የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ወቅታዊ እውነት በኦሪት ዘዳግም


4ኛ ሩብ ዓመት 2021

ከመስከረም 15-21

1ኛ ትምህርት

sep 25-oct 1




የኦሪት ዘዳግም መጽሐፍ መግቢያ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ኢሳ. 14:12–14፣ ሕዝ. 28:12–17፣ ዘፍ. 3:1–7፣ ዘፍ. 12:1–3፣ ሐዋ. 7:20–36፣ ዘፀ. 19:4–8።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “የማይወድ ግን እግዚአብሔርን አያውቅም፤ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና” (1ዮሐ. 4፡8)።

የ ዘዳግም መጽሐፍ እንደው ከምንም ተነስቶ አለመከሰቱ እሙን ነው። እንደ ማንኛውም በሕይወት ማዕቀፍ ውስጥ ያለ ነገር፤ ዘዳግም በአንድ ዐውድ ውስጥ ይገኛል። እንደ ማንኛውም በሕይወት ማዕቀፍ ውስጥ ያለ ነገር ያ ዐውድ--መጽሐፉ ምን እንደሚልና ምን ዓላማ እንዳለው ለማስተዋል ትልቅ ሚና ይጫወታል። ከዚህ መጽሐፍ አስቀድሞ በጣም ብዙ ታሪኮች ገቢራዊ ሆነው አልፈዋል። እነዚህን ያለፉ ክስተቶች የሚያብራራው ታሪክ የሚገልጸው ራሱን መጽሐፉን ብቻ ሳይሆን ዐውዱ የፈጠረውን ዓለም እና አካባቢያዊ ሁናቴ ጭምር ነው።

የመኪና የፊት መስታወት ዝናብ መጥረጊያን ጥቅምና አገልግሎትን ከመኪና ዐውደ ሀሳብ ውጪ ለመረዳት እንደሚያስቸግር ሁሉ፤ በተለይ አሁን ካለን የብርሃን ጭብጥ አንጻር (ዘዳግም እና ወቅታዊው እውነት) ታሪኩ ከሚነሣበት ዐውድ ውጪ፤ የዘዳግም መጽሐፍን ለማስተዋል አስቸጋሪ ይሆናል። በአንድ ወቅት አንድ ሰው 1,500 ገጾች ያሉትን፣ በታዋቂው ሩሲያዊው ደራሲ የተጻፈውን ጦርነት እና ሰላም የተሰኘ መጽሐፍ በሦስት ቀናት ብቻ አንብቦ ጨርሶ ነበር። ታዲያ አንባቢው ስለ መጽሐፉ ይዘት ተጠይቆ ሲመልስ፡ “በቃ! ስለ ሩሲያ ነው የሚናገረው።” አለ ይባላል።

ወደ ኦሪት ዘዳግም መጽሐፍ ከመምጣታችን በፊት የሺዎች ዓመታት ታሪክን በአንድ ሳምንት ለመሸፈን የምናደርገው ሙከራ ተመሳሳይ ነገር እንደ ማድረግ ይቆጠራል። ይሁን እንጂ ጎላ ብለው በቀረቡት ነጥቦች ላይ በማተኮር “በወቅታዊው እውነት” የበለጸገውን መጽሐፍ በተሻለ ለማስተዋል የሚያስችለንን አስፈላጊውን ዐውደ ሀሳብ ማየት እንችላለን።

መስከረም 16
Sep 26

ፍቅር--ፍቅር ተብሎ መጠራት ይችል ዘንድ፤


1 ዮሐ. 4፡8፡ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” ይላል። እነዚህ ሦስት ቃላት (በግሪክ አራት) የቱንም ያህል ቀላል ቢመስሉም ነገር ግን ከበስተ ኋላቸው የተሸከሙት ሀሳብ በጣም ጥልቅና ክብደት ያለው በመሆኑ አንደምታቸውን ማስተዋል ያዳግተናል። ቃላቶቹ እግዚአብሔር አፍቃሪ ነው ወይም እግዚአብሔር ፍቅሩን ገልጦ ያሳያል ወይም ደግሞ እግዚአብሔር የፍቅር መገለጫ ነው አይሉም። ይልቁንም እንደ ማንነቱ መለያ ባህሪ አድርገው በማቅረብ--ፍቅር ነው ይላሉ። በኃጢአት የወደቅን ሰብዓዊ ፍጡራን መሆናችንን ተከትሎ ካለን ዉሱን እውነትን የማገናዘብ አቅም አኳያ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” ማለት ምን ማለት እንደሆነ ሙሉ በሙሉ ለመረዳት አንችልም።

ነገር ግን እጅግ ግሩም የምሥራች የመሆኑን ነገር አብልጠን በእርግጠኝነት መረዳት እንችላለን። “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” በማለት ፋንታ “በጥላቻ የተሞላ ነው” ወይም “በቀለኛ ነው” ወይም ደግሞ “ግዴለሽ ነው” ቢል ኖሮ፤ ይህ ስለ እርሱ የተሰጠ መግለጫ ሊያስጨንቀን በቻለ ነበር። እናም “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” የሚለው እውነት አምላካዊው መንግሥት ፍጥረታትን ሁሉ የሚገዛበት መንገድ ያንን ፍቅር አንጸባራቂ ነው የሚለውን ጽንሰ ሀሳብ በተሻለ እንድናስተውል ይረዳናል። ፍቅር ምናልባትም የመሬት ስበት ካለው አቅም በላይ በሆነ አኳኋን በአጽናፈ ሰማይ ተንሰራፍቷል።

እግዚአብሔር ይወደናል፤ እኛም አጸፋዊ ምላሻችንን በመስጠት እነሆ እርሱን መውደዳችንን ማሳየት ይጠበቅብናል (ዘዳ. 6፡5)፣ ማር. 12፡30)። ፍቅር--ፍቅር ተብሎ መጠራት ይችል ዘንድ እነሆ በነጻ ሊሰጥ የግድ ይሆናል። እግዚአብሔር ፍቅርን ማስገደድ ስለማይችል፣ ይህን በሚያደርግበት ቅጽበት የእርሱ ፍቅር የመሆን ጉዳይ ያከትማል። በመሆኑም እግዚአብሔር ብልህ እና አስተዋይ አዕምሮ ያላቸውን ፍጥረታት--ለማፍቀር የሚያስችላቸውን ኃይል ሰጥቶ በሰማይም ሆነ በምድር በፈጠረበት ወቅት፣ እርሱን መልሰው እንዳይወዱ ሊያደርግ የሚችል አደጋ ሁል ጊዜ ነበር። ይህን ተከትሎ አንዳንዶች እርሱን ከመውደድ በመሰናከላቸው ታላቁ ተጋድሎ በሚል ስያሜ የምናውቀው ታሪክ ተጠነሰሰ።

የሚከተሉት ጥቅሶች ከፍቅር ጋር ለተያያዙ የነፃነት እና የሥጋት ዐውዶች ብቻ ትርጉም የሚሰጡት ለምንድን ነው? (ኢሳ. 14: 12–14፣ ሕዝ. 28:12-17፣ ራእ. 12: 7)።



ይህ መልአክ ማለትም ሉሲፈር ፍጹም በሆነው አምላክ የተፈጠረ ፍጡር ቢሆንም፣ ነገር ግን ክፋት በእርሱ ውስጥ ተገኝቶ እንደ ነበር የሚያወሳው ሕዝ. 28፡15 በተለይ በዚህ ዙሪያ ጥልቅ ምልከታ ይሰጠናል። ይህ የሆነው እርሱ ገና በመጀመሪያ ከዚያ በደል ጋር ስለተፈጠረ አልነበረም። ይልቁንም ሉሲፈር ማፍቀር ከሚያስችለው ኃይል ጋር ከመፈጠሩ ባሻገር እውነተኛ ግብረ-ገባዊ ነጻነትም ነበረው። ምንም እንኳ ይህ ሁሉ ቢሰጠውም (“እያንዳንዱ የከበረ ድንጋይ አስጊጦህ ነበር”) መልአኩ ሉሲፈር ግን ከዚህ የበለጠ ፈለገ። “በሰማይ ጦርነት” እስከተነሣበት ጊዜ ድረስ አንዱ ሌላውን እየነካ ጉዳዩ መቀጣጠሉን ተያያዘው።

ዛሬ በአንዳንድ የበለጸጉ አገራት በባለቤቱ የተሰጠውን ትዕዛዝ ተቀብሎ ከመተግበር ውጪ ምንጣፍ ላይ የማይጸዳዳ ወይም ወንበርና ጠረጴዛ በጥርሶቹ የማይፍቅ የውሻ ሮቦት መግዛት ይቻላል። ይሁን እንጂ ከዚህ “ውሻ” ጋር ይህ ነው የሚባል ትርጉም ያለው ግንኙነት ሊኖርዎ ይችላል? እግዚአብሔር እውነተኛ የፍቅር አጸፋ ሊሰጡት የሚችሉትን ፍጡራን ለምን እንደ ፈለገ ማስተዋል ይችሉ ዘንድ መልስዎ እንዴት ይረዳዎታል?





መስከረም 17
Sep 27

ውድቀት እና የጥፋት ውሃ


በአይዛክ ኒውተን አናት ላይ የወደቀውን የፖም ፍሬ ታሪክ እያንዳንዱ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሰምቷል ለማለት ያስደፍራል። እነሆ ተሳካ! ኒውተን የስበትን ኃይል አገኘ። ወሳኙ ነጥብ የፖሙ ፍሬ በትክክል በአናቱ ላይ መውደቁ ወይም አለመውደቁ ሳይሆን (ወደታች የወደቀ ሁሉ ስለ ስበት ስለሚያውቅ የስበት ኃይል ግንዛቤ የእርሱ ግኝት አይደለም።) ይልቁንም የኒውተን ታላቅ ማስተዋል ፖሙ ቁልቁል እንዲወርድ ያደረገው ያው ተመሳሳይ ኃይል (ስበት) ጨረቃ በምድር ዙሪያ በምሕዋሯ ተጠብቃ እንድትቆይ፣ ምድር በጸሐይ ዙሪያ በምሕዋሯ ተጠብቃ እንድትቆይ ወዘተ ማድረግ መቻሉን መገንዘቡ ነው።

ይህ በጣም አስፈላጊ ግኝት ነበር። ምክንያቱም ለብዙ ሺ ዘመን ብዙ ሰዎች ሰማያትን የሚቆጣጠሩት ሕግጋት ምድርን ከሚቆጣጠሩት ሕጎች የተለዩ ናቸው ብለው ያምኑ ነበር። ኒውተን ይህ እምነት የተሳሳተ መሆኑን አሳይቷል። ምንም እንኳ የኒውተን አስተዋጽኦ በተፈጥሮ ሕግ ምድብ ዙሪያ ቢሆንም፣ ነገር ግን ይኸው መርኅ ለሥነ ምግባር ሕግም ይሠራል። ሉሲፈርን ከሰማይ እንዲወድቅ የገፋፋው ተመሳሳይ ነጻነት፣ በፍቅር ውስጥ የሚገኝ ነጻነት-በተመሳሳይ ሰብዓዊው ፍጡር በምድር እንዲወድቅ ምክንያት ሆኗል።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 2:16-17፣ ዘፍ. 3:1-7። ፍጹም በሆነው አምላክ ተፈጥረው ፍጹም በሆነ አካባቢ ይኖሩ ስለነበሩት ፍጹም ሰዎች የሚናገሩት እነዚህ ጥቅሶች በፍቅር ውስጥ ያለውን ነጻነት ኃያል እውነት የሚያሳዩት እንዴት ነው?



ምንም እንኳ “የሰው ዐመፅ በምድር ላይ የበዛና የልቡም ሐሳብ ዘወትር ወደ ጥፋት ብቻ ያዘነበለ” መሆኑን ጌታ ቢመለከትም ከውድቀት በኋላ ይባስ ብሎ ነገሮች ወደ ከፋ ሁናቴ ተሸጋገሩ (ዘፍ. 6፡5)። ሰው የልቡ ሀሳብ መጥፎ ከሆነ ድርጊቱም ተመሳሳይ መሆኑ አያጠራጥርም። ይህ ሁናቴ ሰዎች እንደ አዲስ የሚጀምሩበትን ሁለተኛ ዕድል ጌታ እስከ ሰጣቸው እና--መላውን ዓለም በጥፋት ውሃ እስካወደመበት ጊዜ ቀጠለ። ይሁን እንጂ፣ የባቢሎን ግንብ ታሪክ እንደሚያሳየው (ዘፍ. 11፡1-9) ሰብዓዊው ፍጡር አሁንም እግዚአብሔርን ለመቃወም ደፍሮ የተነሣ ይመስላል።

“የማማው ግንባታ በከፊል ሲጠናቀቅ የተወሰነው ክፍሉ ለገንቢዎቹ መኖሪያነት የተመደበ ሲሆን ሌሎቹ ክፍሎች በውብ ቁሳቁሶች ተሟልተው እና አጊጠው ለጣኦቶቻቸው ማረፊያነት ውለው ነበር። ሕዝቡ በስኬታቸው በመደሰት የብር እና የወርቅ አማልክቶቻቸውን አመስግነው የሰማይ እና የምድር ገዢ ላይ ፊታቸውን አዞሩ።” (የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት፡ ገጽ 128)። በዚህም እግዚአብሔር ቋንቋቸውን ከመደበላለቅ ባሻገር የወደቀው ዘር በምድር ገጽ እንዲበተን አደረገ። ቀኑን ሙሉ ሲያስቡ የዋሏቸውን ነገሮች በማስታወሻ ላይ ይመዝግቡ። ይህ ስለ ገዛ ልብዎ ሁናቴ ምን ያስተምርዎታል?





መስከረም 18
Sep 28

የአብርሃም መጠራት


አብራም (ኋላ ላይ አብርሃም ተብሎ ተጠርቷል) ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰው በዘፍ. 11 የሴም ትውልድ ሀረግ መግለጫ ላይ ሲሆን፣ ሕዝቡ ከባቤል እንደተበተነ በቀጣይ ቀርቦ እናገኘዋለን። ስለ አብራም መጠራት የሚናገረውን ይህን ጥቅስ ያንብቡ፡ ዘፍ. 12፡1-3። ዛሬ ወደ ኋላ መለስ ብለን ከመስቀሉ በፊት፣ ከየሱስ ሞት እና ከወንጌል መሰራጨት በኋላ የሆነውን ስንመለከት፣ እግዚአብሔር በአብራም በኩል ለማድረግ የገባውን ቃል ኪዳን እንዴት እንረዳለን?



ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ በገላትያ አማኞች መሃል የነበረውን የተሳሳተ አስተምህሮ ለማሳየት ምዕመኑን ወደ ቀደመው የአብርሃም ጥሪ በማመላከት፣ ሁሌም ቢሆን የእግዚአብሔር ዓላማ ወንጌልን ለዓለም ማድረስ እንደነበረ ያሳያቸዋል። “እንግዲህ እነዚህ የሚያምኑት የአብርሃም ልጆች እንደ ሆኑ አስተውሉ። መጽሐፍ፣ እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንደሚያጸድቅ አስቀድሞ በማየት፣ ‘አሕዛብ ሁሉ በአንተ ይባረካሉ።’ በማለት ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ አስታወቀው። ስለዚህ በእምነት የሆኑት፣ የእምነት ሰው ከሆነው ከአብርሃም ጋር ብሩካን ናቸው።” (ገላ. 3፡7-9)።

የአብርሃም መጠራት በመጀመሪያ የተገለጸው በዘፍ. 12 ነው። የተቀረው አብዛኛው የዘፍጥረት ታሪክ ደግሞ በደም ስለሚዛመዱት የእርሱ ትውልዶች ታሪክ ይናገራል። አንዱን የከሸፈ ዘር ተከትሎ ብቅ የሚል ሌላ ዘር፣ አንዱን ስህተት የሠራ ቤተሰብ ተከትሎ የሚመጣ ሌላ ቤተሰብ በየተራ ቢፈራረቁም፣ ውሎ አድሮ ቃል ኪዳኑ ፍጻሜ ማግኘት ነበረበት--በሙሴ ጥሪ ወሳኝ ነጥብ ላይ እስከተደረሰበት ጊዜ ድረስ።

ሰማዕቱ እስጢፋኖስ ስለ ሙሴ እና ስለ እስራኤላውያን ከግብፅ በኃይል መውጣት የገለጸበትን የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ሐዋ. 7፡20-36። ይህ እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር ከገባው የመጀመሪያ ቃል ኪዳን ጋር እንዴት ይስማማል?



አለማወቅ፣ ስህተት እና በአጠቃላይ የእውነት ዕውቀት እጥረት በሞላበት ዓለም (ባለፉት ከሦስት ሺህ ዓመታት በሚልቁ ዘመናት ነገሮች ብዙም አልተለወጡም--አይደል?) እነሆ ጌታ የአብርሃም ዘር የሆነውን ሕዝቡን ከምድረ ግብፅ ጠራ። በእነርሱ ውስጥ የእውነትን ዕውቀት ብቻ ማለትም ስለ ራሱ ስለ ያሕዌ እና ስለ ደኅንነት እቅድ ብቻ ሳይሆን፣ ነገር ግን ስለ ተቀረውም ዓለም ዕውቀት ለማሰራጨት ፈልጎ ነበር።

ዛሬ እኛ እንደ ሰባተኛ ቀን የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂነታችን--ከተቀረው ዓለም ጋር ካለን ግንኙነት አኳያ ራሳችንን እንዴት እንመለከተዋለን? ማለትም በእኛና በጥንቷ እስራኤል መካከል ምን ተመሳሳይነት አለ? ከሁሉም በላይ ደግሞ ይህ መመሳሰል በእያንዳንዳችን ላይ (በግለሰብ ደረጃ) ምን ኃላፊነት ይጥልብናል?

መስከረም 19
Sep 29

ቃል ኪዳን በሲና ተራራ


የእያንዳንዱ ቤት ደጃፍ መቃንና ጉበን በደም እንዲቀባ ከተደረገበት--ቀይ ባሕርን አቋርጠው እስከ ተሻገሩበት ያለው የእስራኤላውያን በኃይል ከምድረ ግብፅ የመውጣት ትዕይንት--እንዴት ያለ ተሞክሮ ነው! ክስተቱን በገዛ ዐይኖቻቸው በተመለከቱ ወገኖች ላይ ይህ ተሞክሮ በጎ ተጽእኖ ማሳደሩ አንድና ሁለት የለውም። (ከግብፅ የበኩር ልጆች አንስቶ እስከ ባሕሩ ግርጌ የወደቁትን እግዚአብሔር ፍትሐዊ ፍርድ ይሰጣቸዋል።) ጌታ እንዲህ ሲል ተናግሯል፡ “በግብፅ ላይ ያደረግሁትን፣ በንስርም ክንፍ ተሸክሜ ወደ ራሴ እንዴት እንዳመጣኋችሁ እናንተ ራሳችሁ አይታችኋል።” (ዘፀ. 19፡4)።

ጌታ አንድን ሕዝብ ከሌላው መሃል ፈልቅቆ አውጥቶ ይህን አስደናቂና አስገራሚ የማዳን ሥራ ለምን ሠራ? ወይም ሙሴ ራሱ እንዲህ ሲል ተናግሮ ነበር፡ “‘ “አምላካችሁ እግዚአብሔር በዐይናችሁ እያያችሁ ለእናንተ በግብፅ እንዳደረገው ሁሉ በፈተና፣ በታምራዊ ምልክቶችና በድንቆች፣ በጦርነት፣ በጸናች እጅና በተዘረጋች ክንድ ወይም በታላቅና በአስፈሪ ሥራዎች ከሌላ ሕዝብ መካከል አንድን ሕዝብ የራሱ ለማድረግ የቻለ አምላክ አለን?” ’ ” (ዘዳ. 4፡34)።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፀ. 19፡4-8። ጌታ ሕዝቡን ከግብፅ ለምን ጠራ?



ጉዳዩ ያን ያህል ቀላል ነበር። እግዚአብሔር የአብርሃም፣ የይስሐቅ እና የያዕቆብ ትውልድ የሆነውን ሕዝብ ከምድረ ግብፅ ጠርቶ አውጣ። ጌታም እንዲህ ሲል ከዚህ ትውልድ ጋር ቃል ኪዳን ገባ፡ “ ‘ “እነሆ ከአሕዛብ ሁሉ የተወደደ ርስቴ ትሆናላችሁ፤ ምንም እንኳ ምድር ሁሉ የእኔ ብትሆንም” ’ ” (ዘፀ. 19፡5)። ይህ ግንኙነት ለቃል ኪዳኑ ወሳኝ ሚና ነበረው።

ሆኖም ይህ “የተወደደ ርስት” ጽንሰ ሀሳብ በቀላሉ በተሰሳተ መንገድ መስተዋል ይችል ነበር (በእርግጥም ሆኗል)። በተለይ የተለየ ሕዝብ የመሆናቸው ነገር በውስጣቸው ካለ ቅድስና ወይም ጻድቅነት የመነጨ አልነበረም። ይልቁንም ለእነርሱ በተሰጣቸው የእግዚአብሔር ጸጋ እና በተቸሯቸው አስደናቂ እውነቶች የተነሳ ነበር። እንደ “የመንግሥት ካህናት” ውሎ አድሮ ለዓለም የሚያሰራጯቸውን እነዚህን እውነቶች መከተል ነበረባቸው።

እግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ውል አካል የሆኑትን አስርቱን ትእዛዛት (ዘፀ. 20) የሰጣቸው ሲሆን፤ ከዚያም ይህ ቃል ኪዳን እንዲጸድቅ ሆነ። አዲስ የተሠራውን መሠዊያ በመሥዋዕት ደም ከረጨው በኋላ “የኪዳኑን መጽሐፍ ወስዶ ለሕዝቡ አነበበላቸው” (ዘፀ. 24፡7)። ሕዝቡም እንደሚታዘዙ በድጋሚ ተናገሩ።

“ሙሴ እያንዳንዱን የሕግ ትእዛዝ ለሕዝቡ ሁሉ ከተናገረ በኋላ… ደም ወስዶ በመጽሐፉና በሕዝቡ ላይ ረጨው፤ እንዲህም አለ፤ ‘እንድትጠብቁት እግዚአብሔር ያዘዛችሁ የኪዳኑ ደም ይህ ነው! ’ ” (ዕብ. 9፡19-20) ። ደሙ ምን ያመለክታል? ይህ ዛሬ ለእኛም ቢሆን በእጅጉ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?





መስከረም 20
Sep 30

ክህደት እና ቅጣት


“ሕዝቡም ሁሉ በአንድ ላይ ‘እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን’ ብለው መለሱ” (ዘፀ. 24፡3 በተጨማሪ ዘጸ. 24፡7) ። ምንም እንኳ ሕዝቡ በየጊዜው እነዚህን ቃላት መናገሩ ባያጠራጥርም፤ ቅዱስ የሆነው ታሪክ እንደሚያሣየው ድርጊታቸው በሚያሳዝን መልኩ በተደጋጋሚ ከንግግራቸው ጋር ይጋጭ ነበር። ምንም እንኳ የተመረጡ ሕዝቦች ቢሆኑም፣ ከጌታ ጋር በነፃነት ቃል ኪዳን ቢገቡም፣ በእነርሱ በኩል የነበረውን ውል ግን አልጠበቁም ነበር።

ቃል ኪዳኑን አስመልክቶ ለእስራኤል ወሳኝ የነበረው ክፍል ምን ነበር? (ዘፀ. 19:4-5)



እግዚአብሔርን እንዲታዘዙ፣ ሕጉን እንዲጠብቁ የቀረበው ጥሪ ከዛሬው የበለጠ ሕግ ጠባቂ ተብለው እንዲቆጠሩ ባያደርጋቸውም (ማቴ. 7፡24-27፣ ዮሐ. 14፡15፣ ያዕ. 2፡20፣ ሮሜ 6፡11-12) የእስራኤል ልጆች የእነርሱን ድርሻ በተደጋጋሚ ከመጠበቅ እየተሰናከሉ ኖረዋል። በርግጥ ገና ከጅምሩ፣ እዚያው እራሱ ሲና ተራራ ፊት ክህደት ፈጽመው ወደቁ (ዘጸ. 32፡1-6)። የሚያሳዝነው፣ ታማኝ አለመሆን ከወትሮው ያልተለመደ ክስተት ሆኖ መታየቱ ቀርቶ የተለመደ ተግባር መሰለ። በመሆኑም ወደ ተስፋይቱ ምድር በፍጥነት ከመግባት ይልቅ ለ40 ዓመታት በምድረ በዳ ተቅበዘበዙ።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘኁ. 14፡28-35። ይህ ሕዝብ ጌታ እንዲያደርግ ያዘዘውን ለማድረግ በመቃወሙ ምን ዓይነት ቅጣት ተጣለበት?



ያኔም እንደ ዛሬው አለመታዘዝ በአብዛኛው የሚከሰተው በቀጥተኛ አመጽ ብቻ ሳይሆን (ምንም እንኳን ይህም ቢከሰትም) እግዚአብሔር በሚነግረን ነገር ላይ እምነት ስለሚጎድለን ነው። ይህን በእስራኤላውያን የተፈጸመ ኃጢአት ይበልጥ የከፋ ያደረገው፣ እግዚአብሔር ራሱ እንደተናገረው እነዚህ ሰዎች “ክብሬን ደግሞም በግብፅና በምድረ በዳ ያደረግኋቸውን ታምራት አይተው” (ዘኁ. 14፡22) ሲያበቁ ተፈታተኑኝ በማለት ይናገራል። ምንም እንኳ በዐይኖቻቸው ያዩአቸውና የተለማመዷቸው ነገሮች ቢኖሩም፣ እግዚአብሔር እንደሚሳካላቸው ተስፋ ቢሰጣቸውም፣ ነገር ግን ጌታን ለመታዘዝና ምድሪቱን ለመውረስ እምቢ አሉ (ዘኁ. ምዕ. 13 እና 14)።

አብዛኛውን ጊዜ አለመታዘዝ የሚመጣው በእግዚአብሔር ቃል ላይ እምነት ስለሚጎድለን ነው--በሚል ከላይ ስለ ተባለው ነገር አሰብ ያድርጉ። ይህ እውነት የሆነው ለምንድን ነው? በእግዚአብሔር ላይ አብልጠን መታመን መማር የምንችለው እንዴት ነው?





መስከረም 21
Oct 1


ተጨማሪ ሀሳብ


በታላቁ ተጋድሎ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ጥልቅ እና አስገራሚ ሀሳብ የሚያስነብበውን እና እግዚአብሔር ፍቅር በመሆኑ ጽንሰ ሀሳብ ላይ የተመሰረተውን የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ጸሐፊ በሆኑት John Peckham የቀረበውን Theodicy of Love: Cosmic Conflict and the Problem of Evil (Grand Rapids, MI: Baker Academic, 2018) ይመልከቱ። ይህ ጽሑፍ ከአድቬንቲስት ውጪ ባለ ማተሚያ ቤት ቢታተምም፣ መልካም የመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀት እንዴት የታላቁን ተጋድሎ ተጨባጭ ሁኔታ በአምላካዊው ቃል መግለጽ እንደሚችል ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።

“በአጭሩ፣ የእግዚአብሔር ፍቅር (በትክክል የተስተዋለው) የዩኒቨርስ ውዝግብ ማዕከላዊ አካል ሲሆን፤ እግዚአብሔር ለፍቅር ያለው የማያወላዳ ቁርጠኝነት ክፉው እንዲኖር ለመፍቀዱ በቂ ምክንያት ይሰጣል ብዬ እሞግታለሁ።”—John C. Peckham, Theodicy of Love: Cosmic Conflict and the Problem of Evil (Grand Rapids, MI: Baker Academic, 2018), p. 4.

“እስራኤላውያን ለአርባ ዓመታት ወደ ከነዓን እንዳይገቡ የተሰጠው ትዕዛዝ ለሙሴ፣ ለአሮን እንደዚሁም ለካሌብና ለኢያሱ መራራ ሽንፈት ቢሆንም፤ መለኮታዊውን ውሳኔ ያለ አንዳች ማጉረምረም ተቀበሉ። ነገር ግን እግዚአብሔር በበጎ ያሰበላቸውን እንደ በደል ተመልክተው ቅሬታ ሲያቀርቡና ወደ ግብፅ እንመለሳለን ሲሉ የነበሩ ሁሉ፤ የናቋቸው በረከቶች ሲወሰዱባቸው አለቀሱ --በጥልቅም አነቡ።

የሚያማርሩበት አንዳችም ምክንያት ላልነበራቸው ለእነዚህ ሕዝቦች አሁን ደግሞ እግዚአብሔር የሚያለቅሱበት ምክንያት ሰጣቸው። ዕድሉ በተሰጣቸው ወቅት ስለ ኃጢአታቸው አዝነው ቢሆን ኖሮ ይህ ውሳኔ ባልተላለፈባቸው ነበር። ነገር ግን ሐዘናቸው ስለ ተሰጠው ፍርድ እንጂ ስለ ንስሐ ባለመሆኑ የተላለፈባቸውን ፍርድ ማስቀልበስ አልቻለም።” (የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት፡ ገጽ 446)


የመወያያ ጥያቄዎች



1.በመምረጥ ነፃነት እና በፍቅር ዙሪያ ተወያዩ። ፍቅር--ፍቅር ተብሎ መጠራት ይችል ዘንድ በነጻ ሊሰጥ የሚገባው ለምንድን ነው? በዓለም ላይ ካለው ሥቃይ አንጻር አንዳንዶች ፍቅር ይህን ያህል ዋጋ ሊሰጠው ባልተገባ ነበር ብለው ይሞግታሉ። ለዚህ ፈታኝ አባባል መልስዎ ምንድን ነው?

2.መታዘዝ የመላው መጽሐፍ ቅዱስ መልእክት አስኳል ከመሆኑ አኳያ--ሕጋውያንነት ምንድን ነው? ለእግዚአብሔር፣ ለቃሉ እና ለትእዛዛቱ ታማኝ ለመሆን የሚደረግ ሙከራ ወደ ሕጋውያንነት ወጥመድ መቀልበስ ሊያስከትሉ የሚችሉ ነገሮች ምንድን ናቸው?

3.በጥንቷ እስራኤል እና በሰባተኛው ቀን የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂዎች ቤተ ክርስቲያን መካከል ባለው ተመሳሳይነት ዙሪያ በማክሰኞ ጥናት መጨረሻ በተጠየቀው ጥያቄ ላይ ተወያዩ። እነዚህ ተመሳሳይነቶች ምንድን ናቸው? ሊያሳስቡን የሚገባውስ ለምንድን ነው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL