የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ማሳደግ



2ኛ ሩብ ዓመት 2026


ግንቦት 1 - 7

7ኛ ትምህርት

May 9 - 15




ተግባራዊ ፀሎት



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ 1 ነገስት 19:1-18 ፣ ማቴ። 6:5-8 ፣ ሉቃስ 11:2-4 ፣ ማቴ. 6:5-15 ፣ ዳን. 9:4-19 ፣ ሮሜ 8:26-27።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “የሕዝብ ማኅበር ሁላችሁ፥ በእርሱ ታመኑ፥ ልባችሁንም በፊቱ አፍስሱ፤ እግዚአብሔር ረዳታችን ነው።” መዝ. 62:8

የጸሎት ሕይወትዎ ምን ይመስላል? ምን ያህል ጊዜ ይጸልያሉ? ጉጉትዎስ ምን ያህል ነው? በየቀኑ ይጸልያሉ ወይስ በአደጋ ጊዜ ብቻ ነው የሚፀልዩት? በጸሎቶችዎ ሁልጊዜ የሚፈልጉትን ነገር ይጠይቃሉ ወይስ በጸሎቶችዎ እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ? እንዲሁም፣ ከመብላትዎ በፊት ጠዋት እና ምናልባትም በተጨናነቀው ቀንዎ መሃል ጸሎት ያቀርባሉ? ምናልባት መደበኛ የጸሎት ቡድን አባል ሆነው ወይም ሌት ተቀን መጸለይ ምን እንደሚመስል ተለማምደው ይሆናል። በሕይወትዎ ውስጥ ያለውን ሁሉ በሚቀይር ጸሎት አማካኝነት የእግዚአብሔርን ኃይል እና መገኘት ተለማምደው ይሆን? ጸሎት በእኛ (ቅርንጫፎቹ) እና በኢየሱስ (በወይኑ) መካከል ያለ የማያቋርጥ ግንኙነት ነው። “ማደግና ማበብ ካለብን፣ ከሕያው ወይን ያለማቋረጥ ጭማቂ እና ምግብ ማግኘት አለብን፤ ምክንያቱም ከወይኑ ተለይተን ምንም ጥንካሬ የለንም።”—ኤለን ጂ. ኋይት፣ ቀደምት ጽሑፎች፣ ገጽ 73። ይህ የዘላቂ እና ፅኑ ጸሎት በረከት ነው። እግዚአብሔር ይሰማናል፣ እና ሁልጊዜም በጊዜው እና ፍጹም በሆነው መንገዱ ይመልሳል - ምንም እንኳን ሁልጊዜ በምንጠብቀው መንገድ ባይሆንም። በዚህ ሳምንት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሌሎች የሚጸልዩ ግለሰቦችን የምንመለከት ስንሆን በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ጸሎትን ለማጠናከር ተግባራዊ መንገዶችን እናሰላስላለን። *ለግንቦት 8 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያጥኑ።

ግንቦት 2
May 10

ኤልያስ- በችግር ውስጥ መጸለይ


ታማኙ ኤልያስ በክፉ ዘመን ይኖር ነበር፣ ንጉሥ አክዓብም “ከእርሱ በፊት ከነበሩት የእስራኤል ነገሥታት ሁሉ ይልቅ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ለማስቆጣት” የበለጠ ባደረገበት ዘመን (1ኛ ነገሥት 16:33) ይኖር ነበር። በሕይወቱ ውስጥ እጅግ አስደናቂ ጊዜያት የመጡት በቀርሜሎስ ተራራ ላይ ከተደረገው ግጭት ጋር ተያይዞ ነው (1ኛ ነገሥት 18ን ይመልከቱ)። በዚህ አስደናቂ ታሪክ ጡዘት ላይ፣ አክዓብ እና መንግሥቱ እግዚአብሔር ጸሎትን እንደሚመልስ በገዛ ዓይናቸው ተመለከቱ። ይህ በእስራኤል ታሪክ ውስጥ የማይረሳ ጊዜ ነበር። እናም በዚህ ታሪክ ውስጥ የመጣው ድንገተኛ ለውጥ አስገራሚ በሆነ መንገድ የሚይዘን በዚህ ምክንያት ነው። 1ኛ ነገሥት 19:1-18ን ያንብቡ፣ በተለይም የኤልያስን ጸሎት እና እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስላለው ግንኙነት ያንብቡ። እዚህ ላይ ለኤልያስ መከፋት ዋናው ምክንያት ምንድን ነው? የእግዚአብሔር ምላሽ በቀርሜሎስ ተራራ ላይ ከተከሰተው የሚለየው እንዴት ነው?



በአንድ ቀን ውስጥ፣ እግዚአብሔር የኤልያስን ጸሎት ሁሉ ቢመልስም፣ የነቢዩ ስሜታዊ፣ አእምሯዊ እና አካላዊ ሁኔታ ብዙም ሳይቆይ ተለዋወጠ። ኤልያስ በዚያ ቀን ከእግዚአብሔር ጋር ታላቅ ድል ቢቀዳጅም፣ በደከመው ጊዜ የሞት ፍርሃት በእግዚአብሔር ላይ ያለውን እምነት እንዲያሸንፍ ፈቀደለት። በዚህ ታሪክ ውስጥ በጣም የሚያስደንቀው ነገር ኤልያስ ለተስፋ መቁረጥ ቢሸነፍም፣ እግዚአብሔር በርኅራኄና በእንክብካቤ ወደ እርሱ በመምጣት ምግብና ውሃ መስጠቱ ነው (1ኛ ነገሥት 19:5-6) - በዚህም ምግብ እስከ 40 ቀናትና 40 ሌሊት ድረስ ቆየ (1ኛ ነገሥት 19:8)። እግዚአብሔርም በመጨረሻ ራሱን ሲገልጥ፣ ከዚህ በፊት ከነበረው በጣም በተለየ መንገድ ነበር። አንዳንድ ጊዜ በሕይወታችን ውስጥ፣ እግዚአብሔር በጣም ቀጥተኛ፣ ኃይለኛ እና የማይካድ በሆነ መንገድ መልስ ይሰጣል። ይህ እምነታችንን ያጠናክራል፣ እናም በሕይወታችን ውስጥ የእግዚአብሔር ቅርብነት ይሰማናል። በሌሎቹ ጊዜያት እግዚአብሔርን በማይለወጥ እምነት መከተል በጣም ከባድ እንደሆነ በማሰብ እንወዛወዛለን እና ለፈተና እንጋለጣለን። የእግዚአብሔርን መልስ የምንፈልገው እኛ እንዲመልስልን በምንጠብቅባቸው መንገዶች ነው፣ የእርሱ ሀሳቦችና መንገዶች ከእኛ እጅግ የላቁና በጥበብ የተሞሉ መሆናቸውን አንገነዘብም (ኢሳ. 55:8-9)። ልክ ስለ እግዚአብሔር ፍጥረት ብዙ ነገር እንደማንረዳው ሁሉ፣ ስለ እርሱ የማንረዳው ነገር መኖሩ ሊገርመን አይገባም። ቸርና ደግ አባታችን እግዚአብሔር ምን እንደሚያስፈልገን በትክክል ያውቃል። በእርሱ ላይ እምነት መጣልና ዓይኖቻችንን በእርሱ ላይ ማተኮር የምንችለው እንዴት ነው? ስለዚህ ጉዳይ አሁን ከእርሱ ጋር እንነጋገር።

ግንቦት 3
May 11

ጸሎቶች መልስ የሌላቸው በሚመስሉበት ጊዜ


ምናልባት ለረጅም ጊዜ፣ ምናልባትም ለዓመታት ስለ አንድ ነገር ጸልየው ይሆናል፣ እናም እግዚአብሔር ጸሎቶችዎን እንዳልሰማ ይሰማዎት ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ “ለምኑ፣ ይሰጣችኋል” ይላል (ማቴ. 7:7)፣ “ማንኛውንም ነገር እንደ ፈቃዱ ብንለምን” (1 ዮሐንስ 5:14) እንደምናገኝ ነግሮናል። ስለ እነዚህ ተስፋዎች ያለዎት ግንዛቤ ምንድን ነው?



ሐና በጣም ግልጽ ለሆነ ነገር የጸለየች ታማኝ ሴት ምሳሌ ናት (1ኛ ሳሙ. 1:10–17)።

መጀመሪያ ላይ እግዚአብሔር ጸሎቷን ያልመለሰላት ቢመስልም ጸናች፣ እግዚአብሔርም ፍጹም በሆነው ጊዜውና እንደ ፈቃዱ መልስ ሰጠ። አንዳንድ ጊዜ በመጠበቅ ውስጥ በእርሱ ላይ የበለጠ እምነት እንድንጥል ስንማር ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ጉዞ ይጠነክራል። መዝሙር 62:8 እንዲህ ይላል፣ “የሕዝብ ማኅበር ሁላችሁ፥ በእርሱ ታመኑ፥ ልባችሁንም በፊቱ አፍስሱ፤ እግዚአብሔር ረዳታችን ነው።”። መታመን። ለጸሎታችን ፈጣን መልስ ባናገኝም እንኳ፣ እርሱ በእርግጥ የተሻለውን እንደሚያውቅ እናምናለን? በመጨረሻ ፍጹም በሆነው ጊዜውና መንገዱ እንደሚመልስ እናምናለን? አንዳንድ ጊዜ ጸሎቶቻችን እኛ በፈለግነው ፍጥነት ወይም በምናስበው መንገድ ላይመለሱ ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ምክር ይሰጠናል?

በዋናነት፣ እግዚአብሔር ትልቁን ምስል ያያል፡ እና ለእኛ የሚበጀውን ያውቃል (ሮሜ 8:28፣ ኤፌ. 3:20፣ ኤር. 29:11-13)። አንዳንድ ጊዜ መልሱ ለጳውሎስ እንደተሰጠው አይነት ብቻ ይሆናል፡- “ጸጋዬ ይበቃሃል” (2ኛ ቆሮ. 12:9)። አልተመለሱም ብለን ላሰብናቸው ጸሎቶች እኛ የምንሰጠውን ምላሽ የሚወስነው ስለ እግዚአብሔር ያለን ምስል ነው። እግዚአብሔርን እንደ ሩቅ እና ግድ የለሽ አድርገን ካየነው፣ ከእርሱ ጋር ያለን ግንኙነት ይሻክራል። በእንደዚህ ዓይነት ጊዜያት፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለእናንተ ያለውን ፍቅር እና እንክብካቤ የሚያሳይ ማስረጃ ፈልጉ። እና ስለ እርሱ ያላችሁ የተዛባ ምስል የበለጠ ግልጽ እንዲሆን ጸልዩ።

ግንቦት 4
May 12



ኢየሱስ እንዴት መጸለይ እንዳለብን ያስተምረናል


በኢየሱስ ዘመን፣ ውስብስብ ቃላትን በመጠቀም፣ ብዙ ጊዜ በቃል የተሸመደዱ ረጅም እና በጥንቃቄ የተቀረጹ ጸሎቶችን መፀለይ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነበር። ኢየሱስ ስለ እነዚህ አይነት ጸሎቶች የሚናገረው ምንም መልካም ነገር አልነበረውም (ማቴ. 6:5-8)። ኢየሱስ፡ “ከአንገት በላይ የሆኑ የታይታ ቅድስናዎች” እንደሆኑ ተናግሯል። ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ሲጸልይ አይተውታል፣ እናም ጸሎት የሕይወቱ ወሳኝ ክፍል እንደሆነ ያውቁ ነበር (ሉቃስ 5:16፣ ሉቃስ 6:12፣ ሉቃስ 9:18፣ ሉቃስ 22:41፣ ሉቃስ 24:30፣ ማርቆስ 1:35፣ ማርቆስ 6:46)። ኢየሱስን ከሌሎች ሃይማኖት መሪዎች ጋር ሲያነፃፅሩት ስለ ጸሎት ብዙ የማያውቁት ብዙ ነገር እንዳለ ተገነዘቡ። ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ መጡና “ጌታ ሆይ፣ እንጸልይ ዘንድ አስተምረን” (ሉቃስ 11:1) ብለው ጠየቁት። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ (እና ለእኛ) በዕለት ተዕለት ቋንቋ በቀላሉ መጸለይ የምንችለው የፀሎት ምሳሌ ሰጠን። ጸሎታችን ከልብ የመነጨ መሆን እንዳለበት አሳየን። ሉቃስ 11:2-4 እና ማቴዎስ 6:5-15ን ያንብቡ እና ኢየሱስ ካስተማረው ጸሎት የሚከተሉትን ገጽታዎች ልብ ይበሉ፡ በሰማይ የምትኖር አባታችን ሆይ፡ የሁላችን አባት መሆኑን እውቅና በመስጠት። ስምህ ይቀደስ፡ የእግዚአብሔርን ቅድስና ማወቅ በአክብሮት በፊቱ እንድንቀርብ እንደሚያደርገን በማስተዋል። መንግሥትህ ትምጣ፡- የክርስቶስን መመለስ እና እርሱ እስኪመለስ ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ መሆንን በመናፈቅ። ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድርም ትሁን፡- ራስን በማስረከብ የእግዚአብሔር ፈቃድ በሕይወታችን እንዲፈጸም እና የምንፈልገውን ብቻ ከመጠየቅ ይልቅ እርሱ የተሻለ እንደሚያውቅ በማመን መጸለይ። የዕለት እንጀራችንን ስጠን ዛሬ፡- ለሥጋችን (ምግብና ውሃ) እና በመንፈሳዊውም በህይወት ለመቀጠል የሚያስፈልገንን (ኢየሱስ እና ሕያው ቃሉ) መጠየቅ። የሚበድሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን፡- ንስሐ መግባት፣ ምህረትን መፈለግ እና እግዚአብሔር ይቅር እንደሚለን የበደሉንን በነፃ ይቅር ማለትን ማስታወስ። ከክፉ አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን፡- በዚህ ዓለም ካለው ክፉ ነገር ጥበቃና መጠጊያ መጠየቅ (መዝሙር 91)። መንግሥት የአንተ ነውና፣ ኃይልና ክብር ለዘላለም አሜን። እኛ የሆንነው፣ ያለንና የምናደርገው ሁሉ የእግዚአብሔር መሆኑን አምነን መቀበል። ክብርና ምስጋና ለእርሱ ብቻ ልንሰጥ ይገባናል (1ኛ ዜና 29፡11)። ትንሽ ትንሽ ብቻ መጸለይዎን አቁመው በየቀኑ ጠዋት ከማንም በላይ ከሚወድዎ ጋር ለምን አይነጋገሩም? ይህን ማድረግ እንዳለብዎ እያወቁ እንዳያደርጉ የሚከለክልዎት ምንድን ነው? አሁኑኑ ኢየሱስ እንደጋበዘዎ አስበው ይጸልዩ።

ግንቦት 5
May 13

ምስጋና፣ ኑዛዜ፣ ልመና


ኢየሱስ እንዴት መጸለይ እንዳለብን እንዳስተማረን፣ በግል፣ ከቤተሰባችን ጋር ወይም እንደ ቤተ ክርስቲያን ወደ እግዚአብሔር ስንመጣ፣ ጸሎት እንደ ጓደኛ ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር መሆኑን በማስታወስ ይህንን ቀላል መንገድ መከተል እንችላለን። ኢየሱስ አብልጠን ከፍ ያሉ ነገሮችን እንድንጠይቅ ቢያስተምረንም ብዙ ጊዜ ጸሎቶቻችን በልመናዎች የተሞሉ ናቸው! በዳንኤል 9:4-19 ላይ የዳንኤልን ጸሎት ያንብቡ እና የጸሎቱን የተለያዩ ክፍሎች ይመልከቱ።



በጸሎቶችዎ ውስጥ የሚከተሉትን ክፍሎች እንዴት ማካተት እንደሚችሉ ያስቡበት፡ አድናቆት፡ አድናቆት እግዚአብሔርን ስለ ማንነቱ እና ስለ ባህሪው በቃላት ማድነቅ ነው።

መዝሙር 100ን ዳዊት ለእግዚአብሔር የሚያቀርበውን ውብ የምስጋና መዝሙር ያንብቡ። የእግዚአብሔርን ብዙ ስሞች እና ድንቅ ባህሪውን ያሰላስሉ። ቤዛዎ፣ አዳኝዎ፣ አጽናኝዎ፣ ፈዋሽዎ፣ መልካም እረኛዎ፣ አልፋ እና ኦሜጋ እና ዓለቱ ስለሆነ፣ አመስግኑት። ኑዛዜ እና ይቅርታ፡ ከእግዚአብሔር ጋር ስንነጋገር እና ከእርሱ ጋር ስንኖር፣ ሊለየን የሚችለውን ማንኛውንም ነገር መተው አይከብደንም። ወደ እርሱ በቀረብን ቁጥር፣ ዋጋቢስነታችንንና ጎስቋላነታችንን የበለጠ እያየን እንሄዳለን። ይህም ኃጢአታችንን እንዲያስወግድልንና ባህሪያችንን በአምሳሉ እንዲቀርጽ እንድንለምነው ያደርገናል።

እግዚአብሔር ይቅር እንዲለን የምንጠብቅ ከሆነ፣ ሌሎችንም ይቅር ለማለት ዝግጁ መሆን አለብን። “እርስ በርሳችሁ በኃጢአታችሁ ተናዘዙ። ትፈወሱም ዘንድ እያንዳንዱ ስለ ሌላው ይጸልይ፤ የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች።” (ያዕቆብ 5:16)። ጥያቄዎች፡- በቤተሰብዎ፣ በጓደኞችዎ፣ በጤናዎ፣ በገንዘብዎ፣ በሥራዎ ወይም በትምህርትዎ ምን አይነት ፈተናዎች እያጋጠሙዎት ነው? በተለይም የእግዚአብሔር እጅ እንዲመራዎ የሚፈልጉት የቱ ጋ ነው? እርዳታዎን የሚፈልገው ማን ነው? እና በተሻለ ሁኔታ መስጠት የሚችሉት እንዴት ነው? ስለ እነዚህ ሁኔታዎች እና ሰዎች እግዚአብሔር ፈቃዱን እንዲፈጽም በመጠየቅ ይጸልዩ። ምስጋና፡- ፊልጵስዩስ 4:6ን ያንብቡ እና በሕይወትዎ ውስጥ ስላሉት በረከቶች ያስቡ።

ጉልህ ነገሮች ወደ አእምሮዎ ሊመጡ ይችላሉ፣ ነገር ግን ብዙ ጊዜ እንደ ቀላል የምንቆጥራቸው ትናንሽ ነገሮችስ? እኛ ዘወትር የእግዚአብሔር ምሕረት ተቀባዮች ነን፤ ሆኖም ምን ያህል ምስጋናችንን እየገለፅን፣ ለእኛ ስላደረገልን ነገር ምን ያህል እያመሰገንነው ይሆን? እግዚአብሔርን ለማመስገን፣ ለእርሱ ለመናዘዝ፣ ከእርሱ ለመለመን እና ለማመስገን ምን ነገሮች ያስፈልጉናል? ለምን አሁን አናደርገውም?

ግንቦት 6
May 14

ስለ ጸሎት ሌሎች ጥያቄዎች


እግዚአብሔር አስቀድሞ ሁሉን እያወቀ መጸለይ ለምን አስፈለገ? እግዚአብሔር ሁሉን አዋቂ ሆኖ እያለ መጸለይ የሚያስፈልገን ለምንድነው? ኤለን ጂ. ኋይት እንዲህ ትገልጸዋለች፡ - “የምንጸልየው ስለ እኛ ሁኔታ ለእግዚአብሔር የሚያውቀውን መረጃ ለመስጠት ሳይሆን፣ እርሱን በልባችን ለመቀበል እንዲያግዘን ነው። ጸሎት እግዚአብሔርን ወደ እኛ አያወርደውም፤ ነገር ግን እኛን ወደ እርሱ ከፍ ያደርገናል።” ኤለን ጂ. ኋይት፣ ወደ ክርስቶስ የሚመራ መንገድ፣ ገጽ 87። በእርግጥም፣ እግዚአብሔር ፍላጎቶቻችንንና ምኞታችንን ያውቃል፣ እናም የልባችንን እያንዳንዱን ፍላጎት ያነባል። ሆኖም፣ ጸሎት ለእኛ መልካም ነው። በሕይወታችን ውስጥ በጥድፊያው መካከል ቆም ብለን እግዚአብሔር በሁሉም ላይ ሉዓላዊ መሆኑን እንድንቀበል እና እራሳችንን በእግሩ ስር እንድናስቀምጥ ይጋብዘናል።

እግዚአብሔር እንዲሰራ ስንጋብዘው እርሱ እንዲሠራ መንገዶች ሊከፈቱ ይችላሉ። መንፈስ ቅዱስ እንዴት መጸለይ እንዳለብን በማናውቅበት ጊዜ ይማልድልናል (ሮሜ 8:26, 27)። ሁሉም ነገር ሰላም ከሆነ ለምን እንጸልያለን? ራሴ ለራሴ ብቁ ነኝ ማለት እና ትዕቢት (3ኛ ትምህርትን ይመልከቱ) ጠንካራ የጸሎት ሕይወትን ከሚያደናቅፉ ትላልቅ እንቅፋቶች መካከል ናቸው። እግዚአብሔርን ምን ያህል እንደሚያስፈልገን ብናውቅ ኖሮ ወደ እርሱ የበለጠ እንጠጋ ነበር! ፍጹም የሆኑ መላእክት እርሱን እያደነቁ እና እያመለኩ ከሆነ፣ እኛ እንደ ኃጢአተኞች እርሱ ብዙም እንደማያስፈልገን ለምን እናስባለን? ማቴዎስ 5:6 እና ኢሳይያስ 44:3 ስለዚህ እውነት ምን ይላሉ? በጸሎት ውስጥ የእምነት ሚና ምንድን ነው? ዕብራውያን 11:6ን ያንብቡና እነዚህን ቃላት አስቡባቸው፡- “ፀሎትና እምነት የተያያዙ ናቸው። በአንድ ላይ መጠናትም ይኖርባችኋል።

በእምነት በሚፀለይበት ጊዜም መለኮታዊ ሳይንስ አለ። የሕይወቱን ሥራ የተሳካ ለማድረግ የሚጥር ሁሉ ሊያስተውለው የሚገባ ሣይንስ ነው። ክርስቶስ እንዲህ ይላል። የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፥ ይሆንላችሁማል። (ማር 11፡24) አጠያየቃችንም እንደ እግዚአብሔር ፍላጐት መሆን እንዳለበት ግልጽ ያደርጋል። እርሱ ቃል የገባልንን ነገሮች ነው መጠየቅ ያለብን። የምናገኘውንም ሁሉ መልሰን የርሱን ፈቃድ ለማሟላት ተግባራት እንዲውሉ ማድረግ አለብን። . . . ለሚሰጠን በረከት ሌላ ውጫዊ ማስረጃ መሻት አያስፈልገንም። ስጦታው በተስፋው ቃል ውስጥ አለ።” ስነ ትምህርት ገፅ 290 ከማን ጋር መጸለይ አለብኝ? ከሁሉም በላይ በግል መጸለይ አለብን (እግዚአብሔርና እናንተ ብቻ)፣ ምክንያቱም ጸሎትና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት የሕይወት ደም ስር ናቸው። ለመጠየቅና ለመስማት ልባችንንም ለመመርመር ጊዜ እንመድብ (ማቴ. 6:6)። እንዲሁም ከቤተሰቦቻችን ጋር ወይም በትንሽ ቡድን (የሐዋርያት ሥራ 12:12) መጸለይ አለብን፤ ምክንያቱም ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች በሚሰበሰቡበት ቦታ እግዚአብሔር እዚያ አለ (ማቴ. 18:20)። በመጨረሻም፣ ከቤተክርስቲያናችን ማኅበረሰቦች ጋር መጸለይ አለብን (ያዕቆብ 5:13-16)። ሦስቱም የጸሎት ዓይነቶች አስፈላጊ ናቸው። እንዴት ማዳመጥ ይኖርብኛል? ጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር ከመነጋገር የበለጠ ነገር ነው፤ እርሱ እኛን “እንዲከረክመን” እና በሕይወታችን ውስጥ እንዲናገር መፍቀድ አለብን።

ይህንን ለማድረግ በጣም ግልጽ እና የተሻለው መንገድ ጸሎትን እና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትን በአምልኮ ጊዜዎ ውስጥ መጨመር ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ከመመርመር ይልቅ አእምሯችንን ባዶ ማድረግ ወይም የራሳችንን ሀሳብ ማዳመጥ አያስፈልገንም። ከላይ ከተጠቀሱት ነጥቦች በጣም ፈታኝ ሆኖ ያገኙት የትኛውን ነው?

ግንቦት 7
May 15


ተጨማሪ ሀሳብ


“ከራሳችን ይልቅ ስለ ኢየሱስ ብዙ ካሰብንና ከተናገርን የርሱን መገኘት እየተለማመድን እንሄዳለን።” ወደ ክርስቶስ የሚመራ መንገድ ገፅ 102 “ከጥርጣሬያችንና ከፍርሃታችን ጋር ብንማከር፣ ወይም ያለ እምነት በትክክል ልናያቸው የማንችላቸውን ነገሮች ሁሉ ለመፍታት ብንታገል፣ ጭንቀታችን እየጨመረና እየጠነከረ ከመሄድ ውጪ ሌላ የሚሆን ነገር አይኖርም። ነገር ግን ረዳተቢስ እንደሆንንና ድጋፍ እንደሚያስፈልገን በመረዳት ራሳችንን በማዋረድ፣ እውቀቱ ወሰን ለሌለው፣ በፍጥረተ ዓለም ውስጥ ያለውን ነገር ሁሉ ለሚያየው፣ በፈቃዱና በቃሉ ሁሉን ለሚያስተዳድረው ለእግዚአብሔር በእምነት የሚያስፈልገንን ነገር ብናቀርበው ጩኸታችንን ሊሰማ ይችላል፤ ደግሞም ይሰማል፤ በልባችንም ላይ ብርሃን ያበራል።” ወደ ክርስቶስ የሚመራ መንገድ ገፅ 90 “ነፍስ በምስጋና ክንፍ ወደ ሰማይ ትበራለች። በላይ በሰማይ አደባባዮች እግዚአብሔር በመዝሙርና በሙዚቃ ይመለካል። እኛ ደግሞ በዚህ ምድር ላይ ምስጋናችንን በመግለጥ ስናመልክ የሰማይ ሠራዊትን አምልኮ እየተጠጋን እንሄዳን። «ምስጋናን የሚሰዋ ሁሉ» እግዚአብሔርን ያከብራል። መዝ. 50፡ 23። «በምስጋናና በዜማ ድምጽ» በአክብሮት በተሞላ ደስታ ወደ ፈጣሪያችን እንቅረብ። ኢሳ. 51፡3።” ወደ ክርስቶስ የሚመራ መንገድ ገፅ 99


የመወያያ ጥያቄዎች




1. ከላይ ከተጠቀሱት ጥቅሶች ውስጥ የበለጠ ያነቃቃዎት የትኛው ጽንሰ ሐሳብ ነው? የተገዳደረዎትስ የትኛው ጽንሰ ሐሳብ ነው?

2. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካሉ ከሌሎች የጸሎት ሕይወት ምን ሌሎች ትምህርቶችን ልንማር እንችላለን? (ዕዝራ 10:1፣ 2 ነገሥት 13:4፣ ዮናስ 4:2-3፣ ዕንባቆም 3:1፣ 2 ነገሥት 19:14-19፣ ኤር. 32:16-25፣ ነህ. 1:4-11፣ 1 ነገሥት 8:22–54ን ይመልከቱ።)

3. ከጸሎት ጎን ለጎን የጾም ሚና ምንድን ነው?

4. በዚህ ሳምንት ትምህርት ምክንያት በጸሎት ሕይወትዎ ውስጥ መለወጥ ወይም ተግባራዊ ማድረግ የሚፈልጉት አዲስ ነገር አለ? ስለዚህ ለምን ዛሬ አይጀምሩም? ማጠቃለያ፡ መጽሐፍ ቅዱስ ሕያው፣ ዘላቂ የጸሎት ሕይወት የነበራቸውን እና ያልነበራቸውን ሌሎች ሰዎችን ታሪክ ያካፍላል። ገጾቹን ስንገልጥ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ሁልጊዜ ታሪካቸው ከእኛ ጋር የሚቀራረቡ ሰዎችን እናገኛለን። በአምልኮ ሕይወታችን ውስጥ የሚያበረታቱንና የሚመሩንን ብዙ፣ ብዙ ተስፋዎችንም እናገኛለን።

መንፈሳዊ እድገት ግባችን መሆን አለበት - ዓይኖቻችን በሁሉም ነገር ውስጥ ዋናው ምሳሌ እና የእምነታችን ጀማሪና ፈጻሚ በሆነው በኢየሱስ ላይ መሆን አለባቸው።




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL