የሕይወት ምዕራፎች
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 2ኛ ሩብ ዓመት 2019

ከሚያዝያ 26 - ግንቦት 2

6ኛ ትምህርት

May 04 - May 10




ንጉሣዊው የፍቅር መዝሙር



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ መኃልየ መሓልይ፣ ዘፍ. 2:7፣ 1ቆሮ. 7:3–5፣ ዮሐ. 17:3፣ 1ዮሐ. 1:9፣ ሮሜ. 1:24–27፣ ገላ. 5:24።


መታሰቢያ ጥቅስ:- “በልብህ እንዳለ፣ በክንድህም እንደምትይዘው ማኅተም አስቀምጠኝ፤ ፍቅር እንደ ሞት የበረታች፣ ቅናቷም እንደ መቃብር ጨካኝ ናትና” (መኃል. 8፡6)፡፡

ከ ታላላቆቹ የህይወት ምዕራፎች አንዱ ጋብቻ ነው። ቀደም ብለን እንደ ተመለከትነው ሁሉም ሰው ትዳር አይዝም። ሆኖም ለሚያገቡ ግን ትዳር የተለዩ ተግዳሮቶችን እንዲሁም የተለዩ በረከቶችን ይዞ ይመጣል። ከበረከቶቹ አንዱና ግሩም የሆነው የሩካቤ ሥጋ ስጦታ ነው። ይህ ስጦታ በትክክለኛው ጊዜና ቦታ ገቢራዊ መሆን ሲችል ብርቱ የፍቅር መግለጫ ይሆናል።

ብዙዎች ከሚጋሩት ሃሳብ በተቃራኒ መጽሐፍ ቅዱስ በሩካቤ ሥጋ ላይ ተቃውሞ የለውም። ሆኖም ተቃውሞው ያለው ይህ በፈጣሪ ለሰብዓዊው ፍጡር የተሰጠ ስጦታ በተሳሳተ መንገድ ጥቅም ላይ ሲውል ነው።

አነስተኛ ገጽ ካሏቸውና ከመነበብም አንጻር አነስተኛውን ስፍራ የሚወስደው መጽሐፍ መኃልየ መሓልይ--በወጣቷ ሙሽራ እና በምትወደው ሙሽራ መሃል ያለውን ግንኙነት የሚገልጽ ሲሆን ሙሽራው ራሱ ንጉሥ ሰሎሞን እንደሆነ ይታመናል። መጽሐፉ የሰብዓዊውን ጥብቅ ግንኙነት ምስጢርና በጋብቻ የተጣመሩ ጥንዶችን ፍቅር አስደሳችነት ገልጦ ያሳያል።

ምንም እንኳ የሰሎሞን መዝሙር በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ወይም በክርስቶስና በቤተ ክርስቲያን መሃል ያለውን ግንኙነት ምናባዊ በሆነ መንገድ እንደሚገልጽ ተደርጎ በተደጋጋሚ ቢታሰብም፤ በወንድ እና ሴት ተጨባጭ ግንኙነት መሃል ያለውን ፍቅር የሚገልጽ ግጥም መሆኑ ለአፍታም መዘንጋት የለበትም። በዚህ ሣምንት በብሉይ ኪዳን መጽሐፍ በቀረበው የጋብቻ ሁኔታ ላይ ምልከታ እናደርጋለን።

ሚያዝያ 27
May 05

ሊከፋፈል የማይችል ህይወት


በሚከተሉት ጥቅሶች መሰረት መጽሐፍ ቅዱስ በሰብዓዊው አካል ላይ ያለውን አመለካከት እንዴት ይገልጹታል? ዘፍ. 2:7፣ መዝ. 63:1፣ 84:2፣ 1ቆሮ. 6:19-20፣ 1ተሰ. 5:23።



አንዳንድ ኃይማኖቶች በሁለትዮሽ ማንነት ያምናሉ። በዚህ ሰብዓዊው አካል ለነፍስያ ህይወት ችግር መሆኑን በሚያትተው ፍልስፍና--አካል በክፉ፣ ነፍስ ደግሞ በበጎ ተፈርጆአል። ሆኖም ሰብዓዊው አካል ወሲባዊ ባህሪያትን ጨምሮ ከአጠቃላዩ ማንነት ጋር ዉሁድ ነው። ህይወት “አካል” እና “ነፍስ” ነው (ዘፍ. 2፡7)። ባለመዝሙሩ ለእግዚአብሔር በሚያቀርበው አምልኮ መላው እርሱነቱን አሳልፎ ሲሰጥ ይስተዋላል (መዝ. 63፡1፣ 84፡2)። ሙሉው ማንነት ሊቀደስና ለአምላካዊው ዓላማ ሊለይ የግድ ነው።

አዎንታዊው የሰብዓዊ አካል አተያይ ከሩካቤ ሥጋ ዐውድ በሰሎሞን መዝሙር ተንጸባርቆአል። ጥቅሶቹ ይህን አመለካከት እንዴት ይገልጹታል? መኃል. 1:2-13፣ 2:6፣ 5:10–16፣ 7:1–9።



በእነዚህ ቅዱስ ጽሑፎች ሰብዓዊው አካል በሁሉም ገጾች ተደንቆአል። የጋብቻ ፍቅር አካላዊ ገጽታዎች አስነዋሪ አለመሆናቸውን ተከትሎ ከመጀመሪያ አስከ መጨረሻ ያለው ሙሉ የስሜት ሁኔታ በግልጽ ቀርቦአል።

በብዙ ባህሎች እያደረጉ ከማይናገሩት አንዱ የሆነውን ወሲብ ነክ ጉዳይ ማንሳት ፍጹም የተከለከለ ነው። በዚህ የተነሳ ያገቡ ጥንዶችም በጠለቀ ወዳጅነታችው ዙሪያ ጤነኛ ሃሳብ መለዋወጥ ተራራ እንደ መግፋት አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል።

በተመሳሳይ ልጆችም ከክርስቲያን ቤት እሴቶች አኳያ ትክክለኛውን ወሲብ ነክ ጉዳይ ሊያውቁ የሚችሉበትን ዕድል ተነፍገዋል። መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ዙሪያ ያለው ግልጽነት የእግዚአብሔርን ሕዝቦች በርዕሰ ጉዳዩ ዙሪያ ከፍ ወዳለ የመጽናኛ ደረጃ እንዲወጡ ጥሪ የሚያደርግ ነው። ይህ ወሳኝ የህይወት ገጽታ ከፈጣሪ የተሰጠ ስጦታ እንደመሆኑ ተገቢው ክብር ተችሮት ሊታይ ይገባል። ወሲባዊውን ግንኙነት ፈጽሞ በአፍ እንዳማያወሩት እንስሳዊ ድሪያ ወይም አሳፋሪ ነገር ከሚቆጥረው ባህላዊ ተጽእኖ ራሳችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው? ሁለቱም ጽንፎች የተሳሳቱ መሆናቸውን መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት ያሳየናል?

ሚያዝያ 28
May 06

የፍቅር መዝሙር--ፍቅር


በመኃልየ መሓልይ የቀረቡትን የተለያዩ የፍቅር ሁኔታዎች ለመግለጽ ይሞክሩ፡ መኃል. 1:2-13፣ 2:10–13፣ 16፣ 3:11፣ 4:1–7፣ 5:16፣ 6:6፣ 7:1–9፣ 8:6-7።



መኃልየ መሓልይ ወይም የሰሎሞን መዝሙር የፍቅር ጓደኛሞች እንዴት በአንድ ላይ ሆነው ጊዜአቸውን በስስት እይደሚያጠፉ፣ በግልጽ እንደሚወያዩና አንዱ ለሌላው ስለሚያደርገው የተለየ ጥንቃቄ ብዙ ይለናል። በሰሎሞን መዝሙር ሁለት መልካም ወዳጆች በጋብቻ ለመተሳሰር ይበቁና ሚስት “ውዴ ይህ ነው” (መሐል. 5፡16) በማለት በይፋ ትናገራለች። በጥቅሱ ባልንጀራዬ በሚል ጥቅም ላይ የዋለው ቃል ከወሲብ በራቀ ንጽህና የተሞላ አብሮነትንና ወዳጅነትን ይገልጻል። የትዳር ጓደኛው የከበረ ወዳጅ የሆነችው ወይም የሆናት ሴት ደስተኛ ናቸው።

በመላው የግጥሙ ክፍል የሚንጸባረቀው ጥልቀት ያለው ግንኙነት፣ ሰላምታና የፍቅር አኳኋን--ወንዱ በሴቷ ሴቷም በወንዱ በሚያገኙት አካላዊና ስሜታዊ ደስታ ያላቸውን ጠንካራ መሳሳብ ያሳያል። ተፈጥሮአዊው ጥልቀት ያለው የፍቅር ስሜት ጥንዶች በጋብቻ እንዲተሳሰሩ የሚረዳ የፈጣሪ ስጦታ ነው።

የትዳር ተጣማሪዎች መለኮታዊው ፍቅር በልባቸው እንዲሠራ ውስጣቸውን ክፍት እስካደረጉ ድረስ ሰብዓዊ ፍቅራቸው “የጠራ፣ የነጠረ፣ ጥልቅና የከበረ ይሆናል”—Ellen G. White, The Adventist Home, p. 99.

በተጨማሪ እነዚህ ጥቅሶች ፍቅርን አስመልክቶ የገዘፈ ሀሳቦችን ይዘዋል። ለነገሩ እውነተኛ ፍቅር ለሰብዓዊው ልብ ተፈጥሮአዊ ሳይሆን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ነው (ሮሜ 5፡5)። እንዲህ ያለው ፍቅር ባልና ሚስት እስከ መጨረሻው የተሳሰረ ሕብረት እንዲኖራቸው ያስችላል። በታዳጊ ወጣቶች ልብ የመተማመን ስሜት ለመገንባት የሚያስችል፣ ለልጆችና ወላጆች ትስስር እጅግ ወሳኝና ቁርጠኝነት የሚጠይቅ ጥልቅ ፍቅር ነው። አማኞችን በክርስቶስ አካል በአንድ የሚያስተሳስር ራስን የመስጠት ፍቅር ነው። ከፍቅር ተጣማሪያችን ጋር ባለን ግንኙነት ይህንን ፍቅር እንደ ቀስቃሽ ኃይል እንድንጠቀም የሰሎሞን መዝሙር ጥሪ ያቀርብልናል።

ለመሆኑ እንዲህ ያለው ትስስር ከእግዚአብሔር ጋር ሊኖረን እንደሚችለው ትስስር በራሱ መንገድ የሚንጸባረቀው እንዴት ነው? ከዚህ አጓዳኝ የሆኑ መስመሮችን (ለምሳሌ አብሮ ጊዜ ማጥፋት፣ ራስን ሙሉ ለሙሉ አሳልፎ መስጠት ወዘተ) መሳል የሚቻለው እንዴት ነው?

ሚያዝያ 29
May 07

በፍቅር የተሞላ “ዕውቀት”


ብዙዎች ወደ ኤደን የመመለስን መልእክት ጭብጥ በመኃልየ መሓልይ መመልከት ችለዋል። ምንም እንኳ እነዚህ ግጥሞች ስለ መጀመሪያው ወንድ እና የመጀመሪያዋ ሴት የፍቅር ግንኙነት የሚገልጹ ባይሆንም ሰብዓዊውን አእምሮ ወደ ቀደመው የኤደን አትክልት ስፍራ ይዘው ጭልጥ ማለታቸው ግን እሙን ነው። ሁለቱ “አንድ ሥጋ” (ዘፍ. 2፡24-25) መሆናቸው አምላካዊው እቅድ መሆኑን የሚገልጹ ውብ ተምሳሌታዊና ዘይቤአዊ አነጋገሮች በመልክ በመልክ ተሰድረውና ፍንትው ብለው ለአንባቢው ቀርበዋል።

መኃልየ መሓልይ በባለትዳር ጥልቅ ግንኙት መሃል የሚኖረውን የጋራ ቁርጠኝነት እንዴት ይገልጸዋል--መኃል. 4:7–5:1? ጳውሎስ በ1ቆሮ. 7፡3-5 የሰጠው መመሪያ ከዚህ ጋር እንዴት ይመሳሰላል?



ሰሎሞን “አብረሽኝ ነይ” (መኃልየ. 4፡8) ሲል ለሙሽራው ግብዣ ያቀርብላታል። እርሷም ቆየት ብላ “ውዴ ወደ አትክልት ቦታው ይግባ” ስትል ትመልስለታለች። ከዚያም ቀጣዩን ምላሽ በምዕ. 5፡1 ይሰጣታል። በዚህ የጠበቀ ግንኙነት ውስጥ አንዳችም ጉልበት ወይም ማስፈራሪያ አለመኖሩን አምላካዊው ቃል ያስተምረናል። በመሆኑም ሁለቱም ተጣማሪዎች ወደዚህ አብሮነት የሚገቡት በነፃነትና በፍቅር ነው። “የአትክልት ቦታዬ” “የአትክልት ቦታው” ነው።

ሙሽራውና ሙሽሪት ውዴ እየተባባሉ ሰላማዊ የሆነውን ሙገሳ በጋራ ይሞጋገሳሉ (መሐል. 4፡1-5፣ 5፡10-16)። የግንኙነታቸው ሚዛን ጥምር ሆነው በቀረቡት የሥነ ግጥም አጻጻፍ ዘይቤዎችና ጥቅሶች በጉልህ መታየት ይችላል። “ውዴ የእኔ ነው፤ እኔም የእርሱ ነኝ” (2፡16) በሚል የቀረበው ኪዳናዊ አገላለጽ “እነሆ፤ ይህች ዐጥንት ከዐጥቴ፣ ሥጋም ከሥጋዬ ናት” (ዘፍ. 2፡ 23) በሚል የተደመጠውን የኤደን የአትክልት ስፍራ ድምፅ ያስተጋባል።

“ዐወቃት” በሚል በትዳር የተጣመሩ ጥንዶችን ግንኙነት ለመግለጽ ጥቅም ላይ የዋለው ቃል ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን የግንኙነት አረዳድ ማዳበር የሚችለው እንዴት ነው--ዘፍ. 4:1፣ 25፣ 1ሳሙ. 1:19፣ ሉቃ. 1:34፣ ዮሐ. 17:3፣ 1ቆሮ. 8:3?



መጽሐፍ ቅዱስ የባልና ሚስትን ጥብቅ ግንኙነት ለመግለጽ “ዐወቃት” የተሰኘውን ቃል ይጠቀማል። እጅግ ድብቅና ጥልቅ የሆነው ውስጣዊ ማንነት በዚህ በፍቅር የተሞላ “ዕውቀት” አንዱ ለሌላው ይሰጣል።

ሁለት አካላት ብቻ ሳይሆን ሁለት ልቦችም “አንድ ሥጋ” ይሆናሉ። በተጨማሪ ማወቅ የተሰኘው ቃል በሰዎችና በእግዚአብሔር መካከል ያለውን ግንኙነት ይገልጻል። በዓይነቱ ልዩ የሆነውና ጥልቅ ምስጢር ያዘለው ክርስቲያናዊ የትዳር አብሮነት፣ ቁርጠኝነትና ያልተገደበ ደስታ-ልብ የሚማርከውንና እጅግ ቅዱስ የሆነውን የክርስቶስንና የቤተ ክርስቲያንን ሕብረት በሙላት ይገልጣል።

ሚያዝያ 30
May 08

ፍቅር በትክክለኛው ጊዜ


ጥቅሱን ያንብቡ፡ መኃል. 4፡8፤5፡1



በሰሎሞን መዝሙር መካከል ላይ የሚገኘው ምዕ. 4፡16 እና 5፡1 በሁለቱ መካከል ያለው ግንኙነት ወደ መጨረሻው ከፍታ አድጎ በሕጋዊ ጋብቻ ወደ ተሟላ ፍጽምና መድረሱን ያመላክታል። ሰሎሞን በተከታዮቹ ጥቅሶች እየተናገረ ያለው ስለምንድን ነው--መኃል. 4:12፣ 16፣ 5:1፣ 8:8–10?



እጮኛሞች ከጋብቻ አስቀድሞ ባላቸው የወዳጅነት ወይም የመጠናናት ጊዜ ከሩካቤ ሥጋ ተጠብቀው እስከ ጋብቻቸው ቀን በንጽህና መቆየታቸው አምላካዊው ፈቃድ መሆኑን የሚያሳዩ ተጨባጭ ማስረጃዎች በሰሎሞን መዝሙር እናገኛለን። እርሷ “ቅጥር” ብትሆን ወይም “በር” ብትሆን ብለው ወንድሞቿ የተደነቁበትና የእንስቲቱ የልጅነት ዘመን የተጣቀሰበት አቀራረብ ከእነዚህ መካከል አንዱ ብርቱ ማሳያ ነው።

በሌላ አነጋገር እስከ ጋብቻ ቀኗ ድረስ በክብረ ንጽህናዋ ጸንታ (ቅጥር) ትቆይ ይሆን ወይስ በምንዝር ትወድቅ (በር) ይሆን? ይህች እንስት ዕድሜዋ ለአካለ መጠን ሲደርስ ንጽህናዋን እንደ ጠበቀች ወደ ባሏ መጥታ “እነሆ እኔ ቅጥር ነኝ” ትለዋለች (መኃል. 8፡10)።

በእርግጥ እስከ ጋብቻቸው ምሽት ክብረ ንጽህናዋን ጠብቃ መቆየቷን በሚያረጋግጥ ቃና “የታጠረ የአትክልት ቦታ፣ ዙሪያውን የተከበበ ምንጭ፣ የታተመም ፏፏቴ ነሽ” ሲል ተባዕቱ ይናገራል (4፡12)። ጓደኞቿ የፍቅርንና የትዳርን ነገር እጅግ በጥንቃቄ እንዲይዙት ከራሷ የግል ተሞክሮ ተነስታ ምክረ ሀሳቧን ትለግሳቸዋለች። ልጃገረዶች ትክክለኛው የፍቅር ህይወትና ጊዜ ላይ እስኪደርሱ ጥልቅ በሆነ ፍቅር እንዳይነሆልሉ “የኢየሩሳሌም ቆነጃጅት” በሚል ሦስት ጊዜ ለተጠቀሱት እንስቶች ምክሯን ትለግሳለች፡ (መኃል. 2፡7፣ 3፡5፣ 8፡4)። ይኸውም ልክ እንደ እርሷ ጥልቅ ፍቅር በሚገለጥበትና ሰላማዊ ስሜት ሊያመጣላቸው በሚችል የጋብቻ ቃል ኪዳን እስኪተሳሰሩ በንጽህና የመቆየታቸው አስፈላጊነት ነው።

በግጥሙ ውዴ ብሎ የሚጠራት ሙሽራው ከእርሱ ጋር እንድትመጣ ለሁለተኛ ጊዜ ግብዣ ያቀርብላታል (መኃል. 2፡10፣ 4፡8)። ከጋብቻቸው አስቀድሞ የቀረበላትን ግብዣ መቀበል ባትችልም፤ አሁን ግን ወደ አትክልት ቦታዋ የምትጋብዘው እርሷ ራሷ ናት (4፡16)። እርሱም ግብዣዋን በደስታ ይቀበላል (4፡9)። የተሳበው በቁንጅናዋ ባይሆንም ልቡን ግን ሰርቃዋለች (4፡9)። በፍቅሯ ሰክሮአል (4፡10)። እርሷ የሌላ የማንም ሳትሆን እስከ መጨረሻው የእርሱ ብቻ በመሆኗ ደስታው ወደር የለውም፡ “ሙሽራዬ፤ የታጠረ የአትክልት ቦታ፣ ዙሪያውን የተከበበ ምንጭ፣ የታተመም ፏፏቴ ነሽ” (4፡12)። ከዚህች ፍጹም ሴት ጋር ያገኘው አንድነት ወደ ተስፋይቱ ምድር መግባቱ እንዲሰማው ያደርገዋል፡ “ከንፈሮችሽ የማር ወለላ ያንጠባጥባሉ፤ ከአንደበትሽም ወተትና ማር ይፈልቃል” (4፡11)።

ከወሲባዊ ግንኙነት ጋር በተያያዘ ላደረጉት የተሳሳተ ምርጫ ለሚጸጸቱ ሰዎች ምን ዓይነት መልካም የምስራች አለ? 1ዮሐ. 1:9፣ መዝ. 103:12፣ ኢሳ. 55:7፣ ዮሐ. 8:11።

ግንቦት 1
May 09

ለአምላካዊው ስጦታ ዘብ መቆም


እግዚአብሔር ሰብዓዊውን ፍጡር ወንድ እና ሴት አድርጎ ሲፈጥር የተለየ ዓላማ ነበረው (ዘፍ. 1፡26-28)። እያንዳንዳቸው የእርሱን አምሳል መሸከማቸውና የእነዚህ ተቃራኒ ፆታዎች በጋብቻ “አንድ ሥጋ” መሆን፤ በመለኮት ውስጥ ያለውን አንድነት በተለየ መንገድ ያንጸባርቃል።

ከፈጣሪ እቅድ ውጪ ሊተገበሩ በሚችሉ የግብረ ሥጋ ግንኙነቶች ዙሪያ መጽሐፍ ቅዱስ ያለው አመለካከት ምን ይመስላል? ዘሌዋ. 20:7–21፣ ሮሜ 1:24–27፣ 1ቆሮ. 6:9–20



እግዚአብሔር በሰብዓዊው ፍጡር የገለጠውን የገዛ አምሳሉን ሊለውጥ ወይም ሊያጠፋ የሚችል ማንኛውንም አካሄድ መጽሐፍ ቅዱስ ይቃወማል። እግዚአብሔር አፈንጋጭ የሆኑ አንዳንድ ወሲባዊ ግንኙነቶችን በመጥቀስ ሕዝቡን ወደ ትክክለኛው የግንኙነት ዓላማ ይመራል። ሥጋዊው ተሞክሮ ከአምላካዊው መርኅና አስተምህሮ ጋር ሲጋፈጥ ነፍሱ በኃጢአተኝነት ትፈረጃለች።

በወደቀው ዓለም ከወሲብና ሌሎች ተጓዳኝ ግንኙነቶች ጋር በተያያዘ ለክርስቲያን አማኞች ምን ዓይነት ምሪት ተሰጥቶአል? ሮሜ 8:1–14፣ 1ቆሮ. 6:15–20፣ 2 ቆሮ. 10:5፣ ገላ. 5:24፣ ቆለ. 3:3–10፣ 1ተሰ. 5:23-24።



አማኞች ከኃጢአት ጉስቁልና ነፃ የሚወጡበትን የክርስቶስ ዳግም ምጽአት በተስፋ ይጠባበቃሉ። ክርስቶስ በመስቀል ላይ በከፈለላቸው መሥዋዕትነት ራሳቸውን ለኃጢአት ሙት አድርገው እየቆጠሩ በዳግም ምጽአቱ ሕያው የሚሆኑባትን ያቺን ዕለት በእምነት ይጠባበቃሉ።

በማያቋርጥ ጸሎት፣ በትጋትና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ኃጢአተኛው ተፈጥሮአቸው እንደ ተሰቀለ እየቆጠሩ አሳባቸው ነጋ ጠባ ክርስቶስን መታዘዝ ይሆናል። እግዚአብሔር የአካላቸውም ሆነ ወሲባዊ ህይወታቸው ባለቤት መሆኑን ስለሚቀበሉ እንደ መለኮታዊ እቅዱ ይጠቀሟቸዋል። ንስሐ የሚገቡትን እግዚአብሔር ይቀበላል (1ዮሐ. 1፡9)። በምንዝር ኃጢአት ወድቀው የነበሩ ከቀድሞ መንገዳቸው ተመልሰው የአማኞች ኅብረት አካል የሚሆኑበትን ኃይል ወንጌል ሰጥቶአቸዋል። ኃጢአት የሰብዓዊውን ወሲባዊ ማንነት የለወጠበት መጠንና ስፋት እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ጥቂቶች እንዴት ከዚህ ሁኔታ ማገገምና መመለስ እንደሚቻል ላይገነዘቡ ይችላሉ። ምናልባት ከዚህ የተነሳ አንዳንዶች በማንኛውም አምላካዊ ቃል የተከተለከለ ወሲባዊ ግንኙነት ውስጥ ከመግባት ይልቅ የብሕትውና ህይወት ይመርጣሉ።

ለምሳሌ እኛ እንደ ቤተ ክርስቲያን ከግብረ ሰዶማውያን ጋር እንዴት ያለ አግባብ ሊኖረን ይገባል? የገዛ የወሲባዊ ህይወት ዝንባሌአቸው ገጽታ በምንሰጠው ምላሽ ላይ ተጽእኖ የሚኖረው እንዴት ነው?

ግንቦት 2
May 10

ተጨማሪ ሀሳብ


: “ጋብቻ የክርስቶስን ቡራኬ በመቀበሉ እንደ ተቀደሰ ተቋም ሊታይ ይገባል። እውነተኛ ኃይማኖት ከጌታ እቅዶች በተቃራኒ አይሠራም። ወንድ እና ሴት በተቀደሰው ጋብቻ ተሳስረው የሰማያዊው ተምሳሌትና አርአያነት ያለው ቤተሰብ ይመሰርቱ ዘንድ እነሆ አምላካዊው ድንጋጌ ነው። ክርስቶስ ምድራዊ አገልግሎቱን በይፋ እንደ ጀመረ በኤደን ፈቃድ ላገኘውና ለተቋቋመው ተቋም ጥብቅ ድጋፉን ሰጠ። በዚህም በጋብቻ ሥነ ስርዓት ላይ እንደሚገኝ ለሁሉም አበሰረ።

ጋብቻ በንጽህናና በቅድስና፣ በእውነትና በጽድቅ ላይ ሲመሰረት ለሰብዓዊው ፍጡር ከተሰጡት ታላላቅ በረከቶች አንዱ ይሆናል።”—Ellen G. White, Daughters of God, pp. 180, 181. በሰለሞን መዝሙር ማለትም በመኃልየ መሓልይ እንደታየው በጋብቻ ፍቅር የተሳሰረው የግብረ ሥጋ ግንኙነት ግሩምና ድንቅ ነው። ነገር ግን ዘላቂነት ያለው ግንኙነት በውጪያዊ ውበትና በአካላዊ ማማር ላይ የተመሰረተ ሊሆን አይችልም።

የተለየ የአመጋገብ መርኅ በመከተላችን ወይም የፕላስቲክ ቀዶ ጥገና በማድረጋችን ወጣት ልንመስል ብንችልም--አካላችን ማርጀቱም ሆነ መበስበሱ አይቀሬ ነው። የሰሎሞንና የሙሽራው ጋብቻ የዕድሜ ልክ ታማኝነት ግንኙነት ነው። “ውዴ የእኔ ነው እኔም የእርሱ ነኝ” እየተባባሉ ይህንኑ ቃል ከአንዴም ሦስቴ ሲያጸኑ ተደምጠዋል (መኃል. 2፡16፣ 6፡3፣ 7፡10)። የመጀመሪያው ለጋራ ማንነታቸው እውቅና የመስጠት ሲሆን (ኤፌ. 5፡21፣33) ሁለተኛው እርሷ ራሷን ለእርሱ አሳልፋ መስጠቷን የምታረጋግጥበት ነው (ኤፌ. 5፡24-32)። ሦስተኛው እርሱ ለእርሷ ያለው ምኞት የሚገለጽበት ነው (ኤፌ. 5፡24-32)። እንዲህ ያለው ፍቅር ሊጠፋ አይችልም (መኃል. 8፡7)። ሊሰወር እንደማይችል ማኅተም ነው (መኃል. 8፡6)።


የመወያያ ጥያቄዎች




፡ 1.ሰሎሞን ሚስቱን የገለጸበት መንገድ (መኃል. 4:1–5፣ 6:8፣ 7:1– 9) አዳም ሔዋንን ከገለጸበት አኳኋን ጋር እንዴት ይነጻጸራል? (ዘፍ. 2፡23)። ባሎች ከሚስቶቻቸው ጋር ያላቸው ዝምድና ምን ሊመስል ይገባል--(ኤፌ. 5፡28-29)?

2.አንዳንዶች በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ወይም በየሱስና በቤተ ክርስቲያኑ መካከል ያለውን ግንኙነት በሰሎሞን ተምሳሌታዊው መኃልየ መሓልይ መመልከታቸውን ይናገራሉ። በእርግጥ መልእክቶቹን ከመጠን በላይ ምናባዊ ወይም እንደማይጨበጡ አድርገን ከመውሰድ መጠንቀቃችን እንዳለ ሆኖ፤ ከእግዚአብሔር ጋር ካለን ግኙነት ጋር መስተያየት የሚችለው የትኛው ዓይነት ግንኙነት ነው? ኢሳይ. 54:4-5፣ ኤር. 3:14፣ 2ቆሮ. 11:2።

3.ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ምሳ. 31፡26፣ መኃል. 5፡16፣ 25፡11። የጋብቻ ጓደኛችንን በማነጽ ወይም በማኮስመን ትዳራችንን በማጠንከር ወይም በማዳከም ረገድ ከአንደበቶቻችን የሚወጡ ቃላት ምን ያህል ወሳኝ ናቸው? በተጨማሪ ጥቅሶቹን ይመልከቱ፡ ያዕ. 1፡26፣ 3፡ 5-11።