ያለ ቦታ ይፈልጉ - ከቤት ውጭም ቢሆን። እግዚአብሔር ልብዎን ትሁት እንዲያደርገውና እንዲናገርዎ ይጋብዙት። መዝሙር 138ን ቃል በቃል ይፃፉ። ሲጽፉ ሳለ በተለይ ለእርስዎ የተለየ ትርጉም የሚሰጡዎት የትኞቹ ቃላት ናቸው?

ሚያዝያ 9
Apr 17


ተጨማሪ ሀሳብ


“ወደ ኢየሱስ በቀረብንና የባህሪውን ንጽሕና በግልፅ ባወቅን ቁጥር የኃጢአትን ክፉነት በግልጽ እንገነዘባለን፤ ራሳችንን ከፍ ከፍ የማድረግ ፍላጎታችን ይቀንሳል። ሰማይ እንደ ቅዱሳን የሚቆጥራቸው ሰዎች የራሳቸውን መልካምነት ለማሳየት የሚፈልጉት አይደሉም።” የክርስቶስ ምሳሌያዊ ትምህርቶች፣ ገጽ 160 “ከክብር በፊት ትሕትና ነው። በሰዎች ፊት ከፍ ያለ ቦታ ለመያዝ፣ ሰማይ እንደ መጥምቁ ዮሐንስ በእግዚአብሔር ፊት ዝቅ ያለ ቦታ የሚይዝ ሠራተኛን ይመርጣል። በጣም እንደ ልጅ ትሁት የሆነው ደቀ መዝሙር ለእግዚአብሔር ሥራ ውጤታማው ነው። ሰማያዊ አካላት ራሳቸውን ከፍ ከፍ ለማድረግ ከሚተጉት ጋር ሳይሆን ነፍሳትን ለማዳን ከሚፈልጉት ጋር ይተባበራሉ። . . . “ሰዎች ለእግዚአብሔር ታላቅ ዕቅድ ስኬት አስፈላጊ እንደሆኑ ተሰምቷቸው ራሳቸውን ከፍ ከፍ ሲያደርጉ፣ ጌታ ወደ ጎን እንዲቀሩ ያደርጋቸዋል። . . . “ለኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ስለ መንግሥቱ ተፈጥሮ መማር ብቻ በቂ አልነበረም።

የሚያስፈልጋቸው ነገር ከመሠረታዊ መርሆዎቹ ጋር እንዲስማሙ የሚያደርግ የልብ ለውጥ ነበር። ትህትና፣ ራስን መርሳት እና የትንሽ ልጅ የመተማመን ፍቅር ሰማይ የሚያደንቃቸው ባህሪያት ናቸው። እነዚህ የእውነተኛ ታላቅነት ባህሪያት ናቸው። . . . “ቅን፣ የተጸጸተች ነፍስ በእግዚአብሔር ፊት ውድ ናት። በደረጃቸው፣ በሀብታቸው፣ በአእምሮአቸው ታላቅነት ሳይሆን፣ ከክርስቶስ ጋር ባላቸው አንድነት ምክንያት የራሱን ማኅተም በሰዎች ላይ ያስቀምጣል።”—ኤለን ጂ. ኋይት፣ የዘመናት ምኞት፣ ገጽ 436-437።


የመወያያ ጥያቄዎች




1. የሚከተሉት ክፍሎች ስለ ትዕቢትና ትሕትና ምን ተጨማሪ ግንዛቤዎችን ይሰጣሉ? ማቴዎስ 23:12፤ መዝሙር 25:9፤ መዝሙር 149:4፤ እና ያዕቆብ 4:6፣10።

2. በሐቀኝነት ያስቡ፡- ለመጨረሻ ጊዜ “ስለ ራስዎ መልካምነት” የተናገሩት መቼ ነው? ይህ ከእግዚአብሔር ወይም ከነገሯቸው ሰዎች ጋር ባለዎት ግንኙነት ላይ ተፅዕኖ ያሳደረው እንዴት ነው?

3. ከእርሱ ጋር ያለዎትን ጉዞ ለማጠናከር በእግዚአብሔር ፊት ራስዎን ለማዋረድ በሕይወትዎ ውስጥ ምን መለወጥ ያስፈልግዎ ይሆን? ማጠቃለያ፡- ትዕቢት ከእግዚአብሔር ጋር ባለዎት ግንኙነት ውስጥ ለማደግ እንቅፋት ከሚሆኑት ታላላቅ ነገሮች መካከል አንዱ ሊሆን ይችላል። ለራሴ በቂ ነኝ የሚል ስሜት ከተሰማን እና ይህ ግንኙነት እንደሚያስፈልገን የማንገነዘብ ከሆንን አንፈልገውም።

በተቃራኒው፣ ኢየሱስ በምድር ላይ እጅግ ትሑት የነበረ ሲሆን ከእግዚአብሔር ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዴት እንደሚኖር ያሳየን ፍጹሙ ምሳሌያችን ነው።




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL