የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ማሳደግ



2ኛ ሩብ ዓመት 2026


ሚያዝያ 10 - 16

4ኛ ትምህርት

Apr 18 - 24




የመጽሐፍ ቅዱስ ሚና



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሳምንት ጥናት ያንብቡ፡ ሰቆ. 3:22-23፣ 2ኛ ጢሞ. 3:15-17፣ ዮሐንስ 17:17፣ ኤፌ. 1:13፣ መዝ. 119:11፣ 1ኛ ቆሮ. 2:14።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፥ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፥ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል፤” (ዕብራውያን 4:12)።

መጽሐፍ ቅዱስ! ቢያንስ አንድ ምናልባትም ብዙ መጽሐፍ ቅዱሶች እንደሚኖርዎት ጥርጥር የለውም። ከታሪክ አንፃር ይህ ውድ መጽሐፍ በድብቅ በእጅ ተፅፏል፤ በድብቅ ተጥሎ ታግዷል። በዓለም ላይ፣ በማንኛውም ቋንቋ፣ በከፍተኛ ቁጥር የታተመ እና ከጥንታዊዎቹ አንዱ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ተጠብቆ እንዲተላለፍ አንዳንዶች ሞተዋል። መጽሐፍ ቅዱስ በሕይወትዎ ውስጥ ያለው ቦታ ምንድነው? ያነቡታል ወይስ ከአልጋዎ አጠገብ ተቀምጧል? ወይስ በመደርደሪያ ላይ አቧራ እየጠጣ ነው? የእግዚአብሔርን ቃል በእውነት ለማጥናት ጊዜ ለማግኘት ስራ በዝቶ ነው ወይስ ገጾቹን ለመክፈት በጣም ድካም ይሰማዎታል? የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና ኃይለኛ ነው፣ እናም እግዚአብሔር ለልብዎ እንዲናገር፣ እንዲያበረታታዎ፣ እንዲገዳደርዎና እንዲለውጥዎ እንዲሁም መመሪያና ተስፋ እንዲሰጥዎ እየጠራዎ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የትምህርት መጽሐፍ ወይም የጥንት ታሪኮች ስብስብ ብቻ አይደለም።

በምትኩ፣ የአጽናፈ ዓለሙ ፈጣሪ ወደ እርሱ እንዴት ሊያቀርበን እንደሚፈልግ የሚያሳይ ውብና ጥልቅ ዘገባ ነው። ከእግዚአብሔር ጋር ባለዎት ግንኙነት የማደግ ፍላጎት ካለዎት፣ ማድረግ የሚችሉት የተሻለው ነገር በየቀኑ ከእርሱ ጋር ጥራት ያለው ጊዜ ማሳለፍ፣ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን ቃሉን ማንበብ እና ለመታዘዝ ፈቃድዎን ማስገዛት ነው። *ለሚያዝያ 17 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያጥኑ።

ሚያዝያ 11
Apr 19

እጅግ ኃይለኛው መሣሪያ


መጽሐፍ ቅዱስ ለምን በጣም ጠቃሚ እንደሆነ እና በግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ውስጥ እንዴት በጥልቀት መቆፈር እንደምንችል ከመዳሰሳችን በፊት፣ አንድ ነገር መረዳት አለብን፤ ሰይጣን በእኛ ላይ ሊያደርስ ከሚችላቸው በጣም ጉልህ ጥቃቶች አንዱ በቃሉ ከእግዚአብሔር ጋር ጊዜ እንዳናሳልፍ ማድረግ ነው። ሰዎችን በንግድ፣ በግዴለሽነት፣ በድካም ወይም በጥርጣሬ ከመጽሐፍ ቅዱሳቸው ማራቅ ቁጥር አንድ ስትራቴጂው ነው።

በቃሉ ውስጥ ከእግዚአብሔር ጋር ጊዜ ስናሳልፍ ሕይወታችን እንደሚታደስ እና የመንፈስ ምግብ እንደምናገኝ ስለሚያውቅ ይህንን ለመከላከል ሁሉንም ነገር ያደርጋል! “ሰይጣን [ሰዎች] የመጽሐፍ ቅዱስን እውቀት እንዳያገኙ ለመከላከል የሚቻለውን ሁሉ ይጠቀማል፤ ምክንያቱም ግልጽ ንግግሮቹ ማታለያዎቹን ይገልጣሉ” ተብለናል። — ኤለን ጂ. ኋይት፣ ታላቁ ተጋድሎ፣ ገጽ 593። ሰይጣን የእግዚአብሔር ኃይለኛ ቃል እርሱን ኃይል አልባ እንደሚያደርገው ያውቃል። ጸሎትና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሰው ልጅ በሰይጣን ላይ ሊጠቀምባቸው ከሚችላቸው እጅግ ኃይለኛ መሳሪያዎች መካከል መሆናቸውን ሰይጣን ስለሚያውቅ (ኤፌ. 6:17-18፤ ዕብ. 4:12) ከማንበብና ከመጸለይ እንድንቆጠብ የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል። የእግዚአብሔር ቃላት ኃይለኛ እንደሆኑና ይህን ዓለም ወደ መኖር እንዲመጣ እንዳደረጉ ብቻ ሳይሆን ሙታንን ማስነሳት እንደሚችሉ (ዮሐንስ 11:41-44) እና ለማሸነፍ ኃይል ሊሰጡን እንደሚችሉ (ማቴ. 4:1-11) ያውቃል። የእግዚአብሔርን ሕዝብ ከመጽሐፍ ቅዱሳቸው በማራቅ፣ ሰይጣን ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነትም ይጎዳል። ትዳራችን ውጥረት ውስጥ ይገባል፣ በልጆቻችን ላይ እንጮሃለን፣ እና ከጓደኞቻችን ወይም ከሥራ ባልደረቦቻችን ጋር ትዕግስት የለንም። ሕይወት በጣም ቢዚ ትሆናለች፤ ምንም የማምለጫ መንገድ ሳይኖር ውጥረትና ሸክም ይሰማናል። እና በሚገርም ሁኔታ፣ ምን እየተከሰተ እንዳለ ለመረዳት በአብዛኛው በቂ ጊዜ ወስደን እረፍት አናደርግም። ከእግዚአብሔር ጋር ቅርብ እንደሆንን እናስብ ይሆናል፣ ነገር ግን እውነቱ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ሳንከፍት ቀናትና ሳምንታት ሲያልፉ፣ በየቀኑ እየደከምን እንሄዳለን። ከእግዚአብሔር ጋር አንዴ ከፍ አንዴ ዝቅ የሚል ወጥነት የሌለው ግንኙነት ቢኖረንም እንኳ፣ ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:22-23 እንደሚነግረን እግዚአብሔር በሚያስደንቅ ሁኔታ ፅኑ ነው (አይለዋወጥም) ። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ምን ያስተውላሉ? እና ከሰብዓዊ ተፈጥሮአችን ጋር እንዴት ይነፃፀራሉ?



ከመውደቁ በፊት የሚጋርድ ኪሩብ የነበረው ሉሲፈር (ሕዝ. 28:14-17) የእግዚአብሔርን ቃል ከዚያ በፊት ሰምቶ ስለሚያውቅ አስደናቂ ኃይላቸውን ያውቅ ነበር። አሁን ይህንን እውነት ይጠላል፤ ስለዚህ የእግዚአብሔርን ቃል መስማት እና ወደ ዕለታዊ ሕይወታችን ማምጣት ሳንመርጥ ስንቀር አእምሯችንና ልባችን ለምን እንደሚደነዝዝ ግልጽ ነው። የአምልኮ ሕይወትዎ ምን ያህል ወጥነት አለው? መልስዎ አንዳንድ ለውጦችን ስለማድረግ ምን ይነግርዎታል?

ሚያዝያ 12
Apr 20

ባለሥልጣኑ ቅዱስ መጽሐፍ


ባለሥልጣኑ ቅዱስ መጽሐፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን እና ተግባር በገጾቹ ውስጥ በግልጽ ተቀምጧል። 2ኛ ጢሞቴዎስ 3:15-17ን ያንብቡ እና ይፃፉት። እነዚህ ጥቅሶች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ተግባር የሚነግሩዎትን ልብ ይበሉ። የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትን በተመለከተ፣ መጽሐፍ ቅዱስ በአብዛኛው ከእግዚአብሔር ጋር አብረው የማይሄዱትን ዓላማዎቻችንን ወይም አመለካከቶቻችንን እንዲደግፍ መጠበቅ የለብንም። ለምሳሌ፣ “ዓይናችንን ጨፍነን አንድ ጥቅስ ማውጣትና መጠቆም” የለብንም፣ ምክንያቱም እግዚአብሔር በቃሉ በኩል ከእኛ ጋር ሊነጋገር የሚፈልገው በዚህ መንገድ አይደለም። እግዚአብሔር በገመድ ላይ የተንጠለጠለ እና ፍላጎታችንንና ፈቃዳችንን ለማሟላት ብቻ የሚጠብቅ አሻንጉሊት አይደለም። መንገዶቹና ሐሳቦቹ ከእኛ በጣም ከፍ ያሉ (ኢሳ. 55:9) ስለሆኑ ለእኛ የሚናገራቸውን ቃላት ለመቆጣጠር ፈጽሞ መሞከር የለብንም። ለእኛ ምቾት የሚሰጡንን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ብቻ መምረጥም የለብንም። ቀላል የሆኑትን፣ የተለመዱ ምንባቦችን ከማንበብ እና የሚገዳደሩንን ወይም ፈታኝ የሆኑትን ከመተው ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ሙሉ ጥቅል አድርገን ማየት ይኖርብናል።

እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ እንዲናገር በእውነት ከፈለግን፣ እርሱ መስማት የሚያስፈልገንን እንደሚገልጥልን በማመን፣ ጤናማ ዘዴዎችንም በመጠቀም፣ መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ሙሉ ጥቅል አድርገን በመውሰድ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት አለብን። እንዲሁም፣ ኢየሱስ ራሱ፡- “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ።” (ማቴ. 22:37) በማለት ተናግሯል። ይህም ማለት እግዚአብሔር አእምሯችንን ችላ እንድንል አይፈልግም፤ ይልቁንም በከፊልም ቢሆን በቃሉ በኩል የተገለጹትን ሰፊ እውቀትና መረዳቶች ሊገልፅልን አእምሯችንን መድረስ ይፈልጋል። ኢየሱስ ከሰዎች ጋር ካደረጋቸው ብዙ ውይይቶች በተጨማሪ እግዚአብሔር እንደ ሄኖክ፣ አብርሃም፣ ሙሴ እና ኢዮብ ካሉ ሰዎች ጋር ውይይት ያደረገባቸውን ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትረካዎች ማንበብ እንችላለን። እግዚአብሔር የሰውን ምክንያታዊነት ችላ አይለውም፤ ነገር ግን መዳናችንን “ሲፈጽም” ለቃሉና ለጥበቡ ራሳችንን እንድናስረክብ ይጋብዘናል። የሰው ልጅ አስተሳሰብ ግን አሁንም የሰው ልጅ ነው-የሚሳሳት እና የሚታለል። ፈጽሞ የማይሳሳት አይደለም። የሰው ልጅ አስተሳሰብ ራስን ከእግዚአብሔር ጋር እኩል ወይም ከፍ አድርጎ የሚያስቀምጥ እና ነገሮችን በራሱ ለመፍታት በማሰብ እግዚአብሔርን ወደ ጎን ሊገፋ የሚችል ነው። ሰዎች ሁሉንም ነገር ከዚህ በፊት እንደሰሙት እና አዲስ ነገር እንደሌለ በማሰብ በትዕቢትና በጥርጣሬ መንፈስ መጽሐፍ ቅዱስን መቅረብ ይችላሉ። አስፈላጊ የሆንን፣ በራስ መተማመን ያለን፣ ራሳችንን የቻልን እና ምንም የማያስፈልገን አይነት ስሜት ሲሰማን ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ችላ ብለን በራሳችን ውስን እውቀት እና የተሳሳተ አስተሳሰብ ላይ መታመን እንጀምራለን።

ሚያዝያ 13
Apr 21

የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት


በ1960ዎቹ የነበሩ አንዳንድ ሊበራል(ልል) የስነ መለኮት ባለሙያዎች እግዚአብሔርን ከሥነ መለኮት መስክ ውጭ ለመግለፅ ይሞክሩ ነበር። በ2017፣ የታይም መጽሔት የሽፋን ታሪክ “እውነት ሞቷልን?” የሚል ርዕስ ይዞ ወጣ። ይህ አዝማሚያ የዛሬውን የኅብረተሰባችንን አቋም ስለሚያሳይ አስደናቂ ነው። “እውነት” የሚባለው ነገር ራሱ እየጠፋ ከመምጣቱ የተነሳ ማንም ሰው እውነት ምን እንደሆነ አያውቅም። ብዙሃን በሚከተሉት ባህል መሠረት፣ የማይለወጥ እና የጊዜን ፈተና የሚቋቋም አስተማማኝ መለኪያ፣ መሠረትም የለም። ከዚህ በተቃራኒ ኢየሱስ “እኔ… እውነት ነኝ” ብሏል (ዮሐንስ 14:6)። ቃሉ ክርስቶስ ፍፁም ንፁህ የሆነው እውነት ስለ መሆኑ ይመሰክርልናል። የሚከተሉትን ሦስት ጥቅሶች ቀስ ብለው ያንብቡ፣ ከዚያም ለሁለተኛ ጊዜ እንደገና ያንብቡዋቸው። ስለ እነዚህ መልእክቶች ምን ያስተውላሉ? ዮሐንስ 17:17



ምሳሌ 30:5-6



መዝ. 12:6



መጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊውን እውነት ማለትም፣ ኢየሱስ ራሱ እንደማይለወጥ ይናገራል (ዕብ. 13:8)። በተመሳሳዩ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል ስናነብ፣ ስለ እግዚአብሔር እና ስለ እውነት ያለን ግንዛቤ ያድጋል። “ገና ያልተገኙ ነገር ግን በቅንነት በሚቆፍር ሰው የሚገኙ የእውነት ማዕድናት አሉ።”—ኤለን ጂ. ኋይት፣ የቤተ ክርስቲያን ምክሮች፣ ጥራዝ 5፣ ገጽ 704። ኤለን ጂ. ኋይት “እውነት” ስትል እውነትን በቃሉ በኩል በእግዚአብሔር የተገለጠ መሆኑን ትጠቅሳለች።

መጽሐፍ ቅዱስ ቀደም ብለው የታወቁትን እውነቶች ፈጽሞ ስለማይቃረን ይልቁንም በእነርሱ ላይ ስለሚገነባ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጨማሪ ብርሃን መፈለግ እንችላለን። 1ኛ ተሰሎንቄ 2:13፣ መዝሙር 33:4-5፣ እና ኤፌሶን 1:13ን ያንብቡ። እነዚህ ቦታዎች ላይ ያለው ዋና መልእክት ምንድን ነው?



በመጨረሻ፣ እውነቱን የምንረዳበት መሠረታዊ ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ እና መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ መሆን አለበት። ሌሎች ምንጮች ሁሉ በእግዚአብሔር ቃል መሞከር እና መፈተን አለባቸው።

“ምክንያታዊነት” ብለን የምንጠራው እንኳን በእግዚአብሔር ቃል መፈተን አለበት።

አንዳንድ ሰዎች እውነት የለም ብለው መከራከር ይፈልጋሉ። ይህ አባባል ራሱን የሚቃረን የሆነው ለምንድን ነው? ማለትም፣ እውነት የለም የሚለውን አባባል ማቅረብ እውነትን ለማወጅ የሚደረግ ሙከራ እና የራሱን ስህተትነት የሚያረጋግጥ የሆነው ለምንድነው?

ሚያዝያ 14
Apr 22

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ራሱ የተናገራቸው


ትልቅ ውሳኔ መወሰን ቢኖርብዎ፣ የግንኙነት ችግር ወይም ፈተና ሲያጋጥምዎ መጽሐፍ ቅዱስዎን ቢከፍቱ በቤትዎ ውስጥ ምን ሊለወጥ ይችል ይሆን? የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ሰዎች ዓለምን የሚመለከቱበት እና ለመኖር የሚመርጡበት መነጽር ቢሆኑ በሥራ ቦታዎ ወይም በቤተ ክርስቲያንዎ ውስጥ ምን ለውጥ ሊመጣ ይችላል?



የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆኑ ያውቁ ነበር። እንደ እነዚህ ቃላት ሌላ መጽሐፍ ሊናገረን አይችልም። ቃላቶቹ በመጽሐፍ ቅዱስዎ ውስጥ ባሉ ገፆች ውስጥ ሊቀመጡ ይችላሉ፡ ነገር ግን በልባችን ውስጥ ማስቀመጥ የምንችለው እንዴት ነው? በመዝሙር 119:11 ላይ የዳዊት ምክር ምንድን ነው፣ እና እንዴት መከተል እንችላለን? (ዕብ. 4:12ን ይመልከቱ) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ራሱ ከሚናገራቸው መግለጫዎች አንዱ በዕብራውያን 4:12 ውስጥ ይገኛል። እንደ ባለ ሁለት አፍ ሰይፍ ኃይለኛ እና ስለታም ነው፣ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ የሰው መሳሪያዎች ለሰው ነፍስ ማድረግ የማይችሉትን ሊያደርግ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ራሱን ሕያው እንደሆነ ይገልጻል።

ከሺህዎች ዓመታት በፊት መጻፉን ከግምት ውስጥ በማስገባት ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል ብላችሁ ትጠይቁ ይሆናል፣ ነገር ግን ኢየሱስ “ ‘የምነግራችሁ ቃል መንፈስ ነው፣ ሕይወትም ነው’” ብሏል (ዮሐንስ 6:63)። ልባችሁ ከተሰበረ ወይም ሕይወታችሁ እየተበላሸ ከሆነ፣ እግዚአብሔር ቃሉን ለእናንተ ሊናገርና ነገሮችን ሊለውጥ ይችላል። ብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔርን ቃል በጣም ንቁ እንጂ ፈጽሞ የማይንቀሳቀስ እንዳልሆነ ይገልጻል (ኢሳ. 55:11ን ይመልከቱ)። ዳዊት የእግዚአብሔር ቃል በሕይወቱ ላይ ስላለው ተጽእኖ ሲያሰላስል፣ “ይህ በመከራዬ መጽናኛዬ ነው፣ ቃልህ ሕይወት ሰጥቶኛልና” ሲል ጽፏል (መዝ. 119:50)። ምናልባት በሕይወትዎ ውስጥ በሆነ ወቅት ከባድ ረሃብ አጋጥምዎት ይሆናል፣ ወይም ምናልባት ጾመው ወይም ልዩ አመጋገብን እየተከተሉ ይሆናል። ከረሀብ በኋላ ምግብ ጥሩ ጣዕም ይኖረዋል አይደል? በመንፈሳዊ መልኩ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ለነፍሳችን ምግብ ነው። መንፈስዎ ባዶና የተራበ ከሆነ ሕያው የሆነውን ቃል ይክፈቱ። ኤርምያስ 15:16፣ 1ኛ ጴጥሮስ 2:2 እና ማቴዎስ 4:4ን ያንብቡ። የእግዚአብሔር ቃላት አእምሮና ልብን ደስ ያሰኛሉ፡ እኛም ስናነባቸው፣ ቃል እንደገባልን ይሞሉናል ይደግፉናልም። በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ያሉት ቃላት የመጡት ከእግዚአብሔር ነው። እግዚአብሔር በተለይ ለእኛና እርሱን ለሚፈልጉት ሁሉ ልኮላቸዋል።

በጸሎትና ክፍት በሆነ ልብ ስናነባቸው፣ እነዚህ ቃላት አይባክኑም። መጽሐፍ ቅዱስ በአሁኑ ጊዜ በሕይወትዎ ውስጥ ምን ዓይነት ትግሎችን እያከመ ይሆን? እኔነት ቃሉ የሚነግርዎትን ከመከተል እንዳይከለክልዎት መፍቀድ የሌለብዎ ለምንድነው?

ሚያዝያ 15
Apr 23

የልብ ሁኔታ


ከእግዚአብሔር ቃል መመሪያ የመቀበል ችሎታችን (ኢዮብ 22:22) በአብዛኛው የሚመሰረተው ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ስንቀርብ በሚኖረን የልብ ዝግጅት(ሁኔታ) ላይ ነው።

1ኛ ቆሮንቶስ 2:14 ይህንን የሚያብራራው እንዴት ነው?



በመንፈስ መመርመር ማለት መንፈሳዊ ማስተዋልና ግንዛቤ ማግኘት ማለት ነው።

ስለዚህ፣ መንፈሳዊ ክፍት አስተሳሰብ ያለው ሰው መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ረገድ መንፈሳዊ ዝግ አስተሳሰብ ካለው(ለመቀበል ዝግጁ ያልሆነ) ሰው ይልቅ በጣም የተሻለ በረከት ይቀበላል። መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ሞኝነት ነው ብሎ የሚያስብ ሰው በገጾቹ ውስጥ እውነትን አይፈልግም።

ስለዚህ፣ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለን አመለካከትም ሆነ መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ ያለን የልብ ዝግጅት ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት እንዲያድግ በጣም አስፈላጊ ነው። ጳውሎስ ይህንን በ1ኛ ተሰሎንቄ 2:13 ላይ የሚያብራራው እንዴት ነው?



በምናምንበት ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል በእኛ ውስጥ ይሠራል። መጽሐፍ ቅዱሳችንን ስንከፍት እና እግዚአብሔር በገጾቹ ላይ ባሉት ቃላት የሚነግረን ነገር እንዳለው ስናምን፣ በእርግጥ ይናገረናል፤ በሕይወታችን ውስጥም ይሠራል። ነገር ግን አብዛኛው ነገር የሚወሰነው በእምነታችን እና በልባችን ዝግጁነት ላይ ነው። መልካም ዜናው እምነታችን እንደ ሰናፍጭ ቅንጣት(ሉቃስ 17:6) እንኳን ትንሽ እንደሆነ ከተሰማን እግዚአብሔር እንዲያድግ ሊረዳን ይችላል (ማርቆስ 9:24)። ከመጽሐፍ ቅዱስ ዋና ዓላማዎች አንዱ ከእግዚአብሔር ጋር ስላለን ግንኙነት መግለጥ እና እንዴት ማጠናከር እንዳለብን መምከር ነው። ልባችን ለመንፈስ ቅዱስ ክፍት ከሆነና ቃሉን በትህትና ከቀረብን፣ ሁልጊዜም ለውጥ ይኖራል፣ እንዲህ ዓይነቱ ለውጥ እና እድገት ግን ብዙውን ጊዜ ቀስ በቀስ የሚጨምር ስለሆነ ይህንን ወዲያውኑ ላናውቅ እንችላለን። ነገር ግን ግድየለሽነታችንንና ኃጢአታችንን አጥብቀን ከያዝን እና ለመለወጥ ፈቃደኛ ካልሆንን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ብዙም ጥቅም ላይኖረው ይችላል። መንፈስ ቅዱስ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንድንቀርብ ያነሳሳናል። ወደ ፊት መራመድ እንፈልጋለን? ከሆነ “መዳን የሚገኝበትን ጥበብ” እናገኛለን (2ኛ ጢሞ. 3:15)፣ እና ፈጽሞ ያላሰብናቸውን ነገሮች እናያለን። ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ስቀርብ የልቤ እና የአዕምሮዬ ሁኔታ ምን ይመስላል? ወደ መጽሐፍ ቅዱስ የምቀርበው ሀሳቦቼ ትክክለኛ እንደሆኑ ለማስረገጥ ነው ወይስ እግዚአብሔር ዛሬ ሊነግረኝ የሚፈልገውን ለመስማት እንደ ልጅ ክፍት አእምሮ ይዤ ነው የምቀርበው? ይህ መልስ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድነው?

ሚያዝያ 16
Apr 24


ተጨማሪ ሀሳብ


ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ የተናገሯቸውን ቃላት ወደ ኋላ ሄደው ያስታውሱ፣ እንዴት ይገመግሟቸዋል? አፍቃሪ፣ ደግ፣ ደስተኛ፣ የሚያነቃቁ ነበሩ? ወይስ የተበሳጩ፣ የደከሙ፣ የተጨነቁ፣ የተናደዱ፣ ሐሜተኞችና ተንኮለኞች? መጽሐፍ ቅዱስ “በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ይናገራል” ይላል (ማቴ. 12:34)። በልባችን ውስጥ ቆሻሻ ሲኖር፣ በቃላቶቻችን ውስጥ ይወጣል። ሁላችንም የተስፋ መቁረጥ፣ የድካም ወይም የጭንቀት ስሜት ተሰምቶን ያውቃል፤ እናም ያ ሁኔታ ከአፋችን የሚወጣውን ነገር ይለውጣል (በአብዛኛው ካለፈ በኋላ እንጸጸትባቸዋለን)። በተቃራኒው፣ ልባችን በአንድ ሰው ፍቅር ሲሞላ፣ በቃሎቻችን ውስጥ ይፈሳል። በተመሳሳይ መንገድ፣ የእግዚአብሔር ቃል ስለ እርሱ ልብ እና ለእኛ ስላለው ኃሳብ ይናገራል። ፣ በቀጥታ ከእግዚአብሔር ልብ የተወሰዱት እነዚህ ቃላት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በእጃችን መሆናቸው አስደናቂ ነው። የእግዚአብሔር ቃላት በታሪክ ውስጥ የያዙትን ኃይል ማየት በእውነትም አስደናቂ ነው። “መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ጥሩ የሥነ ምግባር መመሪያ መጽሐፍ አድርጎ መያዝ፣ ከዘመኑ መንፈስ እና በዓለም ላይ ካለን አቋም ጋር በሚስማማ መልኩ መከተል አንድ ነገር ነው፤ በትክክል እንደ ሆነው ማለትም እንደ ሕያው የእግዚአብሔር ቃል፣ ሕይወታችን እንደሆነው ቃል፣ ድርጊታችንን፣ ቃላቶቻችንን እና ሀሳባችንን እንደሚቀርጽ ቃል አድርጎ መመልከት ደግሞ ሌላ ነገር ነው። የእግዚአብሔርን ቃል ከዚህ ያነሰ ነገር አድርጎ መያዝ ደግሞ ቃሉን አለመቀበል ነው።

እናም ይህንን እንደሚያምኑ በሚናገሩ ሰዎች የሚደረገው ቃሉን መግፋት በወጣቶች ውስጥ የጥርጣሬ እና የክህደት መንስኤዎች ከሆኑት መካከል ዋነኛው ነው።”— ኤለን ጂ. ኋይት፣ ስነ ትምህርት፣ ገጽ 260


የመወያያ ጥያቄዎች




1. ለእምነትዎ ያለዎት ምክንያቶች ምንድናቸው? ሲዘረዝሯቸው ምናልባት ከሚያስቡት በላይ ብዙ ይሆናሉ።

2. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እና ጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት መሠረት

እንደሆኑ እንዴት ማረጋገጥ እንችላለን? ያለ ጸሎት እና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዴት ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ሊኖረን ይችላል?

3. አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከር ከፈለገ፣ ከየትኛው

የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ማንበብ እንዲጀምር ይመክሩታል?

4. ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው ቃል ሁሉ መኖር የሚቻለው እንዴት ነው? (ዘዳግም 8:3)። ይህ በሕይወታችን ውስጥ ምን ሊመስል ይችላል?

5. የሚከተሉት ጥቅሶች ስለ እግዚአብሔር ቃል ምን ይነግሩናል? ዕብ. 11:3፤ መዝ. 33:6፤ ማቴ. 11:4-5፤ 1 ተሰ. 4:16፤ ኤፌ. 6:17፤ ያዕቆብ 1:21። ማጠቃለያ፡- መጽሐፍ ቅዱስ ሕያውና ኃይለኛ ነው፣ እናም ቃሉን ማንበብ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ለማሳደግ መሠረት ነው። ስለ እግዚአብሔር ድንቅ ባሕርይ እና በምድር ታሪክ ውስጥ ከሰው ልጅ ጋር ስላለው ግንኙነት የሚያስተምረን ብቻ ሳይሆን ዛሬም በትሕትና ስንቀርበው ለእያንዳንዳችን ይናገረናል።




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL