የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ወቅታዊ እውነት በኦሪት ዘዳግም


4ኛ ሩብ ዓመት 2021

ከመስከረም 29 -ጥቅምት 5

3ኛ ትምህርት

oct 9-Oct 15




ዘላለማዊው ኪዳን



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘፍ. 12:1–3፣ ሮሜ. 4:1–5፣ ዘፀ. 2:24፣ ዘዳ. 5:1–21፣ ዘዳ. 26:16–19፣ ዘዳ. 8:5፣ ማቴ. 28:10.


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “ ‘በእኔና በአንተ፣ ከአንተም በኋላ ከዘርህ ጋር ከትውልድ እስከ ትውልድ የዘላለም ኪዳኔን እመሠርታለሁ፤ በዚህም የአንተና ከአንተም በኋላ የዘርህ አምላክ እሆናለሁ’ ” (ዘፍ. 17፡7)።

“ከ ዚያም ሌላ መልአክ በሰማይ መካከል ሲበር አየሁ፤ እርሱም በምድር ላይ ለሚኖሩ ለሕዝብ፣ ለነገድ፣ ለቋንቋና ለወገን ሁሉ የሚሰብከውን የዘላለም ወንጌል ይዞ ነበር” (ራእ. 14፡ 6)። “ዘላለማዊ ወንጌል”--እንደ ሁልጊዜ ዘላለማዊ፣ ሁሌም በዚያ የነበረና በክርስቶስ የሱስ “ከዘመናት በፊት” የተሰጠን መሆኑን ልብ ይሏል (ቲቶ 1፡2)።

ከዚህ አኳያ መጽሐፍ ቅዱስ በሌላ ጊዜ ስለ “ዘላለማዊ ኪዳን” መናገሩ አያስደንቅም (ዘፍ. 17፡ 7፣ ኢሳ. 24፡5፣ ሕዝ. 16 60፣ ዕብ. 13፡ 20)። የወንጌል መሠረታዊ ነጥብ ኪዳን--የኪዳን መሠረታዊ ነጥብ ደግሞ ወንጌል እንደመሆኑ፡ እግዚአብሔር ከሚያድን ጸጋውና ፍቅሩ የተነሣ የማይገባዎትንና በራስዎ ፍጹም ሊያገኙት የማይችሉትን ደኅንነት አቅርቦሎታል። “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህና በፍጹም ኀይልህ ውደድ” (ማር. 12፡30) ተብሎ እንደተጻፈው እርስዎም ለሕጉ ተገዢ በመሆን የፍቅር አጸፋዊ ምላሽ ይስጡ፡ “እግዚአብሔርን መውደድ ትእዛዙን መፈጸም ነውና” (1ዮሐ. 5፡3)። በዚህ ሳምንት ቃል ኪዳኑ እና በውስጡ የያዘው ሁሉ የተገለጠበትን-በዘዳግም መጽሐፍ የቀረበውን የቃል ኪዳኑን ሃሳብ እንመለከታለን።

መስከረም 30
Sep 30

ኪዳኑ እና ወንጌል


ኪዳን እና ወንጌል በመላው የመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች በአንድነት ቀርበው ይታያሉ። ምንም እንኳ የቃል ኪዳን ጽንሰ ሀሳብ ከእስራኤል እንደ ሕዝብ መመስረት አስቀድሞ የነበረ ቢሆንም (ለምሳሌ ከኖህ ጋር የተገባው ኪዳን)፤ እንዲሁም የቃል ኪዳኑ የተስፋ ቃል የተሰጠው ከእስራኤል አስቀድሞ ቢሆንም፤ የኃይማኖት አባቶች ከነበሩት ወላጆቻቸው ጋር ጀምሮ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ባደረገው መስተጋብር በጉልህ ተገልጾ ነበር። ገና ከመጀመሪያውም ቢሆን የቃል ኪዳኑ ማዕከላዊ እውነት ወንጌል ነበር፡ መዳን በእምነት ብቻ!

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 12፡1-3፣ ዘፍ. 15፡5-18 እና ሮሜ 4፡1-5። ለአብርሃም የተሰጠው ኪዳናዊ የተስፋ ቃል ምን ነበር? ወንጌል በዚያ ኪዳናዊ የተስፋ ቃል የተገለጠው እንዴት ነበር?



አብርሃም እግዚአብሔርን ብሎም አምላካዊውን የተስፋ ቃል በማመኑ ጻድቅ ሆኖ ተቆጠረ። ይሁን እንጂ ይህ ስለ እርሱ የተሰጠ መግለጫ ርካሽ ጸጋ አልነበረም። በዘፍ. 22 ሞሪያ ተራራ ላይ እንደታየው አብርሃም በእርሱ በኩል የነበረውን የኪዳን ክፍል በመታዘዝ ጠብቆ ለማቆየት ፈለገ--“ጽድቅም ሆኖ ተቆጠረለት” (ሮሜ 4፡5)። ይህ ከሆነ ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ-እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር በገባው ቃል ኪዳን መኖር ምን ማለት እንደሆነ አስመልክቶ ጳውሎስ አብርሃምን በምሳሌነት የተጠቀመው ለዚህ ነበር። ይህ ጭብጥ በመላው የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክቶች ውስጥ ያስተጋባል።

ጳውሎስ በዘፍ. 3፡6 የቀረበውን ይህንኑ ሀሳብ “እርሱ እግዚአብሔርን አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቆጠረለት” (ዘፍ. 15፡6) በማለት በእርሱ ዘር ሕዝቦች ሁሉ እንደሚባረኩ (ገላ. 3፡9) አስቀድሞ ለአብርሃም የተገባውን የተስፋ ቃል ወደ ኋላ ሄዶ በገላ. 3፡6 ይጠቅሳል። የቃል ኪዳኑ ተስፋዎች የተሰጡት ለሁሉም “የሚያምኑ” (ገላ. 3፡7) አይሁድ እና አሕዛብ ወገኖች ነው። እነዚህ ወገኖች ሕጉ የሚጠይቀውን ሳይፈጽሙ የጸደቁ ቢሆንም፤ በኪዳኑ ምክንያት ሕግን የመታዘዝ በዛ ያሉ ግዴታዎች ነበሩባቸው።

ኤርምያስ ስለ አዲሱ ኪዳን ሲናገር ከሕጉ ዐውድ አኳያ እንደሚከተለው ያቀርባል፡ “ ‘ነገር ግን ከዚያ ጊዜ በኋላ፣ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ኪዳን ይህ ነው ይላል እግዚአብሔር፤ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፤ በልባቸውም እጽፈዋለሁ። እኔ አምላክ እሆናቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ።’ ” (ኤር. 31፡33)። ነቢዩ የተጠቀመው ቋንቋ ወደ ኋላ መለስ ብሎ በዘሌዋውያን መጽሐፍ የቀረበውን ያንጸባርቃል፡ “በመካከላችሁ እመላለሳለሁ፤ አምላካችሁ እሆናለሁ፤ እናንተም ሕዝቤ ትሆናላችሁ” (ዘሌዋ. 26፡12)።

የሕግ እና የወንጌል የቃል ኪዳን ጽንሰ ሀሳብ የእግዚአብሔር የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መልእክት ከሆነው ከሦስቱ መላእክት የራእይ 14 መልእክቶች ጋር ፍጹም ሆነው የሚገጥሙት እንዴት ነው?





ጥቅምት 1
Oct 1

ኪዳኑ እና እስራኤል


“ ‘ምድራቸውን ገብተህ የምትወርሳት ከጽድቅህ ወይም ከልብህ ቅንነት የተነሣ ሳይሆን፣ ለአባቶችህ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ የማለላቸውን ቃል ለመፈጸም አምላክህ እግዚአብሔር እነዚህን አሕዛብ በክፋታቸው የተነሣ ከፊትህ ስለሚያባርራቸው ነው።’ ” (ዘዳ. 9፡5 በተጨማሪ፡ ዘዳ. 9፡27)።



በዚህ ስፍራም እንዲሁ በተመሳሳይ የጸጋው ቃል ኪዳን ቀርቦ እንመለከታለን፡ ስህተታቸው የማያቋርጥ ቢሆንም፣ እነሆ እግዚአብሔር ስለ እነርሱ ሠራላቸው። (ይህ በእርግጥም ወንጌል ዛሬ እንዴት መሥራት እንዳለበት ያመለክታል።) እግዚአብሔር ለአባቶቻቸው በገባው የተስፋ ቃል የተነሣ አምላካዊው ጸጋ ለወደፊት ትውልዳቸው እንዲሰጥ ሆነ።

ሙሴ በሕዝቡ እና በእግዚአብሔር መካከል የተደረጉትን የሁለት ወገን ኪዳኖች ሲጠቅስ፣ በተደጋጋሚ እንደ ማጣቀሻ ይጠቀም የነበረው የቀደመውን በአባቶች እና በእግዚአብሔር መካከል የተደረጉ ውሎችን ነው። ጥቅሱን ያንብቡ፡ ዘፀ. 2፡24፣ ዘፀ. 6፡8፣ ዘሌዋ. 26፡42። በሁለት አካሎች መካከል የሚደረጉ ውሎች የሚሠሩበትን መንገድ ጥቅሶቹ እንዴት ያሳዩናል?



የእግዚአብሔር የማዳን ጸጋ ታላቅ ተምሳሌት የሆነው በብርቱ ኃይል ከግብፅ የመውጣታቸው እውነታ፣ ጌታ ለአባቶቻቸው በፈጸመው ቃል ኪዳን ላይ የተመሠረተ ነበር። በዚህም የቃል ኪዳኑ ተጠቃሚዎች ከመወለዳቸው በፊት እንኳ ተስፋዎቹ ስለ እነርሱ ተሰጥተው ነበር። በመሆኑም ያለ አንዳች መልካም ሥራቸው--በታምራትና ድንቃድንቅ፣ በታላቅ ኃይል ከግብጽ ምድር እንደሚወጡ ቃል የተገባውን አርነት ተቀበሉ።

እርግጥ ነው--ነገሩ በዚያ ብቻ አላበቃም። ከግብጽ ወዴት ሄዱ? አዎ፣ ከእነርሱ ጋር “ይፋዊ” (ዘፀ. ምዕ. 20) የቃል ኪዳን ውል ወደ ታሰረበት ሲና አመሩ። እናም፣ የዚያ ኪዳን አስኳል ወንጌል እና ሕጉ--ማለትም እንዲታዘዙት የተጠሩበት አሥርቱ ትእዛዛት ነበር። ትእዛዛቱ ቀደም ሲል ከዋጃቸው (ወንጌል) ጋር የነበራቸው የማዳን ግንኙነት መገለጫ ነበር። በመሆኑም ይህንን በሲና የጸደቀ ሕግ የቃል ኪዳን ክፍል አድርገው ይታዘዙ ዘንድ በዘዳግም መጽሐፍ ተደጋጋሚ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።

ለእኛ በጸጋው ለዳንን የእግዚአብሔር ሕግ ዛሬ በህይወታችን ውስጥ ምን ሚና ሊኖረው ይገባል? ያ ሕግ ከእግዚአብሔር ጋር ላለን ተሞክሮ እጅግ ወሳኝ የሆነው ለምንድን ነው?





ጥቅምት 2
Oct 2

የቃል ኪዳኑ መጽሐፍ


ምንም እንኳ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ያለውን ግንኙነት ለመግለጽ ጥቅም ላይ የዋለው የቃል ኪዳኑ ጽንሰ ሀሳብ (በዕብራይስጥ ቤሪት) በመላው የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክቶች ወስጥ ቢገኝም፤ ቃሉ በዘዳግም መጽሐፍ በስፋት መገኘቱን ተከትሎ፣ “የቃል ኪዳኑ መጽሐፍ” የሚል መጠሪያ ተሰጥቶታል። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘዳ. 5፡1-21። የቃል ኪዳኑ ጽንሰ ሀሳብ ለዘዳግም መጽሐፍ ምን ያህል አስኳል እንደሆነ ለማሳየት በዚህ ስፍራ እየሆነ ያለው ምንድን ነው?



የእስራኤል ልጆች ከግብፅ መቤዠት አግኝተው ብዙም ሳይቆይ--ወደ ተስፋይቱ ምድር ይገባሉ ተብሎ ከታሰበበት ጊዜ ጥቂት ቀደም ብሎ እግዚአብሔር በሲና ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳኑን መሠረተ። ከዚያም 40 ዓመት ተዟዙረው እንደገና ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ጥቂት ሲቀራቸው--የኪዳኑ ማዕከላዊ ክፍል የሆነውን (ዘፍ. 12፡7፣ ዘፀ. 12፡25) አሥርቱን ትእዛዛት ጌታ እንደገና በሙሴ ቃል አቀባይ በኩል ሰጣቸው። ይህ፣ የቃል ኪዳን ግዴታቸውን ማደሳቸው ምን ያህል አስፈላጊ እንደነበር በድጋሚ በጉልህ የቀረበበት መንገድ ነበር።

ጌታ ለእነርሱ የገባውን ቃል ኪዳን ለመፈጸም ተዘጋጅቶ የነበረ ሲሆን፤ በአጸፋው እነርሱም የሚጠበቅባቸውን ያን የገቡትን ስምምነት የመጠበቅ ግዴታ ነበረባቸው፡ “ ‘እርሱ ኪዳኑን ይኸውም እንድትከተሏቸው ያዘዛችሁን ዐሠርቱን ትእዛዛት ዐወጀላችሁ፤ ከዚያም በሁለት የድንጋይ ጽላቶች ላይ ጻፋቸው’ ” (ዘዳ. 4፡13)። ይህን ያደረገው ሲና ላይ የነበረ ሲሆን፤ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ለአባቶቻቸው ቃል የገባላቸውን ምድር ሊወስዱ ጥቂት ሲቀራቸው፣ በሲና ላይ ያደረገውን አሁን ደግሞ በሞአብ በድጋሚ እያደረገ ነበር። ይህ ዓለም ከመፈጠሯ አስቀድሞ የነበረው “የዘላለማዊ ቃል ኪዳን” መገለጫ ነው።

“ሰው በሰይጣን ቢሸነፍ እርሱን ለማዳን አብና ወልድ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ቃል ኪዳን ገብተው ነበር። ክርስቶስ የሰብዓዊ ዘር ዋስ እንዲሆን የተቀደሰ ቃል ኪዳን በመግባት እጅ ለእጅ ተጨባብጠው ነበር። የዘመናት ምኞት፡ ገጽ 885 ጥቅሱን ያንብቡ፡ ዘዳ. 5፡3። ጥቅሱ ምን ትርጉም አለው?



ሙሴ ምን እያላቸው ነበር? አባቶቻቸው በማለፋቸው፣ እነዚያ ከእነርሱ ጋር ተደርገው የነበሩ ድንቅ የሁለት ወገን ኪዳኖች እነሆ አሁን ከትውልዶቻቸው ጋር እንዲጸኑ ሆነዋል። ይህ--ያለፈው ትውልድ የፈጠረው ዓይነት ቀውስ በዚህኛውም እንዳይደገም ሙሴ ለሕዝቡ የገለጸበት የራሱ መንገድ ሊሆን ይችላል። የተስፋ ቃሎቹ (እንዲሁም ግዴታዎቹ) አሁን የእነርሱ ናቸው።

ጥቅምት 3
Oct 3

የእርሱ የተለዩ ሕዝቦች


እስራኤላውያን በምድረ በዳ ይንከራተቱ በነበረበት ወቅት አብዛኛው የጥንታዊው ዓለም ሁናቴ ምን ይመስል እንደነበረ ለመረዳት ለእኛ ዛሬ ከባድ ነው። የዚያን ዘመኖቹ ታላላቅ መንግሥታት ውድቀት በደረሰባቸው ቁጥር ወደ ፍርስራሽ ክምር ብቻ የሚቀየሩ ከሆነ፣ በእስራኤላውያን ዘመን በውሱን አካባቢ ይኖሩ ስለነበሩ ትናንሽ አረማውያን ብሔራት ምን ማወቅ እንችላለን? ብዙም ባይሆን ነገር ግን አንድ ነገር እናውቃለን፡ እነዚህ ሕዝቦች አረማውያን፣ ብዙ አማልክት የሚያመልኩ እንዲሁም ህፃናትን መሥዋእት አድርጎ እስከ ማቅረብ የደረሰ አጸያፊ ተግባራት የሚፈጽሙ ነበሩ። በስመ አማልዕክት-በገዛ ልጆቻቸው ላይ እንዲህ ዓይቱን አጸያፊ ድርጊት የሚፈጽም ባህል እና ኃይማኖት ምን ያህል አዋራጅ እና አሰቃቂ ሊሆን እንደሚችል ለማሰብ ይሞክሩ።

በጥንቷ እስራኤል ታሪክ ጌታ ሕዝቦቹ በዙሪያቸው ያሉ አሕዛብን ልማድ እንዳይከተሉ ደጋግሞ ማስጠንቀቁ እምብዛም የሚገርም አይሆንም። “ ‘አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚሰጥህ ምድር በምትገባበት ጊዜ፣ በዚያ የሚኖሩት አሕዛብ የሚፈጽሙትን አስጸያፊ መንገድ አትከተል” (ዘዳ. 18፡9)። ይህ የሆነበት ምክንያት እግዚአብሔር ይህን ሕዝብ ለልዩ ዓላማ በመጥራቱ ነው። እስራኤላውያን ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን በመግባታቸው የተለዩ ሕዝቦች መሆን ነበረባቸው፣ ሰማይንና ምድርን ለፈጠረው ብቸኛው አምላክ-ለዓለም ምስክር መሆን ይጠበቅባቸው ነበር።

ጥቅሱን ያንብቡ፡ ዘዳ. 26፡16-19። በእግዚአብሔር እና በእስራኤላውያን መካከል ያለው ኪዳናዊ ግንኙነት በእነዚህ ቁጥሮች ጠቅለል ብሎ የተገለጸው እንዴት ነው? ለቃል ኪዳኑ የሚኖራቸው ታማኝነት፣ ይሆኑ ዘንድ ለሚጠበቅባቸው ማንነት እንዴት መገለጥ ነበረበት? በተመሳሳይ እኛ ከዚህ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?



ሙሴ እነዚህን አራት ጥቅሶች “በዛሬይቱ ዕለት” በሚሉ ቃላት አጅቦ ማቅረቡ ምንኛ አስደናቂ ነው። አሁንም እንደገና እግዚአብሔር እነዚህን ነገሮች እንድታደርጉ ያዛችኋል (ሐሳቡን በቁጥር 17 ይደግማል)። እነዚህን ነገሮች ያደርጉ ዘንድ ገና ከመጀመሪያ አንስቶ አዟቸው ነበር። በዚሁ ቅጽበት አሁንም በድጋሚ ታማኝ፣ ቅዱስ፣ እና ልዩ ህዝቦች እንዲሆኑ እየነገራቸው ይመስላል። ይህ ደግሞ በእርግጥም እንደ ቃል ኪዳን ሕዝብ የመፈጠራቸው እውነተኛው ምክንያት ነው። እንደ ሕዝብ--እውነተኛውን አምላክ፣ ስለ እርሱ የቀረበውን እውነት እና ሰዎች እንዴት መኖር እንዳለባቸው የሚፈልግበትን መንገድ በማወቅ ረገድ ብቸኞቹ ነበሩ።

እንደ እውነቱ ከሆነ እነዚህ ሕዝቦች የወቅታዊው አውነት ባለቤት ብቻ ሳይሆኑ ነገር ግን ራሱ “እውነት” (ዮሐ. 14፡ 6) የሆነው የሱስ እስኪመጣ እርሱን የመግለጽ ጉዞ ላይ ነበሩ። ለእግዚአብሔር እና ለቃል ኪዳኑ መስፈርቶች ሊኖር የሚገባውን ቁርጠኝነት አስመልክቶ “በዛሬይቱ ዕለት” በሚል የቀረበው ጽንሰ ሀሳብ ዛሬ ለእኛም ቢሆን አግባብነት ያለው ለምንድን ነው?





ጥቅምት 4
Oct 4

ሌሎች ምስሎች


የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን እስራኤል ከእግዚአብሔር ጋር በገባችው ቃል ኪዳን እና በመንግሥታት መካከል ባሉ ሌሎች የቃል ኪዳን ስምምነቶች መካከል ተመሳሳይነት መኖሩን ከተገነዘቡ ሰነባብተዋል። ይህ መመሳሰል አስገራሚ ሊሆን አይገባም። ጌታ በቀላሉ ሊስተዋል በሚችል አኳኋን ከሕዝቡ ጋር እየሠራ ነበር።

በተመሳሳይ--ሕጎች፣ አንቀጾችና ደንቦች የተካተቱበት በሁለት አካላት መካከል የሚፈጸም ሕጋዊ ስምምነት የሆነው የቃል ኪዳኑ ጽንሰ ሀሳብ፣ ሞቅ ያለ ስሜት የማይሰጥና ሥርዓታዊ ሊመስል ይችላል። ምንም እንኳ ያ ባህሪ በእርግጥ መኖር ቢኖርበትም (ሕግ ሰጪው እግዚአብሔር ነው) እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር እንዲኖረው የፈለገው ዓይነት የግንኙነት ጥልቀት እና ስፋት የማካተት ግዝፈት ግን የለውም። በመሆኑም በእግዚአብሔር እና በእስራኤል መካከል ያለውን ኪዳን በጉልህ ማሳየት የሚችሉ ሌሎች ምስሎች በዘዳግም መጽሐፍ ጥቅም ላይ ውለዋል። ይህ የሆነው፣ ተጨማሪ ስፋትና ጥልቀት ለመስጠት ያህል ብቻ ነው።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘዳ. 8፡5፣ ዘዳ. 14፡1፣ ዘዳ. 32፡6፣ 18-20። በዚህ ስፍራ ጥቅም ላይ የዋለው ምን ዓይነት ምስል ነው? እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር እንዲኖረው የፈለገውን ግንኙነት እንዴት ለመግለጥ ያስችለዋል?



በእያንዳንዱ ሁኔታ ቤተሰባዊ ጽንሰ ሀሳብ ያለ ሲሆን ይኸውም የተቀራረበ፣ ጥብቅ ትስስርና መዋደድ ያለው መሆን ይኖርበታል። እግዚአብሔር ሁሌም ቢሆን እንዲህ ያለውን ግንኙነት ከሕዝቦቹ ጋር ለመመሥረት ይፈልግ ነበር። ጌታ በተሰቀለበት ወቅት አሳፋሪ ተቃውሞ አሳዩት። ይህም ሆኖ ከዕርገቱ በኋላ “‘አትፍሩ፤ ሂዱና ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ንገሯቸው፤ በዚያ ያዩኛል’” (ማቴ. 28፡10) ሲል ለእነ ማርያም ነገራቸው። እርሱ ከሞት የተነሣ ማንነት የተላበሰ ክርስቶስ ሆኖም እንኳ “ወንድሞቼ” ብሎ ሲጠራቸው ይስተዋላል። ይህ በእርግጥ ለማይገባቸው የተቸረ ከፍቅር የሚፈልቅ የፍቅርና የጸጋ ምሳሌ ነው።

ከእግዚአብሔር ጋር ያለዎት ግንኙነት ምን ይመስላል? ሕጉን የማክበር የቃል ኪዳን ግዴታዎን እየተገነዘቡ ጎን ለጎን ግንኙነቱ ጥልቀትእንዲኖረው ማድረግና እርሱን መውደድ መማር የሚችሉት እንዴት ነው?





ጥቅምት 5
Oct 5


ተጨማሪ ሀሳብ


“የባርነት መንፈስ የሚወለደው በኃይማኖታዊ ሥርዓት መሠረት ለመኖር አጥብቀን ስንሽት--ይኸውም የሕግን ጥያቄዎች በራሳችን ኃይል ለመፈጸም ጥረት ስናደርግ ነው። ተስፋ የሚኖረን በክርስቶስ የሱስ በማመን የጸጋ ቃል ኪዳን በሆነው በአብርሃም ቃል ኪዳን ሥር ስንውል ብቻ ነው። አብርሃም ተስፋ አድርጎት በነበረው መንገድ የተሰበከለት ወንጌል፣ ዛሬ ለእኛ ከተሰበከልንና ተስፋ ካደረግነው ወንጌል ጋር አንድ ነው። አብርሃም የእምነታችን ጀማሪና ፍጹም አድራጊ ወደ ሆነው የሱስ ተመለከተ።

—Ellen G. White Comments, The SDA Bible Commentary, vol. 6, p. 1077. “ሰው በሰይጣን ቢሸነፍ እርሱን ለማዳን አብና ወልድ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ቃል ኪዳን ገብተው ነበር። ክርስቶስ የሰብዓዊ ዘር ዋስ እንዲሆን የተቀደሰ ቃል ኪዳን በመግባት እጅ ለእጅ ተጨባብጠው ነበር። ክርስቶስ ይህን ቃል ኪዳን አክብሯል። የሱስ በመስቀል ላይ ሆኖ ‘ተፈጸመ!’ ሲል በጩኸት ያሰማው ቃል ለአብ የተነገረ ነበር። አብና ወልድ የተስማሙበት ጉዳይ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ስለሆነ የሱስ ለእግዚአብሔር፣ አባቴ ሆይ! ተፈጸመ አለው። አባት ሆይ ፈቃድህን ፈጸምሁ፤ የማዳንን ሥራ አጠናቀቅሁ አለው። ‘አባቴ ሆይ! ዓለም ሳይፈጠር ስለወደድኸኝ የሰጠኸኝን ክብሬን እንዲያዩ እነዚህ አንተ የሰጠኸኝም እኔ ባለሁበት ከእኔ ጋር እንዲኖሩ አወድዳለሁ’ አለው። ዮሐ. 19፡ 30፣ 17፡24)።” የዘመናት ምኞት ገጽ፡ 885-886።


የመወያያ ጥያቄዎች



1.ሰብዓዊው ዘር በኃጢአት የሚወድቅ ከሆነ--ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ አብ እና ወልድ እኛን ለመዋጀት በኪዳን አንድ ሆነው ነበር በሚለው ጽንሰ ሀሳብ ላይ ተወያዩ። ይህ ለእኛ ተስፋ ሰጭ የሆነው ለምንድን ነው? እኛ እንድን ዘንድ እግዚአብሔር አጥብቆ ስለመፈለጉ ይህ ምን ሊያስተምረን ይገባል?

2.እንደ ሰባተኛ ቀን የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂ ቤተ ክርስቲያን፤ የጥንቶቹ እስራኤላውያን በጊዜው ሊፈጽሙት የሚገቡ ኃላፊነቶች እንደነበሯቸው ሁሉ፤ እኛም የተሰጠንን ሚና በምን መንገዶች ማከናወን ይኖርብናል? እነርሱ የሠሯቸውን ስህተቶች ማስወገድ እንዴት መማር እንችላለን?

3.ወንጌል እና የወንጌል ተስፋዎች ለመላው የአዲስ ኪዳን ጽንሰ ሀሳብ ወሳኝ የሆኑት ለምንድን ነው? አዲስ ኪዳንን አስመልክቶ ሌሎች ክርስቲያኖች በተለምዶ ከሚያስተምሩት በተቃራኒ-በአዲሱ ኪዳን ሕጉም ሆነ ሕጉን መታዘዝ አለመሻሩን የሚያሳዩ ምን ዓይነት ጥቅሶች ከአዲስ ኪዳን ማግኘት ይችላሉ? ብዙ ክርስቲያኖች ወንጌል አሥርቱን ትእዛዛት የመጠበቅ አስፈላጊነትን ይሽራል የሚሉት ለምን ይመስሎታል?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL