
ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ ፡- ዕብ. 9፡24፤ ዘጸ. 19፡ 3-4፤ ዕብ. 12፡18-21፤ ዘሌ. 16፡1-2፤ ዕብ. 10፡19-22፤ ቆላ. 3፡1።
የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “ ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሰራች፥ የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደ ምትሆን ቅድስት አልገባምና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ።” (ዕብ. 9፡24)
ኢ
የሱስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ወዲያውኑ ከደብረ
ዘይት ተራራ ላይ ሲመለሱ በደስታና በድል ተሞልተው ነበር።
ጌታቸውና ወዳጃቸው በአለም ላይ ገዢ ወደ ሚያደርገው ስፍራ
አረገና ፍጹም በሆነ መተማመን በስሙ ወደ አብ እንዲቀርቡና ከዚህም
የተነሳ አብ ጸሎታቸውን እንደሚመልስላቸው ተናገራቸው (ዮሐ. 14፡13፤
17)። በአለም ሲጓዙ በክፉ ሀይል ጥቃት ቢደርስባቸውም ተስፋቸው ግን የጸና
ነበረ። ኢየሱስ ስፍራ ሊያዘጋጅላቸው ወደ ሰማይ እንዳረገ ተረድተዋል (ዮሐ.
14፡1-3)። ኢየሱስ የድነታቸው ጌታ ሆኖ በደሙ በኩል የሰማያዊ ቤታችንን
መንገድ እንደከፈተላቸውም አውቀዋል።
የክርስቶስ ወደ ሰማይ ማረግ በዕብራውያን መጽሐፍ የስነ መለኮት አስተምህሮ
ውስጥ ማዕከላዊ ስፍራን ይይዛል። ይህም የየሱስ አገዛዝ ጅማሮ ምልክት
እና በእኛ ምትክ ሆኖ የሊቀ ካህንንነት አገልግሎት መጀመሩን ያሳያል።
በስተመጨረሻም ወሳኙ ነገር የየሱስ እርገት በእግዚአብሔር ፊት በድፍረት
አምነን እንድንቀርብ የሚያደርገንን አዲስ ኪዳን መጀመሩን የሚያመለክት
ምሳሌ ነው። አሁን በኢየሱስና በርሱ ፅድቅ በኩል በእግዚአብሔር ፊት
በድፍረት እንድንደርስ እድልን አግኝተናል።
የዚህን ሳምንት ትምህርት አጥትንተው ለየካቲት 26 ሰንበት ይዘጋጁ።
ዕብ. 9፡24ን ያንብቡ። በዚህ ጥቅስ መሠረት ኢየሱስ ወደ ሰማይ ያረገበት አላማ ምንድነው?
እግዚአብሔር የእስራኤል ወንዶች በየአመቱ ሶስት ጊዜ ወደ እስራኤል ሄደው
“በእግዚአብሔር ፊት እንዲታዩ” አዘዘ። የተቆረጠው ጊዜም የቂጣ በአል፤ ዳስ
በአል እና የመከር በአል ነው (ዘጸ. 23፡14-17፤ ዘጸ. 16፡6)። የፋሲካ(ቂጣ) በአል
የሚከበረው እስራኤል ከግብፃውያን ነፃ የወጡበትን ጊዜ ለማስታወስ ነው።
በአዲስ ኪዳን የጴንጤቆስጤ ቀን የሚከበረው ህጉ በሲና ተራራ መሰጠቱን
ለማስታወስ ሲሆን መከር የሚሰበሰብበትን ጊዜ ለማሰብ ነው። የዳስ በአል
ደግሞ እስራኤል በምድረ በዳ በቆየበት ጊዜ እግዚአብሔር ያሳያቸውን ጥንቃቄ
ለማስታወስ የሚያከብሩበት ነው።
ዕብ. 9፡24 ኢየሱስ ወደ አባቱ ማረጉን ይገልፃል። “እውነተኛ” ወደ ሆነችው
ሰማያዊ ቤተ መቅደስ ደርሶ በእግዚአብሔር ፊት የሚበልጥ መስዋዕት ይዞ
ማለትም በገዛ ደሙ ታየ” (ዕብ. 9፡23-24)።
ኢየሱስ ሃይማኖታዊ የበአል ስርአቶቹን አስደናቂ በሆነ ትክክለኛነት
ፈጸማቸው። የፋሲካ በአል ሊከበር ሲዘጋጁ በነበረበት ቀን ልክ የፋሲካው
ጠቦት መስዋዕት በሚደረግበት ጊዜ ማለትም ዘጠኝ ሰዓት ላይ ሞተ (ዮሐ.
19፡14፤ ማቴ. 27፡45-50)። ልክ ካህኑ የመከሩን በኩራት ነዶ ተቀባይነት
እንዲያገኝላቸው በእግዚአብሔር ፊት እንደሚወዘውዘው (ዘሌ. 23፡10-12)
በሶስተኛው ቀን ኢየሱስ ከሞት ተነሳና መስዋዕትነቱ ተቀባይነት እንዳገኘ
ማረጋገጫ ለመቀበል ወደ ሰማይ አረገ (ዮሐ. 20፡17፤ 1ቆሮ. 15፡20)። ከዚያ
ከ40 ቀናት በኋላ ወደ ሰማይ አረገና በአብ ቀኝ ተቀምጦ በጴንጤቆስጤ በአል
ቀን አዲስ ኪዳን በይፋ አስጀመረ (ሐዋ. ሥራ 1 እና 2)።
በጥንታዊ እስራኤላውያን ዘንድ የሃይማኖታዊው ጉዞ አላማ “የእግዚአብሔርን
ፊት” ለማየት ነበር (መዝ. 42፡2)። ይህም ከእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስን
ማግኘትን ለመለማመድ ነው (መዝ. 17፡15)። በተመሳሳይ በዕብራይስጡ
“የእግዚአብሔርን ፊት መፈለግ” ማለት እግዚአብሔር እንዲያግዘን መጠየቅ
ነው (2 ዜና 7፡4፤ መዝ. 27፡8፤ መዝ. 105፡4)። በዕብራውያን መጽሐፍ ስለ
ኢየሱስ ማረግ ሲናገር ይህን ማለቱ ነው። እርሱ ወደ ሰማይ ያረገው ፍጹም
መስዋዕት ከሆነ በኋላ ነው። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲያርግም በእግዚአብሔር
ሀልዎት ውስጥ ከፊታችን ቀዳሚ ሆኖ ነው (ዕብ. 6፡19-20)። “መኖሪያን
ሽተው”፣ “የተሻለ አገርን” ናፍቀውና “ከእግዚእብሔር ዘንድ የተሰራችን
ከተማ” ወደፊት እያዩ ለሚጓዙት አማኞች እውነተኛ የተስፋ ቃልን ሰጣቸው
(ዕብ. 11፡10፤ 13-16)።
በድጋሚ ክርስቶስ ለኛ በመስቀል ላይ ያደረገልን ብቻ ሳይሆን
በሰማይ ለኛ እያከናወነ ያለው ተግባር ስለ መዳናችን ምን ያክል
ማረጋገጫን ይሰጠናል?
ዕብ. 12፡21ን ያንብቡ። በሲና ተራራ ላይ እስራኤላውያን ምን አይነት ነገር ተለማመዱ?
እግዚአብሔር እስራኤልን ከግብጽ ሲጠራቸው አላማው ከእነርሱ ጋር ግላዊና
የጠበቀ ግንኙነት ለመመስረት ነበር። “በግብፃውያን ያደረጉትን በንስርም
ክንፍ እንደተሸከምኳችሁ ወደ እኔም እንዳመጣኋችሁ አይታችኋል።” (ዘፀ.
19፡3-4) ብሏቸዋል።
ስለዚህም በሙሴ በኩል እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ይገናኝ ዘንድ እንዲዘጋጁ
መመሪያን ሰጠ። ህዝቡ አስቀድመው ራሳቸው መቀደስ ነበረባቸው (ዘፀ. 19፡
10-15)። ያለ ዝግጅት የወጣ ሰው ሁሉ ይሞታል። ሆኖም ህዝቦቹ ራሳቸውን
ለሁለት ቀናት ካዘጋጁ በኋላ በሶስተኛው ቀን “የመለከት ድምጽ በኃይል ሲነፋ
. . . ወደ ተራራው እንዲቀርቡ” አዘዘ (ዘጸ. 19፡13)።
ሙሴና የህዝቡ መሪዎች
ወደ ተራራው ሲወጡ ሳለ የሚለማመዱትን ነገር ማለትም “እግዚአብሔርን
ማየትና” በፊቱ “መብላትና መጠጣትን” (ዘፀ. 24፡9-11) ህዝቡ እንዲለማመዱት
ፈለገ። ህዝቡም ቆየት ብለው የእግዚአብሔርን ክብር እንዳዩ እግዚአብሔርም
“ከሰው ጋር ሲነጋገርና ሰውዬውም በህይወት ሲኖር” (ዘዳ. 5፡24) አዩ። ነገር
ግን ያ ጊዜ ሲደርስ እምነታቸውን አጡ። ሙሴ ከዘመናት በኋላ ሲናገር “እናንተ
በእሳቱ ምክንያት ፈርታቿልና ወደ ተራራውም አልወጣችሁምና” (ዘፀ. 5፡5)
ብሎ ነበር። በዚህ ፈንታ ግን ሙሴ የእነርሱ አማላጅ ሆኖ እንዲቀርብ ጠየቁት
(ዘዳ. 5፡25-27ን ከዘፀ. 20፡18-21 ጋር ያነፃፅሩ)
እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ ቅድስናውን ሲገልጽ ህዝቡ እርሱን “መፍራት”
ወይም ማክበርን እንዲማር ነበር። “እግዚአብሔርን መፍራት” ወደ ህይወት፣
ጥበብ እና ክብር ይመራል (ዘዳ. 4፡10ን ከመዝ. 111፡10፣ ምሳሌ 1፡7፣ ምሳሌ
9፡10፤ ምሳሌ 10፡27 ጋር ያነፃፅሩ)። እርሱም ባለ ምህረት እና በፀጋ የተሞላ
እንደሆነ እንዲረዱ ነበር (ዘፀ 34፡4-8)።
እናም እግዚአብሔር እስራኤል
ወደርሱ እንዲመጡ ሲሻ ህዝቡ ግን ፈሩና ሙሴ እንዲያማልዳቸው ጠየቁት።
በዕብራውያን መፅሐፍ ላይ በሲና ተራራ ስለተከናወነው ሁኔታ ሲያብራራ
ሙሴ ህዝቡ እምነት ስለማጣታቸው አስቀድሞ ካስታወሳቸው እና ለወርቅ
ጥጃ ስለ መስገዳቸው ከተናገረ በኋላ በሀጢያታቸው የተነሳ እግዚአብሔርን
ለመገናኘት እንደፈራ ተናገረ (ዘዳ. 9፡19)። የህዝቡ ምላሽ እንደ እግዚአብሔር
እቅድ ሳይሆን በተቃራኒው እምነት የማጣታቸው ውጤት ነበር።
በኢየሱስ ምክንያት ቅዱስ ወደ ሆነው አምላክ ለመቅረብ መፍራት
የሌለብን ለምንድነው? ወደርሱ ለመቅረብ ከኛ የሚጠበቀው ነገር
ምንድን ነው?
መጋረጃው ሁለት ተግባራት አሉት። መጋረጃ የሚለውን ቃል ዕብራይስጡ “ኬትፕታስማ” ብሎ ሲገልፀው የአደባባዩ ደጃፍ መጋረጃን(ዘጸ. 38፡18)፣ ወደ ቤተ መቅደሱ ውጫዊ ክፍል መግቢያ ላይ የሚገኘውን መጋረጃ ወይም ቅዱሱን ክፍል ከቅድስተ ቅዱሳን ክፍል የሚለየውን መጋረጃ ሊገልፅ ይችላል (ዘፀ. 26፡31-35)። እነዚህ መጋረጃዎች ጥቂት ሰዎች ብቻ የሚገቡባቸው የመከለያ ድንበሮች ነበሩ። ዘሌ. 16፡1-2 እና ዘሌ. 10፡1-3ን ያንብቡ። በነዚህ ጥቅሶች ውስጥ የምናገኘው ማስጠንቀቂያ ምንድነው?
መጋረጃው ቅዱስ በሆነው አምላክ ፊት ካህናቱ ሲያገለግሉ ሳለ መከለያቸው
ነበር። ለወርቅ ጥጃ ሰግደው ሀጢያት ከሰሩ በኋላ እግዚአብሔር ለሙሴ ህዝቡ
“አንገተ ደንዳኖች” ስለሆኑ በእሳት ሊያጠፋቸው ስላሰበ ወደ ተስፋዪቱ ምድር
እየመራ እንደማያገባቸው ነገረው(ዘጸ. 33፡3)። ሙሴም የመገናኛውን ድንኳን
ከሰፈሩ ውጪ አውጥቶ ተከለው (ዘፀ. 33፡7)። ሙሴ ለህዝቡ ከማለደ በኋላ
እግዚአብሔር በመካከላቸው ሆኖ ሊመራቸው ተስማማ (ዘጸ 33፡12-20)።
ነገር ግን በህዝቡ መካከል ሲሆን እነርሱን ለመጠበቅና ብዙ መከላከያዎችን
መሰረተ።
ለምሳሌ እስራኤል ቤተ መቅደሱን በመሃል አድርገው አራት ማዕዘን ሰርተው
እንዲቀመጡ በጥብቅ ታዘው ነበር። በተጨማሪም ሌዋውያን በቤተ መቅደሱ
ዙሪያ ሆነው ቤተ መቅደሱንና በውስጡ ያሉትን ዕቃዎች እንግዳ ከሆኑ ሰዎች
እንዲጠበቅ በዛ መስፈር ነበረባቸው (ዘሁ 1፡51፤ ዘሁ 3፡10)። በእርግጥም
ሌዋውያኑ የእስራኤልን ህዝቦች እንደሚከላከሉ ሰብአዊ መጋረጃዎች ነበሩ።
“ነገር ግን በእስራኤል ልጆች ላይ ቁጣ እንዳይወርድ ሌዋውያን በምስክሩ
ማደሪያ ዙሪያ ይሰፈሩ ሌዋውያንም የምስክሩን ማደሪያ ይጠብቁ” (ዘሁ. 1፡53)
ኢየሱስ የኛ ካህን ስለሆነ የእኛም መከለያ መጋረጃችን ነው።
በእርሱ ስጋ
መልበስ የተነሳ እግዚአብሔር ድንኳኑን በመካከላችን አኖረ፤ ክብሩንም
እንድናይ አስቻለን (ዮሐ 1፡14-18)። በኢየሱስ አማካኝነት ቅዱሱ እግዚአብሔር
ሀጢያተኛ ከሆነ ህዝብ ጋር ለመኖር ቻለ።
አለማትን ሁሉ የፈጠረ ጌታ በወቅቱ ከባርነት ካመለጡ ህዝቦች
ጋር አብሮ የመሆኑ አንድምታ ዙሪያ ያስቡ። ይህ እግዚአብሔር
ምን ያክል ለእኛ ቅርብ እንደሆነ ምን ያስተምረናል?
ዕብ. 10፡19-22 ያንብቡ። በዚህ ጥቅስ ውስጥ የምናገኘው ጥሪ ምንድነው?
የዕብራውያን መጽሐፍ ኢየሱስ ወደ ሰማያዊ ቤተ መቅደስ እንደገባና
የእርሱን ፈለግ እንድንከተል እየጋበዘን እንዳለ ይገልፃል። ይህ ኃሳብ ከዚህ
ቀደም ኢየሱስ የአማኞች “መሪ” እና “ቀዳሚ” ስለመሆኑ ከተገለፀው ሀሳብ
ጋር ይስማማል (ዕብ. 2፡10፤ ዕብ. 6፡19-20፤ ዕብ. 12፡2)። “አዲሱና ህያው
መንገድ” ኢየሱስ በመስዋዕትነቱና ዕርገቱ የመረቀልን አዲስ ኪዳን ነው።
“አዲስ እና ህያው” የሚለው አገላለፅ ስለብሉይ ኪዳን ሲነገር “ያረጀ እና ያፈጀ”
(ዕብ. 8፡13) ከሚለው ጋር ተቃራኒ ነው። የኃጢያትን ይቅርታ ሰጥቶ ህጉን
በልባችን በማስቀመጥ በራሳችን ወይም እኛ ባደረግነው ነገር ሳይሆን ነገር ግን
ቃል ኪዳኑ የሚጠይቀውን ግዴታ ሙሉ በሙሉ ኢየሱስ በመፈፀሙ ብቻ
በእግዚአብሔር ፊት በድፍረት እንድንቀርብ የሚያደርገን አዲሱ ኪዳን ነው።
የዕብራውያን መፅሐፍ እንደሚነግረን የብሉይ ኪዳን መጀመር የቤተ መቅደሱ
እና የካህናቱ ቅዱስ ሆኖ መጀመርን ያካትታል (ዕብ. 9፡18-21ን ከዘፀ. 40 እና
ዘሌ. 8ና 9 ጋር ያነፃፅሩ)። የቃል ኪዳኑ አላማ በእግዚአብሔር እና በእርሱ
ህዝቦች መካከል የጠበቀ ግንኙነት መመስረት ነበር (ዘፀ. 19፡4-6):: እስራኤል
ይህንን ግንኙነት ሲቀበል እግዚአብሔር ወዲያውኑ በመካከላቸው እንዲያድር
ቤተ መቅደስን እንዲሰሩለት አዘዘ። በእግዚአብሔር እና በእስራኤል መካከል
የተገባው ኪዳን ሙሉ የሆነው ቤተ መቅደሱ ሲመረቅና እግዚአብሔር በህዝቡ
መካከል ሲገኝ ነበር።
ይህ በአዲሱ ኪዳንም ይሰራል። አዲሱ ኪዳን የሚያመለክተንም የኢየሱስ
በእኛ ምትክ ሆኖ የክህነት አገልግሎቱን መጀመሩን ነው (ዕብ. 5፡1-10፤ ዕብ.
7፡1-8፤ 13)
በእግዚአብሔር ፊት የሆነው የየሱስ እርገት ለእግዚአብሔር ህዝቦች አዲስ
ዘመን ከፈተ። ዘካርያስ 3 ሰይጣን በእግዚአብሔር ፊት ሆኖ የእግዚአብሔርን
ህዝብ ያውም በሊቀ ካህኑ ኢያሱ ተወክሎ የቀረበውን ሊከሰው ቀረበ። ይህ
ከሳሽ በኢዮብ ታማኝነት ላይ ጥያቄ ያነሳው ያው ከሳሽ ነበር (ኢዮብ 1-2)።
በየሱስ መስዋዕትነት ግን ሰይጣን ከሰማይ ተጣለ (ራዕይ 12፡7-12ን ከዮሐ.
12፡31፤ ዮሐ. 16፡11 ጋር ያነፃፅሩ)። አሁን ለኛ የሚያማልደው ኢየሱስ ሲሆን
በመስዋዕቱና በታማኝነቱ በኩል ድነትን ለኛ ሰጥቶናል!
ሰይጣን ቢፈቀድለት እናንተን በምን አይነት ክስ ሊከሳችሁ
ይችላል? ምንም እንኳን ሀሰተኛ ቢሆን እናንተን ለመኮነን ምን
ያክልስ ሀሰትን ይናገራል? የእናንተ ብቸኛ ተስፋስ ምንድን ነው?
ዕብ. 12፡22-24ን ያንብቡ። የእግዚአብሔር መገኛ ወደ ሆነችው ሰማያዊቱ እየሩሳሌም መድረስ የምንችለው በምን ሁኔታ ነው?
አማኞች በእምነት ወደ ጽዮን ተራራ፣ ሰማያዊቱ ኢየሩሳሌም እንደደረሱ
ተገልጧል። በዚህ አግባብ የነርሱ ተሞክሮ የወደፊቱን ሁኔታ ያሳያል። ስለዚህ
ሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም “ተስፋ የምናደርገው” እና “ያላየነው” ሲሆን በእምነት
የተረጋገጠልን ተብሎ የተነገረው ሃሳብ ውስጥ የሚካተት ነው (ዕብ. 11፡1)።
ነገሩ እውነት ቢሆንም የዚህ ጥቅስ ሙሉ ፍቺ ግን ይሄ አይደለም። እኛን
በወከለን ኢየሱስ በኩል የእግዚአብሔር መገኘት ወዳለበት የጽዮን ተራራ
ደርሰናል (ኤፌ. 2፡5-7፤ ቆላ. 3፡1)። የክርስቶስ ወደ ላይ ማረግ የእምነት ጉዳይ
ሳይሆን እውነታ ነው። ይህ የዕብራውያን መጽሐፍ ላይ እምነታችንን አጥብቀን
እንድንይዝ የተሰጠን ምክር ሀይል የሆነው ይህ የየሱስ እርገት የታሪክ ገፅታ
ነው። ጳውሎስ እንዳለው “እንግዲህ በሰማያት ያለፈ ሊቀካህናት ስላለን…
በእምነት እንቅረብ።” (ዕብ. 4፡14 እና 16)
ስለዚህ በወኪላችን በኩል መድረስ ስለቻልን በዚሁ መሠረት ልንኖር ይገባናል።
በእርሱ በኩል እኛ “ሰማያዊውን ስጦታ ቀምሰናል… መልካሙ የእግዚአብሔር
ቃልና ሊመጣ ያለውን የአለም ሀይል ቀምሰናል” (ዕብ. 6፡4-5)። የክርስቶስ
ዕርገት እና በሰማያዊ ቤተ መቅደስ ያለው አገልግሎት እውነታ ጠንካራ “የነፍስ
መልህቅ” ነው (ዕብ. 6፡19)። የተስፋ ቃሉ ትርጉም ያለውና ልንተማመንበት
እንደሚገባ ያረጋግጥልናል (ዕብ. 7፡22)። ለኛ እምነት ታሪካዊ መልህቅ አለው።
የእግዚአብሔር አላማ የሚፈፀመው በኢየሱስ ብቻ ሳይሆን በእኛም ነው።
እንዳልነውም የኢየሱስ እርገት የእስራኤልን ሁለት የመጀመሪያ አመታዊ
በአላትን የፈፀመ ነው። ይኸውም የፋሲካ በአልና የመከር (የጴንጤ ቆስጤ)
በአላትን ነው። በዕብራውያን መጽሐፍ እና በራዕይ መጽሐፉ መሰረት
የመጨረሻው ሃይማኖታዊ ጉዞ የዳስ በአል ገና ወደፊት የሚፈፀም ነው።
“ከየሱስ ጋር” እግዚአብሔር በሰራትና በፈጠራት … ከተማ የምናከብረው ነው
(ዕብ. 11፡10፤ 13-16)። ዳስ አንሰራም፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ዳስ ወይም
ድንኳን ከሰማይ ወደ ምድር ትወርዳለች ከእርሱም ጋር ዘላለም እንኖራለን
(ራዕይ 7፡15-17፤ ራዕይ 21፡1-4፤ ራዕይ 22፡1-5፣ ዘሁ. 6፡24፡26)
አለማችን በስቃይና ህመም የተሞላች ቢሆንም የዘላለም ሕይወት
ተስፋ እውነት ስለመሆኑ መማር የምንችለው እንዴት ነው? ይህ
እኛ አሁን በዚህ ህይወት የተሻለ ስሜት እንዲሰማን የሚያደርግ
የፈጠራ ሃሳብ ነው ለሚሉ ምን አይነት ምላሽ ይሰጣሉ?
“የክርስቶስ ወደ ሰማይ ማረግ ተከታዮቹ ተስፋ
የተገባላቸውን በረከት እንደሚቀበሉ አመላካች ነው። የሱስ ሰማያዊውን ደጃፍ
አልፎ ሲገባ በመላዕክት አድናቆትና አጀብ ይነግሳል። ይህ ስርአት እንዳለቀ
መንፈስ ቅዱስ በሙላት ወረደ ክርስቶስም ከዛለም በፊት በነበረው በአባቱ
ክብር በእርግጥም ከበረ። የጴንጤቆስጤ መንፈስ መውረድ አዳኙ የከፈተው
ሰማያዊ ግንኙነት መፈጸም ነው። በቃል ኪዳኑ መሰረት ለተከታዮቹ መንፈስ
ቅዱስን ላከ እንደ ካህን እና ንጉስነቱም በሰማይና በምድር ሁሉ ላይ ስልጣንን
ተቀበለ በህዝቦቹም ላይ ተቀባ….
በድፍረት የኢየሱስን ስም እየጠሩ ወዳጄ ወይንም ታላቅ ወንድሜ ማለት
አይችሉምን ከክርስቶስ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዲያደርጉ ስለተደረጉ
በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አብረው ተቀምጠዋል። ለእርሱ ምስክር እንዲሆኑ
ታዲያ ምን አይነት አንገብጋቢ ቃላትን ተጠቅመው ሃሳባቸውን ያስረዳሉ።”
Ellen G. White, the acts of Apostles, pp. 38, 46::
1.ባለመዝሙሩ ሲናገር “ነፍሴ ወደ ሕያው አምላክ ተጠማች፤
መቼ እደርሳለሁ? የአምላክንስ ፊት መቼ አያለሁ?” (መዝ.42፡
2) ይላል። ስለ እግዚአብሔር ሃልዎት ተመሳሳይ ጥማት ሊኖረን
የሚችለው እንዴት ነው? እርሱን ስናመልከውና በእምነት ወደ
እርሱ መገኘት ስንመጣ ደስተኞች ካልሆን ወደፊትስ ደስተኛ
እንሆናለን? በእግዚአብሔር ፊት እንድንደሰት የሚያደርጉን ነገሮች
ምንድን ናቸው?
2. በእምነት ላይ የሚዘብት መጽሐፍ ላይ የእኛን እምነት
የሚያምንልን ሮቦትን ፈጠረ። ምንም እንኳን ይሄ ውሸት ያዘለ
ቀልድ ቢሆንም እስራኤሎች በበረሃ የሰሩትን ስህተት ላለመድገም
ማለትም በእኛና በእግዚአብሔር መካከል ሌላ አማላጅ ከመፈለግ
መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው? ሌሎች ሰዎች በኛ ፈንታ
መጽሐፍ ቅዱስን አጥንተው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ላይ
እንዲደርሱ ልንፈልግ እንችላለን። ሌሎች ሰዎች ደግሞ በነርሱ
ፈንታ ሌሎች ሰዎች የሚፀልዩት ጸሎት ከነርሱ ይልቅ ትልቅ ሀይል
እንዳለው ሊያስቡ ይችላሉ። ከዚህ መንፈሳዊ ወጥመድ መጠበቅ
የምንችለው እንዴት ነው? ያለማንም ሰው ድጋፍ በኢየሱስ በኩል
ወደ እግዚአብሔር መድረስ የምንችለው እንዴት ነው?
3. የዕብራውያን መጽሐፍ የሚነግረን ስለ ድነት ማረጋገጫ ነው።
ይህንን ከሚገባው በላይ በድፍረት ከመጠቀም የምንቆጠበው
እንዴት ነው?