
ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ - ዕብ. 7፡11-19፤ ዕብ. 8፡ 10-12፤ ኤር. 31፡31-34፤ ዕብ. 8፡1-6፤ ዘጸ. 24፡1-8፤ ህዝ. 36፡26-27
የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “አሁን ግን በሚሻል ተስፋ ቃል በተመሠረተ በሚሻል ኪዳን ደግሞ መካከለኛ እንደሚሆን በዚያ ልክ እጅግ የሚሻል አገልግሎት አግኝቶአል።” (ዕብ. 8፡6)
ፍ
ጹም የሆነ ህይወትን በመኖር እና በእኛ ምትክ በመሞት ኢየሱስ
በእኛና በእግዚአብሔር መካከል አዲስ እና የሚሻል ኪዳንን
መሠረተ። በሞቱ በኩል በመተላለፋችን ምክንያት ልንከፍለው
የሚገባንን የሞት ቅጣት ሽሮ አዲስ ኪዳን እውን እንዲሆን አደረገ።
ይህ እውነት በዕብ. 10፡5-10 የተገለፀ ሲሆን ቃል ኪዳኑ የሚፈልግበትን
ፍጹም መታዘዝ ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ እንደታዘዘ ይነግረናል። መዝሙር 40
ላይ ዳዊት ለእግዚአብሔር ሊያሳይ የሚሻውን ፍጹም መታዘዝን በመጥቀስ
“በዚያን ጊዜ አልሁ፤ እነሆ መጣሁ ስለ እኔ በመጽሐፍ ራስ ተጽፎአል። አምላኬ
ሆይ ፈቃድህን ለማድረግ ወደድሁ ህግህም በልቤ ውስጥ ነው።” (መዝ. 40፡
7-8) ማለቱን ያስታውሳል።
መዝሙሩ እግዚአብሔር ከእስራኤል ህዝብ ጋር
ስላለው ቃል ኪዳን፤ በመታዘዝ ስላለው ደስታ እና በልብ ውስጥ ስለተፃፈው
ህግ ይገልጽልናል (ዘዳ. 6፡4-6)። ነገር ግን ዳዊት ሊያከናውን ሲሻው የነበረውን
ተግባር ኢየሱስ ፈጸመው።
ለጳውሎስ ይህ መዝሙር የኢየሱስን ሥጋ መልበስ ወሳኝነት ይገልፃል። አየሱስ
ለአዲሱ ኪዳን መታዘዝን በአካል ገለፀ፤ እርሱ ምሳሌያችን ነው። የዳንነው
በእርሱ ሞት ብቻ ሳይሆን በእርሱ ፍፁም መታዘዝ ምክንያት ነው።
የዚህን ሳምንት ትምህርት አጥንተው ለየካቲት 12 ሰንበት ይዘጋጁ።
ዕብ. 7፡11-19ን ያንብቡ። አዲሱ ኪዳን ያስፈለገው ለምን ነበር?
በዕብራውያን መጽሐፍ መሠረት በመልከ ጼዴቅ ሹመት ኢየሱስ ካህን
ሆኖ መሾሙ አዲሱ ኪዳን ተመርቆ መከፈቱን ያመላክተናል። ብሉይ
ኪዳን በሌዋውያን ክህነት በኩል የተሰጠ ነበር (ዕብ. 7፡11)። የሌዊ ክህነት
በእግዚአብሔር እና በእስራኤል መካከል አማላጅ ሆነው እንዲያገለግሉ
ሲያደርጋቸው ህጉም ሌሎች ሰዎችን በሞላ ከክህነት ውጪ ያደርጋቸዋል።
ጸሐፊው ሲደመድም የክህነቱ መለወጥ የክህነት ህጉ እንዲሁም ቃል ኪዳኑ
መለወጡን (ዕብ. 7፡12፣ 18-19) ያመላክታል።
የብሉይ ኪዳን ችግር ፍጹምነትን አለማጎናፀፉ ነበር (ዕብ. 7፡11)። ጳውሎስ
እየነገረን ያለው ስለ ሌዊ ክህነት እና ስለአገልግሎቱ (ስለ መስዋዕትነቱ፣ ስለ
ማዕዱ ወዘተ) ነው። የእንስሳት መስዋዕትነቱ እውተኛና ሙሉ መንፃትም ሆነ
ወደ እግዚአብሔር መድረስን ሊያመጡ አልቻሉም (ዕብ. 10፡1-4፣ ዕብ. 9፡
13-14፣ ዕብ. 10፡19-25)
የአዲሱ ኪዳን አስፈላጊነት እውነታ እግዚአብሔር ብሉይ ኪዳንን ለእስራኤል
መስጠቱ ፍትሃዊ አይደለም የሚያስብል አይደለም የሌዋውያን እና የቤተ
መቅደሱ አገልግሎት የታቀደው እስራኤላውያንን ከጣኦት ለመጠበቅ እና
የወደፊቱን የየሱስ አገልግሎት ለማመልከት ነው። የዕብራውያን መጽሐፍ
አጽንኦት ሰጥቶ የሚነግረን መስዋዕቱ “ሊመጣ ያለው የበጎ ነገር ጥላ ነው”
(ዕብ. 10፡1)
መስዋዕቱ ወደ ኢየሱስ በማመላከት ህዝቦቹ ተስፋቸውን እና እምነታቸውን
“የዓለምን ሀጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” ላይ እንዲያደርጉ ነው
(ዮሐ. 1፡29ን ከኢሳ. 53 ጋር ያነፃፅሩ) ጳውሎስ ስለ ህጉ ሲናገር “ህግ ወደ
ክርስቶስ የሚያመጣ ሞግዚታችን ነው” (ገላ. 3፡24) ካለው ወይንም ደግሞ
“የሚያምኑ ሁሉ ይጸድቁ ዘንድ ክርስቶስ የሕግ ፈጻሚ ነውና” (ሮሜ 10፡4)
ካለው ሀሳብ ጋር ተመሳሳይነት አለው።
በሌላ አባባል፤ አስርቱ ትዕዛዛት በጎና ፍጹማን ቢሆኑም ጽናትን ግን ሊሰጡን
አይችሉም (ሮሜ 3፡20፤ ሮሜ 7፡12-14)። ለጽድቅ የሚያስፈልገውን ፍፁማዊ
መመዘኛ ይሰብካሉ እንጂ ጽድቅን አያመጡልንም። ልክ ፊትን በመስታወት
ማየት የፊት ጉድፍን እንደማያስወግድ ማለት ነው። ፍጹም ፃድቅ ለመሆን
የኢየሱስ ምትክነት ያስፈልገናል።
ህጉ ሊያድነን ያልቻለው ለምንድነው? ደግሞስ ሁሉንም ህጎች
ያለእንከን ብንጠብቅ እንኳን የማያድኑን ለምንድነው?
ዕብ. 8፡10-12ን ከዘዳ. 6፡4-6፤ ዘዳ. 30፡11-14 እና ኤር. 31፡ 31-34 ጋር ያነፃፅሩ። ስለ አዲሱ ኪዳን ባህሪ ምን የሚያስተምሩን ነገር አለ?
በዕብራውያን መጽሐፍ የምናገኘው የአዲስ ኪዳን ተስፋ ወደ ኤርምያስ
መጽሐፍ እንድንመለስ ያደርገናል። በኤርሚያስ መጽሐፍ መሠረት
እግዚአብሔር በአዲስ ኪዳን በኩል የገባው የተስፋ ቃል አስቀድሞ በሙሴ
በኩል ከእስራኤል ጋር የገባውን ቃል ኪዳን ዳግም ያደሰ ነበር (ኤር 31፡3134)። ስለዚህ ኤርምያስ 31 የሚናገረው ስለ አዲስ ኪዳን ሳይሆን ቀድሞ
ከእስራኤል ጋር ስለተገባው ኪዳን “መታደስ” ነው ብሎ መከራከር ይቻላል።
እንደውም አዲስ ለሚለው ቃል የዕብራይስጥ አቻው “ሃዳሻህ” የሚል ሲሆን
“መታደስን” ወይንም “ፍፁም አዲስነትንም” የሚገልፅ ነው።
የብሉይ ኪዳን ችግር ህዝቡ ህጉን መጣሱ (ዕብ. 8፡8-9) ነው። ችግሩ ያለው
ቃል ኪዳኑ ላይ ሳይሆን ህዝቡ ላይ ነበር። እስራኤል በተሰጠው ምሳሌ በኩል
የመሲሁን መምጣት መመልከት ቢችሉ እና በእርሱ ላይ እምነታቸውን ማሳረፍ
ቢችሉ ኖሮ ቃል ኪዳኑ አይፈርስም ነበር። እንደዛም ሆኖ በእስራኤላውያን
ታሪክ የቃል ኪዳኑ ዓላማ የተፈፀመላቸው እና ህጉን በልቦናቸው ያደረጉ
ብዙዎች ነበሩ (መዝ. 37፡31፤ መዝ. 40፡8፤ መዝ. 119፡11፤ ኢሳ. 51፡7)።
አዲሱ ኪዳን የብሉይ ኪዳን መታደስ ስለሆነ በእርግጥም አዲስ ነው። ኤርምያስ
የገለፀው “አዲስ ኪዳን” ሕዝቡ ክህደት ውስጥ በተደጋጋሚ በመውደቃቸው
ምክንያት ከመማረካቸው አስቀድሞ ተጥሶ ዳግም ስለታደሰው የቃል ኪዳኑ
ይዘት ብቻ እያሰበ አልነበረም። ህዝቡ ወደክህደት የገቡት ከእግዚአብሔር ጋር
በገቡት ኪዳን ውስጥ ከነርሱ የሚጠበቀውን ስላላደረጉ ነበር (ኤር. 13፡22)።
ስለዚህ እግዚአብሔር አዲስን ነገር ሊያደርግ ቃል ገባ (ኤር. 31፡22)። ኪዳኑ
“ከአባቶቻቸው ጋር” እግዚአብሔር እንደገባው ያለ ኪዳን አይሆንም (ኤር.
31፡32)። በህዝቡ ታማኝነት ማጉደል የተነሳ በሙሴ በኩል እግዚአብሔር
የሰጠው ቃል ኪዳን ተፈፃሚ ሊሆን አልቻለም። አሁን ኢየሱስ ለሚሻል ኪዳን
ዋስ ስለሆነ (ዕብ. 7፡22) እግዚአብሔር የእርሱን ቃል ኪዳን ይፈጽመዋል።
እግዚአብሔር ህጉን አልለወጠም ወይንም ያስቀመጠውን መመዘኛ ዝቅ
አላደረገም። በምትኩ ለቃል ኪዳኑ ዋስ እንዲሆን ልጁን ላከ (ዕብ. 7፡22፤ ዕብ.
6፡18-20)። ቃል ኪዳኑ ላይ በረከት ብቻ እንጂ እርግማን የሌለበት ኢየሱስ
ፍጹም በሆነ ሁኔታ ስለፈፀመው ነው።
2ጢሞ. 2፡13ን ያንብቡ። እኛ ከሌሎችና ከእቅዶቻችንን ጋር
ያለንን ግንኙነት ግምት ውስጥ ስናስገባ እግዚአብሔር ለህዝቡና
ለእቅዱ ካለው ታማኝነት ምን የምንማረው ነገር አለ?
ዕብ. 8፡1-6ን ያንብቡ። ኢየሱስ የኪዳኑ የሚሻል መካከለኛ ሆኖ የቀረበው እንዴት ነው?
መካከለኛ (meditator) የሚለው ቃል የመጣው ከግሪኩ ቃል “መሲቲስ”
ሲሆን መካከል “meditator” (ሜዲዬተር) ከሚለው ቃል የተወሰደ ነው።
ቃሉ አንድ ሰው የሚከተሉትን አንድ ወይም ከዚያ በላይ ተግባራት ሲፈጽም
የሚሰጠው ነው። (1) በሁለት ወይንም ከዛ በላይ በሆኑ ቡድኖች መካከል ያለ
ዳኛ (2) አደራዳሪ ወይንም የንግድ ደላላ ሲሆን (3) ህግን በተመለከተ እማኝ
ሆኖ ሲቀርብ (4) ለአንድ ስምምነት መፈፀም ዋስ ሆኖ የቀረበ ሰው ሲሆን
ነው።
የእንግሊዝኛው “mediator” (ሜዲዬተር) የሚለው ቃል “mesitēs”
(መሲቲስ) ከሚለው ከዕብራይስጡ ቃል ጋር ሲነፃፀር ጠበብ ያለ ትርጓሜ ያዘለ
ነው። ምክንያቱም በግሪኩ በተጠቀሱት የመጀመሪያዎቹ ሁለት ወይም ሶስት
አይነት መገለጫዎች ብቻ ላይ ትኩረቱን ስለሚያደርግ ነው።
የዕብራይስጡ
ቃል ግን አራተኛው ተግባር ላይ አጽንኦት ይሰጣል። ኢየሱስን የምናየው
በአብ እና በሰው ልጆች መካከል የተፈጠረውን ጥል ለማብረድ ሁለቱንም
አካላት ለማስታረቅ እንደመጣ አስታራቂ ወይንም ህጋዊ ስምምነት ላይ
እማኝ ሆኖ ሊያረጋግጥ እንደመጣ ሰው አይደለም። ይልቁንም የዕብራውያን
መፅሐፍ እንደሚያብራራልን ኢየሱስ የአዲስ ኪዳን ዋስትና ነው (ዕብ. 7፡22)
በዕብራይስጡ “መካከለኛ” ለሚለው ቃል አቻ ቃሉ “ዋስ” የሚለው ነው።
እርሱ የቃል ኪዳኑ የተስፋ ቃል እንደሚፈጸም ዋስትና ይሰጣል።
ከእስራኤል ጋር የተገባውና የተጣሰው የመጀመሪያው ኪዳን የሚጠይቀውን
ጥያቄ አሟልቶ ስለመለሰ (ዕብ. 9፡15-22) የክርስቶስ ሞት አዲሱ ኪዳን
እንዲቋቋም አደረገ። በዚህ አግባብ ኢየሱስ የተጣሰውን ህግ ቅጣት ራሱ
የሚወስድ ዋስ ሆነ። በሌላ አገላለፅ የክርስቶስ በሰማይ መክበር እግዚአብሔር
ለሰብአዊ ዘር የገባው ቃል ኪዳን እንደሚፈፀም ያረጋገጣል (ዕብ. 6፡19-20)።
የእግዚአብሔር ተስፋዎች እውነት መሆናቸውን ስላሳየ ኢየሱስ የቃል ኪዳኑ
ዋስ ነው። ኢየሱስን ከሞት በማስነሳት እና በቀኙ በማስቀመጡ አብ እኛንም
ከሞት እንደሚያስነሳንና ወደ ራሱ እንደሚያመጣን አሳየን።
ኢየሱስ ከሙሴ ይልቅ ታላቁ አማላጅ ነው፤ ምክንያቱም በሰማያዊው ቤተ
መቅደስ ስለሚያገለግል እና ለኛ ፍጹም መስዋዕት በመሆን ራሱን ስለሰጠ ነው
(ዕብ. 8፡1-5፤ ዕብ. 10፡5-10)። የሙሴ ፊት የእግዚአብሔርን ክብር አንፀባረቀ
(ዘፀ 34፡29-35)፤ ኢየሱስ ግን ራሱ የእግዚአብሔር ክብር ነው (ዕብ. 1፡3፤
ዮሐ. 1፡14)። ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ፊት ለፊት ተነጋገረ (ዘፀ 33፡11)፤
ኢየሱስ ግን የእግዚአብሔር ቃል ነው (ዕብ. 4፡12-13፤ ዮሐ. 1፡1-3፣ 14)
አዎ፤ ኢየሱስ ቃል ኪዳኑ የሚጠይቀውን መታዘዝ ፈፅሟል። በዚህ
ብርሃን አንፃር መታዘዝ ለህይወታችን ያለው ሚና ምንድነው?
አሁንም አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድነው?
ከብሉይ ኪዳን የበለጠ ትልቅ ሽልማት ስላለው (ሰማያዊ ቤት፤ የዘላለም
ህይወት ወዘተ) አዲሱ ኪዳን “የተሻለ የተስፋ ቃል” አለው ለማለት እንፈተን
ይሆናል። እውነታው ግን እግዚአብሔር ለብሉይ ኪዳን አማኞችም ለእኛም
የሚሰጠው ተመሳሳይ ሽልማትን ነው (ዕብ. 11፡10፤ 13-16 ያንብቡ)። ዕብ. 8፡
6 ላይ “ስለሚሻል የተስፋ ቃል” የሚናገረው ስለተለያዩ የተስፋ ቃል አይነቶች
ነው።
በእግዚአብሔር እና በእስራኤል መካከል የነበረው ቃል ኪዳን በእርሱና
በእስራኤል መካከል በግልፅ የተከናወነ የቃል ኪዳን ልውውጥ ነበር።
እግዚአብሔር ቀዳሚውን እርምጃ ተራምዶ እስራኤልን ከግብጻውያን ነፃ
አወጣና ወደ ተስፋይቱ ምድር እንደሚያደርሳቸው ቃል ገባላቸው።
ዘጸ. 24፡1-8 እና ዕብ. 10፡5-10ን ያነፃፅሩ። በነዚህ ሁለቱ ቃል
ኪዳኖች መካከል ያለው መመሳሰልና ልዩነት ምንድነው?
በእግዚአብሔር እና በእስራኤል መካከል ያለው ቃል ኪዳን የተረጋገረጠው
በደም ነው። ይህ ደም የተረጨው እግዚአብሔርን በሚወክለው በመሰዊያው
ላይ እንዲሁም ህዝቡን በሚወክለው በአስራ ሁለቱ ምሰሶዎች ላይ ነበር።
የእስራኤል ህዝቦች እግዚአብሔር የተናገረውን በሙሉ ለመታዘዝ ቃል ገቡ።
ይህ መለኮታዊ ቃል ኪዳን ሲሆን እኛም ወደዚህ ኪዳን ስንገባ ይፈልግብናል።
“የዘላለም ህይወት ጉዳይ ቀደምት ወላጆቻችን በሀጢአት ሳይወድቁ በገነት
በነበሩበት ጊዜ እንደነበረው ሲሆን ይህም ለእግዚአብሔር ህግ ፍፁም
መታዘዝና ፍጹም ጽድቅ ነው። የዘላለም ህይወት ከዚህ ከጎደሉ ቅድመሁኔታዎች ተሰጥቶ ቢሆን ኖሮ ዩኒቨርስ ሁሉ አደጋ ላይ ይጣል ነበር።
የኃጢአት
መንገድ ተከፍቶ በውጤቱም ሀዘንና ምስቅልቅል ያለ ህይወት ዝንተአለም
ሰፍኖ ይኖር ነበር።” ኤለን ጂ. ኋይት፣ ወደ ክርስቶስ የሚመራ መንገድ፣ ገፅ
57 (በአማርኛው)
እግዚአብሔር የአዲሱን ኪዳን መጠይቅ ሙሉ በሙሉ በሚያሟላ መንገድ
መለሰልን፤ ምክንያቱም አንድያ ልጁ መጥቶ የቃል ኪዳኑ ተስፋ በርሱ በኩል
እንዲፈጸምና ፍጹም ህይወት በመኖሩ በእምነት ይህን ሁሉ እንድንቀበል
አድርጎናል። የኢየሱስ መታዘዝ ለቃል ኪዳኑ ተስፋ ዋስትና ይሰጠናል (ዕብ
7፡22)። እግዚአብሔር የቃል ኪዳኑን ባርኮት ለእርሱ ከሰጠው በኋላ እርሱ
ደግሞ ለእኛ እንዲሰጠን ይጠበቅበታል።
በእርግጥም “በክርስቶስ” የሆኑ ሁሉ
ለእርሱ በተገባው ቃል ኪዳን ሁሉ ሀሴትን ያደርጋሉ። በሁለተኛ ደረጃ ህጉን
መጠበቅ እንድንችል እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን ሰጥቶናል።
ክርስቶስ ህጉ የሚጠይቀውን ጥያቄ በሙሉ ስለመለሰ ተስፋዎቹ
ለእኛም ስለመፈፀማቸው ጥርጥር የለንም። ይህ 2 ቆሮ. 1፡20-22
ያለውን ክፍል እንድናስተውል እንዴት ያግዘናል? በዚህ ስፍራ
ላይ የምናገኘው አስደናቂ ተስፋ ምንድነው?
ኤር. 31፡33 እና ህዝ. 36፡26-27 ላይ የሚገኙትን የአዲስ ኪዳን ተስፋዎች ያነፃፅሩ። በምን መንገድ ይዛመዳሉ?
የመጀመሪያው የቃል ኪዳን ጽሁፍ በድንጋይ ፅላት ላይ በእግዚአብሔር ተፅፎ
እግዚአብሔር ከህዝቡ ጋር ለገባው ቃል ኪዳን ምስክር እንዲሆኑ በታቦቱ
ውስጥ ይቀመጥ ነበር (ዘጸ. 31፡18፤ ዘዳ. 10፡1-4)። በጽላቱ ላይ የተጻፈው
ፅሁፍ ሊሰበር ወይም ሊወረወር ኤርሚያስ እንደተመለከተውም ሊቀደድ
ወይንም ሊቃጠል የሚችል ነበር (ኤር. 36፡23)።
አሁን ግን እግዚአብሔር ህጉን በህዝቡ ልብ ውስጥ ይፅፈዋል። ልብ
የሚወክለው ማስታወስ እና መረዳት የሚችለውን አይምሮአችንን ነው (ኤር.
3፡15፤ ዘዳ. 29፡4) በተለይም በንቃት የሚሰጡ ውሳኔዎችንም ይገልጽልናል
(ኤር. 3፡10፤ 29፡13)።
ይህ የተስፋ ቃል እያንዳንዱ በቀላሉ ህጉን አውቆ ወደ ህጉ መድረስ እንደሚችል
ማረጋገጫን አይሰጠንም። ከምንም በላይ አስፈላጊው ነገር በህዝቦች ልብ
ውስጥ ትክክለኛውን ለውጥ ማምጣት መቻል ነው። እስራኤል ላይ ያለው
ችግር ሀጢያታቸው “በብረት ብዕር እና በተሾለ እብነ በረድ… በልባቸው ጽላት
ተቀርጾ” ተቀምጧል (ኤር. 17፡1)። በልባቸው እልከኝነት ስለሚመሩ (ኤር. 13፡
10 ኤር. 23፡17) በጎ የሆነውን ነገር ማድረግ አይችሉም (ኤር. 13፡23)።
ኤርሚያስ እያወጀ ያለው ስለ ህጉ መለወጥ አይደለም ምክንያቱም የእስራኤል
ችግር ህጉ ሳይሆን ልባቸው ነበር። እግዚአብሔር ለእስራኤል ስላደረገው ነገር
በበጎነት የተሞላ ምላሽ በመስጠት ታማኝነታቸውን እንዲገልፁ ይፈልጋል
ስለዚህ በታሪካዊ ዳራ ፍቅሩንና እንክብካቤውን በመግለፅ አስርቱን ትዕዛዛት
ሰጣቸው (ዘፀ. 20፡1-2)።
እግዚአብሔር ህጉን እንዲታዘዙ የፈለገው ለእነርሱ
ምርጥ የሆነውን ነገር ሊሰጣቸው ስለሚሻ ነው፤ ከግብፃውያን ዘንድ በታላቅ
ሀይል ነፃ ማውጣቱ ይህንን እውነታ ይገልፃል። መታዘዛቸው ምስጋናቸውን
ከእርሱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚገልጹበት መንገድ ነው።
ዛሬም ይህ ነገር ለኛም እውነት ነው። ኢየሱስ ለኛ በመሞት የገለፀው ፍቅር እና
እንክብካቤ የአዲስ ኪዳን መክፈቻ ነው (ሉቃስ 22፡20)። እውነተኛ መታዘዝ
የፍቅር መግለጫ ሆኖ ከልብ ይመነጫል (ማቴ. 22፡34-40)። መንፈስ ቅዱስ
በአማኙ ህይወት ውስጥ ስለመኖሩ ማሳያው ይህ ፍቅር ነው። እግዚአብሔር
በመንፈሱ በኩል ፍቅሩን አፈሰሰልን (ሮሜ 5፡5) ይህም በፍቅር ይገለፃል (ገላ.
5፡22)።
ጥንታዊ እስራኤላውያን ስለ ክርስቶስ ሞት ሳይረዱ እግዚአብሔርን
ሊወዱት ከተገባቸው እኛ ታዲያ ከእነርሱ በተሻለ ሁኔታ
እግዚአብሔርን እንዴት አብልጠን አንወደው? መታዘዝ የፍቅርን
እውነታ የሚገልፀው እንዴት ነው?
ልባችን በእግዚአብሔር አምሳል ከታደሰ፤ የመለኮት ፍቅር
በነፍሳችን ውስጥ ከተተከለ ህጉ በእኛ ህይወት የማይፈፀመው እንዴት ነው?
የፍቅር መርህ በልባችን ውስጥ ሲተከል ሰዎችም በራሱ አምሳል በፈጠራቸው
አምላክ ሲታደስ የአዲስ ኪዳኑ የተስፋ ቃል ተፈፃሚ ይሆናል። “ህጌን
በልባቸው አኖራለሁ በልቦናቸውም ላይ እፅፈዋለሁ” ዕብ. 10፡16። ታዲያ ህጉ
በልባቸው ከተፃፈ እንዴት ህይወታቸውን ቅርፅ ማስያዝ አልቻለም መታዘዝ፡
- አገልግሎት እና የፍቅር ታማኝት የእውነተኛ ደቀ መዝሙር ስለመሆናችን
ምልክት ነው። ስለዚህ የእግዚአብሔር ቃል ሲናገር “ትዕዛዙን ልትጠብቁ
የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና” “እርሱን አውቀዋለሁ እያለ ትዕዛዙን
የማይጠብቅ ሀሰተኛ ነው እውነትም በእርሱ ውስጥ የለም” (1 ዮሐ. 5፡3)።
በእምነት እና በእምነት ብቻ የክርስቶስ ፀጋ ተካፋዮች እንሆናለን፤ ያም መታዘዝ
እንድንችል ያደርገናል…
“ወደ ክርስቶስ የበለጠ በቀረባችሁ ቁጥር የበለጠ ኃጢአተኛ መሆናችሁ
ይታያችኋል፤ እይታችሁም የበለጠ ግልጽ እየሆነ ክፋታችሁ በሰሌዳ
እንደሚታይ እየታየ እና ፍጹም ለሆነው ማንነቱ ምን ያክል ተፃራሪ መሆናችሁ
ይገባችኋል። ይህ ደግሞ የሰይጣን ማሳሳቻ ሃይሉን እንዳጣና ህይወት ሰጪ
የሆነው የእግዚአብሔር ኃይል እያነሳሳችሁ እንደሆነ ማረጋገጫ ነው።
“በልቡ ለየሱስ ጥልቅ ፍቅር ያላደረበት ሰው የራሱን ኃጢአተኝነት ሊረዳ
አይችልም። በክርስቶስ ፍቅር የተለወጠ ነፍስ መለኮታዊ ባህሪን ማድነቅ
ይችላል። ነገር ግን የራሳችን የሞራል ዝቅጠት እስካልታየን ድረስ የክርስቶስን
ውበት እና ታላቅነት ማየት እንደሚሳነን አያጠራጥርም” Ellen g. White,
Steps to Christ, pp. 60, 64, 65
1.ከላይ ኤለን ጂ ኋይት ስለተናገረችው ሀሳብ እስቲ ያስቡ። ወደ
ክርስቶስ የበለጠ በቀረብን መጠን የበለጠ ሀጢያተኛ መሆናችንን
ስናይ ሀጢያተኝነትን ማወቃችን በእምነታችን ላይ ተስፋ
እንድንቆርጥ እንዳያደርገን የምንሆነው እንዴት ነው?
2.ህጉ በልባችን ስለመጻፉ የበለጠ አጽንኦት ሰጥታችሁ አስቡ። ይህ
ለክርስቲያኖች መንፈሳዊ ህይወት የሚሰጠው ትርጉም ምንድነው
ይህንን እውነት ማስተዋልና መለማመድ ህጋውያን “legalism”
ሆነን “ለመታዘዝ” ከማሰብ እና “የሞተ ስራ” ተብሎ ከተገለፀው
ውጪ ሆነን እንድንቆይ የሚያግዘን እንዴት ነው(ዕብ. 9፡14)?