የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ወቅታዊ እውነት በኦሪት ዘዳግም


4ኛ ሩብ ዓመት 2021

ከመስከረም 22-28

2ኛ ትምህርት

Oct 2-oct 8




የሙሴ ታሪክ ትምህርት



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘዳ. 1–3፣ ዘፀ. 32:29–32፣ ዘኁ. 14፣ ኤፌ. 3:10፣ ዘፍ. 15:1–16፣ ዮሐ. 14:9።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “ሁሉም ከአንድ መንፈሳዊ ምግብ በሉ፤ ሁሉም ከአንድ መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፣ ይከተላቸው ከነበረው መንፈሳዊ ዐለት ጠጥተዋልና፤ ያ፣ ዐለት ክርስቶስ ነበረ።” (1ቆሮ. 10፡3-4)።

እ ነዚህ ከላይ የቀረቡት ሙሴ በዘዳ. 1፡1 የተናገራቸው ቃላት ሲሆኑ፤ የዘዳግም መጽሐፍ በዚህ መልኩ ይጀምራል። ምንም እንኳ ሙሴ ከእነዚህ የመክፈቻ ቃላት አንስቶ በሞአብ ምድር እስከ ሞተበት (ዘዳ. 34፡5) ጊዜ ድረስ በመጽሐፉ ገዝፎ ቢታይም፤ የዘዳግም መጽሐፍ (እንደ ተቀረው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል) የሚናገረው ስለ ጌታ የሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ የፈጠረን (ዘፍ. 1፣2፣ ዮሐ. 1፡1-3)፣ ደግፎ የያዘንና (ቆለ. 1፡15-17፣ ዕብ. 1፡3) የሚዋጀን (ኢሳ. 41፡14፣ ቲቶ 2፡14) አምላካችን ነው። እነዚህ በዘዳግም የምናገኛቸው ቃላት በገደምዳሜ የሚነግሩን--ጌታ በዚህ ወሳኝ የደኅንነት ታሪክ ወቅት እንዴት ሕዝቡን መፍጠር፣ ጠብቆ መያዝ እና መዋጀት እንደቀጠለ ነው።

የእስራኤል ልጆች በመጨረሻ ወደ ከነዓን ሊገቡ ባሉበት ወቅት ሙሴ በመላው መጽሐፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ የቀረበ ርዕሰ ነጥብ የሆነውን ታሪካዊ ትምህርት ይሰጣቸዋል፡ ጌታ ባለፉት ጊዜያት ያደረገላችሁን አስታውሱ! ይህ ምክረ ሀሳብ የላቀችው የተስፋይቱ ምድር ድንበር ላይ ለምንገኘው ለእኛ ትልቅ ትርጉም ሊኖረው ይገባል፡ “ያለፈውን ታሪካችንን መለስ ብለን ስንመረምር፣ ዛሬ የምንገኝበት ላይ ለመድረስ ለተጓዝነው ለያንዳንዱ የዕድገት ደረጃ… በክርስቶስ መሪነት ላይ ያለን መተማመን ያስደንቀኛል። ጌታ የመራንን መንገድ እና ባለፈው ታሪካችን ያስተማረንን ትምህርት እስካልረሳን ድረስ ስለ ወደፊቱ የሚያስፈራን አንዳች ነገር አይኖርም።”—Ellen G. White, Life Sketches, p. 196.

መስከረም 23
Oct 3

የሙሴ አገልግሎት


ሙሴ በመላው የመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች አሻራውን ትቶ እንዳለፈ ሆኖ ይሰማል። ምንም እንኳ ሙሴ እስከ ዘፀ. 2፡2 ባይጠቀስም የእግዚአብሔርን ሉአላዊ አምላክነት፣ የማንነታችንን መሠረታዊ ታሪክ--ማለትም እንዴት እንደመጣን፣ ነገሮች ዛሬ የያዙትን ክፉ ገጽታ ለምን እንደያዙና፣ እንዲህም ሆኖ ለምን ተስፋ ማድረግ እንደምንችል የሚያወሳውን የዘፍጥረት መጽሐፍ የጻፈው እርሱ ነው። ፍጥረት፣ ውድቀት፣ የመቤዠት ተስፋ፣ የጥፋት ውኃ፣ አብርሃም፣ ወንጌል--የሁሉም መነሾ ኦሪት ዘፍጥረት ሲሆን ደራሲው ደግሞ ነቢዩ ሙሴ ነበር። ይህ አንድ ሰው የሚኖረውን ተጽእኖ በበቂ ሁኔታ ለመገመት አስቸጋሪ ቢመስልም፣ የሆነው ሆኖ ይህ እንከን ሊያጣው የማይችል ግለሰብ ጌታን ስለወደደ እና እርሱን ለማገልገል ስለፈለገ ለእግዚአብሔር መትጋት ችሏል።

ከወርቁ ጥጃ ክፉ ኃጢአት በኋላ በጌታና በሙሴ መካከል የተደረገውን ውይይት የሚዘግበውን ዘፀ. 32፡29–32 ያንብቡ። ይህ ታሪክ ስለ ሙሴ ባህሪ ምን ያስተምረናል? የቱንም ዓይነት እንከን ሊኖርበት ቢችልም እንኳ፣ ጌታ በእንዲህ ያለ ብርቱ መንገድ ሊጠቀምበት የቻለው ለምንድን ነው?



ምንም እንኳ ሙሴ ከኃጢአተኛው ሕዝብ ጋር ምንም ግንኙነት ባይኖረውም፣ ስለ እነርሱ ሲል ነፍሱን ለማጣት እንኳ ሳይሳሳ ለዚህ ኃጢአተኛ ሕዝብ አማልዶ ነበር። ሙሴ በዘፀ. 32፡32 “ኃጢአታቸውን ይቅር በል” ብሎ እግዚአብሔርን የጠየቀበት ቃል- “ተሸከም” የሚል ትርጉም ያለውን ግስ ይዟል። በዚህም ሙሴ የኃጢአትን ክብደት እና ለማስተሰረይ ምን እንደሚጠይቅ በመገንዘቡ እግዚአብሔርን ኃጢአታቸውን “ተሸከም”ሲል ይጠይቀዋል። ይህ የሆነበት ምክንያት ያ የሠሩት ኃጢአትም ሆነ ማንኛውም በደል ውሎ አድሮ ይቅር ሊባል የሚችለው በዚህ መንገድ ብቻ ስለሆነ ነው።

እነሆ በእነዚያ የቀደሙ የመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች እግዚአብሔር ራሱ በየሱስ አካል የኃጢአታችንን መቀጮ ሙሉ በሙሉ የሚሸከምበት ብርቱ መግለጫ ተሰጥቶናል--ለመንግሥቱ እና ለሕጉ መርኅዎች በታማኝነት ለሚጸኑ የሰው ልጆች እግዚአብሔር አስቀድሞ የወሰነው የማዳን መንገድ! ጴጥሮስ ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ እንዲህ ሲል ስለ የሱስ ጽፏል፡ “ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት መስቀል ላይ ተሸከመ፤ በእርሱ ቁስል እናንተ ተፈውሳችኋል” (1ጴጥ. 2፡24)። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በሙሴ ታሪክ እንደቀረበው፣ እርሱ በኃጢአት ስለ ወደቁት ሕዝቦች በሚሰጠው አጸፋዊ ምላሽ የሱስ ለእኛ የሚያደርግልንን የሚያበስረውን (ዕብ. 7፡25) የአማላጅነት ሚና ይዞ ብቅ ለማለት ሲሞክር እንመለከታለን።

ስለ ሕዝቡ ሲል ነፍሱን ለማጣት ፈቃደኛ ነውን? እነዚህ ቃላት ምን ትርጉም እንዳላቸው ይበልጥ ለማሰብ ይሞክሩ። ሌሎችን በእውነት መውደድ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ከዚህ ምን እንማራለን?

መስከረም 24
Oct 4

ፍጻሜ ያገኘው ትንቢት


ዘመናዊው ሳይንስ እውነት አድርጎ ለማወጅ የሚሞክራቸው አንዳንድ ስህተቶች ቢኖሩም፤ (ዩኒቨርስ “ፍጹም ከምንም” ተነስቶ በራሱ የመጣ አካል ነው ወይም በምድር ላይ ያሉ ሕይወት ያላቸው ነገሮች በሙሉ ቀላልና ውስብስብነት ከሌላቸው ንጥረ ነገሮች በአጋጣሚ የተከሰቱ ናቸው።) ስለ አምላካዊው የመፍጠር ኃይል አንዳንድ አስገራሚ ግንዛቤዎችን ያስጨብጠናል። የበርካታ ተፈጥሯዊው ዓለም ገጽታዎች ስምምነት፣ ሚዛናዊነትና ትክክለኛነት-ከኃጢአት ውድቀት በኋላ የሚገኙም እንኳ ሆነው፣ እነዚህን ነገሮች የሚያጠኗቸውን አብልጠው ማስደመማቸውን ቀጥለዋል።

እግዚአብሔር ግዑዝ ለሆኑ ነገሮች ይህን ያህል ጠንቃቃ መሆን ከቻለ ለመንፈሳዊ ነገሮችም እንዲሁ መሆን ይችላል። በመሆኑም በዘዳግም የመጀመሪያ ቁጥሮች ላይ የእርሱን አስገራሚ ትክክለኛነት የበለጠ ማየት እንችላለን።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘዳ. 1፡1-6። ዘዳ. 1፡3 ስለ “አርባኛው ዓመት” የመናገሩ ትንቢታዊ ጠቀሜታ ምንድ ነው?



ሙሴ ከቃዴስ በርኔ ሰላዮችን መልምሎ ምድሪቱን እንዲሰልሉ ሲልክ ሕዝቡ ምድሪቱን እንዲወርሱ የቀረበውን ጥሪ ተቃወሙ--ከዚያስ ምን ተከሰተ? ተስፋ ባደረጉት መሠረት ወደ ተስፋይቱ ምድር እንደማይገቡ ተነገራቸው። ታዲያ ከመግባታቸው በፊት ምን ያህል ጊዜ መጠበቅ ይኖርባቸው ይሆን? “ምድሪቱን ለመሰለል በቆያችሁበት አርባ ቀን ልክ እያንዳንዱ ዓመት እንደ አንድ ዓመት ተቆጥሮ ስለ ኃጢአታችሁ አርባ ዓመት መከራ ትቀበላላችሁ” (ዘኁ. 14፡34) ።

ስለሆነም እግዚአብሔር በነገራቸው መሠረት ልክ በአርባኛው ዓመት የሆነው በዘዳግም መጽሐፍ ሰፍሯል። በሌላ አነጋገር አምላካዊው ትንቢታዊ ቃል ልክ እንደ ራሱ እንደ እግዚአብሔር የታመነ ነው። እናም በዚሁ የዘዳግም መጽሐፍ መግቢያ ላይ የምንመለከታቸው ቁጥሮች ይህንኑ ታማኝነቱን ይበልጥ የሚያጠናክሩልን ማስረጃዎች ናቸው። እግዚአብሔር አደርገዋለሁ ብሎ የተናገረውን የሚያደርግ አምላክ ነው።

በእርግጥ፣ ይህ እግዚአብሔር በተናገረው መሠረት የተፈጸመ ብቸኛው የትንቢታዊ ጊዜ አይደለም። ዛሬ ከምንገኝበት ጊዜ ወደ ኋላ መለስ ብለን ዳን. 9፡24-27 ስንመለከት የሱስ ወደዚህ ምድር የመጣበት ዘመን ጌታ በተናገረው መሠረት ፍጻሜ እንዳገኘ እንረዳለን። “ለዘመን፣ ለዘመናት፣ ለዘመን እኩሌታ” (ዳን. 7፡25፣ በተጨማሪ ራእ. 12፡6፣ 14፣ ራእ. 13፡5) በታሪክ ፍጻሜ ማግኘቱንና የዳን. 8፡14 የ2,300 ቀናት ትንቢትም መፈጸሙን መመልከት እንችላለን። የዳን. 2፣ 7፣ 8 ትንቢቶች የዓለምን ታሪክ በትክክል ከመተንበያቸውና ከትክክለኛ የጊዜ አላባነታቸው በተጨማሪ፣ እግዚአብሔር የወደፊቱን አስቀድሞ የሚያውቅ፣ የሚቆጣጠርና የሚታመን አምላክ መሆኑን የሚያረጋግጡ በርካታ ማስረጃዎች ሰጥተውናል።

ጌታ ልክ በተናገረው መሠረት እነዚህን ያለፉ ትንቢቶች በታማኝነት ወደ ፍጻሜ እንዳመጣቸው መመልከት እንችላለን። ይህ እርሱ አስቀድሞ ይሆናሉ ብሎ በተናገራቸው--ማለትም ወደፊት የሚከሰቱ ነገሮችን አስመልክቶ በእርሱ መተማመን እንዲኖረን የሚያደርገው እንዴት ነው?

መስከረም 25
Oct 5

ሺህ ጊዜ ያብዛችሁ


እስራኤላውያን በምድረ በዳ ረጅም ጉዞ ካደረጉ በኋላ እርሱ በጌታ ቦታ ሆኖ (ሙሴ በእርግጥም ከነቢይ በላይ ነቢይ ነበር) እንዲህ አላቸው፡ “እነሆ፤ ይህችን ምድር ሰጥቻችኋለሁ፤ እንግዲህ እግዚአብሔር ለአባቶቻችሁ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ከእነርሱም በኋላ ለዘሮቻችሁ ሊሰጥ የማለላቸውን ምድር ገብታችሁ ውረሱ።” (ዘዳ. 1፡8)።

በመቀጠል ምን እንደተከሰተ ልብ ይበሉ፡ ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘዳ፣ 1፡9-11። የእነዚህ ቃላት አንደምታ ምንድን ነው--በተለይ በቃዴስ በርኔ አመጽ ምክንያት በእግዚአብሔር ቅጣት ከመቀበላቸው አኳያ?



እዚህ ላይ የእግዚአብሔር አምላክን ቸርነት የሚያሳይ ሌላ ምሳሌ እንመለከታለን። በምድረ በዳ በተንከራተቱባቸው በእነዚያ ጊዜያቶች ተባርከው ነበር፡ “ ‘በምድረ በዳ አርባ ዓመት መገብሃቸው ምንም ያጡት አልነበረም፤ ልብሳቸውም አላላቀም፣ እግራቸውም አላበጠም” (ነኽ. 9፡21)። ሙሴ ለሕዝቡ ያለውን ፍቅር በድጋሚ በመግለጽ እግዚአብሔር ቀደም ሲል ከባረካቸው ሺህ ጊዜ እጥፍ እንዲያበዛቸው ጠየቀ።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘዳ. 1፡12-17። የእግዚአብሔርን ቀጥተኛ መባረክ ውጤት ተከትሎ ምን ተከሰተ? ሙሴ ራሱን ከሁኔታው ጋር ለማስማማት ምን ዓይነት ቅደም ተከተሎችን ተግባራዊ አደረገ?



ጌታ በመካከላቸው በኃይል በተገለጸበት በዚያ ጊዜም እንኳ የድርጅት፣ የመዋቅር፣ የተጠያቂነት ሥርዓት ያስፈልግ ነበር። እስራኤል ቃሃል ማለትም የተደራጀ ጉባዔ (ዘዳ. 31፡30) የነበረ ሲሆን፣ ይኸውም የአዲስ ኪዳኗ ኤክለሽያ “ቤተ ክርስቲያን” ቀዳሚ ጥንስስ ነበር (ማቴ. 16፡18)። ምንም እንኳ ጳውሎስ ከዚህ በተለየ ዐውድ ቢሠራም፣ ከአይሁድ ሥረ መሰረቱ ፈጽሞ የራቀ አልነበረም። የቤተ ክርስቲያን አካል በአግብባቡ ይሠራ ዘንድ በተለያየ ሚና ብቃት ያላቸው ሰዎች ማስፈለጋቸውን በዘዳግም ቃሃል የተደራጀ ስብስብ የተመለከትነው ዓይነት ሁናቴ በ1ቆሮ. ምዕ. 12 በግልጽ እንመለከታለን። የዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን እንደ ጥንቱ ቃሃል በስጦታቸው መሠረት የተለያዩ ኃላፊነቶችን የሚወጡ ሰዎች ያሏት የተዋሃደ አካል መሆን ያስፈልጋታል።

ምንም እንኳ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች “በተደራጀ” ኃይማኖት ላይ ምሬታቸውን ሲያሰሙ ብንመለከትም (ምርጫቸው ምንድን ነው--ያልተደራጀች ቤተ ክርስቲያን?) የእግዚአብሔር ቃል፣ በተለይም አዲስ ኪዳን ለተደራጀችው እንጂ ሌላው ዓይነት ዕውቅና አይሰጥም።

መስከረም 26
Sep 26

ቃዴስ በርኔ


በዘዳግም መጽሐፍ የመጀመሪያ ክፍሎች የቀረበው ቃዴስ በርኔ በፍጹም ከሀሳብ የሚጠፋ አይደለም። ይህ አሳዛኝ ታሪክ፣ እስካሁን እንዳየነው የዘዳግም መጽሐፍን ታሪካዊ ዳራ በቅርበት ያስቀመጠ ሲሆን፣ በጥልቀት መመርመሩ ተገቢ ይሆናል።

ጥቅሱን ያንብቡ፡ ዘኁ. 14። የሰላዮቹን ዘገባ የሰማው ሕዝብ ምን ዓይነት ምላሽ ሰጠ? ምላሻቸው ያስከተለው ውጤት ምን ነበር? (ዘዳ. 1፡20-46)።



ከዚህ ታሪክ ብዙ ጠቃሚ ትምህርቶችን ማግኘት እንችላለን። ነገር ግን በመጽሐፉ እንደገና የሚከሰተው አንድ አስፈላጊ ትምህርት በተጨማሪ በዘኁ. 14 መገኘት ይችላል። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘኁ. 14፡11፡20። ምንም እንኳ ሙሴን እንደገና በአማላጅነት ሚና ብናየውም፣ ጌታ ሕዝቡን ሊያጠፋ እንደማይገባ አስመልክቶ ከእርሱ ጋር ያደረገው ሙግት አንደምታው ምንድን ነው?



ሙሴ ለእግዚአብሔር ስለነገረው ነገር አሰብ ያድርጉ። ይህን ብታደርግ በግብፃውያንና በአካባቢው ባሉ ሌሎች ሕዝቦች ፊት እንዴት ልትታይ እንደምትችል ተመልከት። ይህ ነጥብ አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር ሊያደርግ የፈለገው ማንኛውም ነገር ውሎ አድሮ ለእስራኤል ሲባል ብቻ አልነበረም--ለመላው የሰው ዘር ጭምር እንጂ። የእስራኤል ሕዝብ የዓለም ብርሃን መሆን ነበረበት። እነዚህ ሰዎች ባመለኳቸው ከንቱ ጣዖቶች ሳይሆን--በእውነተኛው አምላክ ስለሚገኘው ፍቅር፣ ብርታት እና ደኅንነት ለጥንቱ ዓለም ምስክር መሆን ነበረባቸው።

ለነገሩ ሙሴ እንዳለው--ጌታ ሕዝቡን ከምድረ ገጽ ብያጠፋ ከዚያ ምን ሊባል ይችላል? “እግዚአብሔር ለዚህ ሕዝብ ይሰጠው ዘንድ በመሐላ ቃል ወደገባለት ምድር ሊያስገባው ባለመቻሉ በምድረ በዳ ፈጀው” (ዘኁ. 14፡16) በሌላ አነጋገር እዚህ ላይ የምናየው ጭብጥ የመላው መጽሐፍ ቅዱስ ጭብጥ ሲሆን፣ ይኸውም እግዚአብሔር በሕዝቡ ፊት ሊከብር የሚገባው አምላክ የመሆኑ ጽንሰ ሀሳብ ነው። የእግዚአብሔር ታላቅ ክብር፣ መልካምነት፣ ፍቅርና ኃይል በሕዝቡ አማካይነት በሚሠራው ሥራ በቤተ ክርስቲያኑ ሊገለጥ ይገባል። እርግጥ ነው፣ እርሱ ይህን ያደርግ ዘንድ ሁሌም ቢሆን ሕዝቡ ምቹ ሁናቴ ባይፈጥርለትም ነገር ግን ውሎ አድሮ እግዚአብሔር በምድር ላይ በሚያከናውናቸው ተግባራት ይከብራል።

ጥቅሱን ያንብቡ፡ ኤፌ. 3፡10። ጳውሎስ ምን እያለ ነው? ይህ እንዴት መሆን ይችላል? “ብዙ ገጽታ ያለው የእግዚአብሔር ጥበብ” በሰማያዊ ስፍራ ላሉ የሚታወቀው እንዴት ነው? ይህን በማምጣቱ ረገድ እንደ ግለሰብ ምን ሚና ይኖረናል?

መስከረም፡27
Sep 27

የአሞራውያን ኃጢአት


ሙሴ በዘዳ. ምዕ. 2 እና 3 የእስራኤላውያንን ታሪክ መተረኩን በመቀጠል በእግዚአብሔር በጎነት እንዴት ጠላቶቻቸውን እንዳሸነፉ ይነግረናል። እነዚህ ሕዝቦች ለእግዚአብሔር ታማኝ በነበሩበት ወቅት እጅግ ረጃጅምና ግዙፍ (ዘዳ. 2፡11፣20፣ ዘዳ. 3፡13) በሆኑት ዝርያዎች ላይ ሳይቀር ድል ይሰጣቸው ነበር። የእነዚህን ሰዎች መጥፋት አስመልክቶ፣ ሁኔታው ቢያንስ ጨረፍ አድርገነው ልናልፍ ወደ ሚገባ አስቸጋሪ ርዕሰ ጉዳይ ይመራናል። የእስራኤል ልጆች አንድን ከተማ ለመውጋት በሚዘምቱበት ጊዜ በመጀመሪያ የሰላም ጥሪ ማስተላለፍ ይጠበቅባቸዋል (ዘዳ. 20፡10-11)።

ሆኖም ሕዝቡ ጥሪውን ሳይቀበል ሲቀር አንዳንዴ እስራኤላውያን ዘልቀው በመግባት ሴቶችንና ሕፃናትን ሳይቀር ይደመስሱ ነበር። “ ‘አምላካችን እግዚአብሔር በእጃችን ላይ ጣለው፤ እኛም እርሱን ከወንድ ልጆቹና ከመላው ሰራዊቱ ጋር አንድ ላይ መታነው። በዚያን ጊዜ ከተሞቹን በሙሉ ወስደን የሚኖሩባቸውን ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆቻቸውን ጭምር ፈጽመን አጠፋናቸው፤ አንዳቸውንም በሕይወት አላስቀረንም።” (ዘዳ. 2፡33)።

አንዳንዶች እነዚህ ታሪኮች እውነትነት ሊኖራቸው አይችልም ለማለት ቢዳዳቸውም፤ እኛ ሰባተኛ ቀን የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂዎች ግን “ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው፤ ለማስተማር፣ ለመገሰጽ፣ ለማቅናት በጽድቅም መንገድ ለመምከር ይጠቅማሉ” (2ጢሞቴ. 3፡ 16) ብለን እናምናለን። በመሆኑም እነዚህን ክስተቶች አስመልክቶ ከበድ ያለው ጥያቄ አሁንም በእንጥልጥል አለ።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 15፡1-16። እግዚአብሔር በዘፍ. 15፡16 አብርሃምን ምን ብሎት ነበር? በዚህ አስቸጋሪ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ምን ብርሃን ይፈነጥቅልናል?



ከእነዚህ አረማዊ ሕዝቦች መካከል አብዛኞቹ ከረጅም ጊዜ አስቀድሞ ተገቢነት ያለው አምላካዊ ቁጣና ቅጣት ሊቀበሉ የሚችሉ እጅግ ጨካኝና አረመኔዎች መሆናቸው ፈጽሞ አያጠያይቅም። ይህ እውነት ነው። አካሄዳቸውን ይለውጡ እንደሆነ እግዚብሔር በትዕግሥት ቢጠብቃቸውም እንኳ አለመለወጣቸው-- 24 - ህፃናትን ጨምሮ ሰዉን ሁሉ ስለ መፍጀት የተስተዋለውን አስቸጋሪ ተጨባጭ እውነታ አይለውጥም። (እርግጥ ነው በእስራኤላውያን ከተገደሉት ህፃናት ይልቅ በጥፋት ውሃ ያለቀው ቁጥር የትዬለሌ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል።)

ለአሁን፣ ክስተቶቹን አስመልክቶ ከአጠቃላዩ ዐውድ አኳያ ያለንን ውሱን መረጃ ከግምት በማስባት፣ ይህን አስቸጋሪ እውነታ ተቀብለን በሌሎች በርካታ መንገዶች በተገለጠው አምላካዊ ቸርነት መታመን ብቻ ይኖርብናል። እምነት ውብ በሆነ ቀን አስደናቂ ትዕይንት የሚስተዋልበት እና ለጆሮ የሚጥሙ ድምጾች የሚሰሙበት ተፈጥሮ ውስጥ እግዚአብሔርን መውደድ ብቻ አይደለም። ይልቁንም ሙሉ በሙሉ ልናስተውለው በማንችለው ሁኔታ ውስጥም ቢሆን በእርሱ ላይ መታመን ነው።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 1ቆሮ. 10፡1-4፣ ዮሐ. 14፡9። ስለ አምላክ ካለን ግንዛቤ ጋር የሚጣረሱ የሚመስሉ አስቸጋሪ ሁናቴዎችን ብናይ እንኳ፣ እነዚህን እና ሌሎች እነዚህን የመሳሰሉ ጥቅሶች በእግዚአብሔር ፍቅር፣ ፍትሐዊነት እና መልካምነት መታመን እንድንችል እንዴት ይረዱናል?

መስከረም 28
Sep 28


ተጨማሪ ሀሳብ


እስራኤላውያን በእነዚህ ብሔራት ላይ በፈጸሟቸው ድርጊቶች ዙሪያ የሚነሱ ከባድ ጥያቄዎችን ለመመለስ አንድ የሥነ መለኮት ምሁር የሞከሩበት መንገድ እንደሚከተለው ቀርቧል። “እግዚአብሔር የሁሉ ነገር ፈጣሪ እና በሁሉ ላይ ሉዓላዊ ገዥ አምላክ እንደመሆኑ፤ ከማንም ጋር የፈለገውን ማድረግ፣ ብሎም ይህን በማድረጉም ትክክል መሆን ይችላል… “የእግዚአብሔር መንገድ ምስጢራዊ ነው። እርሱን ፈጽሞ ሙሉ ለሙሉ ልናስተውለው ስለማንችል በአእምሯችን ውስጥ ሊኖሩ በሚችሉ ጥያቄዎች ዘና ማለት እንችል ይሆናል። ኢሳ. 55፡8-9 ጥቂት ማጽናኛዎችን ይሰጠናል።

“መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ከነዓናውያን ከሚሰጠን ምስል አኳያ እነዚህ ሕዝቦች እጅግ ክፉዎች ነበሩ፤ የእነርሱ መደምሰስ ስለ ኃጢአታቸው የደረሰባቸውን አምላካዊ ፍርድ አመላካች ነበር። እግዚአብሔር በከነዓናውያን ላይ ውድመት ሲያደርስ የመጀመሪያውም ሆነ የመጨረሻው አልነበረም።

ከዘፍ. ምዕ. 6-9 በተገለጸው መሠረት በከነዓናውያን እና በተቀረው ሰብዓዊ ፍጡር ፍርጃ መካከል ያለው ልዩነት (ከኖኀ ቤተሰብ በስተቀር) የቁጥር እና የወኪል ባህሪን ያካትታል… “እስራኤላውያን ባዕዳን ጠላቶቻቸውን ሙሉ በሙሉ እንዲደመስሱም ሆነ ይህን በፖሊሲ ደረጃ ይተገብሩ ዘንድ እግዚአብሔር ፈጽሞ አስቦ አያውቅም። የጥቃት ዒላማ የሆኑትን ሕዝቦች በዘዳ. 7፡1 ወስኖ አስቀምጧል። ከዚህ ውጪ በአራማውያን ወይም ኤዶማውያን ወይም ደግሞ በግብፃውያን እንዲሁም ከእነዚህ ሌላ በማናቸውም ሕዝቦች ላይ እነዚህን ፖሊሲዎች መከተል አልነበረባቸውም (ዘዳ. 20፡10-18)።

“ከነዓናውያን በስተ መጨረሻ ሁሉም ኃጢአተኞች የሚደርስባቸውን ቅጣት ይኸውም አምላካዊውን ፍርድ ተቀበሉ… “እግዚአብሔር ከነዓናውያንን መደምሰሱ በደኅንነት ታሪክ እንደ ትልቅ እርምጃ የሚታይ ነበር… “ከነዓናውያን በአጠቃላይ የአምላካዊው ፍርድ ዒላማ ቢሆኑም ቢያንስ ከአርባ ዓመታት አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ነበር። (see Rahab’s confession in Josh. 2:8–11).”—Daniel I. Block, The NIV Application Commentary: Deuteronomy (Grand Rapids, Mich.: Zondervan, 2012), pp. 98, 99.


የመወያያ ጥያቄዎች



1.ለጥያቄዎቻችን ሁሉ መልስ ማግኘት የምንችልባቸው አንድ ሺህ ዓመታት እንዳሉን ስለሚጠቁመው ስለዚህ ዘመን (አንድ ሺህ ዓመት) አሰብ ያድርጉ። አሁን የቱንም ዓይነት ከባድ ጥያቄዎች ሊኖሩን ቢችሉም ይህን ማስተዋላችን በእግዚአብሔር ላይ መታመን እድንማር እንዴት ይረዳናል?

2.ስለ ወደፊቱ ጊዜ በእርሱ ላይ እምነት መጣል እንዲማሩ የሚረዱዎ ቀደም ሲል በእግዚአብሔር ምሪት ያገኙባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው? ጌታ በሕይወታችን ውስጥ እንዴት እንደሠራ መዘንጋት የሌለብን ለምንድን ነው?

3.ሙሴ ስለ ሕዝቡ ሲል የገዛ ነፍሱን ለማጣት ፈቃደኛ በሆነበት ነጥብ ዙሪያ በእሁድ ጥናት መጨረሻ ላይ የቀረበውን ጥያቄ በሰንበት ትምህርት ጥናት ክፍለ ጊዜ ተመልከቱ። ይህ ሊኖረን የሚገባ ትክክለኛ መንፈስ ነውን? በተለይ የአንድን ሰው ነፍስ ለመዋጀት ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለ ከግምት ስናስገባ?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL